Thursday, December 1, 2022
ሌሎች ዓምዶች

  የዕምነት ፖለቲካ – የአፍሪካ የዘመኑ ሥጋት

  - Advertisement -spot_img

  በብዛት የተነበቡ

  ባህር ዳር ጣና ሐይቅ ዳርቻ ላይ በሚገኘው ውቡ የብሉ ናይል (ቀድሞ አቫንቲ) ሪዞርት ሚያዝያ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. ከሰዓት 10 ሰዓት አካባቢ ጥቂት የአፍሪካ አገሮች መሪዎች፣ የቀድሞ መሪዎች፣ ታዋቂ ምሁራንና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ወደ ኤርፖርት ለማምራት በዝግጅት ላይ ነበሩ፡፡ እንግዶቹ በየዓመቱ ለሁለት ቀናት የሚካሄደውን የጣና ከፍተኛ እርከን የደኅንነት ፎረም እያጠናቀቁ ነበር፡፡ ይሁንና ከሰዓት በኋላ ምን እንደሚያሰማቸው የጠበቁት ነገር አልነበረም፡፡ 30 ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን ራሱን ‘ኢስላሚክ ስቴት’ እያለ በሚጠራው አሸባሪ ቡድን በአሰቃቂና በኢሰብዓዊ ሁኔታ በሊቢያ መገደላቸው ከግምታቸው ውጪ ነበር፡፡

  ብዙዎቹ ዜናውን ወዲያው ለመቀበል ተቸግረው ነበር፡፡ አሸባሪ ቡድኑ የለቀቀው ቪዲዮ እውነተኛነት ላይ የተጠራጠሩ የመኖራቸውን ያህል፣ የጥቃቱ ሰለባ ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን መሆናቸውንም ያለመቀበል አዝማሚያ ታይቷል፡፡ በሃይማኖታዊ አክራሪ ቡድን የአፍሪካውያን መገደል መቀጠሉን የሚያመላክት ሌላ ክስተት ነበር፡፡ ፎረሙ በይፋ በመጠናቀቁ የዜናውን ምንነት ተሳታፊዎች በቡድን በቡድን እየሆኑ ይመክሩበት ነበር፡፡ የሚዲያ ሰዎች ስለዜናው ዝርዝር ለማወቅ መሯሯጥ የጀመሩ ቢሆንም፣ የአብዛኛዎቹ ተሳታፊዎች ስሜት በድንጋጤ የተሞላ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንን ጨምሮ በፎረሙ ተሳታፊ ለነበሩት የኢትዮጵያ ልዑክ አባላት ሕመሙ እጥፍ ድርብ መሆኑ ይታይ ነበር፡፡

  ጉዳዩ ይበልጥ የሚገርመውና ክስተቱን በተቃርኖ የሚሞላው ለአራተኛ ጊዜ ከሚያዝያ 10 እስከ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. የተካሄደው የጣና ፎረም የተመካከረበት ጉዳይ በአፍሪካ ስላለው የሃይማኖት አክራሪነትና ሃይማኖትን ለፖለቲካ ዓላማ ስለማዋል መሆኑ ነው፡፡ በፎረሙ ላይ የታደሙት የአገሮች መሪዎች አፍሪካ በዚሁ ጉዳይ አጣብቂኝ ውስጥ ስለመውደቋ ገልጸው ነበር፡፡ የሚያሳዝነው ነገር የፈሩትና ለማስወገድ ምን ማድረግ አለብን ሲሉ የነበረው ጉዳይ በደቂቃዎች ልዩነት ተጠናክሮ መቀጠሉን መረዳታቸው ነው፡፡

  የአፍሪካ አኅጉር በአጠቃላይና አባል አገሮቹ ከአዎንታዊ ዜና ይልቅ እንደ ረሃብና ድህነት፣ የእርስ በርስ ጦርነት፣ ሙስና፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ከምርጫ ጋር የተያያዙ ውዝግቦችና የመሠረታዊ አገልግሎቶች እጦት በመሳሰሉ አሉታዊ ዜናዎች ይታወቁ ነበር፡፡ እነዚህ ችግሮች አሁንም ሙሉ በሙሉ አልተወገዱም፡፡ ይሁንና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከተለያዩ አካባቢዎች የሚሰሙ የስኬት ታሪኮች ቁጥርና መጠን እየጨመረ ነው፡፡

  የአፍሪካ ልጆች የራሳቸውንና የሌሎችን ኑሮ ለመለወጥ የላቸውም የተባለውን ቁርጠኝነት በማሰባሰብ የቀድሞ ስማቸውንና ምስላቸውን ለመቀየር ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያደረጉ ባለበትና አንፃራዊ ስኬትን እያስመዘገቡ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ ያልጠበቁት ጉዳይ ዋና መሰናክል ሆኖ ብቅ ብሏል፡፡ ይህም ሃይማኖትን መሠረት ያደረግ ግጭትና ብጥብጥ እንዲሁም ጭፍጨፋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ መምጣቱ ነው፡፡ ችግሩን ከግምት ያስገባው የጣና ፎረም የመወያያ ርዕስ አድርጎ የመረጠው ለዚሁ ነበር፡፡

  ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አፍሪካ ጥሩ ዜናዎችን ማምረት በጀመረችበት በአሁኑ ወቅት የሃይማኖት ነፃነትንና ሃይማኖትን ለፖለቲካ ዓላማ የመጠቀም አዝማሚያን የቀላቀሉ ድርጊቶች፣ ለአኅጉሪቱ መሰናክል መሆናቸው አሳዛኝ መሆኑን በፎረሙ መክፈቻ ላይ ባሰሙት ንግግር አመልክተዋል፡፡ ‹‹አፍሪካ፣ ‘ጥቁሩ አኅጉር’ ከሚለው ምሥል ቀስ በቀስ በመላቀቅ ላይ ባለችበት፣ በሚወጡት ፖሊሲዎች ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበች ባለችበት፣ ለመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት በጀመረችበት በአሁኑ ወቅት፣ በብዙ የአፍሪካ አገሮች የተቀሰቀሱት ተከታታይ ቀውሶች ለዓለማዊ የፖለቲካ ሥርዓቶች ሥጋት ሆነዋል፤›› ብለዋል፡፡

  የጣና ከፍተኛ እርከን የደኅንነት ፎረም ምክክርና ውይይት ግጭትን በዘላቂነት ለማስወገድ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማስፋፋት ያለመ ፎረም ነው፡፡ በየዓመቱ ወደ ባህር ዳር የተጋበዙ የአገር መሪዎች፣ ከትምህርትና ከምርምር ተቋማትና ከተለያዩ ድርጅቶች የሥራ ኃላፊዎች የሚመጡ እንግዶች፣ በአፍሪካ ሰላምና ደኅንነት ላይ ተፅዕኖ አለው ተብሎ በሚመረጠው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ይመክራሉ፡፡ ፎረሙ በዓለም የደኅንነት አጀንዳ የአፍሪካ ድምፅ እንዲጎላ ለማድረግም ይሠራል፡፡

  በ2004 ዓ.ም. ብዝኃነትን ስለማስተናገድና ስለአገሮች ተሰባሪነት በመምከር የጀመረው የጣና ፎረም፣ በ2005 ዓ.ም. ስለተደራጀ ወንጀል ችግር እንዲሁም በ2006 ዓ.ም. ደግሞ የሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ተፅዕኖ ላይ መክሯል፡፡

  የዘንድሮው የጣና ፎረም በእጅጉ የተለየ ነበር፡፡ የዚህ አንዱ መገለጫ ፎረሙን የታደሙት እንግዶች ብዛትና ተዋፅኦ ነው፡፡ 11 የአገር መሪዎችና የቀድሞ መሪዎች በፎረሙ ተሳትፈዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ፣ የዩጋንዳ ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ፣ የማሊ ፕሬዚዳንት ኢብራሒም ቡባከር ኪየታ፣ የፑንትላንድ ፕሬዚዳንት አብዲወዲ ሞሐመድ አሊ፣ የደቡብ ሱዳን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የቻድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሙሳ ፋኪ ማሃማት፣ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ፣ የቀድሞው የቦትስዋና ፕሬዚዳንት ፌስተስ ሞሃይና የቀድሞው የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት ቤንጃሚን ምካፓ በፎረሙ ላይ ከተገኙ አመራሮች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ፎረሙ በተመሳሳይ በዕውቅ አፍሪካውያን፣ በሲቪል ማኅበራት መሪዎች፣ በፖሊስ አውጪዎችና በተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ የደመቀ ነበር፡፡ ኢትዮጵያን ከወከሉ ተሳታፊዎች መካከል የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ፕሮፌሰር አንድሪያስ እሸቴ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ካሳ ተክለብርሃን፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ ዶ/ር ሳሙኤል አሰፋ፣ ዶ/ር መሐሪ ታደለ ማሩ፣ ዶ/ር ሰለሞን አየለና አምባሳደር ቆንጅት ሥነ ጊዮርጊስ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

  የሃይማኖትና የመንግሥት መለያየትና የደኅንነት ሥጋት

  የሃይማኖትና የመንግሥት መለያየት ጽንሰ ሐሳብ በዘመናት ሒደት መቋጫ ካላገኙት ጽንሰ ሐሳቦች መካከል የሚካተት ነው፡፡ የሃይማኖትና የመንግሥት ቀጭን ድንበርን የመለየት ጉዳይ አሁንም ድረስ አወዛጋቢ ነው፡፡

  መንግሥትና ሃይማኖት የተለያየ ዓላማና አሠራር ያላቸው ተቋማት በመሆናቸው፣ ጽንሰ ሐሳቡ በብሔራዊ የፖለቲካ ምኅዳሩ የሚሳተፉ አካላት ሃይማኖታዊ ሳይሆን ዓለማዊ የፖለቲካ አጀንዳ ማራመድ እንደሚኖርባቸው ያስገነዝባል፡፡

  አክራሪ ሃይማኖተኞች ግን ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች የተቀላቀሉ እንደሆኑ፣ አልፎ አልፎም አንድ እንደሆኑ ይምናሉ፡፡ በዚህ አረዳድ ደግሞ ሃይማኖት ዒላማዊ ጉዳዮችን ሊመራ እንደሚገባና ብቸኛም ተቀባይነት ያለው አመራርም ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ ብቻ ነው ይላሉ፡፡

  ይህ ሃይማኖትን ለፖለቲካ ዓላማ የማዋል አዝማሚያ በአፍሪካ እየተጠናከረ መምጣቱ ብቻ ሳይሆን፣ የተለያዩ ውጥረቶችንና ግጭቶችን እየፈጠረ መምጣቱን የፎረሙ ተሳታፊዎች አስረድተዋል፡፡ በአፍሪካ የተለያዩ ቦታዎች ይህ ችግር ማኅበራዊ መስተጋብሮችን እያፈራረሰና ውጥረት እያነገሰ መምጣቱንም የተለያዩ ጥናቶች ጠቁመዋል፡፡

  የጣና ፎረም የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት የቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ፣ የአፍሪካን የ2015 የሰላምና ደኅንነት ሁኔታ በዳሰሳው ሪፖርታቸው፣ ሃይማኖትና የእምነት መገለጫዎች ውጥረትና የደኅንነት ሥጋት እየፈጠሩ መምጣታቸውን አመልክተዋል፡፡ ኦባሳንጆ ሃይማኖትን ለፖለቲካ ዓላማ መጠቀም የደኅንነት ሥጋት የሚሆነው ግለሰቦችና ቡድኖች እምነታቸውን በኃይል ለመጫን ሲሞክሩ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

  መሰል አዝማሚያዎች በአፍሪካ መታየት ከጀመሩ የሰነባበቱ ቢሆንም፣ የሃይማኖት ተቋማትና የመንግሥት አካላት የጋራ ጉዳያቸው ላይ በተገቢው ሁኔታ እየሠሩ እንዳልሆነ ተሳታፊዎቹ ጠቁመዋል፡፡ የተመድ ምክትል ዋና ጸሐፊ ኃይሌ መንቆሪዎስ የሃይማኖት ተቋማት የመንግሥትን ጥበቃ እንደሚሹት ሁሉ መንግሥት ባህል፣ ልምድ፣ ሞራልና እሴቶችን ለመገንባት የሃይማኖት ተቋማትን እንደሚጠቀም አስታውሰዋል፡፡ ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉ ውጥረቶችንና ግጭቶችን ለማስወገድ ይህን ማጠናከር እንደሚገባ ምክትል ዋና ጸሐፊው አሳስበዋል፡፡ የጀርመን የኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት ቶማስ ሲልበርሆርን በተመሳሳይ የመንግሥትና የሃይማኖት አካላት ሊመካከሩ እንደሚገባ፣ አንዳቸው በአንዳቸው አሠራር ላይ ገንቢ ትችት የሚያቀርቡበት ምኅዳር መኖር እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡

  የሃይማኖትና የመንግሥት መለያየት ማለት በመንግሥትና በሃይማኖት ተቋማት መካከል ጥላቻ ይኖራል ማለት እንዳልሆነም ተሳታፊዎቹ አመልክተዋል፡፡ የሃይማኖትና የመንግሥት መለያየት ጽንሰ ሐሳብን የፈጠረው የሃይማኖት ተቋማት የመንግሥት ጣልቃ ገብነትን ለማስወገድ ያደረጉት ትግል እንደሆነም ኤክስፐርቶች ጠቅሰዋል፡፡

  ይሁንና ወደኋላ የተለያዩ ምክንያቶች በጽንሰ ሐሳቡ ላይ ስምምነት እንዲጠፋ ማድረጋቸውን ጥናቶቹ ይጠቁማሉ፡፡ በተለይ በአንዳንዶች ዘንድ ጽንሰ ሐሳቡ ሃይማኖትን ከመጥላት ጋር መያያዙ ዋነኛ ከሚባሉት የሚጠቀስ ነው፡፡ ይኼው ነጥብም የተሳታፊዎችን ትኩረት የሳበ ነበር፡፡ በበርካታ አጋጣሚዎች በፀረ ሃይማኖተኛ ፈላስፎችና የፖለቲካ ተዋንያን የሚቀርበው የሃይማኖትና የመንግሥት መለያየት ጽንሰ ሐሳብ ማብራሪያ፣ ሃይማኖትን ስለመጥላት የሚሰብክ መሆን ችግሩን ይበልጥ እያወሳሰበው እንደመጣም ጥናት አቅራቢዎቹ አስረድተዋል፡፡ ይህ ደግሞ ሃይማኖት ተቋማት ባላቸው የድጋፍ መሠረት ጽንሰ ሐሳቡ በጥርጣሬ እንዲታይ መሠረት መጣሉንም አመልክተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ ይህ ዓይነቱ በሃይማኖት ጥላቻ የተቃኘ የጽንሰ ሐሳቡ ገለጻ ከታጣቂ ቡድኖች ሥጋት ለይተው እንደማያዩት ገልጸዋል፡፡

  አንዳንድ የፎረሙ ተሳታፊዎች የፖለቲካ መሪዎችና የሃይማኖት መሪዎች ኃላፊነታቸውን የሚወጡት በተመሳሳይ አካባቢ እንደሆነ ግንዛቤ ውስጥ እንዲገባ ጠይቀዋል፡፡ በበርካታ ሁኔታዎች የሁለቱም ተቋማት አባላት ተመሳሳይ እንደሆኑም ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹እነዚህ መሪዎች የቡድናቸውን አባላት ከማስተዳደር፣ ከመምራትና አቅጣጫ ከማሳየት ባሻገር ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ፖለቲካ ወይም ሃይማኖት ብቻውን የሚገኝበት ቦታ የለም፡፡ አንዱ በሌላው ውስጥ አለ፡፡ ዋናው ጥያቄ ሁለቱን እንዴት ማስማማትና አብረው እንዲኖሩ ማስቻል ይቻላል ነው፤›› ያሉት ፖል ካጋሜ ናቸው፡፡

  ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ ‹‹የሃይማኖትና የመንግሥት መለያየት ማለት ከሃይማኖት የፀዳ ማኅበረሰብ መፍጠር ማለት ነው ብለው የሚረዱ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ የሰው ልጅ መንፈሳዊ እንስሳ በመሆኑ ይህ ፈጽሞ አይታሰብም፤›› ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ ኦባሳንጆ ሃይማኖትና መንግሥትን ፍፁም መለያየት ከምኞት ባሻገር የሚቻል ነገር እንደልሆነ ተከራክረዋል፡፡

  በርካታ የፎረሙ ተሳታፊዎች መንግሥትና የሃይማኖት ተቋማት ሊኖራቸው በሚገባው ሚና ላይ ስምምነት የነበራቸው ቢሆንም፣ አንዳንዶች ግን ሃይማኖት በመንግሥት አስተዳደር ውስጥ ሊኖረው ስለሚገባው ቦታ የተለየ ሐሳብ አንፀባርቀዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ዋነኛ ተጠቃሽ የሚሆኑት የቱኒዚያ ንሃዳ ፓርቲ ሊቀመንበር የሆኑት ራችድ አልጋኑቺ ናቸው፡፡ አልጋኑቺ አስተዳደሩ ዓለማዊ ይሁን ወይም ሃይማኖታዊ ምርጫው ለሕዝቡ ሊተው ይገባል ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ ፖለቲካና ሃይማኖት በስምምነት ሊኖሩ ቢችሉም፣ ምርጫው ሁለቱንም በአንድነት የያዘ ሥርዓት ካመጣ ተቀባይነት እንዳለው አስገንዝበዋል፡፡

  የአገሮች ኃላፊነቶች

  እያንዳንዱ አገር የዜጎቹን መብት የመጠበቅ፣ የማክበርና የማሟላት ግዴታ አለበት፡፡ የአፍሪካ አገሮች በተለያዩ ምክንያቶች እነዚህን ኃላፊነቶቻቸውን ለመወጣት ይቸገራሉ፡፡ ለዚህ አንዱ ዋነኛ ችግር ከብዝኃነት ጋር የተያያዘው ነው፡፡ ይሁንና ሙሴቬኒ በአፍሪካ ለብዝኃነት የተሰጠው ትርጉም የተዛባ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ሰዎች አፍሪካውያን በጣም የተለያየን እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን የሥነ ቋንቋ ኤክስፐርቶች በአፍሪካ አራት የቋንቋ ቡድን ብቻ እንዳለ ይናገራሉ፡፡ ከቻይናና ከአውሮፓ በተለየ በአፍሪካ ሰዎች ልዩነት ላይ ያተኩራሉ፤›› በማለት፣ በአፍሪካ የተለየ የብዝኃነት ችግር እንደሌለ ተከራክረዋል፡፡

  ከዚህ በተቃራኒ የጣና ፎረም መደበኛ ታዳሚ የሆኑት ካጋሜ፣ በአፍሪካ ብዝኃነትን ከማስተናገድ ጋር የተያያዙ ውስብስብ ጉዳዮች በአፍሪካ ሃይማኖትን በመጠቀም የፖለቲካ ዓላማቸውን ለማሳካት የሚሠሩ ቡድኖች ለሚፈጥሩት አደጋ በር እየከፈተ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ‹‹እኛ አፍሪካውያን ብዙ ነገሮች ነን፡፡ የብሔር፣ የሃይማኖትና የመሳሰለው ብዝኃነት አለን፡፡ በማኅበረሰባችን የተለያየ ደረጃ ላይ ያሉ ተዋንያንና ገጽታዎች አሉ፡፡ አንዳቸው ከሌላው የተለዩ ናቸው፡፡ ከዚህ ብዝኃነት ምን እንጠቀም? እንዴት እናደራጀውና እንምራው? የሚል ጥያቄ ይነሳል፡፡ ዞሮ ዞሮ ጉዳዩ የአስተዳደር፣ የአመራርና የፖለቲካ ነው የሚሆነው፤›› ብለዋል፡፡

  ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ዜጎችን ከታጣቂ አክራሪ ሃይማኖታዊ ኃይሎች የመጠበቅ ግዴታ መንግሥትን፣ ዜጎችንና አገርን እንደሚጠቅም ይገልጻሉ፡፡ ‹‹የአሸባሪዎች መረብ በሃይማኖት ስም በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን እየገደለ ነው፡፡ በብዙ ቦታዎች አገሪቱን ያለመንግሥት እያስቀሩ ለማስተዳደር የማይቻሉ እያደረጉ ነው፡፡ ይኼ የአገሮቹ የተናጠል ችግር ሳይሆን፣ በጋራ የምንፈታው የሁላችንም ጉዳይ ሆኗል፤›› ብለዋል፡፡

  የፎረሙ ተሳታፊዎች የውጭ ኃይሎች ሃይማኖትን ተገን አድርገው ከተቋቋሙ አፍሪካዊ ቡድኖች ጋር ጥምረት በመፍጠር ቅርብና ተደራሽ አደጋ እያስከተሉ ስለመሆኑም መክረዋል፡፡ ይህን ለመከላከል አገሮች የራሳቸውን አቅም በማጎልበት ወታደራዊ ኃይላቸውን ከማሰማራት ባሻገር፣ ርዕዮተ ዓለምን መሠረት ያደረጉ የሐሳብ የበላይነት የሚያዝባቸው ሥራዎችን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ተመክረዋል፡፡ ከፎረሙ መጠናቀቅ በኋላ በሊቢያ ‹‹ኢስላሚክ ስቴት›› በኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን ላይ ያደረሰው ጥቃት ይህንኑ ሥጋት ያረጋገጠ ሆኗል፡፡ በአፍሪካ እንደ አልቃይዳ፣ ቦኮ ሐራምና አልሸባብ ያሉ ቡድኖች መጠነ ሰፊ ጉዳት እያደረሱ መሆኑ ይታወቃል፡፡

  አንዳንዶች ከእነዚህ ጽንፈኛ ቡድኖች ጋር በመወያየትና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የተሻለ ውክልና እንዲኖራቸው በማድረግ ችግሩን መቅረፍ እንደሚቻል ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ ይህ ሐሳብ ሁሌም የሚሠራ አይመስልም፡፡ ለአብነት ያህል የአልሸባብ አባላት በአብዛኛው ወጣቶች ሲሆኑ፣ ይህ ነው የሚባል የፖለቲካ ፕሮግራም የላቸውም፡፡ በቅርቡ በኬንያ ጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ አልሸባብ ያደረሰው ጥቃት የ148 የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን ሕይወት የቀጠፈ ሲሆን፣ ከጥቃቱ ፈጻሚዎች መካከል ከከበርቴና የተማሩ ቤተሰቦች የወጡ ወጣቶች መገኘታቸውም የዚሁ ተቃርኖ ማሳያ ነው፡፡

  ‹‹በአስቸጋሪ ሁኔታዎችም ጭምር ውይይትን የዕለት ተዕለት ሕይወታችን መገለጫ ማድረግ አለብን፡፡ ሕገ መንግሥታዊና የሕግ ሥርዓት በመፍጠር መቻቻልን፣ ነፃነትንና ዴሞክራሲያዊ ባህልን ማዳበር ያስፈልጋል፡፡ የሕግ ማዕቀፉ ማኅበረሰቡ የሚቀበለውንና የማይቀበለውን መለየት አለበት፤›› ያሉት ካጋሜ ናቸው፡፡ በማሊ ያለው ሁኔታ ከሩዋንዳ ፈጽሞ የተለየ ቢሆንም፣ የማሊው ፕሬዚዳንት ኢብራሒም ቡባከር ኪየታ በጽንፈኞች ለምትታመሰው አገራቸው ችግር መፍትሔው ውይይትና መረዳዳት መሆን እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ በቅርቡም ከአማፅያኑ ጋር የሰላም ስምምነት እንደሚደረግ ይፋ አድርገዋል፡፡

  መገለልና ውክልና ማጣት

  የፎረሙ ተሳታፊዎች የአገሮች ድክመትና ውድቀት ከፋፋይ የሃይማኖት ቡድኖች በአፍሪካ ግጭቶችን እንዲስፋፉ ዕድል እንደፈጠረላቸውም አመልክተዋል፡፡ አገሮቹ ብሔራዊ አንድነት መፍጠር ባለመቻላቸው አክራሪ ሃይማኖታዊ ቡድኖች ቀውስ ለመፍጠር እንዲችሉ በናይጄሪያ፣ በሶማሊያ፣ በሱዳንና በማሊ ሁኔታዎች እንደተመቻቹም ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

  ኦባሳንጆ፣ ‹‹በአፍሪካ ዘላቂ ልማት ለማምጣትና ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም፣ ድህነትና የሀብት ልዩነት በአኅጉሩ ግጭትና አለመረጋጋት እንዲፈጠር ምክንያት እየሆኑ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ዜጎች ከአገሮቹ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ድጋፍ እየተደረገላቸው ባለመሆኑ አሁን በአፍሪካ በማኅበረሰቡና በአገር መካከል፣ በዜጎችና በመንግሥት መካከል፣ በወጣቱና በአዋቂ መካከል ውጥረትና አለመተማመን መፈጠሩን አስረድተዋል፡፡ አፍሪካ ከድህነት፣ ከፀረ ዴሞክራሲ፣ ከሙስና፣ ከስደትና ከተደራጀ ወንጀሎች ጋር የተያያዙ ችግሮችን በአግባቡ መፍታት ካልቻለች የሽብር ቡድኖች ከዚህ በፊት ባልደረሱባቸው ቦታዎች መድረሳቸው እንደማይቀር ኦባሳንጆ አስጠንቅቀዋል፡፡

  የናይጄሪያ ካኖ ግዛት አስተዳዳሪ የሆኑት ማላም ሳኑሲ ላሚዶ ሳኑሲ፣ ‹‹የቦኮ ሐራም ሥጋት በምን ያህል መጠን የመንግሥት ውድቀት ውጤት ነው?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹ሰሜን ምሥራቃዊ ናይጀሪያ በአገሪቱ እጅግ ደሃ የሆነ አካባቢ ነው፡፡ እነዚህ የሽብር ቡድኖች ሃይማኖታዊ ቋንቋ ቢጠቀሙም ቅሬታቸው ግን ዓላማዊ ነው፡፡ የትምህርት ዕድል፣ የጤና አገልግሎትና የሥራ ዕድል ይፈልጋሉ፤›› በማለት ተከራክረዋል፡፡ የቦኮ ሐራምን ድርጊት ባይቀበሉም መሪዎች እነዚህ ቅሬታዎች የሚነሱበትን ዓውድ በአግባቡ ሊረዱ እንደሚገባ ግን አሳስበዋል፡፡ ‹‹በኋላቀርነትና በአክራሪነት መካከል ቀጥተኛ ግንኙነት አለ፡፡ ቢያንስ በከፊል እነዚህ አክራሪ ቡድኖች እንዲፈጠሩ የተመቻቸ መነሻ በመስጠታችን ተጠያቂ ነን፤›› ብለዋል፡፡

  በአንዳንድ ጉዳዮች ለእነዚህ አክራሪ ኃይሎች ከወታደራዊ ምላሽ ውጪ ሌላ አማራጭ የሌለ ቢሆንም፣ ምሁራኑ አንዳንዶቹ በመንግሥት የተሻለ ቦታ ከተሰጣቸውና በውይይት ሌላ ማዕቀፍ እንዲይዙ ከተደረጉ ገንቢ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ አመልክተዋል፡፡

  የኪራይ ሰብሳቢዎች ጨዋታ

  ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ከመገለልና ከመንግሥት ኃላፊነት ይልቅ ቁልፍ ችግር ያሉት፣ ጥቂት የሃይማኖት ልሂቃን ኪራይ ለመሰብሰብ አክራሪ ቡድኖችን በሃይማኖት ሰበብ የማደራጀት አዝማሚያን ነው፡፡ ‹‹ሰዎች ሃይማኖትን ተጠቅመው ፖለቲካ ዓላማ ለምን ያራምዳሉ? የፖለቲካ ግባቸው ሃይማኖትን በመጠቀም ሥልጣን መያዝ ነው፤›› ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ የኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ከእያንዳንዱ የማንነት ጥያቄ ጀርባ የጥቅም ጥያቄ እንዳለ አመልክተዋል፡፡

  ‹‹በፎረሙ ከመልስ ይቅር ብዙ ጥያቄዎች እንደሚኖሩ አምናለሁ፡፡ ነገር ግን ሃይማኖትን በመመርኮዝ ፖለቲካዊ ዓላማቸውን ለመፈጸም የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች የሚፈጥራቸውን የደኅንነት ሥጋቶች ተፈጥሮ ለመለየት ከረዳ የውይይት መድረኩ ዓላማውን እንዳሳካ እወስደዋለሁ፡፡ የሃይማኖትና የመንግሥት መለያየት ጽንሰ ሐሳብን ሳንጥስና የሃይማኖት ነፃነትን ሳንጋፋ ደኅንነታችንን የምንጠብቅባቸውን መንገዶች ከጠቆመ ስኬት ይሆናል፤›› ያሉት የአዘጋጁ አገር መሪ ናቸው፡፡ ከ220 በላይ እንግዶች የመሰላቸውን ሐሳብ በነፃነት በመግለጽ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐሳብ በዓይነት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ፎረሙ በንቁ ተሳትፎ ታጅቦ በድምቀት የተካሄደ ሲሆን፣ ተገቢነት ላላቸው ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ለመስጠት የመጀመርያ ዕርምጃ መሆናቸውን ባረጋገጡ ተሳታፊዎች የተሞላ ነበር፡፡ የሊቢያው ክስተት ስሜታቸውን እስኪበርዘው ድረስ እስከ ቀጣዩ የጣና ፎረም መድረክ የሚሠሩ ሥራዎችን ታሳቢ በማድረግ፣ ተሳታፊዎቹ በፈገግታና በጋለ ስሜት አድራሻ እየተለዋወጡ ነበር የተለያዩት፡፡

                      

   

   

  spot_img
  - Advertisement -

  ትኩስ ጽሑፎች

  ተዛማጅ ጽሑፎች

  - Advertisement -
  - Advertisement -