Saturday, June 15, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ከሽብርተኝነት እስከ የውጭ ዜጎች ጥላቻና የሰሞኑ አደጋ

በባንትይርጉ አንተንይስጠኝ

በቅርቡ በደቡብ አፍሪካና በሊቢያ በወገኖቻችን ላይ የደረሰው አሰቃቂ ግፍ መላው ሕዝባችንን ከዳር እሰከ ዳር ልብ ሰባሪ ሐዘን ውስጥ የከተተ ክፉ አጋጣሚ ሆኖ አልፏል። የንፁኃን ዜጎች ደም በጥላቻ በታወሩና ከሰብዓዊነት ስሜት በተፋቱ አሸባሪዎችና አረመኔዎች የሚዘገንን የግፍ አገዳዳል መፈጸሙ ኢትዮጵያውያንን የሐዘን ጽልመት ያለበሰ አረመኔያዊ ተግባር ነበር። የሰው ልጅን በሰብዓዊነቱ የሚጋራውን ሥነ ምግባር ሁለንተናዊነት ለመጠየቅ ግድ በሚያስብል መልኩ ጭምብል ያጠለቁ የአይኤስ ቡደን አባላት፣ ክቡሩን የሰው ልጅ እንደ መስዋዕት እንስሳ በካራ መቅላታቸው የቀሰቀሰው ቁጣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵውያን በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ባደረጉት ሠልፍ የተንፀባረቀ ነበር.። መንግሥት የሦስት ቀናት ብሔራዊ የሐዘን ቀን በማወጅ፣ ኅብረተሰቡ ሐዘኑን በታላላቅ ሰላማዊ ሠልፎች እንዲገልጽ በማድረግ የሕዝቡን የቁጭትና የሐዘን ሰሜት የሚጋራ መሆኑን በሰከነ ሁኔታ አሳይቷል። መንግሥት የደረሰው አደጋ የሚያስፈልገው ምላሽ ግብታዊነት የሚነዳው ዕርምጃ ሳይሆን፣ ሕገወጥ ስደትንም ሆነ ሽብርተኝነት ከምንጩ ማድረቅ የሚቻለው ኅብረተሰቡን ማዕከል ያደረገ፣ ትግሉን ከመቼውም በላይ በላቀ ደረጃ ማከናወን እንደሚያስፈልግ ያረጋገጠ ክፉ ቀስቃሽ (rude awakening) አድርጎ እንደሚረዳው በተለያዩ አጋጣሚዎች ገልጿል። በሌላ በኩል መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በወገኖቻችን ላይ የደረሰው ግፍ ከተሰማ ጀምሮ በአገራችን ባህልና ወግ መሠረት ተጎጂ ቤተሰቦችን በማፅናናትና በመደገፍ ለአይኤስና ለአጋሮቹ አንድነቱ በጥብቅ መሠረት ላይ የቆመ መሆኑን መልዕክት ያስተላለፈበት አጋጣሚ ሆኖ አልፏል።  

በዚሁ ሁሉ ውስጥ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ መነጋጋሪያ ሆኖ የሰነበተው ጉዳይ ሽብርተኝነትና ሕገወጥ ስደት  ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። እያሱ፣ ባልቻ፣ ሃዱሽና ሌሎች ወገኖቻችን በሊቢያ በረሃ በግፍ ለምን ሞቱ? የስደት ሰቆቃ መቼና እንዴት ይቆማል? የሚሉት ጥያቄዎች የብዙዎቻችንን አዕምሮ ወጥረውት ከርመዋል። የዚህ ጽሑፍ ዓላማም በተነሱት ጥያቄዎች ላይ ሙሉ ምላሽ መስጠት ሳይሆን፣ እንድም የደረሰው ሐዘን የፈጠረው ግብታዊ ስሜት የጋረዳቸውን አንዳንድ ነጥቦች በማንሳት በጉዳዩ ላይ ለሚደረግ ውይይት ጠቃሚ ናቸው ያልኳቸውን የበኩሌን ሐሳቦች ለመወርወር ነው። በዚሁ ሐሳብ መነሻነት ቀዳሚ የትኩረት ነጥብ ብዬ የወሰድኩት በደቡብ አፍሪካም ሆነ በሊቢያ የተፈጸሙ ጥቃቶች በእርግጥ በኢትዮጵያውያን ላይ የተነጣጠሩ ናቸው ወይ የሚለው ጥያቄ ነው። ለዚህም ምክንያቴ የሽብርተኝነት ድርጊቱም ሆነ የውጭ ዜጎች ጥላቻው በኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመ ነው የሚል ስኁት አረዳድ በበርካቶች ዘንድ ሲንፀባረቅ በማየቴ ነው።

ደቡብ አፍሪካ ቀስተ ደመናዋ አገር?

ደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ ማግሥት ጀምሮ የህብራዊነት፣ የእኩልነትን፣ የነፃነትና የተስፋ አየር ሰማይዋን ሞልቷት ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም። የአገሪቷን ህብራዊነት ለማወጅና የቀለም ልዩነት ታሪክ መሆኑን ለማመልከትም ቀስተ ደመናዋ አገር ተብላ ትንቆለጳጰስ ነበር። ነገር ግን ይህንን ታላቅ ህልም ዕውን የማድረጉ ክብደት የዳገት ሩጫ መሆኑ ብዙም ሳይቆይ የታየ ነበር። በዚህ ረገድ በተለይ በደቡብ አፍሪካ የኤኤንሲ መንግሥት ሥልጣን ላይ ከወጣ ጀምሮ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ኢ-እኩልነት የሚያበቃበት፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል የሚረጋገጥበት፣ ፖለቲካዊ ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊ አርነት በመቀዳጀት ብዙኃኑ ጥቁር ደቡብ አፍሪካዊ የሀብት ተጋሪ የሚሆንበት ሥር-ነቀል ለውጥ አለመምጣቱ ጥያቄው ላለፉት ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ ለሆነ ጊዜ በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ሲንከባለል የቆየ ትልቅ ጉዳይ ነው ለማለት ይቻላል። የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ባለፉት ሃያ ዓመታት በተለይ “Broad Based Black Economic Empowerment” በተሰኘ ፕሮግራም ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ያላቸውን ድርሻ ለማሳደግ ጥረት ቢያደርግም፣ ደቡብ አፍሪካ በዓለም በሀብት ክፍፍል ኢፍትሐዊነት ሦስተኛ ደረጃ ላይ መገኘቷ ብዙኃኑ ጥቁር ደቡብ አፍሪካዊ ኢኮኖሚያዊ መገፋት (economic marginalization) የደረሰበት መሆኑን በግልጽ ያመላክታል። ዘጋርዲያን ጋዜጣ “South Africa’s ‘miracle transition’ has not put an end to white privilege” በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ በ2013 ባወጣው ጽሑፍ፣ የአገሪቱ 80 በመቶ መሬት አሥር በመቶ  በሚሆኑ ነጮች እጅ መሆኑ፣  ነጭ ደቡብ አፍሪካውያን 80 በመቶ ከሚሆኑት ከጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን ጋር ሲነፃፀር በስድስት እጥፍ የላቀ የነፍስ ወከፍ ገቢ ያላቸው ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ ሲታይ፣ ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን መዋቅራዊ የሆነ የኢኮኖሚ መገለል ሰለባዎች እንደሆኑ ጠንካራ ክርክር ለማድረግ ያስችላል ሲል ጽፏል።

በመዋቅራዊ መገለልና ፍትሐዊ ክፍፍል አለመኖር ምክንያት በአነስተኛ ንግድና በጉልበት ሥራ ላይ የተሰማራው ብዙኃኑ ጥቁር ደቡብ አፍሪካዊ ዘንድ ስደተኛ ሠራተኛች በአነስተኛ ክፍያ በመቀጠር የሥራ ዕድሎችን እያጣበቡብን ነው የሚል ስሜት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቶ፣ በተለይ ከ1990ዎቹ ጀምሮ የሌሎች አፍሪካውያን ንብረት መዝረፍ፣ ሱቆችን ማቃጠል፣ ከባቡር ላይ መወርወርና የመሳሰሉ ወንጀሎች ይፈጸሙ ነበር። ይሁን እንጂ በውጭ ዜጎች ጥላቻ መስፋፋት ላይ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች እንደሚያመለክቱት ለጥላቻው መስፋፋት ከመዋቅራዊ መገለልና የሀብት ኢ-እኩልነት ባለፈ፣ ታሪካዊና መዋቅራዊ ምክንያቶች እንዳሉት ይገልጻሉ። “South African Civil Society and Xenophobia” በሚል ርዕስ የቀረበ ጥናት እንደሚያመለክተው፣ ለውጭ ዜጎች ጥላቻና ተከትሎት ለመጣው በውጭ ዜጎች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ምክንያት አድርጎ የሚያስቀምጠው፣ ድህነትና መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ኢ-ኩልነት፣ ድኅረ-ዘረኝነት (post-racial) ሥርዓት ግንባታ ሽግግር መዘግየት፣ የውጭ ዜጎችን ከኅብረተሰቡ ጋር የሚያዋህዱ (integration) ፖሊሲዎች አለመኖርና በአፓርታይድ ለደረሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ካሳን ጨምሮ ፍትሕ ያለማግኘት ስሜት አገራዊ ህሊና (national psyche) ላይ የፈጠረው ጨለምተኝነት እንደሆነ ይገልጻል። 

በዚህም ምክንያት ከ1990ዎቹ ጀምሮ በተለያዩ አጋጣሚዎች በውጭ ዜጎች ላይ ጥቃት ሲፈጸም የቆየ ሲሆን፣ በተለይ እ.ኤ.አ በ2008 ከ40 በላይ በውጭ ዜጎች ጥላቻ በታወሩ መንገኞች (mob) መገደላቸው በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ማሳያ ነው። በቅርቡ ለሰባት ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነውም ጥቃት እንደከዚህ ቀደሞቹ ሁሉ  በደቡብ አፍሪካ የተሻለ የኢኮኖሚ ዕድሎች አሉ የሚል እሳቤ ያመጣቸው የኢትዮጵያ፣ የሞዛምቢክ፣ የኮንጎ፣ የዚምባብዌ፣ የሌሶቶ፣ የሶማሊያ፣ የናይጄሪያና የህንድ ዜጎች ላይ የተፈጸመ መሆኑን ስናስተውል፣ ጥቃቱ በመሠረታዊነት በአገሪቱ መዋቅራዊ ችግሮች አለመፈታት ምከንያት የተፈጠረ እንጂ፣ በኢትዮጵያም ሆነ በሌላ አገር ላይ በተናጠል  በተፈጠረ የጥላቻ ስሜት ያልተፈጸመ እንደሆነ እንረዳለን።

ከዚህ በተጨማሪ በሁለተኛ ደረጃ ሊታይ የሚገባው እውነታ የደቡብ አፍሪካ መንግትሥትም ሆነ ገዢው ፓርቲ ለደቡብ አፍሪካ ነፃነት በተለይ አፍሪካውያን ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ትውልዱ እንዲረዳው በማድረግ ረገድም ሆነ፣ የፓን አፍሪካኒዝም ጽንሰ ሐሳብ ከማስረፅ አኳያ የሠራው ሥራ አናሳ መሆኑን ነው።  በተለይ ኢትዮጵያ ለደቡብ አፍሪካ የነፃነት ትግል ፕሬዚዳንት ማንዴላንና አሁን ያለውን የኤኤንሲ አመራር ከማሠልጠንም በላይ፣ በፓን አፍሪካዊነት መርህ የተባበረች አኅጉር ዕውን የማድረግን አፍሪካዊ ህልም ከማሳከት እንፃር ትልቅ ሚና ያላት አገር ከመሆኗ አኳያ፣ የባለዕዳነት ስሜት በደቡብ አፍሪካውያን ከብዶ ሊታይ ይገባው ይሆን እንጂ፣ ፀረ ኢትዮጵያዊነት ስሜት ሊፈጠር ይችላል ማለት እንዴትስ ይቻላል? ያኔ ድምፃቸው ሰሚ ያልነበረውን የደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች በመወከል ዘረኛውን የአፓርታድ መንግሥት በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት የገተረች ኢትዮጵያ፣ ለኤኤንሲ ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ ትግል ድጋፍ የሰጡ የዚምባብዌና የማላዊ ዜጎች ለምን ሞቱ ስንል ምላሹ፣ አንድም የአገሪቱ አመራር በአገሪቱ አንፃራዊ የሀብት ክፍፍል ለማስፈን አለመቻሉና አፍሪካዊ ወንድማማችነትን የሚወክለውን የፓን አፍሪካኒዝም ጽንሰ ሐሳብ ትውልዱ እንዲረዳው አለማድረጉ እንደሆነ እንረዳለን።

አይኤስ – ቅራኔ ማስፋትና ዓለማዊ ዕይታው

አይኤስ ከውልደቱ ጀምሮ ዛሬ በኢራቅና በሶሪያ ሰፊ ግዛት በመያዝ ‹እስላማዊ ካሊፌት› የመመሥረት ህልሙን ዕውን ለማድረግ የተጓዘበት መንገድን የሚያሳየን የሽብር ድርጊቱ ከወላጁ አልቃይዳ በመጠነኛ ደረጃ በርዕዮተ ዓለምና በስትራተጂ  የተለየ መሆኑን ነው። በርዕዮተ ዓለም ደረጃ በተለይ ‹እስላማዊ ካሊፌት› የሚመሠረተው በኃይል ነው ብሎ ማመኑ፣ እንዲሁም ለዘብተኛ የእስልምና ዕምነት ተከታዮችን ዋና የጥቃት ዒላማ አድርጎ መውሰዱ፣ ከአልቃይዳም የከፋና የጽንፈኝነቱን ዳር የረገጠ አረመኔያዊ ድርጅት አደርጎታል። በዚህ ረገድ ግሎባል ኦብዘርቫቶሪ የተሰኘ ድረ ገጽ “A Tale of Two Jihads: Comparing the al-Qaeda and ISIS Narratives” በሚል ርዕስ ባወጣው መጣጥፍ፣ የአይኤስ የሺአ እምነት ሃይማኖታዊ ምልክቶች (shrines) ማፍረስ የሙስሊሞች ሃይማኖታዊ ኃላፊነት አድርጎ እንደሚመለክት አትቷል። ቡድኑ በተለይ በኢራቅ የኑሪ አልማሊኪ መንግሥት የሱኒ እምነት ተከታዮችን ያገለለ አካሄድ ሃይማኖታዊ መስመር እንዲይዝ በማድረግ በርካታ ወጣት ሱኒዎችን ተዋጊዎቹ ማድረግ ችሏል። ወሰን የሌለው የጭካኔ ተግባርን በሰላ የማኅበራዊ ሚዲያ ፕሮፓጋንዳ በማጀብ ከምዕራቡ ዓለም በርካታ የውጭ ተዋጊዎችን በማማለል እንዲቀላቀሉት አድርጓል። በመሆኑም አይኤስ ዓለማዊ ዕይታው ከመሠረቱ  ቡድኑ የሚከተለውን አክራሪ የእስልምና ትርጓሜ የማይቀበሉትን ጠላቶች፣ የሚቀበሉትን ደግሞ ወዳጆች የሚል እንጂ አገራዊ መሠረት ያለው አይደለም።

የጥቃቱ መለያ መሥፈርት ዜግነት ሊሆን ይቅርና ሃይማኖታቸው የአክራሪውን መስመር ካልተከተለ በቀር አይኤስ ሙስሊሞችንም በጭካኔ እንደሚገድል በሶሪያና በኢራቅ አሳይቷል። ለዚህ ሐሳብ ማጠናከሪያ የሚሆነው የአይኤስ ጥቃት ሰለባዎች ከግብፅ፣ ከጃፓን፣ ከጆርዳን፣ ከአሜሪካ፣ ከእንግሊዝና ሌሎች በርካታ አገሮች ዜጎችን የያዘ መሆኑ ነው። ከዚህ አኳያ የአይኤስ የሽብር አደጋ በሰብዓዊነት ላይ የተመዘዘ ሰይፍ መሆኑን፣ የሽብር ድርጊቱም ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው መሆኑን ደርቦ ማሰብ ይጠይቃል። አይኤስ የእኔን እምነት መስመር ያልተከተለውን በኃይል እንዲከተል ማድረግ ወይም ማጥፋት የሚል ግልጽ ዓላማ  ያለው መሆኑን ልብ ይሏል። እዚህ ላይ አይኤስ ራሱ ባሰራጨው ቪዲዮ ላይ ኢትዮጵያውያንን የጥቃት ዒለማ ማድረጉን በማንሳት፣ ጥቃቱ በኢትዮጵያ ላይ የተነጣጠረ ተድርጎ ክርክር ሊቀርብ ይችላል። ነገር ግን ይህ ክርክር ብዙ ርቀት የማያስጉዝ እንደሆነ ግልጽ ሆኖ የሚታየው የሽብርተኝነትን ባህሪና አይኤስ የሚንቀሳቀስበት ማዕቀፍ (modus operandi) ለብሔራዊ ማንነቶች ዋጋ የማይሰጥ ብቻ ሳይሆን፣ በሃይማኖት ስም የሚፈጸመው ግድያም የሚመዘነው ከድርጅቱ ጠባብ ፍላጎት አንፃር መሆኑን ስንረዳ ነው። በመሆኑም በኢትዮጵየውያኑ ላይ የተፈጸመው ግድያ ሊታይ የሚገባው አይኤስ በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች መካከል የልዩነት ሽብልቅ በመክተት፣ ቅራኔውን አይኤስ የመጠቀም እኩይ አጀንዳው ማሳያ ከመሆን በዘለለ በኢትዮጵያዊነት ላይ የተነጣጠረ አደጋ አድርጎ መረዳት የሽብርተኝነትን የዓለም ዕይታ (outlook) አዛብቶ መረዳት ይሆናል። በመሠረቱ በግብፅ የኮፕቲክ ዕምነት ተከታዮችም ሆነ በኢትዮጵውያኑ ላይ የተፈጸመው ግድያ ከዚህ የተለየ ዓላማ እንደሌለው መገንዘብ ያሻል።

በጥቅሉ ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች ከደቡብ አፍሪካውም በላይ አይኤስ የፈጸመው ግፍ በኢትዮጵያ ላይ ብቻ የተነጣጠረ አድርጎ ለማቅረብ ቢሞከር ውኃ የሚቋጥር የአመክንዮም ሆነ የሀቅ ክርክሮች ሊቀርቡበት የሚቻል አይሆንም። በተለይ  ይህን መሰሉ ጥቃት ከዚህ ቀደም ተሰምቶም የማያውቅ ከመሆኑ አኳያ መንፈሱ ጥቃት አድራሾቹን እዚያው ወዲያው የመበቀል ግንፍል ስሜት የገፋው አተያይ እንደሆነ በብዙ መንገዶች ይጠቁማል። ይህም ሁኔታ ዜጎች እንደዚህ ያለው አገራዊ ትራጀዲ ሲፈጠር በዚህ ዓይነት ስሜት ውስጥ ማለፋቸው ተፈጥሯዊ ከሚል ድምዳሜ ውጪ ሌላ ትርጓሜ ሊሰጠው አይችልም።

ማጠቃለያ

ለማጠቃለል በተለይ የአይኤስን ተግዳሮት ከብሔራዊ ስሜት መነጽር በዘለለ መረዳት የሚገባው፣ የበሽታውን ዓይነት በቅጡ መረዳት ብቻ ወደ ትክክለኛው መፍትሔ የሚያደርስ መሆኑ የታመነ እውነት በመሆኑ ነው።

ከዚህ አኳያ አይኤስን የምናሸንፈው ሕገ መንግሥቱ ያስቀመጠውን በሴኩላሪዝም (ዓለማዊ) መርህ መሠረት ሃይማኖትና መንግሥት ልዩ መሆናቸውን በመረዳት ለመርሁም ተግባራዊነት ዘብ ስንቆም ነው.። ከዚሁ ጎን ለጎን ሽብርትኝነትን መመከት የሚቻለው የዳበረ የሃይማኖት መቻቻል ባህላችንን ከአለት በጠነከረ መሠረት ላይ እየገነባን ስንሄድ መሆኑን መረዳት ይገባል። አይኤስን ድል የምንመታው በአገራችን ከየትኛውም ሃይማኖት የሚመነጭ የአክራራነትና የሽብርተኝነት አደጋ እንዳያቆጠቁጥ የሚያስችል ሥራ መሥራት ስንችል ነው። ይህ ሥራ ደግሞ በዋናነት በሶማሊያ አልሸባብና ሌሎች ዓለም አቀፉ ጽንፈኛ ኃይሎችን በወታደራዊ መንገድ ከመደምሰስ ጎን ለጎን፣ ውጊያው የርዕዮተ ዓለምም መሆኑን በመረዳት አክራሪዎች ለሚነዙት የአክራሪነት ስብከት ሰለባ የማይሆን በሥነ ዜጋ የታነፀ ትውልድ መፍጠር ያሻል።

ከሁሉ በላይ ሽብርተኝነት መሠረት ኖሮት አገሮችን የሚያፈራርሰው የጨነገፈ የአገር ግንባታ ሒደት፣ የከሰረ ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊና ይኼው ሁኔታ የሚፈጥረው ሽብርተኝነት የሚሸከም ማኅበረሰብ ሲኖር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። በአገራችንም አይኤስና ሌሎች ሽብርተኞች ጥቃት ለመፈጸም ያልቻሉት ሽብርተኝነት ሊረታው የማይችል የዳበረ የሃይማኖት መቻቻል ባህል ያለን በመሆኑ፣ ሃይማኖትና መንግሥት የተለያዩ መሆናቸውን ያረጋገጠና መንግሥታዊ ሃይማኖት እንደማይኖር ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና የሰጠ ፖለቲካዊ ሥርዓት በመዘርጋቱ፣ እንዲሁም በድህነት ላይ የተጀመረውን ትግል የዜጎችን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ በመሄድ ላይ በመሆኑ ነው። የአክራሪነትና የሽብርተኝነትን ዓለም አቀፋዊ ባህርይ መረዳት ሌላው ጠቀሜታው ችግሩ ዓለም አቀፋዊ ትግልን የሚጠይቅ ስለሆነ፣ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር በመሆን የበኩላችንን ለማበርከት ግንዛቤ የሚፈጥር በመሆኑ ነው። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ከምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ጋር በመሆን አልሸባብን ለመታገል የምታደርገው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። በተመሳሳይ በደቡብ አፍሪካ የተከሰተው ችግር ከመሠረቱ በኢትዮጵያውያን ላይ የተነጣጠረ ባለመሆኑ የሚፈታውም የዜጎች ሕገወጥ ስደትን መከላከል ሲቻል ብቻ መሆኑን መረዳት ይገባል። አገራችን ለደቡብ አፍሪካ ነፃነት ካደረጋቸው አስተዋጽኦ በጥላቻ ለታወረው መንገኛ ማስታወሱ አንድ ጉዳይ ሆኖ፣ ችግሩን ከሥሩ ለመፍታት ሁሉን አቀፍና ሕዝብን ማዕከል ያደረገ ንቅናቄ በማድረግ፣ ከአዲስ አበባ እስከ ጆሐንስበርግ የተዘረጋውን የሕገወጥ ሰዎች ዝውውር መረብ መበጣጠስ ይገባል እላለሁ።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜል አድራሻቸው  [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles