Monday, March 27, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የንግድ ምክር ቤት አባልነት በውዴታ ወይስ በግዴታ?

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 341/1995 ለማሻሻል ከተለያዩ አካላት የመነሻ ሐሳቦች ቀርበው እየተመከረባቸው ናቸው፡፡ ከ70 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያላቸው ንግድ ምክር ቤቶች በአዋጅ ቁጥር 314/1995 መሠረት እንደ አዲስ ሲደራጁ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት የሚል መጠሪያ ይዘው እንዲቋቋሙ ተደርጓል፡፡

ይሁንና በዚህ አዋጅ መሠረት ከተደራጁ በኋላ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ሲነሱ የነበሩ ጥያቄዎች ሲብላሉ ቆይተው አዋጁን ለማሻሻል ወደሚያስችሉ ተግባሮች እየገባ ነው፡፡ ለዚህ አንዱ ማሳያ አዋጁ እንዴት ሊሻሻል ይገባል? በምን ዓይነት መልክ ይሻሻል? የሚለውን ነጥብ በመያዝ፣ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላት በየራሳቸው ያስጠኑትን ጥናትና አዋጁን ለማሻሻል ያግዛል ብለው ያመኑባቸውን መነሻ ሐሳቦች እያቀረቡ ናቸው፡፡ ከዚህም በኋላ ቢሆን ተጨማሪ ሐሳቦችን ለማቅረብ የሚያስችል ዕድል ተሰጥቶ አዋጁን ለማሻሻል ተፍ ተፍ እየተባለ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች አደረጃጀት ጋር በቀጥታ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የኢንዱስትሪና ንግድ ሚኒስትሮች ዋነኛ ተጠቃሽ ሲሆኑ፣ አዋጁን ለማሻሻል ይረዳል ያሉትን ሐሳብ በጥናት አስደግፈው በማቅረብ ተጠቃሽ ሆነው ቀርበዋል፡፡ በተለይ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ለአዋጁ መሻሻል ጠቃሚ ናቸው ያላቸውን በርካታ መንደርደሪያ ሐሳቦች ያካተተበት ሰነድ አሁን ሥራ ላይ ያለው አዋጅ አለበት ያላቸውን ክፍተቶች በዝርዝር በመለየት ለውይይት በሚያመች መልክ አቅርቧል፡፡ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አዋጁ መሻሻል እንደሚኖርበት ካስቀመጣቸው ዝርዝር የማሻሻያ ሐሳቦች መረዳት የሚቻለው፣ ከ12 ዓመታት በፊት ንግድና ዘርፍ በሚል የንግድና የዘርፍ ምክር ቤቶቹ ቢለያዩ ዘርፉ ወይም አምራች ማኅበሩ ራሱን ችሎ መውጣት አለበት የሚለው አንዱ ነው፡፡ ነገር ግን በሚሻሻለው አዋጅ ውስጥ መሠረታዊ ለውጥ ለመምጣት ከተፈለገ የንግድ ምክር ቤቶች  አባላትን የሚመለከተው ነጥብ ሌላው እንደሆነ ታውቋል፡፡ አባልነት እንዴት ይሁን የሚለው ጉዳይ ዋነኛ አጀንዳ ሊሆን እንደሚገባም አንዳንድ የንግድ ምክር ቤት አባላት የሚጠቁሙ ሲሆን፣ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የንግድ ምክር ቤቶች ገቢ ምን ይሁን የሚለውም ጉዳይ ሌላው መነጋገሪያ ነው፡፡

በአዋጅ ቁጥር 341/95 የተቀመጠው አባልነት በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ መሆን እንደሚኖርበት የሚጠቁም ነው፡፡

ከሰሞኑ አዋጁን ለማሻሻል የቀረበው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የማሻሻያ ሐሳብ ሰነድ ውስጥ ይኸው አባልነት በግዴታ ይሁን በውዴታ የሚለው ነጥብ ሊመከርበት የሚገባ ጉዳይ ስለመሆኑ ያሳያል፡፡ አዋጁ ሲሻሻል ይህ ጉዳይ መታሰብ እንደሚኖርበት የሚጠቁመው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሰነድ፣ ጉዳዩ በሚገባ ሊታሰብበት የሚገባ መሆኑን የሚያመላክት ዝርዝር ማብራሪያም አስቀምጧል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የቀድሞ ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን አፈወርቅም፣ የንግድ ምክር ቤቶች አባላት ጉዳይና የገቢ ምንጫቸው ምን ይሁን የሚለው ነገር በደንብ ተመክሮበት ውሳኔ ላይ ሊደረስበት ይገባል ይላሉ፡፡

የሚሻሻለው አዋጅ የአባልነት ጉዳይ ትኩረት የሚያሻው በተቋማቱ ዙሪያ ያሉ ችግሮችን ሊፈታ የሚችል ከመሆኑም በላይ፣ ጠንካራ ሆነው እንዲወጡ ከተፈለገ በማሻሻያ አዋጁ ሊተኮርባቸው ከሚገቡ ጉዳዮች አንዱ መሆን አለበትም ብለዋል፡፡

አሁን ባለው አዋጅ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶችን አባልነት በተመለከተ የተቀመጠው ሐሳብ፣ የከተማ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አባልነት በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ሆኖ የተቀረፀ ነው፡፡ በሌላ በኩል ግን የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አባልነት፣ የክልል ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች አባልነትና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች አባልነት ግዴታ ስለመሆን አለመሆኑ አዋጁ የጠቀሰው ነገር አለመኖሩን ነው፡፡ ሆኖም የአገሪቱ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 31 መሠረት መደራጀት መብት እንጂ ግዴታ ባለመሆኑ በተጠቀሱት የአዋጁ ክፍሎች የምክር ቤት አባልነት በፈቃደኝነት ስለመሆን ስላለመሆኑ ባይገለጽም፣ አባልነት በፈቃደኛነት ላይ የተመሠረተ ነው ለማለት እንደሚቻል ይኸው ሰነድ ይገልጻል፡፡ ይህም ሆኖ ግን በመርህ ደረጃ የምክር ቤት አባልነት በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ መሆኑ በግልጽ ማመልከት ይገባው ነበር የሚል ሐሳብ በመሰንዘር፣ አዋጁ በአባልነት ጉዳይ ክፍተት ያለበት መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነም ያመላክታል፡፡

እንደ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ የአባልነት ዓይነቶች ሦስት እንደሆኑ በመጥቀስ አንደኛ ግለሰቦች ለማኅበራት አባልነት፣ ሁለተኛ ማኅበራት ለምክር ቤቶች አባልነትና ሦስተኛ ምክር ቤቶች ለምክር ቤቶች አባልነት ናቸው ይላል፡፡ ከዚህ አንፃር የሚነሳው ጉዳይ በንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ግለሰብ ነጋዴዎች አባል መሆን ሲችሉ በዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ግን አባላት የሚሆኑት ማኅበራት እንጂ ግለሰቦች አይደሉም፡፡ ይህ ነጥብ ለማሻሻያው የሚኖረው አግባብነት ሊታይ እንደሚገባው ጠቁሞ፣ አባልነት በግዴታ ይሁን ማለት የአገሪቱ የበላይ ሕግን ይጥሳል ይላል፡፡ በሌላ በኩል ግን አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ እንደሚያሳየው ከሆነ፣ አባልነት በፈቃደኝነት ላይ መሆኑ ማኅበራቱና ምክር ቤቶቻቸው በብዙ መልኩ ደካማ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል የሚለውን እምነት በዚሁ ሰነድ ላይ አስፍሯል፡፡ እንደውም አባልነት ‹‹በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ሆኖ በዚሁ ከቀጠለ ደግሞ የባሰውኑ እየተዳከሙ መሄዳቸው አይቀርም፤›› በማለት የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች የአባልነት ጉዳይ በመርህ ላይ በተመሠረተ በግዴታ ሊሆን ይገባል ወደሚለው አመለካከት ያጋደለ ሐሳቡን ያቀርባል፡፡ አቶ ሰለሞንም ከዚህ ሐሳብ ጋር ይስማማሉ፡፡ በእርግጥም አባልነት በግዴታ የሚለው ነገር ሕገ መንግሥቱን ይጻረራል፡፡ ሆኖም በተዘዋዋሪ አባልነት በግዴታ ይሁን የሚለውን ጉዳይ ይደግፉታል፡፡ እንደ ጀርመን ያሉ አገሮች የንግድ ምክር ቤቶቻቸው አባላትን በግዴታ ያስቀምጣሉ፡፡ ይህ ማለት መንግሥት አንዳንድ አገልግሎቶች በንግድ ምክር ቤቶቹ በኩል እንዲሰጥ ተደርጎ ምክር ቤቶቹ የገቢ ምንጭ እንዲኖራቸው ለማስቻል ጭምር ይጠቀሙበታል፡፡ እንደ ጂቡቲ ያሉ አገሮች ደግሞ መንግሥታቸው ከወደብ ገቢው በዓመት 20 ሚሊዮን ዶላር ፈሰስ እንዲያደርግላቸው በማድረግ ንግድ ምክር ቤቶች እንዲጠናከሩ ያደርጋሉ፡፡ በ1970 በወጣው ሕግ መሠረት የንግድ ምክር ቤቶች አባላትን በተዘዋዋሪ አባል እንዲሆኑ ለምሳሌ የንግድ ፈቃዳቸውን ሲያድሱ የንግድ ምክር ቤቶችን ዕውቅና እንዲያገኙ ወይም አባል መሆናቸውና በትክክል የሚሠሩ ስለመሆናቸው ማረጋገጫ መስጠት አንዱ ነው፡፡ ይኼ በተዘዋዋሪ አባልነት በግድ መሆኑን የሚያሳይ በመሆኑ፣ አንድ ነጋዴ ከንግድ ምክር ቤቶች ዕውቅና ውጪ የንግድ ፈቃዱን እንዳያድስ የሚያደርግ ነው፡፡ ዕውቅና ሲሰጥ ደግሞ ገቢ ይገኛል ይላሉ፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሰነድ አባልነት በግዴታ ቢሆን ያለውን ጠቀሜታ ከፍ ለማድረግ የሌሎች አገሮችን ልምድ አስታውሷል፡፡ በመላው ዓለም ያሉ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች የአደረጃጀት ዓይነቶችን የኮንትኔንታል ሞዴል፣ አንግሎሳክሰን ሞዴልና ቅይጥ ሞዴል በሚል የሚከፈሉ ሲሆን፣ ከአባልነት ጋር በተያያዘ የኮንትኔንታል ሞዴል ዋና መለያ ባሕሪያት የግዴታ አባልነት እንዲኖር ማድረጉ ነው ይላል፡፡ ፈረንሳይ፣ ኦስትሪያ፣ ጣሊያን፣ ሆላንድና ስፔን የዚህ ሞዴል ተከታይ ከሆኑ አገሮች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ይህን ሞዴል ከአዋጁ የማሻሻያ ነጥቦች አንዱ አድርጎ መጠቀም አስፈላጊነት ትኩረት ተሰጥቶት ሊመከርበት ይገባል የሚል እምነት ተንፀባርቋል፡፡ ይህ ከታመነበት ደግሞ የግዴታ አባልነት በሕጉ በግልጽና በቀጥታ ከመደንገግ ይልቅ እንደ ፈቃድ ዕድሳት ያሉ ሥራዎች ተሠርተው በተዘዋዋሪ ወደ አባልነት የሚያስገቡ ዘዴዎችን በማሻሻያው ማካተቱ፣ ሕጋዊነቱ የጠበቀ እንዲሆን ያደርገዋል የሚል ሐሳብ ሰንዝሯል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የመንደርደርያ ሐሳብ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት አባልነት በግዴታ እንዲሆን መፈለጉን ያሳየው፣ ስለንግድ ምክር ቤቶች ያወጣው አዋጅ ቁጥር 148/1970 አባልነት ግዴታ እንዲሆን በግልጽ የተደነገገ መሆኑን በማስታወስ ጭምር ነው፡፡ ይኸው ሰነድ አመልክቶ ከዚህ ድንጋጌ ለማሻሻያው መወሰድ ያለበት የመንግሥት ሙሉ ድርሻ ወይም ከፊል ድርሻ ያላቸው የንግድ ወይም የአምራች ድርጅቶች በግዴታ አባል እንዲሆኑ በማሻሻያው የማካተት አስፈላጊነት ላይ ሊመከርበት እንደሚገባም አመላክቷል፡፡

አባልነት በግዴታ ይሁን ከተባለ ስለንግድ ምክር ቤቶች ከወጣው የቀድሞ አዋጅ ቁጥር 148/1970 ለአዲሱ ማሻሻያ ግብዓት ይሆናል ያለውን አንቀጽ አስታውሷል፡፡ ይህም በአስመጪነት፣ በላኪነትና በጅምላ ሻጭነት የተሰማራ ሁሉ፣ በተጨማሪም በምክር ቤቱ የካፒታላቸውን መጠን መሠረት በማድረግ ድርጅቶች አባል እንዲሆኑ ስለሚያስገድድ እነዚህን ድንጋጌዎች ለሚሻሻለው አዋጅ ግብዓት ሊሆን የሚችልበት ዕድል እንዳለም ጠቁሟል፡፡ ለምሳሌ ኃላፊነታቸው የተወሰነ የግል ማኅበራትና የአክሲዮን ማኅበራት የግዴታ አባል እንዲሆኑ በማሻሻያው ስለሚካተትበት አግባብ፣ ተቀባይነት ኖረው አልኖረው በጉዳዩ ላይ መነጋገር ለማሻሻያው የራሱ አስተዋጽኦ ሊኖረው እንደሚችልም አመልክቷል፡፡

አቶ ሰለሞን ደግሞ ንግድ ምክር ቤቶች የመንግሥትን ሥራ በውክልና ተቀብለው መሥራታቸው በርካታ ጠቀሜታ ይኖረዋል የሚለውን ጉዳይ ይስማሙበታል፡፡ በማሻሻያ አዋጁም መካከት አለበት ባይ ናቸው፡፡ በውክልና የሚሠሩ በርካታ ሥራዎች መኖራቸውን የጠቀሱት አቶ ሰለሞን፣ ለምሳሌ የመንግሥት የጨረታ ሰነዶች በንግድ ምክር ቤቶቹ በኩል ቢካሄድ የጨረታ ሰነድ ሽያጭ ገቢውን መውሰድ ይችላሉ ብለዋል፡፡ በመሆኑም አባልነት በተዘዋዋሪ አስገዳጅ ማድረግ ጎን ለጎን ንግድ ምክር ቤቶች ከመንግሥት  የውክልና ሥራዎች ከመውሰድ በላይ ንግድ ምክር ቤቶች የመንግሥት ድጋፍ ሰጪዎች መሆናቸውን በማመን የሚተገብረው ነው፡፡

ከግዴታ አባልነት ይልቅ በተዘዋዋሪ አባል እንዲሆኑ የሚያስችል ዘዴ መቀመጥ እንዳለበት የሚያመለክተው ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ እንደ አማራጭ የሚታዩ ሌሎች ዘዴዎች መኖራቸውንም አመልክቷል፡፡ ከነዚህም ዘዴዎች አንዱ አድርጎ የጠቀሰው መንግሥት በልማት ባንክ በኩል የሚሰጠው ብድር፣ የኤክስፖርት ማበረታቻና የመሳሰሉትን ሲሰጥ በንግዱ እንዲሁም በዘርፍ ማኅበራቱና በምክር ቤቶቻቸው በኩል የሚሰጥበት አግባብ መፍጠር ነው፡፡ እንዲህ ያለው አማራጭ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መቅረቡ መንግሥት ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች የውክልና ሥራ ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ ፍላጎት ያለ መሆኑን የሚጠቁም እንደሆነ የገለጹ አሉ፡፡ ይህም ጉዳይ ለማሻሻያው በሚደረግ ውይይት ላይ ሊመከርበት የሚገባ ነው የሚለው ሰነድ፣ የአባልነት ጉዳይ እንዲህ ባለው ሐሳብ ተጠናክሮ ሕግ ሆኖ ከወጣ ጠቀሜታው የጎላ ነው ይላል፡፡

አዋጅ ቁጥር 341/95 ለማሻሻል እንደመንደርደሪያ የቀረበው ሌላው ሐሳብ ከዚሁ ከአባልነት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በሰነዱ እንደሰፈረው በአዋጅ ቁጥር 341/95 የአባላት መዋጮና የንግድና ዘርፍ ማኅበራት መዋጮን በተመለከተ በተለያዩ አንቀጾች ውስጥ የሰፈሩት ናቸው፡፡ ሁሉም ምክር ቤቶች አባሎቻቸው መዋጮ እንዲያዋጡ የመወሰን ሥልጣን ሰጥቷቸዋል፡፡ ‹‹የመዋጮው መጠን ምን ያህል ነው? ለሚለው አዋጁ ምላሽ አላስቀመጠም፡፡ በማሻሻያው ላይ የመዋጮ መጠን ይህን ያህል ብሎ ማስቀመጥ አግባብነትም ሆነ አመቺነት አይኖረውም፤›› የሚለው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የማሻሻያ ሐሳብ፣ ነገር ግን የመዋጮ መጠን ለመወሰን የሚያስችሉ መሠረታዊ ነጥቦች በማሻሻያው መጠቀስ አለባቸው ይላል፡፡ አዋጅ ቁጥር 148/1970 አንቀጽ 25/2/ሀ እና ለ መሠረት አባላት የሚያዋጡት የመመዝገቢያና የዓመታዊ መዋጮ ዓይነት ሲሆን፣ መጠናቸው የሚወሰነው በአባሉ የካፒታል መጠን መሠረት እንደሆነም ያስታውሳል፡፡ ከካፒታል በተጨማሪ ዓመታዊ ትርፍ፣ የተሰበሰበ ዓመታዊ መዋጮ (ለማኅበራትና ለምክር ቤቶች) የመሳሰሉትን መሠረት አድርጎ መጠኑ ሊወሰን እንደሚገባ በአማራጭነት በመያዝ በማሻሻያው ሊካተት የሚችልበትን አግባብ ማየት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ የንግድ ምክር ቤቶች ገቢ እንደቀድሞ ካፒታልን መሠረት ያደረገና ከዓመታዊ ትርፍ ላይ የሚሰበሰብ እንዲሆን የሚለው ነጥብ ላይ ውይይት ይደረጋል፡፡ ነገር ግን በቀድሞው አዋጅ (1970) ከዚህ ቀደም በ1939 ዓ.ም. ስለነጋዴዎች ምክር ቤት መተዳደሪያ ደንብ ቁጥር 90/1939 አንቀጽ 16 የንግድ ፈቃድ ለማውጣት ለመንግሥት ገቢ ከሚደረገው ገንዘብ ውስጥ 25 በመቶ ለምክር ቤቱ ፈሰስ እንደሚደረግ ይደነግግል፡፡ ስለንግድ ምክር ቤቶች የወጣ ቁጥር 148/1970 አንቀጽ ደግሞ 25/1/መ፣ 2/ሠ መንግሥት ለምክር ቤቶቹ አስፈላጊ በሆነ ጊዜ የገቢ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡ አዋጅ ቁጥር 148/1970 ከደንብ ቁጥር 90/1939 ሲነጻጸር ፈሰስ የሚደረገው ከየትኛው ሒሳብ ነው? መጠኑስ? የሚለው ምላሽ አይሰጥም፡፡ የደንብ ቁጥር 90/1939 ግን ምላሽ እንደሚሰጥ ያሳያል፡፡ በአጠቃላይ ግን እነዚህ ነጥቦች በማሻሻያው አዋጅ ማካተቱ አስፈላጊ ነው ወይ? ከተካተቱስ መንግሥት እንዴት ፈሰስ ማድረግ አለበት? በዝርዝር ሊገለጽ አይገባም ወይ? የሚሉት ነጥቦች ላይ መነጋገር እንደሚያስፈልግ መረጃው ያሳያል፡፡ ይህን ማሻሻያ አስፈላጊ ከሚያደርጉት ምክያቶች ዋነኛው በምክር ቤቶችና በአባላቶቻቸው መካከል አለመግባባትን ከሚፈጥሩ ጉዳዮች መካከል አንዱ ስለመሆኑ በገሃድ የታየ በመሆኑና ይህንን ለመቅረፍ ስለሚረዳ መሆኑንም የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ለአዋጁ ማሻሻያ ብሎ ከሰነዘራቸው ሐሳቦች ውስጥ ተካትቷል፡፡ አቶ ሰለሞንም አንድ ወጥ የሆነ የመዋጮ ሥርዓት ስለሌለ አሁን ያሉ ንግድ ምክር ቤቶች ደሃ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ አባላትን ማብዛት ለሥልጣን ወይም ለምርጫ መጠቀሚያ አድርጎታል በማለት ገልጸዋል፡፡ እንዲህ ያሉት ሐሳቦች ከተለያዩ አቅጣጫዎች እየመጡ ሲሆን መቋጫው እየተጠበቀ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች