Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየሰማያዊ ፓርቲን የገንዘብ ምንጭ ለማወቅ ምርመራ ተጀመረ

የሰማያዊ ፓርቲን የገንዘብ ምንጭ ለማወቅ ምርመራ ተጀመረ

ቀን:

‹‹በፋይናንስ ግኝታችን ጥያቄ ሊነሳ አይገባም›› ሰማያዊ ፓርቲ

በኢትዮጵያ ፖለቲካ አነጋጋሪ ሆኖ ብቅ ያለው ሰማያዊ ፓርቲ ለ2007 ዓ.ም. ምርጫ ይፋ ያደረገው የበጀት መጠን ‹‹ከፍተኛ መሆን››፣ የውጭ ፋይናንሰሮች እጅ አለበት የሚል ጥርጣሬ በማስነሳቱ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑ ተጠቆመ፡፡

ሰማያዊ ፓርቲ ለዘንድሮ ምርጫ 92 ሚሊዮን ብር በጀት እንደያዘ ካስታወቀ በኋላ፣ ከሚያነሳቸው ፖለቲካዊ አጀንዳዎች በተጨማሪ የያዘው በጀት መጠን የወቅቱ መነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ ሆኗል፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ መንግሥት ሰማያዊ ፓርቲ ለምርጫው በያዘው በጀት መጠን ላይ ጥርጣሬ አለው፡፡

‹‹ሰማያዊ ፓርቲ ይህንን ገንዘብ ሊያመነጭ የሚችልበት መንገድ የለውም፡፡ ምክንያቱም በግልጽ እንደሚታወቀው ኮንሰርት አላዘጋጀም፡፡ ከባለሀብቶች የተዋጣ ገንዘብ የለም፡፡ ምርጫ ቦርድ የመደበለት ገንዘብም ይታወቃል፤›› ያሉት አቶ ሬድዋን፣ ‹‹አባላቱ ይህንን ገንዘብ ሊያዋጡ የሚችሉ ቱጃሮች አይደሉም፡፡ በቁጥርም አነስተኛ ናቸው፤›› በማለት ገንዘቡ ሕጋዊ መሠረት የለውም የሚል ትንታኔ ይሰጣሉ፡፡

አቶ ሬድዋን እንደሚሉት፣ ሰማያዊ ፓርቲ 92 ሚሊዮን ብር በጀት ይዣለሁ በማለት በይፋ ሲያውጅ የማይነጥፍ የሀብት ምንጭ  አለው ማለት ነው፡፡ ይህ የሀብት ምንጭ ደግሞ በእርግጠኝነት ሕገወጥ ነው በማለት በገንዘቡ ጤናማነት ላይ መንግሥት ያለውን ጥርጣሬ አስገንዝበዋል፡፡

በዋናነት የመንግሥት ጥርጣሬ ትኩረት የሚያደርገው ሰማያዊ ፓርቲ ይህንን ገንዘብ፣ በተለያዩ አገሮች ከሚገኙ ሕጋዊነት ከሌላቸው አካላት ፈሰስ ተደርጎ ሊሆን ይችላል የሚል ነው፡፡

አቶ ሬድዋን የአገሪቱ የባንክ ሥርዓት የዚህ ዓይነት የገንዘብ ዝውውሮችን ለመቆጣጠር ያን ያህል የዳበረ አሠራር ያለው አይደለም ይላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ያለመፈተሽ መብት ባላቸው ሰዎች አማካይነት የሚገባ ገንዘብ ይኖራል በማለት ያክላሉ፡፡

መንግሥት እነዚህን ምልክቶች ማስተዋሉን የሚናገሩት አቶ ሬድዋን፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ምርመራ እያካሄዱ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በተለይ ከፓርቲዎቹ ጋር በተያያዘ በሕግ ኃላፊነት የተሰጠው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ለፓርቲዎች ያከፋፈለውን በጀትና ለምርጫ የወጣውን ሒሳብ ኦዲት በሚያደርግበት ወቅት ሊታወቅ የሚችል እውነታ መሆኑን እየገለጸ ነው፡፡

ለገዥው ፓርቲ መሪዎች ያስደነቀው ግን ከተመሠረተ ሦስት ዓመታት ብቻ ያስቆጠረው ሰማያዊ ፓርቲ፣ ለዘንድሮ ምርጫ 92 ሚሊዮን ብር መያዙ ብቻ ሳይሆን፣ ይህ ገንዘብ ኢሕአዴግ ከያዘው በጀት መብለጡ ነው፡፡

የኢሕአዴግ የሕዝብና የውጭ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደስታ ተስፋው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሰማያዊ ፓርቲ የያዘው በጀት ኢሕአዴግ ከያዘው በጀት ጋር ሲነፃፀር እጅግ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ኢሕአዴግ በ2002 ዓ.ም. ምርጫ 23 ሚሊዮን ብር በጀት የመደበ መሆኑን፣ በ2007 ዓ.ም. ምርጫ የያዘው በጀትም ከ23 ሚሊዮን ብር እንደማይበልጥ የኢሕአዴግ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ረዳኢ ሓለፎም ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የሰማያዊ ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ በዚህ ሐሳብ አይስማሙም፡፡ ምክንያቱም ሰማያዊ ፓርቲ ይህንን በጀት የያዘው በግንቦት 2007 ዓ.ም. ምርጫ ከያዘው ግብ አኳያ ነው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ ፓርቲው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 500 ዕጩዎችን ለምርጫ አቅርቦ 380 መቀመጫ በማሸነፍ ከገዥው ፓርቲ ሥልጣን ለመረከብ ግብ አስቀምጧል፡፡ ነገር ግን 200 ዕጩዎች ከምርጫ ውድድር ውጪ በመሆናቸውና በአንዳንድ አካባቢዎች የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ ባለመቻሉ፣ የተያዘውን በጀት ለመጠቀም አለመቻሉን አቶ ዮናታን ተናግረዋል፡፡

‹‹እየተደረገብን ባለው ተፅዕኖ የተያዘውን በጀት ለመጠቀም አልተቻለም፤›› ያሉት አቶ ዮናታን ጨምረው እንደገለጹት፣ ይህንን በጀት ፓርቲያቸው የቀረፀው ማንኛውም ባለበጀት መሥሪያ ቤት ለሚያካሂደው ሥራ የሚያስፈልገውን በጀት እንደሚያዘጋጀው ነው፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ከዚህ አንፃር የተለያዩ ቲሸርቶችን በመሸጥ፣ ከአባላት ከሚገኝ መዋጮ፣ የፓርቲውን ዓላማ ከሚደግፉ ባለሀብቶች፣ አውሮፓና ከሰሜን አሜሪካ ከሚገኙ ደጋፊዎች ይህንን ገንዘብ ማሰባሰቡን ገልጸዋል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 800 ሺሕ ብር ያገኘ መሆኑንም አቶ ዮናታን ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

‹‹በፋይናንስ ግኝታችን ጥያቄ ሊነሳ አይገባም፡፡ በውስጥና በውጭ ኦዲት ሒሳቡ በሚመረመርበት ወቅት በግልጽ ይታወቃል፤›› ሲሉ አቶ ዮናታን ከፓርቲያቸው ላይ የተሰነዘረው ክስ መሠረተ ቢስ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...