Sunday, April 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርስለአረጋዊያን ሕፃናትና የአዕምሮ ሕሙማን ሐሳብና መፍትሔው

ስለአረጋዊያን ሕፃናትና የአዕምሮ ሕሙማን ሐሳብና መፍትሔው

ቀን:

በኢትዮጵያ ምድር አረጋዊያን፣ ሕፃናትና የአዕምሮ ሕሙማን የሚበሉትና የሚረዳቸው አጥተው ሲሰቃዩ ማየት ከእግዚአብሔር ቁጣና ቅጣት ያመጣል፡፡ እንደዚሁም በረከትን ያሳጣል፡፡ በጨረሻው ቀን በእግዚአብሔር የፍርድ ወንበር ፊት መቆም ያመጣል፡፡ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ማኅበራዊ ሕይወት ቀውሶች ከዕለት ወደ ዕለት እየተበራከቱና እየተባባሱ ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ ይህን ችግር እያዩ እንዳላዩ ዝም ማለትና መፍትሄ አለመፈለግ ህሊና የሚጎዳና የሚያስጠይቅ ጉዳይ ይሆናል፡፡ ማንኛውም ሰው እኔ በእነሱ ቦታ ብሆንስ ብሎ ቆም ብሎ ማሰብ አለበት፡፡ አለበለዚያ ሰው ከእንስሳ በምን መልኩ ይለያል?

አረጋውያን በእርጅና ምክንያት መሥራት ስለማይችሉና ጠዋሪ ስለሌላቸው፣ በየመንገዱና በየቤተ ክርስቲያኑ ደጃፍ ወድቀው በልመና ላይ ይገኛሉ፡፡ እንደዚሁም ወላጅ አልባ ሕፃናትን ተንከባክቦና ደግፎ የሚያሳድጋቸው በማጣታቸው፣ ይኸው በየጎዳናው ወድቀውና ተጥለው ለተለያዩ ችግሮችና በሽታዎች ተጋልጠው ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም በአገራችን ባለው ማኅበራዊ ሕይወት ቀውስና በሰው ሠራሽ ችግሮች ምክንያት በተለይ በአሁን ወቅት የአዕምሮ ሕሙማን ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት እየባሰና እየጨመረ መጥቷል፡፡ በየቀኑ በተለያዩ ቦታዎች ራሳቸውን ስተው፣ ራቁታቸውን የሚሄዱ ሰዎችን ማየት በቂ ማስረጃ ነው፡፡

ይህን በአገራችን ላይ የተንሰራፋውን ችግር በግንባር ቀደምትነት ለመፍታት መጣርና መሥራት የነበረባት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ብትሆንም፣ እስከ አሁን ዝም ብላ እያየች ትገኛለች፡፡ ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያኗ የሰብዓዊነት ሥራ መሥራት አለባትና፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ይህን ችግር መፍታት የነበረበት መንግሥት ሲሆን፣ ችግሩን በዘለቄታው ለመፍታት የሚያደርገው ጥረት አይታይም፡፡ ችግሩም ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ ከመምጣት በስተቀር አልተፈታም፡፡

የአንድ አገር ልማት ትርጉም ምን ማለት ነው? ሠርቶ ማደር የሚችለውን ብቻ በመደገፍ የተሻለ ኑሮ እንዲኖረው ማድረግ ነው? ወይስ አረጋዊያንና ሕፃናቱ መደገፍ የለባቸውም? እነሱ ኢትዮጵያውያን አይደሉምን? የአገሪቷ ልማት እነሱን አይመለከትም?

ስለዚህ ይህንን ጉዳይ በጥልቀትና በስፋት መመልከት ይገባል፡፡ የሆነ ሆኖ ይህንን ችግር ለመፍታት መንግሥት አቅምና ገንዘብ የለኝም ሊል ይችላል፡፡ ይህ ዓይነቱ ግን ምክንያት ሆኖ መቅረብ አይችልም፡፡ ምክንያቱም የተለያዩ ዘዴዎችንና የሥራ ስልቶችን መቀየስ ይችላልና፡፡ አሁን መንግሥት ይህንን ችግር ለመፍታት ከራሱ ካዝና ገንዘብ ያውጣ ወይም ይመድብ አንልም፡፡ እኛ ዜጎቹን ያስተባብረንና የመፍትሔ ሐሳብ ያቅርብ፡፡ ከእያንዳንዳችን ኪስ የምናወጣበትና የምንደግፍበት የአሠራር ስልት ሥራ ላይ ያውል ነው የምንለው፡፡ ስለዚህ በኢትዮጵያ ያለው ማኅበራዊ ሕይወት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሚከተለውን ሐሳብ አቀርባለሁ፡፡

ለምሳሌ በኢትዮጵያ በትንሹ አንድ ሚሊዮን የመንግሥትና የግል ድርጅት ሕጋዊ ግብር ከፋይ ሠራተኞች ቢኖሩ፣ በተጨማሪም አራት ሚሊዮን ሕጋዊ ግብር ከፋይ ነጋዴዎች ቢኖሩ እያንዳንዱ ሠራተኛም ሆነ ነጋዴ በወር በትንሹ አሥር ብር ቢከፍል ወይም ቢያዋጣ፣ በወር በትንሹ ሃምሳ ሚሊዮን ብር መሰብሰብ ይችላል፡፡ ነገር ግን ከዚህ በላይ እስከ አንድ መቶና ሁለት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ የመሰብሰብ ዕድል ሊኖር ይችላል፡፡

በየወሩ ይህን እንዴት መሰብሰብ ይቻላል? አፈጻጸሙ እንዴት ይሆናል? ለሚለው ጥያቄ መልሱ እንደሚከተሉው ይሆናል፡፡ እንደሚታወቀው የመንግሥት ግብር ሰብሳቢ መሥሪያ ቤት ከእያንዳንዱ የግልም ይሁን የመንግሥት ሠራተኛ በየወሩ የሥራ ግብር (Income tax) እየሰበሰበ ለገንዘብ ሚኒስቴር ያስረክባል፡፡ በተመሳሳይ መንገድ ማኅበራዊ ዋስትና (Social Service) በሚል መለያ የራሱ የሆነ የተለየ ኮድ ተሰጥቶት የደሞዙን አንድ ከመቶ ቀጥታ ከደመወዝ መከፈያ ሰነድ ላይ ልክ እንደ የሥራ ግብር ተቆርጦ ለገንዘብ ሚኒስቴር በየወሩ ገቢ ማስደረግ ይቻላል፡፡

ሁለተኛ ነጋዴውን በተመለከተ ግብር ሊከፍል በሚመጣበት ወቅት በሚከፍልው የግብር መጠን ላይ አሁንም የገቢውን አንድ ከመቶ ተጨማሪ እንዲከፍልና አሁንም የተለየ የራሱ መለያ ተሰጥቶት ግብር ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት ስብሰቦ ለገንዘብ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ቢያስረክብ፣ ያለሐሳብና ያለችግር ዘላቂ የሆነ ገቢ ማግኘት ይቻላል፡፡ የተሰበሰበው ገንዘብም አግባብ ባለው መንገድ በበጀት ወጪ እየሆነ የአገራችንን ችግር መፍታት ይቻላል፡፡

አሁን ሠራተኛውም ሆነ ነጋዴው ለዓባይ ግድብ በየወሩ የሚቆረጡ ወጪዎች አሉበት፡፡ በተጨማሪም ኑሮውም በጣም ከብዷል፡፡ መቋቋም አይቻልም የሚል ሐሳብ ሊመጣ ይችላል፡፡ ነገር ግን ነገሩን ሰፋ አድርገን ካየነው አንድ ለአንድ መደጋገፋችን የግድ ነው፡፡

ለምሳሌ የአንድ ሺሕ ብር ደመወዝተኛ በወር የሚያወጣው አሥር ብር ብቻ ነው፡፡ የሁለት ሺሕ ብር ደመወዝተኛ ሃያ ብር፣ እንደዚሁም የአምስት ሺሕ ብር ደመወዝተኛ ሃምሳ ብር ብቻ ነው፡፡ ይሄ እንግዲህ ካለው የአረጋዊያንና የሕፃናት ችግር አንፃር ስናየው፣ ሠራተኛውን ይጎዳዋል ማለት እነሱ የሚበሉትና የሚደግፋቸው አጥተው ይሙቱ፣ ይሰቃዩ እንደ ማለት ይሆናል፡፡

ነጋዴው ኅብረተሰብን በተመለከተ ለምሳሌ በዓመት ከሁለት ሺሕ እስከ አሥራ ሁለት ሺሕ ብር ዓመታዊ ግብር የሚከፍሉ ነጋዴዎች፣ በሙሉ በየወሩ አሥር ብር ወይም በዓመት 120 ብር በተጨማሪ እንዲከፍሉ ቢደረግ፤ እንዲሁም ከአሥራ ሁለት ሺሕ ብር በላይ ዓመታዊ ግብር የሚከፍሉ ነጋዴዎችን ከሚከፍሉት የግብር መጠን ላይ አንድ ከመቶ በተጨማሪ እንዲከፈሉ ቢደረግ ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ በዓመት 25,000 ብር፣ 50,000 ብር፣ 100,000 ብር እና 1,000,000 ብር የሚከፍሉ ነጋዴዎች፣ እንደ ቅደም ተከተላቸው በዓመት የሚያደርጉት አስተዋጽኦ 250 ብር፣ 500 ብር፣ 1,000 ብር እና 10,000 ብር ነው፡፡ ይኼ በየወሩ ሲሰላ በጣም ትንሽና ነጋዴውን ኅብረተሰብ የማይጎዳ ነው፡፡ ስለዚህ ተደጋግፈንና ተረባርበን የአገራችንን ችግር በዘላቂነት ካልፈታን ከሕሊና ወቀሳና ተጠያቂነት አንድንም፡፡ በተጨማሪም በውጭ ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በዘመኑ ቴክኖሎጂ ተጠቅመው ሳይንገላቱ፣ ባሉበት የሥራ ቦታ ሆነው ወደ ኤምባሲ መሄድ መምጣት ሳይኖርባቸው በወር አንድ ዶላር የሚከፍሉበት ዘዴ ቢመቻችላቸው፣ ምንም በማይጎዳቸው መልኩ በብዙ የሚገመት ድጋፍ ማድረግ ይችላሉ፡፡

አረጋዊያን፣ ሕፃናትና የአዕምሮ ሕሙማን የሚንከባከቡ ማዕከላት እንዴትና የት ይመሥረቱ ለሚለው ጥያቄ፣ ሁሉም ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች የየራሳቸው ማዕከላት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ለምሳሌ ትግራይ፣ አፋር፣ ሶማሌ፣ ጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ሐረሪና ድሬዳዋ እያንዳንዳቸው አንዳንድ ማዕከል ቢኖራቸው፤ እንደዚሁም አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ሕዝቦችና አዲስ አበባ ሁለት ሁለት ማዕከላት ለመጀመርያ ጊዜ ቢኖራቸውና ለወደፊቱ ግን አቅምና የችግሩ ስፋት እየተገናዘበ ተጨማሪ ማዕከላት ይሠራሉ፡፡ በዚህ መልኩ ለመጀመርያ ጊዜ አሥራ አምስት ማዕከላት ብንከፍትና በየወሩ ስልሳ ሚሊዮን ብር ገቢ ቢገኝ ወይም ቢሰበስብ አንድ ማዕከል አራት ሚሊዮን ብር ብር ወርሃዊ በጀት ይኖረዋል ማለት ነው፡፡

ማዕከላቱ የሚገነቡበት ገንዘብ ከየት ይገኛል? ለሚሉ ሥራ ላይ ከዋለ በኋላ ለመጀመርያ ስድስት ወራት ገንዘቡ እንዲሰበሰብና በዚያ መነሻነት መሥራት ይቻላል፡፡ በዚህ ዘዴ የአገራችንን ችግር ደረጃ በደረጃ እየፈታንና እርስ በራሳችን እየተደጋገፍን ዘላቂ መፍትሔ ካላመጣን፣ ዝም ብለን ከንፈራችንን ብንመጥ ዋጋ የሌለው ነው፡፡ አንዳንድ በጎ የሚያስቡ ሰዎች የሚያደርጉት ጥረት ዓመት ጠብቀው በሚዘጋጁት የድጋፍ ማሰባሰቢያና ገቢ ማስገኛ ዝግጅት በአጠቃላይ በመላው ኢትዮጵያ ያለውን ችግር ይፈታል ማለት የማይታሰብ ነው፡፡ ከላይ በተገለጸው ሐሳብ መሠረት በመላ ኢትዮጵያ የሚገኘውን ሠራተኛም ሆነ ነጋዴ በማሳተፍና በማስተባበር፣ ካለሐሳብና ልመና ቀጥተኛና ቋሚ ገቢ ካልተገኘ በስተቀር፣ የአገራችን ችግር ጥቂት ሰዎችን በማሳተፍ፣ ጥቂት ሰዎችን በመርዳት፣ የልመና ዝግጅት በማዘጋጀት የማኅበራዊ ሕይወት ችግር ይፈታል ማለት የማይሆን ነው፡፡

በአጠቃላይ ይህ የመትፍሔ ሐሳብ ነገሩን ሰፋ አድርጎ በማሰብና በማገናዘብ ተጨማሪ ሐሳቦችና ዘዴዎች ካሉ በመጨመር የአገራችን ማኅበራዊ ሕይወት ቀውስ ተፈትቶና አረጋዊያን የሚበሉት አጥተው ጎዳና ላይ ከመውጣት ድነው፣ ሕፃናት የሚያሳድጋቸውና የሚንከባከባቸው አጥተው መንገድ ላይ ከመውደቅ ድነው፣ የአዕምሮ ሕሙማን ለሕክምና የሚደግፋቸው አካል አጥተው ከመሰቃየት ድነው ለማየት ቸሩ እግዚአብሔር ይርዳን! አሜን!

***********

ግቡን ያልመታ ደንብ አይሻሻልምን?

ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከዩኒቨርሲቲ በጤና መኮንነትና በነርስ የተመረቁ ተማሪዎችን የሚመለከት አስገዳጅ የሥራ ስምሪት ደንብ አለ፡፡

ይህ ደንብ ከዩኒቨርሲቲ ከላይ በተጠቀሱት የጤና ሙያ የተመረቁ ተማሪዎች በተመደቡበት ቦታ እንዲሠሩ ለማስገደድ ከሌሎች ተማሪዎች በተለየ ጊዜያዊ የትምህርት ማስረጃን ይከለክላል፡፡ የትምህርት ማስረጃውን በተመደቡበት ቦታ ላይ ሳይሠሩ መውሰድ ከፈለጉ፣ የወጪ መጋራት ሒሳቡን ሁለት እጥፍ እንዲከፍሉ ያስገድዳል፡፡

የደንቡ ዓላማ ሰፊው ገበሬ የጤና አጠባበቅ በአቅራቢያው እንዲያገኝ በመሆኑ ትክክል ነው፡፡ አገራዊና ትውልዳዊ ፋይዳው እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ የሚደገፍ ነው፡፡ ነገር ግን እኔ በቅርብ እንደተገነዘብኩት በበርካታ ተመራቂዎች ተቃውሞ ስለገጠመው፣ ደንቡ የተነሳበትን ዓላማ በተሟላ መንገድ አላሳካም፡፡ ምክንያቶቹ አያሌ ቢሆኑም ዋና ዋናዎቹ የተመራቂዎች ዝግጁነት አለመኖር፣ የተመደቡበት አካባቢ የኑሮ ሁኔታ አስቸጋሪነትና ሕይወትን በአቋራጭና በቀላሉ ከመምራት ፍላጎት የመነጨ ነው፡፡

ስለሆነም ብዙዎቹ ተመራቂዎች በዕጣ ወደተመደቡበት ቦታ አንደሄድም ብለው ቤት ሲቀሩ፣ ጥቂቶቹ ደግሞ የተመደቡበት ቦታ ደርሰው ለትንሽ ጊዜ ሠርተው ተመልሰው ቤት ውልዋል፡፡ የተመለሱት ምሩቃንም አቅም ያላቸው ወላጆቻቸውን በማሳመን የወጪ መጋራት ክፍያውን ከፍለው የቀናቸው ወደ ውጭ አገር ሲሄዱ፣ ከፊሎቹ ደግሞ በአገር ውስጥ ትምህርታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ቀሪዎቹ ደግሞ በተቀራራቢ ሙያ ወይም በሙያቸው በግል ድርጅቶች ተቀጥረዋል፡፡ የራሳቸውን ሥራ ያቋቋሙት ጥቂቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች በዘመድ ከተረዱት ጋር ሲደመሩ ብዙ አይደሉም፡፡ ሌሎች ደግሞ በድብርት በሽተኛ ሆነው በአሳዛኝ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ፡፡

በቤት ውስጥ ቦዝነው ሲደብራቸውም በቤት ሠራተኝነት ተቀጥረው ወደ ዓረብ አገር ለስደት ተዳርገዋል፡፡ ከፊሎቹ ደግሞ ለእነሱ በማይመጥን ኢ-ሞራላዊ ሥራ በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህ በመሆኑ የወጪ መጋራት ክፍያው ባክኖ ከመቅረቱም በላይ፣ ከራሳቸው አልፈው ቤተሰብና አገር ይጠቅማሉ ተብለው ተስፋ የተጣለባቸው ዜጎች ባክነዋል፡፡ ይህ የአገርና የሕዝብ ኪሳራ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ስለሆነም በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን አድኖ አገርና ሕዝብ እንዲጠቅሙ፣ ደንቡ ሁሉንም አሸናፊ በሚያደርግ መንገድ መሻሻል የግድ ይላል፡፡ የግዳጅ ስምሪቱም ማሻሻሉ ተገቢ ነው፡፡ የማሻሻያው መፍትሔው እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

  1. የወጪ መጋራት ሒሳብ ቢበዛ በባንክ ወለድ እንዲወሰን ማድረግ፡፡
  2. ለሌሎች ምሩቃን እንደተደረገው ለጤና ባለሙያዎችም ጊዜያዊ የሥራ መፈለጊያ ማስረጃቸው ተለቆላቸው፣ በሙያቸው መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችና በግል ሠርተው በሙያቸው ወይም በተቀራራቢና ተመሳሳይ ሙያ ተቀጥረው ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ጠቅመው፣ የተማሩበትን የወጪ መጋራት ሒሳብ በመክፈል የአገርን ሀብት ከብክነት ማዳን አለባቸው፡፡

ይህ መፍትሔ ሁሉንም ወገኖች የሚጠቅም፣ በተለይ ወጣቱ በአገሩ ሥራ ላይ  እንዲያተኩር የሚያበረታታ ስለሆነ፣ ወጣቱን የሚያሳምኑ ደንቦች በየጊዜው ሊፈተሹ ይገባል፡፡ በተለይ ከመንግሥት ዘለቄታዊ የልማት ዓላማ ጋር በማጣጣም፣ ወጣቱ ትልውድ በሙያው እንዲሠራ ማትጋት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ስለዚህ  የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ይህን ቀና አስተሳሰብ ተመልክቶ ደንቡን እንዲያሻሽለው በርካታ ተማሪዎች በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡

(ደደ ዘገዬ፣ ከአዲስ አበባ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኦቲዝምን ለመቋቋም በጥምረት የቆሙት ማዕከላት

ከኦቲዝም ጋር የሚወለዱ ልጆች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ...

አወዛጋቢው የወልቃይት ጉዳይ

የአማራና ትግራይ ክልሎችን እያወዛገበ ያለው የወልቃይት ጉዳይ ዳግም እየተነሳ...

ተጠባቂው የቴሌኮም ኦፕሬተሮች የውድድር መለኪያ የሆነው የሞባይል ገንዘብ ዝውውር በኢትዮጵያ

የሞባይል ገንዘብ ዝውውር የሞባይል ስልክን በመጠቀም ሊገኙ የሚችሉ የፋይናንስ...

የአማራና ደቡብ ክልሎች ለሠራተኛ ደመወዝ መክፈል መቸገራቸውን የፓርላማ አባላት ተናገሩ

በአማራና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት...