Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሚድሮክ በአዲስ አበባ አጥሮ ባስቀመጣቸው ቦታዎች ግንባታ እንደሚጀምር አስታወቀ

ሚድሮክ በአዲስ አበባ አጥሮ ባስቀመጣቸው ቦታዎች ግንባታ እንደሚጀምር አስታወቀ

ቀን:

–  ከሸራተን ማስፋፊያ የፌዴራል ፖሊስ ጋራዥ እንዲነሳ ጠየቀ

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሚድሮክ ኢትዮጵያ ለያዛቸው 13 ቦታዎች በልዩ ሁኔታ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው ትዕዛዝ መስጠቱን ተከትሎ፣ ሚድሮክ በቦታዎቹ ላይ ግንባታ ለማካሄድ መዘጋጀቱን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡ ከሸራተን ማስፋፊያ የፌዴራል ፖሊስ ጋራዥ እንዲነሳለትም ጠይቋል፡፡

በጉዳዩ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የሚድሮክ ከፍተኛ ኃላፊዎች በቅርቡ መነጋገራቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በተለይ በተጓተተው የሸራተን አዲስ ማስፋፊያና በፒያሳ መንታ ፎቅ ሕንፃዎች ግንባታ ላይ ባለሥልጣናቱ ረዥም ጊዜ የወሰደ ምክክር ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ 148 ቦታዎች ታጥረው ረዥም ጊዜ ማስቆጠራቸው ይታወቃል፡፡ በእነዚህ ቦታዎች የአዲስ አበባ ካቢኔ ዕርምጃ ለመውሰድ ቢሞክርም፣ በተለይ በተወሰኑት ቦታዎች ላይ ለሚወስደው ዕርምጃ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አቅጣጫ እንዲሰጠው መጠየቁን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡

በዚህ መሠረት አስተዳደሩ ራሱን ችሎ 88 ቦታዎች ወደ መሬት ባንክ እንዲገቡ ሲወስን የተቀሩት የመንግሥትና የዕምነት ተቋማት ቦታዎች ባሉበት እንዲረጉ፣ የሚድሮክ 13 ቦታዎችና ከአምስት የማያንሱ በሌሎች ባለሀብቶች የተያዙ ቦታዎች በልዩ ሁኔታ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጣቸው፣ ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ጋር በጋራ ተወስኗል፡፡ ለውሳኔ ቀርበው የነበሩት የሚድሮክ ቦታዎች በተለይም ለሸራተን ማስፋፊያ ከተሰጠው ቦታ የፌዴራል ፖሊስ ጋራዥና ሠራዊት ማስቀመጫ ካምፕ እንዲነሳም ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

ምንጮች እንደገለጹት፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ከቦታው ላይ ጋራዡንና ካምፑን ለማንሳት ቢወስንም በተሰጠው ምትክ ቦታ ላይ ግንባታ አካሂዶ እስኪጨርስ የተወሰነ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡

የሚድሮክ ኃላፊዎች በበኩላቸው ጋራዡ ሳይነሳ ግንባታ ማካሄድ የማይቻል በመሆኑ፣ ፌዴራል ፖሊስ ጋራዡን እንዳነሳ ወደ ግንባታ እንደሚገቡ በወቅቱ ማስታወቃቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ሚድሮክ የሸራተን አዲስ ማስፋፊያን ፕሮጀክት ለማካሄድ ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ አዲስ አበባን በሚያስተዳድሩበት ወቅት፣ የመሬት ጥያቄ አቅርቦ 42 ሔክታር መሬት እንዲሰጠው ተፈቅዶለታል፡፡

በአራዳና በቂርቆስ ክፍላተ ከተሞች የሚገኘው ይህ ቦታ 88 ሚሊዮን ብር ሙሉ የሊዝ ክፍያ በወቅቱ ተከፍሎበታል፡፡ አስተዳደሩ ይህንን መሬት ከአምስት ዓመታት በፊት በቀድሞው ከንቲባ ኩማ ደመቅሳ አስተዳደር ወቅት ከቦታው ላይ ነዋሪዎችን ያነሳ ሲሆን፣ በብቸኝነት የቀረው የፌዴራል ፖሊስ የሚጠቀምበት ቦታ ነው፡፡

በሌላ በኩልም በከፍተኛ ባለሥልጣናቱ መነጋገሪያ የሆነው የሚድሮክ እህት ኩባንያ ሁዳ ሪል ስቴት በመሀል ፒያሳ ከ16 ዓመት በፊት የያዘው 16 ሔክታር ቦታ ነው፡፡ ሚድሮክ በዚህ ቦታ ላይ ሁለት ግዙፍ መንታ ሕንፃዎችን ጨምሮ ሌሎች አነስተኛ ግንባታዎችን ለማካሄድ የያዘው የመጀመርያ ዕቅድ ተሰርዟል፡፡

የአዲስ አበባ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሐሰን አብዱ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ፒያሳ የቆየ የከተማው ክፍል በመሆኑና አስተዳደሩ በቅርቡ በቆዩ የከተማ ክፍሎች ስለሚካሄዱ ግንባታዎች በወጣው መመርያ መሠረት፣ የሕንፃ ከፍታው ከአካባቢው ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ተወስኗል፡፡ በዚህ መሠረት ሚድሮክ የቀድሞውን ዲዛይን በመቀየር ሒደት ላይ ነው ብለዋል፡፡

ሚድሮክ ቆየት ላለ ጊዜ ታጥረው በተቀመጡ ሁሉም ቦታዎች ግንባታ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ መሆኑን፣ ለፌዴራልና ለአዲስ አበባ ከተማ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ቢሮዎች ማስታወቁን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...