Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበተደጋጋሚ አደጋ የሚያደርሱ ተሽከርካሪዎችን ለመቆጣጠር አዲስ መመርያ ሊወጣ ነው

በተደጋጋሚ አደጋ የሚያደርሱ ተሽከርካሪዎችን ለመቆጣጠር አዲስ መመርያ ሊወጣ ነው

ቀን:

–  ለኢንሹራንስ የሚከፍሉትን ዓረቦን ለማሳደግ ታቅዷል

የኢትዮጵያ መድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ የሦስተኛ ወገን መድን ሽፋን ገዝተው ተደጋጋሚ አደጋ የሚያደርሱ ተሽከርካሪዎችን ለመቆጣጠርና የሚከፍሉትን የዓረቦን ክፍያ ለማሳደግ የሚያስችል አዲስ መመርያ እያዘጋጀ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የኤጀንሲውን የዘጠኝ ወራት የሥራ ክንውን በማስመልከት ባለፈው ዓርብ በተሰጠው መግለጫ ላይ እንደተገለጸው፣ ተደጋጋሚ አደጋዎችን የሚያደርሱ ተሽከርካሪዎችን ለመቆጣጠር ያስችላል ተብሎ እየተዘጋጀ ካለው አዲስ መመርያ በተጨማሪ ሌሎች ስድስት መመርያዎችንና ደንቦችን እያዘጋጀ ነው፡፡

የኤጀንሲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዘውዱ ወንድም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በተለይ ተደጋጋሚ አደጋዎችን የሚያደርሱ ተሽከርካሪዎችን ለመቆጣጠር ያስችላል ተብሎ እየተዘጋጀ ያለው መመርያ ተደጋጋሚ አደጋ አድራሾችን በተለየ ሁኔታ እንዲስተናገዱ የሚያስችል ነው፡፡

እስካሁን ባለው አሠራር በሦስተኛ ወገን የመድን ሽፋን ከተገባላቸው ተሽከርካሪዎች ውስጥ፣ በዓመት አንድና ከዚያም በላይ አደጋዎችን እያረሱ ያሉትም ሆኑ ምንም አደጋ ሳያደርሱ ዓመቱን የጨረሱ ተሽከርካሪዎች የተመደበውን የዓረቦን መጠን እኩል ሲከፍሉ ቆይተዋል፡፡

አሁን ግን ተደጋጋሚ አደጋ አድራሾች ምንም አደጋ ሳያደርሱ በየዓመቱ ክፍያ እየፈጸሙ ካሉት እኩል መስተናገድና እኩል ዓረቦን መክፈል ስለሌለባቸው፣ ተደጋጋሚ አደጋ የተመዘገበባቸው ተሽከርካሪዎች የሚከፍሉት ዓመታዊ የዓረቦን መጠን ከፍ ብሎ እንዲሰላ ለማድረግ አዲሱ መመርያ እየተዘጋጀ ነው ተብሏል፡፡

ተደጋጋሚ አደጋ አድራሾችና አደጋ የማያደርሱ ተሽከርካሪዎች የሚከፍሉት ዓረቦን መጠን እንዲለያይ መደረጉ አጥፊዎችን መቆጣጠር ከማስቻሉም በላይ፣ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችም ተጠቃሚ እንደሚሆኑበት አቶ ዘውዱ ገልጸዋል፡፡

በዓመት አንዴ በሚከፈል ክፍያ ብቻ ተደጋጋሚ ጥፋት እየተፈጸመ የሚከፈለው ካሳ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን ከፍተኛ ወጪ በማስወጣት የሚጐዳ ስለሆነ፣ የአዲሱ መመርያ መውጣት የኢንሹራንስ ኩባንያዎችንም ይታደጋል የሚል እምነት አላቸው ብለዋል፡፡ መመርያው ሌሎች ድንጋጌዎችንም የሚያካትት እንደሆነ ከገለጻው ለመረዳት ተችሏል፡፡ ከዚህ መመርያ በተጨማሪ እስካሁን ለሦስተኛ ወገን የመድን ሽፋን ይከፈል የነበረውን የዓረቦን መጠን ለማሻሻል አዲስ መመርያ እየተዘጋጀ ነው፡፡ የኤጀንሲው ኃላፊዎች አዲሱ የዓረቦን ተመን መጠን ከቀድሞ ያነሰ ወይም የሚበልጥ እንደሆነ መግለጽ ባይፈልጉም፣ ተመኑን ለማውጣት ግን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በቅርቡም ፀድቆ ተግባራዊ ይሆናል ብለዋል፡፡ ሌሎች እየተዘጋጁ ነው ተብለው ከተጠቀሱት መመርያዎችና ደንቦች ውስጥ የካሳ ጥያቄ አፈጻጸም መመርያና የመድን ፈንድ ክፍያዎች አፈጻጸም መመርያዎች ይገኙበታል፡፡

የተሽከርካሪ አደጋዎች እየጨመሩ መምጣታቸውና ከዚሁ ጋር ተያይዘው የሚፈጠሩ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውሶችን ለመከላከል የወጣውን የተሽከርካሪ የሦስተኛ ወገን የመድን አዋጅን በተመለከተ፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ያከናወናቸው ሥራዎችንም ኤጀንሲው ይፋ አድርጓል፡፡ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ክንውኑም የሦስተኛ ወገን የመድን ሽፋን በሚመለከታቸው ጉዳዮች፣ በኤጀንሲውና በኢንሹራንስ ኩባንያዎች አማካይነት ከ64.5 ሚሊዮን ብር በላይ ለተጎጂዎች ወጪ መደረጉን ገልጿል፡፡

በተሽከርካሪ አደጋ ለተጐዱ፣ ለሞቱና ለወደሙ ንብረቶች ወጪ ከተደረገው ገንዘብ ውስጥ በኢንሹራንስ ኩባንያዎች በኩል 63.7 ሚሊዮን ብር በማውጣት፣ በአዋጁ መሠረት ተጐጂዎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ተብሏል፡፡ በኤጀንሲው በኩል ደግሞ ለ28 የሞት አደጋዎች ለአሥር አካል ጉዳቶችና ለዘጠኝ ተመላላሽ ታካሚዎች በጥቅሉ 49 ተጎጂዎች 1.15 ሚሊዮን ብር ካሳና የሕክምና ወጪ ማውጣቱን ኤጀንሲው አስረድቷል፡፡ 18 የሞትና የአካል ጉዳት የካሳ ጥያቄዎችም በመታየት ላይ ናቸው ተብሏል፡፡

በ2007 ዓ.ም. በዘጠኝ ወራት ኤጀንሲው ያወጣው ወጪ ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ614,916 ብር ብልጫ አለው፡፡ የተጎጂዎቹ ቁጥርም በ29 ከፍ ብሏል፡፡ ኤጀንሲው ለተጎጂዎቹ የጉዳት ካሳና የሕክምና ወጪያቸውን የሚሸፍነው ባልታወቁና የሦስተኛ ወገን መድን በሌላቸው ተሽከርካሪዎች ለደረሱ አደጋዎች ነው፡፡ ማንኛውም በተሽከርካሪ የሚደርስ አደጋን የመካስ ኃላፊነት ያለበት ይህ ኤጀንሲ፣ አደጋ አድራሾቹ ባይገኙም በአደጋው ለሞተና ለተጎዱ ሰዎች አስፈላጊውን ክፍያ ከፈጸመ በኋላ አደጋ አድራሾቹ ሲያዙ ያወጣውን ወጪ እንዲመልሱ ያደርጋል፡፡ በበጀት ዓመቱ ግን ሁለት መድን ያልተገባላቸው አደጋ ያደረሱ ተሽከርካሪዎችን በማስያዝ፣ እነርሱ ባደረሱት ጉዳት ለተጎጂዎች የተከፈለውን ለማስመለስ ጉዳዩን ፍርድ ቤት ማቅረቡ ታውቋል፡፡ የመድን ሽፋን ያልገቡ ተሽከርካሪዎችን በመቆጣጠሩ ረገድ 270 ተሽከርካሪዎች መያዛቸውን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡

አሥራ ሰባት የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዘጠኝ ወራት ውስጥ ካወጡት ወጪ ውስጥ 10.08 ሚሊዮን ብር የሚሆነውን ለ420 የሞት አደጋዎች ካሳ የከፈሉ መሆናቸው፣ 2.17 ሚሊዮን ብር ደግሞ በተሽከርካሪ አደጋዎች የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው 249 ተጐጂዎች የከፈሉት ካሳ መሆኑም ተገልጿል፡፡ ለካሳ ክፍያ ካዋሉት ገንዘብ በተጨማሪ ለ137 ተመላላሽና ተኝተው ለሚታከሙ ተጐጂዎች 1.47 ሚሊዮን ብር፣ ለ113 አስቸኳይ ታካሚዎች ደግሞ 565,626 ብር ወጪ መደረጉን ኤጀንሲው አስታውቋል፡፡

በሦስተኛ ወገን የመድን ሽፋን ተጠቃሚ ሆነዋል ለተባሉት ተጐጂዎች ወጣ ከተባለው ወጪ በተጨማሪ፣ በ2,854 የንብረቶች ላይ ለደረሰ ጉዳት የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ 49.4 ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጋቸው ተጠቁሟል፡፡

በሌላ በኩል በዘጠኝ ወራት ውስጥ በአገሪቱ ተከሰቱ በተባሉት የተሽከርካሪ አደጋዎችና በሦስተኛ የመድን ሽፋን በተስተናገዱ ተጎጂዎች መከከል ልዩነት መኖሩ ታውቋል፡፡ ጥቂት የማይባሉ በተሽከርካሪ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸው ተጎጂዎች በሕግ የተፈቀደላቸውን ካሳና ሊያገኙ የሚገባቸውን የሕክምና ወጪ በኤጀንሲውም ሆነ በኢንሹራንስ ኩባንያዎች አልተሸፈነላቸውም፡፡ ኤጀንሲውም ይኼንን የሚያምን ቢሆንም ምክንያቱን ለማወቅ እየተሞከረ መሆኑን ገልጿል፡፡

እንደ ኤጀንሲው መረጃ፣ በሦስተኛው ወገን የመድን ሽፋን የገዙ ተሽከርካሪዎች ቁጥር 340,773 ደርሷል፡፡ በ2007 ሙሉ በጀት ዓመትም የሦስተኛ ወገን የመድን ሽፋን የሚገዙ ተሽከርካሪዎችን ቁጥር 454,363 ማድረስም ዕቅዱ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...