አቶ ሚካኤል ዐምደሚካኤል፣ የደደቢት እግር ኳስ ክለብ የቴክኒክ ዳይሬክተር
ዋሊያዎቹ ከአፍሪካ ዋንጫ ጋር ዳግም ለማገናኘት እንዲያስችሉ ፖርቱጋላዊው ማሪያኖ ባሬቶን የቀጠረው ብሔራዊ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሕልሙ ሳይሳካለት በመቅረቱ አሠልጣኙን ዓመት እንኳ ሳይሠሩ አሰናብቷቸዋል፡፡
ባሬቶ ብሔራዊ ቡድኑን ለዘጠኝ ወራት ሲይዙ ካደረጓቸው ለ2015 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያና የመላው አፍሪካ ጨዋታ አንድን ጨዋታ ከማሸነፍ በቀር በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ተደጋጋሚ ሽንፈትን አስተናግደዋል፡፡
ይህን የሽንፈት ክስተት የተረዳው ብሔራዊ ፌዴሬሽን አሠልጣኙን ለማሰናበት አላቅማማም፡፡ ከሚመለከታቸው የቴክኒክ ክፍል በቀረበለት ሪፖርት መሠረት ከአሠልጣኝ ባሬቶ ጋር የነበረውን ውል አቋርጧል፡፡
ሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ አዲስ አሠልጣኝ ለመቅጠር ባደረገው እንቅስቃሴም ከአገር ውስጥ አሠልጣኞች መካከል የተሻሉ ናቸው ያላቸውን የደደቢት እግር ኳስ ቡድን አሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌን የመረጠ ሲሆን ሰኞ ቡድኑን አስረክቧቸዋል፡፡
አዲሱ አሠልጣኝ የቆይታቸው ጊዜ የሚወሰነው በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያና በቻን ውድድሮች በሚያስመዘግቡት ውጤት መሠረት መሆኑን ፌዴሬሽኑ ይፋ አድርጓል፡፡ የአሠልጣኝ ዮሐንስ ወርኃዊ ደሞዝ 75,000 ብር እና ልዩ ልዩ ጥቅማ ጥቅሞችን ያካትታል፡፡
የዘንድሮው የፕሪሚየር ሊግ ውድድር ሊያበቃ አምስት ጨዋታዎች ሲቀረው ከደደቢት የተለየው አሠልጣኝ ዮሐንስ፣ ክለቡ በክብር አሸኛኘት አድርጎለታል፡፡ ከትናንት በስቲያ (ሚያዚያ 26) በደሳለኝ ሆቴል በተደረገው የአሸኛኘት ሥነ ሥርዓት ላይ የክለቡ የቴክኒክ ዳይሬክተር አቶ ሚካኤል ዐምደሚካኤል፣ የአሠልጣኝ ዮሐንስ የደደቢት ቆይታ አወድሰዋል፡፡
አሠልጣኙ ክለቡን ሲቀላቀሉ ከጥቅማጥቅም ይልቅ ያስቀደሙት የሥራ ነፃነትን መሆኑን ያስታወሱት ዳይሬክተሩ፣ ጥያቄያቸው በመቀበላቸው ክለቡ ከነበረበት ተደጋጋሚ ሽንፈትና ዝቅተኛ ደረጃ ቀድሞ ወደ ነበረበት ግርማ ሞገሱ ማስመለሳቸው፣ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው ሦስተኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡
‹‹አሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ጋር መሥራት ትምህርት ቤት የመግባት ያህል ነው፤›› በማለት የገለጹት ዳይሬክተሩ ክለቡ አሠልጣኝ ዮሐንስን ማጣቱ እጅግ እንደሚጎዳው ብናውቅም አገራዊ ጥሪ በመሆኑ በደስታ ልንሸኘው ተገደናል ብለዋል፡፡
አሠልጣኝ ዮሐንስ በበኩላቸው፣ ስለደደቢት ቆይታቸው ሲናገሩ፣ የሚፈልጉትንና የሚያምኑበትን የሥራ ነፃነት ማግኘታቸው ለክለቡ ውጤታማነት በር መክፈቱን አውስተዋል፡፡ በዚህም ከተስፋ ቡድን በርካታ ተጫዋቾች በማብቃት ከዋናው ቡድን ጋር አብረው እንዲሠሩ ከማድረጋቸውም በላይ በፕሪሚየር ሊጉ ክለቡ ላስመዘገበው ተከታታይ ድል ወጣቶቹ ባለድርሻ እንደነበሩም ተናግረዋል፡፡
በደደቢት ለወጣቶች የሰጡትን ትኩረት በብሔራዊ ቡድን ውስጥም እንደሚቆጥሉም ሳይናገሩ አላለፉም፡፡ ደደቢት ቀሪውን የውድድር ጊዜ በምክትል አሠልጣኙ ዳንኤል ፀሐዬ እየተመራ እንደሚቀጥልም ተነግሯል፡፡
በሌላ በኩል በአሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የሚዘጋጀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያው ማጣሪያ ጨዋታ ሰኔ 7 ቀን 2007 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስታዲየም ከሌሴቶ አቻው ጋር ይጫወታል፡፡ ከሳምንት በኋላ ደግሞ ለቻን ማጣሪያ ከኬንያ ብሔራዊ ቡድን ጋር በአዲስ አበባ ስታዲየም እንደሚቀጥል የወጣው የውድድር ፕሮግራም ያስረዳል፡፡
ከቻን ማጣሪያ በኋላ በጳጉሜን መጀመርያ ከሜዳው ውጪ ከሲሸልስ ጋር የሚጫወት ሲሆን፣ ለ2018 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ምድብ ድልድል በጥቅምት 2008 ይፋ እንደሚደረግ፣ የማጣሪያዎቹ ጨዋታዎችም እንደሚቀጥሉ ነው የታወቀው፡፡ ለአሠልጣኝ ዮሐንስ ጠንካራ ተፎካካሪ እንደሚሆን የሚጠብቀው የአልጄሪያ ቡድን ሲሆን፣ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ደግሞ በመጋቢት ወር 2008 ዓ.ም. እንደሚከናወን ከብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የወጣው መረጃ ያሳያል፡፡