Sunday, April 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የምግብ ነክ ምርቶችን ደረጃ የሚመዝነው የግል ተቋም

ተዛማጅ ፅሁፎች

ወይዘሮ ሕሊና በለጠ የ28 ዓመት ወጣት ነች፡፡ ብሌስ አግሪ ፉድ ላብራቶሪ አገልገሎት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በዋና ሥራ አስኪያጅነት ትመራለች፡፡ የዚሁ ኩባንያ እህት ኩባንያ የሆነውንም ሕሊና ገንቢ ምግቦች አምራች ድርጅት የኦፕሬሽን ምክትል ሥራ አስኪያጅ በመሆን እያገለገለች ነው፡፡ ሁለቱም ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ያልተለመደ በሚባል አገልግሎት ላይ የተሰማሩ ናቸው፡፡ በተለይ ብሌስ አግሪ ፉድ ላብራቶሪ የተለያዩ ምግብ ነክ ምርቶችን ደረጃ ምዝና በማድረግ የምግብ ንጥረ ነገሮችቻቸውን መጠን በመለየት ማረጋገጫ የሚሰጥ ተቋም ነው፡፡ ሁለቱ ኩባንያዎች በጥቅሉ ከ330 በላይ ሠራተኞች አሉዋቸው፡፡ ከብሌስ ሌላ በዚህ ዓይነት አገልግሎት ላይ የተሰማራው መንግሥታዊው የደረጃዎች መዳቢ ኤጀንሲ ብቻ ስለመሆኑ ወይዘሮ ሕሊና ትገልጻለች፡፡ ምግብ ነክ በሆኑ ምርቶችን በሚመዝነው ላብራቶሪ የራሱ የሆነ የሥልጠና ማዕከልም አለው፡፡ ወጣትዋና የሥራ መሪዋ ወይዘሮ ሕሊና የመጀመርያ ዲግሪዋን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፐብሊክ አድሚኒስትሬሽን ዴቨሎፕመንት ማኔጅመንት ያገኘች ሲሆን፣ ሁለተኛ ዲግሪዋን ደግሞ ደቡብ አፍሪካ ከሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሳውዝ አፍሪካ (ዩኒሳ) በቢዝነስ ሊደርሺፕ ወስዳለች፡፡ ከዩኒቨርሲቲ ከወጣች በኋላም በቀጥታ ወደዚሁ የቤተሰብ ቢዝነስ ውስጥ የገባች ሲሆን፣ ወላጅ አባትዋ አቶ በለጠ በየነ በኢትዮጵያ ምግብ ነክ ኢንዱስትሪዎችና ተያያዥ ሥራዎች ውስጥ ከ45 ዓመት በላይ ያገለገሉ በመሆናቸው የእሳቸውን ፈለግ ተከትላ ወደዚህ ሥራ ገብታለች፡፡ ሁለቱ ኩባንያዎች እየሠሩዋቸው ባሉ ሥራዎች ዙሪያ ዳዊት ታዬ ወይዘሮ ሕሊናን አነጋግሯል፡፡

ሪፖርተር፡- ምግብ ነክ በሆኑ ዘመናዊ አገልግሎቶች ዙሪያ የሚሠራ፣ የጥራት ደረጃ ይዘታቸውን የሚመዝንና ማረጋገጫ የሚሰጥ ሁለት ኩባንያዎች አሏችሁ፡፡ ስለኩባንያዎቹ የሥራ እንቅስቃሴ ብትነግሪን?

ወ/ሮ ሕሊና፡- ብሌስ አግሪ ፉድ ላብራቶሪ በሁለት ባለሀብቶች የተቋቋመ ድርጅት ነው፡፡ በኢትዮጵያውያን ባለሀብቶችና በፈረንሳይ ባለሀብቶች የተቋቋመ ነው፡፡ ሕሊና ገምቢ ምግቦች ማምረቻ የሚባልም ሌላ ኩባንያ አለን፡፡ ሕሊና ገቢ ምግቦች የሕፃናት ገምቢ ምግቦችን በማምረት የሚታወቅ ነው፡፡ በምግብ እጥረት በተጎዱ፣ በድርቅ ወይም በተለያዩ ችግሮች በምግብ እጥረት ሰውነታቸው ለተጎዱ ሕፃናት እንዲያገግሙ የሚያደርግ ምግብ ነው የምናመርተው፡፡

ከዚህም በሕሊና ገንቢ ምግቦች ማምረቻ ‹‹ጣፎ አዮዳይዝድ ጨው›› በማምረት ወደ ገበያ አስገብተናል፡፡ ምርቱ ከሌሎች አዮዳይዝድ ምርቶች የተለየ ነው፡፡ ለምሳሌ ብዙ ጊዜ በሬስቶራንቶች የሚቀርብልን የገበታ ጨው መያዣ ውስጥ ሩዝ ይከታል፡፡ ጣፎ አዮዳይዝድ ጨው ግን ይህ እንዳይከሰት በሚረዳ አሠራር የተዘጋጁ በመሆኑ ያለ ምንም ችግር መነስነስ ያስችላል፡፡ በሕሊና ገምቢ ምግቦች ማምረቻ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ እየተመረተ ያለው ሌላው ምርት ደግሞ የተለያየ ጣዕም ያላቸው የተቆሉ ለውዞችን ነው፡፡ ሕሊና ከቀድሞው ጀምሮ ትኩረት ሰጥቶ ሲሠራበት የቆየው የምግብ ደኅንነት የተመሠረተ አገልግሎት በመሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ባላቸው የጥራት ደረጃ የተለያዩ ምርቶችን ያመርታል፡፡ ገምቢ ምገቦቹ ደግሞ ትንሽ ባክቴሪያ ካለበት ሊገላቸው ይችላል፡፡ ስለዚህ እንጠነቀቃለን፡፡

ሪፖርተር፡- የእነዚህ ምርቶች ዋነኛ የገበያ መዳረሻ የት ነው? በቂ ገበያ አላቸው?

ወ/ሮ ሕሊና፡- ዋና ገበያችን የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎች ናቸው፡፡ እነሱ የእኛን ምርት ተረክበው ያሰራጫሉ፡፡ ይህንን ምግብ በጣም ለተጎዱ ሕፃናት የሚሰጡ በመሆኑ በጥንቃቄ መመረቱንም ያረጋግጣሉ፡፡ የኛ አመራረት ዘዴ በአውሮፓ ቁጥጥር መሠረት የሚመረት ነው፡፡ በአውሮፓ የምግብ ጥራት ደረጃን ይዘን የምንሠራው በመሆኑ ምርቶቻችንን በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚታወቅ ላብራቶሪ አስመርምረን ማረጋገጫ ካገኘን በኋላ ነው ምርቱን የምንጠቀመው፡፡ ይህን ሒደት ደግሞ የራሳችን ላብራቶሪ እንድናቋቁም በመገፋፋቱ ብሌስ አግሪ ፉድ የላብራቶሪ አገልግሎት የሚባለውን ኩባንያ እንድናቋቁም አድርጎናል፡፡ ምክንያቱም በየሳምንቱ የምናመርተውን  ምርት በእርግጥም በሚፈለገው ደረጃ መመረቱን ለማረጋገጥ በታወቀ ላብራቶሪ መመርመር ነበረበት፡፡ ምርመራው የሚካሄደው ደግሞ ከኢትዮጵያ ውጭ ልከን ነው፡፡ ይህንን በተደጋጋሚ ማድረጉ ከፍተኛ ወጪ ይጠይቀን ነበር፡፡ ጊዜም ይወስዳል፡፡ ለሽያጭ ያዘጋጀውን ገምቢ ምግብ ለመሸጥ የምንልከው ናሙና ማረጋገጫ አግኝቶ ለመምጣት አንድ ወር የምንጠብቅበት ጊዜ ነበር፡፡ ለምርመራው የምንከፍለውም ገንዘብ ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ በውጭ ምንዛሪ የሚከፈል ነው፡፡ ይህ ሒደት በጣም እየከበደን ስለመጣ የራሳችን የሆነ አንድ አነስተኛ ላብራቶሪ አቋቋምን፡፡ በዚህ አነስተኛ ላብራቶሪ እየሠራን እያለ ሥራውን በደንብ እየለመድን በመምጣታችን በከፍተኛ ኢንቨስትመንት ብሌስን ወደ ማቋቋም ገባን፡፡

ሪፖርተር፡- እናንተ ባደራጃችሁት በላብራቶሪ የምታደርጉትን ምዘና ገዥዎቻችሁ ተቀበሉት?

ወ/ሮ ሕሊና፡- አዎ፡፡ ወደ ሥራ ከመግባታችን በፊት በርካታ ሥራዎችን ሠርተን ዕውቅናም አግኝተናል፡፡ የኛ ምርት ውጤት ዋነኛ ገዥው ዩኒሴፍም ይህንን አረጋገጠልን፡፡ ራሳችንን አስፈትሸን ISO 17025 ሰርተፍኬት አገኘን፡፡ ለራሳችን ብለን የጀመርነው የላብራቶሪ ሥራ ያስገኘውን ውጤት ስናይ ደግሞ ሌሎች የአገራችን የኤክስፖርተሮች፣ የምግብ ድርጅቶች አስመጪዎችም የሚልኩትንም ሆነ የሚያስመጡትን ምግብ ነክ ምርት የጥራት ደረጃ በትክክል የሚመዝንላቸው ተቋም በአገር ውስጥ ባለመኖሩ እንደሚቸገሩ ተረዳን፡፡ ስለዚህ ይህንን የላብራቶሪ አገልግሎት ሌሎች የኢትዮጵያ ኩባንያዎች እንዲጠቀሙበት እናደርግ ወደሚል ሐሳብ ገባን፡፡ በዚሁ ሐሳብ መነሻነት አንድ ራሱን የቻለ ኩባንያ ብናቋቁም ለራሳችንም ለሌሎችም ያገለግላል በሚል ብሌስ አግሪ ፉድስ ላብራቶሪን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገባ፡፡ ብሌስ የምግብና ፍተሻ የሚሰጥ ተቋም ነው፡፡ የተለያዩ የምግብ ፍተሻዎችን ያደርጋል፡፡ ፍተሻው የተለያዩ ዘርፎች ያሉት ሲሆን፣ በኬሚካል ዘርፍ ፕሮክሲሜት የሚባሉን እንደ ፋት፣ ፕሮቲን ይዘት አሸ ሃበርና የመሳሰሉትን ይመረምራል፡፡ ምግቦች ምን ያህል የቶክሲክ መጠን አላቸው የሚለውን እንደ ቡና፣ በቆሎ፣ ለውዝና የመሳሰሉ ምርቶች ላይ ምርመራ ይሰጣል፡፡ በማይክሮ ባዮሎጂ ዘርፍ ደግሞ የምግብ ደኅንነትን ለመመስከር የሚያበቃ ምርመራ ማድረግ ነው፡፡ አንድ ምግብ ተበክሏል አልተበከለም ብሎ በመፈተሽ የሚያረጋገጥ ነው፡፡ ብሌስ ላብራቶሪ የራሱ የሆነ ሥልጠና ተቋም አለው፡፡ ይህ ሥልጠና ተቋም በፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ቅድመ ዕውቅና አግኝቷል፡፡

ሪፖርተር፡-  ላብራቶሪው ሲቋቋም የኔዘርላንድ መንግሥት ድጋፍ አድርጓል፡፡ ያረገው ድጋፍ ምንድን ነው?

ወ/ሮ ሕሊና፡- የኔዘርላንድ መንግሥት የኛን ሐሳብ በጣም ስለደገፈውና በተለይም ኢትዮጵያ አግሪካልቸራል ኢኮኖሚ ሥርዓትን የምትከተል ስለሆነች፣ ግብርናውን ሊደግፍ የሚችል ተቋም ይሆናል ብሎ ስላመነበት 750 ሺሕ ዩሮ ስጦታ ሰጥቶናል፡፡ በዚህ ስጦታና ባለአክሲዮኖቹ ተጨማሪ ገንዘብ ባለአራት ፎቅ ሕንፃ አስገንብተን  ይህንን ላቦራቶሪ ማቋቋም ችለናል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ላቦራቶሪ ምን ያህል ኢንቨስት ተደርጎበታል?

እስካሁን ወደ 80 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል፡፡ ከዚሁ ላብራቶሪ ጋር የተዋቀረው ተያያዥ ማሠልጠኛ ተቋም ደግሞ 32 ሚሊዮን ብር ወጥቶበታል፡፡ ይህ ማሠልጠኛ ተቋም እንደሌላው ማሠልጠኛ ወንበርና ጠረጴዛ ብቻ ሳይሆን ያለው ራሱን የቻለ የምርምር ተቋም ነው፡፡ ብዙ መሣሪያዎች አሉት፡፡ ዲጂታል ላይብረሪ አለው፡፡ ብሌስ ከፍተኛ መዋለ ነዋይ የፈሰሰባቸው የላብራቶሪ መሣሪያዎችን አስገብቷል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እኛ ጋር ብቻ የሚገኙ መሣሪያዎችን ጭምር ያካተተ ነው፡፡ በተለይ አንድ ምርት የፔስቲሳይድ ቅሪት አለው ወይ? የሚለውን ለማወቅ ለምሳሌ አበባ ወይም ሌላ ምግብ ነክ ምርት ፔስቲሳይድ ቅሪት እንዳለውና እንደሌለው የሚለይ መሣሪያ አለን፡፡ ይህ የእኛን ምርት የሚገዙ እንደ ጃፓን አሜሪካና አውሮፓ አገሮችን ያሳስባል፡፡ ቡናና ማር ላይ ያሳስባቸዋል፡፡ የዚህ ማረጋገጫ ካልተሰጣቸው አይገዙም፡፡ አሁን ይህን ማረጋገጫ እኛ ጋር በመሆኑ ለአገር ትልቅ ጥቅም ነው፡፡ በሌሎችም ምርቶች ላይ ተመሳሳይ ፍተሻና ማረጋገጫ የሚሰጡን መሣሪያዎች አሉን፡፡ በቅርቡም ሌሎች መሣሪያዎችን እናስገባለን፡፡ እነዚህ መሣሪያዎችን በእጃችን ካስገባን ላብራቶሪያችን ተወዳዳሪና ዓለም አቀፍ ተቋም ወደ መሆን ደረጃ ያሸጋግረዋል፡፡ ይህ የአገር ሀብት እንደማለት ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- ወደ ውጭ የሚላኩ ምግብ ነክ ምርቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚታወቅ ምዝና ተቋም ማረጋገጫ ካልተሰጠው በተለይ እንደ አውሮፓና አሜሪካ ያሉ አገሮች ምርቱን ላይቀበሉ ይችላሉ፡፡ እናተ የሕሊና ምግቦችን ለመሸጥ የጥራት ደረጃውን ለማስመርመር የሚወጣው ወጪ ምን ያህል ነበር?

ወ/ሮ ሕሊና፡- ብዙ ነው፡፡ ለምሳሌ እኛ በየሳምንቱ ምርቱን ከመላካችን በፊት ትክክለኛነቱን ለማስፈተሽ ወደ ውጭ ላብራቶሪዎች እንልክ ነበር፡፡ ለዚህም እንደየምርት ዓይነት ከ30 እስከ 140 ዶላር እንከፍላለን፡፡ ይህም በዓመት ከ30 ሺሕ ዶላር በላይ ያስከፍለን ነበር፡፡ አሁን ግን እዚህ ባለው ላብራቶሪ በመጀመሩና ማረጋገጫ ማግኘቱ በውጭ ምንዛሪ እናወጣ የነበረውን ወጪ አስቀርቶልናል፡፡

ሪፖርተር፡- እናንተ ለሌሎች የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ለምትሰጡት የላብራቶሪ ምርመራ ምን ያህል ታስከፍላላችሁ?

ወ/ሮ ሕሊና፡- የኛ ክፍያ ውጭ ከሚመረመርበት በግማሽ ያነሰ ነው፡፡ የምናስከፍለው ደግሞ በብር በመሆኑ አገልግሎቱን የሚያገኙ ድርጅቶች በውጭ ምንዛሪ ይወጣ የነበረውን ገንዘብ ያድናል፡፡ ምርመራውን ለማካሄድ ለናሙና መላኪያ ያወጣ የነበውንም ወጪ ያስቀርለታል፡፡ በተለይም ውጭ የተላከው ናሙና ተፈትሾ እስኪመጣ ጊዜ ይወስዳል፤ ይህም ሌላ ጥቅም ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እንደዚህ በላብራቶሪ ምርመራ የሚከናውን ሌላ ተቋም አገር ውስጥ አለ?

ወ/ሮ ሕሊና፡- በግል ደረጃ ምንም የለም፡፡ አፍሪካ ውስጥም በሁለት አገሮች የሚገኝ ነው፡፡ እኛም ይኽንን አስበን ነው ከፍተኛ ኢንቨስትመንት በማድረግ ወደ ሥራ የገባነው፡፡ ያወጣነውን ኢንቨስትመንት እንደሌላው ዘርፍ ወዲያው የሚመልስ አይደለም፡፡ ጊዜ ይወስዳል፡፡ ኢንቨስተሮችም ወደ ዘርፉ ለመግባት ትንሽ ሊከብዳቸው ይችላለ ብዬ የምገምትበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው፡፡ ኤክስፐርቲዝሙም በጣም ከባድ ነው፡፡  የኔዘርላንድ መንግሥትና የባለአክሲዮኖቻችን ዕርዳታ ባይኖር ለኛም ሊከብደን የሚችል ዘርፍ ነው፡፡ ሥራው ጥንቃቄና ብቃትን የሚጠይቅ በመሆኑ፣ እኛ በዘርፉ ለመሥራት ካለን ፍላጎት አንፃር የገባንበት ነው፡፡ ሥራው በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሠራ በመሆኑ ሠራተኞቻችን ኔዘርላንድ እንዲሠለጥኑና ጥሩ ክህሎት እንዲያገኙ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- ከገለጻው ለመረዳት እንደቻልኩት ላብራቶሪያችሁ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ባላቸው መሣሪያዎች ከመደራጀቱም በላይ እናንተ መርምራችሁ የምትሰጡት ውጤትም በየትኛውም ዓለም ተቀባይነት ያለው መሆኑ ነው? ከዚህ አንፃር የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ምን ያህል እየተጠቀሙበት ነው? ያሰባችሁበትን ያህል መጓዝ ችላችኋል?

ወ/ሮ ሕሊና፡- እንዳልኩህ ስንነሳ ቢዝነስ ፕላኑ እንሚያሳየው ቀስ እያለ እያገ የሚሄድ ቢዝነስ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ተቋሞች ላደጉ ኢኮኖሚዎች በጣም ይጠቅማል፡፡ ይህ ተቋም እያደገ ላለ ኢኮኖሚ ቀድሞ የሚገኝ ነው፡፡ እኛ አሁን ቀድመን የተገኘን ነን ልል እችላለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ደግሞ በፍጥነት እያደገ በመሆኑ የኛን አገልግሎት እየደረሰበት ነው ልል እችላለሁ፡፡ ላብራቶሪውን በኬሚስትሪ በኩል ለምሳሌ በቶክሲክ በርካታ ይዘቶችን እንፈትሻለን፡፡ አንድ ምግብ ባጠቃላይ የምግብ ይዘቱ የምንፈትሽበት እጅግ ዘመናዊ በሆኑ መሣሪያዎች የተደራጀ ነው፡፡ የፋትና የፕሮቲን ይዘት መለካት ላይ በጣም እየሠራን ነው፡፡ የምግብ ደኅንነትን የተመለከተው ሥራ ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ገና ነው፡፡ የምግብ ደኅንነት ፋሲሊቲያችን የምንጠብቀውን ያህል ደንበኛ የለንም፡፡ እዚህ ላይ ኅብረተሰቡ ግንዛቤ ሊኖረው ይገባል፡፡ ምግብ ደኅንነትን መጠየቅ አለበት፡፡ ጥራት ላለው ምግብ የሚገባውን የመክፈል ፈቃደኝነት ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህ ፈቃደኝነት በኅብረተሰቡ ውስጥ ከሌለ ድርጅቶችም ምርቶቻቸውን ለማስፈተሽና የጥራት ደረጃቸውን ለመጠበቅ አይገፋፋም፡፡ ምክንያቱም ወጪው ቀላል አይደለም፡፡ ኅብረተሰቡ በትክክል የጥራት ደረጃዎች የሌላቸው ምርቶች ሊያስከትሉ የሚችሉትን ጉዳት ከተረዳ ግን መጠየቅ ይጀምራል፡፡ ይኽም ጥያቄ የሚቀርቡለት ምርቶች የጥራት ደረጃቸው የተጠበቀ ስለመሆኑ አረጋግጡልኝ በማለት ወደ ማስገደድ ይገባልና ግንዛቤው በኅብረተሰቡ ውስጥ መስረጽ አለበት፡፡ ስለዚህ ጥያቄውን ማቅረብ ያለበት ኅብረተሰቡ ነው፡፡ የጥራት ደረጃውን ይዞ ለሚመጣ የተሻለ ለመክፈል ፈቃደኛ መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ የምግብ ደኅንነት አሁን አስገዳጅ ነገሮች እየመጡበት አስገዳጅ ደረጃ እየሰጠ ስለሆነ ለውጥ ሊመጣ ይችላል፡፡  

ሪፖርተር፡- እንደው አሁን ኅብረተሰቡ በእምነት እየሸመቱ የሚጠቀምባቸው የተለያዩ ምግብ ነክ ምርቶች በትክክል ደረጃቸውን የጠበቁ ናቸው?

ወ/ሮ ሕሊና፡- ደረጃቸውን የጠበቁ ናቸው ማለት አንችልም፡፡ ለምሳሌ አንድ ምርት አሜሪካና አውሮፓ ችግር አስከትሎ ዘጠኝ አሥር ሰዎች ሲሞቱ እንደ ትልቅ ጉዳይ ነው የሚታየው፡፡ እንዲህ ባለ ምክንያት የሚፈጸም ጉዳት ሊኖር ይችላል፡፡ እኛ ጋር ግን ጉዳቱ የደረሰበትን ምክንያት አናውቅም፡፡ ለዚህ ነው ኅብረተሰቡ ማወቅ አለበት የምንለው፡፡ ድርጅቶችም ተጠያቂነት መውሰድ አለባቸው፡፡ የኅብረተሰቡ ደኅንነት ስለሚመለከታቸው የድርጅታቸውን ሠራተኞች ማሠልጠን አለባቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ መሠረታዊ ኃይጂን መሟላት አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- የዚህ የላብራቶሪ አገልግሎት በአገር ውስጥ ያለው ዕውቅና ምን ድረስ ነው? እንደ ደረጃዎች መዳቢ ኤጀንሲ በአገር ውስጥ ያሉ ምርቶችን የማረጋገጥ ዕድል አውጥታችኋል?

ወ/ሮ ሕሊና፡- ብሌስ ዕውቅና ያለውና ለዚህ ሥራ ዕውቅና የተሰጠው ተቋም ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ማነው ማረጋገጫ የሰጣችሁ?

ወ/ሮ ሕሊና፡- ሳናስ የተባለና መቀመጫውን ደቡብ አፍሪካ ያደረገ ተቋም ይህንን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ብቃት ማረጋገጫ ሰጥቶናል፡፡ ይህ አክሪዲቴሽን ደግሞ አገሮች የአቻ ዕውቅና ስምምነት በሚባል የተፈራረሙበት ሰነድ አለ፡፡ የዚህ ሰነድ ፈራሚ የሆነች አገር በኛ ላብራቶሪ ተመርምሮ ማረጋገጫ ሰርተፍኬት የተሰጠውን ምርት ለመቀበል ግዴታ አለበት፡፡ ለምሳሌ በብሌስ የተመረመረ ምርት ጃፓን ደግማ ላትፈትሸው ትችላለች፡፡ በኛ አረጋጋጭነት የተሰጠን ሰርተፍኬት መቀበል አለበት ማለት ነው፡፡ የስምምነቱ መሪ ቃል ራሱ ‹‹ዋንስ ቴስትድ ኤክስፔክትድ ኤቭሪዌር›› የሚል ነው፡፡ አንዴ ከተመረመረ በየትኛውም አገር ተቀባይነት አለው፡፡ ይህ ስምምነት ዕውቅና ከተሰጣቸው እንደ ብሌስ ባሉ ተቋማት የተሰጠ ምርመራና ማረጋገጫ በድጋሚ እንዳይደረግ ለማድረግ ጭምር ነው፡፡ እኛ በግል ከምንሠራው ሥራ ባሻገር አሁን የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ የሚሠራቸውን ሥራዎች ለመሥራት ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ጋር እየተነጋገርን ነው፡፡ ከዚህ ቀደም እሱ ብቻ የሚሠራው ሥራ ነበር፡፡ በብቸኝነት ይሠራው የነበረውን ይህንን ሥራ ብሌስም አሁን ዕውቅና ያለው ድርጅት ስለሆነ ከደረጃዎች ኤጀንሲ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሞ ብሌስ ዕውቅና ባገኘባቸው ምርመራዎች አገልግሎቱን ለመስጠት እንዲቻል ለማድረግ ነው፡፡ ይህም በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- አንድ ኩባንያ በእናንተ አስመርምሮ ማረጋገጫ ያገኘበት ምርት ለምሳሌ ቡና ቢሆን ተቀባዩ አገር እንዴት ሊቀበለው ይችላል?

ወ/ሮ ሕሊና፡- ቡና የሚልክ ወይም ሌላ ማንኛውም ላኪ እኛ ጋር አስመርምሮ ቢላክ ሰርተፍኬታችን ላይ የአይላክ ኢንተርናሽናል አክሬዲቴሽን ኮርፖሬሽን ዓርማ ሰርተፍኬታችን ላይ ስላለ፣ ይህንን ዓርማ ሲያይ ምርት ተቀባዩ አገር ይቀበላቸዋል፡፡  ሰርተፍኬታችን ላይ የአይላክና ሰናስ ዓርማ አለ፡፡ ይህንን ዓርማ ማስቀመጥ ግዴታችን ነው፡፡ ይህንን የኛን ሰርተፍኬት ይዞ የወጡ ማንኛቸውም ድርጅቶች ሌላም አገር ተቀባይነት አላቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ከፍተሻው ባሻገር ሥልጠና ተቋሙ በተለየ የምንሠራበት ነው ብለሻል፤ የተለየ የሚያስብለው ምንድን ነው?

ወ/ሮ ሕሊና፡- ሥልጠናው የአጭር ጊዜ ሥልጠና ሆኖ በኒውትሬሽን ዙሪያ ያሉ ሥልጠናዎችን ለምሳሌ ከሁለት እስከ ሦስት ሳምንት የሚደርሱ ሥልጠናዎችን ነው የሚሰጠው፡፡ የኛ ሥልጠና ለየት የሚያደርገው ከኛ የወጡ ሠልጣኞችን ሥራ ፈጣሪዎች ማድረግ ነው፡፡ ለምሳሌ የመጀመርያ ሥልጠናችን የአኩሪ አተር ፕሮሰሲንግን የሚመለከት ነው፡፡ ሶያን በመጥቀም ወይም የተለያዩ ቴክኒኮችን በመጠቀም የአኩሪ አተር ወተት፣ ዓይብ፣ ዱቄትና የመሳሰሉትን ምርቶች መሥራት የሚያስችል ነው፡፡ በዚህ የሠለጠነ ሰው በአጭር ጊዜ ውስጥ በአኩሪ አተር በሚሠሩ እንደ ወተት ያሉ ምርቶችን አቀነባብሮ ለአካባቢው ሱፐር ማርኬት ማቅረብ ያስችላል፡፡ አስተሻሸግና ተያያዥ ሥራዎችን የሚያጠቃልል በመሆኑ፣ በምን ዓይነት ሁኔታ ወተት መታሸግ እንዳለበት የምግብ ይዘቱን ሳይቀንስ እንዴት መታሸግ እንደሚኖርበት ተግባር ጭምር የሚያሳይ በመሆኑ በምግብ ነክ ምርቶች ዙሪያ የተለየ ሥልጠና የምንሰጥበት ይሆናል፡፡ ይህንንም ልናረጋግጥበትና በተግባር ትምህርቱን ለመውሰድ የሚያስችል የራሳችን ቴስት ኪችን አለን፡፡ ኪችን አሠልጣኞቻችን የሚያሳዩበት ሠልጣኞች ሙከራ የሚያደርጉበት ነው፡፡ እያንዳንዱ የሙከራ ሥራም ለዚህ ሥራ በተቀጠሩ ቀማሾች ይከናወናል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሥልጠና በዋናነት ለዳቦ ቤቶች፣ ለእንጀራ አቅራቢዎች፣ ለዱቄት አምራቾችና ለመሳሰሉት ይጠቅማል፡፡ መጠኑን የጠበቀ ኒውትሬሽኑንና ዋጋንም ያገናዘበ ዱቄት እንዲያዘጋጁና እንዲጠቀሙ ያስችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ዋጋን እንዴት ያገናዘበ ይሆናል?

ወ/ሮ ሕሊና፡- ዋጋን ያገናዘ ስንል በገበያ ላይ የትኛው ምርት ነው ውድ? የትኛውን እህል ከየትኛው ተደባልቆ ነው የምንፈልገውን እንጀራ ወይም ዳቦ የሚያመርተው? በማለት ዋጋውን ጭምር በማስላት እንዲሠሩ ያስችላሉ፡፡ ሥልጠናውም በሙያው ልምድ ባላቸው ኒውትሬሽኖችና በሆሚ ኢኮኖሚስቶች የሚሰጥ ነው፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች የኢትዮጵያ ኒውትሬሽን ኢንስቲትዩት በመባል ይታወቅ በነበረው ተቋም ውስጥ ሲሠሩ የነበሩ ናቸው፡፡ ይህንን ሥልጠና ወደ ሥራ ስናስገባም ያንን ተቋም እንደገና እንመልሰዋለን ብለን በማሰብ ነው፡፡ የእኛ ሥልጠና የላብራቶሪው ቴስቲንግ ኪችኑ መኖር ደግሞ የተለየ ያደርገናል፡፡ ለሠልጣኙም ትርጉም ያለው ሥልጠናችን በዚህ ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡ ምን መብላት እንዳለብን፣ ዕድሜው የገፋ ወይም በተለያዩ በሽታዎች የተጠቃ ሕመምተኛ ካለ በአጭር ጊዜ ሥልጠና ምን መመገብ እንዳለበት እንዴት ማዘጋጀት እንደሚችል ሁሉ ሥልጠና የሚሰጥበት ነው፡፡ ለምሳሌ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ፉድ ሳይንስ ኒውትሬሽን ዲፓርትመንት አለ፡፡ ግን ኒውትሬሽን ብዙ ትኩረት አያደርግበትም፡፡ ስለዚህ እኛ ይህንን ክፍተት ነው መድፈን የምንፈልገው፡፡ የሆቴል የሬስቶራንት ማናጀሮች በምግብ ደኅንነት ማሠልጠን እንፈልጋለን፡፡ በዚህ ረገድ የሆቴሎች ማናጀሮችን ማሠልጠንም እናካትታለን፡፡

ሪፖርተር፡- ሥልጠናችሁን በዚህን ያህል ረገድ መስጠታችሁ ሊሰጥ የሚችለው ውጤት ወይም ጠቀሜታ ምንድን ነው?

ወ/ሮ ሕሊና፡- ብዙ ጠቀሜታ አለው፡፡ ሆቴሎች ከሆኑ እንዲህ ዓይነቱን ሥልጠና ተጠቃሚዎች ያደርጋሉ፡፡ በሌላ አንፃርም ለቱሪስቶች ደኅንነት ጭምር ይጠቅማል፡፡ አዳዲስ ምግቦችን መፍጠር ለሚፈልግም የሙከራ ሥራ የሚሠራበት መሣሪያዎችም አሉ፡፡ ሌሎች የሥልጠና ዘርፎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ጤፍን እንውሰድ አሁን ጤፍ እየተወደደ ነው፡፡ እንጀራ ከጤፍ፣ ከማሽላ፣ ከሌሎች ምርቶች ጋር በመደባለቅ በመጨመር ወይም የተለያዩ እህሎችን በመጨመርና በማደባለቅ የእንጀራ የምግብ ይዘቱን ሳይቀንስ ማዘጋጀት ይቻላል፡፡ የተለያዩ ሰብሎችን በመደበላለቅ እንጀራ ወይም ዱቄት ለማውጣት የሚያስችል የተለየ ሥልጠና ይሰጣል፡፡  

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች