Monday, September 26, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ኪንና ባህልበሙዚቃ የተቃኘው ስፖርት

  በሙዚቃ የተቃኘው ስፖርት

  ቀን:

  አካባቢው በጉም ተሸፍኗል፡፡ በልግ ነውና አልፎ አልፎ ያካፋል፡፡ ባሌ ሮቤ ውስጥ ነው፡፡ በተፈጥሮ ሀብት አጠባበቅ ላይ የሚያጠነጥን ኮንፈረንስ ተዘጋጅቷል፡፡ ቦታው ከዓመት አብዛኛውን ወራት የሚዘንብበት ስለሆነ ታዳሚዎች ለአየሩ እንደሚስማማ ለብሰዋል፡፡ ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች፣ ከአፍሪካ አገሮችና ከአውሮፓም የተውጣጡ የተፈጥሮ ልማት ባለሙያዎች ከመድረኩ የሚቀርበውን ንግግር በጥሞና ይከታተላሉ፡፡

  ኮንፈረንሱ ከሚካሄድበት ሆቴል አዳራሽ በአንዱ ጠረጴዛ ዙሪያ ኬንያውያንና ኢትዮጵያውያን ተሳታፊዎች ተቀምጠዋል፡፡ ከኬንያውያኑ አንዱ እጁን አውጥቶ ጥያቄ እንዳለው አስታወቀ፡፡ መድረክ መሪው ዕድል ሰጠው፡፡ ‹‹መዝፈንና መደነስ እንፈልጋለን፤›› ኬንያዊው ተናገረ፡፡ በአዳራሹ ከነበሩ ጥቂቱ ኬንያዊው እየቀለደ ስለመሰላቸው ሳቁ፤ የተገረሙም ነበሩ፡፡

  በአቅራቢያው የነበሩና ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የመጡ ተሳታፊዎች ግን በሐሳቡ እንደሚስማሙ ገለጹ፡፡ መድረክ መሪው አላንገራገረም፡፡ መሰል ውይይቶች ከኢትዮጵያ ውጭ ሲካሄዱ የስብሰባው እኩሌታ ላይ መዝፈንና መጨፈር የተለመደ መሆኑን ተናገረ፡፡ ጥያቄውን ባቀረበው ኬንያዊ መሪነት ወንበሮችና ጠረጴዛዎች የአዳራሹን ጥግ ያዙ፡፡ በኬንያ ባህላዊ ልብስና ጌጣጌጥ የተዋበች አንድ ተሳታፊ ከመድረክ መሪው ማይክ ተቀብላ መዝፈን ጀመረች፡፡ ጭፈራውም ደራ፡፡

  እዛው ባሌ የተወለዱ ባልቴትም ኦሮምኛ ዘፈኑ፡፡ ቋንቋውን የማያውቁ ሳይቀሩ  የሙዚቃ ምቱን ተከትለው ጨፈሩ፡፡ መንፈሳቸው ዘና ያለው ታዳሚዎች ወደ ውይይቱ ሲመለሱ በትኩስ ኃይል ተሞልተው ነበር፡፡

  በበዓላት፣ በሠርግ ወይም ሌሎች ሰዎችን ሐሴት በሚሰጡ ክንውኖች ላይ ሙዚቃና ጭፈራ የተለመደ ነው፡፡ አንዳንዴ እንደ ኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች በማይገመት ቦታም ይስተዋላል፡፡ ማንኛውም ዓይነት የሰውነት እንቅስቃሴ አንዳች ስልት ያለው ዳንስ እንደሚፈጥር ይታመናል፡፡

  የዘርፉ ባለሙያዎች ዳንስ ወይም ውዝዋዜ ከሰው ልጅ የዕለት ከዕለት አኗኗር ጋር የጠበቀ ቁርኝት እንዳለው ያስረዳሉ፡፡ ሰውን ከራስ ፀጉር እስከ እግር ጥፍር በዘዬ  የሚያንቀሳቅሰው ዳንስ ወደ አካል ብቃት እንቅስቃሴ መንደር ጎራ ካለም ሰነባብቷል፡፡ በአገርኛ ሙዚቃዎች በታጀበ ባህላዊ ውዝዋዜ ወይም በውጭ ዘፈኖች  ስፖርትን የሚያዘወትሩም ተበራክተዋል፡፡

  ለጤና፣ ለአካል ጥንካሬ፣ የሰውነት ቅርፅን ለመጠበቅና ሌሎችም ተያያዥ ውጤቶች ወደ ጂምናዝየም የሚያመሩ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው፡፡ ስፖርት በሙዚቃ ታጅቦ መሥራት የተመለመደ ነው፡፡ አሁን ግን ባህላዊ ውዝዋዜና ዳንስን እንደአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚሠሩ አሉ፡፡

  በአዲስ አበባ ተዘዋውረን ካየናቸው ካፒታል ሆቴልና ስፓ ጂምናዝየም አንዱ ነው፡፡ በጂሙ አንድ ክፍል በትሬድሚል፣ ሳይክልና ሌሎችም ዘመን አመጣሽ መሣሪያዎች ስፖርት የሚሠሩ ተጠቃሚዎች አሉ፡፡ ኤሮቢክስ፣ ካርዲዮ፣ ስፒኒንግና ኢንሳኒቲ ከስፖርቱ ጥቂቱ ናቸው፡፡

   ሌላው ክፍል በአራቱም አቅጣጫ በመስታወት ተሸፍኗል፡፡ በክፍሉ ልዩ ልዩ ባህላዊ ሙዚቃዎች ይከፈታሉ፡፡ አሠልጣኙ ተጠቃሚዎቹ ምቱን ተከትለው እንዲወዛወዙ ይመራል፡፡ ወደዘመናዊ ዳንስ የሚያዘነብሉም ተራቸውን ጠብቀው ይስተናገዳሉ፡፡ እንደ ሌሎች የስፖርት ዓይነቶች ሰውነት ማሟሟቂያ (መግቢያ) እና ማቀዝቀዣ (መደምደሚያ) አለው፡፡ እንቅስቃሴው በሙዚቃዎች ፍጥነት ይወሰናል፡፡ የባህላዊ ውዝዋዜን ‹‹ቱባ ፊትነስ›› በሚል እንደ ስፖርት የሚያሠለጥነው ዳንሰኛ ጌታነህ ፀሐዬ ነው፡፡

  ጌታነህ በባላገሩ አይዶል ላይ በዳኝነት ይታወቃል፡፡ የመድረክ ውዝዋዜና ዳንስ ኬሮግራፍ ያደርጋል፡፡ የቴዲ አፍሮ፣ የኬቨን ሊትል፣ የናቲ ማንና የጆኒ ራጋ ኮንሰርቶች ይጠቀሳሉ፡፡ በስፖርት ዘርፍ ለ11 ዓመታት ቴኳንዶ ሠርቷል፡፡

  በ‹‹ቱባ ፊትነስ›› ለስፖርት አመቺ የሆነ ሙዚቃና ውዝዋዜ ይመረጣል፡፡ የጉራግኛ፣ የኩናማ፣ የኮንሶ፣ የጉሙዝ፣ የጋምቤላና የራያ ሙዚቃ ምታቸውና አጨፋፈራቸው ለስፖርት እንደሚሆን ጌታነህ ይናገራል፡፡ ወደነዚህ ውዝዋዜዎች ከመሸጋገራቸው በፊት የአማራ ክልል ሙዚቃዎችን ሰውነት ለማሟሟቅ ይጠቀሙበታል፡፡ ትከሻና አንገት ለማፍታታትና ቀስ በቀስ ወደ ፈጣን ሙዚቃ ለመሸጋገር ያመቻሉ፡፡

  አንድ ሰዓት የሚወስደው ስፖርት የሚጠናቀቀው ሰውነት አቀዝቅዞ በማሳሳብ (ማፍታታት) ነው፡፡ በማጠቃለያው በባቲና በትዝታ ቅኝት ያሉ ሙዚቃዎችን ይከፈታሉ፡፡ እንደ ዳምፔልና ስቴፐር ያሉ መሣሪያዎች በሌሎች የስፖርት ዓይነቶች ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ በ‹‹ቱባ ፊትነስ›› ደግሞ በተለይም በኦሮምኛ፣ በራያና በከሚሴ ባህላዊ ውዝዋዜ ማጀቢያ የሆነው ዱላ ይካተታል፡፡ ጌታነህ እንደሚለው፣ ለስፖርቱ የሚሆኑ ሙዚቃዎች ውስን ስለሆኑ ያለውን ደጋግመው በሥራ ለማዋል ተገደዋል፡፡

   ጌታነህ ‹‹ቱባ ፊትነስ››ን ከሌሎች ስፖርቶች ጋር ያነፃፅራል፡፡ እንደ ምሳሌ የሚጠቀሰው ኢንሳኒቲን ነው፡፡ እንቅስቃሴው ፈጣን በመሆኑ ሁሉንም ዕድሜና የጤና ሁኔታ ያማከለ አይደለም ይላል፡፡ በተቃራኒው ዙምባ (ከላቲን አገሮች የተወረሰና በላቲን ሙዚቃና ዳንስ ስፖርት የመሥራት ሥልት) ለብዙዎች ቀላል ነው፡፡ ጌታነህ እንደሚለው፣ እንደ ዙምባ የኢትዮጵያ ባህላዊ ውዝዋዜ ለስፖርት ግብዓት የሚሆኑ እንቅስቃሴዎች ያሉት በመሆኑ በስፋት ጥቅም ላይ መዋል ይገባዋል፡፡

  ‹‹በባህላዊ ውዝዋዜ ስፖርትን መሥራት ጤናማ ለመሆን፣ ለሰውነት ቅርፅ መስተካከልና አእምሮን ዘና ለማድረግም ይረዳል፡፡ የኢትዮጵያን ባህል በአቋራጭ መንገድ ለማሳወቅም ያግዛል፤›› ይላል፡፡ ሰውን ወደ ስፖርት ለመሳብ ከሚውሉ መንገዶች እንደ አንዱ መውሰድ እንደሚቻልና ባህልና ጤንነት መጣመሩ ብዙዎችን እንደሳበም ያምናል፡፡ ‹‹ስንጀምር በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች ብቻ ነበሩ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን የተጠቃሚው ቁጥር ጨምሯል፤›› ይላል፡፡

  ዙምባ ከላቲን አገሮች አልፎ በዓለም ተስፏፍቷል፡፡ ባህላዊ ውዝዋዜም በስፖርት ዘርፍ በዓለም መታወቅ እንደሚችል ያምናል፡፡ ከባህላዊ ውዝዋዜ በተጨማሪ ዘመናዊ ዳንስ የሚያሠለጥን ሲሆን፣ ሒፖፕና ዳንሶልን በአሥራዎቹና በሃያዎቹ ዕድሜ ክልል ያሉ ያዘወትሯቸዋል፡፡ ጌታነህ ‹‹እንደየሰው ፍላጎት ባህላዊ ውዝዋዜ ብቻ ሳይሆን ዘመናዊ ዳንስንም ለስፖርት ማዋል ይቻላል፤›› ይላል፡፡

  የኢትዮጵያ ባህላዊ ውዝዋዜ እንደ ስፖርት ሲተዋወቅ በመላው ዓለም የታወቁ የዳንስ ዘዬዎች በመጠኑ ቢታከሉበት በፍጥነት ትኩረት ይስባል ይላል፡፡ ለ‹‹ቱባ ፊትነስ›› የፓተንት መብት ለማውጣት ተቃርቧል፡፡ እንቅስቃሴው ከጂም ባለፈ በብዙዎች እንዲዘወተር በሲዲ የማሳተም ዕቅድም አለው፡፡

  ማትያስ ገብረሥላሴ ስፖርትን በውዝዋዜና ዳንስ ከሚሠሩ አንዱ ነው፡፡ ባህላዊ ውዝዋዜና ኤሮቢክስን ነጣጥለው መሥራት የሚፈልጉ ሰዎችን እንደሚያጣምር ያምናል፡፡ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን ውዝዋዜና የተለያዩ አገሮችን ዳንስ እንደ ስፖርት መሥራት ከጀመረ በኋላ በሰውነቱ ለውጥ እንዳየ ይናገራል፡፡ የተስተካከለ አቋም እንዳለው ይገልጻል፡፡ ‹‹ውዝዋዜ በዕድሜና የጤና ሁኔታ አይገደብም፤ ሁሉም በአቅሙ ልክ የሚሠራው ዓይነት እንቅስቃሴ አለ፤›› ይላል፡፡  

  ጂም ውስጥ ከሚሰጡ የስፖርት ዓይነቶች መካከል በውዝዋዜና በዳንስ ስፖርት መሥራት ተጠቃሚዎችን የበለጠ እንደሚያቀራርብ ያምናል፡፡ ከተለያየ ሙያ የተውጣጡ ሰዎች የሚገኙበት እንደሆነም ይናገራል፡፡ ስፖርት ‹‹ከባድ ነው›› በሚል ሰዎች እንዳይሸሹት ይረዳል የሚለው ማትያስ፣ ‹‹ውዝዋዜና ዳንስ ስፖርትን ቀላልና አዝናኝ አድርጎልኛል፤›› በማለት ይገልጸዋል፡፡ 

  ተወዛዋዡ ቢንያም ፈቃዱ በዓለም ፊትነስ ሴንተር የባህላዊ ውዝዋዜ እንቅስቃሴዎችን በመጠቀም ስፖርት ያሠለጥናል፡፡ በባህላዊ ውዝዋዜ ሙያ ለዓመታት ሠርቷል፡፡ አሁን በግል ትምህርት ቤቶች ውዝዋዜ ያስተምራል፡፡ ውዝዋዜ በስፖርት መልክ በጂም መሰጠቱ ባህልን የማስተዋወቅ ሚና እንዳለው ከሌሎች አስተያየት ሰጪዎች ጋር ይስማማበታል፡፡

  የተለያዩ ብሔረሰቦች ባህላዊ ውዝዋዜዎች የሰውነት እንቅስቃሴን ከስፖርት ጋር አዛምዶ ይገልጻቸዋል፡፡ እንቅስቃሴው ከፊት ገጽታ ይነሳል፡፡ የተለያዩ ብሔረሰቦች በዕለት ከዕለት ሕይወታቸው ላይ የተመረኮዘ ውዝዋዜ አላቸው የሚለው ቢንያም፣ ይህ በውዝዋዜ ወቅት ፊታቸው ላይ ይንፀባረቃል ይላል፡፡

   በመቀጠል አንገት፣ ትከሻ፣ ወገብ፣ ዳሌና ሌሎችም የሰውነት ክፍሎችን የሚያንቀሳቅስ የውዝዋዜ ዓይነት አለ፡፡ አንድ ሰው ስፖርት ለመሥራት ሲያቅድ የተነሳለትን ዓላማ ተከትሎ በአንድ ብሔረሰብ ሙዚቃ ላይ ሊያተኩር ይችላል፡፡ ወላይትኛ ጭፈራ ከወገብ በታች ያለ ሰውነትን ወደ ግራና ቀኝ ያወዛውዛል፤ በአካባቢው ያለውን ስብ ያቃጥላል፡፡ ሱማልኛም ተመሳሳይ ውጤት ይሰጣል፡፡

   አብዛኛው ባህላዊ ውዝዋዜ ትከሻን ያንቀሳቅሳል፡፡ የጎጃም እንቅጥቅጥ ከወገብ በላይ ላለ ሰውነትና በተለይም ትካሻ ለማንቀሳቀስ ይውላል፡፡ ከኦሮምኛ እንደ ሶምሶማ ሩጫ ያለ እንቅስቃሴውን መጠቀም ይቻላል፡፡ ፍጥነት ጨምሮ ሰውነትን ለማሟሟቅ ጉራግኛ፣ ለማቀዝቀዝ ደግሞ ትግርኛ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

  ቢንያም እንደሚለው፣ ውዝዋዜ ለአተነፋፈስ ሥርዓትም ይረዳል፡፡ ኦሮምኛ፣ ጉራግኛ፣ ትግርኛና ሌሎችም ሙዚቃዎች የየራሳቸው ትንፋሽ አወጣጥ አላቸው፡፡ ‹‹በባህላዊ ውዝዋዜዎች መካከል ያለው ልዩነት ስፖርት እንዳይሰለች ያደርጋል፤›› የሚለው ተወዛዋዡ፣ በተጨማሪም አንድ ሰው በሰውነቱ ላይ የሚፈልገውን ዓይነት ለውጥ እንደሚያመጣ ያምናል፡፡ ውዝዋዜ በትምህርት ቤቶች ወይም በቴአትር ቤቶች ሲሰጥ በሙያተኞች ብቻ ስለሚወሰን ወደ ጂም መምጣቱ ተደራሽነቱን ያሰፋዋል ይላል፡፡ እሱ እንደሚለው፣ በተለያየ የዕድሜ ክልል ያሉ ሰዎችን ሲያሠለጥን ነፃ የመሆን፣ በራስ የመተማመንና ሌሎችም ውጤቶች እንዳገኙ ይገልጹለታል፡፡ ‹‹ዮጋ፣ ኤሮቢክስ ወይም ሌላ ስፖርት መሥራት የሚፈልጉ ሰዎች ይህን ውጤት አያገኙም ማለት አይደለም፤ ውዝዋዜ ግን ዘና ስለሚያደርግ ይለያል፤›› ይላል፡፡

  በጂሙ ያገኘናት ቤተልሔም ማሩ ‹‹እንቅስቃሴው በአንድ በኩል ጤናማ ለመሆን ተያይዞም ባህላዊ ውዝዋዜና ዳንስ ለማወቅ ያግዛል፤›› ትላለች፡፡ ስፖርት ብቻውን መሥራት ወይም እንደሷ ከውዝዋዜ ጋር የሚመርጡ ሰዎች በሁለቱም መንገድ ግባቸውን እንደሚመቱ ታምናለች፡፡ ቢሆንም ከውዝዋዜ ጋር ሲሆን፣ የበለጠ ሰውነትን የሚያዝናና እና ቀለል ያለ መንፈስ የሚፈጥር ነው ትላለች፡፡ ብዙዎች የውዝዋዜና ዳንስ ችሎታቸውን ለማዳበርም ይጠቀሙበታል፡፡ አሠራሩ ተመራጭ እየሆነ የመጣው ለዚህ ይሆናል ትላለች፡፡

  ጌታሁን ደሳለኝ በካፒታል ሆቴልና ስፓ ጂም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ክፍል ምክትል ኃላፊ ነው፡፡ ከኢኮኖሚ ዕድገትና ዓለም አቀፋዊነት መስፋፋት አንፃር ጂም ማዘውተር እየተለመደ እንደመጣ ይናገራል፡፡ አንዳች ዓይነት ውጤት ለማግኘት ልዩ ልዩ የስፖርት ዓይነቶች በባለሙያዎች ይመከራሉ፡፡ ከነዚህ መካከል በውዝዋዜ ወይም በዳንስ ስፖርት መሥራት ሲመረጥ ይስተዋላል ይላል፡፡

  ውዝዋዜና ዳንስን በስፖርት ዓይነቶች ላይ መጨመር ከቢዝነስ አኳያም ተመራጭ ነው፡፡ አማራጮች ሲበራከቱ የተጠቃሚው ቁጥርም አብሮ እንደሚጨምር ያስረዳል፡፡ ‹‹ኬሮግራፊው መስመር እስከያዘ ድረስ ውዝዋዜን ስፖርት ማድረግ እንደሚቻል ማስረጃ ከሚሆኑ አንዱ ዙምባ ነው፤›› የሚለው ጌታሁን፣ ይህንን ወደ ኢትዮጵያ ባህላዊ ውዝዋዜ ማምጣት ጂሙን እንደጠቀመው ያስረዳል፡፡ ተጠቃሚዎችም ተመሳሳይ ሐሳብ ሰጥተውናል፡፡ ውዝዋዜና ዳንስን እየተማሩ ስፖርት መሥራቱ ‹‹በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ›› እንደሚባለው እየሆነ ይመስላል፡፡  

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በኢትዮጵያ ላይ የቀጠለው የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት

  ምዕራባውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዲፕሎማሲም...

  የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የድጎማ በጀት ለፖለቲካ ሥራ ማስፈጸሚያ እንደሚውል የሚያሳይ ሪፖርት ቀረበ

  ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረግ የበጀት ድጎማ ከመደበኛው ሥራ ይልቅ ከዋናው...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የአመራሮች ምርጫና ቀጣይ ዕቅዶቹ

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሲጠበቅ የነበረውን...