Friday, July 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየኦሮሚያ መስታወት

የኦሮሚያ መስታወት

ቀን:

አባ ገዳና ሀደ ገዳ ከነሙሉ ባህላዊ አልባሳቸውና ቁሳቁሳቸው ይታያሉ፡፡ አጠገብ ለአጠገብ የቆሙትን የኦሮሞ ጥንዶች የሚያሳየው ግዙፍ ሀውልት የኦሮሞ ባህል ማዕከል መግቢያ ላይ ይገኛል፡፡ በኦሮሞ ማኅበረሰብ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው የገዳ ሥርዓትን የዕድሜ እርከን የሚያስቃኙ ሀውልቶች ከጥንዶቹ በቅርብ ርቀት ይታያሉ፡፡ የእያንዳንዱ እርከን አባል ያለበትን ኃላፊነት የሚያስረዱት ቅርጾች በዕድሜ ደረጃ ተቀምጠዋል፡፡

ደበሌ ከ0 እስከ 8 ዓመት ያሉ እንክብካቤ የሚሹ ሕፃናት ናቸው፡፡ ጋሜ ከ8 እስከ 16፣ ኩሳ ከ10 እስከ 24 ዓመት፣ ራባ ከ24 እስከ 32፣ ዶሪ ከ32 እስከ 40 እና ከ40 እስከ 48፣ ዮባ ከ48 እስከ 56፣ 56 እስከ 64 እና 64 እስከ 72 ዓመት በሚል ይታያሉ፡፡ በየዕድሜ እርከኑ ከብት የማገድ፣ ለጦርነት ልምምድ የማድረግ፣ ለመሪነት የመዘጋጀትና የመምራት ኃላፊነት ይጣልባቸዋል፡፡ አዛውንቶች የሚገኙበት እርከን ደግሞ ገደሞጂ ከ72 እስከ 80ና ጃርሳ ከ80 እስከ 88 ዓመት ነው፡፡

ሀውልቶቹን አልፈው ወደ ማዕከሉ ሲዘልቁ ሙዝየም፣ ቤተ መጻሕፍት የጥናትና ምርምር ማዕከል፣ የቴአትርና ሲኒማ አዳራሽ እንዲሁም ሌሎች ክፍሎችን ያገኛሉ፡፡ በቅርቡ ተመርቆ ሥራ የጀመረው የኦሮሞ ባህል ማዕከልን በጎበኘንበት ወቅት ከክልሉ ዘጠኝ ዞኖች የተውጣጡ ቅርሶችን ተመልክተናል፡፡

የማዕከሉ ዋነኛ የቱሪስት መስህብ ሙዝየሙ ነው፡፡ በውስጡ ከሚገኙ ክፍሎች የኢትኖግራፊ (ባህላዊ ቅርሶች) ስብስብ ክፍል አንዱ ነው፡፡ በኦሮሚያ ክልል ካሉ ዞኖችና አዋሳኞቻቸው የተሰባሰቡ አልባሳት፣ መገልገያ ቁሳቁሶችና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡ የሸዋ፣ የጅማና ኢሊባቡር፣ የወለጋ፣ የጉጂና የቦረና፣ የሐረርጌና የወሎ፣ የአርሲና የባሌ እንዲሁም የራያና ከሚሴ ይጠቀሳሉ፡፡

ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች፣ ገበጣን የመሰሉ ባህላዊ ጨዋታዎች የሚከናወኑባቸው ቁሳቁሶች እንዲሁም ለጦርነት የሚውሉ መሣሪያዎች ይገኛሉ፡፡ ጦር፣ ጋሻ፣ ጎራዴና በጦርነት ወቅት የሚደረጉ ባህላዊ አልባሳት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

የክልሉን ማኅበረሰባዊ ገፅታ የሚያሳዩ የሽመና መሣሪያዎች፣ የንብ ቀፎና የእርሻ መሣሪያዎች ይጠቀሳሉ፡፡ በሌላ በኩል በገዳ ሥርዓት በተለያየ ዕድሜ ክልል ያሉ እንዲሁም የክልሉ ሴቶችና ወንዶች ለክብረ በዓላት የሚለብሷቸው ለዕይታ ቀርበዋል፡፡ መዋቢያዎችና በአልባሳት ላይ የሚታከሉ ጌጣጌጦችም በሙዝየሙ ይገኛሉ፡፡

በኦሮሚያ ክልል ልዩ ልዩ ዞኖች ውስጥ ያሉ ነዋሪዎች በሚያካሂዷቸው ማኅበራዊ ክንውኖች የሚጠቀሙባቸው የመመገቢያ ጠረጴዛ፣ ወንበርና መመገቢያ እንዲሁም የቡና ሥነ ሥርዓት ቁሳቁሶች ትኩረት ሳቢ ናቸው፡፡

ረዥም ዕድሜ ያስቆጠሩ ቅሪተ አካሎች የሚገኙበት የአርኪዎሎጂ ክፍልም በሙዝየሙ ይገኛል፡፡ በኦሮሚያ ክልል የተገኙና ከ1.7 ሚሊዮን ዓመታት በላይ ያስቆጠሩ የሰው ልጅ ቅሪተ አካሎችና ቁሳቁሶች ይጠቀሳሉ፡፡ አብዛኞቹ ከመልካ ቁንጥሬ አካባቢ የተሰባሰቡ ቅሪተ አካሎች ሲሆኑ፣ በየዕድሜ ዘመናቸው ተከፋፍለው ይታያሉ፡፡

የሙዝየሙ ሌላው ክፍል የተፈጥሮ ሀብት የሚታይበት ነው፡፡ የዱር እንስሳት ቅሪተ አካሎችና በኬሚካል የደረቁ እንስሳት ይገኛሉ፡፡ ድኩላ፣ ኒያላ፣ ቆርኬ፣ ከርከሮ፣ የሜዳ ፍየልና ጉማሬ ከእንስሳቶቹ ጥቂቱ ናቸው፡፡

በሙዝየሙ ቴአትርና ፊልምን የመሰሉ ጥበባዊ ሥራዎች የሚታዩበት አዳራሽ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶችና ስብሰባዎች እየተስተናገዱበት ነው፡፡ ከአዳራሹ ጎን ለኪነ ጥበብ ሥልጠና የሚውል ቦታ ተዘጋጅቷል፡፡

የማዕከሉ መረጃ ማከማቻ ማዕከልና ቤተ መጻሕፍቱ ስለኦሮሞ ባህልና ታሪክ ግንዛቤ የሚሰጡ መዛግብት ያሰባስባል፣ ለንባብ ያበቃል፡፡ ከክልሉ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ረዥም ዕድሜ ያስቆጠሩ አገራዊ መዛግብት ያሉ ሲሆን፣ አገሪቱ እንዲሁም ክልሉ ያለፉበትን ታሪክ ያሳያሉ፡፡

ማዕከሉ አሁን መደበኛ አገልግሎት የሚሰጥ ካፍቴሪያ አለው፡፡ በካፍቴሪያው በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ባህላዊ ምግቦችና መጠጦች እንዲቀርቡ የማድረግ ዕቅድ እንዳለ ለማወቅ ችለናል፡፡ ስለ ባህላዊ ምግቦችና መጠጦች ግንዛቤ ለመፍጠርና እንደ ቱሪስት መስህብም ያገለግላል፡፡

ክልሉን በሥዕልና በፎቶግራፍ የሚገልጹ የጥበብ ውጤቶች በማዕከሉ ይገኛሉ፡፡ የክልሉን ባህላዊ አለባበስና የተፈጥሮ ሀብት ከሚያሳዩ ሥዕሎች መካከል የለማ ጉያ፣ ኤልያስ አረዳ፣ የቡርቱካን ጅማና የግርማ ቡልቲ ሥዕሎች ይጠቀሳሉ፡፡ የማኅበረሰቡን ታሪክና ነባራዊ ሁኔታ የሚያንፀባርቁ መረጃዎች፣ ታሪካዊ ሥፍራዎችና የተፈጥሮ ሀብቶችን የሚያሳዩ የዕደ ጥበብ ውጤቶች በማዕከሉ ያሉ ሲሆን፣ በምስል፣ በቪዲዮና በድምጽ የሚገኙ መረጃዎች በቤተ መዛግብቱ ተቀምጠዋል፡፡

አቶ ሁሴን ኢንዴሳ የማዕከሉ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ማዕከሉ የተቋቋመበት ዋነኛ ዓላማ የኦሮሞን ባህል፣ ቋንቋ፣ ጥበብ፣ ታሪክና ቅርስ አጥንቶና ሠንዶ ለሕዝብ ለማሳየት ነው ይላሉ፡፡ ማዕከሉ ቅርሶችን አሰባስቦ ከማሳየት ጎን ለጎን ቅርሶች በሚገኙበት አካባቢ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ያደርጋል፡፡ ቅርሶች የሚገኙባቸው አካባቢዎች ነዋሪዎች ሀብቶቻቸውን ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚያውሉበት መንገድም ይመቻቻል፡፡

በጥበብ ዘርፍ የሙዚቃና ስዕል ክፍልን መጥቀስ ይቻላል፡፡ አቶ ሁሴን እንደሚሉት፣ የክልሉ የሙዚቃ ሀብቶች ሰፊ ጥናት ተደርጎባቸዋል ለማለት አይቻልም፡፡ የማዕከሉ ጥናትና ምርምር በዘርፉ ሰፊ ሥራ እንደሚጠብቀው ገልጸው፣ የተሰባሰቡትን ሙዚቃ ነክና ሌሎችም ጥበባዊ ሥራዎች በመድረክ የማሳየት ዕቅድ አለን ብለዋል፡፡

በማዕከሉ ከሚገኙት አንዱ የጥናትና ምርምር ተቋም ነው፡፡ በክፍሉ የኦሮምኛ ቋንቋ ጥናትና ምርምር የሚካሄድ ሲሆን፣ የቋንቋው አመጣጥና እየሰጠ ያለው ግልጋሎት እንዲሁም ሌሎች ማኅበራዊና ሳይንሳዊ ጉዳዮችም ይጠናሉ፡፡ ዳይሬክተሩ እንደሚገልጹት፣ የማኅበረሰቡን ለውጥ ተከትሎ የሚመጣውን የቋንቋ ዕድገት የሚያሳዩ ጥናቶች ለተጨማሪ ምርምሮች መዋል ይችላሉ፡፡ ስለየአካባቢው የአነጋገር ዘይቤ (ዳይሌክት)ና የቃላት አጠቃቀም የሚያስገነዝቡ መረጃዎችንም በማዕከሉ ማግኘት ይቻላል፡፡

‹‹ቅርስ ያለፈውን ትውልድ ከዛሬው ጋር የሚያስተሳስር መሆኑ እሙን ነው፤›› የሚሉት አቶ ሁሴን፣ ማዕከሉ ጥናት ሲያካሂድ ምን ዓይነት ቅርሶች የት አካባቢ ይገኛሉ ከሚለው እንደሚነሱ ይገልጻሉ፡፡ በመቀጠል ጥቅም ላይ የሚውሉበት ወይም እንደ ታሪክ የተያዙበት ሁኔታ ይጠናል፡፡ ጥናቱ የአሁኑ ትውልድ ስለቀደመው መረጃ የሚያገኝበትና ተመራማሪዎች ጥናት እንዲያካሂዱ የሚያነሳሳ ነው፡፡ ዳይሬክተሩ፣ ቅርሶቹ ማኅበረሰቡ ስለማንነቱ የጠለቀ መረጃ እንዲያገኝ የሚያግዙ ከመሆናቸው ባሻገር የቱሪስት መስህብ ናቸው ይላሉ፡፡

አቶ ሁሴን እንደሚናገሩት፣ በጥናትና ምርምር ክፍሉ የሚካሄዱ ጥናቶች መፍትሔ አመላካች እንዲሆኑ ይፈለጋል፡፡ ‹‹ጠቀሜታ እንደሚኖራቸው ወይም ችግር እንደሚፈቱ የታመነባቸው ጉዳዮች ላይ ጥናቶች ይካሄዳሉ፤›› የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ ጥናት ከተሠራ በኋላ ለሕዝብ ክፍት ይሆናል ይላሉ፡፡ በተለይ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር የመሥራት ዕቅድ እንዳላቸው ይገልጻሉ፡፡

ሙዝየሙ አሁን አስፈላጊ ግብዓቶችን በማሟላት ላይ እንደሚገኝ አቶ ሁሴን ይናገራሉ፡፡ ከፍተኛ ክፍተት የፈጠረው በጥናትና ምርምር ክፍሉ የሚሠሩ ተመራማሪዎች እጥረት ነው፡፡ በመጪው ዓመት ጥናት የሚደረግባቸው ርዕሰ ጉዳዮች የተመረጡ ሲሆን፣ ተመራማሪዎች ሲሟሉ እንደሚጀመር ይናገራሉ፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፣ አሁን ሙዝየሙና አጠቃላይ የባህል ማዕከሉ ከሚፈለገው አንድ አራተኛ ሠራተኛ ብቻ ነው ያለው፡፡ ባለሙያ አሟልቶ የጥናትና ምርምር ማዕከሉን የማጠናከርና ሙሉ መረጃ የሚሰጥ የማድረግ ዓላማ አላቸው፡፡ በክልሉ የሚገኙና በሙዝየሙ መካተት ያለባቸው ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶችን የማሰባሰብና በየፈርጃቸው የማደራጀት ሥራው ቀጣይነት ይኖረዋል፡፡

የቴአትርና ፊልም አዳራሹ በቋሚነት አገልግሎት እንዲሰጥ መርሀ ግብር እየወጣ ነው፡፡ ሙዝየሙ በሁሉም ቀናት እንዲጎበኝ የማሰናዳትና የክፍያ መጠን የመተመን ሥራም እንዳጠናቀቁ ይናገራሉ፡፡

‹‹ሙዝየሙ ለኦሮሚያ ክልል ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፤ የቱሪስት ፍሰቱንም ይጨምራል ብለን እንጠብቃለን፤›› ያሉት አቶ ሁሴን፣ ማዕከሉ ከተመረቀበት ጊዜ አንስቶ የበርካታ ጎብኚዎች መዳረሻ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ከጎብኚዎቹ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ከፍተኛውን ቁጥር ሲይዙ፣ የውጪ አገር ቱሪስቶችም እየጎበኙ ነው፡፡

‹‹ባህል ማለት ሕዝብን የሚያስተሳስር ነው፤ የማንኛውም ብሔር ተወላጅ በኦሮሚያ ክልል መዘዋወር ሳያስፈልገው ከማዕከሉ በርካታ መረጃ ማግኘት ይችላል፤ ማንኛውንም ባህል ማወቅ የሰውን ልጅ የዕውቀት አድማስ ያሰፋል›› የሚሉት አቶ ሁሴን፣ ሌሎች ክልሎችም ባህላቸውን የሚያስተዋውቁባቸው ማዕከሎች ቢያቋቁሙ መልካም ነው ይላሉ፡፡

የባህል ማዕከሉ ሙዝየም ኪውሬተር አቶ ማሞ ሰቦቅሳ እንደሚናገረው፣ በሙዝየሙ የሚገኙ መዛግብትና ባህላዊ ቁሳቁሶች የክልሉን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሥርዓት ያንጸባርቃሉ፡፡ እንደ ምሳሌ የጠቀሰው በተለያዩ ዞኖች ያለውን የአመጋገብ ሥርዓት ነው፡፡ በኅብረት መመገብ የኅብረተሰቡን ትስስርና ኢኮኖሚያዊ ደረጃ የሚያሳይ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ በሌላ በኩል የጦር መሣሪያዎቹ ክልሉ ያለፈበትን ፖለቲካዊ አውድ ያመላክታሉ ይላል፡፡ ሌሎች በማዕከሉ የሚገኙ ቅርሶች ባህልና ታሪኩን ለመተንተን ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸው ይናገራል፡፡

ቅርሶች የማሰባሰብ ሥራ እንደማይቆም፤ በስብስቡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ዓለም አቀፋዊነት ሲስፋፋ አገልግሎት መስጠት ያቆሙ ቁሳቁሶች እንደሚካተቱ አስተያየት ይሰጣሉ፡፡ በሌላ በኩል ኦሮሚያና ሌሎች ክልሎች የሚጋሯቸውና የኦሮሚያን ክልል ባህልና ታሪክ የሚያንፀባርቁ ቅርሶች ይሰባሰባሉ፡፡

በሙዝየሙ ያሉ መዛግብት፣ ባህላዊ ቁሳቁሶች፣ ቅሪተ አካሎችና የጥበብ ሥራዎች በተለያየ መንገድ ተገኝተዋል፡፡ የተለያዩ ዞኖች መገለጫ የሆኑ ባህላዊ ቁሳቁሶች በየአካባቢው ባሉ አዛውንቶችና የባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች አማካይነት ተሰባስበዋል፡፡

የማዕከሉ ግንባታ ዘጠኝ ዓመታት የፈጀ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት ተጠናቆ መጋቢት 16 ቀን ተመርቋል፡፡ አዲስ አበባ ስታዲየም አካባቢ የተገነባው ማዕከሉ በ57 ሺሕ 100 ካሬ ሜትር ላይ ሰፍሯል፡፡ ማዕከሉ 311 ሚሊዮን ብር ወጥቶበታል፡፡ በምረቃው ላይ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሙክታር ከድር፣ አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳና ሌሎችም ተገኝተው ነበር፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...