አርመናውያን ከ100 ዓመታት በፊት ኦቶማን ቱርክ ካደረሰባቸው ፍጅት ከተረፉት ዕጓለ ማውታን (የሙታን ልጆች) መካከል፣ አርባዎቹን ልጆች በዘመኑ የኢትዮጵያ አልጋ ወራሽ የነበሩት ራስ ተፈሪ መኰንን (በኋላ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ) በ1916 ዓ.ም. አውሮፓን ለመጎብኘት ሲያመሩ፣ በኢየሩሳሌም ያገኟቸውና በመስከረም 1917 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ያደርጓቸዋል፡፡ እነዚህ ‹‹አርባ ልጆች›› በመባል የሚታወቁት ወጣቶች የሙዚቃ ማርሽ ባንድ ባልደረቦች በመሆን ሙዚቃ በማጥናት በአዲስ አበባ አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ፡፡ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ ለደረሱት የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር ዜማውን ባዘጋጁት ነርሲስ ናልባንዲያን አማካይነት ዜማውን በማጥናት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የንግሥ በዓል ላይ መጫወታቸው በታሪክ ተመዝግቧል፡፡ ፎቶግራፉ በ1923 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ የታክሲ ሥራ ይሠሩ የነበሩትን አርመናውያን ሾፌሮች የሚያሳይ ሲሆን፣ ከአርባዎቹ ውስጥም በታክሲ ሥራ የተሰማሩ እንደነበሩ ይነገራል፡፡
ዘር……
ዘር ሰብሳቢ አጥቶ ከዘር ተለይቶ
በአሸዋማው ሜዳ ተጥሎ ተረስቶ
በበረሃው ንዳድ ነፍሮና ፈንድቶ
ካፋፉ ከፈፋው ተጥሎ በስብሶ
ገላው ተፈርክሶ ዐይነ-ውሀው ፈስሶ
በ’ድሉ አማሮ በውስጡ አልቅሶ
አመድ ተከናንቦ የሀፍረት ሸማ ለብሶ
የሠው አፈር በልቶ፤ አሸዋውን ቅሞ-ድንጋይ ተንተርሶ፤
አንገቱ ተቀልቶ ደሙ እየፈሰሰ፤ እየተገረፈ-እየተገፈፈ
የልቡ ሳይሞላ-ሕልሙ ሳይሳካ፤ ዘር-ዘርን ሳይተካ ወገን ተላለፈ፤
ቤት እንደሌለው ዘር- እንደ ወፍ ዘራሹ፤ እንደ ዛፉ ፍሬ በስብሶ ረገፈ።
ዘር ዘርቶ ያጣ አገር ዘር እየናፈቀ
ፍሬው ከቤት ወጥቶ ካፈሩ እየራቀ
መከራን ከችግር እያፈራረቀ
በበረሃው ሀሩር – በአሸዋው ንዳድ እየተቃጠለ
ተስፋ እየዘገነ ላጣው እያደለ
እንግልቱ ዜጋ ቀድሞም ያልታደለ፤
በባህር በየብሱ ስቃይ ተቀበለ
ሞትን እንደጽዋ እየተቃመሠ ባላለበት ዋለ።
ዛፉም መካን ሆነ ላያብብ ወሰነ
አፈሩ ነጠፈ – ካገሩ እየሸሸ – ከነፈ በነነ
አበባው አኩርፎ በሐዘን ዘጎነ
መሬቱ አመረረ በፍጡር ጨከነ
ወገን አንገት ደፋ፤ ልቡ ተሠበረ፤ ነደደ በገነ።
ከቤት የወጣ ዘር ካገሩ እየራቀ
ዘር ዘርቶ ያጣ አገር ዘር እየናፈቀ
እንደ ሾላው ፍሬ ነቀዝ እንደበላው
እንደ ወፍ – ዘራሹ ፈላጊ እንደሌለው
እንዳበደ ውሻ መርዝ እንደጎረሠው
እንደ ዛፍ – ቅጠሉ ደርቆ እንደሚነደው
ጠውልጎና ደርቆ ወድቆ ተገንድሶ
በበረሀው አረር ተቃጥሎ ተጠብሶ
በናፍጣ በቤንዝን ርሶና ረስርሶ
ደግሞ አመድ ይሆናል በ’ሣት ተለኩሶ።
ወገን እንደሌለው ካብራክ እንዳልዎጣ
ምድር እንደጠፋው መብቀያ እንዳጣ
ዕድሉ ሆነና የመጎሣቆሉ – መከራና ጣጣ
በተሰደደበት በቁሙ ተቀጣ
የሀገሬ ፍሬ የወንዜ ዘር – ሀረግ የሞት ፅዋ ጠጣ።
ይህን ያህል ውርደት እንዲህ ዓይን ያወጣ
ነፍስን የሚኮንን ሥጋን የሚቀጣ
ጭንቅን እያበዛ፤ ፈተናን የሚያከብድ የፈጣሪ ቁጣ፤
ከእኛ ላይ እንዲወርድ ዳግም እንዳይመጣ
እባክህ ፈጣሪ ወይ ውረድ ወይ ፍረድ
ወይ እኛን ‹‹ሰው›› አርገን – ወይ ምድሪቱን ውሰድ።
ሙሴ ደለለኝ (ጀኔቭ 2015)
በተሰደዱበት ቦታና ሥፍራ (በሄዱበት ሁሉ) ተነግሮ የማያልቅ መከራና ግፍ ለተፈፀመባቸው ወገኖቼ ማስታወሻ ትሁንልኝ
***********
ስለብልጽግና በሚናገርበት ጊዜ ስለድህነትም
በፈረንጅ ‹‹Dialectic›› ይሉታል፡፡ ቃሉ ከጥንት ግሪክ የመጣ ነው፡፡ ትርጓሜውም በመጀመሪያ ጥያቄና መልስ ወይም ክርክር ማለት ነበር፡፡ ከጊዜ ብዛት ሌላ ዘይቤ ወስዶአል፡፡ ዋናው ሄግል የሚባለው የጀርመን ፈላስፋ የወሰነው ነው፡፡ ይህም ባጭሩ ሕገ ተቃርኖ ተብሎ ሊሠየም ይቻላል፡፡ ሕሊናችን የሚሠራው በማናቸውም ጊዜ በዚህ ሕግ እየተመራ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል አንድ አስተማሪ ስለነፃነት አኀዝ (Term) በሚናገርበት ጊዜ ግድ ሕሊናው መርቶት ስለባርነትም መናገር አለበት፡፡ ስለብልጽግና በሚናገርበት ጊዜ ስለድህነትም መናገር አለበት፡፡ ምክንያቱም አንዱ አኀዝ ከሌላው ከተቃራኒው ጋር በሕሊናችን ውስጥ ተፃምሮ ስለሚገኝ ነው፡፡ ሁለቱ ሊለያዩ አይችሉም፡፡ ያንዱ አላድ ሁለት መልክ ናቸው፡፡ ሕሊናችን ወይም መንፈሳችን የሚሠራው እንደ ግድግዳ ሰዓት እንጥንጥል ካንዱ አኀዝ ወደ ተቃራኒው በመመለስ ነው፡፡ በሁለቱ ተቃራኒነት ሕሊና የነገሩን ጠባይዕ ስለሚረዳ ከሦስተኛው ቦታ ይደርሳል፡፡ እዚህ ዘንድ ተቃራኒነታቸው ቀርቶ ተፃማሪ ይሆናሉ፡፡
እሊህ ሦስት የሕሊና ተግባሮች በፈረንጅ ቋንቋ ሦስት ስሞች አሉዋቸው፡፡ ‹‹thesis, antithesis, synthesis›› በአማርኛችን አንብሮ፣ ተቃርኖ፣ አስተፃምሮ ብለናቸዋል፡፡ እሊህን አኀዞች በምሳሌ ለማስረዳት እንሞክራለን፡፡ ስለማኅበራዊ ኑሮ ሥነ ሥርዓት ሦስት የጥንት ዘመን ግሪኮች በአንድ ቦት ቁጭ ብለው ሲከራከሩ አንዱ ከሌሎቹ ቀደም ብሎ አንድ ይግዛ የሚል ፍርድ ያስቀምጣል፡፡ ይህንን አንብሮ እንበለው፡፡ ሁለተኛውም ደግሞ ተቀዳሚውን በመቃወም ሁሉም ይግዛ የሚል ተቃራኒ ፍርድ ያስቀምጣል፡፡ ይህንን ተቃርኖ እንበለው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ የቀደሙትን ሁለት ፍርዶች አነጻጽሮ ሳይሽር በማፃመር የሚችል ይግዛ ይላል፡፡ ይህንን አስተፃምሮ እንለዋለን፡፡ በሦስተኛው ፍርድ ተቀዳሚዎቹ ሁለቱ ፍርዶች ተፃምረው ይገኛሉ፡፡ የሚችል አንድም ብዙም ሊሆኑ ይችላሉ ማለት ነው፡፡ በዚህ የሐሳብ ዘዴ መሠረት ሦስት የሐልዮት ሕንፃዎች ሲስቴሞች ስለ አገዛዝ ተፈጥረዋል፡፡ አንድ ይግዛ ያለው ሞናርሽስት ይባላል፡፡ ሁሉም ይግዛ ያለው ዲሞክራት ይባላል፡፡ የሚችል ይጋዛ ደግሞ ያለው አሪስቶክራት ይባላል፡፡ እነዚህ ሦስት ተከራካሪዎች ከዚህ የደረሱት ሕሊናቸው በሕግ ተቃርኖ በዲያሌክቲክ እየተመራ ይራመድ ስለነበር ነው፡፡
- እጓለ ገብረ ዮሐንስ ‹‹የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ›› (1956)
***********
ሕይወትን በአራቱ ወቅቶች
አራት ልጆች የነበሩት አንድ ሰው ነበር፡፡ እናም ልጆቹ በነገሮች ችኩል እንዳይሆኑና ቀድመው ማደማደምን እንዳይለምዱ የሕይወት ትምህርት ያስተምራቸው ዘንድ ወደደ፡፡ ስለሆነም ከአካባቢያቸው በብዙ ርቀት የሚገኝ ዛፍን አይተው ያዩትን ነገር ይዘው እንዲመጡ ተልዕኮ ሰጥቶ አሰማራቸው፡፡ የመጀመሪው ልጅ፡ በበጋ ሁለተኛው በበልግ ሦስተኛው በክረምት አራተኛውና የመጨሻውን በመከር ደርሰው ያዩትን ይዘው እንዲመለሱ አደረገ፡፡ የመጀመሪያው ያየውን ሲያቀርብ…ዛፉ በጣም አስጠሊታ ነው፡፡ ተጣጥፏል፣ ተሰባብሯልም አለ፡፡ ሁለተኛው ቀጠለ በአረንጓዴ ልምላሜ የተሞላ ቅርንጫፍ አውጥቷል፣ ለወደፊትም የማፍራት ተስፍ ይታይበታል ሲል ያየውን አብራራ፡፡ ሦስተኛው በዚህ አባባል አልተስማማም፤ እሱ ያየውን ለአባቱ ሲያቀርብም ዛፉ በአበባ ተጨናንቋል ያበቦቹ መዓዛም እጅግ ያውዳል እናም በጣም ቆንጆ ነው፡፡ እንደዛ አስደሳች ነገር ከዚህ በፊት በሕይወቴ አላየሁም ሲል ባግራሞት ተናገረ፡፡ የመጨረሻው ልጅ ቀዳሚዎቹ ሦስቱ ወንድሞቹ ባቀረቡት አልተስማማም፡፡ እናም እንዲህ አለ ዛፉ በበሰሉና እጅግ ባማሩ ፍሬዎች ተጨናንቋል፣ ሕይወትንም በደስታ ይሞላል፡፡ አባት የሁሉንም እይታ ካዳመጠ በኋላ ሁላችሁም ትክክል ናችሁ ምክንያቱም ያያችሁት አንድ ዛፍ ቢሆንም ያያችሁበት ወቅት ግን ለዛፉ ሕይወት የተለያየ ትርጉም ባለበት ወቅት ነው፡፡ አስከትሎም እንዲህ አላቸው ሰውንም ሆነ ዛፍን በአንድ ወቅት ገጽታ ብቻ እንዲህ ነው ብሎ መናገር አይቻልም፡፡ ሕይወትን በችግራችን ወቅት ብቻ ከተረጐምናት፤ በበጋው ዛፉ ደርቆ እንደታየው ካየናት እንጠላታለን፣ የበልጉን ተስፋና የክረምቱን ውበትም አናየውም፡፡ የሕይወት ጥፍጥና የሚመዘነው በሁሉም ወቅቶች ድምር እንጅ አንደኛው ወቅት በፈጠረው ገጽታ ብቻ አይደለም ፡፡
(ምሥጋናው ግሸን ወልደ አገሬ)
****************
ጡንቻ ሳይሆን አእምሮ
እንስሳት ሁሉ ተሰብስበው አደን ተሰማርተው ብዙ ግመሎችን በመያዝና በመግደል ተከፋፍለው በሏቸው፡፡ ከመብላታቸው አስቀድሞ ግን ቀበሮ ብድግ ብሎ “አንድ ግዜ አድምጡኝ ወንድሞቼ! ምን እንደሚያበሳጫችሁ ንገሩኝና ወደፊት በስህተት አላበሳጫችሁም፡፡” አላቸው፡፡ እነእርሱም በሃሳቡ ተስማምተው የእርስ በእርሳቸውን ጥንካሬና ድክመት ማወቅ እንዳለባቸው ወሰኑ፡፡
እናም አንበሳው በመጀመሪያ እንዲህ አለ፡፡ “እኔ እምብዛም የምጠላው ነገር የለም፡፡ ነገር ግን ሌሊት መተኛት አልችልም፡፡ የምተኛው ጠዋት ላይ በመሆኑ ድምፅ መስማት አልወድም፡፡”
ከዚያም ጅብ ቀጠለ “እኔ ሆዴ ላይ ሲመቱኝ አልወድም፡፡” አለ፡፡
ቀጥሎ ነበር እንዲህ አለ “እኔ ብዙም ችግር የለብኝም፡፡ ነገር ግን ማንም እንዲያስፈራራኝ፣ አትኩሮ እንዲያየኝም ሆነ እንዲያፈጥብኝ አልፈልግም፡፡”
ከዚያም እባብ “ስተኛ እስካልረገጣችሁኝ ድረስ ሌላ ምንም ነገር አያበሳጨኝም፡፡” አለ፡፡
ከርከሮም ቀጥሎ “ግር እያልኩ ስሄድ ወይም ስደነግጥ ጆሮዬ ውስጥ ቢጮሁብኝ በጣም ያበሳጨኛል፡፡” አለ፡፡
በመጨረሻም ሁሉም ወደ ቀበሮ ዞረው አንተስ?” ሲሉት እኔ እንደተላላኪ ልጅ ወዲያ ወዲህ ሲያዙኝ አልወድም፡፡” አለ፡፡ በዚህ ሁኔታ ከቆዩ በኋላ ትንሽ ስጋ በልተው ተኙ፡፡
ከዚያም ቀበሮ ወደ ነብሩ ጠጋ ብሎ “ተመልከት፣ ጅቡ ተኝቷል፡፡ እናም ሆዱን እንውጋው፡፡” አለው፡፡
ነብሩም “አይሆንም፡፡ አንድ እንስሳ አልወድም ካለ ያለውን ነገር ማክበር አለብን፡፡” አለው፡፡
ሆኖም ቀበሮው “እሱ ፈሪ ነው እኮ፡፡ ጅብ ፈሪ ነው፡፡
ትፈራዋለህ እንዴ?” ብሎ ሞገተው፡፡
ነብሩም “እባክህ ተወው፡፡” አለው፡፡
ነገር ግን ቀበሮው ዘሎ የጅቡን ሆድ ረገጠው፡፡ ጅቡም ዘሎ በንዴት በመነሳት ከነብሩ ጋር ተፋጠጠ፡፡ እናም ነብሩ ማስፈራራትን ይጠላ ነበርና ሁለቱ መጣላት ጀመሩ እየተንከባለሉም ከተኛው አንበሳ ጋር ተጋጩ፡፡ አንበሳውም በጣም ተናዶ በመነሳት ሁለቱንም ገደላቸው፡፡
ከዚያም መለስ ሲል እስሩ የነበረውን እባብ በስህተት ረገጠው፡፡ ጥፍሮቹ እባቡን ገደሉት፡፡ ሆኖም እባቡ ቀድሞ ነድፎት ስለነበረ አንበሳውም ሞተ፡፡ በዚህ ሁሉ ብጥብጥ ውስጥ ከርከሮ ደንብሮ መሮጥ ጀመረ፡፡ ቀበሮውም ጆሮው ውስጥ ስለጮኸበት ከርከሮ ከፍራቻው የተነሳ ገደል ውስጥ ገባ፡፡ በዚህ ግዜ ቀበሮው እስኪጠግብ በላ፡፡ ከዚያም ወደ አንበሳው አስክሬን ሄዶ ቆዳውን በሳር በመሰግሰግ ያልሞተ አንበሳ አስመሰለው፡፡ ከዚያም በአካባቢው ሲያማትር አንድ ሌላ ቀበሮ አገኘ፡፡
ከዚያም እንዲህ አለ፡፡ “አንተ ምስኪን ቀበሮ፣ እኛ ከጥጋባችን የተነሳ በስጋ ኳስ እንጫወታለን፡፡ አንተ ግን ተርበህ አመድ ላይ ትንከባለላለህ፡፡ በል ናና አንድ አጥንት ብላ፤ ነገር ግን አጎቴ አያ አንበሳ ስለተኛ ምንም አይነት ድምፅ እንዳታሰማ ፤ ከነቃ ይገድልሃል፡፡” አለው፡፡
እናም የተራበው ቀበሮ ሲመጣ ጥጋበኛው ቀበሮ ብዙ አጥንቶች ያሉበትና ድምፅ የማያወጣ አከርካሪ አጥንት ሰጠው፡፡ ቀበሮውም በጣም በመጠንቀቅ ድምፅ ሳያሰማ እየበላ ሳለ ሰተንኮለኛው ቀበሮ ምን እያደደረገ እንደሆነ አላስተዋለም፡፡ ተንኮለኛው ቀበሮ የተራበውን ቀበሮ ጅራት ከተጠቀጠቀው አንበሳ ጋር እየሰፋው ነበር፡፡
ከዚያም “ተጠንቀቅ! ተጠንቀቅ! አጎቴ ተነስቷል፡፡” አለው፡፡ ቀበሮውም መሮጥ ጀመረ፡፡ ነገር ግን የአንበሳው አካል ጅራቱ ላይ ተሰፍቶበት ስለነበረ አንበሳው እየተከታተለው መስሎት በድንጋጤ ገደል ውስጥ ገባ፡፡
ይህ የሚያመለክተው በህይወት ጫካ ውስጥ ስኬታማ ለመሆን ጠንካራ መሆን ሳይሆን ብልጥ መሆን ማስፈለጉን ነው፡፡
- በመሐመድ አህመድ አልጋኒ የተተረከ የአፋር ተረት