Friday, December 2, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  በሐሳብ መለያየት ሞት አይደለም!

  የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ጠቅላላ ጉባዔ በወሰነው መሠረት በየዓመቱ እ.ኤ.አ. ሜይ 3 ቀን የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ነው፡፡ ይህ የፕሬስ ነፃነት ቀን የሚከበርበት ምክንያትም የፕሬስ ነፃነትን አስፈላጊነት ግንዛቤ ለማዳበር ከመሆኑም በላይ፣ መንግሥታት እ.ኤ.አ. በ1948 የፀደቀውን ሁለንተናዊ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ መሠረት በማድረግ፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን እንዲያከብሩና እንዲያስከብሩ ለማስገንዘብ ነው፡፡ የፕሬስ ነፃነት የሰብዓዊ መብቶች አካል ከሆነው ሐሳብን በነፃነት ከመግለጽ መብት ጋር ከፍተኛ ዝምድና አለው፡፡ ለዚህም ነው በአምባገነኖች መዳፍ ሥር ከሚገኙ እጅግ በጣም ጥቂት አገሮች በስተቀር በጣም በበርካታ አገሮች በከፍተኛ ስሜት የሚዘከረው፡፡

  እኛ የፕሬስ ነፃነት ቀንን ለምን እናከብራለን? በአገራችን ከምናውቃቸው ሃይማኖታዊና ባህላዊ ወይም ፖለቲካዊ ሥነ ሥርዓቶች ምን የተለየ ያደርገዋል? ሌሎቹ በዓላት ወይም ሥነ ሥርዓቶች ዓላማቸው ታውቆ በሚመለከታቸው ወገኖች ከልብ ሲከበሩ፣ የፕሬስ ነፃነት ቀንስ እንዴት ነው የሚታሰበው? በየሆቴሉ ለታይታ በሚደረጉ ዲስኩሮችና ግርግሮች ነው? ወይስ ከልብ ታምኖበት? የፕሬስ ነፃነት ቀንን ለምን እንደምናከብር ግልጽ መሆን አለበት፡፡

  የፕሬስ ነፃነት ቀን ሲታሰብ በአገር ደረጃ ምን አገኘን? ምን አጣን? የተሟላው የቱ ነው? የተጓደለውስ? እያልን የሒሳብ ማወራረጃ ካላደረግነው ችግር አለ፡፡ በሐሳብ መለያየት ብርቅ ባልሆነበት ዓለም ውስጥ በልዩነቶቻችን ምክንያት የተከሰቱ ችግሮችን ከሥር መሠረታቸው ዘክዝከን ማየት ካቃተን፣ የፕሬስ ነፃነት ቀን ተዘከረ ማለት አይቻልም፡፡ የሚዲያ ሰዎች እርስ በርሳቸው፣ ከመንግሥትና ከሕዝቡ ጋር በፕሬስ ነፃነት ዙሪያ በሚታዩ ሥር የሰደዱ ችግሮች ላይ መነጋገር ካልቻሉ ስለፕሬስ ነፃነት ማውራት ፋይዳ የለውም፡፡ ለፕሬስ ነፃነት ቀን እንኳን አደረሰን ተብሎ መልካም ምኞት ለመለዋወጥም አይመችም፡፡

  ሒሳብ የምናወራርድበት የፕሬስ ቀን ምን ማለት ነው? ጋዜጠኞችና ኤዲተሮች ስለሚጽፉት ወይም ስለሚዘግቡት ጉዳይ መነጋገር ብቻ ሳይሆን፣ ከፕሬስ ውጤቶች ሕዝቡ የሚያገኘው ምንድነው? መረጃዎች ትክክለኛና ሚዛናዊ ሆነው ይደርሱታል? ወይስ እየተቀባቡ ነው የሚወጡት? ሚዲያው የራሱን ችግር መነጋገሩ እንዳለ ሆኖ፣ መረጃ ያለምንም እንከን ወደ ሕዝቡ ይፈሳል ወይ? ጋዜጠኞች ራሳቸውን በራሳቸው ሳንሱር እያደረጉ ነው ወይ ለሕዝቡ የሚያቀርቡት? የሚተላለፈው መረጃ በሕዝቡ የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ የሚፈጥረው አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ምን ይመስላል? የሚሉት ተጠቃሽ መሆን አለባቸው፡፡

  በአገሪቱ አንድ የምርጫ ክልል (Constituency) ውስጥ 100 ሺሕ ሕዝብ ይኖራል፡፡ በአገራችን የሚገኙ ጋዜጦች ምን ያህል ናቸው? የጋዜጦቻችን የአንድ ወር ኅትመት በአንድ የምርጫ ክልል ውስጥ የሚኖር ሕዝብን ማዳረስ ካልተቻለው፣ የፕሬስ ነፃነት ቀንን እንዴት ነው የምናከብረው? በመላ አገሪቱ ከ30 በላይ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች አሉ፡፡ የአገራችን ጋዜጦች የአንድ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብን መድረስ ይችላሉ ወይ? በአማርኛ ቋንቋ የሚታተሙት ሁሉም ጋዜጦች የአገሪቱን የተማረ የሚባል የኅብረተሰብ ክፍል መድረስ ይችላሉ ወይ? የፕሬስ ነፃነት አለ ስንል በእንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ውስጥ ነው ወይ? ስለፕሬስ ነፃነት ስንነጋገር ሚዲያው ሊደርስበት ያልቻለውን የአገሪቱን ሕዝብ ከዘነጋን ትልቅ ችግር አለ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለው ልዩነታችን ከፍተኛ የሆነ የሐሳብ ሙግት ያስፈልገዋል፡፡

  በአገራችን ውስጥ መቻቻል ወይም መታገስ የሚባለው ጽንሰ ሐሳብ ወደ ጐን እየተገፋ ትችቶችን ያለመስማት ፈተና ተጋርጧል፡፡ ከመንግሥት ጀምሮ በየደረጃው የራሳቸውን ከባቢ የፈጠሩ ጉልበተኞች ትችትን አይታገሱም፡፡ ልዩነትን አይታገሱም፡፡ የሐሳብ ልዩነትን አይቀበሉም፡፡ ትችትንና ልዩነትን፣ እንዲሁም በሐሳብ መለያየትን መታገስ የሚፈልጉ አለመኖራቸው ለፕሬስ ፈተና እየሆነ ነው፡፡ በሐሳብ መለያየት ሞት ይመስል ድንፋታዎች ይሰማሉ፡፡ የፕሬስ ነፃነትን በመጋፋት ፀጥና እረጭ ያለ ድባብ እንዲሰፍን ይፈለጋል፡፡ ይህ ችግር የመንግሥት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የባለሀብቶችና ለፕሬስ ነፃነት ቀናዒ የሆነ መንፈስ የሌላቸው ግለሰቦች ጭምር ነው፡፡

  ለፕሬስ ነፃነት ፈተና ከሆኑ ችግሮች መካከል አንዱ ሚስጥራዊነትና ተጠያቂነት ያለመኖር ነው፡፡ አትዩኝ፣ አትናገሩኝ፣ አትጠይቁኝ የሚሉ እየበዙ በመሆናቸው እስኪ እንነጋገር መባል አለበት፡፡ ይህ ችግር ከመንግሥት ጀምሮ እስከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ድረስ በጉልህ የሚታይ ነው፡፡ የሕዝብ የማወቅ መብትን እየተጋፋ መረጃ ከሚከለክል የመንግሥት ሹም አንስቶ በአገሪቱ የሚታየው የሚስጥረኝነትና ተጠያቂ ያለመሆን ችግር የፕሬስ ነፃነትን እየፈተነ ነው፡፡ በዚህ ዓይነቱ ከባቢ ውስጥ ለሐሳብ ልዩነት ዕውቅና መስጠት ይቅርና እስከ መፈጠሩም ማወቅ የማይፈልጉ አሉ፡፡ ይህም ያሳዝናል፡፡

  መንግሥት እያንዳንዱን ፖሊሲ ሲቀርፅ የንግግር ነፃነትን ለማክበርና ለማስፋፋት ጥረት ያደርጋል ወይ? ካላደረገስ መፍትሔው ምን ሊሆን ነው? በሕገ መንግሥቱ የሠፈረው አንቀጽ 29 ለፕሬስ ነፃነት ዋስትና ሰጥቷል፡፡ መንግሥት ደግሞ ይህንን ነፃነት የማስከበር ኃላፊነት አለበት፡፡ በተግባር ሲታይ መንግሥት ለፕሬስ ነፃነት መከበር ያበረከተው አስተዋጽኦ ከሚፈለገው ጋር ይመጣጠናል? በጭራሽ፡፡ እጅግ በጣም በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ከጋዜጠኞች ጋር ለዓመታት የዘለቀው አተካሮ አሁን ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ የምናስበው በሐዘን ነው፡፡ ይህም የፕሬስ ነፃነት ቀን ሲዘከር በሐሳብ መለያየት ሞት አይደለም ነበር ብለን እንድናስብ ያደርገናል፡፡

  ይህ እያገባደድነው ያለው ዓመት የምርጫ ዓመት ነው፡፡ የምርጫ ወቅት ደግሞ በርካታ ክስተቶች የሚታዩበት ከመሆኑ አንፃር፣ በልዩ ሁኔታ ይታያል፡፡ በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ግን በጣም የሚያስገርሙ ክስተቶችን እናያለን፡፡ በዘንድሮ የምርጫ ቅስቀሳ እንኳ በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ ለምርጫ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች የገጽ ሽፋንና የአየር ሰዓት የመስጠት ኃላፊነት ያለባቸው ሚዲያዎች የንግግር ነፃነትን ሲገድቡ ታይተዋል፡፡ አንድ ፓርቲ ላዘጋጀው የቅስቀሳ መልዕክት ራሱ ተጠያቂ መሆን ሲገባው፣ ሚዲያዎቹ ግን ተጠያቂ እንሆናለን በሚል ሰበብ የፓርቲዎችን የቅስቀሳ መልዕክቶች ሲመልሱ ታይተዋል፡፡ ከዚያም አልፈው ተርፈው ኤዲት ለማድረግም ሞክረዋል፡፡ በዚህ ዓይነቱ ከባቢ ውስጥ ነው የፕሬስ ነፃነት የሚከበረው?

  በአሁኑ ጊዜ ዓለም ስም ማጥፋት (Defamation) የሚባለውን ነገር ከወንጀል ሕጐች ውስጥ እያስወጣው ነው፡፡ ጋዜጠኞች ከስም ማጥፋት ጋር በተያያዘ በወንጀል ሕግ መጠየቅ የኋላቀርነት መገለጫ እየሆነ ነው ያለው፡፡ ይህ ዓለምን እያግባባ ያለ ጉዳይ የማይናቅ ቁጥር ባላቸው የአፍሪካ አገሮች ጭምር ተግባራዊ መደረግ ጀምሯል፡፡ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ በሆነችው ኢትዮጵያ ውስጥ ግን በስም ማጥፋት እንከሰሳለን እያሉ የሚያስፈራሩና የሚከሱ ባለሥልጣናት፣ ባለሀብቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ግለሰቦች ብዙ ናቸው፡፡ ይህ የንግግር ነፃነትን የሚጋፋ ተግባር ጋዜጠኞችንም ሆነ ሐሳባቸውን በነፃነት መግለጽ የሚሹ ወገኖችን ያሸማቅቃል፡፡ ግፋ ቢል ከፍትሐ ብሔር ክርክር ማለፍ የማይገባው ጉዳይ በወንጀል ሕጉ ሲያስከስስ ኧረ ነውር ነው የሚል ከሌለ፣ ስለፕሬስ ነፃነት ወይም ስለንግግር ነፃነት እንዴት ነው መነጋገር የሚቻለው?

  በፕሬስ ነፃነት ጉዳይ የሕዝብ ሚና ግልጽ ሆኖ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ሕዝብ የንግግር ነፃነትን መቀበል ወይም መውደድ አለበት፡፡ ለምን ቢባል የንግግር ነፃነት ይኑር ሲባልና ይህንን ነፃነት ከጥቃት መከላከል እንዳለበት መተማመን ሲኖር፣ ሕዝብ የሚስማማውን ብቻ አይደለም መስማት ያለበት፡፡ እንዲያውም የማይፈልገው ሐሳብ ጭምር እንዲደመጥ ማበረታታት አለበት፡፡ የማንፈልገውን ጭምር ካልሰማን የንግግር ነፃነት ውበት የለውም፡፡ የምንጠላውን ወይም የማንስማማበትን ጭምር መስማት የንግግር ነፃነትን መደገፍ ነው፡፡ ለማይስማማን ንግግር ጭምር ጥብቅና መቆም ካቃተን የራሳችን ንግግር ጭምር አደጋ ውስጥ መውደቁን ሊገባን ይገባል፡፡ እየመረረንም ቢሆን ለሐሳብ ልዩነት ክብር መስጠት ያስከብራል እንጂ አያስነቅፍም፡፡ የሐሳብ ልዩነት በነፃነት ካልተስተናገደ ስለፕሬስ ነፃነት የሚደረግ ዲስኩር ትርጉም ያጣል፡፡ ለዚህም ነው በሐሳብ መለያየት ሞት አይደለም የሚባለው!      

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  አሜሪካ ሕወሓትን በማሳመንና በመጫን በሰላም ሒደቱ ትልቅ ሚና መጫወቷን የኢትዮጵያ ዋና ተደራዳሪ አስታወቁ

  የተመድና የአውሮፓ ኅብረት አበርክቶ አሉታዊ እንደነበር ጠቁመዋል በመንግሥትና በሕወሓት መካከል...

  የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅን የሚተካ ረቂቅ ተዘጋጀ

  ከቫት ነፃ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል ገደብ ተቀመጠለት የገንዘብ ሚኒስቴር ከሃያ...

  አዋሽ ባንክ ለሁሉም ኅብረተሰብ የብድር አገልግሎት የሚያስገኙ ሁለት ክሬዲት ካርዶች ይፋ አደረገ

  አዋሽ ባንክ ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች በዘመናዊ መንገድ ብድር ማስገኘት...

  በፍላጎት ላይ የተመሠረተ ብሔራዊ አገልግሎት የተካተተበት አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ

  የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ወይም የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ወጣቶች በፈቃደኝነት...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...

  የጉድለታችን ብዛቱ!

  ከፒያሳ ወደ ሜክሲኮ ልንጓዝ ነው። ጎዳናውን ትውስታ እየናጠው ሁለትና...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ለዘመኑ የማይመጥን አስተሳሰብ ዋጋ ያስከፍላል!

  በኳታር እየተከናወነ ያለው የዓለም ዋንጫ በእግር ኳስ ጨዋታ ውስጥ ያልተጠበቁ ማራኪ ቴክኒኮችንና ታክቲኮችን ከአስገራሚ ውጤቶች ጋር እያስኮመኮመ፣ ከዚህ ቀደም በነበረ ችሎታና ዝና ላይ ተመሥርቶ...

  መንግሥት ለአገር የሚጠቅሙ ምክረ ሐሳቦችን ያዳምጥ!

  በሕዝብ ድምፅ የተመረጠ መንግሥት ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሐሳቦችን የማዳመጥ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሥራውን ሲያከናውንም በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ መመራት ይኖርበታል፡፡ እያንዳንዱ ዕርምጃው በሕግ ከተሰጠው ኃላፊነት አኳያ...

  የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ ይደረግ!

  የሰላም ስምምነቱ ‹‹ታጥቦ ጭቃ›› ሊሆን የሚችልባቸው ምልክቶች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ሚሊዮኖችን ለዕልቂት፣ ለመፈናቀል፣ ለከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰትና መሰል ሰቆቃዎች የዳረገው አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት...