Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ባቫሪያ በሐበሻ ቢራ ውስጥ ያለውን ድርሻ ወደ 71 በመቶ አሳደገ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከሁለት ሳምንታት በኋላ ምርት ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀው ሐበሻ ቢራ ውስጥ ከፍተኛውን የባለቤትነት ድርሻ የያዘው ባቫሪያ የተባለው የኔዘርላንድ ኩባንያ የባለቤትነት ድርሻ ወደ 71 በመቶ ከፍ አለ፡፡

ከስምንት ሺሕ በላይ ባለአክሲዮኖችን የያዘው ሐበሻ ቢራ አክሲዮን ማኅበር ውስጥ አብላጫውን የባለቤትነት ድርሻ የያዘው ባቫሪያ፣ ድርሻውን 71 በመቶ ያደረሰው ለሦስተኛ ጊዜ የአክሲዮን ድርሻውን ለማሳደግ ባደረገው ስምምነት ነው፡፡ ባቫሪያ ሐበሻ ቢራን እንደአንድ ባለአክሲዮን ሲቀላቀል 39 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ በመያዝ የሚያስችለውን አክሲዮን ገዝቶ ነበር፡፡ ከዚህ ስምምነት በኋላ፣ ባለፈው ዓመት ደግሞ የባለቤትነት ድርሻን ወደ 60 በመቶ የሚያሳድግ ስምምነት ካደረገ በኋላ እንደገና ለሦስተኛ ጊዜ ባደረገው ስምምነት ተጨማሪ አክሲዮን ገዝቶ የባለቤትነት ድርሻውን ወደ 71 በመቶ ማሳደግ ችሏል፡፡

ባቫሪያ የባለቤትነት ድርሻውን ይህንን ያህል ደረጃ ያሳደገው ቢተር ሊንሰን ከሚባለው ኩባንያ ጋር ተጣምሮ ነው፡፡ የባቫሪያ የባለቤትነት ድርሻ በዚህን ያህል ደረጃ ያደገበት ምክንያት ለሐበሻ ቢራ ፋብሪካ ግንባታ ኢንቨስትመንት የሚፈለገው ገንዘብ በተጠበቀው ደረጃ ከባለአክሲዮኖች ሊሰበሰብ ካለመቻሉ ጋር የተያያዘ ነው፡፡

አክሲዮን ማኅበሩ ከአንድ ሳምንት በፊት ባደረገው ጠቅላላ ጉባዔ ላይም የባቫሪያን የአክሲዮን ድርሻ በሚመለከት ከባለአክሲዮኖች ጥያቄ የቀረበ ሲሆን፣ ቦርዱም ምክንያቱን አስረድቷል ተብሏል፡፡ ባቫሪያ የባለቤትነት ድርሻውን እያሳደገ የመጣበት ዋነኛ ምክንያት ተብሎ የሚጠቀሰውም ፕሮጀክቱ ለኢንቨስትመንት ወጪው ከባለአክሲዮኖች ከሚያስፈልገው ገንዘብ ውስጥ 30 በመቶውን ከያዘ በኋላ ቀሪውን በባንክ ብድር ለመሙላት የተያዘው ዕቅድ ሊሳካ ባለመቻሉም ነው ተብሏል፡፡

የአክሲዮን ማኅበሩ አመራሮች እንደሚገልጹትም፣ ለኢንቨስትመንቱ ከሚያስፈልገው ገንዘብ 30 በመቶን በቅድሚያ በመሰብሰብ ቀሪውን 70 በመቶ የኢንቨስትመንት ወጪ በብድር ለመሸፈን ለባንኮች ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት አለማግኘቱ የኔዘርላንዱን ኩባንያ አክሲዮን ድርሻ በማሳደግ ሥራውን ማጠናቀቁ በማስፈለጉ ነው፡፡

አንዳንድ ባለአክሲዮኖች ግን ወደ መጠናቀቂያው የደረሰውና ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የተደረገበት ፕሮጀክት ተመልክቶና ንብረቱን ይዞ ብድር የሚሰጥ ባንክ እንዴት ሊጠፋ ይችላል? የሚል ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ በተለይ ልማት ባንክ በኢንዱስትሪ ዘርፍ ለተሰማሩ ኩባንያዎች ማበደር ያልቻልኩት ከፍተኛ ገንዘብ አለኝ እያለ፣ ሐበሻ ቢራ አክሲዮን ማኅበር ብድር ሊያገኝ ስላልቻለ በሚል ለባቫሪያ ዕድሉ መሰጠቱ ግራ እንደገባቸውም ይናገራሉ፡፡

አንዳንድ ባለአክሲዮኖች ደግሞ ከዚህ የተለየ አስተያየት አላቸው፡፡ ችግሩ የሁሉም ባለአክሲዮን መሆኑን የሚጠቁሙት እነዚህ አስተያየት ሰጪዎች ባለአክሲዮኖች፣ ከዚህ ቀደም ያስፈልጋል የተባውን ገንዘብ ለማሟላት ተጨማሪ አክሲዮኖችን ካለመግዛታቸው ጋር የተያያዘ ነው ይላሉ፡፡

ባለአክሲዮኖቹ በተሰጠው ዕድል መሠረት ተጨማሪ አክሲዮኖችን ቢገዙ ኖሮ፣ በሐበሻ ስም የተቋቋመውን ኩባንያ አብላጫውን የባለቤትነት ድርሻ ኢትዮጵያውያን ይይዙት ነበር በማለትም ገልጸዋል፡፡

እንደ ሐበሻ ቢራ ፋብሪካ አይሁን እንጂ ሌሎቹም የቢራ ፋብሪካዎች ለመገንባት በአክሲዮን ኩባንያ ደረጃ የተቋቋሙት ሦስቱም አክሲዮን ኩባንያዎች የውጭ ኩባንያዎችን በማስገባት እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡

ራያ ቢራ ውስጥ የፈረንሳዩ ቢጂአይ ኢትዮጵያ 42 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ አለው፡፡ በምሥረታ ላይ የሚገኘው ዘቢደር ቢራም 65 በመቶውን የባለቤትነት ድርሻ ለቼክ ኩባንያ ለመስጠት ስምምነት አድርጓል፡፡

ሐበሻም በተመሳሳይ መንገድ 71 በመቶውን ለባቫሪያ መስጠቱ በሁሉም የአክሲዮን ኩባንያዎች የተቋቋመ የቢራ ፋብሪካዎች ውስጥ ብልጫ ያለውን ድርሻ የውጭ ኩባንያዎች መያዛቸውን ያመለከተ ሆኗል፡፡

ሐበሻ ቢራ ከአዲስ አበባ 120 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ደብረ ብርሃን ከተማ እየገነባ ያለው የቢራ ፋብሪካ፣ በአሁኑ ጊዜ በመጠናቀቁ ከሁለት ሳምንታት በኋላ በፋይ ሥራ ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በዓመት 300 ሺሕ ሔክቶ ሊትር ቢራ የማምረት አቅም ያለው ይህ ፋብሪካ፣ ሐበሻ በሚል መጠሪያ ያለውን ቢራ ምርት ለገበያ ካቀረበ በኋላ በቀጣዩ ዓመት የማስፋፊያ ግንባታ እንደሚያካሂድ መግለጹ ይታወሳል፡፡

ባቫሪያ ቢራ በኔዘርላንድ ሁለተኛው ቢራ አምራች ኩባንያ ሲሆን፣ በዓመትም አምስት ሚሊዮን ሊትር ቢራ ያመርታል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች