Thursday, December 1, 2022
ሌሎች ዓምዶች

  ችግሮቹን ለይቶ መፍትሔ የሚሻው የኢትዮጵያ ሚዲያ

  - Advertisement -spot_img

  በብዛት የተነበቡ

  በኢትዮጵያ ያለው የዴሞክራሲ ሁኔታ መሠረታዊ ችግር ያለበት ለመሆኑ ማሳያ ተደርገው ከሚወሰዱ ጉዳዮች አንዱ የፕሬስ ነፃነት ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ከዚህ ቀደም ለበርካታ ዘመናት ሥልጣን ላይ እንደነበሩ ኃይሎች ሁሉ፣ ለሐሳብ ብዝኃነት ቦታ ስለማይሰጥ ጋዜጦችና የሚዲያ ተቋማት እሱ ካስቀመጠላቸው አቅጣጫ ዝንፍ ካሉ፣ መቃብራቸውን ይምሳል ሲሉ የሚተቹት የአገር ውስጥና የውጭ አካላት ህልቆ መሳፍርት ናቸው፡፡ በምዕራቡ ዓለም ያሉት እንደ አሸን የፈሉ የሚዲያ ተቋማትን ለንፅፅር ማቅረቡ ቢቀር፣ እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ባሉት አገሮች ደረጃ እንኳን ለ90 ሚሊዮን ዥንጉርጉር ሕዝብ የሚመጥን የሚዲያ አቅርቦት እንዳይኖር መንግሥት የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስድም ይወቅሳሉ፡፡

  ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት የግል ፕሬስን እንደ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ለይስሙላ ሳይሆን በተግባር እንዲንቀሳቀስ ሕጋዊና አስተዳደራዊ ዕርምጃዎችን በመውሰዱ የሚያመሰግኑ አካላት፣ የሽግግር ጊዜው ወደ ጐን ቢደረግ እንኳን አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ከፀደቀበት ኅዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም. በኋላ ባሉት ከ20 ዓመታት የበለጡ ጊዜያት ለፕሬሱ ዕድገት የሚጠቅሙ ድጋፎችን ከማድረግ ይልቅ፣ በየጊዜው የሚያቀጭጩ ውሳኔዎችን መወሰኑንና ምክንያታዊ ያልሆኑ ጣልቃ ገብነቶችን እንደፈጸመም ይከሳሉ፡፡

  መንግሥት በበኩሉ የፕሬስ ነፃነትን ይዞታ ለማሻሻል ማነቆዎች የሚመነጩት ከመንግሥት ብቻ እንዳልሆነ ይከራከራል፡፡ የሕዝቡና የሕዝቡ ነፀብራቅ የሆነው የመንግሥት ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ ባህል ገና በግንባታ ላይ መሆኑንም ያስገነዝባል፡፡ የሚዲያ ተቋማቱና ባለሙያዎችም ውስጣዊና ውጫዊ ስንክሳር መሠረታዊ ጫናን በኢንዱስትሪው ላይ እንዳሳረፈም ያመለክታል፡፡

  ሚያዝያ 24 ቀን 2007 ዓ.ም. በኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴል በተከበረው የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን እነዚህና ሌሎች ተዛማጅ አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን፣ መፍትሔ ናቸው የተባሉ ምክረ ሐሳቦችም ተሰጥተዋል፡፡ የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን በተመድ ውሳኔ መሠረት እ.ኤ.አ. ከ1993 ጀምሮ በመላው ዓለም ይከበራል፡፡ በዓሉ ሲከበር አራት ዋና ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩር ተመድ ይመክራል፡፡ እነዚህም የፕሬስ ነፃነት መርሆዎች፣ የፕሬስ ነፃነት ወቅታዊ ሁኔታ፣ የሚዲያ ተቋማት ነፃነትና በሚዲያ ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ናቸው፡፡ የዘንድሮው በግል መሪ ቃል ‹‹የተሻለ ዘገባ፣ የፆታ እኩልነትና በዲጂታል ዘመን የሚዲያ ደኅንነት›› የሚል ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ‹‹ሚዲያ ለሰላም፣ ለዕድገትና ለሕዝቦች ጥቅም›› በሚል መሪ ቃል ተከብሯል፡፡

  ‹‹የተለየውን ነገርና ለውጡን ንገሩን››

  በበዓሉ ተሳታፊ የነበሩት ጠበቃና ‘ሥነ ሕግ’ የተሰኘ የሬዲዮ ፕሮግራም አቅራቢ አቶ ገብረ አምላክ ገብረ ጊዮርጊስ የቀረበው አስተያየት፣ የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን በኢትዮጵየ የሚከበርበትን መንገድ ዳግም ለመፈተሽ ዕድል የሚሰጥ ነው፡፡ ‹‹ስለግል ፕሬሱ ስናወራ ስለ ሕጋዊ ማዕቀፍ ብቻ ነው ወይ ማውራት ያለብን? ሕገ መንግሥቱ ምን ይላል? ሕጉን ተመሥርቶ ምን ያህል ፈቃዶች ተሰጡ የሚለው ነው ወይስ ይህንን ነፃነት መተግበር ከጀመርን ጊዜ አንስቶ በመንግሥት በኩል ጥበቃ እየተሰጠ እንደዚህ ዓይነት ውጤት መጥቷል የሚል መነገር ያለበት? በግል ፕሬሱም በኩል ባደረግናቸው ጥረቶች መንግሥት ይህን እንዲያደርግ፣ ፖሊሲውን እንዲቀይር አድርገናል የሚል ውጤትና ለውጥ ላይ ያተኮረ ገለጻ መቅረብ አለበት፡፡ አለዚያ ሰዎች ይናገራሉ፣ መንግሥትም ይሰማል፡፡ ለውጥ እስካልመጣ ድረስ ግንኙነቱ ለውጥ አይኖረውም፤›› ብለዋል፡፡

  የአቶ ገብረ አምላክ አስተያየት መነሻ የዘንድሮው በዓል ቢሆንም፣ ከዚህ ቀደም በነበሩ ተመሳሳይ መድረኮች ላይም በተለይ የመንግሥት ተወካዮች ለሚጠየቋቸው ተጨባጭ ጥያቄዎች መልሶቻቸው በአብዛኛው የሕግ ማዕቀፎችን ከመጥቀስ የዘለለ አልነበረም፡፡ በዕለቱ መንግሥትን በመወከል ከቀረቡት መካከል የበዓሉ አዘጋጅ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን፣ ሕገ መንግሥቱና ሕጎቹ የሁሉም ነገር መሠረት በመሆናቸው ትኩረት መደረጉ ተገቢ ነው ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሸን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ባልደረባ የሆኑት አቶ ታምራት ደጀኔ ‹‹የነፃ ፕሬስ ዕድገት በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ ያቀረቡት ጽሑፍም በአብዛኛው ሕጋዊ ማዕቀፉን የሚያብራራ ነበር፡፡

  ከዚህ ይልቅ የሕጎቹ ውጤት ከሕጎቹ የበለጠ ለበዓሉ ቅርብ እንደሆነ ያመለከቱት አቶ ገብረ አምላክ፣ ‹‹መንግሥት ፕሬስ ውስጥ ያሉ ሰዎች ጩኸት ምንድን ነው ብሎ ካልሰማ፣ ይኼ ጩኸታቸው መነሻ አለውና ለፖሊሲና ለሌላ ነገር ግብዓት ልጠቀምበት ካላለ፣ ፕሬሱም የሕዝብ ጠባቂነቱ የልምድና የሱስ ከሆነና ስህተት በተፈጠረ ቁጥር መጮህ ከሆነ፣ በመንግሥት አስተዳደር ላይ ግብዓት የመስጠትና ተፅዕኖ የማድረግ ዕድል አይኖርም፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

  የሪፖርተር ጋዜጣ አሳታሚ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽንስ ሴንተር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አማረ አረጋዊ በተመሳሳይ፣ የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀንን ጨምሮ ከመንግሥት ጋር የሚደረጉት ውይይቶች በውጤትና በለውጥ የታጀቡ አለመሆናቸውን አመልክቷል፡፡ አልፎ አልፎም በቃል ደረጃ ስምምነት ከተደረገ በኋላ በተግባር ተቃራኒ ነገር ሲፈጸም እንደሚታይም አስረድቷል፡፡ ለአብነት ያህልም በፕሬስ ሕጉ ረቂቅ ላይ ሰፊ ውይይት ከተደረገ በኋላ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሕጉ ተቃውሞ ስለገጠመው እንደማይፀድቅና ተሻሽሎ እንደሚቀርብ ቃል ቢገቡም፣ የወንጀል ሕጉ ውስጥ ተካተው በጓሮ በር እንደፀደቀ ጠቅሷል፡፡ የመረጃ ነፃነትና የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ የወንጀል ሕጉ ከፀደቀ ከሦስት ዓመት በኋላ በ2000 ዓ.ም. መፅደቁ ይታወሳል፡፡

  አቶ አማረ በተሻሻለው የብሮድካስቲንግ አዋጅ የተካተተው የቴሌቪዥን ባለቤት ሬዲዮ፣ የሬዲዮ ባለቤትም ቴሌቪዥን ሊኖረው አይችልም የሚለው የመስቀልያ ባለቤትነት (Cross Ownership) ጽንሰ ሐሳብን በተሳሳተ መንገድ በመተርጎም፣ ጋዜጣ ያለው መጽሔት አይፈቀድለትም የሚለውን ውሳኔ ተቃውሟል፡፡ ከመንግሥት ጋር ውይይት ሲደረግ ስህተቱን ያመኑ ቢሆንም፣ ሪፖተር መጽሔት ዳግም ለመጀመር ለቀረበው ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አለመገኘቱንም ጠቁሟል፡፡

  በረቂቁ የፕሬስ ሕግ የፕሬስ ካውንስል (የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት) በመንግሥት እንደሚቋቋምና አባልነትም አስገዳጅ እንደሆነ ተገልጾ የነበረ ቢሆንም፣ የሚዲያ ተቋማት ባደረጉት ጫና ራሳቸው እንዲያቋቁሙ ማድረጉን እንደ አንድ አዎንታዊ ተግባቦት ወስዶታል፡፡ ይሁንና በአጠቃላይ መንግሥት በግሉ ፕሬስ ላይ ያለው አመለካከት የችግሮቹ ምንጭ እንደሆነ አቶ አማረ አስገንዝቧል፡፡ ‹‹መንግሥት ስለ ልማት የሚያስበው የመንግሥት ሚዲያን ነው፣ የግሉ ሚዲያ ኪራይ ሰብሳቢ ነው የሚል አመለካከት አለው፡፡ ይኼ የግል ሚዲያዎችን ብቻ ሳይሆን የመንግሥትንም ሚዲያ የሚጎዳ ነው፡፡ አሁን የመንግሥት ሚዲያ በመንግሥት የተዘጋጁ ስብሰባዎችን እንኳን እንዳለ ማንፀባረቅ የማይችል ሆኗል፡፡ በግሉ ፕሬስ ከሚንፀባረቁት ሐሳቦች መካከል ይኼ ሐሳብ ይጠቅማል ብሎ ከማየት ይልቅ ይኼ የኪራይ ሰብሳቢዎች ወይም የኒዮ ሊበራሎች ነው ተብሎ ውድቅ ይደረጋል፤›› ብሏል፡፡

  አቶ ሬድዋን መንግሥት ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና የተሰጠውን ሐሳብን በነፃነት የመናገር መብት ተግባራዊነት ለማረጋገጥ እየተረባረበ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡ የመረጃ ነፃነትና የመገናኛ ብዙኃን አዋጅን ሙሉ በሙሉ ለመፈጸም ይረዳሉ የተባሉ ዝርዝር ድንጋጌዎች መጠናቀቃቸው፣ የማስታወቂያ አጠቃቀም ፍትሐዊነትን የሚያረጋግጥ አሠራር ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅቱ የተጠናቀቀ መሆኑና ራሱን የቻለ የሚዲያና የኮሙዩኒኬሽን ፖሊሲ ረቂቅ እየተጠናቀቀ መሆኑ የዚህ ቁርጠኝነት ማሳያዎች እንደሆኑም አመልክተዋል፡፡

  ባለፈው ዓመት በተከበረው ተመሳሳይ በዓል ላይ በወቅቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር የነበሩት ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ለአቶ ሬድዋን ያቀረቡት አንድ ጥያቄ፣ የተሳታፊዎቹን ትኩረት በመሳብ የውይይት ርዕስ ሆኖ ነበር፡፡ አቶ ሬድዋን በወቅቱ የፕሬስ ነፃነት ኢትዮጵያን በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ ዘርፍ ለመለወጥ ያለውን አስተዋጽኦ አጉልተው ተናግረው ነበር፡፡ ዶ/ር ዳኛቸው፣ ‹‹የፕሬስ ነፃነትን አንድ ነገር ለማግኘት ሳይሆን በራሱ ያሰፈልጋል ብሎ መንግሥትዎ አያምንም ወይ?›› በማለት ነበር የጠየቁት፡፡

  ይህን በማስታወስ ይመስላል በአሁኑ ንግግራቸው፣ ‹‹መንግሥት ለፕሬስ ነፃነት መጠበቅና መጎልበት የሚተጋው ይኼው መብት ራሱን እንደቻለ ተገቢነትና ፋይዳ ያለው አንድ መብት ስለሆነ ብቻ ሳይሆን፣ በተገቢው መንገድ ኃላፊነቱን መወጣት ከቻለ ለፍትሕ፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፣ ለማኅበራዊ ልማት፣ እንዲሁም ለሕዝቦች ወሳኝነት የማይተካ ሚና የሚጫወት ዓይነተኛ መሣሪያ መሆኑን በፅኑ በማመን ነው፤›› በማለት የፕሬስ ነፃነት መሣሪያ ብቻ ሳይሆን በራሱ ግብ እንደሆነ ተቀብለዋል፡፡

  ለፕሬስ ነፃነት በተገቢው ሁኔታ አለመዳበር አስተዋጽኦ ካደረጉ አካላት አንዱ መንግሥት መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሬድዋን፣ መንግሥትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በድክመታቸው የሚወቀሱበትን ያህል በጥንካሬ የሚመሰገኑበት ሥራ እንዳለ አመልክተዋል፡፡ ‹‹በሁሉም መስክና ተዋንያን ዘንድ መጎልበትና መሻሻል የሚኖርባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ መንግሥት፣ የንግድና የሕዝብ ብዙኃን መገናኛዎች፣ የትምህርትና የምርምር ተቋማት፣ በአጠቃላይ ሕዝቡ ባለፉት ሁለት አሠርት ዓመታት አገራችን ለተጎናፀፈቻቸው ሁሉን አቀፍ ድሎችና ለተፈጠረው አንፃራዊ በጎ ገጽታ ብቻ ሳይሆን፣ ለጉድለቶቹም ለመፍትሔዎቹም የየራሳቸው ሚናና ድርሻ አላቸው፡፡ የመፈጸም አቅም፣ አንፃራዊ ክፍተት፣ ነባራዊና በሁሉም ተዋንያን ዘንድ የሚታይ በመሆኑ መንግሥትም በቅድሚያ በራሱ ዘንድ የሚታየውን ጉድለት እየለየ በመፍታት ላይ ይገኛል፤›› ብለዋል፡፡

  የሕግ የበላይነትና ‹አክቲቪስት› ጋዜጠኞች

  የኢትዮጵያ መንግሥት ለፕሬስ ነፃነት ደንታ ቢስ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ የደረሱ አካላት ዋነኛ ማስረጃቸው፣ ባለፉት ዓመታት በጋዜጠኝነት ሙያ ተሰማርተው በነበሩ ግለሰቦች ላይ የወሰደው የእስር ዕርምጃ ነው፡፡ እስር በመፍራት የተሰደዱ ጋዜጠኞች ቁጥርም ተጠቃሽ ነው፡፡ ወደ ሥራ የገቡት የሚዲያ ተቋማት ብዙ ሳይቆዩ ለመዘጋታቸውም ተጠያቂ የሚያደርጉት መንግሥትን ነው፡፡ በተለይ በ2001 ዓ.ም. ወደ ሥራ የገባው የፀረ ሽብርተኝነት ሕግ በኢትዮጵያ ያለውን ሐሳብን በነፃነት የመግለጽና ሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥትና ፓርቲ መቃወምን ወደ ወንጀልነት ያሸጋገረ እስኪባል ድረስ፣ የመብቱን አፈጻጸም ማመናመኑን የሚጠቁሙ ተመራማሪዎችና ተንታኞች አሉ፡፡

  መንግሥት በጋዜጠኝነት ሙያ ተሰማርተው በነበሩ ግለሰቦች ላይ የወሰደው ውሳኔ ከሙያው ጋር የተገናኘ ሳይሆን፣ ከፈጸሙት ከጋዜጠኝነት ሙያ ጋር የማይገናኝ ድርጊት የተነሳ እንደሆነ በመግለጽ ራሱን ይከላከላል፡፡ አቶ ሬድዋንም በተመሳሳይ ‹‹መንግሥት ለፕሬሱ መጠናከር አበክሮ የሚሠራውን ያህል ለሕግ የበላይነት የመንቀሳቀስ ጉዳይም ከአንድ መንግሥት የሚጠበቅ ትንሹ ተግባር ነው፡፡ ጦርነት ቀስቃሹንና የአገር ሰላምና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ለማፍረስ የሚሠራውንም ማረቅ ግዴታው ነው፤›› ብለዋል፡፡

  አቶ ሬድዋን በኢትዮጵያ የንግድ ሚዲያው የሙያ ሥነ ምግባሩን ጠብቆ በኃላፊነት መንፈስ ከመንቀሳቀስ አንፃር ውስንነቶች የሚታዩበት እንደሆነም ተከራክረዋል፡፡ ‹‹የአቅማቸውን ያህል የሚንቀሳቀሱ የንግድ መገናኛ ብዙኃን የመኖራቸውን ያህል ጥላቻን፣ የሐሰት ውንጀላን የሚሰብኩ የአርበኝነትን ሚና ተላብሰው የተገኙም አሉ፡፡ የከፋ ጫፉን ከወሰድነውም የሽብር ተግባርና ሽብርተኝነትን እስከማወደስ የሚደርሱም ይስተዋላሉ፡፡ ይህም ምንም ዓይነት ምቹ ሁኔታ ቢፈጠር ፕሬሱን ራሱን በራሱ ጠልፎ እንዲጥል የሚያደርገው ነው፤›› ብለዋል፡፡          

  የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ የዕለት ተዕለት አተገባበር ላይ በርካታ ጥያቄዎች እንደሚነሱ ያስታወሱት አቶ ሬድዋን፣ የተፈጸመው ድርጊት በፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ ውስጥ ያርፋል ወይስ አያርፍም የሚለውን የመለየት ሥራ አስቸጋሪ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ ‹‹አንዳንዴም በሌሎች ሕጎች ልንሸፍናቸው የምንችላቸው ጉዳዮች ወደ ፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ መጥተው ሊታዩ ይችላሉ፡፡ ይኼ የአተገባበር ጉዳይ ነው፡፡ እየታረመና እየተስተካከለ ሊሄድ የሚችል ነው፡፡ ሕጉን መቀየር አያስፈልግም፤›› ሲሉም መፍትሔው የተሻለ አፈጻጸም እንጂ አንዳንዶች እንደሚሉት ሕጉን መሻር እንዳልሆነ ተከራክረዋል፡፡

  መንግሥት የራሱ ውስንነት ቢኖርበትም አንዳንድ ችግሮች ግን የተከሰቱት በራሳቸው በግል ሚዲያ ተቋማት እንደሆነም አቶ ሬድዋን ተችተዋል፡፡ ‹‹አቶ አማረ ያነሳው እንወያይበታለን ግን አንተገብረውም ያለው በአንድ በኩል እውነት ነው፡፡ ግን የማይተገበረው መንግሥት ብቻ አይደለም፡፡ የጉዳዩ ባለቤት የሆኑት የሚዲያ ሰዎች በጋራ ጥቅማቸው ዙሪያ ለመስማማት አሥር ዓመት ከፈጀባቸው መንግሥት በአጠቃላይ በአገሪቱ ችግሮችን ለመፍታት አንዱን ሲፈታ አንዱ ቢያመልጠው ምኑ ይገርማል?›› ብለዋል፡፡ አቶ ሬድዋን መንግሥት መረጃ የመያዝ እንጂ የመስጠት ባህሉ ደካማ በመሆኑ እሱን በሥልጠናና በዝርዝር ሕጎች ለመቀየር ሥራዎች ተጠናክረው እየተሠሩ መሆኑንም አውስተዋል፡፡

  የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ መሠረት አታላይ መንግሥት የኢትዮጵያን ሚዲያ ሕግ በማውጣት የደገፈውን ያህል ተጨማሪ ድጋፍ የማድረግ ቁርጠኝነት እንደሚያንሰው አመልክተዋል፡፡ በሌላ በኩል የሚዲያው ማኅበረሰብ ሕግ በማስከበር ሰበብ ከመንግሥት በኩል የሚደርስበትን ጡጫ ለመከላከል ቀድሞ ራሱን በሙያው ሥነ ምግባር ማነፅና ሥርዓትና ሕጉን ተከትሎ መንቀሳቀስ እንደሚኖርበት አሳስበዋል፡፡ ለዚህ ቁልፉ መፍትሔ በፍጥነት የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤትን ማቋቋም መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡

  በዕለቱ በኢትዮጵያ ‹አክቲቪስት› ጋዜጠኞች ያላቸውን ሚና በተመለከተ ገለጻ ያደረገው ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ነው፡፡ አቶ ዳዊት በአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ መንግሥት ላይ የሰላ ትችት በማቅረብ የሚታወቅ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት በአውራምባ ታይምስ ኦንላይን የሚያቀርባቸው ጽሑፎች የመንግሥትን አቋም የሚያንፀባርቁ ናቸው፡፡ ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ይመስላል ገለጻውን የጀመረው፡፡ ‹‹ይህ ዓይነት መድረክ ላይ ለመጨረሻ ጊዜ የተገኘሁት ፀረ ሰላም ኃይሎችን ወክዬ ነበር፤›› በማለት ነው፡፡ መንግሥት ጫና አድርጎብኛል በማለት ወደ አሜሪካ ተሰዶ የነበረው አቶ ዳዊት ‹‹ልብ ገዝቼ ተመልሻለሁ፤›› ብሏል፡፡

  ‹አክቲቪስት› ጋዜጠኞችን የለውጥ ኃይል አራማጆች ሲል የጠራቸው አቶ ዳዊት፣ ጋዜጠኝነት ከአክቲቪዝም የሚለዩት መሠረታዊ ባህሪያት እንዳሉም ተከራክሯል፡፡ ጋዜጠኝነት ነፃ፣ ገለልተኛና ተጨባጭ አዘጋገብን የሚከተል እንደሆነና አክቲቪስቶች ግን በሚዲያ የግላቸውን አስተሳሰብ ያለ ተጨባጭ ማስረጃ በማንፀባረቅ እንደሚታወቁም ገልጿል፡፡ የሕዝብን ጥቅም እስካረጋገጠ ድረስ የትኛውም ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መንገድ እንደሚጠቀሙም ጠቁሟል፡፡ ይሁንና በተግባር እነዚህ ግለሰቦች ዋና ግባቸው ሕዝብን መጥቀም ሳይሆን፣ ለጥቂት ቡድኖች ወይም ግለሰቦች ጥቅም መቆም እንደሆነም አመልክቷል፡፡

  በኢትዮጵያ ያሉ አክቲቪስት ጋዜጠኞች የመንግሥት ተቃዋሚ እንጂ ጋዜጠኞች አይደሉም ሲል የተከራከረው አቶ ዳዊት፣ የዚህ ችግር መነሻ በሽግግሩ ጊዜ የሚዲያ ተቋማት መሪዎችና ጋዜጠኞች በአብዛኛው የኢሕአፓ፣ የኦነግና የደርግ አባላት መሆናቸው ነው ሲልም ገልጿል፡፡ ኢሕአዴግ በ2001 ዓ.ም. የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤትን እስኪያቋቁም ድረስ ከግሉ ፕሬስ ጋር ጤናማ ግንኙነት ለመፍጠር አለመሞከሩ ችግሩን እንዳባባሰውም ጠቁሟል፡፡ በኢትዮጵያ እስካሁን የተመሠረቱት የግል ሚዲያዎች በአብዛኛው የነፃ አውጭነት ሚና አለን ብለው መነሳታቸው ብዙም ሳይቆዩ እንዲጠፉ ማድረጉንም አመልክቷል፡፡ አክቲቪስት ተብለው ከሚጠሩ አሥር ግለሰቦች መካከልም ስድስቱ የግንቦት ሰባት አባላት መሆናቸውንም አቶ ዳዊት ጠቅሷል፡፡ እዚህ ዝርዝር ውስጥ አቶ ታማኝ በየነና አቶ አበበ ገላው እንደሚካተቱም ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

  አቶ ዳዊት አክቲቪስት በመባል ሥራቸው መንግሥትን መቃወም ከሆኑ አካላት ጀርባ የውጭ ኃይሎች እጅ በስፋት እንደሚገኝም አስገንዝቧል፡፡ ይህን ከግል ልምዱ መረዳት መቻሉንም አብራርቷል፡፡ አቶ ዳዊት ያነሳውን የውጭ ኃይሎች ተፅዕኖ በተመለከተ አቶ አማረ፣ የውይይቱ መሪ የነበሩት ደ/ር ነገሪ ሌንጮና አቶ ሬድዋንም ተስማምተዋል፡፡ አቶ ሬድዋን፣ ‹‹ለእነዚህ ዓለም አቀፍ ተቋማት እዚህ ያለውን ፈተና ተቋቁመው፣ አጠቃላይ ሥርዓቱ ያለበትን ፈተና ተቋቁመው የዘለቁ አገር ውስጥ ያሉ ጋዜጠኞች ጀግኖች አይደሉም፡፡ እንደምንም ብለው ከአገር ውጭ መውጣት አለባቸው፡፡ አገር ጥሎ የሚሄድ ሰው ነው ጀግናቸው፡፡ እዚህ ሕጉን አክብሮ፣ ፈተና ተቋቁሞ፣ ፕሬስ እንዲያብብ የበኩሉን ያደረገ ሰው፣ ዴሞክራሲና ልማታችን ያለውን ጉድለት እየተቸ የሚሠራ ሚዲያን ማበረታታት አይፈልጉም፤›› ሲሉ የውጭ ኃይሎችን አሉታዊ ተፅዕኖ አስረድተዋል፡፡

  ጉዳያቸው ፍርድ ቤት በመታየት ላይ ያለው የዞን ዘጠኝ ጦማሪያንን በተመለከተ አቶ ዳዊት እንደ ጋዜጠኛ መቁጠር የሚቻለው ሁለቱን (ተስፋለም ወልደየስና የአዲስ ጉዳይ መጽሔት ባልደረባ የነበረው አስማማው ኃይለ ጊዮርጊስ) ብቻ እንደሆኑ ጠቅሷል፡፡ ሌሎቹ ከማኅበራዊ ሚዲያ (በተለይ ፌስቡክ) ውጪ በኢትዮጵያ ለጋዜጠኝነት ሙያ ያደረጉት አንዳች አስተዋጽኦ እንደሌለም ገልጿል፡፡ ዞን ዘጠኝ ጦማሪም ቢሆንም ከአባላቱ መታሰር ከአንድ ዓመት ከስድስት ወራት በፊት መዘጋቱንም ጠቁሟል፡፡ በዞን ዘጠኝ ጉዳይ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን ጨምሮ በመላው ዓለም የሚገኙ አካላት ከፍተኛ ትኩረት ያደረጉት የራሳቸውን ጥቅም ለመጠበቅ በማሰብ እንደሆነም አመልክቷል፡፡

  ሚዲያ እንደ ቢዝነስ

  የሚዲያ ወይም ጋዜጠኝነት ሙያ ውግንና የሕዝቡ ጥቅም በመሆኑ እንደ አንድ የቢዝነስ ተቋምና ለትርፍ እንደሚሠራ አካል መታየት የለበትም የሚል ክርክር ይቀርባል፡፡ ይሁንና የዓለም ተጨባጭ ሁኔታ የሚያሳየው ከፍተኛ ትርፍ በማግኘት የሚዲያ ተቋማት ቀዳሚነቱን እንደያዙ ነው፡፡

  በዕለቱ ተሳታፊ የነበረው የኢትዮጵያ ቢዝነስ ሪቪው መጽሔት ባለቤት አቶ አማንይሁን ረዳ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሚዲያ ያላደገበት ዋና ምክንያት እንደ ቢዝነስ እየተመራ ባለመሆኑ ነው ሲል ተከራክሯል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ሚዲያዎች አንባቢው የሚፈልገውን መረጃ የሚለዩበትን መንገድ፣ ኅትመቶቻቸውን የሚያሠራጩበትና የሚሸጡበትን መንገድ፣ የሚያገኙትን ገንዘብ የሚጠቀሙበትን መንገድ፣ ሠራተኞቻቸውን የሚያስተዳድሩበትን መንገድ ካየን፣ ሙሉ በሙሉ በቢዝነስ መርህ ሳይሆን በጋዜጠኝነት ሙያ ፍቅር ብቻ ነው የሚመሩት፡፡ 20 ዓመት የቆየው ሪፖርተር ለምንድን ነው ሥርጭቱ ከአሥር ሺሕ ያልበለጠው? የፎርቹን ከ7,000 ማለፍ ያልቻለው?›› ሲል ጥያቄውን አቅርቧል፡፡

  አቶ አማረ ለዚህ ጥያቄ በሰጠው ምላሽ፣ ‹‹ችግሩ የቢዝነስ መርህን ያለማወቅ አይደለም፡፡ የሪፖርተር ጋዜጣ ሥርጭት አሥር ሺሕ የሆነው አንባቢ ስላጣ አይደለም፡፡ ከ70 ሺሕ ነው እየወረድን አሥር ሺሕ የደረስነው፡፡ የሪፖርተር የእሑድ ዕትም አሥር ብር ይሸጣል፡፡ ለአዟሪዎች በስምንት ብር እንሰጣቸዋለን፡፡ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ አንዷን ጋዜጣ የምናሳትመው 35 ብር ከፍለን ነው፡፡ ስለዚህ ለእያንዳንዱ ጋዜጣ 27 ብር እንደጉማለን፡፡ ከአሥር ሺሕ በላይ መደጎም ከአቅማችን በላይ ነው፤›› ብሏል፡፡ አሁን ሪፖርተር በወር ለብርሃንና ሰላም 3.8 ሚሊዮን ብር እንደሚከፍል የገለጸው አቶ አማረ፣ የማተሚያ ቤቱን ችግር ለመቅረፍ ሪፖርተር የራሱን ማተሚያ ቤት ለማቋቋም ከጨረሰ በኋላ መንግሥት እንዳስቆመው አብራርቷል፡፡ ‹‹ዱከም ላይ ፋብሪካውን ገንብተን ማተሚያ ማሽኑንም አስገንብተን ነበር፡፡ ልንገጣጥመው ስንል መጥተው አቁሙ አሉ፡፡ አምስት ዓመት ሙሉ ዘግተውበት በቅርቡ ስናየው ማሽኑ ዝጓል፡፡ መቀማትና መቆሙ ሳይሆን ለምን እንዳስቆሙን እንኳን ምክንያቱን አልነገሩንም፡፡ አሁን አስነጥሰን ስንመለስ ዋጋ ጨምሯል እየተባልን ነው እየሠራን ያለነው፤›› ብሏል፡፡

  ይህን የማተሚያ ቤትና የወረቀት ዋጋ እንደ ትልቅ ችግር በማየት የአቶ አማረን ሥጋት የተጋሩት አቶ መሠረት፣ ‹‹ጋዜጦች ላይ የተጫነው የኅትመት ዋጋ እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ የኅትመት ዋጋ ወይ ተመጣጣኝ መሆን አለበት፡፡ ወይም ደግሞ ይህ የማይቻል ከሆነ ይህን የሚያቻችል ሌላ ልዩ ድጋፍ ሊደረግ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡ አቶ ሬድዋን ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹የወረቀት ችግርን በተመለከተ ሁሉንም ነገር ድጎማ ማድረግ አይደለም መፍትሔው፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የወረቀት ማምረቻ አገር ውስጥ ሲገነባ ችግሩ ይቀረፋል፤›› በማለት ችግሩ ጊዜያዊ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

  አቶ አማንይሁን ከድጎማ መልስ መንግሥት የኅትመት ችግሩን የሚዲያ ተቋማት እንዲቋቋሙት የማድረጊያ መፍትሔዎች በእጁ እንዳሉ አስገንዝቧል፡፡ ‹‹ለሌሎች የኢንቨስትመንት መስኮች የሚሰጡ ጥቅማ ጥቅሞችን ለሚዲያ መስጠት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ከቀረጥ ነፃ ማሽኖችን እንዲያስገቡ ሊፈቀድ ይችላል፡፡ የግብር እፎይታ ሊሰጣቸው ይችላል፡፡ እንደ መጻሕፍት ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ወረቀት ከውጭ ለማስገባት የሚጠይቀውን ቀረጥ መቀነስ ይቻላል፤›› ብሏል፡፡

  በአጠቃላይ ለግማሽ ቀን በተካሄደው ውይይት የፕሬስ ነፃነትን በኢትዮጵያ ለማረጋገጥ አሉ በተባሉ ተግዳሮቶችና የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ የተወያዩት ተሳታፊዎች፣ በቀጣዩ ዓመት ከችግሮች ይልቅ በስኬቶች ላይ ለመነጋገር ተስፋ አድርገው ተለያይተዋል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ትኩስ ጽሑፎች

  ተዛማጅ ጽሑፎች

  - Advertisement -
  - Advertisement -