Monday, March 4, 2024

የኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች ስብሰባና የሚጠበቁ ውሳኔዎች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ኢትዮጵያ አንድ መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ያላት አገር እንደሆነች መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በቆዳ ስፋትም ሆነ በሕዝብ ብዛት በግንባር ቀደምትነት ከሚጠሩ የአፍሪካ አገሮች መካከል አንዷ ነች፡፡ የአገሪቱ የሕዝብ ቁጥር ባለፉት 50 ዓመታት በእጥፍ እንዳደገ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የአገሪቱ የሕዝብ ቁጥር እያደገ ከመምጣቱ ጋር በተያያዘ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሲስፋፉና ሲገነቡ ይታያል፡፡ በዚህም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓመት በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ወጣቶች ከከፍተኛ ትምህርት እንደሚመረቁ ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡ መንግሥት በየዓመቱ በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎችን እያስመረቀ ቢገኝም፣ ተመርቀው በግላቸውም ሆነ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ተቀጥረው ወደ ሥራ የሚገቡ ወጣቶች ቁጥር እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ አገሪቱም ካላት የሕዝብ ቁጥር ጋር የሚመጣጠን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበች እንዳልሆነ ይነገራል፡፡

 በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር (ኢሕአዴግ) አገሪቱን መምራት ከጀመረ ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ አስቆጥሯል፡፡ ኢሕአዴግ በሥልጣን ዘመኑ የሠራቸው በርካታ ሥራዎች እንዳሉም ይታወቃል፡፡ ለአብነት ያህልም የህዳሴ ግድቡ ግንባታ፣ የባቡር ትራንስፖርት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግንባታ፣ በጤና ዘርፍ፣ በቤቶችና በመንገዶች ግንባታ በርካታ ሥራዎችን እንዳከናወነና በዚህም እመርታ እንዳሳየ የሚናገሩ ወገኖች አሉ፡፡

የእነዚህ ሥራዎች ጅምር አበረታች ቢሆንም፣ የአገሪቱ ሕዝብ በተለይም ወጣቱን ተጠቃሚ ከማድረግ አኳያ እየተሠራ ያለው ሥራ ዝቅተኛ መሆኑ በተደጋጋሚ ተገልጿል፡፡  

ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ ከመልካም አስተዳደር፣ ከፍትሕ፣ ከዴሞክራሲ መጎልበትና የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ ከማድረግ አኳያ ብዙ ክፍተቶች እንዳለበት ይገለጻል፡፡ ለዚህም አገሪቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት የቆየችበት የፖለቲካ ቀውስ በማሳያነት ይጠቀሳል፡፡

ኢትዮጵያ በተለይም ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ ቀውሶች ተተብትባ እንደምትገኝ፣ ከዚህ ጋር በተያያዘም ወጣቶች በሚያነሱት ጥያቄ መሠረተ ልማቶች ሲወድሙ የሰው ሕይወት የጠፋ መሆኑም ይታወቃል፡፡ የዜጎች ሕይወት ከመጥፋቱ ባሻገርም ከመኖሪያ ቀዬአቸው እየተፈናቀሉ በመጠለያ ካምፕ ውስጥ እንዲኖሩና በዕርዳታ እንዲተዳደሩ መገደዳቸውም እንዲሁ፡፡

 የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማኅበራዊ ችግሮችን ለመፍታትም ኢሕአዴግ ከላይ ታች ሲል ይስተዋላል፡፡ ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣ ወዲህ በአገሪቱ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ደረጃ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የእርስ በርስ ግጭት ተቀስቅሶ  የሰው ሕይወት እንደጠፋና ንብረት እንደወደመ ይታወቃል፡፡ በተለይም በኦሮሚያና በሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት በርካቶች ሕይወታቸውን ከማጣታቸውም በላይ፣  በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፡፡

ባለፉት ወራት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ በተማሪዎች መካከል ተቀስቅሶ በነበረው ግጭትም የአራት ተማሪዎች ሕይወት እንደጠፋ ትምህርት ሚኒስትር ገልጿል፡፡ በርካቶች ግጭቱን በመፍራትም ትምህርታቸውን አቋርጠው እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ወጣቶች ተቃውሞችን ሲያነሱ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በዚህም የዜጎች ሕይወት ጠፍቷል፣ ንብረት ወድሟል፡፡ እነዚህንና ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለ17 ቀናት በዝግ ሲመክር እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በስብሰባው ማጠቃለያ ላይ ባወጣው መግለጫውም፣ በአገሪቱ እየተከሰተ ያለው ችግር በድርጅቱ የአመራር ቁርጠኝነት ማነስ እንደሆነ ገልጾ፣ በዚህም በይፋ የአገሪቱን ሕዝብ ይቅርታ ጠይቋል፡፡ በየአካባቢው እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮችን ለመፍታትም ከግንባሩ አባል ድርጅቶች ጋር ስምምነት መድረሱን መግለጹ የሚታወስ ነው፡፡

የኢሕአዴግ ግንባር ድርጀቶች ሊቃነ መናብርት በሰጡት መግለጫም፣ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የደረሰበትን አጠቃላይ ውሳኔ ወደ ግንባሩ ድርጅቶች የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በማውረድና ከአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማዛመድ ተመሳሳይ ስብሰባ እንዲካሄድ አቅጣጫ እንዳስቀመጠ፣ በዚህ መሠረትም የኢሕአዴግ አራቱም ብሔራዊ ድርጅቶች ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ስብሰባ ላይ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የሕዝባዊ ወያኔ ኃርነት ትግራይ  (ሕወሓት) ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባውን ከቀናት በፊት አካሂዷል፡፡

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የ17 ቀናት ዝግ ስብሰባ ከመካሄዱ በፊት፣ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ለ35 ቀናት ስብሰባ አድርጎ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ሕወሓት ለ35 ቀናት አድርጎት በነበረው ስብሰባ የድርጅቱ ስትራቴጂካዊ አመራር ክልላዊና አገራዊ ተልዕኮውን ከመወጣት አንፃር ያለበትን ቁመና እንደገመገመ መዘገቡ አይዘነጋም፡፡ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ያደረገውን ዝግ ስብሰባ ሲያጠናቅቅ ኅዳር 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ስትራቴጂካዊ አመራሩ እየተዳከመ ተልዕኮውን ለመወጣት የሚያስችል ቁመናው፣ አመለካከቱና አደረጃጀቱ በየጊዜው እየተሸረሸረ እንደመጣ፣ ሕዝባዊነቱ እየቀነሰ በትንንሽ ድሎች የሚረካ፣ ለችግሮች መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ ራሱ አመራሩ የችግር ምንጭ እንደሆነ መገምገሙን መዘገቡ ይታወሳል፡፡ በዚህም የድርጅቱን ሊቀመንበር ከማንሳት በተጨማሪ የማዕከላዊ ኮሚቴ አመራሮችን ማሸጋሸጉም እንዲሁ፡፡

ከኢሕአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ የ17 ቀናት ስብሰባ በኋላም የሕወሓት ማዕከላዊ  ኮሚቴ ከጥር 24 እስከ ጥር 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሦስት ቀናት ስብሰባ አካሂዷል፡፡

ማዕከላዊ ኮሚቴው ለሦስት ቀናት ባካሄደው ስብሰባ በድርጅቱ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ሒደት ላይ ውይይት ማድረጉን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የድርጅቱ ስትራቴጂካዊ አመራር የተሰጠውን ኃላፊነት በቁርጠኝነት እንዲሠራና የክልሉን ሕዝብ ሁለንተናዊ ችግሮች እንዲፈታ ስምምነት ላይ መድረሱን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ በስድስት የኮሚቴ አባላት ላይም የዕርምት ዕርምጃ መወሰዱንም ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል፡፡ በዚህም ወ/ሮ አረጋሽ በየነና አቶ ብርሃነ ኪዳነ ማርያም ከማዕከላዊ ኮሚቴው እንዲነሱና በሌሎች ማንነታቸው ባልታወቁ አራት አመራሮች ላይ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፡፡

የድርጅቱ ስትራቴጂካዊ አመራር ባካሄደው ግምገማ፣ የሕወሓት ከፍተኛ አመራር በየዞኑ ውይይት ማካሄዱን እንደገመገመና ከላይ እስከ ታች ያለው አመራር የክልሉን ሕዝብ ጥያቄዎች ለመፍታት ስምምነት ላይ እንደደረሰ ታውቋል፡፡ መድረኮቹ የክልሉንና የአገሪቱን ወቅታዊ ጥያቄዎች በአስተማማኝ መንገድ መልስ እንዲያገኙና የድርጅቱ ሕዝባዊ ወገንተኝነት ለማረጋገጥ በሚያስችሉ አቅጣጫዎች ስብሰባው መካሄዱን የማዕከላዊ ኮሚቴው መግለጫ ጠቁሟል፡፡ ውይይቶቹ የማዕከላዊ ኮሚቴው ግምገማ በጥልቀት በሚያስቀጥልና የሕዝቡን ጥያቄ በተገቢው መንገድ ለመመለስ ምቹ ሁኔታ መፍጠር የሚያስችል መግባባት ላይ መድረሱ ተገልጿል፡፡ በሚቀጥሉት ጊዜያትም የድርጅቱ አመራሮች የሕዝቡን ችግር ለመፍታት በየደረጃው ያለው አመራር ተጠያቂነትን በማያረጋግጥ እንዲገመገም አቅጣጫ ማስቀመጡ ተጠቁሟል፡፡

ሌላው የኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጅት የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ  (ብአዴን) ሲሆን፣ ማዕከላዊ ኮሚቴው ስብሰባ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ከጥር 17 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በሁለት አጀንዳዎች፣ ማለትም የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለ17 ቀናት አካሂዶት በነበረው ዝግ ስብሰባ ላይ የመከረባቸው ጉዳዮችና የአምስት ዓመቱን የአካባቢ፣ የቀበሌና የወረዳ ምክር ቤት ምርጫ በተመለከተ ውይይት እያደረገ እንደሆነ መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፣  ጥር 12 ቀን 2010 ዓ.ም. በወልዲያ ከተማ በተቀሰቀሰው ግጭት ሳቢያ ስብሰባው ለቀናት ያህል ተቋርጦ ቆይቷል፡፡

ተቋርጦ የነበረው የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባም ቅዳሜ ጥር 27 ቀን 2010 ዓ.ም. መጀመሩን የድርጅቱ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዓለምነው መኮንን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ አቶ ዓለምነው እንደገለጹት፣ ተቋርጦ የነበረው ስብሰባ ሲቀጥል በዋናነት በወልዲያና በአካባቢው በተፈጠረው ችግር ላይ እንደሚመክርና አዳዲስ ውሳኔዎች ያሳልፋል፡፡

በወልዲያና በአካባቢው የተፈጠረውን ግጭት በተመለከተም የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ለክልሉ ሚዲያ በሰጡት መግለጫ፣ ለችግሩ ዋነኛ መንስዔ የክልሉ አመራር እንደሆነ ጠቁመው ነበር፡፡

አቶ ዓለምነው በበኩላቸው፣ በወልዲያና በአካባቢው የተፈጠረውን ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት አመራሩ ቁርጠኝነቱን የሚያሳይበት ግምገማ እንደሚካሄድ አረጋግጠዋል፡፡

በወልዲያ ከተማ ጥር 12 ቀን 2010 ዓ.ም. የዘገሊላ በዓልን በሚያከብሩ ወጣቶችና በፀጥታ ኃይሉ መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት የዜጎች ሕይወት መጥፋቱ ይታወሳል፡፡ በዕለቱ የተከሰተው ግጭት ወደ መርሳ፣ ቆቦና ሌሎች ከተሞች በመዛመት በአጠቃላይ የ15 ሰዎች ሕይወት እንደጠፋ የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት (ካቢኔ) ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል፡፡ የክልሉ ካቢኔ ጥር 25 ቀን 2010 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ግጭቱ እንዲከሰት ያደረጉ ኃይሎች ማንነት ከተጣራ በኋላ ሕጋዊ ዕርምጃ ይወሰድባቸዋል ብሏል፡፡

ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በአማራ ክልል በተለይም በጎንደር፣ በሰሜን ወሎ፣ በሰሜን ሸዋና በሌሎች ዞችኖችና አካባቢዎች በሚነሱ ሕዝባዊ ጥያቄዎች ሳቢያ በርካቶች ሕይወታቸው ጠፍቷል፣ ንብረታቸው ወድሟል፡፡

ሌላው የኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጅት የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ሲሆን፣ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በማዕከላዊ ኮሚቴ ደረጃ ስብሰባ እያካሄደ ነው፡፡ ማዕከላዊ ኮሚቴው እያደረገ ባለው ስብሰባ፣ በዋናነት የክልሉን ወጣቶች ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ትኩረት ሰጥቶ እየተዋወያየ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የክልሉ ሚዲያ የአማርኛው ክፍል እንደዘገበው፣ ማዕከላዊ ኮሚቴው ለኦሮሞ ሕዝብ አንድነት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየመከረ ነው፡፡

በክልሉ ያለውን የፖለቲካ ምኅዳር ለማስፋት ሲባልም በአገር ውስጥና በውጭ አገር ከሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ ለመሥራት የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ መወሰኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ማዕከላዊ ኮሚቴው እያደረገ ባለው ስብሰባም የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ነጋሶ ጊዳዳ (ዶ/ር)፣ ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱበት መኪና ለመግዛትና በአገር ውስጥና በውጭ አገር ሕክምና እንዲያገኙ ለማድረግ መወሰኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በኦሮሚያ ክልል ወጣቶች በሚያነሷቸው ጥያቄዎችና ሳቢያ እየተፈጠሩ ባሉ ግጭቶች የበርካቶች ሕይወት ከመጥፋቱ በላይ፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ንብረት መውደሙን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከወጣቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጥያቄና ፖለቲካዊ ችግሮች ሳቢያ ተደጋጋሚ የሆኑ ግጭቶች ሊከሰቱና የተቃውሞ ሠልፎች ሲካሄዱ ነበር፡፡

ከ2010 ዓ.ም. መግቢያ ጀምሮ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭትም ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ የክልሉ ዜጎች ሕይወታቸውን ከማጣታቸው በላይ፣ ከስድስት መቶ ሺሕ በላይ ዜጎች መፈናቀላቸው ይታወሳል፡፡ በሁለቱ ክልሎች መካከል የተከሰተው ግጭትና መፈናቀል ካለመቆሙ ጋር በተያያዘ፣ በክልሉ ያሉ ወጣቶች በተደጋጋሚ ጊዜ ጥያቄ ሲያነሱና ችግሩ እንዲፈታ ሲጠይቁ ነበር፡፡

የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባም እነዚህንና ሌሎች በክልሉ ወጣቶች የሚነሱ  ማለትም የመልካም አስተዳደር፣ የሙስናና ሌሎች ችግሮችና ጥያቄዎችን ለመፍታት የሚያስችል ውሳኔ ያስተላልፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

አራተኛ የኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጅት የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ሲሆን፣ የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ ከጥር 23 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ስብሰባ እያካሄደ መሆኑ ታውቋል፡፡ የማዕከላዊ ኮሚቴው ዋነኛ የመወያያ አጀንዳ ወቅታዊ በሆኑ በክልላዊና በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ያተረኮ እንደሆነ እየተገለጸ ነው፡፡ በስብሰባው መጨረሻም ማዕከላዊ ኮሚቴው ባለፉት ዓመታት የተደረጉ እንቅስቃሴዎችን በመገምገም የክልሉን ፖለቲካዊ፣ ኦኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች የሚፈታ ውሳኔ ያስተላልፋል ተብሎ እየተጠበቀ እንደሆነ ይጠበቃል፡፡

ለውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ መጥበብና ለአድርባይነት መስፈን ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን እንደሚያጣራም እየወጡ ያሉ ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡  

ብሔራዊ ድርጅት የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያስተላለፋቸው ውሳኔዎች፣ ከየክልሎቻቸው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማዛመድ ሁለንተናዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ውሳኔ ያስተላልፋሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡

ድርጅቶቹ በማዕከላዊ ኮሚቴ ደረጃ ስብሰባ እያደረጉ መሆኑ ቢታወቅም፣ አሁንም በየክልሎቻቸው የሚነሳውን የሕዝብ ጥያቄ ሊፈቱ ይችላሉ? ወይስ አይችሉም? የሚለው የብዙዎቹ ጥያቄ ሆኗል፡፡

ኦሕዴድ ያስተላለፋቸው ውሳኔዎች በዝርዝር እስካሁን ባይታወቁም፣ የቀድሞ የአገሪቱን ፕሬዚዳንት ነጋሶ ጊዳዳ (ዶ/ር) ድጋፍ ለማድረግ መወሰኑና ከአገር ውስጥም ሆነ ውጭ አገር ካሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ ለመሥራት ፍላጎት ማሳየቱ በብዙዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡

ከወራት በፊት የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ለ35 ቀናት አድርጎት በነበረው ስብሰባ የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ዓባይ ወልዱን አንስቶ በምትካቸው አቶ ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤልን መተካቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ሌሎች የኢሕአዴግ ግንባር ድርጀቶች ሰሞኑን እያደረጉት ባለው ስብሰባ ተመሳሳይ ውሳኔና ዕርምጃ ይወስዳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -