በአገራችን ስለእባቦች የተለያየና ብዙ ጊዜም ከእውነት የራቀ እምነት አለ፡፡ ከዋና ዋናዎቹም መካከል፣ እባቦች ዘለውና ተወርውረው ይናደፋሉ፤ ቀርከሃ ሰርስረው ያልፋሉ፤ ሰውን እያባረሩ ያጠቃሉ የሚሉት ናቸው፡፡ በተጨባጭ ግን ከላይ እንተገለጸው አብዛኛው የአካል ክፍላቸው መሬት ቆንጥጦ የተወሰነ የአካል ክፍላቸው ብቻ ተወንጭፎ ያጠቃል ወይም ይናደፋል እንጂ፤ በአየር ላይ በመምዘግዘግም ሆነ በማሯሯጥ ጥቃት አያደርሱም፡፡
አንዳንድ እባቦች ሕይወት ያለው ልጅ እባብ ይወልዳሉ፤ እንደ ሰውና ሌሎች አጥቢዎች፡፡ ከእነዚህም መካከል በአንድ ጊዜ ከ50 በላይ የሚወልዱ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ አብዛኞቹ ግን ዕንቁላል ይጥላሉ፡፡ ዕንቁላል ከሚጥሉትም መካከል መቶና ከዛ በላይ የሚጥሉ ይገኙበታል፡፡ ብዙዎቹ ሴት እባቦች ዕንቁላል ከጣሉ በኋላ ደብቀው ይሄዳሉ፡፡
ወንዱ እባብ ወደ ሴቷ ለወሲብ የሚጠጋው ሽታ ስቦት ነው፡፡ አንድ ወንድ፣ ሽታ እያነፈነፈ ወደ ሴቷ ሲጠጋ ሌላ ወንድ በተመሳሳይ ሁኔታ ለተመሳሳይ የወሲብ ጥያቄ ሲመጣ ሊያጋጥመው ይችላል፡፡ በዚህን ጊዜ ታዲያ ‹‹ሴቷ የኔ ነች›› በሚል ወንዶቹ ይፎካከራሉ፡፡ ተያይዘው በመታገል የጥሎ መነሳት ዓይነት ድብድብ ያካሂዳሉ፡፡ ሁለቱም አካላቸውን ከመሬት ከፍ አድርገው ነው የሚታገሉት፡፡ በዚህም አንዱ አንዱን ጥሎ ተሸናፊውን ካባረረ በኋላ ሴቷን ይገናኛል፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ ግን ታግለው ይሸናነፋሉ እንጂ አይነካከሱም፡፡ ወንዱ ከሴቷ ጋር በሚገናኝበት ጊዜ አካላቸውን አቆላልፈው ለጥቂት ደቂቃዎች ወይም ለረጅም ሰዓታት ይቆያሉ፡፡
- ማንይንገረው ሸንቁጥ ‹‹ባለአከርካሪዎች›› (2004 ዓ.ም.)