Saturday, December 9, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ፓርላማው ያፀደቀው ተጨማሪ በጀት ሕጋዊነት አከራካሪ ሆነ

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ፌዴራል መንግሥት ለክልሎች የደመወዝ ጭማሪ የማድረግ ሥልጣን የለውም›› ባለሙያዎች

የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ያዘጋጀውና በሚኒስትሮች ምክር ቤት ታይቶ ይሁንታ ያገኘውን የስምንት ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ፓርላማው ሚያዝያ 22 ቀን 2007 ዓ.ም. አፀደቀ፡፡ ይሁን እንጂ ፓርላማው ባፀደቀው ተጨማሪ በጀት ላይ የሕግ ክርክሮች እየተነሱ ነው፡፡

የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ባዘጋጀው የተጨማሪ በጀት ረቂቅ አዋጅ ማብራሪያ፣ ተጨማሪ በጀቱ ያስፈለገበት ዋና ምክንያት መንግሥት በ2007 በጀት ዓመት ለፌዴራልና ለክልሎች የመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ በማድረጉ ምክንያት፣ በመጠባበቂያ የተያዘው በጀት ወጪውን ሊሸፍን ባለመቻሉ ተጨማሪ የደመወዝ በጀት አስፈላጊ መሆኑን ያስረዳል፡፡

ይኸው የተጨማሪ በጀት ረቂቅ ሰነዱ ማብራሪያ በ2007 በጀት ዓመት ለፌዴራልና ለክልሎች ለደመወዝ ጭማሪ ከመንግሥት ግምጃ ቤት ስድስት ቢሊዮን ብር በመጠባበቂያ በጀት የተያዘ ቢሆንም፣ በተጨማሪ የሚያስፈልገውን ወጪ ሊሸፍን አለመቻሉን ይገልጻል፡፡ በመሆኑም ከክልሎችና ከፌዴራል መንግሥት በተገኘው መረጃ መሠረት ለደመወዝ ጭማሪ ወደ 14 ቢሊዮን ብር በማስፈለጉ ስምንት ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ይገልጻል፡፡

ረቂቅ አዋጁ ሚያዝያ 6 ቀን 2007 ዓ.ም. ለፓርላማው በቀረበበት ወቅት አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት የደመወዝ ጭማሪው ሲታቀድ የሚያስፈልገው ወጪ እንዴት እንዳልታሰበ መንግሥት እንዲጠየቅ ጥያቄያቸውን አቅርበው ነበር፡፡

ይህንንና ሌሎችን መርምሮ እንዲያቀርብ የተመራለት የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሚያዝያ 22 ቀን 2007 ዓ.ም. ባቀረበው ሪፖርት ‹‹ለደመወዝ ጭማሪው ቀድሞ የተያዘው መጠባበቂያ በቂ ባለመሆኑ የተነሳ የቀረበ የበጀት ማሟያ መሆኑን፣ ይህም በጀት የሚሸፈንበት የገቢ በጀት ተለይቶ ከወጪው ጋር ተመዛዝኖ የቀረበ ስለሆነ ምንም ዓይነት የበጀት ጉድለትም ሆነ የዋጋ ንረት የማያስከትል መሆኑን፣ ባደረግነው የምርመራ ሒደት ተገንዝበነዋል፡፡ ስለሆነም የተከበረው ምክር ቤት ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳቡን መርምሮ አዋጅ አድርጐ ያፀድቀው ዘንድ አቅርበናል፤›› በማለት በኮሚቴው ሰብሳቢ ወ/ሮ መሰለች ወዳጆ አማካይነት አቅርቧል፡፡

በቀረበው የኮሚቴ ውሳኔ ሐሳብ ላይ ተንተርሶ ምክር ቤቱ ምንም ዓይነት ተጨማሪ ውይይት ሳያደርግ አፅድቆታል፡፡ ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለሙያዎች፣ በመጀመርያ ለደመወዝ ጭማሪ የሚውል ገንዘብ ለምን በመጠባበቂያ ገንዘብነት ተያዘ የሚል ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፣ የመጠባበቂያ ገንዘብ በአገሪቱ ውስጥ አስቸጋሪና ድንገተኛ ሁኔታዎችን ለመቋቋም የሚውል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የዕለት ተዕለት ወጪ በመጠባበቂያ በጀትነት መያዙ አስገራሚ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ሌላ ባለሙያ በበኩላቸው፣ ክልሎችና የፌዴራል መንግሥት የየራሳቸውን ገቢና ወጪ ተከትለው የመፈጸም ኃላፊነት እንዳለባቸው በሕገ መንግሥቱ መደንገጉን፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 52 ንዑስ አንቀጽ 2(ረ) ክልሎች የራሳቸው የሲቪል ሰርቪስ መዋቅር እንደሚኖራቸው፣ ይህንንም የማስተዳደር ኃላፊነትና ሥልጣን እንዳላቸው፣ በዚህ ውስጥ ብሔራዊ የደመወዝ ደረጃን ብቻ እንዲከተሉ ክልሎች እንደሚገደዱ እንደሚደነግግ ጠቅሰዋል፡፡

በመሆኑም የፌዴራል መንግሥት ለክልል ሠራተኞች የሚሰጠው የፋይናንስ ድጋፍ ከሕገ መንግሥቱ አኳያ መሠረት አለው ብለው እንደማያምኑ ገልጸዋል፡፡   

በሌላ በኩል በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 94 ላይ የፌዴራልና የክልሎች የገንዘብ ግንኙነትን በተመለከተ ሦስት ነጥቦችን እንደሚያነሳ፣ እነዚህም ክልሎች በውክልና የሚፈጽሙት ተግባር ካለ ለዚያ ውክልና ባወጡት ወጪ መጠን ከፌዴራል መንግሥት ክፍያ እንደሚያገኙ፣ እንዲሁም ለመልሶ ማቋቋም፣ ለልማት ማስፋፊያና ለአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ የፌዴራል መንግሥት ለክልሎች የተመጣጠነና ዕድገታቸውን በማይነካ ሁኔታ በብድር ወይም በዕርዳታ ሊሰጣቸው እንደሚችል የሚደነግግ ቢሆንም፣ የቀረበው ተጨማሪ በጀት እንጂ ከላይ በተጠቀሰው ሁኔታ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ክልሎች ለሠራተኞቻቸው ለማድረግ ያቀዱትን የደመወዝ ጭማሪ መሸፈን አቅቶናል የሚል ጥያቄ ለፌዴራል መንግሥት ማቅረብ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጡ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት የሕግ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርን ለማግኘት የተደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡ ይሁን እንጂ የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሃጂ ኢብሳ ገንዶ በጉዳዩ ላይ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ የክልሎችን ከ50 በመቶ በላይ የሚሆን ወጪ የሚሸፍነው የፌዴራል መንግሥት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ በወቅቱ በመላ አገሪቱ ለተደረገው የደመወዝ ጭማሪ ይበቃል ተብሎ የተያዘው ገንዘብ ባለመብቃቱ ማሟያ ነው የተደረገው ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች