Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ሕገወጥ ንብረቶች ተወረሱ

ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ሕገወጥ ንብረቶች ተወረሱ

ቀን:

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ሕገወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ለመግታት በተደረገ ቁጥጥር፣ ግምታቸው ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ ንብረቶችና 40 ተሽከርካሪዎች በኮንትሮባንድ ተይዘው መወረሳቸውን፣ በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የጂግጂጋ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኮሎኔል ኃይሌ ታደለ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተያዙትና የተወረሱት ንብረቶች የገቢና የወጪ ዕቃዎች ተብለው የተለዩ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ንብረቶች ውስጥ ብዛት ያላቸው የተለያዩ ሸቀጦች፣ ምግብ ነክ ዕቃዎችና የቁም እንሰሳት ናቸው፡፡ እንዲሁም ለጊዜው ግምት ያልወጣላቸው 40 ተሽከርካሪዎችም በባለሥልጣኑ ከተወረሱት ንብረቶች ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል፡፡

እንደ እሳቸው ገለጻ፣ በሕገወጥ መንገድ ወደ ውጭ ሲወጡ የተያዙት ግምታቸው ከ13.8 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆኑ ምግብ ነክና የቁም እንስሳት ናቸው፡፡ ገቢ ኮንትሮባንድ ተብለው የተለዩት ደግሞ ከ65.9 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ሸቀጣ ሸቀጦች በቁጥጥር ሥር ሲውሉ፣ ከእነዚህም ውስጥ ኤሌክትሮኒክስ፣ አልባሳት፣ ኮስሞቲክስና የግንባታ ዕቃዎች እንደሚገኙበት ኮሎኔል ኃይሌ አስረድተዋል፡፡

- Advertisement -

ከዚህም በተጨማሪ አሁን ባለው ምንዛሪ ከ2.13 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ፣ 104,069 ዶላርና 73,051 ዩሮ በሕገወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ መያዛቸውን ገልጸዋል፡፡ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የኮንትሮባንድ ፍሰትን ለመቆጣጠር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ከሶማሌ ክልል መንግሥትና ከፌዴራል ፖሊስ ጋር የተቀናጀ ሥራ መሥራቱ ያስገኘው ውጤት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ምሥራቃዊው የአገሪቱ ክፍል 90 በመቶ የሚሆኑት የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎች የሚታዩበት መሆኑን የሚናገሩት ኃላፊው፣ የድንበሩ ስፋትና የመልክዓ ምድሩ አቀማመጥ ሜዳማ መሆን ለኮንትሮባንድ መስፋፋት ዋንኛ ምክንያት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ሥራው ፈታኝ ቢሆንም በክልሉ ባሉት 18 ኬላዎች የተጠናከረ የቁጥጥር ሥራ እየተካሄደ ነው ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በየካቲት ወር 2007 ዓ.ም. አንድ ዲፕሎማት ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ለማስገባት ሲሞክሩ፣ በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት  በተቆጣጣሪዎች መያዛቸውን የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን አስታውቋል፡፡ ተያዙ የተባሉትን ዲፕሎማት ማንነት ሳይጠቅስ ባለሥልጣኑ ባወጣው መግለጫ፣ መነሻውን ከግብፅ ካይሮ ባደረገ የመንገደኞች አውሮፕላን ከሌሊቱ 9፡30 ሰዓት አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት የደረሱት ዲፕሎማቱ፣ በርካታ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ለማሳለፍ ሲሞክሩ በቁጥጥር ሥር ውለዋል ብሏል፡፡

እኚህ ስማቸው ያልተገለጸ ዲፕሎማት ያለመፈተሽ መብታቸውን ሽፋን በማድረግ በሻንጣዎቻቸው ከ60 ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝኑ የብር ጌጣጌጦች፣ ፕሮጀክተርና ባርኮድ ስካነሮች ይዘው ለማለፍ የሞከሩ ቢሆንም፣ ጥርጣሬ በነበራቸው የጉምሩክ ሠራተኞች በቁጥጥር ሥር ሊውሉ መቻላቸውንም አስታውቋል፡፡ ከዚህ በፊትም ተመሳሳይ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን ለማስገባት ሙከራ ያደረጉ ዲፕሎማቶች በቁጥጥር ሥር ውለው እንደነበረ በመግለጫው ተገልጿል፡፡ ከወራት በፊት ተያዙ የተባሉትን ዲፕሎማት ማንነትም ሆነ ዜግነት ለማወቅ ሪፖርተር ያደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡

በተያያዘ ዜናም በሕግ ጥሰት ምክንያት የተያዙና የተወረሱ ተሽከርካሪዎች ማቆያ የሚሆን መጋዘን ገንብቶ ካጠናቀቀ በኋላ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡ መጋዘኑ በአንድ ጊዜ ከ500 በላይ ተሽከርካሪዎችን የመያዝ አቅም እንዳለው፣ የቀረጥ ነፃ መብትን ያላግባብ አገልግሎት ላይ ሲያውሉ የተገኙትን፣ የታክስ ዕዳ ያለባቸውንና ተያያዥ ችግሮች የሚስተዋልባቸውን ተሽከርካሪዎች በራሱ ክትትል ከሚይዛቸው በተጨማሪ፣ ከኅብረተሰቡ በሚመጣ ጥቆማ መሠረት በቁጥጥር ሥር እንደሚያውል ገልጿል፡፡

ባለሥልጣኑ ከዚህ በፊት የሕግ ጥሰት አለባቸው ብሎ የያዛቸውን ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ሥር ካዋለ በኃላ ለፀሐይና ለዝናብ ሲጋለጡ ቆይተዋል፡፡ መጋዘኑ ተሽከርካሪዎቹ ለረዥም ጊዜ በመቆም ከአገልግሎት ውጪ የሚሆኑበትን ዕድል የሚቀንስ በመሆኑ፣ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውም የላቀ መሆኑን ባለሥልጣኑ አስረድቷል፡፡

አጠቃላይ ይዞታውን ሳይጨምር የተገነባው መጋዘን ከ500 በላይ ተሽከርካሪዎችን የመያዝ አቅም ያለው በመሆኑ፣ ከዚህ በፊት በቁጥጥር ሥር ውለው በአዲስ አበባና ዙሪያዋ ለፀሐይና ዝናብ ተጋልጠው የነበሩት ተሽከርካሪዎች ደኅንነታቸው ተጠብቆ ለማቆየት እንደሚያስችል ተገልጿል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...