Saturday, June 22, 2024

የዘረኝነት ሰለባ የሆኑት ቤተ እስራኤላውያን

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ኢትዮጵያዊው ዳማስ ፓኬዳህ ወደ እስራኤል ተጉዞ የእስራኤል ዜግነት ካገኘ ጊዜ ጀምሮ በአገሪቱ መከላከያ ኃይል ውስጥ የሚያገለግል ወጣት ነው፡፡ በሚስጥር ካሜራ ተቀርጾ የተሰራጨው ቪዲዮ እንደሚያሳየው ግን፣ ወታደራዊ ዩኒፎርሙን እንደለበሰ በአንድ ጐዳና ላይ በመጓዝ ላይ ሳለ ከአንድ ነጭ ፖሊስ ጋር ይጋጫል፡፡ ቀጥሎም ሌላ ነጭ ፖሊስ ተደርቦ ለሁለት በመሆን መሬት ላይ ጥለውት ጭንቅላቱን ተጭነው ሲያሰቃዩትና ሲደበድቡት ይታያል፡፡ ግጭቱ በምን ምክንያት እንደተቀሰቀሰ አይታወቅም፡፡

ይህንን የተመለከቱ ኢትዮጵያውያን ቤተ እስራኤላውያን ብስጭታቸውን የሚገልጹበት ሌላ መንገድ ያገኙ አይመስልም፡፡ ሐርቴዝ የተባለው የአገሪቱን ታዋቂ ሚዲያ ዋቢ በማድረግ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እንደዘገቡት፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ እስራኤላውያን የቴልአቪቭን ጐዳና የተቆጣጠሩት ባለፈው እሑድ ነበር፡፡ እንደ ዘገባዎቹ ከሆነ፣በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እስራኤላውያን ወደ ጐዳና የወጡት ያለአንዳች ቀስቃሽና አስተባባሪ ሲሆን፣ የአካባቢውን ዋና ዋና መተላለፊያ መንገዶች ተቆጣጥረው በመዝጋት፣ አመፁ ከፖሊስ ቁጥጥር ውጪ ለመሆንም በቅቷል፡፡

እንደ ሚድያዎቹ ዘገባ ከሆነ፣ ከ56 በላይ የፖሊስ አባላት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፣ ከሠልፈኞቹም ጉዳት የደረሰባቸው በርካቶች ናቸው፡፡ በተለይ ሲኤንኤን በቀጥታ ሥርጭቱ የግጭቱን ምሥል ያሳየበት ዘገባው፣ በትውልደ ኢትዮጵያዊው ላይ የተፈጸመው ጥቃትና የመብት ጥሰት ለረጅም ጊዜ ታፍኖ የቆየው የዘረኝነት ችግር እንዲፈነዳ ምክንያት እንደሆነ ያስረዳል፡፡ በዘረኝነት ላይ ያነጣጠረው ተቃውሞ ቀደም ሲል ወደ አካባቢው የተጓዙት ቤተ እስራኤላዊ ኢትዮጵያውያን፣ በትምህርትና በሥራ ቅጥር እንዲሁም በተለያዩ ማኅበራዊ አገልግሎቶች ወይም በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ጥቁር በመሆናቸው የማግለልና የመድልኦ ድርጊት ሲፈጸምባቸው እንደቆየ ይታወቃል፡፡ የተለያዩ ሚዲያዎች በዚህ የዘረኝነት ጉዳይ ላይ ሲጽፉና ሲያጋልጡ የቆዩ ቢሆንም፣ ምንም ዓይነት መሻሻል አልተደረገም፡፡ ለዚህም ይመስላል ሲኤንኤን አጋጣሚው የታፈነው የዘረኝነት ችግር መተንፈሻ እንደሆነ ያተተው፡፡  

‹‹ፈላሻ›› በመባል የሚታወቁት ቤተ እስራኤላውያኑ ኢትዮጵያውያን ወደ እስራኤል ያመሩት መጀመሪያ እ.ኤ.አ. በ1984 ሲሆን፣ ‹‹ኦፕሬሽን ሙሴ›› በሚል የሚታወቅ ነው፡፡ ሁለተኛውም እ.ኤ.አ. በ1991 ‹‹ኦፕሬሽን ሰለሞን›› በሚል 14 ሺሕ ሰዎች ተጓጉዘዋል፡፡ በአጠቃላይ ከ135,500 በላይ ቤተ እስራኤላውያን በእስራኤል እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

‹‹በአገሪቱ ታሪክ ከታዩት የሕዝብ ተቃውሞዎች ከፍተኛነቱን ይይዛል፤›› የተባለለት ይኼው የትውልደ ኢትዮጵያውያን ቤተ እስራኤላውያን ተቃውሞ ቀጥታ መነሻ የሆነው፣ በጥቁር ትውልደ ኢትዮጵያዊ ወታደር ላይ ጉዳት በማድረስ የተጠረጠሩት ፖሊሶች ከሥራቸው ተባረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኮሙዩኒቲ አባላትን ግን ውሳኔው የባሰ ያበሳጨ ሆኗል፡፡ አንዳንዶቹ እንዳሉት፣ በተለይ የአገሪቱ ፖሊስ በጥቁር አፍሪካውያን በተለይ ደግሞ በቤተ እስራኤላውያን ላይ ከፍተኛ የዘረኝነት ድርጊት ሲፈጽም በመቆየቱ፣ ‹‹ዘረኝነት ይብቃ›› የሚሉ መፈክሮች ይዘው እንደነበር ዘጋቢዎቹ ያመለክታሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ግን ባለፈው እሑድ አመሻሽ ላይ በአገሪቱ የመንግሥት ቴሌቪዥን እንደተናገሩት፣ በወታደሩ ላይ ተፈጸመ የተባለው ድርጊት በሕግ እንደሚመረመርና አጥፊዎች ተገቢ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ገልጸዋል፡፡ ‹‹እንደዚህ ዓይነት ሕገወጥነትና ብጥብጥ ግን በእኛ አገር ቦታ የለውም፤›› በማለት በሠልፈኞች ላይ ዝተው ነበር፡፡

የአገር ውስጥና የሕዝብ ፀጥታ ጉዳዮች ሚኒስትሮችን ጨምሮ የተለያዩ የአገሪቱ ባለሥልጣን በተገኙበት ጥቃት የተፈጸመበት ቤተ እስራኤላዊ ወታደርና ሌሎች የቤተ እስራኤል ኮሙዩኒቲ አመራሮችን (ተወካዮችን) እንደሚያነጋግሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል ገብተው ነበር፡፡

የአገሪቱ ፖሊስ ኮሚሽነር ዮሐናን ዳኒኖ የተደረገው ተቃውሞ፣ ‹‹በዴሞክራሲያዊ አገር ውስጥ የተደረገ ሕገወጥ ሠልፍ›› በማለት ቢያወግዙትም፣ ‹‹ቤተ እስራኤላውያን የሚያነሱት አብዛኞቹ ቅሬታዎች ግን ከፖሊስ ጋር የተያያዙ አይደሉም፡፡ እነሱን በማዋሀድ ሒደት ላይ ጥልቀት ያለው ችግር እየተከሰተ ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ ኃላፊነት መውሰድ አለብን፤›› ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ የሕዝብ ፀጥታ ጉዳዮች ሚኒስትር በበኩላቸው፣ የቀረቡ ቅሬታዎች ተቀባይነት ያላቸው መሆናቸውንና ፖሊስን ጨምሮ በተለያዩ የአስተዳደር እርከኖች ያሉት ባለሥልጣናት በአጠቃላይ የመፍትሔ ምላሽ ይዘው መቅረብ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

በቃላቸው መሠረት ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጋር በመሆን ቤተ እስራኤላዊውን ወታደርና ሌሎች የአመራር አባላትን ያነጋገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ፣ ‹‹ዘረኝነትን ከአገራችን ከምንጩ ማድረቅ አለብን፡፡ ለዚህም አንድ ላይ መቆም አለብን፤›› ብለዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ በበኩላቸው፣ ‹‹ይህንን የሚያሳየው ግልጽ የሆነ የዘረኝነት ቁስል መኖሩ ነው፡፡ እስካሁን ልብ ብለን አላየነውም፡፡ አላደመጥናችሁም፡፡ አሁን ግን ጠለቅ ብለን እንፈትሸዋለን፤›› ብለዋል፡፡    

‹‹ባልቲሞር አይደለንም››

ባልቲሞር በመባል በሚታወቀው የአሜሪካ ከተማ በጥቁር አሜሪካዊ ላይ በፖሊሶች በተፈጸመ ግድያ ምክንያት የተነሳ ተቃውሞ ነበር፡፡ አንዳንድ ሚዲያዎች በእስራኤል (ቴልአቪቭ) የተነሳው ከፍተኛ ተቃውሞ ‹‹የእስራኤል ባልቲሞር›› በማለት እየገለጹት ሲሆን፣ የሠልፉ ተሳታፊዎች ግን ከዚህ ጋር የሚያያዝ ምንም ነገር እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ ኢግባል ቦጋለ የተባለች ተቃውሞውን ከቀሰቀሱት 20 ያህል ወጣቶች መካከል አንዷ የሆነች ወጣት፣ ሃሬዝ ለተባለው ሚዲያ እንደገለጸችው ‹‹ጥቁሮች ስለሆንን ብቻ ባልቲሞር ነን ማለት አይደለም፤›› በማለት ፖሊስ የተቃውሞ ሠልፉን አጀማመር ሙሉ ምሥል ያሰናዳ መሆኑን ገልጻ፤ ‹‹እሱን እንየውና የሚያመሳስል ካለው ትታዘባላችሁ፤›› ብላለች፡፡

ሌላው ምሥጋናው ፋንታ የተባለው ወጣት ቤተ እስራኤል ፖሊስ ሠልፉን ፖለቲካዊ መልክ ለማስያዝ መሞከሩን ተቃውሟል፡፡ ‹‹እዚህ ማንም ፖለቲከኛ የለም፡፡ ሠልፉን የጠራ አመራርም የለም፡፡ ኮሙዩኒቲያችን በሙሉ እሮሮውን ለማሰማትና ለማልቀስ ነው ወደ ጎዳና የወጣው፤›› ብሏል፡፡ ምሥጋናው እንደሚለው ችግሩ በዚህ አጋጣሚ ይቀስቀስ እንጂ፣ የእስራኤል ፖሊስ በኢትዮጵያውያን ኮሙዩኒቲ ላይ ሲፈጽማቸው የቆዩ ግፎችን ለመቃወም ለተቃውሞ እንደተወጣ ነው፡፡ ‹‹ለአገራቸው አንዳች ነገር አስተዋጽኦ ሊያደርጉ የሚፈልጉ በርካታ ወጣት ቤተ እስራኤላውያንን ፖሊስ የወንጀል ክስ መሥርቶባቸዋል፡፡ ሊዋጉ አልነበረም የመጡት፡፡ እነሱ ግን ወንጀለኞች ብለው ምንም እንዳይሠሩ አድርገዋቸዋል፤›› በማለት ለጋዜጠኛው ተናግሯል፡፡ ምሥጋናው እንደሚለው፣ ቤተ እስራኤላውያን በአገሪቱ ፖሊስ እምነት ያጡበት ሲሆን፣ በዳማስ ፓኬዳህ ላይ የተፈጸመው ዘረኝነት መሆኑ ታምኖበት፣ ወንጀለኞችን ማባረር ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ ቅጣት ሊጣልባቸው ይገባል፡፡

ተቃውሞውን ቀስቅሰዋል በሚል የሚጠረጠሩ ወጣቶች ካሉበት እየተፈለጉ እየታሰሩ ሲሆን፣ ቀደም ሲል የሚተዋወቁ ናቸው፡፡ በተለይ ዮሴፍ ሰላምሲህ የተባለው ወጣት ቀደም ሲል ራሱን እንዲያጠፋ ፖሊስ ምክንያት መሆኑን ያመኑና ቤተሰቡን ሲተባበሩ የቆዩት መሆናቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡

ተቃውሞውን ያቀጣጠሉት ኢትዮጵያውያን ቤተ እስራኤላውያን አባላት በአብዛኛው ወጣቶች ሲሆኑ፣ ብዙዎቹ እዚያው እስራኤል የተወለዱ መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ምሥጋናው እንዳለው፣ ‹‹እኛ እኩልነትንና ፍትሕን እንሻለን፡፡ በተለይ ወጣቱን በወንጀል እየጠረጠሩ ስሙን መመዝገብ ወንጀል እንዲሠራ መገፋፋት ነው፡፡››

የቤተ እስራኤላውያኑ ጥያቄ ከፖሊስም የዘለለ ነው፡፡ ‹‹እኛ የተለየ ጥቅም ወይም እንክብካቤ አንሻም፡፡ እንደ ማንኛውም ዜጋ እኩል እንድንታይ ነው ጥያቄያችን፤›› ማለታቸውን ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡ መኒ እያሱ የተባለው ሌላ ወጣት፣ ‹‹መንግሥት ጥያቄያችን ሳያድበሰብስ መመለስ አለበት፤›› ብሎ፣ ‹‹በአንዳንድ ከተሞች በተለየ እጅግ የከፋ ዘረኝነት እየተጸመብን ነው፡፡ በተለይ በትምህርት ቤትና በሥራ ቅጥር ያለው ችግር ከተቀረፈ በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን ችግር ለመፍታት ቀላል ነው፤›› በማለት አስረድቷል፡፡

እስራኤልና ስደተኞች

በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በመጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስ ክርስቶስን ታሪክ የሚወዳደር የለም፡፡ የዚሁ ሁሉ ታሪክ ማጠንጠኛ ደግሞ፣ እስራኤልና በአካባቢዋ የሚገኙት እንደ ኢየሩሳሌም የመሳሰሉት ታሪካዊ ቦታዎች ናቸው፡፡

እስራኤላውያን በሰው ልጅ ታሪክ ዘንድ ላቅ ያለ ታሪክ አላቸው የሚባለውን ያህል፣ እንደነሱ ግን ግፍ የወረደበት ማኅበረሰብ የለም ይባላል፡፡ በታሪክ አጋጣሚ በዓለም ላይ የተበተኑት እስራኤላውያን በጀርመን ናዚ የደረሰባቸውን የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋን ጨምሮ፣ በተለያዩ አካባቢዎች ከፍተኛ ግፍ፣ ኢሰብዓዊ የሆነ ማግለልና ጭቆና ደርሶባቸዋል፡፡ በጽዮናውያን ንቅናቄና በእንግሊዝ ድጋፍ እንደ አዲስ የተቆረቆረችው እስራኤል ግን በጐረቤቶችዋ በበጐ ዓይን የምትታይ አልሆነችም፡፡ ከፍልስጥኤም ጋር ባላት የቆየ የድንበር ቁርሾ የተነሳ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ስሟ በሰላም ተነስቶ አያውቅም፡፡

ከኃያሏ አገር አሜሪካ ጋር ባላት ታሪካዊ ትስስር ምክንያት እንደ የእንጀራ እናት የምትታይ ሲሆን፣ በፍልስጥኤሞች ምክንያት በየጊዜው የሚደርስባት ውግዘትና ወቀሳ ቁጥር ሥፍር የለውም፡፡ በተመድ ጠንከር ያለ ዕርምጃ ሲወሰድባት ግን አይስተዋልም፡፡

እስራኤል የዓለም ታሪክን በበጐ የተቆጣጠረችው ያህል በተቃራኒ በሞትና በግጭት ስሟ የሚነሳው ግን ከፍልስጥኤም ጋር በተያያዘ ብቻም አይደለም፡፡ እስራኤላውያን ዓለምን በስደት መከራ እንዳላዩ፣ በአገራቸው ከሚደርስባቸው የኢኮኖሚ ችግርም ሆነ የፖለቲካ ጫና ለመሸሽ ድንበሯን ተሻግረው የሚገቡ በተለይ ኤርትራውያን፣ ኢትዮጵያውያንና ሱዳናውያን በማሳደድ፣ በማባረርና በማሰር ተወዳዳሪ የላትም፡፡

አልጄዚራ ቀደም ሲል ከሁለት ዓመት በፊት “Should Israel be Responsible for Immigration?” በሚል ርዕስ አንድ መርማሪ ዘጋቢ ፊልም አቅርቦ ነበር፡፡ አልጄዚራ ለዚሁ መነሻ የሆነው የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት የሰብዓዊ መብት ዓመታዊ ሪፖርት ሲሆን፣ ሪፖርቱ እንደሚለው በእስራኤል ቁጥራቸው የበዛ ስደተኞች የሚገኙ ቢሆንም፣ በአገሪቱ ስደተኞችን ለመርዳት የሚደረግ ምንም ዓይነት ሕጋዊ አሠራር የለም የሚል ነው፡፡ ሪፖርቱ እንደሚለው፣ የእስራኤል መንግሥት ስደተኞችን እንደ ስደተኛ ተቀብሎ የሚያስተናግድበት አሠራር የሌለው ከመሆኑም በተጨማሪ፣ የአገሪቱ ባለሥልጣናት እየተበራከቱ የሚስተዋሉትን ወንጀልን፣ በሽታንና ሽብርን ከስደተኞቹ ጋር በማያያዝ አሰቃቂ ዕርምጃዎች ይወስዱባቸዋል፡፡ ቤተ እስራኤላውያኑም በተመሳሳይ የዘረኝነት ችግር እንደሚደርስባቸው ሪፖርቱ ያሳያል፡፡

ፊልሙ በወጣበት እ.ኤ.አ. በ2012 መጨረሻ ከ4,000 በላይ ስደተኞች ያመለከቱ ሲሆን፣ ከዚህ ሁሉ ቁጥር ተቀባይነት ያገኘው አንድ ሰው ብቻ ነበር፡፡ ጉዳያቸው ያልታየው ሌሎች ከ6,000 በላይ ጥቁር አፍሪካውያን ስደተኞች ነበሩ ይላል ሪፖርቱ፡፡

ጌድዮን ሌቪ የተባለው ሀራዝ ለተባለው የአገሪቱ ታዋቂ ሚዲያ ጸሐፊ ለአልጄዚራ ሲናገር፣ ‹‹በርካታ እስራኤላውያን ወደ ተለያዩ አገሮች በሕገወጥ መንገድ ተሰደዋል፡፡ ብዙዎቹም ተርፈዋል፡፡ መብት የተነፈጉም ነበሩ፡፡ እስራኤል ይህንን ታስተውላለች ብዬ እገምት ነበር፡፡ ችግሩ ግን እስራኤል ስደተኞችን በተመለከተ ወጥ ፖሊሲ እንኳን የሌላት መሆኑን ነው፤›› ብሏል፡፡

እስራኤል ባለፈው ዓመት በርካታ ጥቁር አፍሪካውያን ከአገሯ በግፍ ማባረሯን የሚታወስ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ ኢትዮጵያውያን በብዛት ይገኙባቸዋል፡፡ በቅርቡ አይኤስ የተባለው በግፍ ከጨፈጨፋቸው 30 ሰዎች መካከል አንዱ ከእስራኤል ከተባረሩት ኤርትራዊያን መካከል እንደነበር ተገልጿል፡፡

ሴትህ ፍራንዝማን የተባሉት የኢየሩሳሌም ነዋሪ የመካከለኛው ምሥራቅ የፖለቲከ ተንታኝ እንደሚሉት፣ ማግለል በእስራኤላውያን ዘንድ ሥር የሰደደ በሽታ ነው፡፡ ‹‹ሩሲያውያን፣ ፍልስጥኤማውያን፣ ዓረብና ጥቁር አፍሪካውያን የዚሁ የዘረኝነት ሰለባ ሆነዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ይህንን መቋቋም አልቻሉም፡፡ ተቃውሞአቸው ለውጥ ያምጣ አያምጣ ግን አይታወቅም፤›› ብለዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -