Thursday, July 25, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዋጋው በከፍተኛ መጠን እያሻቀበ ያለው ምስር

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከአዲስ አበባ ወደ ደብረ ብርሃን በሚወስደው መንገድ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው በኬ ከተማ በአንድ የተለየ ክንውን ትታወቃለች፡፡ ምስር ክክ በማዘጋጀት፡፡ ለአዲስ አበባና ለአካባቢዋ ነዋሪዎች ፍጆታ የሚሆነውን ምስር ክክ ማዘጋጀት ሥራ የምትታወቀው ይቺ ከተማ ምስር አብቃይ አይደለችም፡፡ ግን ከተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ ከተማዋ የሚገባውን ድፍን ምስር ወደ ምስር ክክ በመቀየር ሥራ የተጠመዱ ነዋሪዎች ኑሮዋቸው የተመሠረተው በዚሁ ሥራ ነው፡፡ ወደ ከተማዋ ሲገባ በዋና ጎዳናው ግራና ቀኝ ያሉ መንደሮችዋ የተከካ ምስር የሚያናፍሱ፣ የሚለቅሙ፣ የሚያበጥሩ፣ ለገበያ የሚቀርበውን ምስር በማዳበሪያ የሚሞሉ፣ የሚጭኑና የሚያራግፉ ሠራተኞችን በቀላሉ መመልከት ይችላል፡፡

ከዋና ጎዳናው ወደ ውስጥ ለውጥስ መንደሮችዋ ዘልቆ ለተመለከተም በኬና የምስር ትስስር ምን ድረስ ስለመሆኑ በሚገባ ይረዳል፡፡ በእያንዳንዱ መኖሪያ ቤት ደጃፍ ለምስር ክክ ማቀነባበሪያና ማዘጋጃ የሚሆኑ የተሰናዱት አውድማዎቿ ይታያሉ፡፡ እነዚህ አውድማዎች ያለሥራ የሚያድሩበት ጊዜ እንዳልነበርም ሰሞኑን ወደ በኬና አካባቢዋ ተጉዘን ያነጋገርናቸው የከተማው ነዋሪዎች ይገልጻሉ፡፡

ድፍን ምስር በመረከብ፣ በመከካትና በማናፈስ ሥራ ላይ ከሃያ ዓመታት በላይ የቆዩትና የ51 ዓመቱ ጎልማሳ አቶ መኩሪያ ጥላሁን እንደሚገልጹት፣ የበኬ ነዋሪዎች ሕይወት በምስር ሥራ ላይ የተመሠረተ ስለመሆኑ ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ምሳሌ ያደርጋሉ፡፡

በምስር ማበጠር ሥራ ላይ ከ18 ዓመታት በላይ የቆዩት ወ/ሮ ተናኜ እሸቴም፣ ከበኬ ነዋሪዎች ውስጥ ከምስር ሥራ ውጪ ባለ ሥራ የተሰማሩ ጥቂቶች ናቸው ይላሉ፡፡ ይህንን  አባባላቸውን ለማጠናከርም ‹‹የምስር አውድማ የሌለው ወይም የምስር ሥራ የማይሠራ የከተማው ነዋሪን መቁጠር ይሻላል፤›› ብለው፣ አብዛኛው ነዋሪ ከዚሁ ሥራ ጋር የተሰወረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከአንድ ወር ተኩል ወዲህ ግን ብዙዎቹን የበኬ ነዋሪዎች ያሳሰበ ነገር ተፈጥሯል፡፡ ፋታ ያልነበራቸው የምስር ክክ ማሰናጃ አውድማዎችዋ ባዶ ሆነዋል፡፡ ከተማዋን ለሁለት በሚከፍለው በዋና ጎዳናዋ ላይ ሆኖ ግራና ቀኝ እንደ ልብ ይታዩ የነበሩ ድፍን ምስር የሚያበጥሩና የተከካ ምስር የሚያናፍሱ ሠራተኞች እንደቀድሞ አይታዩም፡፡ አልፎ አልፎ ካልሆነ በቀር አብዛኛዎቹ የምስር ክክ ማቀነባበሪያ አውድማዎችዋ ባዶ ሆነዋል፡፡

