Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትከንግግር በላይ የሆነ የፀረ ሽብር ሕግና ትግል የለም

ከንግግር በላይ የሆነ የፀረ ሽብር ሕግና ትግል የለም

ቀን:

በመንግሥቴ አወቀ

ድህነታችንን የአገራችን ቀንደኛ ጠላት አድርገን ከሰየምን ቆየት ብለናል፡፡ በድህነትና በኋላቀርነት ላይ የሚደረገው ጦርነት ዋነኛ ግንባር ደግሞ ልማትና ዕድገት ነው፡፡ ልማት የሙሉ ጊዜ ሥራችን ነው፡፡ የዚህ ዋነኛና የሙሉ ጊዜ ሥራችንም ቅድመ ሁኔታው ዘላቂ ሰላም ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ ነው ብለን የተፈጠምነው ደግሞ፣ መጀመሪያ በ1983 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የሽግግሩ ቻርተር፣ ኋላም ደግሞ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የፖሊሲ መንደርደሪያዎችና መግቢያዎች ላይ ነው፡፡

ልማታችን ሰላማዊ ሁኔታዎችን ይጠይቃል፡፡ ዘላቂ ሰላም ያስፈልገዋል፡፡ ሰላም ማለት ደግሞ ካብ ለካብ በሚተያዩ ቡድኖችና የሕዝቡ ክፍሎች መካከል የሰፈነ ዝምታ ወይም ፀጥታ አይደለም፡፡ የሕዝብ ቅሬታዎች፣ የፖለቲካ አለመግባባቶችና ጠቦች እንደ ቀድሞው ወደ ጠመንጃ የሚሄዱበት ዕድል እየጠበበና እየተዘጋ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መስተንግዶና ስብስቦች እየሰፉ መሄድ አለባቸው፡፡ በአጠቃላይም የእፎይታና የእሰይታ እንዲሁም የአዲስ አገር ግንባታ ሥነ ልቦናዊ ድባብ መፈጠር አለበት፡፡

እነዚህ እርስ በርስ እየተጋገዙ አገሪቷ ቀንደኛ ጠላቷን ድህነትን ማሸነፍ ትችላለች፡፡ ሰላም በሌለበት አገር ጦርነት የመንግሥትን፣ የአገርንና የሠራተኛውን ሕዝብ ሀብት፣ ጉልበትና ጊዜ በሚጋራበትና በሚያዘናጋበት አገር ልማት የሙሉ ጊዜ ሥራ ሊሆን አይችልም፡፡ ዴሞክራሲ ከልማትና ከዕድገት በኋላ ብሎ ነገርን የዛሬው ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ውድቅ አድርጐታል፡፡ ሰላምና ዴሞክራሲ የልማቱ ቅድመ ሁኔታ የመሆኑን ያህል፣ ልማቱ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ እሴቶችን ከግንጥል ጌጥነት ይልቅ የምንገነባው ሥርዓት እስትንፋስ እንዲሆን ያደርጋሉ፡፡

የልማትና የዕድገት ነገር ሊሳካልን ቀርቶ ከረሃብ የመዳን ጥያቄ በአገራችን ዋናው ጉዳይ እስከመሆን የገዘፈውና የአገርም የህልውና ጥያቄ ሆኖ የቆየው፣ በሰላምና በዴሞክራሲ ችግር ምክንያት ነው፡፡

የአንድ አገር ሕዝብ ለዕድገትና ለልማት ቅድመ ሁኔታ የሆነው (በገዛ ራሱ ምክንያትም ግብ ሆኖ የሚያገለግለው) እና ሰላም የሚገኘው የአገር ውስጥ ፀብ አጫሪዎች በሙሉ ታድነው ሲያዙ ወይም መናገሪያ መተንፈሻቸው በሰላይና በፖሊስ ሲዘጋ ሊሆን እንደማይችል፣ ቢያንስ ቢያንስ የቅድመ ኢሕአዴግ ታሪካችን ያስመሰከረውና ያረጋገጠው ጉዳይ ነው፡፡

ሰላምን ከሚያናጉ፣ የዴሞክራሲን መሠረት ከሚሸረሽሩና ልማትን ከሚያደናቅፉ ወቅታዊ ችግሮች መካከል አንደኛው አሸባሪነት ነው፡፡ ድኅረ ቀዝቃዛው ጦርነት በተስፋ መቁረጥ ላይ የተመሠረተው፣ በዚያው ላይ የፋፋውና የተስፋፋው ዓለም አቀፋዊ ሽብርተኝነት በአሜሪካ የሚመራውን በአሸባሪነት ላይ የሚደረግ ጦርነት (War on Terror) አስከትሎ የዓለም ዋና ጉዳይ እሱው እስከመሆን ደርሷል፡፡ ከዚህም የተነሳ ከሞላ ጎደል መላው ዓለም በአሻባሪነት ላይ ትብብር ፈጥሯል፡፡

አሸባሪነት ወንጀል ነው፡፡ የአሸባሪነት ድርጊት ለምሳሌ የኢትዮጵያ የአሸባሪነት ሕግ እንደሚተረጉመው የሃይማኖታዊ ወይም የአይዲዮሎጂ ዓላማን ለማራመድ በማሰብ፣ በመንግሥት ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር ኅብረተሰቡን ወይም የኅብረተሰቡን ክፍል ለማስፈራራት፣ ወይም የአገሪቱን መሠረታዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ሕገ መንግሥታዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወይም ማኅበራዊ ተቋማትን ለማናጋት፣ ወይም ለማፍረስ በሕጉ የተዘረዘሩትን ድርጊቶች መፈጸም ነው፡፡

ሰው መግደል፣ በሰው አካል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረስ፣ የኅብረተሰቡን ወይም የኅብረተሰቡን ክፍል ደኅንነት ወይም ጤና ለከፍተኛ አደጋ ማጋለጥ፣ እገታ ወይም ጠለፋ መፈጸም፣ ወዘተ ራሳቸውን የቻሉ የወንጀል ድርጊቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ድርጊቶች ብቻቸውንና በገዛ ራሳቸው የአሸባሪነት ወንጀሎች አይደሉም፡፡ ሰው መግደል የአሸባሪነት የወንጀል ድርጊት የሚሆነው ሰውየው ወይም ቡድኑ ሰው የገደለው የፖለቲካ ወይም የሃይማኖታዊ ወይም የአይዲዮሎጂ ዓላማን ለማራመድ በማሰብ፣ በመንግሥት ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር፣ ኅብረተሰቡን ወይም የኅብረተሰቡን ክፍል ለማስፈራራት፣ ወይም የአገሪቱን መሠረታዊ ፖለቲካዊ፣ ሕገ መንግሥታዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወይም ማኅበራዊ ተቋማትን ለማናጋት፣ ወይም ለማፍረስ የተፈጸመ ግድያ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ነው ጀርመናዊው ረዳት ፓይለት አንድርያስ ሉቢትስ ዋናውን ፓይለት አስወግዶ 149 መንገደኞችን የያዘውን አውሮፕላን ሆን ብሎ ፈጥፍጦ ያስከተለው ዕልቂት የአሸባሪነት ድርጊት ያልተባለው፡፡

ኢትዮጵያ የአሸባሪነት ድርጊት ሰለባ መሆን የጀመረችው እ.ኤ.አ. ከመስከረም 11 ቀን 2001 ወዲህ አይደለም፡፡ ኦሳማ ቢን ላደን ሱዳን ላይ ሆኖ ይንቀሳቀስ በነበረበት፣ እዚያውም በሆስኒ ሙባረክ ላይ የተቃጣው የመግደል ሙከራ መሰናዶና ዝግጅት በተጠነሰሰበት በ1990ዎቹ ነው፡፡

በዚህ ምክንያት የአሸባሪነት ሕግ ማውጣት፣ በአሸባሪነት ላይ መበርታትና ብርቱ ሕግ መቅረፅ ችግር የለውም፡፡ ይልቁንም ተገቢ ነው፡፡ የመንግሥትንም ግዴታ መወጣት ነው፡፡ ምርጫ በመጣ ቁጥር ወይም ጉዳዩን መነጋገሪያ የሚያደርግ አጋጣሚ ሲመጣ፣ ከሚያነጋግሩት ጉዳዮች መካከል አንዱ ግን የፀረ ሽብር ሕጉ ነው፡፡ የፀረ ሽብር ሕጉ ረቂቅ የሕግ ሐሳብ ሆኖ ከቀረበበት ጊዜ ጀምሮና ሕግ ሆኖ ከፀደቀበት እ.ኤ.አ. ከ2001 መጨረሻ ወዲህ አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል፡፡ አሁንም ማነጋገሩን እንደቀጠለ ነው፡፡

በተለይም በዚህ የምርጫ ዓመት ዋናው የመነጋገሪያ ርዕስ መሆኑ ሳያበቃ፣ በሊቢያ ባህር ዳርቻ በግፍና በገፍ በተገደሉት ኢትዮጵያውያን ምክንያት የአሸባሪነት ጉዳይ ደጋፊ ማሰባሰቢያ ተቃዋሚን ማስጠንቀቂያ ሲሆን አይተናል፡፡ ስለዚህም ይህ የ‹‹አሸባሪነት›› ጉዳይ አነጋጋሪ የሆነውን ያህል ግልጽና ነፃ ውይይት ሲደረግበት ማየት አልታደልንም፡፡

በፀረ ሽብር ሕጉ ላይ የሚነገረው አስተያየት አንድ ላይ በአንድ መድረክ በነፃ ሲገለጽ አንሰማም፡፡ በተለይ ከሚያዝያ ወር ሁለተኛው እሑድ በኋላ (2007) የምንሰማው የመንግሥት መከራከሪያ ‹‹አላልናችሁም ነበር?›› ማለት ድረስ የተራዘሙ የተለያዩ ሐተታዎች የተዘጋጁበት ርዕሰ ጉዳይ ሆኗል፡፡

መስማማት የሌለበት፣ አንድ ላይ ተሰባስበው የማይነጋገሩበት፣ ለእኛም ለእናንተም እኛ ብቻ እናውራ እኛ ብቻ እንደመጥበት የሚባልበት አገር ሆነ እንጂ፣ የፀረ ሽብር ሕግ ጨርሶ አያስፈልግም ማለት አይቻልም፡፡

በፀረ ሽብር ሕጉ ላይ የሚቀርበው ትችትና ተቃውሞ መጀመሪያ ሕጉ ቦርቃቃ ነው የሚል ነው፡፡ የዚህ ትርጉም ሕጉ ሁሉንም ነገር በአሸባሪነት ድርጊት ውስጥ ከማካተት የማይመለስ እንደፈለጉት የሚተረጐም ነው ማለት ነው፡፡ አንድ የፀረ አሸባሪነት ሕግ የልማት አውታሮችንና ሰላማዊ ዜጐችን አዘናግቶ በማጥቃት የሽብር ቀውጢ መፍጠርን ገድሉ ያደረገ እንቀስቃሴን ነጥሎ ዒላማው ማድረግ አለበት፡፡ ከዚህ ውጭ ለምሳሌ በሚስጥር መደራጀትን፣ የትጥቅ ትግል፣ ሕጋዊና ሰላማዊ ስብሰባና ሠልፍ ውስጥ የሚከሰት የሕግ ጥሰትን ሁሉ በአሸባሪነት መፈረጅ የሚያስችል ሕግ፣ አሸባሪነትን መካለከልና መዋጋት ይቅርና ራሱ ጥርጣሬንና ፍራቻን ሳብ ለቀቅ እያደረገ የሚያስበረግግ ሕግ ነው፡፡

ለምሳሌ በሚስጥር መደራጀት ግፋ ቢል ወንጀል ነው፡፡ ሌላ ወንጀል ነው እንጂ ሁልጊዜምና ምንጊዜም በአሸባሪነት ወንጀል ተግባር ውስጥ አይፈረጅም፡፡ የመሣሪያ ትግልም አሸባሪነት አይደለም፡፡ ሌላ ወንጀል ነው፡፡ ኢትዮጵያ በአዋጅ ቁጥር 302/1995 ያፀደቀችው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሽብርተኝነትን ለመከላከልና ለመዋጋት የወጣው ኮንቬንሽን፣ ለነፃነትና የራስን ዕድል በራስ ለመወሰን፣ በቅኝ አገዛዝና በወረራ ላይ የሚደረግ የትጥቅ ትግል ጭምር አሸባሪነት አይደለም ይላል፡፡

በነፃ መናገራቸውን የሚያንገራግር፣ በነፃ መሰማታቸውን የሚያደናቅፍ አሠራርና ሥርዓት እንዲለማ ባይበረታታና ባይደመጥ ኖሮ የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉን የሚቃወሙ ወገኖች የክርክር መሠረት፣ አሸባሪነትን የሚከላከልና የሚዋጋ ሕግና ሥርዓት በጭራሽ አይኖርም የሚል አጐልቶና ጠርቶ በተሰማ ነበር፡፡

ተቃውሞ የሚቀርብበት የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ‹‹ሕዝቦች በሰላም በነፃነትና በተረጋጋ ሁኔታ ለመኖር ያላቸው መብት ከሽብርተኝነት አደጋ ሁልጊዜ መጠበቅ ያለበት›› እንዲሁም ‹‹ሽብርተኝነት ለአገራችን ሰላም፣ ደኅንነትና ዕድገት ፀር፣ ለአካባቢያችን፣ ለዓለም ሰላምና ደኅንነትም ከፍተኛ ሥጋት›› መሆኑን ይገልጻል፡፡ እውነት ነው፡፡ ትክልልም ነው፡፡ እኩል የሚያሳስበውና ምናልባትም ከዚያ በላይ የሚያስጨንቀው ደግሞ ሽብርተኝነትን የመዋጊያ የመንግሥት መሣሪያና ሥልት እንዲሁም ሕግ ሕዝብ በሰላም፣ በነፃነትና በተረጋጋ ሁኔታ ለመኖር ያለውን መብት እንዳይረግጥ ነው፡፡

ከዚህ ውጪ አሸባሪነት ወንጀል አይደለም፡፡ አደጋ አይለደም አልተባለም፡፡ እንኳን አሸባሪነት ሰላማዊ ያልሆነ የመሣሪያ ትግልም በዛሬው ዓለም ያረጀና ያፈጀ የትግል ሥልት ሆኗል፡፡ ሰላማዊ ያልሆነ ትግል ሁሉ አሸባሪነት አይደለም ማለት ግን የተባለው ትግል ሕጋዊ ነው ማለት አይደለም፡፡ በኢትዮጵያና በዓለም ተጨባጭ ሁኔታ የመሣሪያ ትግል ወይም ሥልጣን ከጠመንጃ አፈሙዝ ይወጣል የሚል አስተሳሰብ ውድቅ ነው የሚባለው፣ የትግል ሥልቱ ሕገወጥ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን ዛሬ የማያዋጣና የተተፋ ያረጀ ያፈጀ ሥልት በመሆኑ ነው፡፡

አሸባሪነት ደግሞ ከዚህ የባሰ ነው፡፡ የነፃነትና የመብት የትግል ሥልት ሊሆን አይችልም፡፡ ሰዎችን በነሲብ የሚያጠቃው ሽብር በትግል ባህርይው የሰዎችንና የመብታቸውን መከበር የረገጠና የዳጠ በመሆኑ፣ በጭራሽ የዴሞክራሲ አማራጭ ለመሆን አይበቃም፡፡ በዓለም ደረጃ ተቀባይነት ያገኙት አሸባሪነትን የሚዋጉ ስምምነቶች ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ፣ ፍልስፍናዊ፣ ርዕዮተ ዓለማዊ፣ ብሔረሰባዊ፣ ሃይማኖታዊ ወይም ሌሎች የሥር ምክንያቶች ለሽብርተኝነት ድርጊት መከራከሪያና መከላከያ ሊሆኑ አይችሉም የሚሉት በዚህ ምክንያት ነው፡፡

የአሸባሪነት አደጋ ዓለምን እያስቸገረ ነው፡፡ አሸባሪነትን መታገልና መከላከልም ይደር የማይባል በቀጠሮ የማይቆይ ወቅታዊ ተግባርና ግዴታ ነው፡፡ ከዚህ እኩል ደግሞ ፀረ ሽብር ትግላችን ከሽብር ጥቃት የምንከላከለውን፣ የሕዝብን በሰላም፣ በነፃነትና በተረጋጋ ሁኔታ ለመኖር ያለውን መብት እንዳይደቁስ መጠንቀቅና መከልከል አለብን፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የፀረ ሽብር ሕጋችንና የፀረ ሽብር ትግላችን የዴሞክራሲያዊ ፖለቲካ ዋነኛ ባህርይ የሆነውን የትግል ሥልት ማኮላሸት የለበትም፡፡ በተለይም ሰላማዊ የሐሳብ ትግል በተቀናቃኞች መካከል እንዳይካሄድ የሚያደርግ፣ የተለያየና ተቃራኒ ሐሳብ ያላቸው የተቃዋሚዎች ትግል በሰላማዊ ክልል ውስጥ እንዳይቆይ የሚከለክል አሠራር መገንባት የለበትም፡፡ የፀረ ሽብር ሕጉና ትግሉም መጀመሪያ ከውይይት በላይ መሆን የለበትም፡፡ ውይይትን ከልክሎና አፍኖ የፀረ ሽብር ሕጉ ሊከላከለው የፈለገውን አደጋ ራሱ መልሶ መፍጠር አይገባውም፡፡

የዛሬ አርባ ዓመት የነበረው የፖለቲካዊ ትግል ባቋቋመው ወግ መሠረት ‹‹ታጋይ ይሞታል እንጂ ትግል አይሞትም›› ይባል ነበር፡፡ ይህን የሚለው ሰላማዊና ሕጋዊ ትግል የማያውቀው ደመ  ነውጠኛ ትግል ነው፡፡ በሰላማዊ ትግል ውስጥ ታጋይ በጭራሽ አይሞትም፡፡ ደመ ነውጠኛው ትግል ደግሞ መሞት አለበት፡፡ ደመ ነውጠኛ ትግልም፣ አሸባሪነትም የሚሞተው ፖለቲካዊ እርባና ሲያጣ እንጂ በወታደራዊ ቅጣት አይደለም፡፡ የአገር ውስጥ የነፍጥ ትግልን ለመርታት ዋናው መድኃኒቱ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የአገር ውስጥ መድረክን አጐልብቶ የመሣሪያ ትግል ተዋንያኑን መሰባሰቢያ መንፈግ ነው፡፡

በአገር ውስጥ ውስጣዊ የፖለቲካ ችግሮችን ማቃለል፣ የነፍጥና የደመ ነውጠኛ ትግልን ፖለቲካዊ እርባና አሳጥቶ ግብዓተ መሬቱን መፈጸም፣ የውጭ ፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎችን የውስጥ ተቀፅላ የሚያሳጣ ሁኔታ መፍጠር አሸባሪነትን የመታገያ ዋናው ሥልት ነው፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ያላት ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ስትራቴጂካዊ ነው፡፡ የቀንዱ ክልል ደግሞ ትርምስና የሽብርተኝነት ችግር የተመላለሰበት ነው፡፡ የአፍሪካ ቀንድ ከዚህ በተጨማሪ ለመካከለኛው ምሥራቅ ድልድይ ነው፡፡

ይህን ሁሉ ከቁጥር በማስገባት ዓለም አቀፋዊ አሸባሪነት ለጥቃት የሚስማማው ምክንያት እንዳያገኝ፣ በአገር ውስጥም ቅርንጫፉንና ቅጣዩን ለማብቀልና ለማመስ እንዳይችል፣ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንንም ዒላማ ለማድረግ የሚመች ሁኔታ እንዳይፈጠር፣ የፀረ ሽብር ትግል ፖሊሲያችን በዕውቀት ላይ የተመሠረተና የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማዕከል ያደረገ መሆን አለበት፡፡ ፖሊሲው እንደዚህ ዓይነት ነው? ተብሎ የሚጠየቅ፣ ካልሆነ ደግሞ አይደለም ተብሎ የሚተችና ለተቃውሞ መጋለጥ ያለበት ነው፡፡ ‹‹እሽ አትበሉኝ የሹም ዶሮ ነኝ›› የሚል ዓይነት ፖሊሲም ሆነ ሕግ ኢትዮጵያ ሊኖራት አይገባም፡፡                

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...