Wednesday, July 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የግል ባንኮች በአሥር ወራት ከ3.9 ቢሊዮን ብር በላይ አተረፉ

ተዛማጅ ፅሁፎች

–  የትርፍ ዕድገቱ ዝቅተኛ ነው ተብሏል

በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ያሉ 16 የግል ባንኮች በ2007 በጀት ዓመት አሥር ወራት ከ3.9 ቢሊዮን ብር በላይ ማትረፍ ቢችሉም፣ የትርፍ ዕድገት መጠኑ አነስተኛ መሆኑ ተጠቆመ፡፡

የባንኮቹን የአሥር ወራት የሥራ አፈጻጸም የሚያመለክቱት የመጀመርያ ደረጃ አኃዛዊ መረጃዎች፣ አብዛኛዎቹ ባንኮች ትርፋቸውን ማሳደግ ቢችሉም የዕድገቱ መጠን የተጠበቀውን ያህል መሆን ያልቻለው፣ በአንዳንድ የባንክ አገልግሎት ዘርፎች ይገኝ የነበረው ትርፍ በመቀነሱ እንደሆነ ያሳያሉ፡፡

የአሥር ወራት የተጠቃለለ መረጃ እንደሚያሳየው ከ16 የግል ባንኮች ውስጥ አራቱ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ያነሰ ትርፍ ያስመዘገቡ ሲሆን፣ ሁለት ባንኮች ደግሞ ከፍተኛ ትርፍ አግኝተዋል፡፡ ቀሪዎቹ ባንኮች ደግሞ ትርፋቸው ያደገ ቢሆንም ዕድገቱ ግን ዝቅተኛ የሚባል እንደሆነ ተመልክቷል፡፡

በአሥር ወራት የተገኘው ትርፍ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የትርፍ ዕድገቱ በ400 ሚሊዮን ብር ያነሰ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ግን የትርፍ ዕድገቱ ከዚህም በላይ እስከ አንድ ቢሊዮን ብር ይደርስ እንደነበር ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለሙያዎች ጠቁመዋል፡፡ አምና በተመሳሳይ ወቅት ባንኮቹ አስመዝገበውት ነበር የተባለው ትርፍ 3.6 ቢሊዮን ብር አካባቢ ነው፡፡

እንደባለሙያዎች ገለጻ፣ የዘንድሮ የባንኮች የትርፍ ዕድገት መጠን ሊያንስ የቻለውና አንዳንዶቹም ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ ትርፍ ሊያስመዘግቡ ከቻሉባቸው ምክንያቶች ውስጥ፣ በተለይ ከዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት ያገኙ የነበረው ትርፍ በመቀነሱ ነው፡፡ ይህም ለአጠቃላይ የትርፍ ዕድገታቸው የራሱ የሆነ ተፅዕኖ እንዳሰደረ ባለሙያዎቹ ያምናሉ፡፡

ሁሉም ባንኮች በሚባል ደረጃ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ስለነበረባቸው፣ በተለይ የወጪ ንግድ እንቅስቃሴውና ከውጭ የሚላክ ገንዘብ መጠን መቀዛቀዝ ከዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት ያገኙ የነበረውን ከፍተኛ ትርፍ እንዳያገኙ አድርጓቸዋል ይላሉ፡፡ ብዙዎቹ ባንኮች በበጀት ዓመቱ በርካታ ቅርንጫፎችን መክፈታቸውና አዳዲስ አገልግሎቶችን ለመጀመር የሚያወጡት ወጪ መጨመራቸው፣ በትርፍ ዕድገታቸው ላይ ተፅዕኖ ያሳደሩ ተጨማሪ ምክንያቶች እንደሆኑም ተጠቅሰዋል፡፡

በአንፃሩ ግን የሁሉም ባንኮች የተቀማጭ ገንዘብ እያደገ መምጣቱን የገለጹት እነዚሁ ባለሙያዎች፣ ባሰባሰቡት ተቀማጭ ገንዘብ ልክ ብድር አለመስጠታቸውን ግን ለትርፋቸው መቀነስ ዋነኛው ምክንያት እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡ ባለሙያዎቹ እያደገ በመጣው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን የባንኮቹ የብድር መጠን ማደግ እንደነበረበት ተከራክረዋል፡፡ ብዙዎቹ ባንኮች ይህንኑ ዕድል እየተጠቀሙበት ሲሆን፣ አንዳንዶች ግን ባለመጠቀማቸው የዘንድሮው የአሥር ወራት የትርፍ ምጣኔ የተጠበቀውን ያህል እንዳይሆን አስተዋጽኦ አለው ይላሉ፡፡

የአሥር ወራቱ የግል ባንኮች መረጃ እንደሚያሳየው፣ ሁሉም የግል ባንኮች ተቀማጭ ገንዘባቸው 109.6 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከ24 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ አለው፡፡

ባለፈው ዓመት አሥር ወራት የባንኮቹ ተቀማጭ ገንዘብ 85.8 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ በበጀት ዓመቱ አሥር ወራት ተቀማጫቸውን ካሳደጉት ባንኮች መካከል አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ 17.05 ቢሊዮን ብር፣ ዳሸን ባንክ 19.5 ቢሊዮን ብር፣ አቢሲኒያ ባንክ 10.1 ቢሊዮን ብር፣ ሕብረት ባንክ 10.6 ቢሊዮን ብር አድርሰዋል፡፡

በአሥር ወራት ውስጥ ከፍተኛ ትርፍ ካስመዘገቡት ውስጥ ደግሞ ዳሸን ባንክ 649.6 ሚሊዮን ብር በማትረፍ ቀዳሚ ሆኗል፡፡ አዋሽ ባንክ 642 ሚሊዮን ብር፣ ኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ 445.3 ሚሊዮን ብር በማትረፍ ከአንድ እስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡

በተለይ ኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክና አንበሳ ባንክ የትርፍ መጠናቸውን በከፍተኛ ሁኔታ አሳድገዋል፡፡ እንደ መረጃው ከሆነ አንበሳ ባንክ በዘጠኝ ወራት ያገኘው ትርፍ ከ196 ሚሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ ይህ የትርፍ መጠን ከ2006 ዓ.ም. ሙሉ በጀት ዓመት አስመዝግቦት ከነበረው ትርፍ በላይም ያደገ ነው፡፡ ባንኩ በ2006 በጀት ዓመት በ12 ወራት አስመዝግቦት የነበረው ትርፍ 127 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን በዘጠኝ ወራት ውስጥ ያስመዘገበው ትርፍ አምና በ12 ወራት ካገኘው ትርፍ ከ69 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ አለው፡፡

ባንኩ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ያገኘው የትርፍ መጠን 196 ሚሊዮን ብር በመሆኑ፣ የዘንድሮው ትርፍ ከአምናው የዘጠኝ ወራት ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ አለው፡፡ በአሥር ወራት ሪፖርት ደግሞ የባንኩ የትርፍ መጠን ከ220 ሚሊዮን ብር በላይ ማደጉን መረጃው ያመለክታል፡፡

አንበሳ ባንክ ከእጥፍ በላይ ትርፍ ያስመዘገበበት ዋነኛ ምክንያት ተቀማጭ ገንዘብ በማሰባሰቡ ረገድ ከፍተኛ ሥራ በመሥራቱና ይህንንም ለማበደር በመቻሉ እንደሆነ የባንኩ የሥራ ኃላፊዎች ይገልጻሉ፡፡

ሰኔ 30 ቀን 2006 ዓ.ም. 2.6 ቢሊዮን ብር የነበረው የተቀማጭ ገንዘብ መጋቢት በ2007 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት 3.9 ቢሊዮን ብር መድረሱ ለዕድገቱ ጥሩ ማሳያ ነው ይላሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች