Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊከትምህርት ሥርዓቱ ውጪ የሚያስተምሩ የግል ትምህርት ቤቶች በሕግ ሊከለከሉ ነው

ከትምህርት ሥርዓቱ ውጪ የሚያስተምሩ የግል ትምህርት ቤቶች በሕግ ሊከለከሉ ነው

ቀን:

መንግሥት ከቀረፀው ሥርዓተ ትምህርት ውጪ የሚያስተምሩ የግል ትምህርት ቤቶች በሕግ እንደሚከለከሉ፣ የትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ገለጹ፡፡

ሚኒስትሩ የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ሚያዝያ 20 ቀን 2007 ዓ.ም. ለተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት፣ ‹‹በአዲስ አበባ አንዳንድ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መንግሥት ከቀረፀው ሥርዓተ ትምህርት ውጪ እያስተማሩ ይገኛሉ፡፡ ይህ ሕጋዊ አግባብነት አለው ወይ?›› ሲሉ አንድ የምክር ቤቱ አባል ጥያቄ አቅርበውላቸዋል፡፡

በተለይ ከአንድ እስከ አራተኛ ክፍል ያሉ በግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች መንግሥት በመላ አገሪቱ እንዲተገበር ከቀረፀው ሥርዓተ ትምህርት ውጪ የሆኑ የትምህርት ዓይነቶችን እየወሰዱ ነው፡፡ ትምህርት ቤቶቹን ለማስቆም የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ እየተከታተለ የነበረ ቢሆንም፣ ተቋማቱ ግን ተጨማሪ የትምህርት ዓይነቶቹን መስጠት ተገቢ ነው ብለው እንደ እምነት በመያዛቸው መስተካከል አለመቻሉን የፓርላማ አባሉ ጠቅሰዋል፡፡

- Advertisement -

በአዲስ አበባ ያሉ ተማሪዎች በዋና ከተማነት የሚገኙ ዕድሎችን በመጠቀም ከገጠሩና ከክልሎች አካባቢዎች የተሻለ ግንዛቤ ያላቸው እንደሆኑ ገልጸው፣ የሚመጥናቸው የትምህርት ዓይነት ሊሰጣቸው ይገባል የሚል መከራከሪያ እንደሚያቀርቡም የፓርላማ አባሉ ተናግረዋል፡፡

‹‹በአገር አቀፍ ደረጃ የተቀመጠው ሥርዓተ ትምህርት አይመጥናቸውም፡፡ ከአቅማቸው በታች ነው፤›› እንደሚሉ የገለጹት የምክር ቤቱ አባሉ፣ አግባብ ያለው ሥርዓት የማስያዝ ሥራ በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ለምን አይሠራም? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

   ‹‹ማንኛውም የዚች አገር ዜጋ በሥርዓተ ትምህርቱ መሠረት ነው መማር ያለበት፤›› በማለት ምላሽ መስጠት የጀመሩት ሚኒስትሩ፣ የችግሩ መንስዔ የግል ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ የሚፈቅደው በ1987 ዓ.ም. የፀደቀው ደንብ ግልጽ ባለመሆኑ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ደንቡ መዘርዘር ያለበት በመሆኑ ይህንን ሥራ ትምህርት ሚኒስቴር እየሠራ እንደሆነ ሚኒስትሩ ገልጸው፣ በሚስተካከለው ደንብ መሠረት ክልከላው እንደሚፈጸምም አመልክተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ‹‹ዜጐች ሌላ ሥርዓተ ትምህርት ለመማር ፈልገው የሚጠይቁ ከሆነ መንግሥት ከዚህ አንፃር በሕገ መንግሥቱ መሠረት ለጥያቄው ምላሽ የሚሰጥ ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡

መንግሥት ለአንደኛ ደረጃ ከቀረፀው ሥርዓተ ትምህርት ውጪ ሌሎች ትምህርቶችን ይሰጣሉ ማለት ምን እንደሆነ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ከፍተኛ ባለሥልጣን፣ ‹‹የሌሎች አገሮች መጻሕፍትን መጠቀም፣ ትምህርት ቤቱ በመንግሥት ከተዘጋጀው መጻሕፍት ውጪ ያሉ ጽሑፎችን ሲጠቀምና የመሳሰሉት በራሱ ሥርዓተ ትምህርቱን ጥሷል ያስብላል፤›› ብለዋል፡፡

መንግሥት ሥርዓተ ትምህርቱን የቀረፀው ከሚማሩት ተማሪዎች የዕድገት ደረጃ አኳያ ቢሆንም፣ ከትምህርትና ዕድገት ደረጃው ውጪ ሌሎች ትምህርቶችም መጫን ሥርዓተ ትምህርቱን መጣስ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ መንግሥት ሥርዓተ ትምህርቱን የሚቀርፀው አገር አቀፍ ፍላጐትን፣ ደረጃን፣ ዓላማን፣ የማስተማሪያ ቋንቋን፣ የመመዘኛ ደረጃን ከግምት በማስገባት እንደሆነና አንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች ይህንን እንደሚጥሱ አረጋግጠዋል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአንድ የግል ትምህርት ቤት መምህራን በበኩላቸው፣ ከሥርዓተ ትምህርቱ ውጪ ሌሎች አጋዥ መጻሕፍትን ትምህርት ቤቱ በማሳተም እንደሚያስተምር ገልጸው፣ የትምህርት ሥርዓት መከበርና ወጥነት ሊኖረው ይገባል ከሚል አንፃር ጥያቄው ካልተነሳ በስተቀር፣ ለተማሪዎች ውጤታማነት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

ምንም እንኳን የፓርላማ አባሉ በአዲስ አበባ የሚገኙ አንደኛ ደረጃ የግል ትምህርት ቤቶች ላይ አተኩረው ቢናገሩም፣ ችግሩ በሁለተኛ ደረጃ የግል ትምህርት ቤቶችም ላይ የሚታይ መሆኑን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ከፍተኛ ባለሥልጣኑ ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ክልከላው ተግባራዊ በሚሆንበት ወቅት በአጠቃላይ በአገሪቱ ውስጥ በሚገኙ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ የግል ትምህርት ቤቶችን እንደሚመለከት አክለዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...