የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢ፣ እንዲሁም ሌሎች ሰባት የቦርድ አባላትን ሹመት አፅድቆ ለአንድ ወር እረፍት ተበተነ።
ምክር ቤቱ ዛሬ ጥር 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ባካሄደው ልዩ ስብሰባ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ አድርጎ የሾመው የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር በመሆን ለረጅም ዓመታት ያገለገሉትን ወ/ሮ ሳሚያ ዘካሪያን ነው።
ወ/ሮ ሳሚያ ከ1972 ዓ.ም. እስክ 1998 ዓ.ም. በማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ከቡድን መሪነት እስከ ምክትል ሥራ አስኪያጅነት፣ ከ1998 ዓ.ም. እስከ 2009 ዓ.ም. ደግሞ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲን በዋና ዳይሬክተርነት መርተዋል። በመንግሥት በተሰጣቸው የአምባሳደርነት ሹመት ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በናይጄሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን በማገልገል ላይ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ሆነው እንዲሾሙ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረቡት ደግሞ አቶ ደሞዜ ማሜ ናቸው። አቶ ደሞዜ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በምክትል ኮሚሽነርነት ያገለገሉ ሲሆን፣ ከኅዳር ወር ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል የሕገ መንግሥት ትርጉም ኮሚሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በመሆን ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
የቦርዱ አባል ሆነው እንዲያገለግሉ የተሾሙት ቄሲስ በላይ መኮንን፣ ወ/ሮ የሻረግ ዳምጤ፣ ፕሮፌሰር ፌቶን ዓባይ፣ ወ/ሮ ፀሐይ መንክር ፣ አቶ ተካልኝ ገብረ ሥላሴ ፣ አቶ ጀማል መሐመድና አቶ ሀብቴ ፍላቻ ናቸው።
ምክር ቤቱ ከየካቲት 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ወር ለዕረፍት የተበተነ ሲሆን፣ አባላቱ በዕረፍት ጊዜያቸው ከመረጣቸው ሕዝብ ጋር ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል። ሹመት የተሰጣቸው የምርጫ ቦርድ አባላት ደግሞ ራሳቸውን ከተሰጣቸው ኃላፊነት ለማለማመድ በተጣበበ ሁኔታ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ከጥቂት ወራት በኋላ የሚካሄደውን የአዲስ አበባና የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤቶች ምርጫን እንዲሁም በአገር አቀፍ ደረጃ የአካባቢ ምርጫን የመምራት ኃላፊነት ይጠብቃቸዋል።