Monday, October 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአዲስ አበባ ካቢኔ በመሬት ጉዳይ ውሳኔ ባለመስጠቱ ኢንቨስተሮች መቸገራቸውን ገለጹ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በመሬት ጉዳይ ላይ ውሳኔ እየሰጠ ባለመሆኑ፣ ለከፍተኛ ችግር ተዳርገናል ያሉ ኢንቨስተሮች ምሬታቸውን ገለጹ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ በተለይ ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ መሬት እንዲሰጣቸው ጥያቄ ያቀረቡ 60 ኢንቨስተሮች ምክረ ሐሳብ (ፕሮፖዛል) ከተነተነ በኋላ፣ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጥ ለአስተዳደሩ ካቢኔ ቢያቀርብም ካቢኔው ውሳኔ አለመስጠቱ ታውቋል፡፡

ምንጮች እንደሚገልጹት፣ እነዚህ ኢንቨስተሮች የመሬት ጥያቄ ካቀረቡ ስምንት ወራት ተቆጥረዋል፡፡ ነገር ግን የአስተዳደሩ ካቢኔ በየሳምንቱ ሐሙስ ቢሰበስብም፣ የከተማው አስተዳደር በሌሎች ጉዳዮች በመጠመዱ በመሬት ጉዳይ ላይ ውሳኔ እያሳለፈ እንዳልሆነ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሐሰን አብዱ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ኢንቨስተሮች እንደሚናገሩት፣ የመሬት ጥያቄያቸው ምላሽ ባለማግኘቱ ያቀዱትን ፕሮጀክት በወቅቱ ለማካሄድ ተቸግረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለፕሮጀክቱ የመደቡት ገንዘብ ያለሥራና ያለወለድ በባንክ ታስሮ መቀመጡ፣ ከፍተኛ ችግር እንደፈጠረባቸው አመልክተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ በልዩ ሁኔታ መሬት መስጠት ከጀመረበት ካለፈው ዓመት ጀምሮ 600 ኢንቨስተሮች መሬት እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ ነገር ግን የሚቀርቡት ፕሮጀክቶች ከአነስተኛ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ያሉ በመሆናቸውና መንግሥት ቅድሚያ የሚሰጣቸው ፕሮጀክቶች በውል ተለይተው ለመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ባለመቅረባቸው፣ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የቦታ ጥያቄ ከወራት በፊት እንዲቆም ተወስኗል፡፡

ለቀረቡት ፕሮጀክቶችም ቢሆን መሬት እየቀረበ ባለመሆኑ ኢንቨስተሮቹ በዝግ ሒሳብ ያስያዙት ገንዘብ ዕዳ እየፈጠረባቸው መሆኑንም እየተናገሩ ነው፡፡ መንግሥት በአገልግሎትና በንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲገቡ እየገፋፋ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የመንግሥትን ሐሳብ በመቀበል ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለመግባት የመጡት ባለሀብቶች በመሬት አቅርቦት ችግር እየተጉላሉ መሆኑ አግባብ አለመሆኑን አቶ ሐሰን ገልጸው፣ የከተማው አስተዳደር ባካሄደው የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ላይ ከዚህ በኋላ በየጊዜው በመሬት ጉዳይ ላይ ውሳኔ እንደሚሰጥ መመርያ መስጠቱንም አክለዋል፡፡

አቶ ሐሰን እንዳሉት፣ ከዚህ ቀደም በመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ የመሬት ጥያቄዎችን በፍጥነት ተንትኖ በማቅረብ በኩል ችግር ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ቢሮ ይህንን ችግር መፍታቱን አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች