Friday, September 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢንሹራንስ ኩባንያዎች የጠለፋ ዋስትና ኩባንያ ለማቋቋም 660 ሚሊዮን ብር መደቡ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ የመጀመርያ የሆነውን የጠለፋ ዋስትና ኩባንያ ለማቋቋም፣ በአገሪቱ የሚገኙ 17 የኢንሹራንስ ኩባንያዎች 660 ሚሊዮን ብር አክሲዮን መግዛታቸው ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንትና የአፍሪካ ኢንሹራንስ ሥራ አስፈጻሚ እንዲሁም የጠለፋ ዋስትና ኩባንያውን ለማቋቋም የኢንሹራንስ ማኅበር ያደራጀው ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ኪሮስ ጅራኒ እንደገለጹት፣ 13 የኢንሹራንስ ማኅበሩ አባል ኩባንያዎችንና ሌሎች አራት አባል ያልሆኑ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች በድምሩ 660 ሚሊዮን ብር አክሲዮን ለመግዛት መፈረማቸውን ገልጸዋል፡፡

ብሔራዊ ባንክ ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ባወጣው መመርያ፣ የጠለፋ ዋስትና ኩባንያ በኢትዮጵያውያን ግለሰቦችና ኩባንያዎች ብቻ እንዲቋቋም መፍቀዱ ይታወሳል፡፡ ይኼው መመርያ በሚቋቋም የጠለፋ ዋስትና ኩባንያ የተፈቀደ ካፒታል ውስጥ ባለአክሲዮኖች ከአምስት በመቶ በላይ ድርሻ እንደማይኖራቸው ደንግጓል፡፡ ይሁን እንጂ የመንግሥት ልማት ድርጅቶችና መንግሥት በሚቋቋሙ የጠለፋ ዋስትና ድርጅቶች ውስጥ ተፅዕኖ መፍጠር የሚያስችላቸውን ከአምስት በመቶ በላይ የአክሲዮን ድርሻ መያዝ እንደሚችሉ ይገልጻል፡፡

የአንድ የጠለፋ ዋስትና ኩባንያ የመመሥረቻ ካፒታል 500 ሚሊዮን ብር መሆኑንም በመመርያው ተገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ማኅበር መመርያው እንደወጣ በፍጥነት ባቋቋመው የጠለፋ ዋስትና ኩባንያ አደራጅ ኮሚቴ፣ ለአንድ ዓመት ያህል ከተንቀሳቀሰ በኋላ ሰሞኑን ይፋዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ በዚህ መሠረት በማኅበሩ ሥር ያሉና ሌሎችም ኩባንያዎች የተፈቀደ ካፒታሉ አንድ ቢሊዮን ብር የሆነ የጠለፋ ዋስትና ለማቋቋም ወስነዋል፡፡ ከዚህ የተፈቀደ ካፒታል ውስጥ 13 የማኅበሩ አባላትና አራት አባል ያልሆኑ ኩባንያዎች ሕጉ በሚፈቅድላቸው መሠረት ከአምስት በመቶ በታች ድርሻ፣ ማለትም ከ50 ሚሊዮን ብር በታች አክሲዮን ለመግዛት መፈረማቸውን አቶ ኪሮስ ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም በአጠቃላይ 660 ሚሊዮን ብር የአክሲዮን ድርሻ ለመግዛት በመፈረማቸው ቀሪው 340 ሚሊዮን ብር ለሌሎች ገዥዎች ይፋ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ በእስካሁኑ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቅድመ ፈቃድ እንደሰጣቸውና ዝግ ሒሳብ በባንክ መክፈታቸውን አስረድተዋል፡፡ አክሲዮን ለመግዛት የፈረሙ ኢንሹራንስ ኩባንያዎችም ሆነ ሌሎች በዝግ አካውንት ድርሻቸውን ማስገባት እንደሚችሉ የገለጹት አቶ ኪሮስ፣ ድርጅቱን ለማቋቋም የሚያስፈልገውን ወጪ ባለድርሻዎች የድርሻቸውን አንድ በመቶ አደራጅ ኮሚቴው በከፈተው ተንቀሳቃሽ ሒሳብ ውስጥ እንዲከቱ መደረግ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ እስካሁንም የ200 ሚሊዮን ብር አክሲዮን አንድ በመቶ በተንቀሳቃሽ ሒሳብ ውስጥ መግባቱን ተናግረዋል፡፡

ይህ የጠለፋ ዋስትና ኩባንያ ከስድስት ወራት በኋላ ተግባራዊ እንደሚሆንና ይህንም እውን ለማድረግ አደራጅ ኮሚቴው ደሊጂየንስ ከተባለ የአገር ውስጥ አማካሪ ድርጅት ጋር የኮንትራት ስምምነት አድርጓል፡፡ በስምምነቱ መሠረት አማካሪ ድርጅቱ የድርጅቱን ቅርፅ፣ ዝርዝር የአዋጭነት ጥናት፣ የሰው ኃይል፣ የድርጅቱ መተዳደሪያ ፖሊሲና ሥነ ሥርዓት ማኑዋል የመሳሰሉትን ማዘጋጀት እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የጠለፋ ዋስትና ኩባንያው ወደ ሥራ ሲገባ አገልግሎቱን ለአገር ውስጥና ለውጭ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች እንደሚሰጥ አቶ ኪሮስ አስረድተዋል፡፡ ይህም በመሆኑ ወደ ውጭ ይወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ከመቀነሱም በላይ ተጨማሪ ምንዛሪ እንደሚያመጣ ገልጸዋል፡፡

በአገር ውስጥ የሚገኙ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ዓረቦን የገዙዋቸው ትላልቅ ኩባንያዎች አደጋ ሲደርስባቸው የመድን ሽፋን ለመስጠት ከአቅም በላይ ስለሚሆንባቸው፣ ከውጭ መድን ሰጪዎች የጠለፋ ዋስትና በመግባት ሲያስተናግዱ ቆይተዋል፡፡ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚወጣበትን የጠለፋ ዋስትና በአገር በቀል ኩባንያ ለማስተናገድ ኩባንያው መመሥረቱ ትልቅ ጥቅም እንዳለው ይነገራል፡፡ 

  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች