Friday, April 19, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ድህነትንና ስደትን ለመቀነስ ዴሞክራሲንና ልማትን ማቆራኘት ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ አገራችን በዓለም ፊት የሚያኮሯት አንፀባራቂ ታሪኮች ባለቤት ብትሆንም፣ በፀረ ኮሎኒያሊስት ትግል ተወዳዳሪ ባይገኝላትም፣ በተለያዩ ጊዜያት ሊወሯት የመጡትን በሙሉ አሳፍራ በመመለስ ብትታወቅም፣ ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች ተምሳሌት የሆነችና ለፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ መፈጠር መነሻ ምክንያት መሆኗ ቢታወቅም፣ ይህንን የተከበረና ኩሩ ሕዝብ አንገት ሲያስደፋ የኖረው ድህነት ግን አንደኛው የጨለመ ገጽታዋ ማሳያ ነበር፡፡ አሁንም ነው፡፡ ድህነት ብሔራዊ ክብርንና ማንነትን ያዋረደ የዘመናት ጠላት ከመሆኑም በላይ፣ አሁንም አገሪቱን እየተፈታተናት ያለ ክፉ ደዌ ነው፡፡ ድህነትን ለመቀነስ የሚደረገው የልማት ጥረት የአገራችንን ሕዝብ ብርቱ ትብብር ካላገኘ ችግሩ እየከፋ መሄዱ አይቀርም፡፡ ይህም አስመራሪ በሆነው ስደት እየታየ ነው፡፡

ድህነት የሚባለው አገራዊ ውርደት በፈጣን ልማት ታሪክ ለማድረግ መንግሥት ጥረቱን ማጧጧፉንና በዚህም ውጤት እያገኘ መሆኑን በተደጋጋሚ ሲናገር ሰምተናል፡፡ በእርግጥም በመሠረተ ልማቶችና በተለያዩ ዘርፎች እየታዩ ያሉ ለውጦች ተስፋ ሰጪ ናቸው፡፡ ነገር ግን ይህ የተጀመረ ልማት ከዴሞክራሲ ጋር ካልተቆራኘ አስቸጋሪ ነው፡፡ ድህነት የሚባለው ውርደት ከምንጩ መድረቅ እንዲኖርበት ሲፈለግ፣ ከልማቱ ጐን ለጐን ለዴሞክራሲም ትልቅ ትኩረት መሰጠት አለበት፡፡ ዜጐች አገራቸውን እየተው በገፍ በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች አማካይነት ለምን ይሰደዳሉ ተብሎ ጥያቄ ሲቀርብ ምክንያቱ በአመዛኙ ድህነት ነው ቢባልም፣ በመልካም አስተዳደር እጦትና በሰብዓዊ መብት አለመከበር ሳቢያ የሚሰደዱትን መዘንጋት ተገቢ አይደለም፡፡

በአሁኑ ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጐች ከአገራቸው ርቀው ተሰደው ይኖራሉ፡፡ በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በአውስትራሊያና ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የተሰደዱ ዜጐች በተለያዩ ምክንያቶች ከአገር መውጣታቸው ይታወቃል፡፡ በተለይ በመካከለኛው ምሥራቅና በደቡብ አፍሪካ በስደት የሚኖሩ ዜጐች የአገሪቱን የድንበር ኬላዎች እያቋረጡ በገፍ በአደገኛ ሁኔታዎች ውስጥ ሲሰደዱ ለአገር ክብር ጭምር ውርደት እየሆነ ነው፡፡ ወደ ደቡብ አፍሪካ በሚደረገው ሕገወጥ ስደት ብዙዎች በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ሲታሰሩና ሲንገላቱ፣ የአውሬ እራት ሲሆኑ፣ እንደ ምንም ሕይወታቸው የተረፈው ደግሞ በውጭ ዜጐች ጥላቻ በተለከፉ ሰዎች ሲገደሉና ጥቃት ሲፈጸምባቸው አይተናል፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅም ሲደፈሩ፣ ሲገደሉና ንብረታቸው ተቀምቶ ራቁታቸውን ሲባረሩ አይተናል፡፡ ይህ የአገር ውርደት መገለጫ ነው፡፡ የተከበረች አገር አንገቷን የደፋችበት ውርደታችን ነው፡፡

ይህ ዓይነቱ አደገኛ ክስተት አገሪቷንና ሕዝቧን አንገቷን እያስደፋ ሸክሙ በከበደበት ወቅት፣ በሊቢያ በረሃ በአረመኔዎች እጅ እነዚያ ወገኖቻችን አለቁ፡፡ በሊቢያ አድርገው አውሮፓ በመሻገር ያልፍልናል ብለው ለስደት የተዳረጉ ወጣቶች መርዶ በተሰማበት ወቅትም ሆነ ከዚያም በኋላ ለስደት የተነሱ መኖራቸው በስፋት ይነገራል፡፡ በተጨባጭም ተሰምቷል፡፡ ከድህነቱ መክፋት በላይ ሌላ ችግር ይኖራል የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡ ድህነቱ ዘመናትን የተሻገረ ጠባሳ ነው፡፡ የመልካም አስተዳደርና የሰብዓዊ መብት ጉዳይም እንዲሁ፡፡ ችግሩ ከኋላ የሚመዘዝ ታሪክ አለው ሲባል መፍትሔውም አንድ ላይ ይፈለጋል ማለት ነው፡፡ ልማትና ዴሞክራሲን ማመጋገብ የግድ ይላል፡፡ የችግሩ ግዝፈትም ይህንን ቁልጭ አድርጐ ያሳያል፡፡

ወጣቶችን ለስደት የሚያነሳሳው ምክንያት ሲፈተሽ በአብዛኛው ድህነት የፈጠረው ምሬት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ከዚህ ድህነት ጋር አብሮ ያለና ያደፈጠው ሌላ ችግር ደግሞ ከዴሞክራሲ እጦር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በይበልጥም ከመልካም አስተዳደር እጦት ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ ይህንን ችግር ለማወቅ የሚቻለው ደግሞ ወጣቱ ውስጥ የሚታየውን የተስፋ ቆራጭነት ስሜት ማንበብ ሲቻል ነው፡፡ ተስፋ ለምን ይቆረጣል? ወጣቱ በገዛ የአገሩ ጉዳይ የባይተዋርነት ስሜት ሲሰማው፣ ተሳትፎው ሲገደብ፣ ሐሳቡን በነፃነት የመግለጽና ሰብዓዊ መብቱ እንደማይከበርለት ሲረዳ ምርጫው ስደት ነው፡፡ የፖለቲካ ወገንተኝነት ከዜግነት የበለጠ እንደሆነ የተስፋ ቆራጭነት መጠኑ ያሻቅባል፡፡ ይህም መከፋትን ያመጣል፡፡ ለችግሮቹ አቤቱታ ሲያቀርብ ሰሚ ሲያጣ ደግሞ ስደትን የመጨረሻ አማራጭ ያደርጋል፡፡ ሥራ ለመጀመር የሚያስችል የተወሰነ ካፒታል ይዞ የሚደግፈውና የሚያበረታታው ፖሊሲ ሲያጣ የመጣው ይምጣ ብሎ የቋጠረውን ገንዘብ ለሕገወጦች አስረክቦ አገር ጥሎ ይጠፋል፡፡ ይኼ እንደ አገር ሁላችንንም ማሳሰብ አለበት፡፡

ስደት ብሔራዊ ክብርንና ኩራትን ያዋርዳል ሲባል፣ ዙሪያችንን የከበቡን ችግሮች አንድ በአንድ ተመንጥረው መታየት አለባቸው፡፡ የችግሩን ምንጭ ለማድረቅ ሲፈለግ ደግሞ ዴሞክራሲንና ልማትን በአንድ ላይ ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ ዴሞክራሲንና ልማትን እንደ መፍትሔ መቀበል ብቻ ሳይሆን፣ በተግባር ማረጋገጥ ተገቢ ነው፡፡ ከልማትና ከዴሞክራሲ ማን ይቅደም የሚለው የዶሮና የእንቁላል እንቆቅልሽ ቀርቶ፣ አፍጥጦ ለሚታየው ችግር ተግባራዊ ምላሽ መትጋት የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ በተጨማሪም ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎችና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ርብርብም እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ የአገራችንና የሕዝባችን ክብር ወደፊት ጭምር ሊከሰት ከሚችለው ውርደት የሚድነው በዚህ መንፈስ ችግሩ ሲጤን ነው፡፡

መንግሥት በተደጋጋሚ ችግሮቹ በዋነኛነት የሚመነጩት ከማስፈጸም መሆኑን እየተናገረ፣ ለዚህ ደግሞ የአቅም ግንባታ ቁልፍ ተግባር መሆኑን ያስረዳል፡፡ በአፈጻጸም ላይ ከሚታዩ ችግሮች መካከል አንዱ በተዋረድ ባለው መንግሥታዊ የሥልጣን መዋቅር ውስጥ የሚታየው ፖሊሲዎችን ያለመረዳትና ሥራን በአግባቡ ያለመወጣት ችግር፣ በመልካም አስተዳደር እጦት ላይ የራሱን አሉታዊ ሚና ሲጫወት ይታያል፡፡ የማስፈጸም ችግር አለ ሲባል በሹመት አሰጣጥ ላይ የጥራት ችግር አለ ማለት ነው፡፡ ይህም እንደ ተግዳሮት ተወስዶ መፍትሔ ይፈልጋል፡፡ የመንግሥትን ፖሊሲና ስትራቴጂ ማስፈጸም ያቃተው ሹም ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ቢጥስ አይገርምም፡፡ በየቦታው ያሉ ችግሮች እንዲህ ያሉ መፍትሔዎችን ጭምር ይፈልጋሉ፡፡ የግድ ነው፡፡

ድህነትን እንደ ብሔራዊ ውርደት እቆጥራለሁ የሚለው መንግሥት በስደት ምክንያት የአገሪቱ ገጽታ ሲበላሽ ቆሞ ማየት የለበትም፡፡ ስደተኞች ባህር ውስጥ ሰጠሙ፣ ተደበደቡ፣ ተደፈሩ፣ ተገደሉ፣ ተዘረፉ፣ ወዘተ በተባለ ቁጥር አገር ሲያባንናት ማየት የውርደቱ አንድ ትልቅ ማሳያ ነው፡፡ ዜጎች አገር እያላቸው እንደሌላቸው ሆነው ዘግናኝ የሆኑ በደሎች ሲፈጸምባቸው እያየን ነው፡፡ ይህም ውርደት ነው፡፡ ከድህነት እላቀቃለሁ ብላ የምትተጋ አገር እየተፈጠረች ነው ሲባል፣ ለዜጐቿ የምትመችና ተስፋ የሚደረግባት መሆኗን ለማሳየት የሚረዱ ተግባራዊ ዕርምጃዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ተግባራዊ ዕርምጃዎችም ዴሞክራሲንና ልማትን ያጣጣሙ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ከወገናዊነት የፀዱና ዜጐችን በአንድነት የሚያሰባስቡ ዘለቄታዊነት ያላቸው ዕርምጃዎች፡፡

የዚህ ዘመን ስደት አስፈሪ ነው፡፡ ወትሮም በሁሉም ሥፍራዎች ስደተኞችን ለመቀበል ያለው ፍላጐት ቀዝቃዛ ከመሆኑም በላይ፣ አሁን ደግሞ በጣም ብሶበት አትምጡብን እየተባለ ነው፡፡ የመጣው ይምጣ ብለው በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች አማካይነት ድንበር አቋርጠው የሚሰደዱ ዜጐችን ከመምከር በላይ፣ በአገራቸው ኮርተውና አንገታቸውን ቀና አድርገው የሚራመዱበትን ፖሊሲ ማመቻቸት የግድ ይላል፡፡ የስደትን ምንጭ ማድረቅ የሚቻለውም የአገሪቱ ዜጐች በገንዘባቸው፣ በጉልበታቸውና በዕውቀታቸው ለዚህ የተቀደሰ ተግባር እንዲረባረቡ ብሔራዊ ጥሪ ሲደረግ ነው፡፡ የዜጐችን ተሳትፎ ከፍ ማድረግ ሲቻል ልማቱንና ዴሞክራሲውን ማመጋገብ ይቻላል፡፡ የሁለቱ ቁርኝት ደግሞ የአገር የውርደት መገለጫ የሆኑትን ድህነትና ስደትን ለመቀነስ ይጠቅማሉ፡፡ ዴሞክራሲ የህልውና ጉዳይ ነው ሲባል የምር መሆን አለበት፡፡ ልማት ከድህነት መውጪያ በር ነው ሲባል ሁሉንም ወገን እኩል ተጠቃሚ ማድረግ አለበት፡፡ ሁለቱ አንድ ላይ ሲቆራኙ ውጤቱ አመርቂ ይሆናል፡፡ ለዚህም ተግባራዊ ዕርምጃ ያስፈልጋል!                        

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...

እጥረትና ውጥረት!

ጉዞ ከስድስት ኪሎ ወደ ቃሊቲ፡፡ ‹‹ይገርማል ቀኑ እንዴት ይሄዳል?››...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለፋይዳ ቢስ ጉዳዮች የሚባክነው ጊዜና ሀብት ያሳስባል!

ኢትዮጵያ በወጣት የሰው ኃይል፣ ዕውቀትና ልምድ ባካበቱ አንጋፋዎች፣ በሰፊ ለም መሬት፣ በአፍሪካ ተወዳዳሪ በሌለው የውኃ ሀብት፣ በበርካታ የማዕድናት ዓይነቶች፣ ብዛት ባላቸው የቱሪዝም መስህቦችና የአየር...

የማፍረስ ዘመቻው በብልሹ አሠራሮች ላይም ይቀጥል!

መንግሥት በኮሪደር ልማት አማካይነት የአዲስ አበባ ከተማን ዋና ዋና ሥፍራዎች በማፍረስ፣ አዲስ አበባን ከኬፕታውን ቀጥሎ ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡...

ለድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞም ማስተንፈሻ ይሰጥ!

በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መንግሥት ዋነኛ ሥራው በሕግ መሠረት የተሰጡትን ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት ነው፡፡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ የአገርን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር፣...