Friday, June 9, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አሐዱክስ የምግብ ውጤቶች ማምረቻ ከጅማሬው የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ሥጋት ሆኖበታል

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በቢሾፍቱ (ደብረ ዘይት) ከተማ በ78 ሔክታር መሬት ላይ የተንጣለለው፣ አሐዱክስ የምግብ ውጤቶች ማምረቻ አክሲዮን ማኅበር፣ 800 ሚሊዮን ብር የሚያወጣው ፋብሪካ ሥራ ጀመረ፡፡ በእንግሊዙ ቫሳሪ ግሎባል ኢንቨስትመንት ግሩፕና በአሐዱ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ የእሽሙር ስምምነት መሠረት የግንባታ ሥራውን አጠናቆ ምርት መጀመሩን ይፋ አድርጓል፡፡

የአሐዱክስ አክሲዮን ማኅበር ወደ ምርት ተግባር መሸጋገርን በማስመልከት በፋብሪካው ተገኝተው የመረቁት ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ ሲሆኑ፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሙክታር ከድር፣ የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ አቶ አለማየሁ ከፍያለሁና ሌሎችም ባለሥልጣናት ተገኝተዋል፡፡

በአሐዱ ኩባንያና በቫሳሪ ግሎባል መዋጮ እንዲሁም ከዳሸን ባንክ በተገኘ ብድር በጠቅላላው በ36 ሚሊዮን ዶላር (800 ሚሊዮን ብር) ወጪ የተገነባው የምግብ ውጤቶች ማምረቻ ፋብሪካ፣ የተለያዩ የብስኩት ዓይነቶችንና የፓስታ ምርቶችን በማምረት ለገበያ ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከአገር ውስጥ ገበያ ባሻገር ወደ አፍሪካ፣ መካከለኛው ምሥራቅ አገሮችና ወደ አውሮፓ ምርቶቹን ይልካል ተብሏል፡፡ የአሐዱ ኩባንያ ባለቤትና የአሐዱክስ ምግብ ውጤቶች ማምረቻ ፋብሪካ አክሲዮን ባለድርሻ አቶ ሰሎሞን ወንድምነህ እንደገለጹት፣ የፋብሪካው ግንባታ በሦስት ዓመት ውስጥ ተጠናቆ ወደ ሥራ ለመግባት ችሏል፡፡ በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት ውስጥም ኢንቨስት የሚያደርገው ገንዘብ መጠን 150 ሚሊዮን ዶላር ወይም ሦስት ቢሊዮን ብር እንደሚደርስና ከዚህ ውስጥ ሃምሳ ከመቶ ገቢው ከኤክስፖርት ገበያ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡ በመሆኑም ከዓመታዊ ገቢው ውስጥ 32 ሚሊዮን ዶላሩን ከውጭ ገበያ እንደሚያመነጭ ይጠበቃል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ600 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል የፈጠረው አሐዱክስ አክሲዮን ማኅበር፣ ከሦስት ዓመት በኋላ ዕውን ያደርገዋል በተባለው ማስፋፊያ ፕሮጀክት አማካነት ከ3ዘ000 ያላነሱ ሰዎች የሥራ ዕድል ያገኛሉ ተብሏል፡፡

አሐዱክስ አክሲዮን ማኅበር ግንባታ ከመጀመሩ ቀድሞ 42 ሔክታር መሬት በዝቅተኛ የሊዝ መነሻ ሒሳብ ተሰጥቶት ሥራ ሲጀምር፣ በ12,600 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ የብስኩት ፋብሪካ ሕንፃ፣ በ6,048 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የፓስታ ፋብሪካ፣ በ1,175 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ባለሁለት ፎቅ ሕንፃና በ450 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የኃይል መቀበያና ማሰራጫ ሕንፃ ግንባታዎችን እንዳካሔደ የገለጹት አቶ ሰሎሞን፣ ለማስፋፊያ ተጨማሪ ቦታ ጠይቆ 36 ሔክታር መሬት እንዳገኘ ተናግረዋል፡፡  

ይህም ሆኖ ፋብሪካው የኤሌክትሪክ ኃይል ቢያገኝም ተደጋጋሚ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ችግር እየገጠመው እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ ‹‹ስለሆነም የአካባቢው ኤሌክትሪክ ማሰራጫ ጣቢያ ማስፋፊያ ተደርጐበት አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንድናገኝ እንዲደረግ አመራር እንዲሰጥልን በአክብሮት እንጠይቃለን፤›› በማለት አቶ ሰሎሞን ጥያቄያቸውን ለባለሥልጣናቱ አቅርበዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ከቢሾፍቱ ከተማ እስከ ፋብሪካው ድረስ ያለው የጠጠር መንገድ ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች ጥሬ ዕቃ የሚያመላልሱ ከባድ ተሽከሪካሪዎች የሚያዘወትሩት መንገድ በመሆኑ፣ በየጊዜው እየተበላሸ ለሥራችን አስቸጋሪ ሆኖብናል ያሉት አቶ ሰሎሞን፣ ይህንን በሚመለከት ለኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሙክታር ከድር ጥያቄ ቀርቦ መንገዱ ‹‹ከጥርጊያነት ወደ አስፋልትነት እንደሚያድግ ተስፋ ሰጥተውን የነበረ ሲሆን፣ የአስፋልት ሥራው እውን እስከሚሆን በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን፤›› ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ሰሎሞን ገለጻ የምግብ ውጤቶች ማምረቻ ፋብሪካው የሚገኘው አግሮ ኘሮሰሲንግ ዞን ውስጥ ቢሆንም፣ የኢንዱስትሪያል ውጤቶች አምራች የሆኑ ሌሎች ፋብሪካዎች ቦታ ተሰጥቷቸው ማምረት መጀመራቸው ስብጥሩ ከዓለም አቀፍ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ሰርተፊኬት አሰጣጥ ጋር የሚፃረር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሌሎች የኢንዱስትሪና የኬሚካል ውጤቶችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎች በአካባቢው መኖራቸው ‹‹የውጭ አገር ገበያ ምርት አቅርቦታችን ላይ ተፅዕኖ እንዳያሳድርብን ከፍተኛ ሥጋት ስላለን የሚመለከታቸው ሁሉ አፅንኦት ሰጥተውት የፋብሪካዎች ብክለትን በአፋጣኝ እንዲያስቆሙልን በአክብሮት እንጠይቃለን፤›› በማለት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አቶ ሰሎሞን ባሰሙት ንግግር፣ ቫሳሪ ግሎባል ግሩፕ ከኩባንያቸው ጋር አብሮ ለመሥራት የእሽሙር ስምምነት የፈጸመበትን አኳኋን አስታውሰዋል፡፡ ቫሳሪ ግሎባል ከመምጣቱ አስቀድሞ የፋብሪካው ዋና ዋና ሕንፃዎች ማለትም የብስኩት ፋብሪካ ሕንፃ፣ የፓስታ ፋብሪካ ሕንፃ እንደዚሁም የጽሕፈት ቤት ሕንፃ ግንባታ ሥራዎች ተገባደው የማጠናቀቂያ ሥራ ሲቀራቸው፣ ከፊል የብስኩት ማምረቻ መሣሪያዎች ከጣልያን ተጓጉዘው ፕሮጀክት ጣቢያ በደረሱበት ወቅት ቫሳሪ ግሎባል ግሩፕ የተባለው የእንግሊዝ ኩባንያ በአሐዱክስ ኩባንያ ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት በማሳየቱና እነአቶ ሰሎሞንም በመስማማታቸው፣ ጥናቶችና ድርድሮች ተከናውነው እ.ኤ.አ. በሴፕቴምበር 2013 በይፋ መቀላቀሉን አቶ ሰሎሞን አስታውቀዋል፡፡ የአሐዱክስ አወቃቀር ከግል ኩባንያነት ወደ አክሲዮን ማኅበርነት እንዲቀየር ተደርጐ የዛሬውን ስያሜ ሊይዝ እንደቻለም ጠቅሰዋል፡፡

በዚህ መንገድ የተጣመሩት ሁለቱ ኩባንያዎች ምን ያህል የአክሲዮን ድርሻ እንዳላቸውና እያንዳንዳቸው ምን ያህል ገንዘብ እንዳዋጡ ከመግለጽ መቆጠብን መርጠዋል፡፡ የሁለቱ የቢዝነስ ምስጢር ስለሆነ ይፋ አናደርግም ብለዋል፡፡ ከዳሸን ባንክ መበደራቸውን ግን ይፋ አድርገዋል፡፡

ቫሳሪ ግሎባል ግሩፕ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ሲያደርግ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ የቫሳሪ ግሎባል የቦርድ አባል የሆኑት ድሬክ ጎርደን እንዳስታወቁት፣ እስካሁን በተሳተፈባቸው መስኮች፣ በአሐዱክስ ያለውን ድርሻ ጨምሮ በጠቅላላው ከ200 ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ ገንዘብ ኢንቨስት አድርጓል፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት በጥረት ኢንዶውመንት ፈንድ ሥር ከሚተዳደሩት አንዱ በሆነው ዳሸን ቢራ ፋብሪካ ውስጥ ኢንቨስት ማድረጉ ይታወሳል፡፡

በአንፃሩ አሐዱ ኩባንያ ሃያ ዓመታትን ያስቆጠረ የንግድ ተቋም ሲሆን፣ አሐዱ ሻይ  በተባለው የሻይ ቅጠል ምርቱና ማቀነባበሪያ፣ መድኃኒት በማስመጣትና በማከፋፈል ሥራው በተለይ በአክሱም መድኃኒት ቤቶች ይዞታዎቹ ይታወቃል፡፡ ከእነዚህ ባሻገር በዘመናዊ እርሻ ልማት፣ በሪል ስቴት፣ በምርት ማሸጊያና በንግድ ዘርፎች የተሰማራ ኩባንያ መሆኑን የኩባንያው የኋላ ታሪክ ያስረዳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች