Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናተቃዋሚ ፓርቲዎች ለባከኑ የቅስቀሳ ፕሮግራሞች መንግሥትን ተጠያቂ አደረጉ

ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለባከኑ የቅስቀሳ ፕሮግራሞች መንግሥትን ተጠያቂ አደረጉ

ቀን:

ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምርጫ 2007 የሚዲያ ቅስቀሳዎቻቸው አለመሳካት መንግሥት ተጠያቂ ነው አሉ፡፡ ለዚህም ያቀረቡት ምክንያት የመንግሥት ሚዲያዎች የቅስቀሳ መልዕክቶቻቸውን ሳንሱር ለማድረግ መፈለግና የመሳሰሉትን ችግሮች ጠቁመዋል፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለምርጫ ቅስቀሳ እንዲጠቀሙበት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድና የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለሥልጣን አማካይነት ከተደለደለላቸው የጋዜጣ ዓምድ፣ የሬዲዮና የቴሌቪዥን የአየር ሰዓት ውስጥ መጠቀም የቻሉት 55.6 በመቶ ብቻ መሆኑ ታውቋል፡፡ ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለሥልጣን በተገኘው መረጃ መሠረት የምርጫ ቅስቀሳው ከጀመረበት የካቲት 13 ቀን 2007 ዓ.ም. አንስቶ እስከ ሚያዝያ 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ሰባት ሳምንታት፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መጠቀም የቻሉት የመገናኛ ብዙኃን ድርሻ 55.6 በመቶ ብቻ ነው፡፡

የባለሥልጣኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ወርቅነህ ጣፋ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በተጠቀሰው ወቅት ተቃዋሚ ፓርቲዎች 46 በመቶ የሬዲዮ፣ 84 በመቶ የቲቪ እንዲሁም 37 በመቶ የጋዜጣ ቅስቀሳ አድርገዋል፡፡ ነገር ግን ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተግባር እያጋጠማቸው ያለው አስቸጋሪ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ሚያዝያ 22 ቀን 2007 ዓ.ም. በሀርመኒ ሆቴል ‹‹ለአምስተኛው ዙር አገራዊ ምርጫ ስኬታማነት የባለድርሻ አካላት ሚና›› በሚል ርዕስ በሁለት አገር በቀል ቲንክ ታንክ ተቋማት አማካይነት በተካሄደ የምክክር መድረክ ላይ ነው ይህ የተገለጸው፡፡ የምክክር መድረኩን ያዘጋጁት ሁለቱ አገር በቀል ተቋማት የኢትዮጵያ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ሕዝባዊ የምክክር መድረክና ሴንተር ፎር ዴቨሎፕመንታል ስተዲስ ናቸው፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ ከምርጫ ጋር በተያያዙ ሦስት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ገለጻዎች ተደርገዋል፡፡ ገለጻ የተደረገባቸው ርዕሶችም፣ ‹‹ዴሞክራሲና የዴሞክራሲያዊ ባህል ግንባታ በኢትዮጵያ››፣ ‹‹የኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ፣ የዴሞክራሲያዊ ምርጫ ልምድና ያለፉት ምርጫዎች ተሞክሮ›› እና ‹‹ዴሞክራሲያዊ ምርጫና የሕዝብ ሚና›› የሚሉ ነበሩ፡፡

የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የሕግና የፌዴራሊዝም መምህር አቶ ዘሪሁን ይመር፣ ‹‹የኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ፣ የዴሞክራሲያዊ ምርጫ ልምድና ያለፉት ምርጫዎች ተሞክሮ›› በሚል ርዕስ ገለጻ አድርገዋል፡፡

በዚህ ርዕስ ሥር ገለጻ አቅራቢው የአገሪቱን የምርጫ ታሪክና ልምድ ወደኋላ በመሄድ ዳሰሳና የንፅፅር ማብራሪያ ከማቅረባቸውም በተጨማሪ፣ በርካታ ከምርጫ ጋር የተገናኙ በአገሪቱ የተከሰቱ ጉዳዮችን አንስተዋል፡፡

በዘንድሮ የምርጫ ሒደት ላይም በርካታ ነጥቦችን የዳሰሱ ሲሆን፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አሁን እየሠራባቸው ያሉትን የገንዘብ ክፍፍልና የመገናኛ ብዙኃን ድልድል አጠቃቀምን የተመለከተው ገለጻ የብዙዎችን ትኩረት የሳበ ነበር፡፡

በዘንድሮ ምርጫ የሚካፈሉ ክልላዊና አገር አቀፍ ፓርቲዎች ለቅስቀሳ እንዲጠቀሙበት የተመደበላቸው የአየር ሰዓትና የጋዜጣ ዓምድ አጠቃቀምን ‹‹ትንሽ ደከም ያለ›› በማለት ገልጸውታል፡፡

የዚህ ዋነኛ ምክንያት ከአቅም ውስንነት ጋር እንደሚገናኝ ለሪፖርተር የገለጹት አቶ ዘሪሁን፣ በተጨማሪም ለዚህ ጉዳይ ትኩረት አለመስጠት እንዲሁም አለመዘጋጀትን እንደ ችግር ጠቅሰዋል፡፡

በወቅቱ የምክክር መድረኩን የታደሙ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ደግሞ፣ በጉዳዩ ፓርቲዎቹ ብቻ ሳይሆን መንግሥትና የብሮድካስቲንግ ባለሥልጣን፣ እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት እኩል ኃላፊነት አለባቸው በማለት ወቀሳው ወደነሱ ብቻ ማነጣጠሩን ተቃውመዋል፡፡

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ፣ ‹‹በመድረኩ ላይ የሚነገረው በሙሉ ሳይንሳዊ ነው፡፡ ወደ መሬት ሲወርድ የሚያጋጥመው ግን ሌላ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በእስካሁኑ ሒደት ኢዴፓ አንድም ያመለጠው የጋዜጣ ዓምድ እንደሌለ የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ ‹‹ከዚያ ውጪ ያሉ የኤሌክትሮኒክስ የመገናኛ ብዙኃን ላይ ግን በእርግጠኝነት መናገር የምችለው፣ የምንልከው ነገር ሳንሱር እየተደረገ በመሆኑ ያመለጠን አለ፤›› በማለት አክለዋል፡፡

‹‹እዚያ ጋ ያለው ችግር መስተካከል እስካልቻለ ድረስ ይህንን አልተጠቀማችሁም ተብለን ብንወቀስ ፋይዳ የለውም፤›› በማለት ለመፍትሔው ከፓርቲዎቹ ብቻ ሳይሆን፣ ከመንግሥት በኩልም ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅ ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ ለጉዳዩ በተፈለገው መጠን አለመሳካት መንግሥትንና የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱን የሚወቅሱት፣ የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (ቅንጅት) ፕሬዚዳንት አቶ አየለ ጫሚሶ ናቸው፡፡

‹‹በብሔራዊ ቴሌቪዥን፣ በአዲስ ቴሌቪዥን እንዲሁም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ የተሰጠንን ጊዜ በአግባቡ ተጠቅመናል፤›› ያሉት አቶ አየለ፣ ምንም እንኳን አገር አቀፍ የሆኑ የመገናኛ ብዙኃንን በአግባቡ ቢጠቀሙም የክልል ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ጣቢያዎችን ለመድረስ ግን መቸገራቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹የክልል መገናኛ ብዙኃንን ተጠቀሙ ተብሏል፡፡ ነገር ግን አዘጋጅተን ለማን ነው የምንሰጠው? የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱን ጊዜያዊ ቢሮ እንዲያቋቁምልን ጠይቀን ነበር፡፡ ነገር ግን አልሆነም፤›› በማለት ምሬታቸውን ገልጸዋል፡፡

የተሰጠው አስተያየት ፓርቲያቸውን እንደማይመለከት የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ ናቸው፡፡ ‹‹ኢራፓ ለመጠቀም የሚቻለውን ሁሉ አድርጓል፡፡ በመጀመሪያ ድልድሉ ወጥቶ የጊዜ ሰሌዳው እጃችን ገብቶ እስክንዘጋጅ ድረስ ካመለጠን አንድ የአዲስ ዘመን ዝግጅት በቀር ሁሉንም ተጠቅመናል፤›› ብለዋል፡፡

ፓርቲው ያመለጠውን የቅስቀሳ ፕሮግራም አዲስ ዘመን ጋዜጣ ባዶ አድርጎት እንደበር የሚታወስ ሲሆን፣ ይህንንም አቶ ተሻለ ‹‹ቦታውን ክፍት ማድረግ ሆን ተብሎ እኛን ለማጥቃት የተደረገ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) ፕሬዚዳንት አቶ ትዕግሥቱ አወሉ በበኩላቸው፣ ‹‹እኛ የተሰጠንን ጊዜ ተጠቅመናል፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ዝግጅቶች የተለየ ዝግጅት እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸው፣ ‹‹አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች ደግሞ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ናቸው ማለት ይከብዳል፤›› በማለት ፓርቲዎችን ተችተዋል፡፡ ለችግሩ በሁለተኛነት ያነሱት ነጥብ ደግሞ፣ ‹‹አብዛኛዎቹ ፖለቲከኞች የትርፍ ጊዜ ፖለቲከኞች ናቸው፤›› የሚል ነው፡፡

የኢትዮጵያ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ሕዝባዊ ምክክር መድረክ በ2000 ዓ.ም. የተቋቋመ ተቋም ሲሆን፣ በዜጎች መካከል የነበረውና ያለው አንድነትና አገራዊ መግባባት ይበልጥ የሚጠናከርበትና የሚያድግበትን ሥልት መፍጠርና ለተግባራዊነቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሁሉ አብሮ ለመሥራት የተቋቋመ መሆኑ ይነገራል፡፡

ሴንተር ፎር ዴቨሎፕመንታል ስተዲስ ደግሞ በ2004 ዓ.ም. የተቋቋመ ሲሆን፣ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅና የሕግ የበላይነትን ለማስፈን የተመሠረተ ተቋም እንደሆነ እንዲሁ ይነገራል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