– የአገሪቱ የኃይል ብክነት መጠኑ ጨምሯል
ከሁለት ሳምንታት በፊት በቱርክ በተደረገ ጉብኝት፣ መንግሥት ከቱርክ ባለሀብቶች ጋር የኃይል ማመንጨትና ማሠራጨት ሥራዎች ላይ የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሙ ተገለጸ፡፡ ስምምነቱ ወደ ተግባር የሚለወጥ ከሆነ የቱርክ ባለሀብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ያመነጩትን ኃይል ለመንግሥት በሽያጭ ያቀርባሉ፡፡
ሚያዝያ 28 ቀን 2007 ዓ.ም. 24 የቱርክ ባለሀብቶች በሸራተን አዲስ ከኢትዮጵያውያን የንግድ ማኅበረሰብ አባላት ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ የተገኙት፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አዜብ አስናቀ ለጋዜጠኞች እንዳስታወቁት፣ ከቱርክ ኩባንያዎች ጋር የተደረገው የመግባቢያ ስምምነት ተግባራዊ ከተደረገ በኃይል ማመንጫና በማሠራጫ ሥራዎች ይሰማራሉ፡፡ መንግሥት በበኩሉ ከቱርክ ኩባንያዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ግዥ ይፈጽማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ስምምነቱ ተግባራዊ ሲደረግ የግዥና የሽያጭ ታሪፍ ከወዲሁ መዘጋጀት እንደሚጀምር ይፋ አድርገዋል፡፡
ምንም እንኳ በዝቅተኛው የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከ300 ሜጋ ዋት ኃይል ያላነሰ ማመንጨት የሚቻል ቢሆንም፣ የቱርክ ባለሀብቶች ግን ከ500 ሜጋ ዋት ጀምሮ ባለው ከፍተኛ መጠን ኃይል ማመንጫ ግንባታዎች ላይ ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ኢንጂነር አዜብ አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል በአገሪቱ ከሚመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥ በማስተላለፊያና በሥርጭት መስመሮች ምክንያት የሚባክነው የኃይል መጠን ምን ያህል እንደሆነ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ኢንጂነር አዜብ፣ መጠኑን ለመግለጽ ትክክለኛ አኃዝ እንደሚያስፈልጋቸው፣ ከዚህ ይልቅ ግን በአገሪቱ የሚታየው የኃይል ብክለት ተቀባይነት ካለው ወሰን በላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ምንም እንኳ በሥርጭትና በኃይል ማስተላለፍ ወቅት የሚከሰተውን የኃይል ብክለት ማስቀረት በየትኛውም ዓለም የማይቻል ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ግን መጠኑ ከፍተኛ መሆኑን አምነዋል፡፡
የዓለም አቀፍ የኢነርጂ ኤጀንሲ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ አምና ይፋ በተደረጉ መረጃዎች መሠረት ኢትዮጵያ ከምታመርተው ጠቅላላ የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን ውስጥ 20 በመቶ ያህሉን በሥርጭትና በማስተላለፍ ሒደት ውስጥ ታጣለች፡፡ ይህ ከዓለም አቀፍ አማካይ የ13 በመቶ መጠን ብክነት አኳያ ከፍተኛው እንደሆነም መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ብክነቱ በዚህ መጠን ከቀጠለ በዚህ ዓመት ይኖራል ተብሎ በተሰጋው ብክነት 700 ሜጋ ዋት ኃይል ሊታጣ እንደሚችል ይገመታል፡፡ በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን 2,268 ሜጋ ዋት ሲሆን፣ አብዛኛውም ከውኃ የሚመነጭ ነው፡፡
ኢንጂነር አዜብ አሁን የሚመሩትን ተቋም ከመቀላቀላቸው ቀድሞ በግልገል ጊቤ ሦስት የፕሮጀክት ኃላፊ በመሆን ሠርተዋል፡፡ በዚህ ዓመት መጨረሻ በተወሰነ መጠን ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር የሚጠበቀው ጊቤ ሦስት፣ በጠቅላላው 1,870 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያመነጭ ይጠበቃል፡፡ በአሁኑ ወቅት በተወሰነ ደረጃ ምርት ለማስጀመር ከዝናብ የሚገኘው ውኃ በግድቡ እስኪሞላ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ40 በመቶ በላይ መገባደዱን ያስታወሱት ኢንጂነር አዜብ፣ የገናሌ ዳዋ ኃይድሮ ፕሮጀክት ግንባታም 70 በመቶ መድረሱን ጠቁመዋል፡፡ ገናሌ ዋዳ ግድብ 250 ሜጋ ዋት ኃይል ያመነጫል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ምንም እንኳ እነዚህ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ ቢሆንም፣ ከፍተኛ የኃይል መቆራረጥና ከነጭራሹም የኃይል ሥርጭት መቋረጥ ችግሮች በተደጋጋሚ እየተከሰቱ ይገኛሉ፡፡ ይህ በመሆኑም የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች በተደጋጋሚ ቅሬታቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል፡፡ የውጭ ኩባንያዎች የኃይል አቅርቦት ችግርን በመፍራት ከመምጣት እየታቀቡ እንደሆነ የሚገልጹም አልታጡም፡፡ ኢንጂነር አዜብ በበኩላቸው የኃይል መቆራረጥ ችግሮች ጊዜያዊ እንደሆኑ ያምናሉ፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ የኤሌክትሪክ ምርቶችና መገልገያዎች አምራች የሆኑ 24 የቱርክ ኩባንያዎች፣ ከንግድ ማኅበረሰቡ አባላት ጋር የእርስ በርስ የንግድ ግንኙነት ለመፍጠር ውይይትና ድርድር ማድረጋቸው ታውቋል፡፡ ኢስታንቡል ኤሌክትሪካል፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ማሽነሪና የአይሲቲ ውጤቶች ኤክስፖርተሮች ከተባለው የንግድ ማኅበር የተውጣጡት ነጋዴዎች፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ምርቶቻቸውን የሚረከብ ለማግኘት ከኢትዮጵያ ኩባንያዎች ጋር አብሮ ለመሥራት የማኅበራቸው አባላት ፍላጎት ስላላቸው መምጣታቸውን፣ የማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ ፋቲህ ከማል ገልጸዋል፡፡ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ የንግድ ልዑካኑ በሱዳን ጉብኝት እንደሚያደርጉም ታውቋል፡፡