Thursday, December 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአዲሱ ቱሪዝም በኢትዮጵያ

አዲሱ ቱሪዝም በኢትዮጵያ

ቀን:

ባለፈው ሳምንት በኒውዮርክ ከተማ የሚገኝ አንድ ሆቴል፣ የሠርግ ሥነ ሥርዓታቸውን በሆቴሉ ለመፈፀም ያቀዱ ጥንዶችን የሠርግ ሥነ ሥርዓት በተለየ መልኩ ለማስተናገድ ሞክሯል፡፡

‹‹ማኅበራዊ ድረ ገፆችን በመጠቀም የሠርግ ሥነ ሥርዓትን የማከናወን አገልግሎት›› በሚል መርሆ ሆቴሉ የጀመረው አገልግሎት በጥንዶቹ መልካም ፈቃድ በሆቴሉ የተካሄደውን ሙሉ የሠርግ ፕሮግራም በፎቶና በቪዲዮ አስደግፎ በተለያዩ ድህረ ገፆች ላይ በማዋል የጥንዶቹን የሠርግና የጫጉላ ሽርሽር በብዙ ሺሕ ሰዎች እንዲታይ ማድረግ ችሎ ነበር፡፡

በአገራችን ብዙ ያልተለመደው የስብሰባ ማነቃቂያ፣ የኮንፈረንስና ኤግዚቢሽን ንድፈ ሀሳብ ባደጉት አገሮች መተግበር ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል፡፡ ይሁንና ሀሳቡ በብዙ አገሮች አሁንም በጅምር ላይ ያለ ጉዳይ መሆኑ ይነገራል፡፡ ስኪፍት (skift) በመባል የሚጠራው ዓለም አቀፍ የጉዞ ወኪል ባለፈው ወር ‹‹በቀጣይ የስብሰባዎች መልክ ከቱሪዝም በተጓዳኝ እንዴት ይሆናል›› በሚል ባወጣው ጽሑፉ የቱሪዝምና የጉዞ ወኪሎች ቀጣዩን ዘመን እንዴት ከስብሰባዎችና ኮንፍረንሶች ጋር አያይዘው መጠቀም እንደሚችሉ ይዘረዝራል፡፡

የ‹‹አፍሪካ መዲና›› በሚል መጠሪያ የምትታወቀው አዲስ አበባ ታዲያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የ‹‹ኮንፍረንስ ቱሪዝም›› መናኸሪያ እየሆነች መምጣቷን የሚናገሩ አሉ፡፡ በእርግጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተማዋ እየተገነቡ ያሉ ዘመናዊ ሆቴሎችና የመሰብሰቢያ ማዕከላት ከፀጥታ አስተማማኝነትና ከኅብረተሰቡ እንግዳ አክባሪነት ጋር ተያይዞ ኮንፈረንስ ቱሪዝም እንዲያድግ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል፡፡ ሆኖም የዓለም አቀፉ ተቋማት መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባ በዘርፉ ልታገኝ የሚገባትን ያህል ጥቅም እያገኘች እንዳልሆነ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ፡፡

ለተከታታይ ሦስት ዓመታት ‹‹ሆቴል ሾው ኢትዮጵያ›› በሚል መጠሪያ በኢትዮጵያ የሚገኙ ሆቴሎች አገልግሎታቸውን የሚያስተዋውቁበትንና ሽያጫቸውን የሚያሳድጉበትን መድረክ በማዘጋጀት የሚታወቀው የኦዚ ትሬዲንግ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቁምነገር ተከተል እንደሚገልጹት የኢትዮጵያ የቱሪዝም መስህቦች ብቸኛ የገቢ ምንጭ ሆነው የሚዘልቁበት ዘመን አብቅቷል፡፡ ከስብሰባዎችና ከተለያዩ ጉዞዎች የሚገኘው ገቢም በትልቅነቱ ከጉብኝቶች በሚገኘው ገቢ የገዘፈ ነው፡፡

‹‹አክሱምንና ላሊበላን በማስጎብኘት ሊገኝ የሚችለውና በስብሰባና ጉዞ ቱሪዝም የሚገኘው ገንዘብ የተለያየ መሆኑን የሚገልጹት አቶ ቁምነገር ‹‹አዲስ አበባ ያላትን የስብሰባ ማዕከልነት በከፍተኛ ደረጃ ስታሻሽል አክሱምና ላሊበላን የማስጎብኘቱ ጉዳይ በተጓዳኝነት ሊሠራ ይችላል፡፡›› ይላሉ፡፡

በስፔን ባርሴሎና፣ በዱባይና በደቡብ አፍሪካ የቀሰሙትን ልምድ ይዘው አዲስ አበባን በምሥራቅ አፍሪካ ተጠቃሽ የሆነ የስብሰባና የጉዞ ማዕከል የማድረግ ዓላማ ይዘው በመንቀሳቀስ ላይ እንደሆኑ የሚገልጹት አቶ ቁምነገር ጉዳዩ በመንግሥት የሚገባውን ትኩረት ካገኘ በአጭር ጊዜ እውን ሊሆን እንደሚችል ተስፋ ያደርጋሉ፡፡

ለዚህም በመጪው ሰኔ ወር ላይ ለአራት ቀናት በሚሊኒየም አዳራሽ በሚካሄደው ሦስተኛው የሆቴል ሾው ዝግጅት ላይ ከፍተኛ የመንግሥት አመራር አካላትና ዓለም አቀፍ የዘርፉ ባለሞያዎች የሚገኙበት ስብሰባ በተጓዳኝነት እንደሚካሄድ ጠቁመዋል፡፡ በመጨረሻም የምሥራቅ አፍሪካ 2016 የስብሰባ፣ የማነቃቂያና የኮንፈረንስ ኤግዚቢሽን ኤክስፖ በይፋ እንደሚታወጅም አክለዋል፡፡ በምህፃረ ቃል ‹‹ማይስ›› እየተባለ የሚታወቀውና በእንግሊዝኛው Meeting Incentives & Conference Exhibition (MICE) ተብሎ የሚገለጸው አዲሱን የቱሪዝም ሐሳብ በኢትዮጵያ ለማስረጽ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው የሚናገሩት አቶ ቁምነገር ከወዲሁ የአንዳንድ መንግሥታዊ አካላትን ድጋፍ እያገኙ መሆኑንም ይጠቁማሉ፡፡ በተለይ የመጀመርያውን የስብሰባና የጉዞ ቱሪዝምን ዝግጅት በኢትዮጵያ በመጪው የፈረንጆች ዓመት ለማካሄድ አዳራሾችንና ግቢውን የፈቀደው የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መሆኑን የሚገልጹት አቶ ቁምነገር የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ለጉዳዩ የተሻለ ግምት እንደሚሰጡትና ይህም በከተማዋ እውን ሆኖ ማየትን መፈለጋቸው ለእነሱም የተሻለን ሁኔታ ሊፈጥርላቸው እንደሚችል በመገንዘብ መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡

ኢትዮጵያና መዲናዋ አዲስ አበባ እ.ኤ.አ. ከ2010 እስከ 2013 ድረስ ባስተናገዱት የስብሰባና የኮንፈረንስ ብዛት በአፍሪካ ደረጃ እንኳን ከቀዳሚዎቹ ሦስት አገሮች ጎራ ውጪ መሆናቸውን በዓለም አቀፍ ደረጃ የተጠናን ጥናት ተንተርሰው የሚያስረዱት አቶ ቁምነገር ይህን ዝቅተኛ የኮንፈረንስና የስብሰባ አሃዝ ከፍ በማድረግ የሆቴሎችንና የጉዞ ወኪሎችን ገበያ ማሻሻል እንደሚገባም ይገልጻሉ፡፡

በ2013 ብቻ በአዲስ አበባ ስምንት ያህል ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችና ኮንፈረንሶች መካሄዳቸውን የሚጠቁመው ጥናት ከተማዋን ስብሰባዎችን በማስተናገድ በአፍሪካ 14ኛ ደረጃ ያስቀምጣል፡፡ በአንፃሩ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያና ሞሮኮ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ስብሰባዎችና ኮንፈረንሶች በማስተናገድ በአህጉሪቱ የመሪነት ድርሻን ይዘዋል፡፡

በኢትዮጵያ በተለይም በአዲስ አበባ የኮንፈረንስ፣ የጉዞንና የንግድ ጉባኤዎችን ማስፋፋት በአጠቃላይ የቱሪዝም ሀብት ላይ የተለየ ጥቅምን እንደሚጨምር የሚናገሩት የቱሪዝም ባለሞያው አቶ ተስፋዬ ደሳለኝ በበኩላቸው የአዲስ አበባ ዕድገትና መስፋፋት የተለያዩ ስብሰባዎችንና ጉዞዎችን ከሌሎቹ የአፍሪካ ከተሞች ይበልጥ በመሳብ መታጀብ እንዳለበትም ይጠቁማሉ፡፡ ለአብነትም ባለፈው የፈረንጆች ዓመት በናይሮቢ መሆኑ ቀርቶ በአዲስ አበባ የተከናወነውን ዓለም አቀፍ የሆቴል ኤክስፖ ያነሳሉ፡፡

በሌላ በኩል የአዲስ አበባንና የመላው አገሪቱን ደህንነት ከግምት ውስጥ በማስገባት አዲስ አበባ በኮንፈረንስና የቢዝነስ እንቅስቃሴዎች ቀዳሚ ሆና መውጣት የምትችልበት ዕድለ መኖሩን የሚጠቁሙት ባለሞያዎች፤ በአሁኑ ወቅት ማንኛውንም ዓይነት የኮንፈረንስና የንግድ እንቅስቃሴን በአንድ ቦታ ለማስተናገድ ቀዳሚ ከሚባሉት መሥፈርቶች አንዱ ደህንነት መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡

ከምንም በላይ ደግሞ በእንግዳ አክባሪነቱና በትሁት ሥነ ምግባሩ የሚታወቀውን ሕዝብ እንደ አንድ የምርጫ መሰፈርት በማቅረብ በኢትዮጵያ ተከታታይ የሆኑ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን ለማካሄድ ጥረት መደረግ እንደሚገባውም ይገልጻሉ፡፡ በዚህ ረገድ መንግሥት ወይም የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንደሚገባውና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመምከር አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚችል ሚኒስትሩ አቶ አሚን አብዱልቃድር በሁለተኛው የሆቴል ሾው ዝግጅት ላይ ገልጸው ነበር፡፡

በሚቀጥለው ዓመት ሆቴል ሾው ኢትዮጵያ በሩዋንዳ ኪጋሊ ‹‹አፍሪካን ሆቴል ሾው›› በሚል መጠሪያ እንዲከናወን ጥሪ መቅረቡን የሚጠቁሙት አቶ ቁምነገር በኢትዮጵያ ሆቴሎች በአማካሪነትና በልዩ ልዩ የድጋፍ ዓይነቶች በሠሩበት ወቅት የሆቴሎችን ችግር ለመገንዘብ እንደቻሉ በመግለጽ ለዚህም ዋነኛው መፍትሔ ትላልቆቹ ሆቴሎች በከተማዋና በአገሪቱ ከሚካሄዱ ስብሰባዎችና ኮንፈረንሶች ተጠቃሚ መሆን እንደሚገባቸው ይገልጻሉ፡፡ ‹‹በአሁኑ ወቅት የሆቴል እጦት ተቀርፏል ማለት የምንችልበት ደረጃ ላይ ብንደርስም፤ የሆቴሎች ህልውና ግን አሳሳቢ የሚሆንበት ወቅት ነው ልንል እንችላለን፡፡›› የሚሉት አቶ ቁምነገር በፈረንጆቹ 2020 ከቱሪዝሙ ከአንደ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት አቅዶ የሚንቀሳቀሰው መንግሥት ይህንን የኮንፈረንስና የንግድ ጉዞ የቱሪዝም ዘርፉን በላቀ ሁኔታ ሊሠራበት እንደሚገባም ያሳስባሉ፡፡

በመጪው ሰኔ በሚሊኒየም አዳራሽ በሚካሄደው ሦስተኛው የሆቴል ሾው ኤክስፖ ዋና አጀንዳ የሚሆነው ይኸው የ‹‹ማይስ›› ፅንሰ ሐሳብ እንደሆነና የመጀመሪያውንም የ‹‹ማይስ›› ኤክስፖ በኢትዮጵያ ለማካሄድ ይፋዊ እወጃ እንደሚደረግም ይጠበቃል፡፡ በዚህ የፓናል ውይይትም ዓለም አቀፉ የጉዞና የቱሪዝም አማካሪዎችንና የማስታወቂያ ባለሙያዎችን ጨምሮ የመንግሥት ባለሥልጣናትና የትላልቅ ሆቴሎች ሥራ አስኪያጆች እንደሚገኙ በመጠቆም አዲስ አበባንም ሆነ አገሪቱን በዘርፉ ተጠቃሚና ተጠቃሽ እንዲሆኑ የመጀመርያው ዕርምጃ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...