Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ወዳጅና ጠላት ሲደባለቁስ?

ከሜክሲኮ ወደ ፒያሳ ጉዞ ሊጀመር ነው፡፡ ወያላው ከቢጤዎቹ ጋር ሆኖ ወጪ ወራጅ ሴቶችን እየለከፈ ነው፡፡ ጋቢና የተቀመጠ ጐልማሳ አንገቱን ወደ ውጭ እያሰገገ፣ ‹‹አንተ አርፈህ ሥራህን አትሠራም? ሴቶቹ ቢከሱህ እኔ ምስክር ሆኜብህ ወህኒ ብትወርድ በራስህ እንጂ በማንም እንዳታዝን…›› ሲለው፣ ‹‹ለመሆኑ ጥፋቴ ምን ሆኖ ነው ለክስ በቅቼ ወህኒ የምገባው? ራሳቸው ሴቶቹ አይደሉ እንዴ ለመለከፍ ብለው በሚያሳቅቅ አለባበስ ችግር ውስጥ የሚከቱን…›› በማለት ይመልሳል፡፡ ጐልማሳው አልተዋጠለትም መሰል፣ ‹‹የፈለጉትን መልበስ መብታቸው ነው፡፡ አንተ ግን ስትተነኩሳቸውና ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ለመፍጠር ከሞከርክ ግን አለቀልህ…›› ከማለቱ ሁለት ፖሊሶች ከተቃራኒ አቅጣጫ በጥድፊያ ሲመጡ፣ ወያላው እግሬ አውጪኝ ብሎ ተፈተለከ፡፡

በዚህ ጐዳና ላይ ስንቱ የስንቱን መብት እንደነካ፣ ስንቱን ስንቱን እንዳስለቀሰ፣ ማን በማን እንደተታለለ፣ ጊዜ በነጐደ ቁጥር ለሚያሰላስለው አስገራሚ ትዕይንቶች ድቅን ይላሉ፡፡ ጐዳናው የሁሉም ሆኖ ሁሉም ግን እንደ ፍላጐቱ ስለማይስተናገድበት አድልኦና መገለሉ ቁልጭ ብሎ ይታይበታል፡፡ ትናንት በኩራት የተራመዱበት ዛሬ አቀርቅረው ይታዩበታል፡፡ ትናንት ቆመጥ ወይም ጠመንጃ ይዘው ስንቱን ያስገበሩበት ዛሬ ምፅዋት ይለምኑበታል፡፡ ያኔ ድሮ በአጀብ በሰጋር በቅሎ ወይም በዶጅ የተንፈላሰሱበት ዛሬ ከታሪካቸው በስተቀር እነሱ አይታዩበትም፡፡ ብቻ ሁሉም በጊዜው የተመላለሰበት ጐዳና ዛሬም የስንቶች ፈንጠዝያና ዋይታ ይደመጥበታል፡፡ አንዱ አባራሪ ሌላው ተባራሪ ሆነውም ሲመላለሱበት፣ ከሕይወት ጋር ግብግብ የያዙትም እንዲሁ ላይ ታች ሲሉ ይውሉበታል፡፡ ጐዳናው ጾሙን ውሎ አድሮ አያውቅም፡፡

ጎረምሳው የታክሲ ሾፌር ጃፖኒውን ለብሶ የተወጣጠረ ጡንቻውን እያሳየን መሪው ላይ ሲሰየም ወያላው የለም፡፡ አንገቱን በመስኮት ወጣ አድርጎ ሲጣራ መልስ አጣ፡፡ በፍጥነት ተንደርድረው ያለፉት ሁለት ፖሊሶች አንዱን ጠረንገሎ አንጠልጥለው ሲያልፉ ታክሲውን የሞሉት ተሳፋሪዎች የተመካከሩ ይመስል ሳቅ በሳቅ ሆኑ፡፡ ጋቢና ያለው ጐልማሳ፣ ‹‹ፖሊሶቹ ሲመጡ ደንግጦ ፈርጥጦ ነው፡፡ አቧራው ከሰከነ በኋላ ይመለሳል…›› እያለ ሳለ ወያላው እያለከለከ ተመለሰ፡፡ ትንፋሹ ቁርጥ ቁርጥ ስለሚል ለሾፌሩ ጥያቄ መልስ መስጠት ተስኖታል፡፡ በሳምሰንግ ሞባይሏ የምትመፃደቅ የምትመስል አንዲት ወጣት ስልኳን በእንቁልልጭ ዓይነት እያውለበለበች፣ ‹‹‹አፍህን ስታሞጠሙጥ ጀግና ትመስል ነበር፡፡ ፖሊስ ብቅ ሲል ግን እንደ ጥንቸል ሮጠህ ጠፋህ፡፡ ድሮም ፈሪና ጉረኛ እንዲህ ናቸው፤›› ብላ ስትወርድበት መልስ ለመስጠት አልደፈረም፡፡

ከወጣቷ አጠገብ የተቀመጠ ረዘም ብሎ ቀጠን ያለ ወጣት፣ ‹‹ይኼ እኮ የእሱ ብቻ ችግር አይደለም፡፡ የመላ አገሪቱ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በየቦታው ብትሄዱ ከማይረባ ትችት ጀምሮ መፍትሔ አልባ የሆኑ አስተያየቶችን ስትሰሙ አገሪቱ በምሁራን የተሞላች ይመስላችኋል፡፡ አንዳንዱ በዞረ ድምር (ሐንግኦቨር) የአገሪቱን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመተንተን ሲዳዳው፣ ሌላው ምርቃና ውስጥ ሆኖ ይፈላሰፋል፡፡ አንድ ቀን ተሳስቶ ሚስቱን የቤት ሥራ ረድቶ የማያውቅ ሰው ስለአገር ጉዳይ ኤክስፐርት ሆኖ ይቀርባል፡፡ ለተቸገረ አንዲት ጉርሻ ወይም አንድ ብርጭቆ ውኃ ያላቀበለ በሰው ገንዘብ ላይ ሲፈርድ ታያላችሁ፡፡ ቤተሰቡን በቅጡ ማስተዳደር ያቃተው ስለአገር አስተዳደር መሠረታዊ ግንዛቤ ለመስጠት ይቸኩላል…›› እያለ ርዕሰ ጉዳዩን ከታክሲው ውስጥ ወግ አውጥቶ የአገር ጉዳይ ሲያደርገው ጨዋታው ደራ፡፡ ለዚህ ማን ብሎን?

መካከለኛው ወንበር ላይ የተሰየመች ደርባባ ወይዘሮ፣ ‹‹ለመሆኑ አንተ ደግሞ የትኛው የሰላ ተቺ ሆነህ ነው ይህንን ሁሉ የምትዘባርቀው?›› ብላ ስትናገር ወጣቱ ዞር ብሎ፣ ‹‹እንዴት? እንዴት?›› አላት፡፡ ‹‹እንዴት ማለት ጥሩ፡፡ ዘመናችን እኮ የንግግር ነፃነትን የሚያበረታታ፣ ይህ ነፃነት ስለተሰጠንም ሁሉም እንደ ፍላጐቱ ያለ ገደብ የሚገለገልበት ነው፡፡ ማንም የመሰለውን አስተያየት በመስጠቱ እቤቱ ጓዳ ድረስ እየተገባ እንዴት ነው እንዲህ በሐሜት የሚዘለዘለው?›› ብላ ተነፈሰች፡፡ ወጣቱ የዋዛ አይመስልም፡፡ ‹‹እመቤት ሐሳብሽን ባልቀበለውም መናገርሽን ግን እደግፈዋለሁ፡፡ ይህ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ ነው፡፡ ነገር ግን ማንም የመሰለውን ሲናገር ደግሞ ኃላፊነት አለበት፡፡ ከሕፃናት ጀምሮ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚማሩ ወጣቶችን ጭምር ታሳቢ ማድረግ አለብን፡፡ አለበለዚያ እንዳመጣልን የማይመስል ነገር እየተናገርን ሕዝብና አገር ማታለል ጥሩ አይሆንም፡፡ እየበደለን ያለውም ነገር ይኼ ነው፡፡ አንቺ እንዳልሺው በማንም የተሰጠን ሳይሆን፣ በተፈጥሮ ያገኘነው የንግግር ነፃነታችን ኃላፊነት ይላበስ ማለት አለብን…›› እያለ ሲናገር ታክሲው ውስጥ ትንፋሽ እንኳን አይሰማም ነበር፡፡ አንዳንዱ ሰው ግን ታድሎ ይችልበታል፡፡

ከኋላ መቀመጫ ሁለት ወጣቶች በፌስቡክ ስለሚለዋወጡዋቸው ጉዳዮች ማውራት ጀመሩ፡፡ አንደኛው በቀልድ መልክ የተነገረ ጉዳይ አንስቶ ይስቃል፡፡ ጓደኛው በዝርዝር አስረዳኝ ይለዋል፡፡ ማስረዳት ጀመረ፡፡ ‹‹ተማሪዋ አስተማሪዋን ‹እናቴ ማርገዝ ትችላች?› ስትለው ‹ዕድሜዋ ስንት ነው?› ይላታል፡፡ ልጅቷም ‹40› በማለት ስትመልስ፣ ‹ትችላለች› ይላታል፡፡ ልጅቷ ‹እህቴስ?› ትለዋለች፡፡ አስተማሪም ‹ዕድሜዋ ስንት ነው?› ሲላት ‹18› ትላለች፡፡ ‹ትችላለች› ብሎ ይመልሳል፡፡ ከዚያ ‹እኔስ?› ስትል ‹ዕድሜሽ ስንት ነው?› በማለት መምህሩ ሲጠይቅ ‹12› ነኝ ማለት፡፡ መምህር ‹ፈጽሞ ማርገዝ አትችይም› ይላታል፡፡ ይኼኔ ትንሽ ራቅ ብሎ ቆሞ የነበረ አንድ ሥራ ፈት ቦዘኔ መሳይ ‹አላልኩሽም?› ምንም የሚያሳስብ ነገር የለም እኮ’ ይላታል…›› ብሎ ሲስቅ፣ ይኼንን ጉድ የሰሙ እናት አበዱ፡፡

‹‹ኧረ ፈጣሪዬ ምነው ዝም አልከን? ትውልዱ እኮ ጠፋ? ታላቅ ታናሹን የማይመክርበት ዘመን፣ ትልቁ ትንሹን የማይገስጽበት ጊዜ፣ ወላጅ ለልጅ ፈቃድ አገልጋይ የሆነበት የመዓት ዘመን፣ ውይይይ…›› ሲሉ ፀጥታው ነገሠ፡፡ አዛውንቷ ግራ ቀኙን እያማተሩ፣ ‹‹እናንተ የምፅዓት ጊዜ ደረሰ እንዴ? እንዴት ያለ ጊዜ ላይ ሆነን ነው እንዲህ ያለ አሳፋሪ ነገር ተማሪዎቻችን ጥናታቸውን ትተው የሚከታተሉት? ይኼ ‹ምን ቡክ› የምትሉት ነገር ዳኛ የለውም ወይ? ከሳሽ የለውም ወይ? ተቆጣጣሪ የለውም ወይ? ልጆቹ ላዩ ላይ ተጥደው ብልግና ሲማሩበት መንግሥት የት ነው ያለው? …›› እያሉ ዓይኖቻቸው ላይ የቆረዘዙትን የእንባ ዘለላዎች በነጠላቸው ሲያብሱ ያሳዝኑ ነበር፡፡

ወይዘሮዋ ማስቲካዋን ቀጭ እያደረገች፣ ‹‹ማዘር የድሮውና የአሁኑ ዘመን አንድ አይደለም፡፡ የዘመኑን ነገር ለዘመኑ ሰው ቢተውት እኮ እንዲህ አያንገበግብዎትም ነበር፡፡ በእርስዎ ዘመን ‹ለንጉሡ አጐንብሱ› ወይም ‹ለአምባገነኑ ተንበርከኩ› የሚባልበት ስለነበር፣ አሁን ደግሞ ማንም ሰው በነፃነት ያሻውን የመጠቀም መብት አለው…›› ብላ ስትንጣጣ አዛውንቷ ገርምመዋት ፊታቸውን ወደ ውጭ ትዕይንት መልሰው በሐሳብ ነጐዱ፡፡ ያ ቀጭን ወጣት ግን ወይዘሮዋን አሁንም አልለቀቃትም፡፡ ‹‹የእኔ እመቤት አንቺ ማርስ ላይ ነው ያለሽው? ወይስ ኢትዮጵያ? ከመቼ ወዲህ ነው ማንም ያሻውን በነፃነት ሲጠቀም ያየሽው? ነፃነት ማለት ጫት ነው? ሺሻ ነው? መጠጥ ነው? ሐሺሽ ነው? በፌስቡክ ብልግና መከታተል ነው? ሌሎች መሠረታዊ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ነፃነቶች የታሉ? ከመናገርሽ በፊት ቢያንስ ሁለቴ ብታስቢ ግራ ተጋብተሽ ግራ አታጋቢንም ነበር…›› ሲል ታክሲው ተቀወጠ፡፡

ከወጣቱ ንግግር በኋላ ታክሲው በሦስት ቡድኖች የተከፈለ መሰለ፡፡ አንደኛው ቡድን ነፃነት ኖሮ አይደለም ወይ እንደፈለግን እዚህ የምናወራው የሚል፣ ሁለተኛው ከታክሲ ሲወረድ የሌለ ነፃነት የት እንደሆነ አሳዩን የሚል፣ ሦስተኛው ደግሞ ‹ጐመን በጤና› ብሎ ፀጥ ያለ ነው፡፡ የወይዘሮዋ ደጋፊ የሆነ አንድ ጐልማሳ ከኋላ፣ ‹‹ወይዘሮዋ ያነሳችው ነጥብ በዋዛ የሚታይ አይደለም፡፡ አፋችን ተለጉሞ ለዓመታት ከኖርንበት ነፃ ወጥተን አይደለም ወይ ይኼው እንደፈለግን ስንሳደብ፣ ስንተች፣ የተሠራውን ስናጣጥል፣ ከዚያም አልፈን ተርፈን የፈለግነውን መርጠን የምንሾመው …›› በማለት ተናገረ፡፡ ከተቃራኒው ወገን ያው ቀጭን ወጣት፣ ‹‹ወንድሜ በማንኪያ እየተሰፈረ የሚሰጥህን መብት ሳይሆን፣ ተፈጥሮአዊና የማይገሰሰውን መብት ነው ማሰብ ያለብህ፡፡ ያን መብትህን ደግሞ በኃላፊነት መጠቀም ከቻልክ አገር ጤና አንተ ጤና፡፡ ከዚያ ውጪ ሽንቁር የበዛበት ነፃነት ሳይሆን መበርገግ የበዛበት ኑሮ ነው…›› ብሎ ሲመልስለት በሁለቱም ወገኖች ጉርምርምታ ተሰማ፡፡ አንደኛው ድጋፍ ሌላው ተቃውሞ፡፡ እነ ‹ጐመን በጤና› ወይ አቀርቅረዋል፣ አሊያም ስልኮቻቸው ላይ ተጠምደዋል፡፡ ወይ ጊዜ?

ወያላችን ሒሳቡን ሰብስቦ አኩርፎ ተቀምጧል፡፡ ሾፌራችን በውይይቱ ተመስጦ በዝምታ ማርሹን እየቀያየረ ይነዳል፡፡ አዛውንቷ ጥለውን በሐሳብ ከነጐዱ ቆይተዋል፡፡ ውጭ ውጩን እያዩ ይተክዛሉ፡፡ በዚህ መሀል አንደኛው ጐልማሳ፣ ‹‹ኧረ ለመሆኑ ሁሉም ቦታ እንዲህ ሐሳባችንን በሰላም ብንለዋወጥ ምን ይከፋ ነበር? አለመነጋገርና አለመደማመጥ የወለዱት በሽታ እኮ ነው የሚያናጅሰን፡፡ እኔማ እዚህ ፌስቡክ የሚባል ነገር ውስጥ ገባ ብዬ ቃኘት ቃኘት ሳደርግ በኢትዮጵያውያን ስም የሚነጋገሩት ኢትዮጵያውያን አይመስሉኝም፤›› አለ፡፡ አንዷ ወጣት ደግሞ፣ ‹‹ፌስቡክ የተፈጠረው ፈጣን መረጃ ለማግኘትና ለመስጠት ነበር፡፡ አሁንማ በሕይወት ያለ ሰው ሳይቀር ድንገት ‹ሞተ› ትባላላችሁ፡፡ በቀደም ዕለት አንድ ታዋቂ ድምፃዊ የነበረ፣ አሁን ደግሞ ሰባኪ የሆነ ሰው በፌስቡክ ገድለው ‘RIP’ ወይም ‹ነፍስህ በሰላም ትረፍ› እያሉ ሲያረዱን ደነገጥኩ፡፡ ቆይቶ ኧረ በሕይወት አለ ተባለ፡፡ እንዲያው ምን ይሻለን ይሆን?›› አለች፡፡ ይኼኔ አዛውንቷ ከነጐዱበት ሐሳብ ተመልሰው፣ ‹‹እኔማ የምፈራው በመጽሐፉ ውስጥ የተባሉት የመጨረሻው ዘመን ምልክቶች በሙሉ እዚህ አገር ውስጥ መታየት እንዳይጀምሩ ነው…›› ካሉ በኋላ ‹ወራጅ› ብለው ተሰናበቱን፡፡ አባባላቸው አስደናቂም አስገራሚም ሆነ መሰል ሁላችንም ወጋችን በዚህ ይቋጭ ዘንድ ገባንበት፡፡

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል፡፡ ታክሲያችን የቴዎድሮስ አደባባይን አቀበት በከባድ ማርሽ ሲወጣ ፊት ያለው ጐልማሳ፣ ‹‹እናታችን ያሉዋቸው ምልክቶችማ መታየት ከጀመሩ ሰነባበቱ፡፡ ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥት በመንግሥት ላይ መነሳት ከጀመሩ ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ ይኼው መካከለኛው ምሥራቅ እርስ በርስ ይጨራረሳሉ፡፡ በአሜሪካ የጥቁሮች አመፅ ተፋፍሟል፡፡ ሌላው ቀርቶ ኢትዮጵያውያን አይሁዶች በእስራኤል በደረሰባቸው የዘረኘነት ጥቃት ምክንያት እሪ እያሉ ነው፡፡ አይኤስ የተባለ አረመኔ ወገኖቻችንን ጨምሮ እየፈጀ ነው፡፡ በየቦታው የሚሰማው ወሬ ሁሉ ያሸብራል፡፡ አሁን ግን ሳስበው ችግሩ የእኛ አገር ብቻ ሳይሆን የዓለም ነው፡፡ ዓለም ወዴት እየገሰገሰች እንደሆነች አልታወቅ ብሏል፡፡ መንግሥታት ጠባቸውና ፍቅራቸው ለስንት ጊዜ እንደሚቆይ አይታወቅም፡፡ ሌላው ቀርቶ ድሮ በአገራችን መንግሥት እንደ አባት ይታይ ነበር፡፡ ዛሬስ? ልክ እንደ ጠላት…›› እያለ ሳለ ወያላው ‹መጨረሻ› ሲል ተንጋግተን ወረድን፡፡ አጠገቤ ተቀምጦ የነበረው፣ ‹‹አባትም እንደ ጠላት የሚታይበት ጊዜ ላይ ደረስን?›› ሲል ቀጭኑ ወጣት ጣልቃ ገብቶ፣ ‹‹ወዳጅና ጠላት ሲደባለቁ ምን ይደረግ ታዲያ? ይኼ እኮ በአገር ብቻ ሳይሆን ቤተሰብ ድረስ ወርዷል፤›› ብሎን እብስ አለ፡፡ ወዳጅና ጠላት አትደባልቁ የሚል መካሪ ጠፋ? ወይስ ችግር አለ? መልካም ጉዞ!   

              

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት