Tuesday, March 5, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የሚኳትኑትን መንገድ ይቁጠራቸው!

እነሆ ጉዞ! ከጀሞ ወደ ሜክሲኮ ልንጓዝ ነው። ይኼኛው መንገድ ከትናንትናው በአባት አይገናኝ እንጂ በእናት አንድ ነው። ድልድያቸው ሕይወት ትባላለች። እያንዳንዳችን በኑሮ ውጣ ውረድ ትርፍና ኪሳራ ሆነን ስንጨመቅ የምንንጠባጠብበት ነው። የምንወራረድበት ነው። ‹እዚህ ነበሩ› የምንባልበት ነው፡፡ በዚህ ታይተዋል ተብለን የምንታወስበት ነው። እሸቱን የህልውናችንን ፍሬ በዓይን የማናያቸው አማልክቶች በሥልት የሚፈለፍሉበት ነው ጎዳናው። ‘ተፈልፍለህ ስታበቃ እንደ ቆሮቆንዳ ትወረወራለህ’ ነው የአረማመዱ አጨራረስ ቄንጥ። ‘እቱ! ተፈልፍለሽ ነገር ዓለምሽ ሲያከትም ሞት አውቀን ወደ ማናውቀው ዘለዓለም የሚባል ጊዜ በእግሩ እያንከባለለ የሚነዳሽ ነሽ’ ይሏል ተረኩ፡፡ ሳናስበው ወይም አስበነው ብቅ እያለ አዕምሯችን ውስጥ የሚመላለስ ሚስጥራዊ አፈጣጠር ሰምቶ እንዳልሰማ፣ አስበነው ግን ቦታ እንዳልሰጠነው ሁሉ ማውጠንጠን ይከብደንና ቆም ስንል ታክሲያችን መጥታ ቦታ የመያዝ ሽሚያ ይተካል። የመኖር ጉጉት ጡት እንደሚጠባ ጥጃ እያባበለ በኑሮ ትግል አዙሪት ውስጥ ይከተናል።

ዝንጥ ያሉና የደስ ደስ ያላቸው አዛውንት የጋቢናውን በር ይከፍታሉ። “እስኪ ና ወዲህ! ዓይንህን ልየው? እናቴ ዘንድሮ የአውሮፕላንና የታክሲን መሪ የሚጭብጥ አላምንም። መንበሩን የጨበጡትን ረስተህ ማለቴ ነው! እነ ትራምፕን ማለቴ ነው ደግሞ ሌላ ነገር እንዳታመጣብኝ. . .” እያሉ በቀልድ ይቆጣሉ። የምር መስሎት ሾፌሩ ዓይኑን ሊያስመረምር ከአንገቱ ያሠጋል። “ወይድ! የዓይን ሐኪም አደረገኝ እንዴ ይኼ?” ፌስታል ይዛ የምትከተላቸው ኮረዳ ትስቃለች። “እኔ መቼ ይኼን ብሌንህን አልኩህ? ሰው ዓይኑ ያለው ልቡ ላይ ነው። የሳይንስ ልጅ ከሆንክ ደግሞ አዕምሮ በለው። ያው ነው፡፡ የስም ለውጥ ነው። ከስም ለውጥ፣ ከአውቆ አበድ፣ ከአታላይ ቀስቃሽና አተራማሽ አገራችንን ይጠብቃት! ስምንተኛው ሺሕ መቼስ ከዲሲ አዲስ አበባ የማያሳየንና የማያሰማን የለም?” እያሉ እጆቻቸውን ወደ ሰማይ ዘረጉ። በቆሙበት አቡነ ዘሰማያት ደገሙ። “የዚህን ሾፌር ልብ አንተ ምራ። የውስጡን ቁጭት በእኛ እንዳይወጣ፡፡ እንደ ትራምፕ ሠፈር መርጦ አልጭንም እንዳይል መጫኛውን አላላለት። በቀረው ደግሞ ዛሬ ከሞት ጋር ቀጠሮ ቢኖረው ሐበሻ ነውና አስረፍደው። ሰው መቼም ሙት ብሎ ተብሎ ተቀጥሮ ሞት አይቀርለትም። መዘግየት ነው ጥበብ፣ ማምለጥ አይቻል፤” ብለው ሲያበቁ ተሳፈሩ። አፍታ ሳይቆይ ታክሲያችንም ሞላች። የጀመረውን እንደሚጨርስ ስንቱ ይሆን እርግጠኛ?

ደንባራው ወያላችን ሒሳብ መሰብሰብ ጀምሯል። መጨረሻ ወንበር ጨዋታው ደርቷል። የአገር ባህል ቀሚስ የለበሱት ወይዘሮ ስለቀሚሳቸው ይተርካሉ። “የዛሬን አያርገውና ልጄ አሜሪካ አገር ሊሄድ ሲል ያሰፋሁት ነው። አያምርም?” ይጠይቃሉ። አጠገባቸው የተቀመጠችዋ ወጣት ትመልሳለች፣ “በጣም!” ስትላቸው፣ “አዎ እንዲህ ነው። ሰው በአንድም በሌላም ድንበር ይሻገራል። እሱ አይደለም ጥበቡ። ጥበቡ አሸኛኘቱ ነው። ዛሬ የዶሮ አንገት የሚቀላልኝ ሰው አጥቼ በቴሌቪዥን መስኮት የሰው አንገት ሲቀላ እያየሁ ካች ዓምና ፋሲካን አከበርኩ። አሁን ደግሞ ሁዳዴ ሳይገባ ይኼ ነገረኛ ሰውዬ (ትራምፕን ማለታቸው ነው) ሕዝበ አዳምን በፍየልና በበግ ከፍሎ አንተ ውጣ አንተ ግባ የሚል ነገር አመጣ አሉ። ይህንን ጭካኔ ሰምቼ እግዚኦ አልኩ። አምላክ ይኼን ከምታሳየኝ ለምን አትገለኝም አልኩ።

‹‹ይኼው ይባስ ሊያሳየኝ ሰው በቁም የሚገል አመራር ሲመጣ ሳያስለኝ፣ ሳይቆርጠኝና ሳይፈልጠኝ በጤና አውሎ ያሳድረኛል። ዘንድሮስ እንጃ ዕድሜ እየገፋም ይኼን ያህል ሲታዘቡ መኖር አለ፣ አየሽ? ለነገሩ ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥት በመንግሥት የሚለው ቃሉ ይፈጸም ዘንድ ግድ ነው። ታዲያ የእኛስ ይሁን እንዲያው ዓለም ሳያልፍላት ነው በቃ የምታልፈው?” ይጠይቃሉ አጽንኦት ሰጥተው። “እንግዲህ ምን ይደረግ መንገዶች ሁሉ ወደ ሽብር ይወስዳሉ ሆነ፤” ጥጉን የያዘው ወጣት ጣልቃ ይገባል። ድንገት ደግሞ ጎልማሳው ከጣራ በላይ ደጋግሞ ያስነጥሳል። “ይማርህ!” ተሳፋሪው ያጉረመርማል። ጎልማሳው ይመልሳል፣ “በነፍስ የሚምረን መቼ አጣን? በቁም የሚቀብረንን የሚያስጥለን አጣን እንጂ፤” ይመልሳል። አንዳንዱ ፈገግ ይላል። “ታዲያ ባስነጠስን ቁጥር ግብር ይቀነስልን ልንል ነው? እሱ ነበር የቀረን። እንዴት ነው ነገሩ ዘመኑ እኮ የልማት ነው፤” የምትለኝ ደግሞ አጠገቤ የተቀመጠችው ተሳፋሪ ነች፡፡ ሰው ከትራምፕ ራስ እስከ አገሩ ጉዳይ የልቡን ይለዋል። ወይ ግሎባላይዜሽን!

መጨረሻ ወንበር ከተቀመጡት አንዱ፣ “ኧረ ፊኛዬ ሊፈነዳ ነው። ሾፌር አንዴ አቁመው እስኪ?” አለ ያለምንም ኃፍረት። አጠገቡ የተቀመጠች ዓይነ አፋር፣ “እንዴ ሼም የለም ዘንድሮ?” አለች አምልጧት። “በተፈጥሮ ሕግ የምን ሼም ነው? ሼም ካልሽ ራሳቸውን ያወጡትን ሕግ መልሰው ራሳቸው የሚጥሱትን የሰው ልጆች ሼም አትይም?” ብሎ ከተቆጣ በኋላ፣ “አቁመዋ. . .” አለ ከመቀመጫው እየተነሳ። ወያላው ብሽቅ ብሎ ከኪሱ መጻፊያ አወጣና በነጭ መደብ የተጻፈ ሃይማኖታዊ ጥቅስ ሥር በችኮላ ‘ታክሲያችን ተንቀሳቃሽ መፀዳጃ አይደለም’ ብሎ ጻፈ። አዛውንቱ ቀበል አድርገው፣ “እንዴት ያለ ጉድ ነው? ቢቆምስ መንገድ ላይ ልትለቀው ነው? ነውር አይደለም?” ሲሉት፣ “መንገድ እንደ ፍራሽ ድንጋይ እንደ ትራስ ተደግፎ መተኛት ነው አሳፋሪው? መንገድ ላይ መተንፈስ?” አላቸው።

“ኧረ እንደማመጥ?” ይላል ጎልማሳው። በየት በኩል እንደማመጣለን? ሐሳባችንና ቋንቋችን እንደየፊናችን ተበታትኖ መግባባት አቅቶን አታይም? አንዱ ሲያለማ አንዱ ሲያፈርስ ሰበብ አያጣም። አንዱ ሲቆፍር ሌላው ሲምስ ይሉኝታ የለም፤” ባዩዋ ወይዘሮዋ ናቸው። በዚህ ሁሉ መሀል ሾፈራችን ታክሲያችን ክንፍ አስበቅሎ ያከንፋታል። ከአንዱ መንገድ ጥግ ስንደርስ ጥግ አስይዞ፣ “ፈረስ ያደርሳል እንጂ አይዋጋም ይሉሃል ይኼ ነው። አሁን ከፈለጋችሁ ወርዳችሁ መደባደብ ትችላላችሁ፤” አለን። ደግሞ ሾፌሩ ላይ ሌላ ሂስና ወቀሳ ተነሳ። በዚህ መሀል መጨረሻ ወንበር ተቀምጦ የነበረው በጥባጭ ሾልኮ ወርዶ በላሜራ የታጠረ ታዳጊ ችግኝ ላይ ከመብሉና ውኃው የተጣራውን ማርከፍከፍ ጀመረ፡፡

ወደ መወዳረሻችን ተቃርበናል። ድምፁን አጥፍቶ የቆየው ወያላ ከሾፌሩ ጋር በኮድ ማውራት ጀምሯል። ጥቂት እንደተጓዝን “እውነት ይመስልሃል? ቆይ እሺ ወደ እኛ የሚመጡ ይመስልሃል?” አለው። የግል ጉዳይ መስሎን ጣልቃ አልገባንም። “ቢመጡስ? ምን እንዳያደርጉ? አገሬ እንደሆነ እንኳን ለእነሱ ለፋሺስትም አልተንበረከከችም፤” ሲል ግን ጉዳዩ እንደሚያገባን ገባን። “ማን ናቸው እነሱ?” ይላል አንዱ በርግጎ። “ምንድነው? ማንን ነው?” ብትል ደግሞ ወይዘሮዋ ጎልማሳው ሲጫወትባት፣ “ተወረናል ነው የሚሉት። በማን እንደሆነ እንጃ?” ብሎ የምር ያስመስለዋል። የአንዳንዱ ሰው ቀልድና የአንዳንዱ አሽከርካሪ አነዳድ በየመንገዱ በድንጋጤና በሞት እንደጨረሰን ‘ኤችአይቪ’ እንኳ አልተሳካለትም። አይገርምም?! ይኼን ጊዜ ነበር አዛውንቱ ነገሩ አልጥማቸው ብሎ “ስለማን ነው የምታወራው?” ብለው ወያላውን ጨርቁን የጎተቱት። ወያላው ሁላችንንም እየቃኘ፣ ‹‹ስለትራምፕ ነዋ። ሰውዬው ገና ዓለምን ጉድ የሚያሰኝ የማነካካት ሥራ ሳይሠሩ እንዲሁ በዋዛ የሚሸኙ አይመስሉም። በነገራችን ላይ ትራምፕ የዩፎ ዘር አለባቸው እየተባለ ነው ካላመናችሁኝ፤›› ብሎ ሞባዩሉን መጎርጎር ጀመረ። ይኼኔ ጥጋችንን ይዘናል።

አዛውንቱ በግለሰብ ካሜራ የተቀረፀ ነው የተባለውን እውነተኝነቱ የማያጠራጥር ያልታወቁ በራሪ አካላትን በጥራት ሲቀርፅ የሚያሳይ ‘ቪዲዮ’ በጥሞና ዓይተው እንዳበቁ እየሳቁ፣ “እኔ እኮ በጣም የሚገርመኝ ስለእነዚህ ያልታወቁ በራሪ አካላት ለመስማት ጆሮችንና ልባችን የሚቆመውን ያህል፣ አጠገባችን ስለረሳናቸውና ዕውቅና ስለነፈግናቸው የሰው ልጆች ቅንጣት የማይሰማን ለምንድነው? ደግሞ ዛሬ እኚህ መከረኛ ሰውዬ የወሬ ርዕስ ሆኑ ተብሎ ሌላ ትንግርት ተፈጠረ። በእኛው ስግብግብነት፣ ምቀኝነት፣ ሐሜት፣ አሻጥር፣ ተንኮልና ሙስና ስንቱ ከሰውነት  በታች ወርዶ ዓይተን እንዳላየን እያለፍን እንዲህ ያለውን ምናቸውም የማይገባ የፈጠራ ልቦለዶች ለማየት ‘ኔትወርክ’ ስናጣብብ አናፍርም? ተው ተው እናንተ ልጆች ቴክኖሎጂን ተገን አድርጋችሁ ሰውን ያለስሙ ስም ያለ ግብሩ ግብር መስጠት ተው ተው. . .” ሲሉ ታክሲዋ ቆመች፡፡ ወያላው “መጨረሻ!” ማለት። “ባትልም ነው!” ብለው አዛውንቱ በንዴት ቀድመው ውርድ። ሐሜቱ፣ ሽሙጡ፣ ወሬውና አግቦው በዝቶ እውነት የሚያንገዋልል ወንፊት ፍለጋ የሚኳትኑትን መንገድ ይቁጠራቸው እንጂ ሌላ ምን ይባላል? መልካም ጉዞ!   

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት