Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለሕይወት ትልቅ ዋጋ እንድሰጠው አድርጎኛል››

ወጣት መላኩ ኃይሉ፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አስተባባሪ

ወጣት መላኩ ኃይሉ ተወልዶ ያደገው፣ የመጀመሪያና የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው አዲስ አበባ ውስጥ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት ከዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በሶሺዮሎጂ ተመርቋል፡፡ በተለያዩ ዘርፎች በበጎ ፈቃድ ሥራና የበጎ ፈቃደኞች መሪና አስተባባሪ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡ እያበረከተ ካለው አገልግሎትና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሮታል፡፡

ሪፖርተር፡- በየትኞቹ ዘርፎች ነው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየሰጠህ ያለኸው?

ወጣት መላኩ፡- በወጣቶች ሴቶች ክርስቲያናዊ ማኅበር (ወሴክማ) የሕፃናት ፕሮግራም፣ በማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ እና በሚጥል በሽታዎች (ኤፕልፕሲ) ዙሪያ ነው፡፡ በእነዚህም ዘርፎች ውስጥ በግሌ ከማገለግለው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባሻገር ከ300 በላይ ለሚሆኑ በጎ ፈቃደኞች መሪና አስተባባሪ ሆኜ የበኩሌን አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ እገኛለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በሕፃናት ፕሮግራም ዙሪያ የምታከናውኑት በጎ ሥራ ምንድነው?

ወጣት መላኩ፡- በዚህ ፕሮግራም ብቻ ወደ 200 የሚጠጉ ወጣት በጎ ፈቃደኞች እንዳሉ በቅድሚያ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ እነዚህም በጎ ፈቃደኞች በሕፃናት ፕሮግራም ዙሪያ የሚሠሩትን ሥራ ማስተባበሬ እንደተጠበቀ ሆኖ የሚከናወኑትም ተግባራት ትምህርት ቤቶች ለዕረፍት ሲዘጉ ሕፃናት አልባሌ ቦታ እንዳይውሉ ሒሳብ፣ አማርኛ፣ እንግሊዝኛ ሳይንስ በነፃ እናስተምራቸዋለን፡፡ ከዚህም ሌላ ጥሩ ሥነ ምግባር ተላብሰው የሚያድጉበትን ሁኔታ እናመቻቻለን፡፡ በዚህ መልኩ ከምናመቻቸው ተግባራት መካከል ሕፃናት ቤተሰቦቻቸውንና የአካባቢያቸውን ነዋሪዎች እንዴት እንደሚያከብሩ፣ መታዘዝ እንደሚችሉና የራሳቸውንም ሰብዕና በምን መልኩ እንደሚገነቡ በጭውውትና በድራማ መልክ እናስተምራቸዋለን፡፡ በጎ ፈቃደኞችንም የምንሰበስበው በየትምህርት ቤቶች ማስታወቂያ በመለጠፍ ነው፡፡ ማስታወቂያውንም የተመለከቱና ነፃ አገልግሎት ለማበርከት ፈቃደኛ የሆኑ ወጣቶች እንዲመዘገቡ ይደረጋል፡፡ ከተመዘገቡትም መካከል በማጣሪያ ያለፉት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊዎች ይሆናሉ፡፡ የማጣሪያውም ነጥቦች ትምባሆ ከማጨስ፣ ጫት ከመቃምና ከሌሎች አደገኛ ሱስ አስያዥ የሆኑ ዕፆችን ከመጠቀም ነፃ የሆኑ የሚል ነው፡፡

ሪፖርተር፡-  ከመቼ ጀምሮ ነው በጎ ፈቃድ ሥራ ላይ የተሰማራኸው? በተለይ በካንሰር ሶሳይቲ ምን ዓይነት አገልግሎት ነው የምትሰጠው?

ወጣት መላኩ፡- በዚህ ዓይነት አገልግሎት መሰማራት የጀመርኩት ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ በማቲዎስ ወንዱ ካንሰር ሶሳይቲ ውስጥ በጎ ፈቃደኛና የሶሳይቲው ደጋፊ አባል ነኝ፡፡ ይኼንንም ያደረግኩት ለራሴ ካንሰርን ለመከላከልና ከራሴ ውጭ ደግሞ ለኅብረተሰቡ መቆም እንዳለብኝ በማመኔ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ለካንሰር አጋላጭ በሆኑ እንደ ትምባሆ፣ አልኮልና መጠጥ የመሳሰሉት ጎጂ ልማዶች ምን ያህል አስከፊ እንደሆኑ ለመረዳት ችያለሁ፡፡ በዚህም የተነሳ እኔና ሌሎችም በጎ ፈቃደኞች በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ውስጥ ለሚገኙ የካንሰር ታካሚዎች ሰብአዊ አገልግሎት እንሰጣለን፡፡ የዓለም የካንሰር ቀንን አስመልክቶ በየትምህርት ቤቱ እየተዘዋወርን ለተማሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እናስተምራለን፡፡ በዚህ ዓይነት አገልግሎት ላይ የተሰማሩ ወደ 120 የሚሆኑ በጎ ፈቃደኞች አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- የሚጥል በሽታ ወይም ኤፕሊፕስ ‹‹እርኩስ መንፈስ ነው››፡፡ እየተባለ ይነገራል፡፡ ኅብረተሰቡ ከዚህ አጉል እምነት የዘመናዊ ሕክምና እምነትና አስተሳሰብ እንዲኖረው ለማድረግ ምን እያደረጋችሁ ነው?

ወጣት መላኩ፡- የሚጥል በሽታ እርኩስ መንፈስ ሳይሆን በሕክምና የሚድን መሆኑን በማኅበራዊ ሚዲያና በሌሎችም የመገናኛ ዘዴዎች ኅብረተሰቡን እያስተማርንና ግንዛቤ የማስጨበጭ ሥራ እያከናወንን ነው፡፡ ይኼንንም ሥራ በተከታታይ የሚሠራ ዩዝ ፎር ኢፕሊፕስ የሚባል ቡድን አቋቁመናል፡፡ በዚህ መልኩ መንቀሳቀስ ከጀመርን ሦስት ዓመት ሆኖናል፡፡ በቅርቡም የዓለም የሚጥል ሕመም ቀንን ለማክበር አስፈላጊውን ዝግጅት በማጠናቀቅ ላይ እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ በመሰማራትህ በሕይወትህ ላይ ያገኘኸው ለውጥ ምንድነው? የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ኅብረተሰቡ ተረድቶታል ማለት ይቻላል?

ወጣት መላኩ፡- በጎ ፈቃደኛ በመሆኔ በሕይወቴ ወስጥ ሦስት ፍልስፍናዎች እንዲኖሩኝ አድርጓል፡፡ እነርሱም በዚህ ምድር ላይ ለምን እንደመጣሁ፣ ለምን እንደምኖርና ወዴት እንደምሄድ የጠቆሙኝ ፍልስፍናዎች ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ለሕይወት ያለኝም ግንዛቤ በጣም የጨመረ መሆኑን ለመረዳት ችያለሁ፡፡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለሕይወት ትልቅ ዋጋ እንድሰጠው አድርጎኛል፡፡ ኅብረተሰቡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ያውቀዋል ወይም ይረዳዋል ብዬ ለመናገር ትንሽ ይከብደኛለ፡፡ በኅብረተሰባችን ዘንድ የበጎ ፈቃድ ሥራ ከገንዘብ እርጥባን ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ከዚህ ይልቅ ሰዎች ዕውቀታቸውን፣ ክህሎታቸውንና ኃይላቸውን ሁሉ አስተባብረው ዘላቂነት ያለው አገልግሎት ለኅብረተሰቡ ቢሰጡ ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ በዚህ መልኩ አለመገንዘብ ግን ትልቁ ድክመት ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከየትምህርት ቤቱ ለተወጣጡ በጎ ፈቃደኞች የትራፊክ ማስተናበር ሥራ ላይ ያተኮረ ሥልጠና ሰጥቶ በሥራ ላይ አሰማርቷል፡፡ ይኼ ዓይነቱ አካሄድ ምን የሚታረም ወይም መሻሻል ያለበት ነገር አለው ትላለህ?

ወጣት መላኩ፡- በዚህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ ላይ ከሚታዩት ችግሮች መካከል ወጣቶች የትራፊክ ፍሰቱን በሚያስተባብሩበት ጊዜ ወይም ቁም የሚል ምልክት በእጃቸው ሲያሳዩ ጥሰው የሚሄዱ አሽከርካሪዎች አሉ፡፡ ይኼም የሆነበት ምክንያት አሽከርካሪዎቹ የወጣቶችን ሥራ በንቀት ዓይን በመመልከታቸው ነው፡፡ ስለዚህ ይኼ መጥፎ አዝማሚያ ሊስተካከል ወይም ሊታረም ይገባዋል፡፡ ማኅበረሰቡም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪ የሆኑ ወጣቶች የሚያከናውኑትን ሥራ ካላከበረላቸው፣ ወይም በንቀት ዓይን ከተመለከታቸው፣ ተስፋ የመቁረጥና አገልግሎት የመስጠቱንም ሥራ እርግፍ አድርገው እንዲተዉ ያደርጋቸዋል፡፡ ከዚህም ሌላ እያንዳንዱ ወጣት ያበረከተው ነፃ አገልግሎት በሰዓት፣ በቀን፣ በሳምንትና በወር እየተለየ አለመመዝገቡና ባበረከቱትም ነፃ አገልግሎት ሳቢያ መንግሥት ያወጣ የነበረውን ገንዘብ ምን ያህል እንዳዳኑ አለመታወቁ ወይም አለመመዝገቡ ሌላው ሊታሰብበት የሚገባ ችግር ነው፡፡ በበለጸጉ አገሮች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ትልቅ ቦታ ተሰጥቶታል፡፡ በዚህም የተነሳ ይኼ ዓይነቱን እንቅስቃሴ የሚያስተባብሩት አካላትም ተቋቁመውለታል፡፡ ሁሉም አስተባባሪ አካላት በኔትወርክ ተሳስረዋል፡፡ እያንዳንዱ አካል በየአቅራቢያው ያሉት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪዎች በየዕለቱ ስንት ሰዓት እንደሠሩ፣ በዕውቀትና በጉልበት ምን ዓይነት አገልግሎት እንዳበረከቱ፣ ይኼም አገልግሎት በገንዘብ ቢተመን ምን ያህል እንደሚያወጣ ያስላሉ፡፡ በዓመቱም መጨረሻ በሥራ ያሳለፉት ሰዓት፣ በዚህ ዓይነት አገልግሎት ያበረከቱትን አስተዋፅኦና ከውጪ ያዳኑትን የገንዘብ መጠን የሚገልጽ ሪፖርት ያቀርባሉ፡፡ ይህ ዓይነቱም አካሄድ በአገራችን ቢዘወተርና ለአገልግሎቱም ባለቤት ቢበጅለት ከፍተኛ የሆነ ጠቀሜታ እንደሚኖረው በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡  

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

አደራውን ለመጠበቅ ዕድል ያላገኘው ቅርስ ባለአደራ

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር ከተመሠረተ ሦስት አሥርት አስቆጥሯል፡፡ ማኅበሩ በእንጦጦ ተራራማ ቦታዎች በአደራ በመንግሥት በተረከበው 1,300 ሔክታር መሬት ላይ የተለያዩ አገር በቀል ዛፎችን በመትከል...

ብዝኃ ትምህርቱን ‹ስቴም› ለማስረፅ

ስሜነው ቀስቅስ (ዶ/ር) የስቴም (Stem) ፓውር ግብረ ሰናይ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተርና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ አማካሪ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስና የፒኤችዲ...

‹‹እውነታውን ያማከለ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤን ማጠናከር ያስፈልጋል›› ደመቀ ደስታ (ዶ/ር)፣ በአይፓስ የኢትዮጵያ ተወካይ

በሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ላይ በመሥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሰው አይፓስ፣ የኢትዮጵያን ሕግ መሠረት አድርጎ በሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች...