Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ያስፈልጋል

ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ያስፈልጋል

ቀን:

‹‹የደረስንበት የሥልጣኔ ደረጃ ህያው ሆኖ እንዲቀጥልና ሳይንሳዊ የሆነ ሰብዓዊ ግንኙነት እንዲፈጠር ክፍተኛ ጥረት ማድረግ ከሚጠበቅብን ግዴታ ላይ እንገኛለን፡፡ ጥረቱም የሁሉም አገሮች ሕዝቦች ችሎታ ተሰብስቦ ለሰዎች በሰላም አብሮ መኖርና መሥራት አስተዋጽኦ ማድረግ ይኖርበታል፡፡›› እ.ኤ.አ. ከ1803 እስከ 1903 ድረስ የኖረው የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ፍራንክ ዲላኖ ሩዝቬልት

ዛሬ በአንድ በኩል ‹‹ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የማስፈኑ ሥራ ተጀምሯል፡፡ ጅምሩም ጥሩ አዝማሚያ እያሳየ ነው፡፡ ፍፃሜው እንዲያምርም ሁላችም በተስፋ ጠንክረን መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ የተገኙትን ሕዝባዊ ድሎች እያጠናከርን ወደፊት እንቀጥል፣ ብዙ የፖለቲካ ድርጅቶች ስለተሳተፉ ብቻ ልማት ሊመጣ አይችልም፡፡ በአውራ ፓርቲ እየተመሩም ዴሞክራሲን ማስፈን ይቻላል፡፡ ቻይናም፣ ጃፓንም፣ ሩሲያም እንደኛ በአውራ ፓርቲ የሚመሩ ናቸው፡፡ ያስገኘነው የልማት ውጤት ራሱ ለዲሞክራትነታችን ምስክር ነው፡፡ ስለዚህ…›› የሚሉ ወገኖች እንዳሉ ሁሉ በሌላ በኩል ደግሞ፣ ‹‹በአገሪቱ የዴሞክራያዊ ሥርዓት የለም፣ ፍትሕና ርትዕ ተዛብቷል፣ የአስተዳደር በደል በአገሪቱ ተንሰራፍቷል፣ ያለ ጉቦና ያለ ምልጃ ሥራ አይሠራም፣ በአድሎ የተመሠረቱ አሠራሮች በብዛት ይስተዋላሉ፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ ወደ ሌላ ክልል ሄዶ መሥራት ይቸገራል፡፡ ከክልሌ ውጣ ብለው የሚናገሩም አሉ፡፡ የሃይማኖት እኩልነት፣ የፆታ እኩልነት፣ የብሔር ብሔረሰብ እኩልነት እንደሚባለው የለም፡፡ ጦርነት አለ፣ ሁከት አለ…›› የሚሉ ተቃዋሚ ወገኖችም አሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር ‹‹ጥራኝ ጫካው ጥራኝ ዱሩ፣ ላንተም ይሻላሃል ብቻ ከማደሩ›› ብለው የሸፈቱም አሉ፡፡

ከሁለቱም ወገኖች ስለዴሞክራሲያዊነታቸው መድኅን (ምስክር/ዋስትና) የሚሆናቸውን ከግለሰብ ጀምሮ እስከ አገር መሪና ሳይንቲስት ዋቢ ይጠቅሳሉ፡፡ ሁሉም ወገኖች ለራሳቸው ትክክል ናቸው፡፡ ዳሩ ግን የአንዳቸው ትክክለኛነት የሌላኛውን ትክክለኛነት አይገልጽም፡፡ የአንዱን ዋቢም ሌላው አይቀበለውም፡፡ አንዱ የሌላውን ስም ያጠለሸዋል፡፡ አንዱ ሌላውን ቢችል በግልጽና በድብቅ ወይም የውስጥ አርበኛ በመሆን፣ ከታማኞች ሁሉ የላቀ ታማኝ በመምሰል፣ ችግሮችን ሆን ብሎ በማባባስ መንግሥትን በሾኬ ጠልፎ በአፍጢሙ ደፍቶ ለመጣል ከመታገል ወደኋላ አይልም፡፡ በጥላቻ ላይ የተመሠረተ ፖለቲካ ያናፍሳል፡፡ ‹‹ጠላቱን አቅፎ ወዳጁን አሽቀንጥሮ የጣለበት ጊዜ ነው›› በመሆኑ በራስ ወገን ያለመተማመን ችግር ይስተዋላል፡፡ ስለሆነም ከአንዱ ኃያል መንግሥት እግር ላይ በመጠምጠም ለሥልጣን አብቃኝ፣ ወይም ሥልጣኔን ጠብቅልኝ እንጂ አገሬን የአንተ መጠቀሚያ አደርጋለሁ ብሎ የሚማፀንም ይኖር ይሆናል፡፡ ‹‹ከእርሱ የበለጠ ለአንተ የምታመነው እኔ ነኝ›› ብሎ ያለ አንዳች ይሉኝታ የአገሩን ገመና ገልጦ የሚሰጥም አይጠፋም፡፡ ይህ አመለካከትም በአገር ውስጥና በሠለጠኑ አገሮች በሚገኙ ኢትዮጵውያንም ጭምር የሚንፀባረቅ ነው፡፡ ‹‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል›› ብላ ከተናገረችው አህያ የሚመሳሰል ሁኔታም ይስተዋላል፡፡ በዚህ ረገድ ያለው አመለካከት በከፋ መልኩ ስንመለከተው ደግሞ ምናልባት አንገት አርዶ ንፁህ ደም ከማፍሰስ አይተናነስም ቢባል ይገልጠው ይሆን? 

- Advertisement -

ያም ሆኖ አንዱ ሌላውን ለመተካት የሚፈልገው በኃይል እንጂ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሆኖ ስለማይሰማን ሥራችንን ለመሥራት ነፃ፣ ለመማር ነፃ፣ ለማመን ነፃ፣ አመለካከታችንን ለማራመድ ነፃ፣ ለመናገር ነፃ፣ ለመጻፍ ነፃና ለማሰብ ነፃ የምንሆነው መቼ ነው? ብለን ብንጠይቅ በቅርቡ ሊመጣ እንደማይችል የሚያሳዩ ምልክቶች በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ከሚኖሩ ፖለቲከኞች ወጎኖቻችን እናያለን፡፡ ‹‹በመናገሬ፣ ሐሳብ በመስጠቴ፣ በማመኔ ፖሊስ ከቤቴ አንገቴን አንጠልጥሎ ይወስድና ያሰቃየኝ ይሆን? ያልሠራሁትን ሠርቻለሁ ብዬ እንዳምን እገደድ ይሆን? የማይመለከተኝንና ከእኔ ጋር ፍፁም ግንኙነት የሌለውን እጠየቅ ይሆን? ሀቀኝነቴ እስኪረጋገጥ ለመኖር አስቸጋሪ በሆነ ቦታ ላይ እወረወር ይሆን?›› ብለን ከመጨነቅ የምንገላገልበት ሥርዓት ከእኛ በእጅጉ ሩቆ የሚገኝ ይመስላል፡፡ እናም ማንም ዞር ብሎ ባያየንም የሥጋት ጥላ በየሄድንበት ሊያንዣብብን ይችላል፡፡ ለምን? ለዴሞክራሲ ዴሞክራሲያዊነት ቅድመ ሁኔታ ነዋ!

በመሠረቱ፣ ‹‹ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማስፈን ዴሞክራሲያዊ መሆንን ይጠይቃል›› ካልን ለመሆኑ የዴሞክራሲ ቅድመ ሁኔታ ለሆነው ለሐሳብ ነፃነት ማለትም እኛ በነፃ እንደምንናገረው ሁሉ ሌሎች ሐሳባቸውን በነፃ እንዲሰጡ እንፈልጋለን ወይስ ‹‹ዝም በል፣ አዋቂ ሲናገር አድበህ ቁጭ በል›› እየተባልን እንዳደግነው ሁሉ ሌሎችን ዝም እንዲሉ እንፈልጋለን? እናም ለነፃነት ምን ያህል ነፃ ነን? ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማስፈንስ ምን ያህል ዴሞክራቶች ነን? የሚለውን ጥያቄ መመለስ ይቻል ዘንድ የበሰሉ ሐሳቦችን እንደ ተጨማሪ ግብዓት በማካተት ለመተንተን እንደሚከተለው ጥረት ይደረጋል፡፡

ለዴሞክራሲ መስፈን ዲሞክራሲያዊነት

በእርግጥም ከአንድ ፈላጭ ቆራጭ ዘውዳዊ አገዛዝ ወደ ሌላ ፈራጭ ቆራጭ ወታደራዊ አገዛዝ፣ ከዚያም ስንወጣ በአንድ ፈላጭ ቆራጭ ፓርቲ አመራር ስለኖርንና ፖለቲከኞቹም በዋነኝነት የዚያ ሥርዓት ውጤቶች ስለሆኑም ጭምር በቀላሉ የሥነ ባሕርይ ለውጥ ማምጣት ያስቸግራልና፡፡ የሚፈለገው ዓይነት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ቢዘገይ እምብዛም አያስገርምም፡፡ የደርግ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ለመውደቅ በተንገዳገዱበት ጊዜ ‹‹ሐበሻ ወርቅ ቢያነጥፉለት ፋንዲያ ይመርጣልና ምን ልናደርገው እንችላለን?›› ማለታቸው፣ ‹‹ከእኔ ወዲያ ጎራሽ ማዕድ አበላሽ›› ይል ከነበረው ዘውዳዊ ሥርዓት የወረሱት ነው፡፡ እርሳቸውና የሥልጣን ጓደኞቻቸው የሆኑ ምርጥ መኮንኖች በሚፈልጡበትና በሚቆርጡበት ዘመን፣ ‹‹ጓዶች ለመሆኑ ዛሬ ደርግ አለን?›› ብለው የጠየቁትም ከወታደራዊ አምባገነን መንግሥት ወደ አንድ ፈላጭ ቆራጭ ‹‹የኮሙዩኒስት›› ፓርቲ አመራር ስለተለወጡ ነው፡፡

ዳሩ ግን አሜሪካዊ ፈላስፋና ከፍተኛ የትምህርት ሰው የሆኑት ጆን ዴዊ (1859 እስከ 1952) ‹‹ስኩል ኤንድ ሶሳይቲ›› በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ. በ1937 በጻፉት መጽሐፍ ስለዴሞክራሲና ዴሞክራሲያዊ መንግሥት እንደገለጡት፣ በማንኛውም መልኩ ይተርጎም የዴሞክራሲ መሠረቱ የሰው ልጅ የተፈጥሮ ባሕርይ የሆነው የማሰብ ችሎታ አብሮ የመሥራትና የመኖር ልምድ ነው፡፡ ይህም ሲባል እነዚህ መሠረታዊ ነገሮች በተሟላ ሁኔታ ይገኛሉ ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን እያደር እያደጉና እየተመነደጉ ይመጣሉ፡፡ ለዚህም እንዲበቁ የሰው ልጅ የተባበረ ጥረት ያስፈልጋቸዋል፡፡ የፈላጭ ቆራጭ አምባገነን ፖለቲከኞች አመለክካት ‹‹ከሰው ልጅ ሁለንተናዊ ብልፅግና ይልቅ የጥቂት አዋቂዎች አመራር ይበቃል፡፡ እነዚህ ሰዎች የሚያወጡት ሕግና ደንብ ብቻውን ሕዝቡን ወደሚፈልገው አቅጣጫ ይመራዋል፤›› ብለው ያምናሉ፡፡

ስለሆነም ነገሮችን በጥቅሉ ስንመከታቸው፣ ዛሬ ወደ መድበለ ፓርቲ ሥርዓት ስንገባ ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ እየተፈቱ የግንባታ ሥራዎች ይካሄዱ ዘንድ፣ ከፍተኛ የሥነ ባሕርይ ለውጥ ለማምጣት በግልም ሆነ በቡድን መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ ይህም ጥረት ባል ለሚስቱ፣ ሚስት ለባሏ፣ ወላጆች ለልጆቻቸው፣ ትልልቆች ለትንንሾቻቸው፣ መምህራን ለተማሪዎቻቸውም፣ አለቆች ለበታቾቻቸው በማሳየት እንዲንፀባረቅ በማድረግ የሚገለጥ ይሆናል፡፡ ‹‹ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማምጣት የረጅም ጊዜ ያለሳሰለሰ ጥረትና ትግል ይጠይቃል፤›› የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ ለመሆኑ ዴሞክራሲ እውን መሆኑ በምን ይንፀባረቃል?

አርኪባልድ ማክሌሽ (1892 እስከ 1982) የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ እንደገለጹት፣ ‹‹በአሜሪካውያን ዘንድ ዴሞክራሲ ማለት ግለሰብ ራሱ ለራሱ እንዲያስብና በራሱ ግንዛቤና ውሳኔ መሠረት እውነተኛውን ነገር መረዳት ነው፡፡ ይህም የግለሰቦች መሠረታዊ መብት በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠ ነው፡፡ ማሰብም ሆነ አመለካከት፣ አስተያየትም ሆነ ልምድን በተመለከተ ማንኛውም ሰው ነፃ መሆኑ መታወቅ አለበት፤›› ብለዋል፡፡ እኝሁ አሜሪካዊ በተጨማሪም፣ ‹‹ሌላው ቀርቶ ግለሰቡ ራሱ ፈቃደኛ እስካልሆነ ድረስ የሌሎችን አስተሳሰብ በተፅዕኖ እንዲቀበል መደረግ አይኖርበትም… የብዙኋን አስተያየት ቢሆን እንኳ እንዲቀበል መገደድ የለበትም›› በማለት በአሜሪካን የዴሞክራሲ ምሥል ምን እንደሚመስል ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ በዚሁ ‹‹ሰውን ነፃ ለማድረግ›› በሚለው ጽሑፋቸው፣ ‹‹በዚህች አገር ያለው አስተማማኝ ነገር የግለሰቦች ዕውቀት (አዕምሮ) አስፈላጊ መሆን ነው፡፡ ጥንካሬያችን የሚገኘው ከዚሁ ነው፡፡ ይኼም ጥንካሬአችን በለውጥ ሒደት ከሚገጥመን መሰናክል ጋር ፊት ለፊት እንድንጋፈጥ በቁጥጥር ሥር ለማድረግ ይረዳናል፡፡ ያለፈ ታሪካችን የወደፊቱን ሕይወት እንደ መስተዋት ቁልጭ አድርጎ እያሳየ ባለበት ሁኔታ ለባለሥልጣናት ግትር አመለክካት ቀኖናውያን ሆነን እንቅስቃሴ ሲገታ፣ እንደ በረዶ ደርቀን የምንታይ አይደለንም፡፡ ምንጊዜም በየትኛውም ቦታና በማንኛውም ሁኔታ ቅድሚያ የሚሰጠው ለሰው በመሆኑ ነፃ ነን፡፡ ሀቁ ሌላው እንደሚለው ሳይሆን ራሱ ሰውዬው (ግለሰቡ) የሚያየውን ማክበር ነው፤›› ሲሉ በዴሞክራዊያዊ ሥርዓት የሰብዓዊ ፍጡር መብት ከሁሉም በላይ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ሌሎችም ስለዴሞክራሲ ብዙ ብለዋል፡፡

ዳሩ ግን በጥቅሉም ቢሆን ዴሞክራሲ፡-

  • መሪዎች ከአንድ የተወሰነ ክፍል ሳይሆን ከሁሉም ኅብረተሰብ በአብዛኛው ድምፅ የሚመረጡበት ሥርዓት፣
  • የተመረጡት ሕዝብን ለማገልገል በመሆኑ ይህንን ኃላፊነት በትክክል ሳይወጡ ቢቀሩ ከሥልጣናቸው የሚወገዱበት፣
  • አመራራቸው ለሕዝቡ መሠረታዊ ጥቅሞች ቅድሚያ የሚሰጥ አስተዳደር የሚዘረጋበት፣
  • የአብዛኛው ኅብረተሰብ ክፍል ደስታ የሚረጋገጥበት፣
  • የተወሰኑ ዜጎች በትውልድ ሐረጋቸው፣ በሀብታቸውና በዘራቸው በሌላም በተለየ ተጠቃሚ የማይሆኑበት፣
  • እያንዳንዱ ዜጋ እኩል የመምረጥ፣ የመመረጥ፣ የመሥራት፣ የመኖር፣ ወዘተ መብት የሚገኝበት፣
  • የመጻፍ፣ የመናገር፣ ሐሳብን በነፃ የመግለጽ መብት የተከበረበት፣
  • ለማንኛውም ሰው የሃይማኖቱና የእምነቱ ነፃነት የተጠበቀበት፣
  • ሴቶች ከወንዶች ጋር እኩል መሆናቸው የተረጋገጠበት ሥርዓት እንደሆነ ከልምድና በተግባር ላይ ካዋሉት አገሮች ታሪክ መረዳት ይቻላል፡፡

ይህም ቢሆን የዴሞክራሲን ትርጉም ብቻውን የሚገልጽ አይደለም፡፡ ስለዴሞክራሲያዊ ባሕርይ ሲገለጥ በምርጫ ውድድር የሚፈልጉትን መምረጥ ብቻ ሊመስል ይችላል፡፡ ሰዎች የሚፈልጉትን አመዛዝነው መረጡ ማለት ግን የተመረጠው ምኞታቸውን ይፈጽላቸዋል ወይም የማይፈልጉትን የሚፈጽላቸውን መረጡ ማለት አይደለም፡፡ ተመራጮች የገቡትን ቃል መፈጸማቸውና አለመፈጸማቸው የሚታወቀው በተግባራዊ ውጤታቸው ነው፡፡ ለማንኛውም ዴሞክራሲያዊ ቅርበት ያለው ሥርዓት ከአምባገነናዊ ሥርዓት በጣሙን የተሻለ መሆኑን፣ የሰው ልጅ ዘመናዊ ሕይወት ያመለክታል፡፡

በመሠረቱ ዴሞክራሲ በሰው ልጆች እኩልነት ያምናል ሲባል ምን ማለት ነው?  ይህ ጉዳይ በሰፊውና በልዩ ልዩ አመለካከቶች ሊገለጥ ይችላል፡፡ በአካላዊና በሥነ ባሕርያዊ አመለክካት ሳይሆን በሕጋዊና በፖለቲካዊ ሁኔታዎች ነው፡፡ በዚህም የእኩልነት መብት መሣሪያ ተጠቅሞ (ትንሽም ይሁን ትልቅ) አመለካከቱን፣ አስተሳሰቡንና ውሳኔውን ያሳውቃል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዴሞክራሲ ከድርጊት ጋር የተያያዘ ስለሆነ፣ እያንዳንዱ ሌሎች እንደሚያደርጉት ሁሉ የመረጠውን እንዲያደርግ ያስችለዋል፡፡ የድርጊት ነፃነቱ ከማወቅ፣ ከማስተዋልና ከጥበብ ጋር የተሳሰረ እንዲሆን የበለጠ ያጠናክረዋል፡፡ ምንም ያህል ኢኮኖሚ ቢያድግ የእምነት ነፃነት፣ ሐሳብን የመግለጽ ነፃነትና የማወቅ ነፃነት ከሌለ የኅብረተሰብ ዕድገት ይመጣል ተብሎ አይገመትም፡፡

ከታወቁት እንግሊዛውያን ፈላስፎች በፊት የነበሩትን አሜሪካዊው ፕሬዚዳንት ቶማስ ጀፈርሰንም (1743 እስከ 1826) ‹‹በማንኛውም ሁኔታ በእምነት፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ በሰላማዊ መንገድ በንግድ በታማኝ ጓደኝነት ሳይለይ የተስተካከለና እኩል ፍትሕ ለሁሉም ሰው፣ … የሃይማኖት ነፃነት፣ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ያለመጠየቅ ነፃነት፣ የዘር መድልኦ የሌለበት ዳኝነት፣… እነዚህ መሠረታዊ መርሆች አብዮታዊ የግንባታ ለውጥ እንድናመጣ እንደ ብሩህ ኮከብ ሆነው ለዘመናት ደረጃ በደረጃ እንድንመራ አድርገዋል፡፡ በብልኃት ሲመሩ የነበሩ ጠበብት አባቶቻችንና ጀግኖቻችን ደም የፈሰሰው ለእነዚህ መርሆች ግብ መምታት ነው፡፡ ዛሬም ቢሆን እነዚህ መርሆች ፖለቲካዊ እምነታችን፣ የሲቪክስ ትምህርታችን የምናማቸውን ሰዎች ለማግለል የምንፈትንባቸው መመዘኛዎችን በድንገተኛ ሁኔታ ሆነ በስህተት ጊዜ በፍጥነት ራሳችንን የምናርምባቸው መሆን ይገባቸዋል፤›› ይላሉ፡፡

ስለሆነም ዴሞክራሲ በልዩ የፖለቲካ ቅርፅ ከሚይዘው ሰፋ ያለ ትርጉም አለው፡፡ ‹‹ዴሞክራሲ አንድ መስተዳድር ሕዝቡን እንዴት እንደሚመራ፣ እንደምን ሕግ እንደሚወጣ፣ በምን ዓይነት መንገድ ምርጫዎች እንደሚከናወኑ የሚተነትን ነው…›› ብሎ መደምደም አስቸጋሪ ነው፡፡ በእርግጥ የተጠቀሱት ሁሉ የዴሞክራሲ መገለጫዎች ናቸው፡፡ ፖለቲካና መንግሥት ምሥረታ አንደኛው የዴሞክራሲ ገጽ ሲሆን፣ በደንብ በሥራ ላይ ሊውል የሚችለውም የሰው ልጅ አመለካከት ጥልቅ በሚሆንበት ጊዜ ነው፡፡ ያም እንዲሆን ደግሞ የሕዝቦች ማንነት ታውቆ በታሪካቸው፣ በባህላቸውና በቋንቋቸው እንዲኮሩ ሁኔታዎች መመቻቸት ይኖርባቸዋል፡፡ ሰዎች የመሰላቸውን የምክር አስተያየት በመሰንዘራቸው ምክንያት ሊደሰቱ፣ ሊኮሩ፣ የመንፈስ ነፃነት ሊያገኙ እንጂ ከዛሬ ነገ ምን እንሆናለሁ ብለው መሸማቀቅ አይኖርባቸውም፡፡ ‹‹የበዓሉ ግርማ ዕጣ ፈንታ ይገጥመኝ ይሆን?›› ብለው ማሰብ አይኖርባቸውም፡፡

ከ1984 እስከ 1992 ዓ.ም. በነበሩት ዓመታት ምንም እንኳን የደቡብ አፍሪካን፣ የግብፅን፣ የናይጀሪያንና የመሳሰሉትን አገሮች ባያህልም ከነበረው ሁኔታ አንፃር በርካታ ጋዜጦችና መጽሔቶች በአገራችን ተፈጥረው እንደነበር ይታወሳል፡፡ እርግጥ መጽሔቶቹና ጋዜጦቹ ሁሉ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መስፍን የሚታገሉ ነበሩ ብሎ መናገር ያስቸግራል፡፡ አንዳንዱቹ ራሳቸው መግለጫ የማይገኝላቸው አምባገነኖች ነበሩ፡፡ አንዳንዶቹ የነፃነት ጠበቆች ሳይሆኑ የጭቆና መሣሪያዎች ነበሩ፡፡ መልካሞቹም ነበሩ፡፡ አሁን የሉም፡፡ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጋዜጦችና መጽሔቶችን ቆጥሮ ሁኔታዎችን ያሞገሰበት ጊዜ ነበር፡፡ አሁን እነዚያ የፕሬስ ውጤቶች በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት የሉም፡፡ ሦስት ብር ይሸጡ የነበሩ መጽሔቶች ዛሬ አሮጌዎቹ ከአምስት እስከ አሥር ብር ይሸጣሉ፡፡ ለዚያውም እንዳስፈላጊነቱ አይገኙም፡፡ በታላቋ ኢትዮጵያችን ያሉት ጋዜጦች ከሌሎች ጋር ለማነፃፀር እንችል ዘንድ በጥቂቱ እንመልከት፡፡ ለምሳሌ በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ካሉት በመቶዎች የሚቆጠሩ ጋዜጦች ከፍተኛ ኅትመት ያላቸው 47 ያህል ሲሆኑ፣ የመጀመርያው በየዕለቱ 368,974፣ ሁለተኛው 287,222፣ ሦስተኛው 192,293 በየዕቱ ሲታተም የመጨረሻው 8,000 ያህል ቅጅዎችን አሳትሞ ያሰራጫል፡፡ በኒውዮርክ ከተማ ብቻ ደግሞ 124 ጋዜጦች ሲኖሩ፣ እነሱም በሚሊዮኖች የሚታተሙ ቅጅዎችን ያሰራጫሉ፡፡ ታላቋ ብሪታንያ በየዕለቱ የሚታተሙ ጋዜጦችና መጽሔቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 13 ያህሉ በሚሊዮን ወይም በመቶ ሺዎች የሚቆጠ የሚቆጠር ቅጅ የሚያሳትሙ ናቸው፡፡ በእነዚህ አገሮች ያሉ ጋዜጦች ከተመሠረቱበት ጊዜ ጀምሮ መንግሥትን የሚተቹ ናቸው፡፡

መጻሕፍትንም በሚመለከት ያለን ልዩነት በእጅጉ በጣም ሰፊ ነው፡፡ ለምሳሌ በአገራችን ባለፉት 20 ዓመታት የታተሙት መጻሕፍት በርዕስ ከ600 የሚበልጡ አይደሉም፡፡ ይህም የትምህርት መጻሕፍትን ጨምሮ መሆኑ ነው፡፡ የትምህርት ያልሆኑት በአርዕስት ከ500 የሚበልጡ አይደሉም፡፡ አንድ መጽሐፍ በአማካይ በ5,000 ኮፒ ቢሰላ 2,500,000 ይሆናል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በ100 አርዕስት የተጻፉት የሕፃናት መጻሐፍት ናቸው፡፡ በአብዛኛው ግን ከ1,500 እስከ 3,000 እንደሆኑ ብዙዎቻችን እንገነዘባለን፡፡ ይህን ሥሌት ከአሜሪካ ጋር ማነፃፀር ባይገባንም የዛሬ 15 ዓመት ማለትም እ.ኤ.አ. በ2010 በአንድ ዓመት የታተሙት 328,259 አርዕስቶች ነበሩ፡፡ .እ.ኤ.አ. በ1950 በዓመት 11,200  ይታተሙ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በቅርቡም በአንድ ዓመት ከ700,000 በላይ ዕርዕስት ያለቸው መጻሕፍት እንደታተሙ አሜሪካኖች ይናገራሉ፡፡ እኛ ደግሞ ከ100 እስከ 150 አርዕስት ያላቸውን መጻሕፍት አሳትመን ይሆናል፡፡ ይኼንም ጸሐፊው ጭማሪ አድርጎበት ነው፡፡ በአሜሪካ ከሚታተሙት መጻሕፍት አንዳንዶቹ በአምስትና በአሥር ሚሊዮን ቅጅ የሚታተሙ ስለሆነ የአንድ መጽሐፍ ነፍስ ወከፍ ድርሻ በጣም ብዙ ነው፡፡ የሚቀርቡንም አገሮች ስንመለከት በግብፅ (2000) 9,022፣  በደቡብ አፍሪካ (1995) 5,418፣  በሞሮኮ (1996) 918፣ በቱኒዚያ (1996) 720፣  በሖንዱራስ (2003) 290፣ በኡጋንዳ (1996) 288፣  በሞንጎሊያ (1992) 285፣ በኤልሳልቫዶር (በ2003) 250  በኢትዮጵያ (1991) 240 እንደሆነ ስታቲስቲካዊ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በበለፀጉ አገሮች በርካታ ጋዜጦች፣ መጽሔቶች፣ ጆርናሎችና መጻሕፍት መታተማቸው የመንግሥታቱን ዴሞክራሲያዊ ገጽታ አጠናከሩት እንጂ አላቀጨጩትም፡፡ የጋዜጠኛ ዋነኛ ሥራም መተቸት፣ መውቀስ፣ የተበላሸው አሠራር እንዲስተካከል መንገር ነው፡፡ ይህ ሥራ መርማሪ ጋዜጠኛውንና ደራሲውን ይመለከታል፡፡ ለዴሞክራሲ ማበብ ዴሞክራሲያዊነት የሚያስፈልገውም ለዚህ ነው፡፡

በአጠቃለይ ብዙዎቻችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲሰፍን እንሻለን፡፡ ዴሞክራሲ ግን ስለፈለግነው ብቻ የሚመጣ ወይም እንደ ተስፋ ልብስ አውርደን የምንለብሰው አይደለም፡፡ ኢኮኖሚው መዳበር አለበት፡፡ ኢኮኖሚው እንዲዳብር ደግሞ ዴሞክራዊያዊ አስተሳሰብ ያስፈልጋል፡፡ ለዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ መዳበር ነፃ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ሁለቱም ድርና ማግ ናቸው፡፡ ያለነፃነት ዴሞክራሲ ያለዴሞክራሲ ደግሞ ነፃነት የለም፡፡ ለመሆኑ ለነፃነት ምን ያህል ነፃ ነን?

ለነፃነት ምን ያህል ነፃ ነን?

የሰዎች ደኅንነትና የተሟላ ነፃነት እንዲረጋገጥ ለምንሻበት የወደፊት ዘመን አራት ነገሮች መሟላት አለባቸው፡፡ እነሱም የመናገርና ስሜትን የመግለጽ ነፃነት፣ እያንዳንዱ ሰው የፈለገውን እምነት የመከተል ነፃነት፣ የፈለገውን የመሆን ነፃነት፣ ከፍርኃት ነፃ የመሆን ነፃነት መሆናቸውን ከ70 ዓመት በፊት ታላቅ የፖለቲካ ሥራ አከናውነው ያለፉት አሜሪካዊው የቀድሞ ፕሬዚዳንት ፍራንክሊን ዲላኖ ሩዝቬልት ተናግረዋል፡፡ እኚህ ታላቅ የፖለቲካ ሰው እንዲህ በማለታቸው ከፍተኛ የፖለቲካ ተቀናቃኞች ማፍራታቸው ይታወሳል፡፡ ይልቁንም አገራቸው እጅግ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ድቀት ገጥሟት በነበረችበት ጊዜ በፕሬዚዳንነት ያገለግሉ ስለነበረ፣ እርሳቸውን አሽቀንጥረው በመጣል የራሳቸውን ዕድል ለመሞከር ብርቱ ዓላማ የነበራቸው የፖለቲካ ሰዎች በየፈርጁ የደቀኑባቸው ፈተና የዋዛ አልነበረም፡፡ ይህም ሆኖ ማንኛውም ሰው በአገራቸው ብቻ ሳይሆን በዓለማችን በየትኛውም ሥፍራ የመናገርና ስሜትን የመግለጽ ነፃነትና ከማንኛውም ፍርኃት ነፃ ሆኖ ደኅንነቱ እንዲረጋገጥ ይሟገቱለት ነበር፡፡ እኚህ ሰው አገራቸው የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተካፋይ በነበረችበት ጊዜ የነበሩ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ሆነው የመሩ ሲሆን እሳቸውም፣ ‹‹ታሪክ እንዳረጋገጠው አምባገነናዊነት የሚመጣው ከጠንካራና ስኬታማ ከሆነ መንግሥት ሳይሆን ከደካማና ተስፋ ቢስ ከሆነ መንግሥት ነው፡፡ ሕዝቦች በዴሞክራሲያዊ መንገድ የመሠረቱት መንግሥት ጠንካራ ሆኖ ከረሃብና ከፍርኃት ከጠበቃቸው ዴሞክራሲያቸው የተዋጣለት ሲሆን፣ ካልሆነ ግን ፋይዳ ቢስ ይሆናል፡፡ ፍላጎት በምንም ሆነ በማንም እንደማይደፈር ምሽግ ጠንክሮ የሚጠብቅ መንግሥት ቢኖር፣ ሕዝቡም ይህን ጠንካራ መንግሥት ክንዱ የበለጠ እንዲፈረጥም አስፈላጊውን እገዛ ሲያደርግለትና እንደገናም ሲቆጣጠረው ክብሩ የማይደፈር ይሆናል፤›› በማለት ለሕዝብ የገቡት ቃል የማይታጠፍ መሆኑን ያስገነዝባል፡፡

ፕሬዚዳንት ሩዝቬልት በተጠቀሱት ሁለት አጋጣሚዎች ሕዝብ ከፍርኃት ነፃ መሆን እንደሚገባው መጥቀሳቸው ያለምክንያት አልነበረም፡፡ ከማንኛውም ዓይነት ፍርኃት ነፃ ያልሆነ ሕዝብ ስለዴሞክራሲም፣ ስለነፃነትም፣ ስለሰላምም፣ ስለሌላም መልካም ነገር ባማሩ ቃላት ቢነግሩት ሊገባው አይችልም፡፡ ፕሬዚዳንቱ የዴሞክራቲክ ፓርቲያቸው የሪፐብሊካን ፓርቲ አባሎችን ቢያፍን፣ ወይም ሌሎች ተቀናቃኝ ድርጅቶችን በተለያየ ተንኮል ከፖለቲካ ጨዋታው ውጭ ቢያደርግ ኖሮ የሁለተኛውን የዓለም ጦርነት በአሸናፊነት ይወጣሉ ብሎ ማሰብ በእርግጥ ያስቸግር ነበር፡፡ አንድ ጊዜ ሳይሆን ሁለቴ፣ ከሁለቴም ሦስቴና አራቴ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ሩዝቬልት ተቀናቃኞቻቸው እንኳን አክብሮት ያልነፈጓቸው፣ ሕዝብ ከማንኛውም ፍርኃት ነፃ ሆኖ ስለአገሩ የሚበጅ አስተዋጽኦ እንዲደርግ ግንባር ቀደም ሆነው በማገልገላቸው እንደሆነ ከሕይወት ታሪካቸው እንረዳለን፡፡

ስለሆነም የመንግሥት ባለሥልጣናት ሕዝብን ከማንኛውም ዓይነት ፍርኃት ነፃ ካላደረጉት በስተቀር ፍትሐዊ ሥርዓት ዘርግተናል ቢሉ እንኳን፣ ፍትሐዊ ያልሆነው ሥርዓት የሥነ ልቦና ጦር ተክሎባቸዋልና ሥርዓቱን ለማየት ይችላሉ ብሎ ማሰብ በጣም አስቸጋሪ እንደሆነ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ አባቶቻችን ‹‹እባብ ያየ በልጥ ይሸሻል›› ማለታቸውም ያለ አንዳች ምክንያት አይደለም፡፡ ከ170 ዓመት በፊት የነበሩት ቶማስ ጀፈርሰንም ሰዎች እንደየ አስተሳሰባቸው በሁለት እንደሚከፈሉ ጠቅሰው፣›› ‹‹አንደኛው ሕዝብን የሚፈራና የሚጠራጠር ክፍል ሲሆን፣ ይህም ሥልጣኑን በሙሉ ከብዙኃን እጅ ፈልቅቆ በማውጣት በውህዳን ገዥ መደቦች የሚያስገባ፣ ሁለተኛው ክፍል ደግሞ ራሱን የሕዝብ ወገን ያደርግና በሕዝብ የሚተማመን፣ የሕዝብን ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ባያረካም ሕዝብ የሚታመኑበትና ደኅንነቱ በእነሱ ላይ የተመሠረተ መሆኑን የሚያምን ነው፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡ እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች የማሰብ ነፃነት፣ የመናገር ነፃነትና የመጻፍ ነፃነት ባላቸው በእያንዳንዱ አገሮች እንደሚኖሩም ይተነትናሉ፡፡

በአገራችን በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን የአንድ አካባቢ መስፍን መሆን፣ በአፄ ዮሐንስ ዘመን የእስልምና ተከታይ መሆን፣ ታላቅ የፍርኃት ምንጭ የነበሩትን ያህል በአፄ ኃይለ ሥላሴና በደርግ ጊዜ የሥልጣን ተቀናቃኝ ሆኖ መገኘት (ማሰብ) በእጅጉ አስፈሪ እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ ከሩቅ ወደ ቅርብ ስናተኩር በደርግ ዘመን ፀረ ደርግ መሆን፣ የህቡዕ የፖለቲካ ድርጅቶች አባል መሆን፣ ወጣት መሆን በእጅጉ የሚያስፈራ ነበር፡፡ ምናልባትም የማያስፈራ ነገር አልነበረም ቢባል ይቀል ይሆናል፡፡ የጦር መሣሪያ የታጠቀ ሁሉ ማንም ይሁን ማን የማስፈራራት፣ ሌላው ደግሞ የመፍራት መብት ያለው ይመስል ነበር፡፡ ስለዚህም ቶማስ ካርላይል እንዳሉት ፍርኃትን ማስወገድ አለብን፡፡ ፍርኃትን ለማስወገድ ግን ታጣቂውም፣ መንግሥትም የሕዝብ አገልጋይ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፡፡ ሕዝብ የየትኛውም ብሔርና ብሔረሰብ አባል ቢሆንም፣ በየትኛውም አገርና ሥፍራ ያላንዳች ሥጋት የመኖር መብቱ መረጋገጥ አለበት፡፡

ይሁንና የሕዝብ ለነፃነት እንኳን አለመታደል ዋነኛ ምክንያት ምናልባት በብዙ አምባገነናዊ ሥርዓቶች እንደታየው እያስፈራሩ መግዛት በነፃ ከመግዛት የተሻለ ስለሚሆን ይሆናል፡፡ ሕዝቡን በፍርኃት የመግዛት ሥርዓት ሲዘረጋ ግን ለሥርዓቱ መቆየት አስተማማኝ ሁኔታ ይኖራል ማለት አይደለም፡፡ ፍርኃት የነገሠበት አገዛዝ ከዚያ ቀደም በአገራችንና በተቀረው ዓለም እንደታየው ሁሉ ሕዝቡን ወደ እርስ በርስ መጨፋጨፍ እንዲያመራ አደረገው እንጂ፣ ሰላምና ዴሞክራሲን አላስገኘለትም፡፡ በሰላምና በዴሞክራሲ መኖር የሚገባው ሰው የጦርነት እሳት ማገዶ ሲሆን ከማየት የበለጠ ደግሞ አሳዛኝ ነገር አይኖርም፡፡ ስለዚህም ካለፉት አስፈሪ ሥርዓቶች ነፃ መሆናችንን ለማረጋገጥ እንችል ዘንድ፣ ‹‹ከእንግዲህ ፍርኃት በቃ፣ ይህች አገር በዴሞክራሲ ጎዳና ትራመድ ዘንድ በየትኛውም ሥፍራና ጊዜ ሰዎች በልቦናቸው ውስጥ ያለውን ለመናገር፣ ድምፃቸውን ለማሰማት ቢፈልጉ በደብዳቤ፣ ወይም በፕሬስ ለመግለጽ መቻል አለባቸው፡፡ ዓለማችን እጅግ ያጎሳቆላት ኃይልና ጭቆና ነው፤›› በማለት ጋዜጠኛው ዊልያም አለን ዋይት የገለጸውን ማጤን ተገቢ ይሆናል፡፡ ግሪካዊው ፈላስፋ አርስቶትልም፣ ‹‹የዴሞክራሲያዊ መንግሥት መሠረቱ የሕዝብ ነፃነቱ ነው፤›› ሲል የጻፈውም በቂ ምክንያት ኖሮት ነው፡፡

አንድ ዜጋ ለነፃነት ነፃ የሚሆነው ነፃነቱ በሕግ ተረቅቆ ወረቀቶች ላይ ስለሰፈረለት ብቻ ሊሆን አይችልም፡፡ በአካባቢውም ሆነ ከእሱ በሥልጣን በጣም ርቆ የሚገኝ የፖለቲካ ሰው ‹‹እኔ የምናገረው ምንጊዜም ትክክል ነው›› ብቻ ሳይሆን፣ ‹‹አንተ የምትለው ምንም እንኳን ጠቃሚ ቢሆንም ጠንካራ ክንድ ስለለኝ አልቀበልህም፤›› ካለው፣ ይህ ሰው በምንም ዓይነት መንገድ ነፃ ነው ሊባል ከቶ አይችልም፡፡ እንደገናም ያው ዜጋ ትክክል መሆኑን እያወቀ ተቀባይነት ማጣቱን ከተቀበለ ደግሞ ነፃነት እንኳን ባይኖረው ለነፃነት ብቁ ነው ማለት ያስቸግራል፡፡ በመሠረቱ በባለሥላጣናት፣ በተለይም ኃላፊነት ያላቸው የፖለቲካ ባለሥልጣናት፣ አንድ ችግር በልዩ ልዩ አጋጣሚዎች ይፈጠርና ያ ችግር ሕዝብን ለአደጋ አሳልፈው የሚሰጡ ሁኔታዎችን ይጋብዛል ብለው በመሥጋት፣ አስተያየት እንዳይሰጥበት ለመቆጣጠር ይፈልጉ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ከእንዲህ ያለ መከራ ይልቅ የሕዝብን ነፃ አስተያየት መጠየቅና በሕዝብ አስተያየት መመራት የተሻለ ይሆናል፡፡ ይኸው ሒደት ተከስቶ ያስተዋለው እንግሊዛዊው ፈላስፋና ኢኮኖሚስት ጆን ስቲወርት፣ ‹‹ባለሥልጣናት በራሳቸው ብያኔ ስህተቶች እንዳይታረሙ ከማገድ የበለጠ ትልቅ ስህተት የለም፡፡ ብያኔውን ለሕዝቡ ለራሱ መስጠት አለበት፡፡ መንግሥትም ሆነ ግለሰብ በሚቻለው መንገድ ሁሉ ሀቀኛውን አስተያየት ለመቅረጽና ግልጽ በሆነ መንገድ ለማቅረብ የመጣር ኃላፊነት ቢኖርበትም፣ በሚሰጠው አስተያየት መቶ በመቶ እርግጠኛ ካልሆነ ሕዝብ እንዲቀበለው ማስገደድ አይኖርበትም፡፡ ትክክል መሆናቸውን አረጋግጦ ሀቀኛ አስተያየታቸውን አለመስጠት ግን ከፍርኃትና ከጥርጣሬ ውጪ የሚታይ አይደለም፤›› ይላል፡፡

የመንግሥትና የሕዝብ ግንኙነት

በየትኛውም አገር ቢሆን፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ከዘረጋን መቶ ዓመታት አስቆጥረናል በሚሉት አገሮች ጭምት ሁልጊዜም ባይሆን፣ ለውህዳን ባለሥልጣናት ሲባል የብዙኃን መብት የሚረጋገጥበት ሁኔታ እንደሚኖር አያጠያይቅም፡፡ ነገር ግን በእነዚህ አገሮች ቢንስ ቢያንስ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተለይም የሕግ አውጪ፣ አስፈጻሚዎችና ተርጓሚው ሕዝብ የማይፈልጋቸው ሲሆን ከሥልጣን ለመውረድ ዝግጁ መሆናቸው ሳይታለም የተፈታ መሆን ይኖርበታል፡፡

መንግሥት ሕዝብ የሚተዳደርበትን ፍትሐዊ ሕግ ማውጣት እንዳለበት ሁሉ፣ የግለሰቦች የማሰብና የመቃወም ነፃነት እንደተጠበቀ ሆኖ ሕዝብም በፍትሐዊው ሕግ ሥር ለማደር ራሱን ማዘጋጀት ይኖርበታል፡፡ በሁለቱም መካከል ቀና አመለካከት ሲኖር ስህተቶች በጊዜ ለመታረም የሚችሉበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ የአገር ውስጥ ነፃነቱ የተረጋገጠለትና ዴሞክራሲያዊ መንግሥት እንዲኖር የራሱን ጥረት የሚያደርግ ሕዝብ የውጭ ጠላት ይደፍረዋል ተብሎ አይገመትም፡፡ ይልቅስ ወዳጁና ረዳቱ ይበዛል፡፡ ግሪካዊ ፈላስፋ ፕሌቶ የዴሞክራሲያዊ ጽንሰ ሐሳብ ትርጓሜ፣ ‹‹ነፃ ሕዝቦች በፖለቲካ መሠረታዊ ጥያቄዎች ላይ እኩል መሆን ይገባቸዋል፡፡ ከሆነም ጤነኛ ፖለቲካዊ ግንኙነት ይኖራቸዋል፤›› ማለቱ፣ የፖለቲካ ሰዎች ከሕዝብ ተስፈንጥረው የሚያደርጉት ነገር ሊኖር እንደማይችልና ሕዝብ ‹‹ፖለቲካ የመንግሥት ሥራ ነው›› ብሎ ራሱን ከማግለል መቆጠብ እንዳለበት ለማሳየት ጭምር ነው፡፡

ሕዝብ በእርግጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲዘረጋና የዘመናት ባርነት እንዲወገድለት፣ በልዩ ልዩ መስኮች የተካኑ ምሁራንም በሚቻላቸው መንገድ ሁሉ መንግሥትን በሾርኒም ሆነ በንቃት ሲያዩት መኖር የለባቸውም፡፡ ዛሬ በዕድገታቸው ከፍተኛ ደረጃ ደረሱ የሚባሉት አገሮች እዚህ ደረጃ የደረሱት በሰው ልጅ ተዓምር በተለይም በምሁራን ጥረት እንደደሆነ የታወቀ ነው፡፡ አንዳንድ ምሁራን፣ ‹‹እንዲህ ብል አድርባይ እባላለሁ›› በማለትና መንግሥት ዕርምጃ ይወስድብኛል በሚል ፍርኃት እየተዋጡ፣ እንደ ተራና ማይም ሰው ከሚያንሾካሹኩ ይልቅ ወደ አደባባይ ወጥተው በሕዝባዊ ሥራቸው የፈለገው ዕርምጃ ቢወሰድባቸው የተሻለ እንደሚሆን አያጠያይቅም፡፡ በጣም አነስተኛ መስዋዕትነትም ይህ ነው፡፡

አብርሃም ሊንከን፣ ‹‹ዓለማችን ነፃነት ለሚለው ቃል ጥሩ ትርጉም ኖሯት አያውቅም፡፡ እናም የአሜሪካ ሕዝብ አንድ ጥሩ ትርጉም ማግኘት ከምንጊዜውም የበለጠ ያፈልጋል፤›› ካለ በኋላ፣ ለምን የነፃነትን ትርጉም ማወቅ እንዳስፈለገ ሲገልጽ፣ ‹‹ሁላችንም ስለነፃነት እንለፍፋለን፡፡ ለነፃነት እያንዳንዱ ሰው የሚሰጠው ትርጉም የተለያየ ነው፡፡ ለአንዳንዱ ነፃነት ማለት ሌላው ላቡን አንጠፍጥፎ ያገኘውን ምርት እንዳሻው ለመውሰድ ሊሆን ይችላል፤›› በማለት አምራቹ ደግሞ እንዲህ ያለውን ፍች እንደማይቀበለው ያስገነዝባል፡፡ ለነፃነት መታገላቸውን ታሪክ በስፋት የሚመሰክርላት ሊንከን የነፃነትን ትርጓሜ በምሳሌ ሲያስረዳ፣ ‹‹አንድ እረኛ ቀበሮው የፈጠረቀውን የበግ አንገት ቢያስለቅቀው ነፃ የወጣው ክፍል ሲያመሰግነው፣ የለቀቀው ሊያወግዘው ይችላል፡፡ በዚህም መሠረት ጭቅጭቅ ቢነሳ በጓና ቀበሮው በነፃነት ትርጉም ፈጽሞ ሊግባቡ አይችሉም፤›› ብሏል፡፡ ይህንን እውነታ ደግሞ ሕዝብ በሚገባ እንዲረዳው ምሁራን ገለልተኛ ወይም አኩራፊ ሳይሆኑ፣ በየጊዜው በቅንነት ማስተማር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሊሸሹት የማይችሉት ኃላፊነታቸው መሆኑንም ሊያውቁት ይገባል፡፡

የሕዝባዊ ነፃነት አስፈላጊነት የጥቂት ግለሰቦች አመራር ተወግዶ ሕዝባዊ አመራር እንዲተካ እንደመሆኑ መጠን፣ ሕዝብ ወደዚህ አቅጣጫ የሚጓዝበትን መንገድ ቀና ከሆነ አስተሳሰብ ተነስቶ እገዛ መስጠት አስፈላጊ ይሆናል፡፡

‹‹ግመሎች ተቀጣጥለው በሚጓጓበት ጊዜ ፍጥነታቸውን እንዲጨምሩ የኋለኛውን መደብደብ ፋይዳ አይኖረውም፤›› ይባላል እርግጥም ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እንዲገነባ ከተፈለገ ነፃነቱን በትክክለኛ መንገድ እንዲጠቀምበት፣ በሰላም፣ በፍቅር፣ በመቻቻል፣ በመተሳሰብ፣ በመተባበር ማስተማርና ማስተባበር እንዲኖር ዕውቀት አስፈላጊ ነውና ከመጠምጠም መማር መቅደም ይኖርበታል፡፡ ለዚህ ደግሞ ዓይነተኛው መሣሪያ የፕሬስ ውጤት ነው፡፡

ሕዝብ የፕሬስ ነፃነትን ያህል ከፍተኛ መሣሪያ አንግቦ ሊጠቀምበት ሲገባ፣ ይህንን መሣሪያ በጥቅም ላይ ሳያውለው ቢቀር መጭው ትውልድም ቢሆን ይፈረድበታል እንጂ አይፈረድለትም፡፡ አሁን ‹‹እውነተኛ ነፃነት ሊፀድቅ የሚችለው የእብሪተኞች ደም ሲጠጣ ነው›› የሚለው ከእብሪተኞች የባሱ እብሪተኞች መፈክር በፍፁም ተገቢ እንዳልሆነም ማስተዋል ተገቢ ይሆናል፡፡ መሠረታዊ ጉዳይ ግን ዴሞክራሲን ለማስፈን ምን ያህል ዴሞክራቶች ነን? ለነፃነት ምን ያህል ነፃ ነን? የሚለውን መሪ መጠይቅ ከመመለሱ ላይ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...