Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየቀድሞው የዘውድ ፓርላማ አባሉ ትውስታ

የቀድሞው የዘውድ ፓርላማ አባሉ ትውስታ

ቀን:

በመጨረሻው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (1923 – 1967) ዘመን በነበረው መንግሥት የሕግ መምርያ ምክር ቤት (ፓርላማ) የሕዝብ ተመራጭ እንደራሴዎች መካከል ቀኛዝማች ዘውዴ ብራቱ ደጋጋ ይገኙበታል፡፡ በ1961 ዓ.ም. በተካሄደው የሕዝብ እንደራሴዎች ምርጫ በምዕራብ አዲስ አበባ ተወዳድረው ያሸነፉት (በወቅቱ) አቶ ዘውዴ፣ በቅርቡ ‹‹የሕይወቴ ጉዞ›› በሚል ርእስ የግል ሕይወት ታሪካቸውን አሳትመዋል፡፡ በመጽሔቱ ውስጥ በፓርላማ ስለነበራቸው ቆይታና ስላከናወኑት ተግባር የገለጹት እንደሚከተለው ይነበባል፡፡

በ1958 ዓ.ም. መግቢያ ላይ በቀድሞ አጠራር ፍርድ ሚኒስቴር፣ እየተባለ ለሚጠራው መሥሪያ ቤት፣ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ያበረከትኩትን አገልግሎት፣ ሕግን እና ሥርዓትን በማስፈጸም ረገድ ያለኝን የሥራ ልምድ የሚያረጋግጡ የምስክር ወረቀቶች ከማመልከቻ ጋር አያይዤ፣ የጥብቅና ሥራ ፈቃድ እንዲሰጠኝ አመልክቼ ለጊዜው የመጀመሪያ ደረጃ  የጥብቅና ፈቃድ ተሰጥቶኝ በዚሁ የግል ሥራዬን ጀመርኩ፡፡

በጥብቅና ሥራ ላይ ከተሰማራሁ በኋላ ሙያዬን የበለጠ ለማሻሻል ያስችለኝ ዘንድ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ፣ በአሁኑ ስያሜ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ፋክሊቲ በመግባት በማታው የትምህርት ክፍለ ጊዜ በመማር የሕግ ትምህርቴን ስለአጠናቀቅሁ ሐምሌ 8 ቀን 1961 ዓ.ም. ከግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ የሕግ ምስክር ወረቀት ተቀብያለሁ፡፡

ከ1959 እስከ 1961 ዓ.ም. መጨረሻ በጥብቅና ሥራ ላይ ቆይቼ፣ ፈቃዴን ከአደስኩኝ በኋላ የጥብቅና ሥራውን እየሠራሁ፣ በ1961 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ ፓርላማ የሕዝብ እንደራሴዎች የምርጫ ውድድሩን በአንደኛ ደረጃ ስለአሸነፍኩ በ1962 ዓ.ም. ለመረጠኝ ሕዝብ እንደራሴ ሆኜ ፓርላማ ገብቻለሁ፡፡

ፓርላማ ከገባሁ በኋላ ለመረጠኝ ሕዝብ በገባሁት ቃል ኪዳን መሠረት የሕዝብ ችግሮች ናቸው ያልኳቸውን ጉዳዮች በተደጋጋሚ ለፓርላማው አቅርቤያለሁ፡፡ ከእነዚህም መካከል ውጤት ያመጡትን ጉዳዮች እንደሚከተለው እገልጻለሁ፡፡

1ኛ. ሱቅ በደረቴ ተብለው የሚጠሩ ሸቀጣ ሸቀጥ አዟሪ ነጋዴዎች አማራጭ የሥራ መስክ ሳይከፈተላቸው የማዘጋጃ ቤት ዘበኞች በዱላ እየተደበደቡ፣ ሥራቸውን እንዳይሠሩ ስለአገዷቸው፣ ደረታቻውን ሱቅ አድርገው የሚሠሩትን ዜጎች፣ ያለአማራጭ የሥራ ዕድል እንዲበተኑ ማድረግ የማይገባ መሆኑን ለፓርላማው በማስገንዘብ፣ ሥነ ሥርዓት ያለው የሕግ አቤቱታ አቅርቤያለሁ፡፡ ምክር ቤቱም የቀረበውን አቤቱታ ተቀብሎ ስላመነበት፣ ከንቲባው በማስጠራት በድሆችና ሠርቶ አዳሪዎች ላይ የሚፈጸመው በደል ኢሰብአዊ ነው ብሎ በማውገዝ፣ ዜጎች በአገራቸው ሠርተው እንዲኖሩ የሚል ውሳኔ አሳልፎ፣ ውሳኔውን የመወሰኛ ምክር ቤትም ደግፎት አጽድቆታል፡፡

2ኛ. የቁማር ማሽን በአዲስ አበባ ቡና ቤቶች ተበራክቶ፣ ማሽኑ ሃያ አምስት ሣንቲም እየገባለት የሚያጫውት ሲሆን፣ ደመወዝተኛውንና ወታደሩ ሳይቀር፣ ከኑሮ ያፈናቀለ ስለሆነ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዳቦ ሳይጠግብ ቁማር እንዲጫወት ተጋብዟል በሚል ርእስ ለፓርላማው አቤቱታ አቅርቤ፣ ተቀባይነት ስለአገኘ የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲቀርቡ በማዘዝ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም የላኩት ተወካያቸው በተገኙበት፣ ምክር ቤቱ የጉዳዩን አስከፊነት ከተቸበት በሁዋላ የቁማር ማጫወቻ ማሽኑ በ24 ሰዓት ውስጥ ከኢትዮጵያ እንዲወጣ ያሳለፈውን ውሳኔ የመወሰኛውም ምክር ቤት ተቀብሎ አጽድቆታል፡፡

እነዚህን ሁለት ዓቢይ ጉዳዮች መወሰንና ማስወሰን በመቻሌ እስከዛሬም የሕይወት እርካታ ይሰማኛል፡፡ የሕዝብ እንደራሴ ሆኜ በሠራሁበት ጊዜ የሕዝብ ችግሮች ናቸው ያልኳቸውን ጉዳዮች ሁሉ ለፓርላማው ከማቅረብ ወደኋላ አላልኩም፡፡

በአምስትኛው የሕዝብ እንደራሴ ምርጫ ውድድር ተሳትፌ ሳልመረጥ በመቅረቴ፣ ወደቀድሞው የጥብቅና ሙያዬ ተመልሼ ሕዝባዊ አገልግሎት መስጠቴን ቀጠልኩ፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኩባንያ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ባንኮች ውጤታማነት

የጠቅላላ ጉባኤ፣ የጥቆማና ምርጫ ኮሚቴ፣ የተቆጣጣሪ ቦርድ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...