ሻሜት መጠጥ ማለት ልዝብ መጠጥ ነው፤ ለሰውም ጤና ነው፤ እንደ ሸርበት ነው፡፡ አበጃጀቱ ገብስ እጅግ ሳይገባው ተቆልቶ ይፈጫል፤ ቀጥሎ በወንፊት ይነፋል፡፡ ቀጥሎ ማር አንጥሮ በመጠን ተገብሱ ዱቄት ጋራ ውኃ ጨምሮ፣ በውል አሽቶ በማጥርያ አጥርቶ፣ በገምቦም ሆነ በጠርሙዝ ይቀመጣል፡፡ ውኃ ከገብሱ ዱቄት ሲጨመር መወፈርና መቅጠኑን ባለቤት እንደወደደ ነው፡፡ ሲቀመጥ እድሜው የሦስት ቀን ብቻ ነው፤ ተዚያ ወዲያ መሆምጠጥ ይጀምራል፡፡
ውኃ ሳይገባ በማር ብቻ የገብሱ ዱቄት የታሸ እንደሆነ ስሙ በሶ ይባላል፤ የመንገድ ስንቅ ነው፡፡ ከተሰፈረበትም በማር ከታሸው በሶ በውኃ በጥብጦ ያው ሻሜት ይሆናል፡፡ ደግሞ አንዱ ዓይነት በሶ ውኃና ጨው በዱቄቱ ገብቶ ይታሻል፡፡ ሦስተኛ ዓይነት ደሞ ጨው ብቻ ገብቶ ዱቄቱ ደረቅ እንደሆነ ይያዛል፤ ሲፈለግ በውኃ ይታሻል፡፡
- ማጆር ጄ.አይ.ኢዲ ‹‹የአማርኛ መድበለ ምንባብ››፣ (እ.ኤ.አ. በ1924)