Saturday, December 3, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ኪንና ባህልኢትዮጵያዊነት በካንስ ፊልም ፌስቲቫል

  ኢትዮጵያዊነት በካንስ ፊልም ፌስቲቫል

  ቀን:

  ‹‹ላምብ›› (የበግ ግልገል) ኤፍሬም የተባለ የዘጠኝ ዓመት ኢትዮጵያዊ ታሪክ የሚያስቃኝ ፈልም ነው፡፡ ኤፍሬም ‹‹ጩኒ›› ከተባለች ግልገል በግ ጋር ያለውን ትስስር ታዳጊው በገጠሪቷ ኢትዮጵያ ስለሚገጥመው ፈታኝ ጊዜ የሚያሳየው ይህ ፊልም፣ በ68ኛው ካንስ ፊልም ፌስቲቫል ላይ ለዕይታ ከሚበቁ ፊልሞች አንዱ ለመሆን ችሏል፡፡ ፊልሙ በኢትዮጵያ ሲኒማ ታሪክ በፌስቲቫሉ ሲካተት የመጀመርያው ነው፡፡

  እናቱን በድርቅ የተነጠቀው ኤፍሬም፣ ለግልገሏ ፍቅር ያድርበታል፡፡ አባቱ ኤፍሬምና ግልገሏን በድርቅ ከተጠቃው አካባቢ እንዲርቁ ይወስዳቸዋል፡፡ ከዘመዶች ጋር መኖር ግድ ይሆናል፡፡ ታዳጊው ለዓውደ ዓመት በጉን ለማረድ አጎቱ መወሰኑን ይሰማል፡፡ ጩኒን ለማዳንና ወደ ትውልድ ቀዬው ለመመለስ የሚያደርገውን ውጣ ውረድ ፊልሙ ያስቃኛል፡፡ ‹‹ላምብ›› የተዘጋጀው በያሬድ ዘለቀ ሲሆን፣ በካንስ ፊልም ፌስቲቫል ከሚቀርቡ 15 ዓለም አቀፍ ፊልሞች አንዱ ነው፡፡

  የፊልሙ አዘጋጅ ያሬድ ከማንሀተን ዳይጀስት ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ‹‹በኢትዮጵያ የ3,000 ዓመት ታሪክ ውስጥ አስከፊ በነበረው ወቅት በአዲስ አበባ ጎስቋሏ መንደሮች እኖር ነበር፤›› ሲል ተናግሯል፡፡

  ‹‹ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በወታደራዊ አገዛዝ ከተገለበጡ በኋላ በተደጋጋሚ በሚነሳ ጦርነትና ረሀብ አገሪቱ ትናጥ ነበር፡፡ ይህ አለመረጋጋት ቤተሰቤንና ቤቴን ገና ልጅ ሳለሁ ነጥቆኛል፤›› ይላል ያሬድ በቃለ ምልልሱ ላይ ስለፊልሞቹ መነሻ ሲናገር፡፡

  ያሬድ በከተማዋ ምስቅልቅል ቢኖርም ልጅነቱን ደስተኛ ሆኖ እንዳሳለፈ ይናገራል፡፡ የመጀመርያ ፊቸር ፊልሙ የሆነው ‹‹ላምብ›› ከሕይወቱ ጋር መነፃፀር  እንደሚችል ይገልጻል፡፡ ‹‹ፊልሙ ለእኔ የተለየ ቦታ የሚሰጠውና ያለጥርጥር ፖለቲካዊ ዐውድ ያለው ነው፤›› ሲል ስለ ፊልሙ ያስረዳል፡፡ በከፊል ግለ ታሪኩን የሚነካው ፊልሙ፣ በኢትዮጵያውያን የዕለት ከዕለት ኑሮ ያለውን ልብ የሚሰብር እንዲሁም አስደሳች ሁኔታ ነፀብራቅን ድባብ እንደሚያሳይ ይናገራል፡፡

  ያሬድ የኒዮርኩ ዩኒቨርሲቲ ቲስች ስኩል ኦፍ ፋይን አርትስ ምሩቅ ነው፡፡ ከ‹‹ላምብ›› በፊት አጫጭር ዘጋቢ ፊልሞችን በመጻፍ፣ በማዘጋጀት፣ በአርትኦትና ፕሮዲውስ በማድረግ ተሳትፏል፡፡ ‹‹አሉላ›› እና ‹‹ሎተሪ ቦይ›› ከፊልሞቹ ይጠቀሳሉ፡፡

  ‹‹ዘ ፊውሪየስ ፎርስ ኦፍ ራይምስ›› ከጆሽዋ ሊትል ጋር የሠራው ዘጋቢ ፊልም ሲሆን፣ ጆሽዋ ሽልማት አግኝቶበታል፡፡›› እ.ኤ.አ. በ2009 የሠራቸው ‹‹ዘ ኳይት ጋርደን››ና ‹‹ሐውስ ዋርሚንግ››ም ተጠቃሽ ሥራዎቹ ናቸው፡፡

  ያሬድ ኖርዌይ፣ ናሚቢያና አሜሪካ ከሚገኙ የተራድኦ ድርጅቶች ጋር ሠርቷል፡፡ በቃለ መጠይቁ ከተነሳለት ጥያቄ አንዱ ፊልም መሥሪያ በጀት ለማግኘት አስቸጋሪ በመሆኑ ገንዘብ እንዴት እንደሚያሰባስብ ነበር፡፡ ለሥራዎቹ ከበርካታ የአውሮፓ አገሮች  ፈንድ እንዳገኘ ተናግሯል፡፡

  ‹‹ጠንካራ ሴቶች አሳድገውኛል፤›› የሚለው ያሬድ በሚሠራቸው ፊልሞች ውስጥ ለሴቶች ቁልፍ ሚና የሚሰጣቸው ለዚሁ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ በተለይም በቅርበት ያሳደጉት ሴት አያቱ ይነግሩት የነበረውን ታሪኮች ያስታውሳል፡፡

   በአፍሪካውያን ዘንድ ታዋቂውን አባባል ‹‹ኢት ቴክስ ኤ ቪሌጅ ቱ ሬይዝ ኤ ቻይልድ›› (ልጅን ማሳደግ የመንደርን ትብብር ሁሉ ይጠይቃል) ያሬድ ይጠቅሳል፡፡

  ባደገበት አካባቢ ማኅበረሰቡ በኅብረት ልጆችን እንደሚያሳድግ ይገልጻል፡፡ ‹‹ከደርግ ሥርዓት አስከፊ ነገሮች ወደ ትምህርት ቤት፣ ቤተክርስቲያንና ሲኒማ እየላኩ የተከላከሉን የአካባቢያችን አዛንቶች ናቸው፤›› ይላል፡፡ አስተዳደጉ፣ የአብሮ አደጎቹ ባህሪ፣ የአካባቢው ተፈጥሯዊ አቀማመጥ፣ ባህላዊ ሥርዓቱና ሌሎችም ትውስታዎቹ የጽሑፎቹ መሠረት እንደሆኑ ይገልጻል፡፡

  በፈረንሳዩ ካንስ ፊልም ፌስቲቫል ውዲ አለንና ጋስፐር ኖይን ጨምሮ የሌሎችም የፊልም ባለሙያዎች ሥራዎች ከግንቦት 5 እስከ 16፣ 2007 ዓ.ም. ይቀርባሉ፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...