Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየነፃነት ዋጋ ስንት ነው?

የነፃነት ዋጋ ስንት ነው?

ቀን:

ከሁለት ዓመታት በፊት ለጥናት አዋሬ ሲግናል እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘውን የዓድዋ ዘመቻ መታሰቢያ ድልድይን መነሻ በማድረግ፣ በየዓመቱ የካቲት 23 ቀን ስለሚከበረው የዓድዋ ድል በዓል ለተለያዩ ሰዎች ጥያቄ ሲያቀርቡ ያገኟቸው መልሶች በርካታው ሰው ስለበዓሉ መሠረታዊ የሚባል ነገር እንኳ እንደማያውቅ የሚመሰክሩ ነበሩ፡፡

ድልድዩ በዓድዋ የተሰየመው እዚያ ቦታ ላይ ጦርነቱ በመደረጉ እንደሆነ መልስ የሰጡም ብዙ እንደነበሩ ከጉዞ ዓድዋ አዘጋጆች አንዱ የሆነው አቶ መሐመድ ካሳ ያስታውሳል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ብዙዎች ስድስት ኪሎ አደባባይ ስለቆመው የየካቲት 12 የሰማዕታት ሐውልት እንዲሁም አራት ኪሎ (የሚያዝያ 27 አደባባይ) የሚገኘው ድል ሐውልት ብዙዎች እንደማያውቁ በተለያየ ጊዜ ብዙ ተብሏል፡፡

በዓላቱ በሚከበርባቸው ቀናት የአከባበሩ ሥነ ሥርዓት ከሚካሔድበት ቦታ ላይ የሚገኙ ሰዎች ቁጥር፣ በመገናኛ ብዙኃን የሚሰጠው ሽፋን፣ የበዓሉ ሥነ ሥርዓትን በተመለከተ የሚካሔዱ ዝግጅቶችንና ሌሎች ነገሮችን በመመልከት እነዚህ በዓላት ከአገር ሉዓላዊነት ከዜጐች ነፃነት ጋር የተገናኙ ከመሆናቸው አንፃር በመንግሥት፣ በተለያዩ ተቋማት፣ በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በጥቅሉ በኅብረተሰቡ የተቸረውን ትኩረት በማስተዋል የነፃነት ዋጋ ምን ያህል ነው? ለበዓላቱ የሚገባቸው ዋጋ ተሰጥቷቸዋል ወይ? የሚል ጥያቄ የሚያነሱ ብዙዎች ናቸው፡፡

‹‹ብዙ ሰው በትክክል እነዚህ ቀናት የማንና ምን እንደሆነ አያውቅም›› የሚሉት ፀሐፌ ተውኔትና ገጣሚ አያልነህ ሙላት በተለይም እንደ የካቲት 12 የሰማዕታት ቀን ታስበው የማይውሉት የድል ቀንና የዓድዋ በዓል ከእውነተኛ ምንነትና የማንነት አንድምታቸው የዕረፍት ቀንነታቸው ለብዙ ሰው ትርጉም ይሰጣል ሲሉ ይገልጻሉ፡፡

እሳቸው እንደሚሉት መገናኛ ብዙኃን በዓሉ የዚህ ነው እንደዚህ ነው ብለው የሚያቀርቡት ነገር፣ የመንግሥትም ቀኑ ታስቦ እንዲውል ወይም በተወሰነ መልኩ እንዲያልፍ ማድረግ ዋጋ ቢስ ነው፡፡ ይህ ለድል በዓላቱ፣ ለነፃነት ለተከፈለው ዋጋም ክብር መስጠት ተደርጐ ሊታይ አይችልም፡፡ ይልቁንም የእነዚህ በዓላት ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊ አንድምታ እንዲታይ እንዲታወቅ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በተጨባጭ ሕዝቡ ወደ በዓላቱ የሚሳብባቸውን ተግባራት ተፈጻሚ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

በዓሉን በአንድ ቦታ ላይ ብቻ ከመወሰን በተለያዩ ቦታዎች በተለያየ መንገድ በስፋት እንዲከበር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በአደባባዮች፣ በሕዝብ መናፈሻዎች፣ በቴአትርና ኪነጥበብ ማዕከላት ዝግጅቶች ሊካሄዱ ወታደራዊ ሰልፍና ማርሽም ሊኖር ይገባል ይላሉ፡፡

በዓላቱን ለማክበር ያህል ሳይሆን ሕዝቡ እንዲማርበትና እንዲያውቀው ሕይወት ያለው እንዲሆን ያስፈልጋል የሚሉት አያልነህ ወጣቱ ትውልድ በሚገባ ማወቅና በእነዚያ ታሪካዊ ክስተት ስላለፉ ኢትዮጵያውያን ሕይወትና ምልከታም ማወቅ ይገባቸዋል የሚል እምነት አላቸው፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አንትሮፖሎጂ ዲፓርትመንት መምህር የሆኑት አቶ ወርቁ ደራራም በብዙ መልኩ የአቶ አያልነህን ሐሳብ ይጋራሉ፡፡ በመጀመሪያ በዓላቱ የሚገባቸውን ያህል ዋጋ እንዳልተሰጣቸው ይናገራሉ፡፡ ከበዓላቱ ጋር በተያያዘ እየተሠራ ያለው ነገርም በቂ ነው ብለው አያስቡም፡፡

ዓድዋ የኢትዮጵያውያን ብቻም ሳይሆን በቅኝ ግዛት ሥር ለነበሩ የአፍሪካ አገሮች ሁሉ የነፃነት ሰንደቅ ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ ሁሉ ብዙ ብለዋል፡፡ ነገር ግን ዓድዋ የመላ የአፍሪካ በዓል ነው ቢባልም በተቃራኒው አገር አቀፍ በዓል እንዲሆን እንኳ የተሠራ ነገር አለመኖሩ ላይ ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ እሳቸውም በውስን የሚዲያ ዝግጅቶችና ጥናታዊ ጽሑፎች በሚቀርብባቸው መድረኮች ከመወሰን በዘለለ ትልቅ አገራዊ ፌስቲቫል ሊሆን ይገባል የሚል እምነት አላቸው፡፡ የሙዚቃ ማርሽ ወታደራዊ ፓራድም ያስፈልጋል ይላሉ፡፡

‹‹ስለበዓላቱ ብዙ የተጻፈ ነገር ቢኖርም ሁሉ ሰው ታሪክ አያነብም›› የሚሉት አቶ ወርቁ፣ የበዓላቱ ፋይዳ ከተለያየ አቅጣጫ መነገርና እንዲታወቅ መደረግ አለበት ይላሉ፡፡ ስለ ዓድዋ አሁን የሚታየው ነገር በቂ አለመሆኑን ለማሳየት በኪነ ጥበብ በኩል እንኳ ይህ ነው የሚባል ሥራ አለመሠራቱን የሚጠቅሱት አቶ ወርቁ፣ የአፍሪካ በዓል ለሆነው ለዓድዋ እንኳ ቦታው ላይ ምንም ዓይነት መታሰቢያ አለመኖሩ ለድል፣ ለነፃነት ትግልና ለሰማዕታት የተሰጠውን ዋጋ ያንፀባርቃል የሚል አስተያየት አላቸው፡፡ ማክሰኞ ሚያዝያ 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ሥራዬ ብለው ባይሆንም በአጋጣሚ ከአራት ኪሎው ሚያዝያ 27 አደባባይ ተገኝተው ያስተዋሉት የድል በዓል አከባበርም ይህንኑ አመለካከት የሚያጠናክር ነበር፡፡ ‹‹የተወሰኑ እየተንጠባጠቡ ሰዎች ቦታው ላይ ነበሩ፡፡ ዝግጅቱም እንደዚያው የተወሰነ፡፡ ከአርበኞች ትምህርት ቤት የመጡ ሕፃናት ዜማ ያቀርቡ ነበር፡፡ ያየሁት በጣም ትንሽ ሰው ነበር፤›› በማለት በዕለቱ ቦታው ላይ የነበረውን ነገር ይገልጻሉ፡፡   

ዓድዋም፣ የድል በዓልምና የሰማዕታት ቀን በመንግሥትም ሆነ በአጠቃላይ በኅብረተሰቡ የሚገባቸውን ያህል ዋጋ እንዳልተሰጣቸው የሚናገረውና ዓምና የተጀመረው ጉዞ ዓድዋ አዘጋጅ ከሆኑት አንዱ የሆነው አቶ መሐመድ ካሳ፣ ለታሪክ ለባህላችንም ሩቅ የሆኑ እንደ ቫለንታይን ደይ (የፍቅረኞች ቀን) ዓይነት የውጭ ባህሎች ቀስ በቀስ በኅብረተሰቡ ዘንድ ቦታ እያገኙና በሰዎች ዘንድ ተቀባይነትን እያገኙ መሆኑን በመጥቀስ ያነጻጽራል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ሕንፃዎች ቀይ ቀለም ባላቸው የተለያዩ ነገሮች መድመቅ፣ መንገድ፣ መዝናኛ ቦታዎች ላይ ቀይ የለበሱ መታየት፣ የቫለንታይን ዴይ የተለያዩ ዝግጅቶችና የአበባ ገበያን በማንሳት በዓድዋ ወይም በድል በዓል ከተማው ላይ የሚታይ ይህ ነው የሚባል ነገር አለመኖሩን፣ የዓድዋ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች ስለ ዓድዋ ፀጥ ረጭ የሚሉ መሆናቸውን ይናገራል፡፡

ለዚህ ተጠያቂ የሚያደርገው የአርበኞች ማኅበርን፣ መንግሥትንና መገናኛ ብዙኃንን ነው፡፡ ከመንግሥት ተቋማት ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ኢትዮ ቴሌኮምንም ይጠቅሳል፡፡ ‹‹ለድል በዓል ቴሌ መልዕክት ሊልክልን ይገባ ነበር›› ይላል፡፡ የካቲት 11 ቀን 2007 ዓ.ም. የተከበረውን የህወሓት አርባኛ ዓመት በዓልን በማስመልከት ቀደም ብሎ መልዕክት ሲልክ የነበረው ኢትዮ ቴሌኮም፣ ለየካቲት 23ቱ የዓድዋ በዓል መልዕክት አለመላክ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ብዙዎች ቅሬታቸውን እንዲገልጹ ያደረገ ጉዳይ ነበር፡፡ ዘግይቶም (በዕለቱ ወደ ምሽት 11 ሰዓት ገደማ) ቢሆን የኢትዮ ቴሌኮም መልዕክቶች ለተጠቃሚው ደርሷል፡፡ ይህም ቢሆን ግን የማኅበራዊ ድረ ገፆች ላይ ኢትዮ ቴሌኮም ላይ ይሠነዘሩ የነበሩ አስተያየቶችን አላለሳለሰም፡፡

ለቴአትር ሥራ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴአትር ተማሪዎችን መርጦ ስለዓድዋ ቴአትር ለማሠራት በሞከረበት አጋጣሚ የተሻለ ያነባሉ የሚባሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች እንኳን ስለዓድዋ እንደ ብዙኃን እንደማያውቁ ተረድቷል፡፡ እንደ አቶ ወርቁ ሁሉ በኪነ ጥበቡ ስለ ነፃነት ድል በዓላት ለነፃነት ሲሉ ስለተሰዉ ኢትዮጵያውያን ይህ ነው የሚባል ሥራ ባለመሠራቱ ይስማማል፡፡ ‹‹የሚጠቀስ ሥራ የምለው የጂጂን ብቻ ነው፡፡ የቴዲ አፍሮም ቢሆን ብዙ ስለ ባልቻ ነው፡፡ ስለጃፓን የዘፈንን ሰዎች ነን ስለ ዓድዋ ግን ዘፈንም፣ ግጥምም ቴአትርም ያጥረናል፤›› ይላል አቶ መሐመድ፡፡

እሱ እንደሚለው መገናኛ ብዙኃኑም የሚገባውን ያህል ስለኢትዮጵያዊ ማንነትና ታሪክ አይሠራም ትኩረት የሚሰጠው ነገርም አይደለም፡፡     

በእነዚያ በቀደሙ ትግሎችና ነፃነቶች ባይሆን ዛሬ ኢትዮጵያዊነት ምን ሊመስል ይችል እንደነበር መጠየቅ ያስፈልጋል የሚለው አቶ መሐመድ፣ አገሮች ድል ያደረጉበትን ሳይሆን ድል የተመቱባቸውን ታሪካዊ አጋጣሚዎች በፊልምና በሌሎች ኪነ ጥበባዊ ውጤቶች ለዛሬው አገራዊ ሁኔታቸው እንዲጠቅም በሚያደርጉበት ጊዜ የእኛ የድል በዓላት እንደዋዛ መታየታቸው ትልቅ ችግር ነው ይላል፡፡

የነፃነትና የድል በዓላቱ የሚገባቸውን ያህል ቦታ እየተሰጣቸው አይደለም በሚለው በብዙዎቹ አስተያየት የኢትዮጵያ አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍንም ይስማማሉ፡፡ ለዚህ በምክንያትነት የሚያስቀምጡት ከቀድሞ ጋር ሲነፃፀር ዛሬ ላይ በትምህርት ቤቶች ስለኢትዮጵያ የነፃነት ትግሎችና የድል በዓሎች የሚሰጠው ነገር በቂ አለመሆንና ወላጆችም ለልጆች ስለ አገር ታሪክ ስለኢትዮጵያዊ ማንነት ከመናገር ይልቅ ልጆችን ለውጭ አገር ባህልና እሴት የሚያጋልጡ ነገሮችን ማመቻቸት ናቸው፡፡

ምንም እንኳ በዓሉን ለመታደም የበዓሉ ሥነ ሥርዓት ከሚካሄድባቸው ቦታዎች ላይ የሚገኙ ታዳሚዎች የባለሥልጣናት ዲፕሎማቶች ቁጥር እንዲሁም ለበዓሉ ሥነ ሥርዓት የሚደረጉ ነገሮች በአጠቃላይ ከጥቂት ዓመታት በፊት ከነበረው ሁኔታ ጋር ሲነፃፀር የተሻለ የሚባል ቢሆንም ለበዓላቱ የሚገባቸው ቦታና ክብር አለመሰጠቱን እሳቸውም ያስረግጣሉ፡፡ ይህ ደግሞ ለሳቸው ግዴለሽነት ሳይሆን ቅድሚያ የመስጠት ያለመስጠት ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን ከነፃነትና ከአገር ህልውና የሚቀድም ምን አለ? የሚለውን ጥያቄ የእሳቸውና የሌሎቹም ጥያቄ ነው፡፡ ‹‹ለልጅ ስለ ነፃነት ትግል ስለ ድል አለመንገር እንዲማር አለማድረግ ማወቅ ያለበትን ነገር እንዳያውቅ ማድረግ ነው፤›› የሚሉት ልጅ ዳንኤል ጆቴ፣ አሁን ለበዓላቱ አከባበር በማኅበረሰቡ እየተሰጠ ያለው ግምት፣ የሚታየው ነገር በአጠቃላይ ብዙ መሥራት እንደሚያስፈልግ የደወል ያህል እንደሆነባቸው ይገልጻሉ፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...