Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርብሔራዊ ወይስ የታሪክ ዕርቅ?

ብሔራዊ ወይስ የታሪክ ዕርቅ?

ቀን:

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

በተመሳሳይ ወይም በተለያዩ ምክንያቶች የሚነሱ ግጭቶች የውጭና የውስጥ ተብለው የሚከፈሉ ቢሆኑም፣ አንዳቸው በሌላቸው ላይ ተደርበው የሚከሰቱ እንጂ ለብቻቸው ተነጥለው የሚኖሩ አይደሉም፡፡ ስለሆነም የውጭ ኃይሎች በአንዳች ምክንያት (ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሊሆኑ ይችላሉ) በሌሎች አገሮች ውስጥ ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ተፅዕኖ እንዲፈጠሩ የሚያደርጓቸው ግጭቶች መነሻቸው የራሳቸው የአገር ውስጥ ችግሮች ሊሆኑ እንደሚችሉት ሁሉ፣ በአንድ አገር ውስጥ የሚፈጠሩ ግጭቶችም ቢሆኑ ከውጭ ችግሮች ጋር የተያያዙ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ግጭቶቹ አብዛኛውን ጊዜ የጎሳ፣ የወንዝ፣ የአውራጃና የቀበሌም ሊሆኑ  ይችላሉ፡፡ እንደዚህ ያሉት ግጭቶች አልፎ አልፎ የሚከሰቱና በአገር ሽማግሌዎች የሚፈቱ ቢሆኑም፣ ከዓመታት ታሪካችን ድምር ውጤት አኳያ ሲታዩ የሚያስከትሏቸው ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች በቀላሉ የሚታዩ አይደሉም፡፡ በውጫዊም ሆነ በውስጣዊ ግጭቶች ምክንያት የሚደርሰው ጥፋት ከማኅበራዊ፣ ከኢኮኖሚያዊ፣ ከፖለቲካዊ፣ ከሥነ ልቦናዊ፣ ወዘተ አንፃር የሚታይና የሚተነተን ሲሆን ከሚደርሱት ጥፋቶች ውስጥ ጎላ ጎላ ያሉት እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

ከሁሉ አስቀድሞ ወረራው ከውጭ የሚመጣ ከሆነ ተወራሪው ቅኝ ግዛት የመሆን ዕጣ ይገጥመዋል (ሕዝቡ ይገዛል፣ ሀብትና ንብረቱ እየተዘረፈ ወደ ባዕድ አገር ይላካል፣ የባሕልና የሥነ ልቦና ወረራ ይደርስበታል፣ ይታሰራል፣ ይጋዛል፣ ይገደላል)፡፡ በሰው ሕይወት ላይ የሚደርስ ጥፋት (መሞት፣ መቁሰል፣ ከአምራችነት ውጭ ወይም አካለ ጎደሎ መሆን)፣ በለማዳ እንስሳት ላይ የሚደርስ ጥፋት (በቀጥታ በጦርነቱ ላይ የሚሳተፉ አጋሰሶች፣ በጦርነትና ለጦረኞች የሚታረዱ እንስሳት፣ ድል አድራጊዎች በምርኮ የሚወስዷቸውና ያላግባየሚገድሏቸው እንስሳትና በዚህ ምክንያት የሚከተል ድህነት)፣ በዱር እንስሳት ላይ የሚከተል ጥፋት (ለምግብ አገልግሎት በማዋል፣ በጭካኔ በመግደል፣ ጫካ በማቃጠል)፣ በጫካ መቃጠል (ጠላት እንዳይደበቅበት፣ ለማገዶ፣ በአዝርዕት ላይ የሚከተል (በእርሻ ላይ ያለ መረገጥና መቃጠል፣ በጎተራ ውስጥ የሚገኝ እህል መዘረፍና መቃጠል፣ በዚህም ምክንያት የገበሬው ለድህነት መጋለጥ)፣ የመኖሪያ ቤቶች መቃጠል፣ መውደም (ሰዎች ያለ መኖሪያ መቅረት፣ መኖሪያቸውን ለመሥራት ጫካ መመንጠር፣ ጡብና ድንጋይ ማምረት፣  የሥራ ሰዓታቸውን ቤት በመሥራት ማሳለፍ፣ የነዋሪዎች ሀብትና ንብረት መውደም (በቁሳቁስ፣ በገንዘብ፣ በጌጣጌጥ በመሳሰሉት የሚገለጥ)፣ በማኅበራዊ አውታሮች ላይ የሚደርስ ጥፋት (ለምሳሌ በትምህርት መስክ ላይ የሚደርስ ጥፋት  ማለትም ምሁራን፣ የመማሪያ ቦታዎች ማለትም ከፊደል እስከ ቅኔ የሚያስተምሩ የሃይማኖት ትምህርት ቤቶች፣ ከፊደል እስከ ዶክትሬት የሚያስተምሩ ዘመናዊ ትምህርት ቤቶች፣ ቤተ ሙከራዎች፣  የምሁራን መጻሕፍትና ድርሰቶች፣ የምርምር ውጤቶች)፣ በኢኮኖሚያዊ አውታሮች ላይ የሚደርስ ጥፋት (ለምሳሌ በመንገዶች፣ በቤቶች፣ በማምረቻ ቦታዎች መውደም፣ የሸማ፣ የቅርፃ ቅርፅ፣ የአለላ፣ ወዘተ ሥራዎች፣ የልብስ ስፌት፣ ወይም የፋብሪካ ቦታዎች)፣ ለጦርነቱ ሲባል የሚመደበው በጀት ከፍተኛ መሆንና የዕድገት እንቅስቃሴውን መግታት፣ (በጦርነት ኢኮኖሚ ምክንያትም የኢኮኖሚ ድቀት መድረስ)፣ በጦርነት ምክንያት ለሚከሰቱ በሽታዎች ሰለባ መሆን፣ የአዛውንቶች፣ የሕፃናት፣ የነፍሰ ጡሮች፣ የአካል ጉዳተኞች ለከፋ ጉዳት መዳረግ፣ የሕዝቦች ለረሃብ፣ ለእርዛትና ለልመና መጋለጥና የሥነ ልቦና ቀውስ መፈጠር ናቸው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በጦርነትና በግጭት የሚደርስ ውድመት

ተጽፈው የምናገኛቸው የታሪክ መጻሕፍት በአብዛኛው የጦርነትን ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ገጽታ የሚያጎሉ ሆነው ይገኛሉ፡፡ ከጥንት ጀምሮ እስካሁን ‹‹ብዙ ሰዎች ሞቱ›› እንጂ ‹‹አገር ሞተች›› ብለን አንቆጭም፡፡ የጠላታችን መሞት እንጂ በዚያ ምክንያት የአገራችን መሞት አይታሰበንም፡፡ ‹‹ምን ያህል የጦር ሰውና የጦር መሣሪያ እስከ ስንቅና ትጥቅ ተሠለፈ? ጦርነቱ በተካሄደበት አካባቢ ምን በገንዘብ የሚለካ ጥፋት ወይም ውድመት አደረሰ?›› ተብሎ ቢጠየቅ መልስ የለም፡፡ ለምሳሌ ከረጅሙ የኢትዮጵያ ታሪክ አኳያ ሲታይ ቅርብ የሆነውን የዓደዋ ጦርነትን እንደ ምሳሌ እንመልከት፡፡ በወታደራዊ ምንጮች መሠረት ጣሊያን በወቅቱ በምሥራቅ አፍሪካ በተለይም በኤርትራ ከነበረው 400,000 ሠራዊት በተጨማሪ በሶማሊያ የነበረው 285,000 ሠራዊት ነበር፡፡ የኢትዮጵያ  የዚያን ጊዜ ያንቀሳቀሰችውራሶች የሚመራ 300,000 ሠራዊት ነው (ይህንን ቁጥር አንዳንዶች 500,000 እንደሚደርስ  ይገምታሉ)፡፡ ሠራዊቱ ሲመች ከሚሰጠው ጥይት በስተቀር ስንቁንም ሆነ የጦር መሣሪያውን ይዞ የተሠለፈው ከግሉ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ሠራዊት የራሱ የሆነ በቅሎ ፈረስ፣ ግመልና አህያ ይዞ ከመዝመቱ በስተቀር የጦር መኪና፣ የጦር አውሮፕላን፣ ታንክ የሚባል አልነበረውም፡፡ እያንዳንዱ ሰው በቀን ግማሽ ኪሎ እህል ቢመገብና ይህንም የሚያቀርበው በዓደዋና በአካባቢው የሚገኝ ሕዝብ ቢሆን ያ ሕዝብ ምን ያህል ለእንጀራ፣ ለወጥ ወይም ለቂጣና ለዳቦ የሚሆን እህል እንዲያዋጣ ተገደደ? በዚህስ ምክንያት ምን ያህል ጉዳት ደረሰበት?

 መኳንንቱና መሳፍንቱ በቀን 1,000 ከብቶችን ከአደዋና ከአካባቢው ነዋሪ እየወሰዱ ቢያርዱ ምን ያህል በሬ፣ ላም፣ በግና ፍየል ለዕርድ ቀረበ? አንድ መቶ ሰው በቀን አንድ ዛፍ ለምግብ ማብሰያ፣ በብርድ ጊዜ ለመሞቂያ፣ ለዳስ መሥሪያ ቢጠቀም፣ ከዚህም በተጨማሪ መንገዱ በደን የተሸፈነ በመሆኑ ምክንያት ለመክፈት ሲባል በቀን በሺሕ የሚቆጠር ዛፍና ቁጥቋጦ ቢመነጠር፣ ለምርኩዝ የሚሆን ዱላ ለማበጀት እያንዳንዱ ሰው አንድ ቅርንጫፍ ቢቆርጥ፣ ለጦርና ለወስፈንጥር መሥሪያ ያን ያህል ቢጠቀም፣ አንድ ጦር የሚያሳልፍ መሻገሪያ ድልድይ ለመሥራት ቢያንስ አሥር ትልልቅ ዛፎችን መቁረጥ ቢያስፈልግና በአማካይ 1,000 ወንዞች ያህል ቢደለደሉ፣ ምን ያህል ደን እንደ ተጨፈጨፈ መገመት አያስቸግርም፡፡ ዳሩ ግን መልሱን እኛ ካልመለስነው ማን ሊመልሰው ይችላል? ለመሆኑ የትግራይ፣ የወሎና የጎንደር ተራሮች የዛሬ 500 ዓመት ኢትዮጵያን የጎበኙ የውጭ አገር እንግዶች በደን የተሸፈኑና እንደ ዝሆን፣ አንበሳ፣ ነብር ያሉ የደን እንስሳ የሚርመሰመሱባቸው ነበሩ ብለው ከመሰከሩ፣ ዛሬ በእነዚያ አካባቢዎች እነዚያ ደኖችና እንስሳት ከሌሉ ከእርስ በርስ ጦርነት በስተቀር ማን ወሰዳቸው ብለን እናስባለን?

ጠባብ ብሔርተኝነትና መዘዙ

ነገሩን ከፖለቲካ ሳይሆን ከእምነት አኳያ ስንመለከተው፣ ከሁሉ አስቀድሞ ሰዎችን የአንድ ቤተሰብ አባላት መሆናቸውን በመተው በዘርና በጎሳ መከፋፈል ወይም ከፋፍሎ በሚገዛ ሥርዓት ሕዝብን መምራት መለኮታዊ ትዕዛዝን አለመቀበል ይሆናል፡፡ ብሔርተኛነት ለብዙ መቶ ዓመታት በአያሌው ሲንሰራፋ መኖሩ የታወቀ ነው፡፡ በመሠረቱ ጠላት ፈጠር የሆነው ብሔርተኝነትን ጠላቱን በፍጥነት ዞሮ እንደሚያጠቃ እባብ ለመታገል መቻል ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ጠላቶች ያገኙትን ሁሉ ለመያዝ ስግብግብ እጆቻቸውን ዘርግተው የሚንከወከው ዘንዶዎች ናቸው ብንላቸው እውነት ነው፡፡ በእርግጥም እነዚህን ጠላቶቻችን ፋይዳ ያለው ነገር ያደርጋሉ ብሎ መጠበቅም ከንቱ ነገር ነው፡፡ እነሱን የሚቃወሙ ክፍሎችን የሚቃወም አቋም ይዞ መገኘትም አደገኛና ለሚደረገው ፀረ ዘረኛነት ትግል መዳከምም በእጅጉ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ የታወቀ ነው፡፡ አሉታዊ በሆነ ብሔረተኝነት መፈክር ሥር ተሠልፈው መጠኑን ያለፈ የአርበኝነት ወኔ ለማሰማት ለሚፈልጉ ክፍሎች ልናስታውሳቸው የምንወደው ነገር ቢኖር፣ ይህችን አገር እናፈቅራለን ካላችሁና የእርሷም ጉዳይ ይቆረቁረናል፣ እናስብላታለን፣ እናዝንላታለን፣ የእርሷ ጉዳይ ጉዳያችን ነው የምትሉ ከሆነ አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ የሚመለከት ተግባር በማከናወን አርበኝነታችሁን አስመስክሩ፡፡ ፍቅራችሁንና ክብካቤያችሁን ለማይሹ ለውሁዳኑ የቆማችሁና ለራሳችሁ ጊዜያዊ ዓላማ ግብ መድረስ ለማራመድ ከሆነ ግን፣ ዓላማችሁ የአብዛኛውን ሕዝብ ዓላማ መሠረት ያላደረገ ነውና ብሔራዊ አርበኞች ልትሆኑ አትችሉም፡፡

በብሔራዊ ዕርቅ ብቻ ሳይሆን በታሪክ ዕርቅ እንድናተኩር የሚያደርጉን

አሁን ያለንበት ወቅት የ‹‹ብሔራዊ ዕርቅ›› ጉዳይ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሲንፀባረቅ ይታያል፡፡ የብሔራዊ ዕርቅ ጉዳይ ደቡብ አፍሪካ ከነበረው የነፃነት ንቅናቄና የነፃነት ንቅናቄው ዓላማ ግቡን ከመታ በኋላ ነጮች ወገኖቻቸው በበቀል ጉዳት እንዳይደርስባቸው ከማሰብ የመነጨ ነው፡፡ በዚህ የታሪክ ምዕራፍ ቅኝ ገዥዎችንና አጋሮቻቸውን በአንድ በኩል፣ ነፃ የወጡ ሕዝቦችንና አጋሮቻቸውን በሌላ በኩል እንመለከታለን፡፡ ቅኝ ገዥዎች ለብዙ ዓመታት የአገሬው ተወላጆችን ሲጨቁኑ፣ ሲበዘብዙና ሲገድሉ ኖረዋል፡፡ ግኝ ተገዥዎች ደግሞ በቅኝ ገዥዎቻቸው ግፍ ደርሶባቸዋል፡፡ በዚህ ምክንያት በገዥና በተገዥ መካከል አስመራሪና እልህ አስጨራሽ ትግል ተካሂዷል፡፡ ከዚህ አኳያ የአገራችንን ችግር እንመልከተው፡፡ የውጭ ኃይል አልነበረም፡፡ ትግሉም ከባርነት የመላቀቅ አልነበረም፡፡ የሥልጣን ትግል ነው፡፡ የሥልጣን ትግል ደግሞ በሰላማዊም በጦርነትም ይካሄዳል፡፡ አንዱ አሸናፊ፣ ሌላው ተሸናፊ ይሆናል፡፡ በዚህም መሠረት የአፄ ቴዎድሮስን መንግሥት የአፄ ዮሐንስ መንግሥት፣ የአፄ ዮሐንስን መንግሥት የምኒሊክ መንግሥት፣ የምኒሊክን መንግሥት (እያሱን በኃይል ስላስወገደ) የኃይለ ሥላሴ መንግሥት፣ የኃይለ ሥላሴን መንግሥት ደግሞ የጦር ኃይሉ በጦር መሣሪያ አስገድዶ እንደጣለው ሁሉ፣ የኢሕአዴግም መንግሥት የደርግን መንግሥት አስገድዶ ጥሏል፡፡

በእዚህ ላይ ደርግ መውደቅ ነበረበት፣ አልነበረበትም ከሚለው ክርክር በተጨማሪ ክርክሩን ለማክረር የምንጠቀምባቸው ተጓዳኝ ጉዳዮችን ልናነሳ እንችላለን፡፡ ነገር ግን ጉዳዩን ደቡብ አፍሪካ እንደነበረው ዓይነት ችግር ስላልነበር የብሔራዊ ዕርቅ ጉዳይ የሚነሳበት ምክንያት አለን? ብለን መጠየቅና ታሪካዊ ግምገማ አድርገን ፍርድ ልንሰጥ እንችላለን፡፡ በዚህ ጸሐፊ ዕይታ ይነሳ ከተባለ ግን መነሳት ያለበት ከታላቅነት ወደ ድህነት ያወረደን የጦርነት ታሪክ ወይም በአጭሩ ታሪካዊ ዕርቅ ዕጦት ስለሆነ በዚህ ጉዳይ ትኩረት ልንሰጥ ይገባል፡፡ በጣም የሚገርመው ደግሞ መንግሥት መጥቶ መንግሥት በሄደ ቁጥር እንደምን ጠንካራ የጦር ኃይል እንደሚገነባና ውስጣዊና ውጫዊ ጠላቱን እንደሚያንበረክክ እንጂ፣ ያለፈው የጦርነት ታሪክና ያ ታሪክ ያስከተለው ጥፋት ጉዳዩ አይመስልም፡፡ ያለፈውን መኮነን እንጂ የጠፋው የጋራ ሀብት መሆኑን አምኖ እንደምን መለወጥ እንደሚቻል ማሰብ የእሱ አይመስለውም፡፡

በጥንታዊት ኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ግጭቶች ከአንድ ሺሕ ዓመታት ለበለጠ ጊዜ ሰፍነው የቆዩ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በእርስ በርስ ጦርነት ከግንባር ቀደም ሥልጡንነት ወደ መጨረሻው ድህነት ተሸቀንጥራ ወርዳለች፡፡ የረዥሙን ጊዜ ታሪክ ትተን ከአክሱም ሥልጣኔ ከሚባለው ብንጀምር፣ በጥንታዊ የአክሱም ዘመነ መንግሥት እስከ 30 እና 40 ዓመት ተረጋግተው የገዙ ነገሥታት እንደነበሩ ቢታወቅም፣ አብዛኛው ለጥቂት ዓመታት ወይም ወራት ወይም ቀናት እንደ ነገሡ ከታሪክ ማኅደራችን መረዳት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ከ313 እስከ 339 ባለው ጊዜ አብርሃ ወአጽብሃ ከአዳሎች ጋር የነበራቸው ግጭት፣ አፄ ኢዛና ከ313 እስከ 339 በድንጋይ ላይ ያሰፈሩት ጽሑፍ ስለድላቸው ያወሳል (ፓንክረስት 26-7)፡፡ ከ339 እስከ 351 አፄ ኢዛና ከቤጃዎች ጋር ያደረጉት ጦርነት የአክሱም ነገሥታት ቤጃዎችንና ሳሱዎችን ወረዋል (ፓንክረሰት ገጽ 32)፡፡

በዛጉዌ ዘመነ መንግሥት 16 ነገሥታት ሥልጣን የተፈራረቁ ሲሆን፣ ሦስቱ እያንዳንዳቸው 40 ዓመት፣ አራቱ እያንዳንዳቸው ከ20 እስከ 34 ዓመት፣ አምስቱ እያንዳንዳቸው ከ10 እስከ 15 ዓመት፣ አራቱ እያንዳንዳቸው ከአራት እስከ ስምንት ዓመት እንደነገሡና የሥልጣን ሽግግሩ በአብዛኛው አጭር መሆኑን እንረዳለን፡፡ ይህም የሆነበት አንደኛው ምክንያት በወቅቱ የነበረው የሥልጣን ፉክቻ ለመሆኑ  አያጠያይቅም፡፡ በሸዋው ሰለሞናዊ ሥርወ መንግሥት ዘመን በተለይም በመጀመሪያው 150 ዓመት ከ1270 እስከ 1420ዎቹ አንፃራዊ በሆነ መንገድ ስናየው የተረጋጋ የነበረ ሲሆን ከ1430ዎቹ ወዲህ ግን የእርስ በርስ ግጭት አዳክሞት ነበር፡፡ ገበሬው የዕለት ተዕለት ሥራው ጦርነት በመሆኑም በአሥራ ሰባተኛው ክፍለ ዘመን የተከሰተውን ረሃብ ሊቋቋመው እንዳልቻለ፣ በዚያ ሳቢያ ብዙ ሕዝብ ማለቁን ከታሪክ ምዕራፎች የምንረዳው ሀቅ ነው፡፡ ስለዚህ ብሔራዊ ዕርቁ ከታሪክ ዕርቁ ጋር ካልታየ በስተቀር በእጅጉ አስቸጋሪ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡

ይህም ሆኖ ብሔራዊ ዕርቅ አስፈላጊ ከሆነ ዕውን የሚሆነው መቼ ነው? ከሁሉ አስቀድሞ ብሔራዊ ዕርቁን ዕውን ለማድረግ ሕግ ማውጣት፣ ሕጉን በሪፈረንደም ማስፀደቅ፣ በሕጉ መሠረት በአገር ውስጥና በውጭ አገር የሚገኙ ተቃዋሚዎችን በምሕረት አዋጅ አሰባስቦ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ፣ የብሔራዊ ዕርቅ አስተባባሪ፣ አፈጻጸም አካልና ጽሕፈት ቤት ማቋቋም፣ ብሔራዊ ዕርቅ ጉባዔ መጥራትና የሽግግር መንግሥት ማቋቋምና የሚቋቋመው የሽግግር መንግሥት ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ ይኖርበታል፡፡ ከዚህም በላይ ብሔራዊ ዕርቅ ከሚፈልጉት ውጭ ከሚኖሩ የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚዎች መካከል የአፄ ኃይለ ሥላሴ የልጅ ልጆች የሆኑ ልዑላን፣ መሳፍንትና መኳንንት ዘውዳዊ ሥርዓት እንዲመሠረት ፍላጎት ስላላቸው ነገሩ እንዲህ በቀላሉ የሚታይ ሊሆን አይችልም፡፡ ሀቁ ይህ ከሆነ የሽግግር ዘመኑ ምሥረታ በምን ያህል ጊዜ ተፈጻሚ ይሆናል? ይህም ሆኖ በብሔራዊ ዕርቅ በሚቋቋመው መንግሥት ላይ የማያምፅ ፋኖ ላለመነሳቱ ምን ዋስትና አለ? ስለዚህ ብሔራዊ ዕርቅ ተፈጥሮ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት መቋቋሙን ብቻ ሳይሆን፣ ያንን ለማምጣት እንዴት እንደሚቻል ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ ይህስ ካልሆነ የአንድ ፈላጭ ቆራጭ ፓርቲ አመራርን አሜን ብሎ መቀበል ያዋጣል? ለዚህ መፍትሔው መንግሥትም ሆነ ተቃዋሚዎች ‹‹ከእኛ ወዲያ ጎራሽ ማድ አበላሽ›› የሚለውን ፈሊጥ ትተው ሁሉንም አሳታፊ የሆነ የዴሞክራሲ ሥርዓትን በአፋጣኝ መዘርጋትና ጊዜ ወስዶ ሕዝባዊ መንግሥትን ዕውን ማድረግ ነው፡፡

ለመቻቻልና በሰላም አብሮ ለመኖር ፍቅር

በሰላም ለመኖር በፍቅር መኖርን ይጠይቃል፡፡ ፍቅር የሚጀምረው ከአዕምሯችን ነው፡፡ ስለፍቅር ስናስብ የምናስበውን እንሆናለን፡፡ የፍቅርን ማሰብ፣ የፍቅርን ልምድና የፍቅርን ግንኙነት ይፈጥራል፡፡ ለማፍቀር ስንዘጋጅ ስለራሳችንና ስለሌሎች የነበረንን እምነትና ሐሳብ ይቀየራል፡፡ ሌሎችን ለማፍቀር ስንፈልግ ፍላጎታቸውንና የሚወዱትን ለማወቅ እንጥራለን፡፡ ስለምናፈቅራቸው ሰዎች ስናስብም ስናገኛቸው ምን እንደሚሹ ለማወቅ ያስችለናል፡፡ አንድን ሰው ወይም አንድን ነገር ለማፍቀር በመጀመሪያ ለራሳችን ፍቅር ሊኖረን ይጠበቅብናል፡፡ በመጀመሪያ የምናከብረውም ራሳችንን ይሆናል፡፡ ራስን ማክበር ማለትም ‹‹ከራሴ የማከብረው ምንድነው?›› ብለን መጠየቅ ነው፣ የምንጠላቸውን ጨምሮ፡፡ ሌሎችን  ለማክበርም ‹‹ከእነሱ የማከብረው ምንድነው?›› ብለን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ ፍቅርን የምንሻ ከሆነ እኛም ሌሎችን ከልባችን ማፍቀር ይኖርብናል፡፡ የምንሰጠው ከፍ እያለ በሄደ መጠን የምናገኘውም እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ማፍቀር ማለት ራስን በነፃና ያለቅድመ ሁኔታ መስጠት ማለት ነው፡፡ በማንኛውም ጊዜና ቦታ ደግ ሆኖ መገኘት ነው፡፡ ዕድሜ ልክ የሚዘልቅ ደስታ፣ ዕድሜ ልክ የሚዘልቅ ወዳጅነት በምንቀበለው ሳይሆን በምንሰጠው ላይ የተመሠረተ ነው፡፡

ሰዎችን ካላመናቸው በስተቀር ልናፈቅራቸው አንችልም፡፡ ስለዚህም ግንኙነታችን ለዘለቄታው እንደሆነ ለማሳየት መቻል ይኖርብናል፡፡ ለሁሉም የፍቅር ግንኙነት መተማመን አስፈላጊ ነው፡፡ ራሳችንን እንመን፣ ሌሎችን እንመን፣ ዓለምን እንመን፡፡ እነዚህ ሁሉ የፍቅር ጠንካራ መሠረቶች ናቸው፡፡ የሰላምን ጣዕም ባለፉት አሥር ዓመታት እንዳየነው ለብዙ ዘመናት በአገራችን ሰላም በመጥፋቱ ምክንያት አንፀባራቂ ሥልጣኔያችን ደብዝዟል፡፡ ይልቁንም የውጭ ሰዎች አይተው የሚያደንቁት እንጂ እኛ የማናደንቀው ወይም እያየን የማናየው ሆኗል፡፡ ለምን? መልሱ በጣም ቀላል ላይሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ለብዙ ዓመታት በውስጣችን በነበረ ግጭት ምክንያት ለዚያ ሥልጣኔ ያበቃን የሥራ ባህላችን፣ ማኅበራዊ ባህላችን፣ ማኅበራዊ እሴታችን፣ ማኅበራዊ ሕይወታችን ቀስ በቀስ ተሸርሽሮ ለሥልጣኔአችን ባዕድ ስለሆነ እንደሆነ ግን ጥርጥር የለውም፡፡ ትናንት የፕሪስተር ጆንን ዕርዳታ ማለትም የገናናውን የኢትዮጵያ መንግሥት ወታደራዊ ዕርዳታ ለማግኘት የመጡ አገሮችና እስከ ዋና ከተማቸው ገብተን ያረጋጋናቸው አገሮች፣ ዛሬ እነሱ ራሳቸው ከፈለጉት ጋር የንግድ ትስስር መሥርተው እኛን ከማን ጋር መነገድ እንዳለብንና እንደሌለብን የሚነግሩን በሌላ ምክንያት ሳይሆን ድሆች በመሆናችን ነው፡፡ ሁሉምምነት ስለመልካምና በጎ ተግባር በራሱ መንገድ የሚገልጸው ስላለው በዚህ ገረድ ለጊዜው መተንተን አያስፈልግም፡፡ አንደኛውን ትክክል ሌላውን ስህተት ብሎ መፈረጅም አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ፣ ቢሞከርም በሁሉም በኩል ተቀባይነት አያገኝም፡፡ ትክክል መሆንም፣ ትክክል አለመሆንም አንፃራዊ የሚሆነውም ለዚህ ነው፡፡ ‹‹እከሌ ትክክል አይደለም›› የምንለው በራሳችን መሥፈርት እስከሆነ ድረስ ሌላውም በራሱ መስፈርት ‹‹ትክክል አይደላችሁም›› ሊለን ይችላል፡፡

ስለዚህ ሰማያዊውን መንግሥት በምድር ላይ ሕግ፣ ወታደር፣ እስር ቤት፣ አስተዳደራዊ መዋቅር፣ ወዘተ ካለው ምድራዊ መንግሥት ጋር ጨፍልቀን ልናየው ወይም ልናያይዘው ከቶ አይገባም፡፡ በመንፈሳዊ ተግባራችን የምናከናውነው ለሰማያዊ ቤታችን በምድር የምናከናውነው በጎ ተግባር ደግሞ ለዓለማዊ ቤታችን ይጠቅመናል፡፡ እርግጥ ነው አንዱ በጎ ተግባር ጋር ከሌላው በጎ ተግባር ጋር ሊያያዝ ይችላል፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ ግን ከዓረቦችም ሆነ ከእስራኤል ጋር ያለን ግንኙነት ከሃይማኖት ጋር ብቻ ተደርጎ መታየት የለበትም፡፡ ሩቅ መሄድ ሳያስፈልገንግብፅናሱዳን ጋር ከጥንት ጀምሮ ሁለንተናዊ ግንኙነት አለን፡፡ ሃይማኖቱ ተጨማሪ ነው፡፡ በዓባይ እንገናኛለን፣ ከቆየው ታሪካችን አኳያ እርሱም ተጨማሪ ነው፡፡ ያለ ዓባይ አብረን ልንኖር እንችላለን፡፡ ያለ ቀይ ባህር ስንኖር ነበር፡፡ አሁንም እየኖርን ነው፡፡ ዳሩ ግን ይህን ተጨማሪ ነገር ለበለጠ ወዳጅነት፣ ለበለጠ መቻቻልና ለበለጠ ወንድማማችነት ልንጠቀምበት እንችላለን፡፡

ማጠቃለያ

እውነቱን ገልጠንና ገላልጠን ስንመለከተውም ለሥልጣኔያችን መደብዘዝ መሠረታዊ ምክንያት፣ ሰላማችንን አስፍነን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አቅማችንን ባለማጠናከራችን የተፈጠረ ነው፡፡ ይህንን ሐሳብ ለማብራራት ብዙ መራቅ አያስፈልገንም፡፡ የህዳሴውን ግድብ ለመገንባት የገንዘብና የጠበብትን እገዛ ያላገኘነው ‹‹አቅም ስለሌላቸው የት ይደርሳሉ?›› ከሚል የቆየ ስሜት በመነሳት ጭምር ነው፡፡ ውስጣዊና ውጫዊ ግጭታችንን አስወግደን፣ ከዚያም በራሳችን ተማምነን መሥራት ስንጀምር ግን ዓለምን አስደመምን፡፡ ወደፊትም ብድር የነፈጉን ወዳጆቻችን አቅማችንን ሲያዩ አመለካከታቸውን ይቀይሩ ይሆናል፡፡ ያም ባይሆን እኛም አቅም አጥተን መቅደላ ላይ ተገትሮ እንደቀረው የቴዎድሮስ መድፍ ተጀምሮ ቢቀር እንኳን ለመጭው ትውልድ የፍላጎታችን፣ የቁጭታችን፣ የኅብረታችን፣ የሰላማችን፣ የአብሮነትሰን ሰንደቃችንና የፍቅራችን ጅምር ምልክት ሆኖ ይኖራል፡፡ ከጨረስነው ደግሞ ታሪካችንን በማደሳችን የምንኮራ ዜጎች እንሆናለን፡፡ ሌላው ሐውልታችን በቤንሻንጉል ጉምዝ ይቆማል፡፡ ባለፉት አሥር ዓመታት ባገኘነው ሰላምና ባቋቋምነው ሐውልት ምክንያት ሰላማችንን፣ ፍቅራችንንና አንድነታችንን የበለጠ እናጠናክራለን፡፡ ሌሎች ተመሳሳይ ሐውልቶች በመላው ኢትዮጵያም ይሠራሉ፡፡ 

የዓባይ ግድብ ሰላም ባገኘን በጥቂት ዓመታት ውስጥ ዕውን ሊሆን ሌት ተቀን እየተገነባ ነው፡፡ የሰላም ዋጋ ብዙ ቢሆንም የሚያስገኘው ውጤትም ያን ያህል መሆኑን እያስረዳን ነው፡፡ ዳሩ ግን በጥልቅ መገንዘብ ያለብን ፍሬድሪክ ዳብሊዩ ክለርክ የተባሉ የደቡብ አፍሪካ መሪ «ሰላም ድህነትና የአስተዳደር በደል ባለበት አይመጣም፡፡ ማይምነት በሰፈነበት፣ ትምህርትና መረጃ በሌለበት ሊያብብ አይችልም፡፡ ጭቆና፣ ኢፍትሐዊ አሠራርና ብዝበዛ ከሰላም ጋር ጠላቶች ናቸው፡፡ ሰላም በምቀኝነትና ተግባራዊ ሊሆን በማይችል ነፃ ምኞት ሥጋት ላይ ሊወድቅ ይችላል፡፡ የዘር፣ የመደብ፣ የሃይማኖት አለመቻቻልና አሉታዊ አመለካከት የሰላም ሕያው ጠላቶች ናቸው፤» ይሉናል፡፡ በእርግጥም የተለያዩ ታላላቅ ሰዎች ሰላምን ለመተርጎም ጥረት አድርገዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ቻይናዊው የሃይማኖት አባት 14ኛው ዳላይ ላማ «ሰላም የሚሰፍነው የሰብዓዊ መብት በተከበረበት፣ ሕዝቦች በሚመገቡበት፣ ግለሰቦችና አገሮች ነፃ በሆኑበት ሥፍራ ነው፤» ሲሉ ያስገነዝባሉ፡፡ እኚህ ታላቅ የሃይማኖት አባት «ዛሬ ከፊት ለፊታችን የተደቀኑት ኹከት የተሞላባቸው ግጭቶች፣ ተፈጥሮ የሰጠችንን ፀጋ ማውደም፣ ድህነት፣ ረሃብ፣ ወዘተ ሰው ሠራሽ ችግሮች ሲሆኑ ወንድማማችነትን ስናዳብርና የግንዛቤ አድማሳችን ሲሰፋ በሰው ልጅ ጥረት የሚወገዱ ናቸው፤» ሲሉ ያስገነዝባሉ፡፡ በእነዚህ ሰዎች አንደበት እንደተገለጠው ለሰው ልጅ ሰላም በእጅጉ አስፈላጊ ሲሆን፣ ስለሰላም አስፈላጊነት በልዩ ልዩ መንገዶች መግለጽ የሚያስፈልገውም ቀደም ሲል እንደተገለጸው ግጭት በመኖሩ ነው፡፡ 

ዓመታት አልፈው ዓመታት ተተክተዋል፡፡ ባለፉት አሥር ዓመታት በኢትዮጵያ የታየው ለውጥ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ይህውጤት ለማየት የቻልነው በአራችን ሰላም በመኖሩ ነው፡፡ ከዚህ ላይ በጎረቤቶቻችን ሰላም፣ ፍቅርና አብሮነት ሲሰፍን የኢትዮጵያ ሥልጣኔ የበለጠ ይጎላል፡፡ ችግሮቻችን በእብሪት ሳይሆን በሠለጠነ መንገድ፣ በራስ ወዳድነት ስሜት ሳይሆን በመተሳሰብ፣ በጥገኝነት ስሜት ሳይሆን በራስ የመተማመን ስሜት ለመፍታት ስንችል እንከበራለን፣ እንወደዳለን፡፡ ከዚህ ላይ ውጭ የሚገኙ ወገኖቻችን የፈለገ ዓይነት በደል በግል ወይም በቡድን ቢደርስባቸው ያን ወደ ጎን በማቆየት አገራቸውን መርዳት ቢችሉ ምድረ ገነት ሊያደርጓት ይችላሉ፡፡ ውርደት ሊበቃን ይገባል፡፡ የራሳችን ጌቶች መሆን ሊናፍቀን ይገባል፡፡ መንግሥትም አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ለሕዝባዊ ጥያቄዎች መልስ መስጠት፣ የዴሞክራሲ መድረኩን ማስፋትና አሳታፊ ማድረግ፣ የተለያየ አመለካከትና እምነት ያለውን ሕዝብ የበለጠ ማስተባበር፣ አልፎ አልፎ ለሚከሰቱ ችግሮች የበለጠ ሆደ ሰፊ ሆኖ ለማስወገድ መጣር፣ የሰላም አድማሱን እያሰፋ፣ ልማቱን ለማደናቀፍ ሌት ተቀን እረፍት አጥለው የሚሠሩትን በጥብቅ መከታተልና መከላከል አለበት፡፡ ከአንድ ክልል ወደ ሌላው የሚወስደውን የመዝጋት ብልግና ሊገታ ይገባል፡፡ መንገድ የሚዘጉ ኃይሎች መዝጋታቸውን ብቻ ሳይሆን፣ መዝጋቱ የሚያስከትለውን መዘዝ በሚገባቸው መንገድ ማስረዳት ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ማንም ዴሞክራሲያዊ መንግሥትም ቢሆን በዝምታ ሊያልፈው እንደማይችል ማስታወቅ ይገባል፡፡ ዛሬ ‹‹ማን ገዥ? ማን ተገዥ ሊሆን ነው?›› የሚለው የዘረኝነት መርዝ የተረጨው የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ በአንድ ወይም በሌላ በሚነሳ የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት በመጎዳቱ፣ ጉዳቱም በመሸፋፈኑ፣ ይፋ ወጥቶ ሕክምና እንዳይደረግበት የታፈነ በመሆኑ ስለሆነ ብሔራዊ ዕርቅ ብቻ ሳይሆን የታሪክ ዕርቅ ተግባራዊ እንዲሆንም መሠራት እንዳለበት ጸሐፊው አጥብቆ ያምናል፡፡  

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...