ለወትሮ ሃምሳና ስልሳ የሚሆኑ ሠራተኞች የሚታዩባቸው አውድማዎች ሳይቀሩ ዛሬ ጭር ብለዋል፡፡ እንደ ወ/ሮ ተናኜ አገላለጽ፣ ‹‹ሥራው ስለቀዘቀዘ ሌላ ሥራ ፍለጋ ሄደዋል፡፡›› ተከክቶና ፀድቶ የተዘጋጀውን ድፍን ምስር የሚጭኑ ተሽከርካሪዎች ሰሞኑን በበኬ አይታዩም፡፡ በኬ ቀዝቅዛለች፡፡ ለመከካት የሚመጣ ድፍን ምስርም ሆነ ተከክቶ ወደ ገበያ የሚላክ ምስር ምርት ያለመኖሩ ደግሞ አቶ መኩሪያን ጨምሮ ኑሯቸውን ምስር ክክ በማዘጋጀት ላይ የተሰማሩትን የአካባቢውን ነዋሪዎች አሳስቧል፡፡

በኬ የቀድሞ ሕይወቷን ያደበዘዘውና አብዛኛዎቹን አውድማዎቿን ባዶ ያደረገው እንግዳ ነገር በቂ የሆነ የምስር ምርት መቅረብ ባለመቻሉ ነው፡፡ ከሁለት ወራት ወዲህ ወደ ከተማዋ ይገባ የነበረው የድፍን ምስር ምርት መጠን እየቀነሰ መጥቶ ከሰሞኑን ጭራሽኑ መጥፋቱ ከበኬ የሚወጣው ምስር ክክ እጥረት እንዲገጥመው ሆኗል፡፡ የምርት እጥረቱ ደግሞ በኬን በማቀዛቀዝ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን የምስር ክክ ገበያን ታይቶ በማይታወቅ ዋጋ እንዲንርም አድርጎታል፡፡

ምስር ክክ ማዘጋጃ ከተማነትዋ የምትታወቀው በኬና በድፍን ምስር መገበያያ በሆነች አሌልቱ ከተሞች ባሉ ገበያዎች ሳይቀር የአንድ ኪሎ ምስር የችርቻሮ ዋጋ 42 ብር ገብቷል፡፡ በአዲስ አበባ የችርቻሮ መሸጫ ሱቆችም ሰሞኑን እስከ 48 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ ከአንድ ወር በፊት ግን የአንድ ኪሎ ግራም የምስር ክክ ዋጋ ተወደደ ተብሎ ይሸጥ የነበረው ከ28 እስከ 30 ብር ነበር፡፡

‹‹በበኬ ከተማ አንድ ኪሎ ግራም ምስር ክክ እንዲህ ባለ ዋጋ ተሽጦ አያውቅም፤›› የሚሉት አቶ መኩሪያ፣ በምስር ማበጠርና ማዘጋጀት ሥራ ላይ ከተሰማሩበት ጊዜ ወዲህ እንዲህ ያለ የምርት እጥረትና ከፍተኛ የሚባል ዋጋ ዕድገት እንዳላጋጠማቸውም ተናግረዋል፡፡ በቀን እስከ ሁለት መቶ ኩንታል ድፍን ምስር በተለያየ ደረጃ የሚዘጋጅበት አውድማ አሁን ሁለትና ሦስት ኩንታል እየተሠራበት ነው፡፡ ይህም ምርቱ ከተገኘ ነው፡፡ ምንም ምስር ያልተሰጠባቸው አውድማዎች በዝተዋል ይላሉ፡፡ አልፎ አልፎ የሚገኘውም ድፍን ምስር ቢሆን ዋጋው አልቀመስ በማለቱ ምስር ገዝተው የሚያዘጋጁ ሠራተኞችን አሽሽቷል፡፡ ጥር 2007 ዓ.ም. አንዱን ኩንታል ድፍን ምስር 1,350 ብር ገዝተው እንደነበር ያስታወሱት አቶ መኩሪያ፣ አሁን በአሌልቱ የምስር ገበያ በ3,400 ብር ለመግዛት እንኳን አልቻሉም፡፡

ባሳለፍነው ማክሰኞ በተንጣለለው አውድማ ላይ ሆነው ከአምስት ኩንታል ያልበለጠ ምስር ክክ እያነፈሱ ያገኘናቸው ወ/ሮ ተናኜ፣ ከሁለትና ከሦስት ወር በፊት ቢሆን ሁለትና ሦስት መቶ ኩንታል ምስር ክክ በሚሠናዳበት አውድማ ላይ በርካታ  ሠራተኞች ይኖሩ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ‹‹በዚያ በሞቀ ሥራ የበረታ ሠራተኛ በሳምንት 1,000 ብር ያገኝ ነበር ይላሉ፡፡ የደከመው 500 ብር አያጣም ነበር፡፡ አሁን ግን ሁሉም እኩል ሆኗል፤›› ብለው፣ የምርት እጥረቱ የፈጠረባቸውን ችግር ገልጸዋል፡፡ ‹‹ይህ አውድማ ሃምሳና ስልሳ ሠራተኛ ሲተራመስበት እንዳልነበር አሁን ይኸው ምንም የለም፤›› በማለት የምርት እጥረቱን ጉዳት ይገልጻሉ፡፡ አሁን እየሠሩ ያሉት ቀድሞ የገባ ምርትን በመሆኑ ይህንን ከጨረሱ በኋላ ነገ ከነገ ወዲያ የሚሠሩት ስለሌለ ግራ ተጋብተዋል፡፡

ለምስር መጥፋት ወይም መወደድ የተለያዩ ምክንያቶች ቢሰጠውም፣ አንዳንድ ነጋዴዎች አጋጣሚውን ተጠቅመው ዋጋ በማናራቸውና ምርቱን መያዛቸው ችግሩ ተባብሷል የሚሉም አሉ፡፡ በተለይ የምስር መወደድ ከተሰማ በኋላ ገበሬውም ምስሩን ያዝ በማድረጉ ወደ ገበያ የሚወጣም ምስር አንሷል፡፡ ነጋዴውም ገበያ የሚወጣውን ለመቀራመት የሚገዛበትን ዋጋ ከፍ በማድረጉ ገበያው እንዲጋጋል ሆኗል የሚል አስተያየት ተሰንዝሯል፡፡ ውድ ከተባለ አንዱን ኩንታል ድፍን ምስር መስከረም 2007 ዓ.ም. ከ1,600 እስከ 1,800 ብር ይገዙ የነበሩ ነጋዴዎች፣ አሁን ግን በዚህ ዋጋ መገበያየት ብርቅ ሆኖባቸዋል፡፡ በእጥረቱ ምክንያት ገበያ የሚወጣውን ድፍን ምስር ለመሸመት ነጋዴዎች ባለፈው ሳምንት ለአንድ ኩንታል ድፍን ምስር እስከ 3,400 ብር እየሰጡ ነበር፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ጨረታ መጀመሩ ነገሩን እንዳባባሰው የሚገልጹት አቶ መኩሪያ፣ ትላልቆቹ ነጋዴዎች እየሰጡ ያሉት ዋጋ እነሱን እንደጎዳቸው ተናግረዋል፡፡ የምስር ዋጋንም አስወድደዋል ይላሉ፡፡

የምስር ዋጋ ከሌላው ጥራጥሬ በተለይ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ለመምጣቱ የቅርብ መረጃዎች ብቻ ሳይሆን ቀደም ብሎ ያለው ሒደቱ ቢያሳይም፣ እንደሰሞኑ አይሆንም፡፡ የማዕከላዊ ስታክስቲክስ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ ለምሳሌ ጥር 2000 ዓ.ም.  በአዲስ አበባ አንድ ኩንታል ድፍን ምስር 524 ብር ይሸጥ ነበር፡፡ ይህ ዋጋ ጥቅምት 2001 ዓ.ም. ወደ 1,127 ብር አድጓል፡፡ በአጠቃላይ በ2000 በጀት ዓመት አማካይ የአንድ ኩንታል ድፍን ምስር ዋጋ 925 ብር እንደነበር የሚያመለክተው ይህ መረጃ፣ በ2006 ዓ.ም. በአማካይ ከ1,800 ብር ተሽጦ ከፍተኛ ዋጋ ተብሎ ነበር፡፡

በአገሪቱ የምስር ምርትና ግብይት ዙሪያ ጥናታቸውን በቅርቡ ይፋ ያደረጉት የወሎ ዩኒቨርሲቲው መምህር አቶ አብርሃም ረዳ እንደገለጹት ግን፣ የአገሪቱ የምስር ምርት መጠን እያደገ መሆኑን ነው፡፡ አሁን እየተፈጠረ ያለው ክፍተት በአቅርቦትና የፍላጎት አለመጣጣም ነው ይላሉ፡፡ ባለፉት አሥር ዓመታት በአማካይ 90,159 ቶን ምስር እየተመረተ ነው፡፡ ይህም ምርት ከ92,998 ሔክታር በላይ በሆነ መሬት ላይ የተመረተ ሲሆን፣ የምርት ዕድገቱም እየጨመረ በመሆኑ አገሪቱ የምስር ምርት እያደገ መሆኑን ያሳያሉ፡፡ ኢትዮጵያ አሁንም ከአፍሪካ ቀዳሚ የምስር አምራች ስትሆን፣ ከአሥሩ ከፍተኛ የዓለም ምስር አምራች አገሮች ውስጥም አንዷ ነች ብለዋል፡፡ ወደፊትም የምስር ምርት ይጨምራል ያሉት እኚሁ ምሁር፣ ምስር ከሌሎች ምርቶች የተሻለ ዋጋ እያወጣ በመሆኑ አርሶ አደሩ እዚህ ምርት ላይ ዓይኑን ጥሏል ይላሉ፡፡

የአገሪቱ የምስር ምርት እያደገ ስለመሆኑም የማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ ጠቅሷል፡፡ በ2003/2004 35,274 ቶን ምስር ተመርቷል፡፡ በ2011/12 የምርት ዘመን 128,000 ቶን የነበረው ምርት በ2012/13 151,499 ቶን ደርሷል፡፡

ስለዚህ እየታየ ያለው ክፍተት የተለያየ ምክንያት ቢኖረውም፣ የአገሪቱ የምስር ፍጆታ እየጨመረ ነው የተባለውም የምርት ዕድገት ፍላጎትን የሚሞላ ካለመሆኑ ጋር እንደሚያያዝ የጠቆሙት አቶ አብርሃም፣ በሰሜን ሸዋ ብቻ ሳይሆን ምስር በሚመረትባቸው አንዳንድ የወሎ ዞኖች ሰሞኑን አንድ ኪሎ ምስር ክክ 40 ብር መድረሱን ጠቁመዋል፡፡

በአሌልቱ የምስር ገበያ ያገኘናቸው የምስር ነጋዴዎችና አምራቾች ደግሞ ለምስር መወደድ በአንዳንድ አካባቢዎች ባሉ የምስር እርሻዎች ላይ የተከሰተ በሽታ በመኖሩ ነው ይላሉ፡፡ የአሌልቱ ነጋዴው አቶ አማረ ስፍራው በዚህ ይስማማሉ፡፡ የምርት እጥረቱም ከዚህ ቀደም ከፍተኛ ዋጋ ተብሎ አንዱን ኪሎ ድፍን ምስር በ22 ብር ገዝተዋል፡፡ ይህም የተወሰነ ጊዜ እንጂ ባለፈው ዓመት እንኳን በውድ ዋጋ ከገበሬው ድፍን ምስር የገዙበት ዋጋ 18 ብር እንደነበር አስታውሰው፣ የሰሞኑ የተለየባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይህ ዋጋ እስከዛሬ ያልታየ ይሆናልም ተብሎ ያልታሰበ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ስታስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ እንደሚያሳየውም፣ በዚህ ወቅት የታየው የምስር ዋጋ እስከዛሬ ያልታየ መሆኑን ነው፡፡

በምስር አቅርቦት የምትታወቀው የጊምቢቹ ወረዳ አርሶ አደር የሆኑትና በአሌልቱ ገበያ ያገኘናቸው አንድ አርሶ አደር፣ ለምስር መወደድ ምክንያቱ ምስሩ ማሳ ላይ በመበላሸቱ ነው ይላሉ፡፡ ‹‹ጥሩ ምርት አልሰጠም፤ መድኃኒት ረጭተን ነበር ግን አልሆነም፤›› ይላሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ዘር አጥተው ያለመዝራታቸውም ለእጥረቱ ምክንያት ነው ይላሉ፡፡

‹‹መስከረም ላይ ዋግ ነገር መታውና ምርት አልሰጠም፤›› የሚሉት የአሌልቱ የእህል የጅምላ ነጋዴ አቶ አማረ፣ ለምስር ዋጋ መወደድና መጥፋት ዋናው ምክንያት ምርቱ ቡቃያው መጋሸቡ ነው ብለዋል፡፡ ይህም ምርት ጥራት የሌለው እንዲሆን ከማድረጉም በላይ በቂ ምርት እንዳይኖር አድርጓል በማለት የራሳቸውን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

አቶ አብርሃም ረዳ ግን በሰብሉ ላይ በሽታ ሊኖር ቢችልም ለእጥረቱ ዋነኛ ምክንያት ሊሆን አይችልም ይላሉ፡፡ በጥቅል ሲታይ ግን የአገሪቱ የምስር ምርትና የምስር ማምረቻ መሬት ይዞታ እየጨመረ ቢመጣም፣ አሁን ያለው የአገር ውስጥ ፍላጎትና እየተመረተ ያለው ምስር በቂ ባለመሆኑ የተፈጠረ እጥረት ነው ብለዋል፡፡ አምራቹ ራሱ ከፍተኛ የምስር ተጠቃሚ እንደሆነ በመግለጽ ችግሩ የፍላጎት መጨመር ስለመሆኑ ያሰምሩበታል፡፡ በአገሪቱ የምስር ፍጆታ ከፍተኛ በመሆኑ መንግሥት ምስር ወደ ውጭ እንዳይላክ ማድረጉንም አስታውሰዋል፡፡

ከዕገዳው በፊት ግን የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው፣ በ2005 እስከ 2006 ዓ.ም. 1.08 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የጥራጥሬ ምርቶች ለውጭ ገበያ ቀርቦ ነበር፡፡ ከዚህ ውስጥ የምስር ድርሻ 11,040  ኩንታል ነው፡፡ ይህ መጠን ግን በ2006/2007 ወደ 7,150 ኩንታል ወርዷል፡፡ በ2007/2008 ግን ወደ ውጭ የተላከው ምስር መጠን ወደ 172,190 ኩንታል ሊደርስ ችሎ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ወደ ውጭ እንዳይላክ ተደርጓል፡፡

እንደ አንዳንድ ገበሬዎች እምነት ዘንድሮ የተፈጠረው ችግር ተቀርፎ ምርቱን በደንብ ማቅረብ የሚቻለው የሚቀጥለው ዓመት ነው፡፡ ነገር ግን ቢወደድም ምስር ከገበያ አይጠፋም ይላሉ፡፡ ምስር ከገበያ የማይጠፋበት ምክንያት ደግሞ ከጥቂት ሳምንት በፊት የምስር ዋጋ እየተወደደ ሲመጣ ገበሬው በእጁ ያለውን ምርት ያዝ ስላደረገ ሊያወጣው ይችላል በማለት ነው፡፡ ገበሬው ቀስ በቀስ ያወጣዋል ግን የምስር እጥረቱ መቀጠሉ እንደማይቀርም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

‹‹ገበሬው የሚያቀርበው ምርትና ተቀባዩ ነጋዴ አልተጣጣመም፡፡ ተቀባይ በዛ ምርቱ አጠረ፤›› የሚለው ምስር አንፋሽ ወጣት ደግሞ፣ ነጋዴዎች የሚሰጡትን ከፍተኛ ዋጋ ካስቀሩ መጠነኛ ለውጥ ይኖራል ይላል፡፡ ካልሆነ ግን የምስር ዋጋ አልቀመስ ማለቱን ይቀጥላል ብሏል፡፡

አሁን ባለው ዋጋ ምስር ክክ አዘጋጅቶ ከበኬ ለማስጫን የሚፈጀው ጠቅላላ ወጪ ከ38 ብር በላይ ስለሚሆን፣ በዚህ ዋጋ የተዘጋጀ ምስር አዲስ አበባ ላይ ሊሸጥ የሚችልበት ዋጋ ከፍተኛ ይሆናል፡፡

የበኬዋ ወ/ሮ ተናኜ አሁን የገጠማቸው ችግር እንዴት ሊቀረፍ እንደሚችል ባይገባቸውም ይህ ችግር እንዲቀረፍላቸው ይመኛሉ፡፡ በእጥረቱ ምክንያት የራሳቸው ገቢ ሊቋረጥ ስለመሆኑ ብቻ ሳይሆን የሥራው መቀዛቀዝ የበኬን ሆቴሎች አጠቃላይ ገበያ ማቀዛቀዙ ጭምር እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል፡፡

አቶ አብርሃም ደግሞ ምስር ከሌሎች ጥራጥሬና የእህል ዘሮች አንፃር ሲታይ በቂ ምርምር ያልተደረገበት በመሆኑ ምርምር ቢደረግ የተሻለ ምርት የሚሰጥ ዘር በማውጣት ምርቱን ማሳደጉ ጊዜ የሚሰጠው እንዳልሆነ ይጠቅሳሉ፡፡ እንደ እርሳቸው እምነት ይህ ዘላቂ መፍትሔ ነው፡፡ ትኩረት የተነፈገው ግን እጅግ አስፈላጊ ምርት መሆኑን ጠቅሰው፣ ምርቱን ከዚህም የበለጠ ለማሳደግ ምርታማ የሆኑ ዝርያዎችን ማውጣት ብቻ ሳይሆን አስተራረሱም መቀየር አለበት ይላሉ፡፡ ይህ ካልሆነ በአቅርቦትና እየጨመረ ከመጣው ፍላጎት ማጣጣም አይቻልም ብለዋል፡፡

ከአገሪቱ ከሚመረተው ምስር ውስጥ ደግሞ ከ40 በመቶ በላይ የሚሆነው እዛው ምስር አምራች ለሆኑ አካባቢዎች የሚውል ነው፡፡ ይህ ምርቱ ዋነኛ የገቢ ምንጫቸው ብቻ ሳይሆን ዓብይ ምግባቸውም መሆኑን ያመለክታል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች