Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊደሟሚት (ትትኸበድ) - የልምላሜና የብልጽግና መልዓክ

ደሟሚት (ትትኸበድ) – የልምላሜና የብልጽግና መልዓክ

ቀን:

በብርሃነ ዓለሙ ገሣ

የአንድ ማኅበረሰብ ባህሉን፣ ወጉን፣ ልማዱን በመመርመር ማንነቱን ማወቅ ይቻላል፡፡ ዛሬ ላይ ቆመን የምናደንቀውም ሆነ የምንወቅሰው ባህሉን መሠረት አድርጎ በሚኖረው ኑሮ ነው፡፡ ባህል ለአንድ ማኅበረሰብ መሠረቱና የማንነቱ  መገለጫ ነው፡፡

የጉራጌ ብሔረሰብ ለዛሬ ማንነቱ ባህሉ የራሱ የሆነ ሚና ተጫውቷል፡፡ ሥራ እንዲወድ፣ ከትንሽ ጀምሮ ማደግ እንደሚቻል፣ ተስፋ አለመቁረጥ ወዘተ. ጠንክሮ ሠርቶ ሰው ለመሆን እንዲችል ባህሉ መሠረት ጥሎለታል፡፡ ከዚህ ቀደም ስለ ቦዠ (ኤቸሁ) መልዓክ፣ በዚሁ ጋዜጣ በጻፍኩት መጣጥፍ ለማሳየት ሞክሬያለሁ፡፡ በዚሁ መጣጥፍ ቃል በገባሁት መሠረት ዛሬ ደግሞ በተለይ በምዕራቡ ቤተ ጉራጌ ይዘወተሩ ከነበሩት መካከል የ“ደሟሚት”ን ድርሳን አሳያለሁ፡፡ ደሟሚት፣  የልምላሜና የብልጽግና ሚናን እንድትጫወት ከፈጣሪ (ከጉዌታ) ውክልና ተሰጥቷታል ተብሎ ይታመን እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

አቶ ገብረየሱስ ኃይለማርያም በጻፉት፣ “The Gurague and Their Culture” በሚል ርዕስ በጻፉት  መጽሐፋቸው ገጽ 140 የሚከተለውን ይላል፡፡ “Many Gurague believed Demamwit to be one of the three children of God the Father.”

ደሟሚት እንደ ቦዠ (የኃይልና የፍትህ መልዓክ)፣ ዋቅ (የጦርነት መልዓክ) ሁሉ የምትፈራና የምትከበር መልዓክ ነች፡፡ በሌሎች ኃይማኖቶች ብዙም የማይታየው የሴት መልዓክ ተሳትፎ በጉራጌ ብሔረሰብ ዘንድ ተለይቶ እውን ሆኗል፡፡ ለምን ሊሆን ቻለ?

የደሟሚት (ሙየት) አመጣጥ፣ እንደ “ጉራጌና የባሕል እሴቶቹ” መጽሐፍ አተራረክ ከሆነ፣ “ደሟሚት፣ ከአላባ ተነስታ የዌራ ወንዝን አቋርጣ ወደ ጉራጌ ምድር ከገባች በኋላ ብዛት ያለው ተከታይ እንዳፈራችና መመለክ እንደጀመረች ይነገራል”፤ “የደሟሚት አምልኮ ወደ ጉራጌ ምድር የገባው ነዋሪው የክርስትናንም ሆነ የእስልምናን ኃይማኖት ከመቀበሉ በፊት ነው ይባላል” ይላል፡፡

ቀደም ባሉት ዓመታት በይበልጥ ደግሞ ከ1970ዎቹ በፊት በምዕራቡ ቤተ ጉራጌ የደሟሚት ታላቅነት፣ ተከባሪነትና ተፈሪነት ላቅ ያለ ነበር፡፡ የተለያዩ ኃይማኖቶች እንደዚሁም የተማረው ወገን ሳይቀር በአብዛኛው የባህሉን እሴቶች ኋላ ቀርና ባዕድ አምልኮ ብሎ በመፈረጁ ዛሬ ዛሬ የተከታዮቹ ቁጥር እየቀነሰ መጥቷል፡፡ አሁን ባህሉ ሲጠፋ ምንም ላይመስለን ይችላል፤ የኋላ ኋላ ግን ማንነት ወደመፈለግ ሲኬድ ትልቅ ሃዘንና ጸጸት እንደሚያስከትል እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል፡፡

ባዕድ አምልኮ ብሎ ከመደምደም በፊት ደጋግሞ ቆም ብሎ ማሰብ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ባዕድ አምልኮ ማለት ምን ማለት ነው? ከጥንት ጀምሮ ብሔረሰቡ ሲተዳደርበት የነበረና ከማንነቱ ጋር የተያያዘው ነው ባዕድ አምልኮ ወይስ ከጊዜ በኋላ ከሌሎች የተቀበለው ነው? የማይመስል ነገር ለሚስትህ አትንገር ይላል የአገሬ ሰው፡፡ ስሜታዊ ሆኖ ሳይሆን ከስሜታዊነት ተላቅቆ ዓይንን በደንብ ገልጦ ማየትና ጆሮን አቅንቶ ማዳመጥ ያስፈልጋል፡፡ በጥናትና በምርምር ታግዞ መወሰኑና አቋም መያዙ ተገቢ ይሆናል፡፡ 

የደሟሚትን ሥርዓት ባዕድ አምልኮ ነው ብለን ታርጋ ከለጠፍንለት የብሔረሰቡ በርካታ እሴቶችን አብሮ መደምሰስን ያስከትላል፡፡ በየዓመቱ ኅዳር ወር ላይ የሚከበረውን የእናቶች በዓል (አንትሮሸት)፣ በጥር ወር የሚከበረውን የልጃገረዶች በዓል (ነቈ)፣ ይዳር ሙየትን፣ ሁለት ጎሳዎች ተጣልተው ጠባቸው ከፍተኛ ደረጃ ሲደርስ መሃል ገብተው የሚያስታርቁ ሙየቶችን ወዘተ. ሁሉ መጥፋት አለባቸው ማለት ነው፡፡ እያንዳንዱ እሴታችን ከቦዠ፣ ከደሟሚትና ከዋቅ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የጆካ ታሪክን ወድደን ዋቅን አግልለን አይሆንም፡፡

ማናቸውም ሃይማኖቶች ወደ ጉራጌ ምድር ዘልቀው ከመስፋፋታቸው በፊት፣ ብሔረሰቡ ይተዳደር የነበረው በእነዚህ መልዓኮች ነበር፡፡ እዚህ ላይ በአግባቡ መረዳት የሚያስፈልገው ቦዠ፣ ደሟሚትና ዋቅ አምላክ አይደሉም፤ የፈጣሪ ወኪሎችና ተላላኪዎች እንጂ፡፡ በየመጽሐፉ፣ በየማኅበራዊ ገጹና በየሥፍራው አንዳንድ ወገኖች እንደሚጽፉት የፈጣሪን ሚና አይጫወቱም፡፡ ፍትህና ርትዕ ሲጓደል፣ ሌብነትና ሸፍጥ ሲበዛ፣ ኃይለኞች ደካሞችን ሲያጠቁ፣ ጦርነት ሲከሰት … ፈጣሪ በሰጣቸው ስልጣን መሠረት እርምጃ እንዲወሰድ ያደርጋሉ ተብሎ ይታመናል፡፡

የደሟሚት ቅጣት፣ “ዚት” የተባለ ሕመምን ያስከትላል፡፡ ይህ ሕመም፣ ሆድን አሳብጦ በማመንመንና ዓይንን ወደ ቢጫና ቀይ በመቀየር እቤት የሚያስተኛ ነው፡፡ በዚህ ሕመም የተያዙ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ተጋርዶላቸው ተኝተው የሚቆዩ ሲሆን፣ ሕመምተኛው ታመመ ከማለት ይልቅ አነገሠችው (አረጐሠችንም) ይባላል፡፡  ይህ ሕመም አንዳንዶች የጉበት በሽታ ምልክት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በደሟሚት በሽታ የተያዘ ሰው “ዚተነ” ወይም “ወረዞ” ሆነ ይባላል፡፡ አንድ የደሟሚት በሽተኛን ከሕመሙ ለማንጻት የተለያዩ ሥርዓቶች በየደረጃው ይፈጸማሉ፡፡ ሕመምተኛው በእግሩ መሄድ የሚችል ከሆነ በእግሩ ቅቤ ተቀብቶ የቀላ ቀጭን ዱላ ይዞ፣ በእግሩ መሄድ የማይችል ከሆነ ግን በቃሬዛ ወይም በቅርጫት ሸክም ወደ ገበያ ይወሰድና በደሟሚት ሥም፣ “የህይታ ግድራ” ተብሎ ይለመንለታል ወይም ራሱ ይለምናል፡፡ ገበያተኛውም ከሚሸጠው ዕቃ ወይም ካለው ገንዘብ ላይ ግብር (ድመ) ቆንጥሮ ይሰጣል፡፡ ይህም እንዲደረግ የደሟሚት ሥርዓት ያስገድዳል፡፡  

ቀጥሎ የሚካሄደው ሥነ ሥርዓት ሣምር መጨረስ ነው፡፡ “ሣምር”፣ የደሟሚትን ቁጣ ለማብረድ ወይም ከእሷ ቁጣና ሕመም ነፃ ለመሆን የሚካሄድ የመንፃት ሥነ ሥርዓት ነው፡፡ በሣምር፦ ወገን፣ ዘመድ፣ የገማ ሙየቶች(የደሟሚት ሥርዓት አስፈፃሚዎች) እና ሌሎችም ታዳሚዎች በታማሚው ቤት ይጋበዛሉ፡፡ ወረዞ የሆነ ሰው፦ የፍየልና የዶሮ ሥጋ አይበላም፡፡ ፍየል፣ ዶሮ፣ ነጭ ሽንኩርትና “ፉጋ” ተብለው የተገለሉ ሰዎች አጠገቡ አይደርሱም፡፡ ሰው በበላበት አይበላም፡፡ በሸራፋ ብርጭቆ ወይም ሲኒ አይጠጣም፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ ኦሪት ዘጸአት ምዕራፍ 14 ቁጥር 55፣ “ከአሮን ዘር ለምጽ ወይም ፈሳሽ ነገር ያለበት ሁሉ ንጹህ እስኪሆን ድረስ ከተቀደሰው አይብላ፡፡ ከበድንም የተነሳ ርኩስ የሆነውን ወይም ዘሩ ከእርሱ የሚፈስበትን የሚነካ …” ይላል፡፡ ወደ ዝርዝር ጉዳይ ሲገባ እያንዳንዱ ድንጋጌ ምክንያት አለው፡፡

ወረዞ የሆነው ሰው ከሞተ የሚከናወኑ ተጨማሪ ሥነ ሥርዓቶች አሉ፡፡ አስከሬኑ በሌሊት ወጥቶ በቅርብ በሚገኝ፣ በራሱ ወይም በዘመዱ መሬት ይቀበራል፡፡ መቃብሩ ላይም ከእንሰት የሚገኘው የደረቀው ክፍል (ቈቈሳ) ይከመርበታል፡፡ ቈቈሳው ሙየቶች ካገኙት ያቃጥሉታል፡፡ ምክንያቱም ኃጢአቱ በዚሁ እንዲጠቃለል በማሰብ ነው፡፡

ከሟች ንብረት ውስጥ ለደሟሚት ወኪሎች መሰጠት የሚገባውን በሥርዓቱ መሠረት ይሰጣቸዋል፡፡ በንብረት አሰጣጡ ላይ የወኪሎቿ ሥልጣን እንዳለ ሆኖ፣ ሟቹ እቤት ውስጥ ከሞተና እደጅ ከሞተ ልዩነት አለው፡፡ እደጅ ከሞተ ብዙ ንብረት ማዳን ይቻላል፡፡ በዚህም ሆነ በሌላው የደሟሚት ሥርዓት ማስፈጸሙ ሂደት ላይ ወኪሎቿ ሥርዓት አያጓድሉም ወይም አያዳሉም ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ግን አይቻልም፡፡ ለባህሉ መጥፋት (መሳሳት) አንዱ ምክንያትም ወኪሎቿ በእሷ ሥም የሚያደርሱት የሥነ ምግባር ጉድለትና ጥፋት ነው፡፡ መውሰድ የሌለባቸውን ቁሳዊ ሀብት ይወስዳሉ፤ ማድረግ የሌለባቸውንም ያደርጋሉ፡፡

የደሟሚት ተግባር ልምላሜንና ብልጽግናን ዒላማ ያደረገ እንጂ የሰው ልጅ በሕመም እንዲሰቃይ አይደለም፡፡ ሥርዓት ሲበላሽ፣ ሕግ ሲጠፋ … ግን  ከፈጣሪ በተሰጣት ሥልጣን መሠረት እንዲቆነጠጥ ማድረጓ አይቀሬ ነው፡፡ ቁንጥጫው ሕመም ከፈጠረም የመፈወሻ ሥርዓት አለው፡፡ የደሟሚት ሕመምተኛው ሣምር ከተደረገለት በኋላ ማድረግ የሚገባውን አድርጎ፣ ከተለያዩ ግዴታዎች ነፃ የሚሆንበት ሥርዓት አለ፡፡ በዚህም ሥርዓት መሠረት “ሣዋ” ሆነ ይባላል፡፡

የደሟሚት ተከታዮች (ይዳር ሙየት) በየዓመቱ መስቀል በዓል ሰሞን ወጥተው ከክረምቱ ጎርፍ፣ ከጨለማና ከውኃ ሙላት ወደ ፀሐዩ ወር መስከረም (ይዳር) ያሸጋገረን ፈጣሪ ያመሰግናሉ፤ ክፉውን እንዲያርቅም ይማጸናሉ፡፡ ለደሟሚት ክብርም አረንጓዴ ልምጭ ከፍ አድርገው ይዘው ይዘምራሉ፤ ልዩ ልዩ ትርዒት ያሳያሉ፡፡ ብዙውን ጊዜ ትይንታቸው በገማ ሙየት (በአለቃቸው) እርሱ ከሌለ ግን በአንጋፋ ሴት ሙየቶች ይመራል፡፡ ልክ እንደ ማርሽ ባንድ፣ የፊት መሪዎች እንደሚመሩት ሁሉ፣ ሴት ሙየቶችም በወንድ የገማ ሙየት ይመራሉ፡፡  ሴት ሙየቶች ረፋድ ላይ ወይም ምሽት ላይ ከየቤታቸው ተጠራርተው “ይህ…ይህ…” እያሉ አባላቸው የሆነች ሴት ደጅ ላይ ሲቆሙ፣ አባልዋም “ኦ…ይ…” ብላ ትቀላቀላቸዋለች፡፡ አባላቱ በርከት ሲሉ በኅብረት “ኤሣ ኤሦ” እያሉና ከረቦ እየደለቁ፣ ለጆሮ የሚጥም ዝማሬ እየዘመሩ ጎዳናው (ጀፎረ) ላይ ይጓዛሉ፡፡ የአጨፋፈር ስልቱም በጣም ማራኪና ለየት ያለ ነው፡፡ ይህንንም ለማረጋገጥ የብሔረሰቡ ተወላጅ የሆነው ቁምላቸው ወልዴ ያዘጋጀውን “ክሊፕ” መመልከት ተገቢ ነው፡፡

  የደሟሚትን ገድል አስመልክቶ፣ እንሰት ሲፋቅ (ውሣቻ) ላይ ለሥራ የሚሰባሰቡ ሴቶች፣ “ዋይወቶ”ን ያዜማሉ፡፡ እንዲህ እያሉ፣                                                              

         ብሻ ደሞ! ዳ ኤናህይ ደሞ

         ገረድ በሰሜ ትትወርድ

         ምር አውያም ወረት?

               ….

            ዋይ ዋይ-ወ-ቶ

            ዋይ ዋይ ቤም ግይበፖ

             ኧጃህይ አውየፖ፡፡

            ኧጃህይ የባሰባ

             ቐየሳ የረቅባ

            የᎀክየረር ደቶ

            አᎈነ ምየቶ

            ብሻ የደም ኧርጦ … እያሉ ያዜማሉ፡፡    

ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ስንኞች ቀይዋ ደሟሚት ከሰማይ ስትወርድ ወረቷ ምን ተሰጣት? ብሎ በመጠየቅ ዝናዋን የሚጠቁሙ ናቸው፡፡ ለቋንቋው ተናጋሪዎችና ባህሉን በአግባቡ ለሚረዱ ካልሆነ በስተቀር የዜማውን ትርጉም ለማወቅ ትንሽ ያዳግታል፡፡

የደሟሚት አባላት የሚመለመሉት በዓመታዊዎቹ ኅዳር ወር ላይ ᎀክየረር ላይ በሚከበረው በደሟሚት ክብረ በዓል “ሰንቸ”፣ እንዲሁም የእምነቱ ተከታዮች ባሉበት ሁሉ በጥር ወር በሚከበረው፣ የልጃገረዶች በዓል “ነቈ”  ላይ ነው፡፡ አንዲት ልጅ ለአባልነት የምትመለመለው ዕድሜዋ ከሰባት እስከ ዘጠኝ ዓመት ሲሞላት እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ አንጋፋ ሙየቶች ወይም የገማ ሙየቶች፣ ለሙየት አባልነት ብቁ የሆኑትን መርጠው ይመለምላሉ፡፡ በዚህም ጊዜ “ቁጨቈጭያም” (ተቀጠቀጠች) ትባላለች፡፡ ተመልማይዋም ለተወሰኑ ቀናት ከቤት ሳትወጣ ትቆያለች፡፡ በቆይታዋም ሙየቶችና የሙየት አባላት ብቻ የሚነጋገሩበት ፌድወት የተባለውን የምሥጢር ቋንቋንና የሙየት ሕጎችን ትማራለች፡፡

የደሟሚትን ሥርዓት በበላይነት የሚያስፈጽመው ሰው የዌደማም ተብሎ ይጠራል፡፡ የዌደማም በፆታው ወንድ ሲሆን፣ ከቸሃ ቤተ ጉራጌ ከዋቄ ሰብ ጎሣ ውስጥ የሚመረጥ ነው፡፡ የዌደማም፣ የደሟሚት ሥርዓትን ከማስፈጸም ጎን ለጎን በስለትም ሆነ በሌላ (ከዚት ሕሙማን) የሚመጡለትን ስጦታዎች ይቀበላል፡፡ በተለይ በምዕራቡ ቤተ ጉራጌ ውስጥ ይከሰቱ የነበሩ የተለያዩ ጉዳዮችን ከታዋቂ ሽማግሌዎች ጋር ሆኖ የጆካ ሸንጎ ላይ በመሳተፍ የበኩሉን ድርሻ ይወጣል፡፡

ደሟሚት አንዳንድ ጊዜ “ማርያም”ን የምትተካበት ጊዜም ነበር፡፡ ቀደም ባለው ጊዜ አንዲት እናት ምጥ ሲያስቸግራት፣ “ማርያም፣ ማርያም እምቧ-ሊላ …” እያሉ እናቶች ይማጸኑ እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡ እኔ የዚህ መጣጥፍ ጸሐፊ ልጅ እያለሁ (አሁን አምሳ አካባቢ ነኝ)፣ አንዱን ጉራጌ “እምነትህ ምንድነው?” ተብሎ ሲጠየቅ፣ “አማራ ነኝ” ካለ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ፣ “ጉራጌ ነኝ” ብሎ ከመለሰ ግን የባህላዊ እምነት ተከታይ ተብሎ ይፈረጅ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡

በእርግጥ በምዕራቡ ቤተ ጉራጌ ውስጥ የኦርቶዶክስ (በይበልጥ ቀደም ብሎ በሞህር)፣ የካቶሊክ (በይበልጥ ቀደም ብሎ በቸሃ)፣ የእስልምና፣ ቆይቶ ደግሞ የፕሮቴስታንት ኃይማኖቶች ባህላዊውን እምነት ተክተው ተስፋፍተዋል፡፡ ዛሬ የምዕመናኑም ቁጥር በጣም ብዙ ነው፡፡ የእኔ ዓላማ በኃይማኖት ውስጥ ጣልቃ ለመግባት አይደለም፤ ልግባም ብል አቅሙም ችሎታውም የለኝም፡፡ ምኞቴ ግን፣ ከየትና ከምን ተነስተን የት ደረስን? ምን አግኝተን ምን አጣን? ታሪካችንን በአግባቡ እናውቃለን ወይ? የሚለውን ርዕሰ ጉዳይ በጥልቀትና በዕውቀት፣ በመረጃና በማስረጃ አስደግፈን እንድንነጋገርበት ነው፡፡

በጉራጌ ብሔረሰብ ባህል፣ በተለይ ደሟሚትን በሚመለከት የተሻለ ዕውቀትና እውነት አለኝ የሚል ካለ፣ ዛሬም ነገም ከነገ ወዲያም ለመማር ዝግጁ ነኝ፡፡ የማልፈልገው መከራከሪያ ግን፣ እውነትነት የሌለው ቁንጽል የሆነ መረጃ ተይዞ “እትት፣ አካኪ ዘራፍ …” የሚባልበትን አውድ ነው፡፡ ይልቅ ከሁሉ ከሁሉ ሊያሳስበን የሚገባው የራሳችንን እየጣልን፣ የሌላውን አጥብቀን ይዘን፣ ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ የናቅነውን ባህል፣ ወግና ልማድ መመለስ ከቶ አለመቻላችንን ነው፡፡

ስለዚህ፣ ስሜታዊ ሳንሆን በየምላዳችን፣ “ኲሉ አመክሩ ወዘሰናየ አጽንኡ” (ሁሉን መርምሩ የተሻለውን ያዙ) የሚለውን የመጽሐፉን ቃል ብንይዝ ደስ ይለኛል፡፡ ሰላም!    

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...