Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየፔዳጐጂ ዋጋ

የፔዳጐጂ ዋጋ

ቀን:

በኢኮኖሚክስ የትምህርት ዘርፍ በማይክሮ ኢኮኖሚክ ትምህርት ከሚሰጡ ቲዎሪዎች መካከል ‹‹ጌም ቲዎሪ›› አንዱ ነው፡፡ ቲዎሪውን የፈለሰፈው ኬቭን ናሽ የተባለው የሒሳብ ባለሙያ ነበር፡፡

ከዓመታት በፊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ተማሪ የነበሩት አቶ ሙሉጌታ አበበ (ስማቸው ተቀይሯል) ቲዎሪውን የሚያስተምሩ ሁለት አስተማሪዎች እንደነበሩ ያስታውሳሉ፡፡ አንደኛው መምህር በዘርፉ የዶክትሬት ዲግሪ አላቸው፡፡ ሁለተኛው መምህር ደግሞ በኢኮኖሚክስ የማስተርስ ዲግሪ አላቸው፡፡ ይሁን እንጂ በትምህርት አሰጣጥ ክህሎታቸው የዶክትሬት ዲግሪ ካላቸው የማስተርስ ዲግሪ ያላቸው መምህር ችሎታ ይልቅ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

ልዩነታቸውን ነቅሰው ሲያወጡም በተለይም በጌም ቲዎሪ ላይ የነበረውን የመማር ማስተማር ሒደት ያነሳሉ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹‘ዛሬ የማስተምራችሁ ስለጌም ቲዎሪ ነው’ በማለት ሰሌዳው ላይ ጻፈ፡፡ ስለቲዎሪው የምናውቀው እንዳለም ጠየቀን፡፡ ነገር ግን ማንም እጁን አውጥቶ አልመለሰም፤›› ያሉት አቶ ሙሉጌታ አፍታም ሳይቆይ ከመምህሩ የተሰነዘረላቸውን ተጨማሪ ጥያቄ ለመመለስ የክፍሉ ተማሪ በሙሉ እጁን እንዳወጣ ይናገራሉ፡፡ ጥያቄውም በወቅቱ ቦክስ ኦፊስ ላይ የሚገኘውን ‹‹ዘቢውቲፉል ማይንድ የተሰኘውን ፊልም አይታችኋል?›› የሚል ነበር፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ ስለፊልሙም የተወሰኑ ተማሪዎች ተርከዋል፡፡ ሌሎቹም ቢሆኑ በፊልሙ ዙሪያ ከመምህራቸው የተሰነዘረላቸውን ጥያቄ ተረባርበው ሲመልሱ ነበር፡፡ መምህሩም ተማሪዎቹ ስለፊልሙ የነበራቸውን ግንዛቤ ካረጋገጡ በኋላ የ‹‹ጌም ቲዎሪ›› ፈላስፋ ስለነበረው ኬቭንናሽ ሕይወትና ስለፍልስፍናው እንደሆነ ነገሯቸው፡፡

በክፍሉ የሚገኙ ተማሪዎችም በፊልሙ ላይ ስለሚታዩ ገፀ ባህሪያትና ፍልስፍና እርስ በርስ ተወያዩ፡፡ በመጨረሻም መምህራቸው ለአሥር ደቂቃዎች ያህል ተጨማሪ ማብራሪያ ሰጧቸው፡፡ በወቅቱ በክፍሉ ውስጥ የነበሩ ተማሪዎች ስለቲዎሪው በቂ ግንዛቤ አዳብረው እንደነበር የሚናገሩት አቶ ሙሉጌታ በቲዎሪው ዙሪያ የወጣውን ፈተና ከሌላ ክፍል ተማሪዎች በተለየ ውጤት ማስመዝገባቸውን ያስታውሳሉ፡፡ አጋጣሚው በመደጋገሙም የሌላ ክፍል ተማሪዎች በእነ አቶ ሙሉጌታ ክፍል ለመማር ይጋፉ ጀመር፡፡

አቶ ሙሉጌታ እንደሚሉት መምህራቸው ለተማሪዎቹ በሚገባቸው መንገድ ለማስተማር የሚያደርጉት ጥረት ይሳካላቸዋል፡፡ ‹‹እኛን በሚገባን መልኩ ያስረዳናል፡፡ የዛኔ ጎረምሶች ነበርን፡፡ ሂፕ ሆፕ፣ ራፕ፣ ሬጌ የሙዚቃ ስልቶችን ማድመጥና በቦክስ ኦፊስ ላይ የሚገኙ ፊልሞችን መከታተል ይቀናን ነበር፡፡ የጌም ቲዎሪን የሚያስተምረን መምህር የማስተርስ ዲግሪ ያለው ሲሆን፣ ትምህርቱንም ከውሎአችን ጋር አዛምዶ ያስረዳን ነበር፡፡ እንደ አዲስ ትምህርት ሳይሆን በዕለት ከዕለት እንቅስቃሴአችን በሚታዩ ሁነቶች ያስረዳናል፤›› የሚሉት አቶ ሙሉጌታ መምህራቸው ትምህርቱን መደበኛ በሆነ መንገድ ከማስረዳት ይልቅ የተማሪዎቹን ቀልብ በሚስብ መደበኛ ባልሆነና የዕለት ከዕለት ውሏቸው በሚመስል መንገድ አስረዳቸው፡፡

በመማር ማስተማሩ ሒደት ላይ አንዱ መምህር በተማሪዎች ዘንድ ያለው ተቀባይነት ከሌላኛው መምህር ጋር ይለያያል፡፡ ይህም መምህሮቹ በሚኖራቸው የዕውቀት ልዩነት ሳይሆን ትምህርቱን ለተማሪዎች የሚያስተላልፉበት መንገድ የተለያየ በመሆኑ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ብዙዎቹ ተማሪዎች ስለትምህርቱ ያላቸው ግንዛቤ ዝቅተኛ ሲሆንና እስከነጭራሹም ሲጠሉት ይስተዋላል፡፡ አልያም ‹‹እገሌ ካስተማረኝ በኋላ ትምህርቱን ጠላሁት፤›› ሲሉ ይሰማል፡፡ አንድ መምህር ትምህርቱን ለተማሪዎች እንዴት ማድረስ እንዳለበት ማወቅ ይገባዋል፡፡ ለዚህም ደግሞ ፔዳጐጂ ኮርስ ወሳኝ፡፡ ምንም እንኳ የዶክትሬት ዲግሪ የነበራቸው መምህር የፔዳጐጂ ኮርስ ስላለመውሰዳቸው መረጃው ባይኖረንም በፔዳጐጂ ይህና መሰል ችግሮች ይቀረፋሉ፡፡

አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች እንደሚናገሩት ከዚህ ቀደም በመምህራን ማሠልጠኛ ተቋም ሥልጠና ያልወሰደ መምህር መሆን አይችልም ነበር፡፡ ሥልጠናው በሳል ያደርጋቸዋል፡፡ በመሆኑም ተማሪዎቻቸውን የሚይዙበት መንገድም የተለየ ነበር፡፡ የመማር ማስተማር ሒደቱም ምቹ ይሆናል፡፡ ፔዳጐዷ ይህን ያህል አዎንታዊ ተፅዕኖ ቢኖረውም ፔዳጐጂ ኮርስ ያልወሰዱ መምህራን ያጋጥማሉ፡፡

በሜካኒካል ኢንጂነሪንግ በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቀው አምና ነበር፡፡ የመመረቂያው ጊዜ ሲደርስ አስተማሪ ለመሆን ፍላጐት ያላቸው ተማሪዎች እንዲመዘገቡ ዕድል ተሰጥቷቸው ነበር፡፡ እሱም የዕድሉ ተካፋይ ነበር፡፡ ተመርቆ ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥም ከአዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች በአንዱ መምህር ሆኖ ተቀጠረ፡፡ እሱ እንደሚለው የፔዳጐጂ ትምህርት አልወሰደም፡፡ ‹‹ሥራ ከመጀመራችን በፊት ለሦስት ቀናት ያህል ሥልጠና ሰጥተውናል፡፡ ሥልጠናውን በሚገባም አልተከታተልኩም ነበር፡፡ የመጀመሪያ ቀን አርፍጄ ነው የገባሁት፡፡ የተቀሩትን ብከታተልም ይህን ያህል የተረዳሁት ነገር አልነበረም፤›› ይላል፡፡

በዩኒቨርሲቲው ጥቂት የማይባሉ በፔዳጐጂ ሥልጠና ያልወሰዱ መምህራን መኖራቸውን ይገልጻል፡፡ ይህም በመማር ማስተማሩ ሒደት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን የሚናገረው መምህሩ እሱን ጨምሮ አብዛኛው መምህር የማስተማር ፍላጎት እንደሌለው ይናገራል፡፡ ተማሪዎቹም ቢሆኑ በትምህርት ግዴለሽነት እንደሚታይባቸው ይገልጻል፡፡ አብዛኞቹም ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ ይቸግራቸዋል፡፡ ቢሆንም ግን በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ እንደሚያልፉ ይናገራል፡፡

እንደ ባለሙያዎች ገለጻ ማንኛውም መምህር የፔዳጐጂ ትምህርት ሳይወስድ ማስተማር የለበትም፡፡ በመሆኑም ከፍተኛ ነጥብ ያስመዘገቡ የመጀመሪያ ዲግሪ ምሩቃን ተማሪዎችን እንዲያስተምሩ ዕድል የመስጠቱ አጋጣሚ በዚህ ደንብ ማለፍ ግድ ይለዋል፡፡ ይሁን እንጂ በአሁን ወቅት ካለው የሰው ኃይል እጥረትና የትምህርት ተቋማት ቁጥር መብዛት ደንቡን እየተፈታተነው ይገኛል፡፡

‹‹መምህራን ለተማሪዎች ትምህርት እንዴት ማስተላለፍ እንዳለባቸው ካልተማሩ ትምህርትን በተገቢው መንገድ ማስተላለፍ ይከብዳል፤›› የሚሉት ፕሮፌሰር ጥሩሰው ተፈራ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፔዳጐጂና የባህሪ ጥናት ኮሌጅ ዲን ናቸው፡፡

መምህሩ ያለውን ዕውቀት የሚያስተላልፍበት መንገድ እንደየተማሪዎቹ የአቀባበል ሁኔታ ሊመሠረት ግድ ይላል፡፡ ‹‹አንድ መምህር የተማሪዎችን የመማር ዝግጁነት ማስተዋል ይጠበቅበታል፡፡ ሲያስተምርም ተማሪዎችን ማነቃቃት አለበት፤›› ይላሉ፡፡ ያስተላለፈውም ትምህርት ውጤታማ ስለመሆኑ ግምገማ ማድረግና የማስተማሪያ መንገዱን ማሻሻልም እንደሚገባው ይናገራሉ፡፡

የመምህሩ ግዴታ ተማሪዎቹ ለሚጠበቅባቸው ሥራ ማብቃትና ዝግጁ ማድረግ ነው፡፡ ይህን ለማረጋገጥም መምህሩ የፔዳጐጂ ትምህርት መውሰድ ይጠበቅበታል፡፡ ካልሆነ ግን በጥራቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በመፍጠር የተማሪዎቹንም ብቁነት አደጋ ላይ መጣል ነው ይላሉ፡፡ ‹‹መኪና ለማንቀሳቀስ ቁልፍ እንደሚያስፈልግ ሁሉ ተማሪዎች የሚያስፈልጋቸውን ዕውቀት ለማድረስ ፔዳጐጂ ወሳኝ ነው፤›› በማለት የኮርሱን ወሳኝነት ያጸናሉ፡፡

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በሌሎችም ተቋማት የሚያስተምሩ መምህራን የፔዳጐጂ ትምህርት እየወሰዱ እንደሆነ የሚናገሩት ፕሮፌሰር ጥሩሰው በአንዳንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በአፈጻጸም ረገድ ክፍተቶች መኖራቸውን ይገልጻሉ፡፡ በአሁን ወቅትም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማንኛውም ተማሪ የፔዳጐጂ ትምህርት በመማር ላይ ይገኛል፡፡ ይህ በትምህርት ጥራት ላይ ዓይነተኛ ሚና ቢኖረውም ፔዳጐጂ ለመምህራን እንጂ በሌላ ፊልድ ለሚማሩ ተማሪዎች ትርጉም የለውም የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች አሉ፡፡

‹‹የፔዳጐጂ ኮርስ ለማንም ጠቃሚ ነው፤›› የሚሉት ፕሮፌሰር ጥሩሰው ግን ይህንን ሐሳብ ይቃወማሉ፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ ኮርሱ በማንኛውም የትምህርት ዘርፍ ሊሰጥ ይገባል፡፡ ማኔጅመንት ተማሪ ፔዳጐጂ ቢያጠና ሠራተኞችን እንዴት ማደራጀትና መያዝ እንዳለበት ያውቃል፡፡ እንዲሁም የሕክምና ትምህርት የሚያጠና ተማሪ ፔዳጐጂ ቢወስድ ታካሚውን እንዴት መያዝ እንዳለበት ያመላክተዋል፡፡ በመሆኑም ኮርሱ ለመምህራን ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ሙያ ሊታወቅ እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡

በሌላ በኩል በወቅቱ የትምህርት ሥርዓት ከመምህሩ ጥረት ይልቅ የተማሪው ተሳትፎና ጥረት ሊታከል ይገባል፡፡ መምህሩ መንገድ ከማሳየት ውጪ ሁሉን ነገር የማቅረብ ግዴታ የለበትም በማለት የፔዳጐጂ ኮርስ ባይወሰድም የሚያመጣው ለውጥ አለመኖሩን የሚናገሩ ቢኖሩም ፕሮፌሰር ጥሩሰው ‹‹በእርግጥ መምህሩ መንገድ ማሳየት ዋና ሥራው ነው፡፡ ይህንን ለማድረግም ከተማረው ኮርስ በተጨማሪ ፔዳጐጂ ሊወሰድ ይገባዋል፤›› ይላሉ፡፡

እንደ እሳቸው ገለጻ ተማሪዎች ለኮርሱ ያላቸው አመለካከትም ችግር ሆኗል፡፡ ‹‹የእኔ ሥጋት ትምህርቱ በሚሰጥባቸው ተቋማት ውስጥ በሥርዓት ይሰጣል ወይ? የሚል ነው፡፡ ተማሪዎቹም ለመማር ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ ክፍል ገብተው የመከታተል ፍላጐታቸው በጣም አናሳ ነው፡፡ ይህ ደግሞ መምህሩን ያዳክመዋል፤›› በማለት መመርያውን በተግባር ባዋሉ አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ያለውን ችግር ይገልጻሉ፡፡

በሌላ በኩል የተወሰኑ ዩኒቨርሲቲዎች ኮርሱን ያካተቱ ቢሆንም የሚሰጥበት መንገድ ዕድገቱን እየተፈታተነ ይገኛል፡፡ እንደ ማንኛውም ኮርስ በየሴሚስተሩ አይሰጥም፡፡ የፔዳጎጂ ትምህርት የሚሰጣቸው ከተመረቁ በኋላ ነው፡፡ ይህም በትግበራው ላይ እንከን እየፈጠረ መሆኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የካውንስሊንግ ሳይኮሎጂ መምህር ወ/ሮ ትዕግስት ውሂብ ይናገራሉ፡፡ ወ/ሮ ትዕግስት በፔዳጐጂ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪ አላቸው፡፡

እንደ እሳቸው ገለጻ አንዳንድ ተቋማት ትምህርቱን በመደበኛነት አይሰጡም፡፡ ተማሪዎቹ ትምህርታቸውን ጨርሰው ከተመረቁ በኋላ ለወራት የሚሠለጥኑ ሲሆን፣ የተወሰኑት ተማሪዎች ኮርሱን ሲወስዱ ጥቂት የማይባሉት ይተዉታል፡፡ ይህም የኮርሱን ተግባራዊነት አደጋ ላይ ይጥለዋል፡፡

ፍላጐቷ በሕክምና ትምህርት መማር ቢሆንም አልተሳካላትም፡፡ የተመደበችው በመምህርነት ፋኩልቲ ነበር፡፡ ምንም እንኳን ምርጫዋ ባይሆንም ብዙ አልተከፋችም፡፡ የባዮሎጂ ትምህርት ለመማር ወስና ነበር፡፡ ነገር ግን ይህም አልተሳካላትም፡፡ ምርጫዋ ባይሆንም ዛሬ በወሎ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዓመት የሒሳብ ተማሪ ነች፡፡ ማንነቷ እንዳይገለጽ የፈለገችው ይህች ተማሪ ከተመረቀች በኋላ የሚጠብቃትን የፔዳጎጂ ኮርስ ለመውሰድ ፍላጐቱ የላትም፡፡ እሷ እንደምትለው በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ ብዙ ተማሪዎች የመማር ፍላጎቱ የላቸውም፡፡  

‹‹ተማሪዎች በአንድ ትምህርት የሚጠበቅባቸውን ያህል ዕውቀት የላቸውም፡፡ ለዚህ ምክንያቱ መምህሩ ትምህርት በበቂ የማድረስ ችግር ስላለበት ነው፤›› የሚሉት ወ/ሮ ትዕግስት ኮርሱ በሁሉም ተቋማት በተገቢው መንገድ በመደበኛነት ቢሰጥ ችግሩ እንዳሚቀረፍና የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ እንደሚቻል ይናገራሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...