Sunday, May 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርአንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኀበረሰብን የመፍጠር ፈተናዎችና ቀጣይ አቅጣጫዎች

አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኀበረሰብን የመፍጠር ፈተናዎችና ቀጣይ አቅጣጫዎች

ቀን:

በዳግም መርሻ

‹‹ጎጃም ያረሰውን፣ ለጎንደር ካልሸጠ
ጎንደር ያረሰውን ለጎጃም ካልሸጠ
የሸዋ አባት ልጁን ለትግሬ ካልሰጠ
የሐረር ነጋዴ ወለጋ ካልሸጠ
ፍቅር ወዴት ወዴት፣ ወዴት ዘመም ዘመም
አገርም አለችኝ አገር የኔ ሕመም
ሥሩ እንዳይበጠስ መቋጠሪያው ደሙ
አረንጓ
ቢጫ ቀይ ነው ቀለሙ ...››

ይህን ጥልቅ የሆነ ሐሳብ የያዘ የድምፃዊቷን እጅጋየሁ ሽባባው ተወዳጅ የዘፈን ስንኝ በመግቢያው ላይ ያስቀመጥኩት ያለምክንያት አይደለም። ስንኞቹ በጥቂት የግጥም መስመሮች አሁን በአገራችን እየታየ ያለውን የፖለቲካ ድባብና በአንፃሩም ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የቆየውን የሕዝቡን ትስስር እስከ ወዲያኛው ዘልቆ እንዲቆይ አስፈላጊነቱን የሚጠቁም በጎ ሐሳብ ያዘለ ስለሆነ ነው። ግጥሙ በተከሸነ ሁኔታ የቆየውን የሕዝቡን ታሪክና ፍቅር አመላካች ቢሆንም ሥጋትንም የቋጠረ ነው።

- Advertisement -

ኢትዮጵያ በርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም ሃይማኖቶችን ያቀፈች አገር ከመሆኗ በትይዩ፣ እነዚህ የተለያየ ስብጥር ያላቸው የአገሪቱ ሕዝቦች የውጭ ወራሪ ኃይሎች የአገሪቷን ድንበርና ሉዓላዊነት በተለያየ ጊዜያት ለመድፈር በሞከሩበት ወቅት የጥቃት ሙከራዎቹን በጋራ በመመከት፣ አንድነቷንና ነፃነቷን እስከዚህ ጊዜ ድረስ ጠብቃ በክብር እንድትኖር ያስቻሉ ጀግኖች ሕዝቦችን ያፈራች ታላቅ አገር ነች። የኢትዮጵያን ሕዝቦች የአንድነት መንፈስና የአልበገር ባይነት ስሜት ለማሳየት እንደ ጥሩ ምሳሌ የሚጠቀሰው የዓደዋ ድል ነው። ስለዓደዋ ድል አንፀባራቂነትና ዘመን ተሻጋሪነት በርካታ የታሪክ ተመራማሪዎች የየራሳቸውን ምስክርነት ሰጥተዋል። ሁሉም የታሪክ ጸሐፊዎች የዓደዋ ድል የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካን፣ ከዚያም አልፎ የመላ ጥቁር ሕዝቦችን ታሪክ ቀያሪ ክስተት እንደሆነ ይስማማሉ። ኢትዮጵያዊያን ልዩነታቸውን አቻችለው አገራቸውን ሊወር የመጣውን ዘመናዊ መሣሪያ የታጠቀውን የአውሮፓ ኃይል በኋላቀር መሣሪያ መመከት ችለዋል። ለዓደዋ ድል መገኘት ዋነኛና ትልቁ ምክንያት ኢትዮጵያዊያን ልዩነታቸውን አቻችለውና አንድነታቸውን አጠናክረው ወራሪውን የቅኝ ገዥ ኃይል መመከት በመቻላቸው ነው።

የዓደዋ ድልን ልዩ ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል በዋናነት የሚነሳው ጉዳይ  ኢትዮጵያዊያን በመካከላቸው ያሉትን በርካታ ልዩነቶች (የቋንቋ፣ የባህል፣ የእምነት  ወዘተ.) ወደ ጎን በማድረግ የጋራ ጠላታቸው የሆነውን የውጭ ወራሪ ለመመከት መዝመታቸውና ድል ማድረጋቸው ነው። ሁሉም የአፍሪካ አገሮች በሚባል ደረጃ እዚህ ግባ በማይባል ትግል አገራቸውን ለአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች አሳልፈው ሲሰጡ፣ ኢትዮጵያዊያን ግን በተጋድሎ የአገራቸውን ዳር ድንበር ማስከበር ችለዋል። እንደ ዶናልድ ሌቪን ያሉ ታዋቂ የታሪክ ተመራማሪዎች የዓደዋ ድል ለኢትዮጵያ ሕዝቦች የኋላ ታሪካቸው የትብብር ማሳያ ነው ሲሉ ጽፈዋል። ይህ አባባል ትልቅ መልዕክት የያዘ ነው። የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ስንቅና ትጥቃቸውን ተሸክመው በእግራቸው ሺሕ ኪሎ ሜትሮችን ተጉዘው የአውሮፓ ዘመናዊ መሣርያን የታጠቀን ጦር ገጥመው ድል ማድረግ መቻላቸው፣ ምን ያህል ጥልቅ የአገር ፍቅር እንዳላቸውና ስለአገር ክብርና ሉዓላዊነት ዋጋም ምን ያህል ጥልቅ ግንዛቤ እንደነበራቸው ነው።

የዓደዋን ድል ከአገር አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚሰጠው ልዩ ግምት የተነሳ በቅድሚያ ተነሳ እንጂ፣ ኢትዮዽያውያን በመካከላቸው ያሉ የቋንቋ፣ የባህል፣ የእምነትና የመሳሰሉትን ልዩነቶች ወደ ጎን ትተው በአገር ላይ የተጋረጡ አደጋዎችንም በተለያዩ ጊዜያት በአንድነት መንፈስ ተጋፍጠው ድል አድርገዋል። የሩቆቹን ትተን የቅርብ ጊዜዎቹን ክስተቶች እንኳን ብናነሳ፣ የአምስቱን ዓመት የቅኝ አገዛዝ ሙከራና የኢጣሊያን ሽንፈት፣ የኢትዮ ሶማሊያ ጦርነትና የኢትዮጵያ ሕዝቦች አሸናፊነት፣ የኤርትራ ወረራና ድል ከብዙ በጥቂቱ መጥቀስ ይቻላል። እናም ሕዝቡ ለዘመናት አገሪቱን ከወጭ ወራሪ ኃይሎችና ጠላቶች በጋራ ሲጠብቅ የኖረው በተደረገበት ጫና ወይም ተፅዕኖ ሳይሆን፣ ከልዩነት ይልቅ ለአንድነት ግምት በመስጠቱና የእኔ ናት ብሎ የሚያስባት ኢትዮጵያ የምትባል አገር ሉዓላዊነቷና ክብሯ ተጠብቆ መቆየቱ ምን ያህል ዋጋ እንዳለው በመረዳቱ ነው። ይህ አንድነትና በጋራ ዓላማ የመቆም አኩሪ እሴት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሊዘልቅ የቻለበት መሠረታዊ ሚስጥር፣ ለዘመናት የዘለቀና በጠንካራ መከባበር ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ላይ በመመሥረቱ ነው።

ይህ እንዳለ ሆኖ ግን ባለፉት ጊዜያት አገሪቱን ሲያስተዳድሩ የነበሩ የአገሪቱ መሪዎች የተሰባጠረ ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክ፣ እምነትና መሰል መገለጫዎች ያሉትን ሕዝብ ይመሩት የነበረው ለእነዚህ የማንነት መገለጫዎች ቦታ በማይሰጥና በማያስተናግድ በአንድ አሀዳዊ የመንግሥት አስተዳደር ዘይቤ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። ይህ ‹አንድ ብሔር አንድ መንግሥት› የሚለው የአስተዳደር ዘይቤ (ኔሽን ስቴት) ብሔሮችን ከአገር ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮች እንዲገለሉ የሚያደርግና የአገር ግንባታ ሒደቱ በፈቃደኝነት ላይም የተመሠረተ ስላልነበረ ተቀባይነት አልነበረውም። በዚህም የተነሳ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ለተከሰቱት ግጭቶችና ጦርነቶች ዋነኛ መንስዔ ነበር። ይህ ኅብረ ብሔራዊነትን የማያስተናግድና የተለያዩ ብሔሮችን በጉልበት በመጨፍለቅ ሲተገበር የቆየው አስተሳሰብና ፖለቲካዊ ዓውድ፣ ኢሕአዴግ የደርግን መንግሥት በጦርነት አሸንፎ የአገራችንን ፖለቲካዊ ሥልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ ቋንቋንና ማንነትን መሠረት በማድረግ ለዘረጋው የፌዴራል መንግሥት መዋቅር ተመራጭነት በጉልህ ምክንያትነት ይጠቀሳል። ከላይ የተጠቀሰውን ነባራዊ ችግር ለመፍታት የዛሬ 25 ዓመት በሥራ ላይ የዋለውና እስካሁን ድረስ የዘለቀው የፌዴራል ሥርዓቱ፣ በሕገ መንግሥቱ በተቀመጡ መርሆዎችና ዴሞክራሲያዊ አሠራርን በተከተለ መንገድ ከተተገበረ በርካታ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ ለአብነትም ዴሞክራሲን እስከ ታችኛው የአስተዳደር እርከን ድረስ ለማጎልበት፣ ሕዝቦች ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ በማድረግ የማንነት ጥያቄዎች በአግባቡ እንዲመለሱ፣ ማንነቶችን ለማቻቻልና ፍትሐዊ ልማትን ለማሳለጥ ጠቀሜታዎች እንዳሉት በርካታ ምሁራን ይስማሙበታል።

በዚህም መሠረት ባለፉት 25 ዓመታት የፌዴራል ሥርዓቱ ብሔር፣ ብሔረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ የሚያስችሏቸውን የፖለቲካ መዋቅሮች እንዲገነቡ፣ ቋንቋቸውንና ባህላቸውን እንዲያዳብሩና  የሰው ኃይላቸውን እንዲያደራጁና በአቅም እንዲገነቡ በተለያዩ ልማቶች ተጠቃሚ እንዲሆነ በእጅጉ አስችሏቸዋል። ይህ ማለት ግን የፌዴራል ሥርዓቱ እንከን የማይወጣለት ወይም ከችግር የፀዳ ነው ማለት አይቻልም። የፌዴራል ሥርዓቱ የብሔር ብሔረሰቦችን ጥያቄ ከመመለስና ለማንነታቸው ዕውቅና በመስጠት ዙሪያ ብዙ ውጤቶች የተመዘገቡበት መሆኑ የማይካድ እውነት ቢሆንም፣ ኢትዮጵያዊ ማንነትን ከብሔራዊ ማንነት ጋር ለማስታረቅና የበለጠ ለማበልፀግ በሚፈለገው ልክ ጥቅም ላይ ውሏል ለማለት ግን ያስቸግራል። ከላይ ለተጠቀሰው ሐሳብ እንደ ማሳያ ሆኖ የሚጠቀሰው ጉደይ ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች እዚያና እዚህ እያሰለሱ የሚከሰቱ ብሔርን ማዕከል ያደረጉ ግጭቶችና መፈናቀሎች ናቸው። እነዚህ ብሔር ላይ የተመሠረቱ ግጭቶች ለሰው ለሕይወት መቀጠፍና ለንብረት ውድመት ምክንያት ሲሆኑ ከመታየታቸውም በዘለለ፣ ለረዥም ዘመናት በሕዝቦች መካከል የነበረውን የጠበቀ አዎንታዊ ግንኙነት ለመሸርሸር የማይናቅ ሚና ሊኖራቸው እንደሚችል በርካታ ምሁራንና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች አስተያየት ሲሰጡ ይደመጣሉ። በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ እየተከሰቱ ለሚገኙ በብሔር ላይ የተመሠረቱ ግጭቶች ከበስተጀርባቸው በርካታና ውስብስብ ምክንያቶች መኖራቸው በመንግሥትም ጭምር የታመነ ጉዳይ ቢሆንም፣ ችግሮቹ እንዴት ይፈታሉ በሚለው የመፍትሔ ሐሳብ ላይ የመስኩ ምሁራን፣ የሲቪል ማኅበራት፣ ተመራማሪዎችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ሚናና ተሳትፎ እጅግ አስፈላጊ የሆነበት ጊዜ ላይ ደርሰናል።

ሰሞኑን ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ዓለም አቀፍ የዴሞክራሲ ምርጫ ድጋፍ ሰጪ ኢንስቲትዩት (Institute for Democratic Electoral Assistance (IDE))፣ በኢትዮዽያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂክ ኢንስቲትዩትና ተቀማጭነቱን ኖርዌይ ባደረገው አድላንድ ኮንሰልት በሚባል ተቋም አማካይነት በኢትዮዽያ አገራዊ (ኔሽን) ግንባታና ቀጣይ አቅጣጫ “Nation Building in Ethiopia: The Quest for an Enduring Direction” በሚል ርዕስ በጋራ ባዘጋጁት ሲምፖዚየም (ጉባዔ)፣ በሙያቸው ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ ታዋቂ የሆኑ ምሁራን ሰባት ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል።

የሲምፖዚየሙ አስተባባሪና ሊቀመንበር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ካሳሁን ብርሃኑ በእንኳን መጣችሁ ንግግራቸው፣ ይህ በተከታታይ ጊዜያት በብሔራዊ አንድነት ግንባታ ላይ በማተኮር ለማካሄድ የታቀደው ሲምፖዚየም በዓይነቱ የተለየ መሆኑንና ሲምፖዚየሙ አገራችን በአሁኑ ጊዜ ለምትገኝበት ፖለቲካዊ ፈተና እጅግ ጠቃሚ የመፍትሔ ሐሳቦችና ግብዓቶች የሚገኝበት መድረክ ተደርጎ እንደሚታመን ነበር የገለጹት። ፕሮፌሰር ካሳሁን እንደሚሉት ባለፉት 25 ዓመታት አገሪቷን በማስተዳደር ላይ የሚገኘው መንግሥት፣ በዘረጋው ፌዴራላዊ የመንግሥት ሥርዓት በአገሪቱ በርካታ ስኬታማ ውጤቶች መመዝገባቸውን መካድ አይቻልም። በዚህም ለሰላምና መረጋጋት፣ ለኢኮኖሚ ዕድገት፣ ራስን በራስ ለማስተዳደርና የልማት አቅም ለመፍጠር ምቹ መደላድሎች ተፈጥረዋል። ይሁን እንጂ በዚህ ሒደት ለአስተዳደር መዋቅር ግንባታ የበለጠ ትኩረት በመስጠቱ እጅግ መሠረታዊ የሆነው የብሔራዊ አንድነት ግንባታ ጉዳይ ትኩረት ሳይሰጠው ቀርቷል ሲሉ ተናግረዋል። ፕሮፌሰር ካሳሁን አክለውም የሃይማኖት፣ የባህል የቋናቋና መሰል መገለጫዎች ተሰባጥሮ በሚገኝበት እንደ ኢትዮጵያ ባለ አገር ልዩነቶችን በማቻቻልና በማስታረቅ፣ የጋራ ታሪኮችንና እሴቶችን ለኢትዮጵያ የአገር አንድነት ግንባታ መሠረት አድርጎ ጥቅም ላይ ማዋል እጅግ ጠቃሚና ወሳኝ ጉዳይ ነው ሲሉ አስረድተዋል። አያይዘውም በአንድ በኩል በአገሪቱ ዘላቂነት ያለው አስተማማኝ ሰላም አንዲረጋገጥ ለማድረግ፣ በሌላም በኩል በአገሪቱ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል የጋራ አገራዊ ስሜት ለማዳበር እንዲቻል የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ለሚያጋሯቸው እሴቶችና ታሪካዊ ጉድኝቶች ዕውቅና መስጠትና እንዲዳብሩ ማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ አንዳለው ተናግረዋል። በዚህም ረገድ የተጠናከረ ጥረት ማድረግ ለኢትዮጵያ አገራዊ ቀጣይ የህልውና ዋስትና አዎንታዊ ሚናው የላቀ ነው በማለት አስገንዝበዋል።

አያይዘውም በሕዝቦች መካከል ባሉ ልዩነቶች ላይ በማተኮር የነበሩ አዎንታዊ ግንኙነቶች እንዲሻክሩ ከማድረግ ይልቅ ኅብረተሰቦች በጋራ የሚጋሯቸውን እሴቶች፣ ታሪካዊ ውርሶች፣ አዎንታዊ ምኞቶችና የሚያግባቡ ነጥቦችን ነቅሶ በማውጣት ለኢትዮጵያ አገራዊ አንድነት ግንባታ በሚጠቅም አግባብ በግብዓትነት መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ይህን ግንዛቤ ለማዳበርና በኅብረተሰቡ ውስጥ እንዲስፋፋ ለማድረግ ደግሞ  መንግሥት፣ ምሁራን፣ ሲቪክ ማኅበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የወጣቶችና የሴቶች ማኅበራት፣ እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሌሎች አካላት ላቅ ያለ ሚና አላቸው ብለዋል። ፕሮፌሰር ካሳሁን ንግግራቸውን በመቀጠል አገራችን አሁን ከምትገኝበት ችግር አኳያ በጉዳዩ ላይና በወደፊት አቅጣጫዎች ዙሪያ ከታሪካዊና ባህላዊ ዕይታዎች ጋር በማቀናጀት፣ የዳበረ ውይይትና የሐሳብ ልውውጥ በማድረግ ሰላምና መረጋጋት የሚረጋገጥበትን መፍትሔ ማመላከት አጅግ አስፈላጊ ጉዳይ እንደሆነ አስገንዝበዋል።

በመድረኩ የተገኙት በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል የጥናት ምርምርና አይዲዮሎጂ ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ ነፃነቷንና አገራዊ ሉዓላዊነቷነ ከውጭ ጠላቶችና ከወራሪ ኃይሎች ለረዥም ዘመናት አስጠብቃ መቆየት በመቻሏ አኩሪ ታሪክ ባለቤት ያላት አገር ናት፡፡ የዚህ ታሪከ መሠረታዊ ሚስጥር ደግሞ የአገሪቱ ሕዝቦች በአንድነትና በመተባበር ስሜት ሲፈጽሙ ያለፉበት የጀግንነት ታሪክ ውጤት ነው ብለዋል። ይህ እንዳለ ሆኖ ግን ይህን አኩሪ ታሪክና የሕዝቦች ጠንካራ የትብብር እሴት ዘላቂና ውጤት ወደሚያመጣ የአገር አንድነት ግንባታ ለመለወጥ፣ ትርጉም ያለው ሥራ ስላልተሠራ ብዙ ዋጋ እያስከፈለን ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል። ወ/ሮ ሙፈሪያት አክለውም አሁን በአገሪቱ እየታዩ ላሉ ፖለቲካዊ ችግሮች ምክንያታቸውን በመለየት ወቅታዊና አፋጣኝ ምላሽ ካልተሰጠ፣ እዚያም እዚህም በመታየት ላይ ያሉት ችግሮች በሒደት በእጥፍ አድገው የአገሪቱን ሰላምና አንድነት አደጋ ላይ ሊጥሉ እንደሚችሉ ቆም ተብሎ የሚታሰብበት ጊዜ ነው በማለት ለተሳታፊዎቹ አስገንዝበዋል። ወ/ሮ ሙፈሪያት በንግግራቸው ማጠቃለያ ያለንበት ወቅት የአገራዊ አንድነት ግንባታውን ከመቼውን ጊዜ በበለጠ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ባሳተፈ ሁኔታ ሰፋፊ ውይይቶች መደረግ ያለበት ነው ብለው፣ በመድረኩ የቀረቡ ጥናቶች ብሔራዊ ቅርጽ ወዳለው ፍኖተ ካርታ ከተለወጠ በኋላ መንግሥት የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ የሚመለከት ዝርዝር ፖሊሲ እንዲያወጣ መነሻ ዶክመንት በመሆን ጥቅም ላይ ይውላል በማለት አመልክተዋል።

በሲምፖዚየሙ ከቀረቡት የጥናት ወረቀቶች መካከል የቺካጎ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ታዋቂው ሳይንቲስት ዶ/ር ዘረሰናይ ዓለምሰገድ ያቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ በርካቶችን ያስደመመ ነበር። እንደ ዶ/ር ዘረሰናይ አባባል የአገር አንድነት ግንባታ ሲባል ውስብስብ  ከሆኑ ፖለቲካዊ ገጽታዎቹ ባሻገር፣ በዋናነት ትኩረት ተደርጎ ሊሠራበት የሚገባው ጉዳይ በሰው ልጆች መካከል ባለው የጎላ ትስስር ላይ ነው። ‹‹ከዚህ አኳያ በመካከላችን በታሪክም ይሁን በሌሎች ሁኔታዎች አንፃር ያለንን ትስሰር በደንብ አላጤነውም። ስለሆነም እነዚህን እውነታዎች በደንብ መፈተሽና አሁን ያሉንን መልካም የጋራ እሴቶች በማሳደግ አገራዊ መግባባት መፍጠር ይጠበቅብናል፤›› ያሉ ሲሆን፣ ያን ጊዜም ለብሔራዊ አንድነት ግንባታ ጥሩ መንገድ እንደሚከፈት ተናግረዋል።

ሌላው በሲምፖዚየሙ ላይ ጥናት ያቀረቡት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በርካታ ጥናቶችን በማቅረብ የሚታወቁት ታዋቂው ምሁር ፕሮፈሰር ክርስቶፎር ክላፋም ሲሆኑ፣ እንደ ምሁሩ አገላለጽ በአንድ አገር ውስጥ ያሉ የተለያዩ ሕዝቦች ተመሳሳይ ዓይነት መለያ ወይም የአንድነት መገለጫዎች አለን ብለው የሚያስቡና በአገራቸው ጉዳይ ላይ በእኩል ደረጃ ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚደረጉበት ዕድል ከተመቻቸ፣ ለብሔራዊ አንድነት ግንባታ ጥሩ መደላድል የሚፈጥር መሆኑን አብራርተዋል። በማከለም አገርን የሚያስተዳድሩ መንግሥታት ከዚህ ተቃራኒ የሆነ መንገድ የሚከተሉና የሕዝብን ፍላጎት የማያዳምጡ ከሆነ፣ የአገር አንድነትና ፀጥታ ለአደጋና ለውድቀት ይጋለጣል ብለዋል። ስለሆነም የአገር አንድነት ግንባታ አንድ ጊዜ ተጀምሮ የማያልቅና ረጅም ሒደት ያለው ሥራ በመሆኑ፣ መንግሥታት በየጊዜው የሕዝብን የልብ ትርታ እያዳመጡና ለተፈጠሩ ክፍተቶች ማስተካከያ ዕርምጃ በየጊዜው እየወሰዱ ሊሄዱ ይገባል ሲሉ ያስተላለፉት መልዕክት ብዘዎችን የሲምፖዚየሙ ታዳሚዎች ያስማማ ነበር ማለት ይቻላል።

በሌላ በኩል ኔዘርላንድ የሚገኘው የኤራስመስ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ ሱዳናዊው ፕሮፌሰር መሐመድ ሳሊህ ባቀረቡት ጽሑፍ፣ የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም አገሪቱ ውስጥ ለረዥም ጊዜ ሲካሄዱ ለነበሩ ትግሎች መቋጫ እንዲያገኝ ከማድረጉ ባሻገር ለብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የማንነት ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥቷል ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአገሪቱ በማኅበራዊና በኢኮኖሚያዊ ዘርፍ በርካታ ለውጦች እንዲመዘገቡ ማድረጉን ያነሳሉ፡፡ ለዚህም በአገሪቱ በመካሄድ ላይ ያሉትን የልማት ሥራዎችና የተገኙ ለውጦችን በምሳሌነት አንስተዋል፡፡ ይሁንና ከተመዘገበው የኢኮኖሚና የልማት ዕድገት ትሩፋቶች ዜጎች በእኩልነትና በፍትሐዊነት ተጠቃሚ የሚሆንበትን ዕድል ማመቻቸትና በፖለቲካውም ዘርፍ ዜጎችን ተሳታፊ የሚያደርግ ፖለቲካዊ ሒደት እንደሚያስፈልግ አክለው ተናግረዋል።

በሲምፖዚየሙ የተገኙ የተለያዩ አመለካከቶችን የሚያራምዱ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችና ምሁራን ጠቃሚ ናቸው ብለው የሚያስቧቸውን ሐሳቦችና አስተያየቶችን በስፋት አቅርበዋል። በሐርቫርድ ዩኒቨርሲቲ በሴሜቲክ ቋንቋዎችና ሥልጣኔ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ የኢትዮዽያ ሕዝቦች በታሪካቸው በጠንካራ መሠረት ላይ ያዳበሯቸውን የሚያስተሳስሩ እሴቶች፣ ባህሎችና የአንድነት አኩሪ ታሪኮችን ትልቅ ዋጋ ያላቸው ነገሮች ስለሆኑ፣ አሁን የተፈጠሩትን ችግሮች ለመጠገንና የአገር አንድነት ግንባታ ሥራን ውጤታማ ለማድረግ እንደ ጥሩ መሠረት ሊጠቀሙበት ይገባል ሲሉ ለተሰብሳቢዎች በአጽንኦት ተናግረዋል። ታዋቂው ፖለቲከኛ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ ለተፈጠረው ችግር መሠረታዊ ምክንያት የዴሞክራሲ ዕጦት በመሆኑ፣ የዴሞክራሲ ምኅዳሩን በማስፋት በወሳኝ ጉዳዮች ላይ ሕዝቡን በማሳተፍና አገራዊ ዕርቅና መግባባት እንዲፈጠር በማድረግ ዴሞክራሲያዊና የአስተዳደር ሥርዓት ያለበትን አገር መፍጠር እንችላለን ብለዋል። አክለውም ይህ ተግባራዊ ከሆነ በአገራዊ አንድነት ግንባታ ረገድ የሚታዩ ክፍተቶችንም ጭምር የሚፈታ ጥሩ መሠረት ነው በማለት አስረድተዋል።

በሲምፖዚየሙ የአገር አንድነት ግንባታ (Nation building) ምንነት፣ የአገር አንድነት ግንባታ የተለያዩ ሞዴሎችና ተግዳሮቶች ከአውሮፓ የስካንዲኒቪያን አገሮችንና ጀርመንን፣ ቻይና፣ ከአፍሪካ ናይጄሪያና ደቡብ አፍሪካን በምሳሌነት በመውሰድ በስፋት ተተንትኖ ውይይት ተደርጎባቸዋል። ከዚህ አንፃር የተነሱት ጉዳዮች ሰፋፊ፣ የተለያዩ የአገር ግንባታ ሞዴሎችን የሚያስተዋውቁና በጽንሰ ሐሳብ ላይ ያተኮሩ ቢሆንም፣ አብዛኛዎቹ የጥናት አቅራቢዎች ተመሳሳይ ሐሳብ ወይም አቋም ያንፀባረቁባቸው ጉዳዮችም ነበሩ። ይኸውም የአገር ግንባታ እንዲሁ በአዋጅና በመሪዎች በጎ ምኞት ብቻ አብቦ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለፍሬ የሚበቃ ሳይሆን፣ እልህ አስጨራሽና ብርቱ ትግልና መስዋዕትነትን የሚጠይቅ ረዥም ሒደት ያለው እንደሆነ ነው። አሁን የተዋጣላቸው የበለፀጉ የአውሮፓ ዴሞክራሲ አገሮች የሚባሉትም ቢሆኑ በእንደዚሁ ዓይነት ለምድ እንዳለፉና አሁንም በአንድነት ግንባታ ሒደት ላይ እንዳሉ ነው።

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የዴሞክራሲ ባህል ባልዳበረባቸው፣ በሕገ መንግሥት ውስጥ የተደነገጉ የዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች አተገባበር ላይ በርካታ ክፍተቶች በሚታዩባቸው፣ እንዲሁም በአጠቃላይ በዴሞክራታይዜሽን ሒደቱ ላይ በርካታ መሰናክሎች በሚያጋጥሙዋቸው አገሮች የአገር ግንባታው ሒደትም ፈታኝ ሁኔታዎች እንደሚያጋጥሙት ሳይታለም የተፈታ ነው። ከዚህ በተጨማሪም የፖለቲካ እኩልነት በሕገ መንግሥት ውስጥ ቢደነገግም፣ አመርቂ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እኩልነት ባልሰፈነባቸው አገሮች ዛሬም በዜጎች አመለካከት ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ የሚናቅ እንዳልሆነ ሌላው ከሲምፖዚየሙ የተገኘ ትምህርት ነው። ይህ ሁኔታ የተለያየ ቋንቋና ባህል ያሏቸው ሕዝቦች ውስጥ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጎራ ፈጥረው ነባራዊ የፖለቲካ ሁኔታውን ፈተና ላይ ሊጥል ይችላል። ስለሆነም በአጠቃላይ የሕዝቦችን የተሳሰረ ማንነት በመፍጠር ረገድ የሚታዩ ውስንነቶች አስቸኳይ መፍትሔ ይፈልጋሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ በጉዳዩ ላይ የሚመክሩና መፍትሔ የሚያመላክቱ ቀጣይ የውይይት መድረኮች በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እንዲዘጋጁ በማድረግ፣ ዜጎችን በአገራቸው ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ እንዲመክሩና እንዲወያዩ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህ አሁን በአገሪቱ ውስጥ ለሚታየው ችግር መፍትሔ ለማመንጨት ከማገዙ በተጨማሪ፣ ዜጎች ስለአገራቸው የፖለቲካ ሒደትና ስለሕገ መንግሥት በጎ አመለካከት እንዲያዳብሩ ስለሚረዳ ጠቀሜታው የጎላ ነው። ከዚሁ ጎን ለጎንም ለዚህም የሁሉም ሕዝቦች የጋራ ታሪክ የሆኑ እንደ ዓደዋ ያሉ ድሎችን ለአገራዊ አንድነት ግንባታ ሒደት መጠቀምም ብልህነት ነው።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...