Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን በኢትዮጵያ ተከበረ

የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን በኢትዮጵያ ተከበረ

ቀን:

  • መንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት በፍጥነት እንዲቋቋም ጠይቋል
  • የግል ሚዲያ ተቋማት የመንግሥት የሚዲያ ፖሊሲ እንዲለወጥ አሳስበዋል

በየዓመቱ ሜይ 3 ቀን እንዲከበር በተመድ የተላለፈውን ውሳኔ በማስመልከት ሚያዝያ 24 ቀን 2007 ዓ.ም. በኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴል መንግሥት ባዘጋጀው መድረክ፣ የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ተከበረ፡፡ መንግሥትና የግሉ ሚዲያ ዘርፍን በመወከል የተሳተፉ አካላት ለሚዲያ ነፃነት ተግዳሮት ናቸው ያሉዋቸውን ጉዳዮች አቅርበዋል፡፡ መንግሥት የሥነ ምግባር ጉድለትና የሕግ ጥሰቶችን በዋና ምክንያትነት ሲጠቅስ፣ የግሉ ሚዲያ ተወካዮች ግን ከኅትመት መወደድ እስከ መንግሥት በጎ ያልሆነ የግሉ ሚዲያ ምልከታና ጣልቃ ገብነት ድረስ ቁልፉን ችግር እየፈጠረ ነው ሲሉ ወቅሰዋል፡፡

የዕለቱን መድረክ የከፈቱት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን፣ መንግሥት የፕሬስ ነፃነት በኢትዮጵያ እንዲረጋገጥ ሕግ በማውጣትና በሌሎች አስተዳደራዊ ዕርምጃዎች ቁልፍ ሚና መጫወቱን ጠቅሰዋል፡፡ ክፍተት አለበት ከተባለም የመንግሥት ክፍተት ሌሎች ቁልፍ ባለድርሻ አካላት ካለባቸው ክፍተቶች የበለጠ እንዳልሆነም አመልክተዋል፡፡ በአፈጻጸም ረገድ መንግሥት ያለበት ድክመት ያለባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ሊስተካከል እንደማይችል በመጠቆም፣ ሌሎቹም የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አድርገዋል፡፡ በዋናነት የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት በፍጥነት ሥራ እንዲጀምር ጠይቀዋል፡፡ መንግሥት የበኩሉን ለመወጣት ዝግጁ እንደሆነ ያስታወቁት አቶ ሬድዋን፣ በቀጣዩ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የወረቀት ማምረቻ ፋብሪካዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ሲቋቋሙ የኅትመት ችግር እንደሚቀረፍም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ መሠረት አታላይ መንግሥት በተለይ የኅትመት ዋጋ መናርን እንዲደጉም ጠይቀዋል፡፡ በተጨማሪም መንግሥት በሥልጠናና በተለያዩ ድጋፎች በማኅበራቱና የሚዲያ ተቋማቱን አቅም ለማሳደግ ቁርጠኛ አለመሆኑን ተችተዋል፡፡ ሕግን በማስከበር ሰበብ መንግሥት የግሉ ሚዲያ ላይ ጫና እንዲያሳድር የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤትን በፍጥነት ማቋቋም አስፈላጊ እንደሆነ በመግለጽም ለአቶ ሬድዋን ጥሪ ድጋፍ አድርገዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ በኢትዮጵያ ስላለው የጋዜጠኝነትና የለውጥ ኃይል አራማጆች (Activists) ልዩነትና አንድነት አስመልክቶ ንግግር ያደረገ ሲሆን፣ በውጭው ዓለም የሚታወቀው የለውጥ ኃይል አራማጆች ባህርይ በኢትዮጵያ እንደማይታይ ተከራክሯል፡፡ በኢትዮጵያ በሚዲያ የለውጥ ኃይል አራማጅነት የሚታወቁ ሰዎች ተቃዋሚ ፖለቲከኞች እንደሆኑም አመልክቷል፡፡ ለሕዝቡ ጥቅም ቆሞ መንግሥት የሚቃወም ጋዜጠኛ በኢትዮጵያ ማግኘት ከባድ እንደሆነም ጠቅሷል፡፡

የሪፖርተር ጋዜጣ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አማረ አረጋዊ በኢትዮጵያ ስላለው የፕሬስ ነፃነት ንግግር ያደረገ ሲሆን፣ የፕሬስ ነፃነት በኢትዮጵያ ላለበት ዝቅተኛ ደረጃ መንግሥት፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና የሚዲያ ተቋማት የጋራ ተጠያቂነት እንዳለባቸው አስረድቷል፡፡ የኢትዮጵያ የሚዲያ ሕግና ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ በጣም ጥሩ የሚባል ቢሆንም፣ ለአተገባበሩ ግን ሁሉም አደናቃፊ ሚና መጫወታቸውን በዝርዝር አስረድቷል፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ የመረጃ ነፃነት ሕግን ከደነገጉ አምስት አገሮች አንዷ ብትሆንም፣ በተግባር የመንግሥት የመረጃ ፍሰት አሁንም ደካማ እንደሆነም አቶ አማረ ገልጿል፡፡ መንግሥት በሚያዘጋጃቸው የተለያዩ ክንዋኔዎችና ኮንፈረንሶች የግሉ ሚዲያ መጋበዙ አበረታች ቢሆንም፣ መረጃ ወቅቱን ጠብቆ የመስጠት የመንግሥት ባህል ለውጥ እንደሚያሻው አሳስቧል፡፡ የግል የቴሌቪዥን ጣቢያ እስካሁን ያልተሰጠበት ምክንያት አጥጋቢ እንዳልሆነ አብራርቷል፡፡

  በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያለው ማተሚያ ቤት በፕሬስ ነፃነትና በማንበብ ባህሉ ላይ ትልቅ ደንቃራ መሆኑንም አቶ አማረ ጠቁሟል፡፡ መንግሥት የግሉን ሚዲያን በኪራይ ሰብሳቢነት መፈረጁና አሳማኝ ባልሆኑ ምክንያቶች የሚዲያ ባለሙያዎችን መክሰሱም በድጋሚ ሊጤን እንደሚገባው አሳስቧል፡፡ ‹‹አንድ ጋዜጠኛ ሌላ ጋዜጠኛ እንዲታሰር የሚጠይቅበት አገር ኢትዮጵያ ብቻ ናት፤›› በማለት ጋዜጠኞች እርስ በርስ ከመጠላለፍ ይልቅ ተባብረው ለሙያው ዕድገት እንዲሠሩም ጥሪ አድርጓል፡፡

የነፃ ፕሬስ ዕድገት በኢትዮጵያ የቃኙት አቶ ታምራት ደጀኔ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ባልደረባ ሲሆኑ፣ በዋናነት ለፕሬስ ነፃነት ዕድገት ጠቃሚ ናቸው ያሏቸውን የሕግ ማዕቀፎች በዝርዝር አብራርተዋል፡፡ ሕጎቹን ለመፈጸም ኃላፊነት ያለባቸውን ተቋማት አሠራርም ቃኝተዋል፡፡

በዕለቱ ተሳታፊ የነበሩ ከተለያዩ የሚዲያ ተቋማት የተገኙ ጋዜጠኞችና ባለሙያዎች መንግሥት፣ የሚዲያ ተቋማት፣ የጥናትና ምርምር ተቋማትና ሚዲያው አለበት ያሉትን ችግሮች በመጠቆም ውይይት አድርገዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ (ክፍል አንድ)

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...