አምስተኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ ሊካሄድ የቀሩት በጣም ጥቂት ቀናት ናቸው፡፡ ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. የሚካሄደውን ምርጫ በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን ጉዳዩ የሚመለከታቸው የተለያዩ ባለድርሻ አካላት፣ ለማከናወን ያቀዷቸውን ተግባራት ዳር እያደረሱ እንደሆነ እየገለጹ ይገኛሉ፡፡
ምርጫውን በበላይነት የሚቆጣጠረውና የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ለምርጫው ቅድመ ዝግጅቱ በአብዛኛው መጠናቀቁን በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ አስታውቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሌሎች የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የምርጫውን ክንዋኔ ነፃ፣ ፍትሐዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የራሳቸውን ሚና እየተወጡ እንደሆነ በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡
ከእነዚህ ባለድርሻ አካላት መካከል የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር አንዱ ነው፡፡ ማኅበሩ ከአውሮፓ ኅብረት ‹‹ሲቪል ሶሳይቲ ፈንድ II›› ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ምርጫ ሕግ በንጽጽራዊ ዕይታ›› በሚል ርዕስ ላይ ውይይት አካሂዷል፡፡ ውይይቱ የተካሄደው ሚያዝያ 24 ቀን 2007 ዓ.ም. በግዮን ሆቴል ነበር፡፡ በዕለቱ ለውይይት መነሻ ያቀረቡት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግና የአስተዳደር ትምህርት ጥናቶች ኮሌጅ ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር ጌድዮን ጢሞቲዎስ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ጠበቆች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ በሻዳ ገመቹ ደግሞ አወያይ በመሆን ውይይቱን አካሂደዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በቀረበው ጽሑፍ ላይ ሐሳብ ሰጪ በመሆን ደግሞ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግና የአስዳተዳደር ትምህርት ጥናቶች ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ጌታቸው አሰፋም በመድረኩ ላይ ተገኝተው በዶ/ር ጌዲዮን ሐሳብ ላይ ተጨማሪ አስተያየቶችና የተወሰኑ ጥያቄዎችን ሰንዝረው ነበር፡፡ ዶ/ር ጌድዮን የኢትዮጵያን የምርጫ ሕግጋት ከሌሎች አገሮች፣ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚሠራባቸው መሥፈርቶችና ልማዳዊ አሠራሮች በማነፃፀር ትንተና አቅርበዋል፡፡
የአገሪቱን የምርጫ ሕግጋት በዝርዝር በንፅፅር ዕይታ ከመገምገማቸው አስቀድመው ግን፣ በዴሞክራሲና በምርጫ መካከል ተቀራራቢነት ቢኖርም አንድ እንዳልሆኑ ግን ተከራክረዋል፡፡ በዚህ መሠረት የተለያዩ ምሁራን በጉዳዩ ላይ የሚሰጡትን ሐሳብ በማንሳት ስለጽንሰ ሐሳቦቹ ገለጻ አድርገዋል፡፡ ከዚህ አንፃር ‹‹ምርጫ ለዴሞክራሲ በጣም አስፈላጊ የሆነ፣ ነገር ግን በቂ ያልሆነ፤›› ተግባር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
‹‹አንደኛው ጽንሰ ሐሳብ አንደኛው ላይ የሚመሠረት ቢሆንም፣ በአንድ አገር ምርጫ ተካሂዷል ማለት ዴሞክራሲ አለ ማለት ላይሆን ይችላል፤›› ያሉት ዶ/ር ጌድዮን፣ በሁለቱ ጽንሰ ሐሳቦች መካከል ያለውን ልዩነትና አንድነት እንዲሁም በዘርፉ ያሉ ምሁራን ዘንድ ያለውን ረዘም ያለ ጊዜ ያስቆጠረውን ክርክር ለማሳየት ሞክረዋል፡፡
‹‹ከዚህ አንፃር ያለ ምርጫ ዘመናዊው የውክልና ዴሞክራሲ ይኖራል ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡ ስለዚህ ምርጫ ዴሞክራሲ እንዲኖር የግድ መኖር አለበት፡፡ ነገር ግን ምርጫ መኖሩ ብቻውን ዴሞክራሲ አለ አያሰኝም፤›› በማለት የገለጹት ዶ/ር ጌድዮን፣ ‹‹ምርጫ የዴሞክራሲ አልፋና ኦሜጋ አይደለም፤›› በማለትም ምርጫ ማካሄድ ዴሞክራሲ ስለመኖሩ አንድ መለኪያ እንጂ ፍፃሜው እንዳልሆነ አስገንዝበዋል፡፡
ዶ/ር ጌድዮን አንድ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ እንዲባል መሟላት ካለባቸው መሥፈርቶች መካከል መሠረታዊ የሆኑትን እንዲሁ ዘርዝረው ጠቅሰዋል፡፡
አንድ ምርጫ ተቀባይነት እንዲኖረውና ዴሞክራሲያዊ ነው እንዲባል ከሚያስፈልጉት ወሳኝ ቅድመ ሁኔታዎች መካከል በመራጭነትም ሆነ በተመራጭነት የመሳተፍ ዕድል በሰፊው የተከፈተ መሆን፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን ማክበር፣ እንዲሁም የመደራጀት መብት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ እነዚህ ዝቅተኛ ቅድመ ሁኔታዎች ባልተከበሩበት ዓውድ ውስጥ የሚካሄድ ምርጫ ዴሞክራሲያዊና ቅቡልነት አለው ብሎ ማሰብ አዳጋች መሆኑን፣ የዜጎች ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት መከበር ፋይዳው ብዙ እንደሆነ ያሰመሩት ዶ/ር ጌድዮን፣ ‹‹ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በሌለበት ሁኔታ ውስጥ፣ እንዲሁም ይህ መብት በተገደበበት ዓውድ ውስጥ ዴሞክራሲያዊና ተቀባይነት ያለው ምርጫ ተካሂዷል ማለት አይቻልም፤›› ብለዋል፡፡
የምርጫ ሕጎች በንፅፅር
የአገሪቱን አጠቃላይ የምርጫ ሒደት ለማስተናገድ እንዲሁም ለማከናወን የሚረዱ የተለያዩ ሕጎች ወጥተዋል፡፡ በዚህ ረገድ የጥናት ጽሑፍ አቅራቢውም ‹‹በርካታ ሕጎች አሉ›› በማለት ጠቅሰዋል፡፡
ከእነዚህ በርካታ ሕጎች መካከል የአገሪቱ ከፍተኛው ሕግ ሕገ መንግሥቱ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ከአንቀጽ 466 እስከ 476 ድረስ ያሉት አናቅጽት ምርጫን የተመለከቱ ጉዳዮችን እንደሚያስተዳድሩ አውስተዋል፡፡ በተጨማሪም ስለምርጫ አትኩሮት የሚያደርጉና በዋነኝነት የምርጫ ሕግ የሚባሉት ደግሞ፣ የተሻሻለው የኢትዮጵያ ምርጭ ሕግ አዋጅ 532/1999፣ የተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573/2000 እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ሥነ ምግባር ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 662/2002ን ጠቅሰዋል፡፡
ከነዚህ ሕጎች በተጨማሪ በተለይ በምርጫ አዋጁ ላይ ተመሥርቶ ቦርዱ ወደ ሰባት የሚጠጉ መመርያዎችን ያወጣ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ ‹‹መመርያዎቹ በጣም ዝርዝር የሆኑ ጉዳዮችን የያዙ ናቸው፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡
በአጠቃላይ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሕግጋቱ መብዛት የምርጫውን ሒደት በተመለከተ ክፍተት ብዙም አለ ለማለት እንደማያስደፍር ገልጸዋል፡፡ በዚህ ረገድ ከዓለም አቀፍ ደረጃዎች አንፃር አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ሕጎችም እንዲሁ መሥፈርቶችን ያሟላሉ በማለት ይገልጿቸዋል፡፡ ሆኖም ግን በሕጎቹ አሉ ያሉዋቸውን የተወሰኑ ክፍተቶችን ለማሳየት ሞክረዋል፡፡
ለምሳሌ በሌሎች አገሮች ያለውን በተመለከተ ተመራጭ ሆኖ የመመዝገብ ሒደትን ሲገልጹ፣ ‹‹ተመራጭ ሆኖ ለመቅረብ የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችን ስናይ፣ በአብዛኛዎቹ አገሮች መራጭ ሆኖ መቅረብ የሚችል ሰው ተመራጭ ሆኖ መቅረብ ይችላል፤›› ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ልምድም ተመሳሳይ እንደሆነ አስታውሰው፣ ነገር ግን የተወሰኑ ልዩነቶች እንዳለው ገልጸዋል፡፡ አንድ መራጭ ማሟላት የማይጠበቅበት፣ ግን ዕጩ ሆኖ ለመቅረብ የሚያስፈልገው የክልሉ ወይም የምርጫ ወረዳውን የተለየ የሥራ ቋንቋ የማወቅ ግዴታ ያለበት መሆኑ ነው፡፡ ሌላው ያነሱት ነጥብ ደግሞ በግል ዕጩ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቅረብ የሚደረገውን ጥረት ያሳዩበትና የግል ዕጩ ተወዳዳሪዎች ላይ ያለው ውጣ ውረድ ከሕገ መንግሥት አንፃር የቃኙበት ሁኔታ ነው፡፡
በአጠቃላይ ሲታይ የምርጫ ሕጉ ከግል ዕጩ ተወዳዳሪዎች ይልቅ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ቅድሚያ ይሰጣል በማለት የገለጹት ዶ/ር ጌድዮን፣ በአንድ የምርጫ ክልል ከሚወዳደሩ 12 ዕጩዎች መካከል ቅድሚያ የሚሰጠው ለፖለቲካ ፓርቲዎች ነው፡፡ የግል ዕጩ ተወዳዳሪዎቹ የመወዳደሪያ ዕጣ ውስጥ እንኳን የሚገቡት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ቀጥሎ መሆኑ ወይም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከዕጩነት ውጪ የሚሆኑበት አሠራር ከሕገ መንግሥቱ መሠረታዊ መብቶች ጋር ይጋጫል በማለት ሞግተዋል፡፡
‹‹ቅደም ተከተሉን ስንመለከተው ባለፈው ምርጫ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ የቻሉ ስድስት ፓርቲዎች ቅድሚያ ያገኛሉ፡፡ ሌሎች ፓርቲዎች ደግሞ በዕጣ ይለያሉ፡፡ የግል ዕጩዎች ከዚህ በኋላ ነው የሚታዩት፡፡ የግል ዕጩዎች የዕጣ ውድድር ላይ ሳይቀር ላይገቡ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ በቃ ፉክክርም ውስጥ ሳልገባ ዕጣ ውስጥ እንኳን ሳልገባ ምንም ልቆጣጠረውና ልረዳው በማልችለው ሁኔታ ተፎካካሪ ሳልሆን በዕጣ፣ በዕድል ወይም በአጋጣሚ ከምርጫ መውጣት በሕገ መንግሥቱ ላይ ባሉት ድንጋጌዎች ላይ የተቀመጠ ገደብ ነው፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡
ቁጥሩን በ12 መገደብ የራሱ ምክንያት ሊኖረው እንደሚችልና ይህን እንደሚረዱ የገለጹት ዶ/ር ጌድዮን፣ ‹‹የሚወዳደሩት ሰዎች ቁጥር መገደብ አለበት የሚለው ሊያስማማ ይችላል፡፡ ነገር ግን የሚገደብ ከሆነና 40 ወይም 50 ሰዎች ቢኖሩ ከእነዚያ ሰዎች መካከል 12 የሚመረጡት እንዴት ነው? የሚለው ላይ ይበልጥ ምክንያታዊ የሆነና ከዚሁ የተሻለ አካሄድ ወይም አሠራር ሊኖረው ይገባል፡፡ አሁን ባለው አካሄድ ግን መሠረታዊ የሆነ የሕገ መንግሥታዊ መብት ጥሰት ያለ ይመስለኛል፤›› በማለት የአዋጅ ቁጥር 532/99 አንቀጽ 49ን ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 38 ጋር እንደሚጋጭ በመግለጽ ተቃርኖውን አሳይተዋል፡፡
በዕለቱ በምርጫ ሕጉ የተካተቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የገንዘብ ምንጭ፣ የገንዘብ አጠቃቀም፣ የመገናኛ ብዙኃን አጠቃቀምና እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በማንሳት ከዓለም አቀፍ አሠራር ጋር በንፅፅር አቅርበዋል፡፡ በዕለቱ ከነበሩ በርካታ የውይይቱ ተሳታፊዎች ሕጉን በተመለከተ የተለያዩ ጥያቄዎች ወደ መድረኩ ተሰንዝረዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ጥያቄዎች ያጠነጠኑት ደግሞ በአንድ የምርጫ ክልል ላይ በሚኖረው የምርጫ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ብዛትና ለመወዳደር ከሚጠየቀው ከቋንቋ መስፋፋት ጋር የተያያዘ ነበር፡፡
አንዱ ተወያይ ያነሱት ጥያቄ፣ ‹‹ምርጫ የአማራጭ ውሳኔ ነው፡፡ ዘመናዊ መንግሥት የምርጫ ውጤት ነው፡፡ ከዚህ ተነስተን ነፃና ገለልተኛ ጋዜጣ ወይም ጠንካራ የሲቪክ ማኅበረሰብ ያልተሳፉበት ወይም ጠንካራ የፖለቲካ ተቃዋሚዎች በሌሉበት ዓለም የሚካሄደው ምርጫ፣ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ነው ብሎ መናገር ይቻላል ወይ?›› የሚል ነበር፡፡
ለዚህ ጥያቄ የመድረኩ አወያይ አቶ ባሻዳ ገመቹ፣ ‹‹ጠንካራና ገለልተኛ የሚሉት ቃላት መለኪያው ምንድነው?›› በማለት ጥያቄውን በጥያቄ መልሰው፣ ጉዳዩ አጨቃጫቂ እንደሆነ ከመግለጽ ባለፈ፣ ‹‹ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ስላልተሳተፉ ስለነሱ ማውራት ተገቢ አይሆንም፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በመድረኩ ላይ በርካታ መሠረታዊ ነጥቦች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ ነገር ግን ምርጫው ሊካሄድ ከቀሩት ጥቂት ቀናት አንፃር ውይይቱ ቀደም ብሎ ቢካሄድ የተሻለ እንደነበር ተሳታፊዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው መራጮች፣ ዕጩዎች፣ ለምርጫ ቦርድና እንዲሁም ለሌሎች አካላት አሠራራቸውን እንዲፈትሹ ዕድል ለመስጠት የተሻለ ያስችል እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡ ቢያንስ ግን ለመጪው ጠቅላላ ምርጫ ወይም በመሀል ለሚካሄዱ ምርጫዎች በግብዓትነት ሊጠቅም ይችላል ያሉም ነበሩ፡፡