Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ‹‹ሚያዝያ 27 የድላችን ቀን …››

‹‹ሚያዝያ 27 የድላችን ቀን …››

ቀን:

በባሕር ማዶ በስደት ሳለ ሕይወቱ ያለፈው ድምፃዊ ተስፋዬ ገብሬ፣ ኢትዮጵያና አርበኞቿ የአምስቱን ዓመት የፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ (1928 – 1933) በድል አድራጊነት የተወጡበትን ታሪክ በዘፈኑ፡-

‹‹መጋቢት 28 የድላችን ቀን

ይከበር ዘላለም በሀገራችን፣

መጋቢት 28 በያመቱ ይምጣ

የናንተ መሣሪያ ጦር ጋሻው ይምጣ›› እያለ አቀንቅኖት ነበር፡፡

በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ከ1934 ዓ.ም. እስከ 1966 ዓ.ም. ድረስ የድሉ በዓል ይከበር የነበረው ሚያዝያ 27 ቀን ሲሆን፣ ከደርግ መንግሥት መምጣት በኋላ በዓሉን ወደ መጋቢት 28 ለውጦት ከወደቀም በኋላ እስከ 1987 ዓ.ም. ሲከበር ኖሯል፡፡

ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ በወጣ በአምስተኛ ዓመቱ በነባር አርበኞቹና በኅብረተሰቡ ጥያቄ፣ በታሪክ ምሁራንም አረጋጋጭነት በዓሉ በ1988 ዓ.ም. ወደ መሠረታዊ ቀኑ ሚያዝያ 27 ቀን  ተመልሶ በመከበር ላይ ይገኛል፡፡

ፋሺስት ኢጣሊያ አዲስ አበባን በያዘበት ሚያዝያ 27 ቀን (1928 ዓ.ም.) በሕዝቡና በአርበኞች ተጋድሎ የኢትዮጵያ የድልን ቀን ሚያዝያ 27 ቀን (1933 ዓ.ም.) ተበሰረ፡፡ 74ኛ ዓመቱንም ማክሰኞ ሚያዝያ 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ተዘከረ፡፡

ዘውዴ ረታ ‹‹የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት›› በሚለው መጽሐፋቸው ስለ ታሪካዊቷ ሚያዝያ 27 እንዲህ ጽፈዋል፡፡

‹‹ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም. ደግሞ ንጉሠ ነገሥቱ በከፍተኛ አጀብ እኩለ ቀን ስድስት ሰዓት ላይ ከታላቁ የዳግማዊ ምኒልክ ቤተ መንግሥት አደባባይ ላይ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን ሰንደቅ ዓላማችንን መልሰው ሰቀሉት፡፡ የክብር ዘብ ተሰልፎ፣ በራስ አበበ አረጋይ የሚመራው አሥር ሺህ አርበኞች ያሉት ጦር ዙሪያውን በሀገር ፍቅርና በብሔራዊ ስሜት እንደቆፈጠነ፣ በሱዳን በኩል የመጣውና በሻለቃ ዊንጌት የሚመራው የጌዲዮን ጦርም ተሰልፎ፣ መድፍ ተደጋግሞ እየተተኮሰ ሰንደቃችን በክብር ከፍ አለ፡፡››

ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ከስደት መልስ መናገሻ ከተማቸው ሚያዝያ 27 ቀን ገብተው የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከማውለብለባቸው አራት ወር ግድም በፊት ጥር 12 ቀን ሱዳን ድንበርን ተሻገረው ኢትዮጵያ ገብተው ያውለበለቡት ኦሜድላ ላይ ነበር፡፡

ከሰባት አሠርታት በፊት የድሉን ብሥራት አስመልክተው ባለቅኔው የእንጦጦ ራጉኤሉ አምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ፡-

‹‹ኢትዮጵያ ከማር ለሚጣፍጥ ለስምሽ አጠራር ሰላም ይገባል፡፡

ባምላክ እጅ ለተሠራ ለራስ ፀጉርሽም ሰላምታ ይገባል፡፡

ምሳሌ የሌለሽ መቅደስ ኢትዮጵያ ጠላት ኢጣሊያ ስላረከሰሽና መሠዊያሽን ስላጠፋ ፈንታ ከእንግዲህ ወዲህ ተቀደሽ፣ ኃይልንም ገንዘብ አድርጊ›› ብለው ተቀኝተውላት ነበር፡፡

‹‹እናታችን ኢትዮጵያ ሆይ ለታረዙ ልብስ ነሽና በባንዲራሽ ጥላ ሰብስቢ ልጆችሽን›› እያሉም ዘመሩላት፡፡

አንድ ጸሐፊ አምና በዚህ ወቅት በአንድ መድረክ እንደተናገረው፣ ድምፃዊው ተስፋዬ ገብሬ በሕይወት ቢኖርና ለውጡን አይቶ ቢሆን ኖሮ ዘፈኑን ሪሚክስ አድርጎ ‹‹ሚያዝያ 27 የድላችን ቀን…›› ብሎ በዘፈነ ነበር፡፡

የመከራው አንድ ጥግ

ከሰባ ዘጠኝ ዓመታት በፊት የተፈጸመው የፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ በኢትዮጵያ ላይ ብዙ መከራዎችን ትቶ ማለፉ አይዘነጋም፡፡ እርመኛ አርበኞች የአገሪቱን ነፃነት ለማስከበር የሕዝቡን ልዕልና ለማስጠበቅ ያደረጉት ተጋድሎ የትየለሌ ነው፡፡

ኢጣሊያ በዓድዋ ላይ የደረሰበትን ሽንፈት ለመበቀል ከ40 ዓመት ቆይታ በኋላ በፋሺስታዊ መንግሥቷ አማካይነት በአምስቱ ዘመን (1928 – 1933) የሠራችው ግፍ ተነግሮ አያልቅም፡፡ ወረራውን በፈጸመች ባመቱ በየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. በአዲስ አበባና በአካባቢው ከፈጸመችው ግፍ አንስቶ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢው ብዙ ጥፋትን አድርሳለች፡፡

ከእነዚህም መካከል የመጀመሪያው የፋሺስት ወንጀለኞች የኢትዮጵያን ሠራዊት የፈቱበት በተምቤንና በሐሸንጌ በመርዝ ጋዘ ያደረሱት እልቂት ይጠቀሳል፡፡

‹‹Trying Times›› (ትራዪንግ ታይምስ) በተሰኘው መጽሐፋቸው አቶ ጥላሁን ጣሰው እንደጻፉት፣ ፋሺስት ኢጣሊያ በ1928 ዓ.ም. ኢትዮጵያን የወረረችው፣ በቅኝ በያዘቻቸው በሰሜን በኤርትራ በኩልና በደቡብ ምሥራቅ በኢጣሊያን ሶማሊላንድ በኩል በ400,000  ወታደሮች፣ በ300 የጦር አውሮፕላኖች፣ በ30,000 ተሽከርካሪዎችና በ400 ታንኮች አማካይነት ነበር፡፡ ሙሶሎኒ በወቅቱ የደረሰበትን ሽንፈት ለመቋቋምና ለመቀልበስ የወሰደው እርምጃ ሠራዊቱ በመርዝ ጋዝ እንዲጠቀም ማዘዙ ነው፡፡
የታኅሣሥ 18 ቀን 1928 ዓ.ም. የሙሶሎኒ ትዕዛዝ በተምቤንና በሐሸንጌ ሐይቅ ለሺዎቹ እልቂት ሰበብ ሆኗል፡፡

‹‹በተምቤን ጦርነት ጊዜ ኢትዮጵያውያን ዘመናዊ ባልሆኑ መሣርያዎች ድል አድርገዋል፡፡ የኢትዮጵያ ጦር ድል በማድረጉ ፋሺስት የኬሚካል ጥቃቱን ፈጸመ፡፡ በዚያን ጊዜ ያለቁት 700,000 የሚደርሱ ናቸው፡፡››

አቶ ጥላሁን፣ በተምቤን ጦር ግንባር አዛዥ የነበሩት ራስ ካሳ በመጽሐፋቸው የገለጹትን፣ ከፈረንሣይኛ ተተርጉሞ ያገኙትን አውስተዋል፡፡

‹‹የተምቤን ጦርነት ጊዜ አሸነፍን፤ ዋናው ነገር [ኢጣሊያ] ሩቅ የሚመታ መሣርያ አላቸው፤ እኛ በቅርብ ሆነን ማጥቃት እንችላለን፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ ተዝናንተን ሳለን አንድ ቀን የእነርሱ አውሮፕላኖች ቢመጡ እንፈትሻቸዋለን ስንል በጣም ከርቀት ሆነው አውሮፕላኖቹ ለእርሻ አረም ማጥፊያ በሚሆን መርጪያ ማድረግ ይጀምራሉ፡፡ ጥይት የሚደርስበት አይደለም፡፡ ዝም ብሎ ይወርዳል ኬሚካል ሰልፈር (ድኝ) አለው፡፡ መስተርድ ጋዝና ተቀጣጣይ ፈንጂዎችን ጣሉ፡፡ ሰውም መቃጠል አገርም በሙሉ መቃጠል ጀመረ፡፡ ዋሻው ውስጥም ሆኖ መቋቋም አይቻልም ሰው ሁሉ አለቀ፡፡ አንድም ጣሊያን ከዚያ በኋላ አልሞተም፡፡››

የውጭ አገር ታሪክ ጸሐፊዎች በተለይ የፋሺስት ደጋፊ የሆኑት፣ በተምቤን ስለተካሔደው ጦርነት ‹‹የመጀመርያው የተምቤን ጦርነት››፤ ‹‹ሁለተኛው የተምቤን ጦርነት›› በማለት ታሪኩን ያዛባሉ፡፡

‹‹የመጀመርያው የተምቤን ጦርነት የሚሉት ኢትዮጵያውያኑ የተወሰነ ድል አገኙ፡፡ ሁለተኛው የተምቤን ጦርነት ላይ ግን በራስ ካሳና ራስ እምሩ  ራስ ሥዩም የሚመራውን ጦር አሸነፉት ይላሉ፡፡›› አቶ ጥላሁን እነዚያን ጸሐፍት ከመሞገት አልተመለሱም፡፡

‹‹ሁለተኛ የተምቤን ጦርነት የሚባል ነገር አይኖርም፡፡ ሒሮሺማና ናጋሳኪ ላይ የአቶሚክ ቦንብ በመውደቁ የሒሮሺማና የናጋሳኪ ጦርነት የሚባል ነገር እንደሌለ ሁሉ አንድም ሰው በውጊያ ባልሞተበት በአውሮፕላን በተረጨ መርዝና ከሰልፈር (ድኝ) እና በተቀጣጣይ ፈንጂ በተደበላለቀ ያ ሁሉ ማለቁን ያወጉናል፡፡

በሐሸንጌ ሐይቅ ስለደረሰው እልቂት የራስ ካሳ እይታንም ደራሲው አስታውሰዋል፡፡ ‹‹ሁሉም የቀይ መስቀል ፈረንጆች ሠራተኞች ከተመለሱ በኋላ በሐሸንጌ ሐይቅ ሜዳ ላይ የሔዱት ሰዎች ሐይቁ ከተመረዘ በኋላ በሙሉ ያልቃሉ፡፡››

ይህ ዘግናኝ ክሥተት በውጭ አገር ታሪክ ጸሐፊዎች ሲቀርብ የተገለጸው ‹‹የንጉሠ ነገሥቱ ጦር መሸነፉን በሐሸንጌ ሐይቅ ውስጥ በሞላው ሬሳ አወቅነው፤›› ተብሎ ነው፡፡

የዚያን ጊዜ ያለቁት ከወንድሞቻቸው ጋር ወደ ጦር ሜዳ የሔዱ በአብዛኛው ሴቶች፣ ሲቪልና ጥቂት ቁስለኞች መሆናቸውን ያመለከቱት አቶ ጥላሁን፣ አጽንዖት የሰጡበት ነገርም አለ፡፡

 ‹‹እኛ አዲስ አበባ ውስጥ ስለተደረገውና ጥቂት ሺሕ ሰዎች ስላለቁበት እናስባለን፡፡ ያኛው በገጠር የተከናወነው ግን እየተረሳ ይሔዳል፡፡ ከተሞች ውስጥ የሚሞተው ሁልጊዜ ይታወሳል፡፡ ገጠሮች ላይ የሚሞተው ይጠፋል፡፡››

አንድ ደራሲ እንደከተበው፣

‹‹…ቢነገር ቢወራ ቢተረክ ቢጻፍ

      ፍጻሜ የለውም የፋሺስቶች ግፍ››፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...