አቶ ሬድዋን ሁሴን፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር
ቅዳሜ ሚያዝያ 24 ቀን 2007 በኢሊሊ ሆቴል የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ተከብሮ መዋሉ ይታወሳል፡፡ በዕለቱ ጥናታዊ ጽሑፎች የቀረቡ ሲሆን፣ ሰፋ ያለ ውይይትም ተካሂዷል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴንን፣ የሚዲያን እንደ አንድ የኢንቨስትመንት መስክነት በተመለከተና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ነአምን አሸናፊ እና ውድነህ ዘነበ አነጋግረዋቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- መንግሥት የሚዲያውን ዘርፍ እንደ ኢንቨስትመንት አይመለከተውም የሚል አስተያየት አለ፡፡ ከዚህ አንፃር መንግሥት ዘርፉን እንደ ኢንቨስትመንት ይመለከተዋል? ካልሆነ ለምን? ከሆነስ ዘርፉን ለመደጎም ያደረጋቸው ማትጊያዎች ምንድን ናቸው? በዝርዝር ቢያቀርቡልን፡፡
አቶ ሬድዋን፡- ሚዲያ እንደሚታወቀው አንድ ሰፋ ያለ የሐሳብ ግብይት መድረክ ነው፡፡ የአገራችን ዴሞክራሲና ልማት በአጠቃላይ አንድ ዳር መድረስ ካለበት በዚህ የሐሳብ ግብይት መድረስ መቻል አለበት፡፡ ይህ ደግሞ እንዲሆን የንግድም የሕዝብ ብዙኃን መገናኛዎች መስፋፋት አለባቸው፡፡ ለዴሞክራሲ ያለው ትርጉም ይታወቃል፡፡ በዴሞክራሲ ሥርዓት ውስጥ ያለው ሚና ጉልህ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዚህ ረገድ ጀማሪ እንደመሆኑ መጠን ራሱ ሚዲያው የሚገራበትንና የሚጎለብትበትን አጠቃላይ ሐሳቦችን በተመለከተ ግን ጥቅል ጉዳይ እንዳለ ሆኖ፣ ዝርዝር የኢንቨስትመንት ገጽታ ያላቸው አፈጻጸሞች ጋ ሲገባ በቀጣይ መጎልበትና መታየት ያለባቸው ነገሮች እንዳሉ መውሰድ ይቻላል፡፡ አስቀድመው ብዙ ተፅዕኖ አላቸው ተብለው በኢንቨስትመንት የተለዩ ጉዳዮች ላይ በተለያየ የማትጊያ መንገድ የተሞከረ ነገር አለ፡፡ ነገር ግን እያንዳንዱ ዘርፍ እየጎላ እየጎላ ሲመጣ ተዋናዮቹም እየጨመሩ የሚመጡ መሆኑ ሲረጋገጥ፣ ተሳትፏቸውም በዚያው ልክ እየጎለበተ ሲመጣ ይህንን የሚመጥኑ አሠራሮችን ማበጀት አስፈላጊ ይሆናል፡፡ እስካሁን ያለው ጎላ ብሎ እየወጣ የነበረው የኅትመት ሚዲያው ነው፡፡ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያው ኤፍኤሞች ጋ ተይዞ ነው ያለው፡፡ እስካሁን የነበረው ጠንካራ ጎን ተብሎ የሚወሰደው ወደ ሚዲያው የሚገቡ ሰዎችን ፈጠን ብሎ የማስተናገድ ሥራን የመውሰድ ነው፡፡ ለምሳሌ የኅትመት ሚዲያው ከተወሰደ ፈቃድ እንዳይጠየቅ ምዝገባ ብቻ ይበቃዋል በሚል የተወሰደው አንዱ ሰፋ ያለና ሚዲያ እንዲኖር ከማድረግ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያውም ጋ ኤፍኤሞች ጋ ነው አሁን ሰፋ ያለ በግል ዘርፉ እንቅስቃሴ እየተደረገ ያለው፡፡ ይህንንም በተቻለ መጠን በተለይ ባለፈው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ሰፋ ባለ ሁኔታ ለማስተናገድ የሚያስችል ዕቅድ ተይዞ ሲኬድበት ነበር የነበረው፡፡ አዲስ የሥራ መስክ ስለሆነ ብቃት ያለው ሰው በስፋት ገብቶ የሚንቀሳቀስበት አካባቢም አይደለም፡፡ ይህን ታሳቢ ያደረጉ ሌሎች ተጨማሪ ድጋፎች እንደሚፈለጉ ይታወቃል፡፡
አሁን አንዳንድ ጊዜ ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ ሌሎች አካባቢዎች ሰፋ ያለ የግል የመገናኛ ብዙኃን እንዲመጣ ለማድረግ ተሞክሮ ብዙ አይደለም እየመጣ ያለው፡፡ ባህር ዳር፣ ሐዋሳ፣ መቐለና እንደዚህ የመሳሰሉት አካባቢዎች ዘንድ ከአዲስ አበባ ተመጣጣኝ ስፋት ያለው እንዲመጣ ለማድረግ የሚሞከርበት ነገር አለ፡፡ ብቃት ያለው ሰው ብዙ አይመጣም፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም የተወሰኑ ማየት የሚገቡን ነገሮች እንዳሉ መውሰድ ይቻላል፡፡ ስለዚህ ሐሳቡ አለ፣ ጅምሩ አለ፡፡ ግን የተወሰኑ አካባቢዎች ላይ ችግሮችን መፍታት ይጠይቃል፡፡ አንድ ችግር የነበረው በኅትመት ሚዲያው ላይ ከወረቀት ጋር የሚያያዘው ነው፡፡ እርሱ ባለፈው ጊዜ ስናነሳው እንደነበረው አገር ውስጥ የፐልፕና የወረቀት ኢንዱስትሪን ማደፋፈር፡፡ እንጨት አለ፣ ሰፋ ያለ የሚባክን ጥሬ ሀብት ነው ያለው፡፡ ይህን መልሶ መጠቀም የሚያስችል ማበረታቻ ቢኖር የተሻለ ይሆናል፡፡ ብዙ የደን ሽፋናችንን እያስገባን እያሳደግን ከዚህ ጋር የተያያዙ የወረቀት ምርት ኢንዱስትሪዎችን ማስፋፋት ጠቃሚ ይሆናል ተብሎ፣ አሁን እየተከለሰ በመጣው የኢንቨስትመንት ማዕቀፍም አንደኛው ማደፋፈሪያ ከሚሰጣቸው አካባቢዎች ያለው እርሱ ነው፡፡ ይህ ሲሆን የኅትመት ሚዲያው ሰፋ ብሎ መንቀሳቀስ ይችላል ማለት ነው፡፡
ሁለተኛው አሁን በቅርቡ እያጠናነው የመጣነው ያለነው የሥርጭት አድማሱ መስፋፋት መቻል አለበት፡፡ አሁን ያሉትም ቢሆኑ በአዲስ አበባ ዙሪያና በዋና ከተሞች የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ ሰፋ ብሎ ወደታች የሚሄድበት ሁኔታ የለም፡፡ ስለዚህም ሚዲያ ውስጥ አዘጋጅቶ ማሳተም ብቻ ሳይሆን ተቀብሎ ማሠራጨትም እንደ አንድ የሥራ መስክ መወሰድ አለበት፡፡ ስለዚህም ጋዜጦቹን የሚያሠራጩ አካላት ተደራጅተው እንዲንቀሳቀሱ፣ ተደራጅተው ሲንቀሳቀሱ ደግሞ የሚሠሩበት ቦታ እንዲኖራቸውና ለሚዲያ የሚሆን ቦታ መኖር አለበት ብለን አጥንተናል፡፡ ከአዲስ አበባ እንዲጀመር ዝግጅቱ አልቋል፡፡ ሌላ ቦታ መለየትና ይህን ማዘጋጀት ይህን የመሰለ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ እዚያው ሳሉ ምን ይሆናሉ? የማስታወቂያ ሥራ መሥራት ይችላሉ፡፡ ጋዜጣ ገዝቶ የማንበብ ፍላጎት የሌለው ሰው እዚያው አረፍ ብሎ አንብቦ መልሶላቸው ሊሄድ ይችላል፡፡ ሌሎች አገልግሎቶችንም መስጠት ይችላሉ፡፡ አንድ የሥራ መስክ ይሆናል ማለት ነው፡፡ እንደ አንድ የሥራ መስክ በጥቃቅንና አነስተኛ ሥር ብናደርገው ይህ ሥራ ብዙ ሰዎች የሚሰማሩበት ይሆናል፡፡ በአዲስ አበባ ከተቻለ በክልል ከተሞች ይቻላል፡፡ በክልል ከተሞች ከተቻለ መጠኑ አነስ ቢልምና ተዋናዮቹ አነስ ቢሉም፣ እንደ አንድ የሥራ መስክ ግን ብናደራጃቸውና የመንቀሳቀሻ ገንዘብ ካጡ ከማይክሮ ፋይናንሶች ጋር አያይዘን ብድር ቢያገኙ የመጀመሪያ ጋዜጦችን የሚረከቡበት ገንዘብ እጦት ወደ ሥራ እንዳይገቡ አይከለክላቸውም፡፡ አንድ ቦታ ላይ ሰብሰብ ተደርገው ብዙ ሰው የሚስተናገድባቸው ሱቆች ቢዘጋጅላቸው ሰው ሲያልፍ ሲያገድም መግባት ይችላል፡፡ አሁን እነርሱ ናቸው የሚዞሩት፡፡ እነሱ ሲዘዋወሩ ደግሞ ከሚፈልጋቸው ሰው ጋር ይተላለፋሉ፡፡ ቦታ ካለው ግን በማንኛውም ሰዓት ላይ ጊዜ ያለው ሰው የት ቦታ ሄዶ ጋዜጦችን መግዛት እንዳለበት ለይቶ ያውቃል፡፡ ብዙ ሰው ወደዚያ መሄድ ይችላል ማለት ነው፡፡ አንዱ እንደ አዲስ የጀመርነው ያለነው ሥራ ትግበራው ላይ የተወሰነ መዘግየት አለው እንጂ ዳር ይዟል ማለት ነው፡፡ ማይክሮ ፋይናንሶች አሁን ከአዲስ አበባ ጀምሮ የብድር ሥርዓት አመቻችተዋል፡፡ ጋዜጣ በአማተር መስክም ሆነው በትንሽ መጀመር ከፈለጉ ብድር እንዲያገኙ፣ በአዟሪነት መልክም መንቀሳቀስ ከፈለጉ ብድር እንዱያገኙ፣ በዚህ ደግሞ ተሰባስበው መሄድ የሚችሉበትን ሥርዓት በማዘጋጀት በቂ ጥናት አልቆ አሁን እንደ አዲስ የሚጀመር ሥርዓት ሆኗል፡፡ ይህንን በትላልቅ ማሽኖችና በመሳሰሉት እንዴት እንደግፈው የሚለውንም ማሰብ ግን እንደ ቀጣይ ኃላፊነት ሊወሰድ የሚችል ተግባር ነው በሚለው መግባባት እንችላለን፡፡
ሪፖርተር፡- ባለፉት 20 ዓመታት መንግሥት ኢኮኖሚውን በማበረታታት በኩል ትልቅ ሥራ ሠርቷል፡፡ ፕሬሱንና ሌላውን የሚዲያ ዘርፍ ግን ብዙም አላበረታታውም፡፡ እስካሁን እንደምናየው የሚዲያ ባለሙያዎች ናቸው የሚዲያ ባለቤቶች፡፡ እየታገሉ ነው የመጡት፡፡ እስካሁን ድረስ በሌሎች ዘርፎች ብድር ሊኖር ይችላል፡፡ እዚህ ጋ ግን ማስያዣ ይጠይቃል፡፡ የሚዲያው ዘርፍ ማስያዣ ስለሌለውና በሕገ መንግሥቱ ውስጥ በሕግ ጥበቃ እንደሚደረግ ስለሚገልጽ፣ ከዚህ አንፃር መንግሥት ምን ለማድረግ ያስባል?
አቶ ሬድዋን፡- የማስያዣው ጉዳይ ዞሮ ዞሮ የባንኪንግ ሥርዓት አንድ ሥራ ሆኖ መሄዱ አይቀርም፡፡ ኢንቨስትመንት ነው፡፡ ለዚህ ኢንቨስትመንት ባንኮች ገንዘባቸውን ሲያበድሩ ችግር ሲፈጠር እንዴት መያዝ እንዳለባቸው እርግጠኛ ሆነው የሚሄዱበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ መስኩ ምን ያህል ያተርፋል አያተርፍም የሚለው ደፍሮ የሚገባበት ሰው የራሱ ውስንነት ያለው ነው የሚሆነው፡፡ ኢንዱስትሪው ግን እየጨመረ ሲመጣ ራሱ የሚወልዳቸው አዳዲስ የአሠራር ዘዴዎች መምጣታቸው አይቀርም፡፡ ባንኮችም ፍላጎት ሊያድርባቸው ይችላል፡፡ ሁለት ሦስት ተቋማት በዚህ መስክ ተሰማርተው በበቂ ደረጃ አትራፊ መሆናቸው ሲረጋገጥ፣ ከእነዚህ ተቋማት ጋር መሥራት ከአዳዲስ ጀማሪዎችም ጋር አብሮ መሥራት ሊያዋጣ እንደሚችል ባንኮችም ኢንዱስትሪውን እያዩት ሲመጡ የማበደር ፍላጎታቸው አብሮ ይመጣል፡፡ ስለዚህ በመንግሥት ግፊት አበድር አታበድር ወደሚል ከሚገባ፣ በፋይናንሻል ሥርዓት በአጠቃላይ በባንክ ሥርዓት ውስጥ ያዋጣል አያዋጣም የሚለውን አጥንተው ራሳቸው እንዲገቡበት ከማድረግ ያለፈ ሊሄድ አይቻልም፡፡ ሌላው ከኢንዱስትሪ ጋር የምትነጋገረው በወለድ ምጣኔ ነው፡፡ ምን ያህል ግብር እናቆይላቸው? ምን ያህል የወለድ ምጣኔው ነው? ወደ ኢንዱስትሪና ልማት ባንክ ይሂዱ ወይ ደግሞ ወደ ንግድ ባንክ ይሂዱ የትኛው የተሻለ ሊያስተናግዳቸው ይችላል የሚለውን ነው ልትለይ የምትችለው እንጂ፣ ማስያዣ ሳያስይዙ አበድሩ የሚለው ከባንኮቹ ከራሳቸው አሠራር ጋር አብሮ አይሄድም፡፡ ኢኮኖሚያዊም አይሆንም፡፡ አሠራሩ እንዳለ ሆኖ ይህ ዘርፍ ግን እንዲጠናከርና ትርፋማነቱ እንዲጎለብት፣ በአጠቃላይ በሚደረጉ ድጋፎች በመረጃ አቅርቦቱ ጥሩ ዜና ሠርተው ጥሩ አድማጭና አንባቢ እንዲያገኙ በሚደረገው ጥረት ላይ ከተሳካላቸውና አድማሳቸው እየሰፋ ከሄደ፣ ከመሀል ከተማ ወጥተው ብዙ ቦታ መዳረስ ከቻሉ፣ በእነዚህ መስኮች ኢንቨስት ማድረግ የሚያዋጣ መሆኑን በሕዝቡ በኩል ኢንበቨስት የማድረግ ፍላጎት ይጨምራል፡፡ በባንኮቹ ወገን ያለው የማበደር ፍላጎት ይጨምራል፡፡ እንጭጭ ነው ዘርፉ በሚለው ከተግባባን እንዲያድግ በሁሉም በኩል ድጋፍ ያስፈልጉታል፡፡ ሲያድግ ግን ዞሮ ዞሮ የኢኮኖሚው ፍላጎትና አቅርቦት ነው የሚወሰነው የሚለውን መያዝ ግን የሚያዋጣ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- መንግሥት የተለያዩ ዘርፎችን ለማበረታታት የተለያዩ ባለሀብቶችን ከመጋበዝ ባለፈ የተለያዩ ማትጊያዎችን ያቀርባል፡፡ ከዚህ አንፃር ለሚዲያው ዘርፍ የተደረገ የተለየ ማትጊያ አለ?
አቶ ሬድዋን፡- በሁለት መንገድ እንየው፡፡ አንደኛ አሁን መንግሥት የሚያደፋፍራቸው ከውጭም ሰዎችን መጥታችሁ መሥራት አለባችሁ የሚላቸው ዘርፎች ሁለት ሦስት ነገሮች አሏቸው፡፡ አንዱ አምርተው ወደ ውጭ ዕቃ ልከው የውጭ ምንዛሪ ለአገራችን በስፋት የሚያስገቡ መሆን አለባቸው፡፡ ከዚህ የሚገኘው ሌላኛውንም ኢኮኖሚ ደግፎ መሄድ ስለሚችል፡፡ ሁለተኛው ብዙ ሰው ቀጥረው ብዙ የሥራ ዕድል ፈጥረው በርካታ ዜጎችን ራሳቸውን እንዲችሉ ኑሮአቸው እንዲቀየር ከማድረግ አንፃር ካላቸው ፋይዳ፡፡ ሦስተኛው እኛ ጀማሪ ኢንዱስትሪያላይዜሽን ውስጥ ያለን ከመሆናችን ጋር ተያይዞ አዳዲስ ቴክኖሎጂ እያመጡ ዜጎቻችን ስለቴክኖሎጂ እየተማሩ፣ የራሳቸውን እጅ እያፍታቱ ነገ ወደ ኢንዱስትሪ መሄድ በምንችልበት ሁኔታ ላይ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ያላቸው ፋይዳ ጉልህ የሆኑትን መርጦ እነዚህ ላይ ይረባረባል፡፡ ሚዲያው ጋ ከወሰድነው በሐሳብ ግብዓቱ የራሱ ፋይዳ አለው፡፡ ነገር ግን ልክ የባንኩን ዘርፍ ለውጭ ሰው እንደዘጋነው ይህም ዝግ ነው፡፡ ሁለተኛው ራሳችን ዘንድ ሲመጣም አንዳንድ ጊዜ ከትርፍ ባሻገር በሚዲያው ላይ የመሰማራት ነገር የአቋም ጉዳይ ሆኖ ነው የሚመጣው፡፡ እዚህ አካባቢ ላይ አንድ አስተዋጽኦ አበረክታለሁ ብለህ ካላመንክበት ያን ያህል የጎላ ትርፍ አገኛለሁ ብለህ ሲጀምር አትመጣም፡፡ የምትሠራው ሥራ ጤናማ ሆኖ በምትሠራው ሥራ እየተወደድክ ሄደህ ብዙ ብዙ አድማጭ፣ ተመልካችና አንባቢ እያገኘህ ስትመጣ የራሱ የሆነ ትርፍ አለው፡፡ ነገር ግን ፈተናውም ከበድ ይላል፡፡ በዚህ ረገድ ብዙ ሰዎች ደፍረው የሚገቡበት አይደለም፡፡ ያልናቸውና ሦስቱንም ካየን መንግሥት የተለየ ተፅዕኖ ፈጥሮና በስፋት ተፅዕኖ ያላቸው ነገሮች አድርገህ ከመውሰድ፣ ድባቡን ክፍት በማድረግ የፈለገ ሰው እንዲሰማራ ነገሮችን ቀለል ለማድረግ፣ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ዋናው ጥማቱ መረጃ ስለሆነ መረጃ እንዲያገኝ ለማድረግ ነው ሚዲያን ልታበረታታው የምትችለው፡፡ በዚህ ረገድ የተሠሩ ሥራዎች አሉ፡፡ ነገር ግን ፈተናዎቹ ቀላል ስላልሆኑ እነዚህን ፈተናዎች ደግሞ በሒደት የምናየው ነው የሚሆነው፡፡
ሪፖርተር፡- ለአገር ዕድገት የሚዲያው ዘርፍ ይበጃል ከተባለ ያው ጥበቃና ማትጊያ የግድ ያስፈልጋል፡፡ ሌሎች ባለሀብቶች ወደዚህ ዘርፍ መግባት እየፈለጉ ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ ተመልክተው ፍርኃት ሊገባቸው ይችላል፡፡ ለእነዚህ ሰዎች ምን መልዕክት ያስተላልፋሉ?
አቶ ሬድዋን፡- ሁለት ነገር ነው፡፡ አንደኛ ሚዲያው ራሱ ነው፡፡ ሚዲያው ራሱ ነው ሲባል ሰሞኑን ስናነሳ እንደነበረው የሚዲያ ካውንስል መኖር ነው፡፡ ሰው የሚፈራው ከጥቂቶች በስተቀር ሚዲያው ተናዳፊ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ተናዳፊ ሲሆን የረጅም ጊዜ ሕይወት እንደሌለው የሚያሳይ ምልከታ እየሰጠ ነው የሄደው፡፡ በዚህም ምክንያት የብዙውን ሰዎች አትኩሮት፣ ተስፋ፣ ሕይወትና ወደ ተረጋጋና ወደ ተሻለ መንገድ የሚያመራ ባልሆነበት ሁኔታ ላይ ከእንዲህ ዓይነት ሚዲያ ጋር እንዴት አብሬ እዘልቃለሁ ብሎ ቢዘጋ ነባራዊ ነው፡፡ ይህ ድባብ ባለበት ሁኔታ ይህ የሚፈጥረው ፍትጊያ በራሱ ሚዲያ ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ ለመፈለግ ቀርቶ ከተፈጠረ ሚዲያ ጋርም እንኳን አብሮ በሽርክና መሥራትን ሁለቴ፣ ሦስቴ እንዲያስብ ያስገድደዋል፡፡ ስለዚህ አንደኛው ሚዲያው ራሱ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ፣ የኢትዮጵያን አጠቃላይ ኅብረተሰቦች ግጭት ውስጥ ያስገባ፣ የኢትዮጵያ ልማትና ዲሞክራሲ ያለበትን ደረጃ የወሰደና የኢትዮጵያን አጠቃላይ እንቅስቃሴ የሚያንፀባርቅ፣ ነገር ግን ከውጭውም ጋር አያይዞ ሊወስድ የሚችል ሚዲያ መሆን መቻል አለበት፡፡ ያኔ ሰዎች ራሳቸውን ሚዲያ ውስጥ ያዩታል፡፡ የእነሱ አትኩሮት፣ ሐሳብ፣ ዕይታና ተስፋ በሚዲያ ውስጥ ሲንፀባረቅ ይመለከቱታል፡፡ ከዚያም የሚዲያ ጠቀሜታ ይጨምራል፡፡ ከዕለት ተዕለት ውሏቸው ጋር ያልተያያዘ፣ ከዕለት ተዕለት ጭንቀታቸው ጋር ያልተያያዘ፣ ከዕለት ተዕለት ተስፋቸው ጋር ያልተያያዘ አጀንዳ ሲሆን ግን ለእነርሱ ትርፍ አላስፈላጊ ይሆናል፡፡ ስለዚህ በሚመለከታቸው ነገር ላይ ይጨነቃሉ፡፡ ስለሆነም አንደኛው ከሚዲያው ነው መምጣት ያለበት፡፡ ፈልጎ የሚያነበው እንዲሆን፡፡ አንድ ጉዳይ ከጋዜጣ ሲያነብ በሆነ ጉዳይ ላይ ሞቅ አድርጎ አንስቶ ነገ እንደገና ተፈልጎ ሲመጣ ወረድ ባለ አጀንዳ ሳይሆን በቋሚነት የራሱን ጉዳይ ይዞ የሚሄድ ሚዲያ መሆን መቻሉን ማረጋገጥ አለበት፡፡ ያኔ ማስታወቂያም ይሰጥሀል፣ ዜና ጥቆማም ይሰጥሃል፣ የሠራኸውንም መልሶ ያነብልሃል፡፡
በመንግሥት በኩል ደግሞ ሚዲያዎቹ በመረጃ እጦት በግምት ላይ ወደተመሠረተ የፈጠራ ታሪክ እንዳይሄዱ፣ ሰው ዛሬ ያየው ነገር ነገ ትክክል እንደማይሆን እየገባው ተደጋግሞ የተዋሸ እንዳይመስለው ከተፈለገ በቂ የመረጃ ግብዓት መኖር መቻል አለበት፡፡ ይህ ሲሆን ተዓማኒ ሚዲያ ለመፍጠር ዕድል ይኖርሃል፡፡ በሚዲያውና በሕዝቡ መካከል መተማመን እየተፈጠረ ሲመጣ መንግሥትም ለዚህ የበኩሉን አስተዋጽኦ ሲያደርግ በሚዲያው ዘርፍ መሰማራት ቀለል ያለ ሥራ ሆኖ ይመጣል፡፡ ትርፉም ይታይሃል፡፡ አደጋዎቹም ይቀንሳሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ለትርፍ ብለህ የምትገባበት ሥራ ይሆናል ማለት ነው፡፡ አሁን የትርፍ ጉዳይ አይደለም የሆነው፡፡ የሆነ ምክንያት ሲኖርህ ያችን ምክንያት ይዘህ ለመንቀሳቀስ ነው ሚዲያ ውስጥ የምትገባው፡፡ ቢዝነስ ነው የሚለው አመለካከት ገና አልጎላም፡፡ ስለዚህ ቢዝነስ ነው የሚለውን አመለካከት ለማጉላት ያሉት በአስተማማኝ ሁኔታ መዝለቅ መቻል አለባቸው፡፡ አጠቃላይ ድባቡ ከሕዝቡ ሕይወት ጋር የተያያዘ ጠቀሜታው እንዲጨምር መደረግ መቻል አለበት፡፡ ይህ ጊዜ ይፈልጋል፡፡ በ20 ዓመት ውጤታማ ሆነው መቀጠል የቻሉ ሚዲያዎች መኖር የሚያመላክተው ነገር አለ፡፡ አዳዲስ ሲገቡ የእነርሱ መጨመር የሚያሰፋው ነገር አለ፡፡ ያኔ ሚዲያ አንድ የኢንዱስትሪ መስክ መሆኑን ኅብረተሰቡ ይቀበለዋል፡፡ መንግሥትም እርሱ ላይ ተጨማሪ ድጋፍ ሲያደርግበት እየጎላ ይመጣል፡፡ የእያንዳንዳችን ድርሻ አለበት ብለን ብንወስደውና ጅምር ነው ብዙ መርገፍ ያለባቸው አቧራዎች አሉበት ብለን ብንግባባ ጥሩ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ዘርፉ ካለው ስሱነት አንፃር በሕጉ መሠረት የሚሠሩ የሚዲያ ተቋማት ይኖራሉ፡፡ ከዚህ የሚያፈነግጡም ይኖራሉ፡፡ በዚህም መሠረት የዘርፉን የሙያ ሥነ ምግባር ጠብቀው የሚጓዙትንና ከሥነ ምግባር ውጪ ያሉትን በሚያስተዳድርበት የሕግ ማዕቀፍና ቁጥጥር፣ ሥርዓት ጠብቀው የሚጓዙትንም አብሮ ያሻቸዋልና ይህንንስ መንግሥት እንዴት ያየዋል?
አቶ ሬድዋን፡- በትነን ካየነው ተገቢ ባልሆነ መንገድ የሚሄዱ ሚዲያዎች እየወጡ በሄዱ ቁጥር ተገቢነት ያላቸው ሚዲያዎች እንዲያድጉ ነው ዕድል የሚከፈተው፡፡ 50 እና 60 ጋዜጦች አሉ ብለን ብንወስድና 40ዎቹ ትርምስምስ የሚያወጣ ጦርነት የሚሰብኩ ከሆኑ፣ ከእነሱ ውስጥ ጤነኞቹን ፈልጎ ለማውጣት አንባቢ ይቸገራል፡፡ ያው ነው ሚዲያ ነው ብሎ የሚወስደው፡፡ ምክንያቱም እያንዳንዱን እያነበበ ለማጣጣም ረዥም ጊዜ ይወስድበታል፡፡ ነገር ግን እንደዚህ ዓይነት ችግር ያለባቸው እየረገፉ በእርግጥም የዘላቂ የኢንቨስትመንት የኢንዱስትሪው አንድ ተዋናይ ሆኖ ለመውጣት የሚችሉ ሚዲያዎች ቁጥራቸው ትንሽም ቢሆን፣ ሰው እነርሱን ብቻ በሚያይበት ጊዜ ግን እምነቱ ይጨምራል፡፡ ስለዚህ ሕገወጦቹን ለማረቅ የሚደረገው ሙከራ እንዲያውም መንግሥትን በተደጋጋሚ የግል ሚዲያውን እያመጣ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እያመላከተ በሚሄድበት ጊዜ፣ እነዚህ የሚሞክሩ አሉ ጥሩዎች ናቸው እነዚህ ደግሞ ወደ ጫፍ የሚሄዱ ናቸው ብለህ ለሕዝቡ ስትገልጽለት ይበልጥ የነቃ ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ የትኛውን ላንብብ የሚለውን ለመወሰን ያግዘዋል፡፡ እንዲሁ የተጻፈ ነገር ብቻ እየወሰደ ሲዋሽም መቼ እንደተዋሸ ሳይገባው እያነበበ ከሚቀጥልበት፣ በተለያዩ ጊዜያት ይህን መረጃ ለሕዝቡ በሰጠኸው ቁጥር መርጦ እንዲያነብ ዕድል ያገኛል፡፡ ንቃቱ ይፈጠራል፡፡ ንቃቱ ሲመጣ ተግባራዊ አሠራሩ አብሮ ይመጣል፡፡ ይህን መርጦ የማንበቡ ጉዳይ አብሮ ሲመጣ የማይነበቡ ይኖራሉ፡፡ የማይነበቡት ከገበያ እየወጡ ይሄዳሉ፡፡ የሚቀሩት መቀጠል የነበረባቸው ይሆናሉ፡፡ የመንግሥት እነዚህን ዕርምጃዎች መውሰድ ጤናማ ለሆኑት የሚያግዝ ይሆናል፡፡ ተደባልቀው እንዳይሄዱና ተደበላልቀው አቧራ እንዳይለብሱ በዚያ ውስጥ ሰው የግል ሚዲያ ማንበብ ምንም አዲስ ነገር አያመጣልኝም ብሎ እንዳይተወው፡፡ ጥሩዎቹም አሉበት የሚለውን እንዲመለከት ያግዘዋል እንጂ አብሮ አይመታቸውም፣ በዕርምጃ አወሳሰድ ጊዜ ተደባልቆ የሚመታ ቢሆን ኖሮ ለኃጥአን የመጣ የሚለውን ማንሳት ይቻላል፡፡ በንቃት መፍጠር ደረጃ መሄድ ከተቻለ ግን በጎዎች እንዳሉ እየታወቁ ችግር ያለባቸውን እንዲለዩ ማድረግ ለበጎዎቹ ያግዛቸው እንደሆነ እንጂ፣ እነሱ አብረው እንዲመቱ ያደርጋል የሚል እምነት የለኝም፡፡
ሪፖርተር፡- ይህ ሒደት ጊዜ የሚወስድ ነው፡፡ ይህ ዕርምጃና ጊዜ የመውሰዱ ሒደት የሚያስከፍለው ዋጋ ይኖራል፡፡ በዚህ ሒደት ተጠቃሚዎቹ የመንግሥት ሚዲያዎች ይሆናሉ፡፡ ከዚህ አንፃር እኩል የሆነ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ምን እየተሠራ ነው?
አቶ ሬድዋን፡- የሚዲያ ህልውና የሚመሠረተው ከመሠረታዋ ሕጎች ባሻገር በማስታወቂያ ነው፡፡ እስካሁን ባለው ሒደት እየቀነሰ መሄዱ አይቀርም፡፡ ብዙ ማስታወቂያ ሊያሠራ የሚችለው አንዱ መንግሥት ነው፡፡ ብዙ ግዢ አለው፣ ብዙ ሽያጭ አለው፣ ብዙ የሚያንቀሳቅሳቸው ነገሮች አሉ፣ በርካታ የሕዝብ አደረጃጀት ሥራዎች ይሠራል፡፡ በዚህም ምክንያት መንግሥት ጠርቀም ያለ ገንዘብ ለማስታወቂያ ያወጣል፡፡ አንዱ ይህንን ፍትሐዊ ማድረግ ነው፡፡ ሚዲያዎች ባላቸው አቅምና ልክ፣ ባላቸው ጥረት ልክ፣ በሚኖራቸው አስተዋጽኦ ልክ ፍትሐዊ የሆነ የማስታወቂያ አገልግሎት ሀብት እንዲያገኙ ለማድረግ ያግዛል፡፡ እንግዲህ ይህ ረዘም ያለ ጊዜ ወስዷል፡፡ ባለፈውም እንዳልነው ሒደቱ መፍጠን አለበት፡፡ አንዳንድ አገሮች አላቸው፡፡ ስለዚህ የእነዚህ አገሮች ልምድ ተወስዷል፡፡ ስለዚህ የተማከለ መሆን አለበት ነው፡፡ በአንድ መሥሪያ ቤት ኃላፊ ፍላጎት ላይ፣ በአንድ መሥሪያ ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የማስታወቂያ ዕደላ ሳይሆን የሕዝብ ሀብት ነው፡፡ በሚዲያዎች ማስታወቂያ የሚወጣ ከሆነ፣ በሆነ ሚዲያ ማስታወቂያ ሳወጣ ለምን ያህል ሰው ይደርሳል ብሎ ነው የሚወጣው የሚለው አንዱ መመዘኛ መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ ሥርጭት አንደኛው መመዘኛ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ሃምሳ ሺሕ ሥርጭት ያለውና አምስት ሺሕ ሥርጭት ያለው ሚዲያ እኩል ሊሆኑ አይገባም፡፡
ሁለተኛው ሥራውን በኃላፊነት ሕግ አክብሮ ትርፍ እያገኘና ሕገወጥ ነገሮችን እየመከተ የሚሄድ ሚዲያና አመፅ የሚቀሰቅስ ሚዲያ እኩል ማስታወቂያ ሊያገኙ አይገባም፡፡ አመፅና ሁከት የሚቀሰቅስ ሚዲያ ማስታወቂያ ሲሰጠው አመፁን ራሱ መንግሥት ስፖንሰር ያደርገዋል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የሚወጣው ማስታወቂያ በሙያው መሠረት የሚሠሩ ሚዲያዎች ላይ ነው፡፡ በልማት ውስጥ በዴሞክራሲ ውስጥ መተቸት ያለበትን ገንቢ በሆነ ሁኔታ እየተቹ የሚሄዱበት፡፡ ዞሮ ዞሮ ልማታዊ ሚዲያ ብለን የምንወስደው አንድ በጎ ነገርን እንዳይንቋሸሽ የሚያደርግ በጎ ነገር የጋራ ስለሆነ ነው፡፡ ሁለት ይህን ልማትና ዴሞክራሲ ለማስፈን በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ሳንካዎች ሲያጋጥሙ እንዳይደበቁ ማድረግ፡፡ ምክንያቱም ሳንካው ካልተነቀለ የጋራ ጉዳት ስለሆነ፡፡ በሁለቱም ሚዛን ላይ ነው መጓዝ ያለበት፡፡ ሚዲያ በጎውን ብቻ ተናግረህ እየታየ ያለን እንቅፋትን እንዳያይ ካለፍከው ዞሮ ዞሮ እንቅፋቱ አንድ ቀን ይመታሃል፡፡ የሚመታው ደግሞ ማኅበረሰቡን ነው፡፡ ስለዚህ የተሻለ ጥረት ሲኖርና ውጤት ሲመጣ ራሱን በሚዛን ማቅረብ፣ ወደዚያ ጥረት ደግሞ ሲኬድ ከማንም ይምጣ ከማኅበረሰቡ ከሆነ እሱን መተቸት፣ ከመንግሥት ከሆነ እርሱን መተቸት፣ ስለዚህ ወደ ባለቤቱ እያስጠጋ ጉዳቱንም እያመላከተ መፍትሔውንም የሚጠቁም ሚዲያ ሲሆን ይበልጥ ገንቢ ይሆናል፡፡ ይህ ሚዲያ ማደግ አለበት፡፡ በዚህ ሚዛን የሚመጣ ሚዲያ የማስታወቂያ አገልግሎቱን በፍትሐዊነት ሊያገኝ ይገባል፡፡
ሪፖርተር፡- ሚዲያዎች ገቢያቸው እየጨመረ በሄደ ቁጥር ግዙፍ እየሆኑ ይሄዳሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ኮርፖሬት የሚባሉ የሚዲያ ዓይነቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ መንግሥት ኮርፖሬት ሚዲያ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲፈጠር ፍላጎት አለው?
አቶ ሬድዋን፡- በሁለት መንገድ ብናየው፡፡ ለምሳሌ ብዙዎቹ ሚዲያዎች ተጨፍልቀው ጥቂት ሚዲያዎች ብቻ እንዲፈጠሩ አይፈልግም፡፡ ውጤታቸው ፀረ ዴሞክራሲ ስለሆነ የምናያቸው ትላልቅ ሚዲያዎች የሚባሉት በጥቂት ግለሰቦች እጅ ያሉ ናቸው፡፡ ይህ መሆኑ ለአገሪቱ ወይም ለብዙኃኑ ምን እገዛ አበረከተ ከተባለ ምንም፡፡ የሚያስተጋቡት ከእነሱ በተዋረድ ያለ ኮርፖሬት ጥቅሞችን ነው፡፡ ትላልቅ ድርጅቶችን ነው፡፡ ስለዚህ የሚዲያው መደብ ተቀይሯል ማለት ነው፡፡ ሚዲያዎች የተራው ዜጋ መደብ አይደሉም፡፡ የከፍተኛው መደብ አገልጋይ ናቸው፡፡ ስለዚህ ተነጥለዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ብዙኃኑን የሚታደግ ጥንቅር አይኖራቸውም፡፡ ብዙኃኑን ከፖለቲካ የሚያርቅ ጥንቅር ነው ያላቸው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሚዲያ እንዲፈጠር አንፈልግም፡፡ ስለዚህ የሚያስፈልገን የብዙኃን ሚዲያ ነው፡፡ ነገር ግን የብዙኃን የሆነው ሚዲያ እንዲመጣ በመመርያ አታደርገውም፡፡ ስለዚህ ብዙዎች ተውጠው ጥቂቶች እንዲፈጠሩ አይፈለግም፡፡ አሁን የጠቅላይ ባለቤትነት ችግር አለ ወይ ከተባለ ገና ምኑ ተነካና ማለት ይቻላል፡፡
ሪፖርተር፡- ኮርፖሬት ሚዲያዎች ሲኖሩ መንግሥት ሚዲያዎች እየሄዱበት ያለው መንገድ ሕገወጥ ነው የሚለውን ክርክር ወይም ወቀሳ ለመቅረፍ መፍትሔ ይሆናል የሚል አስተያየት አለ፡፡ ከዚያ አንፃር የመንግሥት ምላሽ ምንድነው?
አቶ ሬድዋን፡- አሁን ያሉት ጽሑፎች የሚያሳዩት ሚዲያዎች በጥቂቶች በተጠቀለሉ ቁጥር ፀረ ዴሞክራሲያዊ ይሆናሉ ነው፡፡ ከሕዝቦች የተነጠሉ የጥቂቶችን ጥቅም የሚያስጠብቁ ይሆናሉ ነው፡፡ ሚዲያዎች በበረከቱ ቁጥር ውድድራቸው ይበዛል፡፡ ውድድራቸው በበዛ ቁጥር የማንን አቋም በማራመድ በሕይወት እንደሚቆዩ እያወቁ ይመጣሉ፡፡ እርስ በእርሳቸው የሚያደርጉት ውድድር የብዙኃኑን ፍላጎት ወደማስተናገድ ይሄዳል፡፡ በትክክለኛ እንውሰደው ካልን የሚዲያ በጥቂቶች ቁጥጥር ሥር መውደቅ ፀረ ዴሞክራሲ ነው የሚሆነው፡፡ የሚዲያ ብዝኃነት ነው የዴሞክራሲ አላባውያን ያለው፡፡
ሪፖርተር፡- ይህንን የጠየቅንዎት መንግሥት ልማታዊ ጋዜጠኝነትን በስፋት እያበረታታ በመሆኑ በዚህ መስክ የተሰማሩ አባላትን ያበረታታል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ፕሮፌሽናል በሆነ መንገድ የራሳቸውን ሥራ የሚሠሩ አካላትን ያበረታታል ወይስ የመጫወቻ ሜዳውን ያጠባል ከሚል መነሻ ነው፡፡
አቶ ሬድዋን፡- አተያይ ነው፡፡ እኛ ለታዳጊ አገር የሚጠቅመው ሚዲያ የብዙኃኑን ጥቅም መሠረተ ያደረገ፣ ብዙኃኑን ለልማት የሚያነሳሳ፣ ብዙኃኑን ለልማት የሚያደፋፍር፣ በጥቂቶች ሳይሆን በብዙኃን ላይ የተመሠረተ መንግሥት በብዙኃን ላይ የተመሠረተ ልማት እንዲመጣ፣ ብዙኃኑ መሳተፍ የሚያስችላቸውን ዕድል የሚያገኙበትን እንቅስቃሴ የሚያዳፍር ሚዲያ ይጠቅመናል ነው የምንለው፡፡ ይህ አተያይ ነው፡፡ መንግሥት የሊብራል አተያይ ያለው ሚዲያ እንዳይኖር ይከለከላል ካልክ፣ መልሱ አይከለከልም ነው፡፡ ነገር ግን የሊበራል አተያይ ያለው ሚዲያ እንደማይጠቅም እናውቃለን፡፡ ግን ደግሞ ሐሳብ እንዳይንሸራሸር አንከለክልም፡፡ ከከለከልን አንድ ቅኝት ያለው ሚዲያ ብቻ እንዲኖር እያደረግን ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ አይደለም፡፡ ግን የሥልጠና ማዕከሎቻችን ልሂቃኖቻችን በምዕራቡ ዓለም የተፈጠረው ዓይነት አተያይን ብትን አድርገው አይተውት፣ ከነፋይዳውና ከነሕፀፁ አይተው የሚባለውን በጥሬው አይተውት ሳይሆን እነሱ ጋ የተፈጠረውን ማኅበራዊ ቀውስ፣ እነሱ ጋ ማን አድራጊ ፈጣሪ እንደሆነ፣ ማን ከጨዋታ ውጪ እንደሆነ፣ ይህ አመለካከት እንዴት ሊገነባ እንደቻለ መረዳት ይኖርባቸዋል፡፡ እኛ ደግሞ በተለየ ዓለም የምንኖር ነን፡፡ የራሳችን ፍላጎት ያለን ነን፡፡ ሌላው የራሱን ፍላጎት ሊጭንብን የሚፈልግብን ነን፡፡ የእኛ ፍላጎት ይጠበቅ፡፡ የእኛ ማኅበረሰብ እንዴት ተጠቃሚ ይሁን የምንል ነን፡፡ ሚዲያው በጥቂቶች የሚሸከረከር ይሁን ወይስ በብዙኃን ተሳትፎ ላይ ይመሥረት የሚለው ጉዳይ ሊጤን ይገባዋል፡፡ በእርግጥ ይህንን አስረግጦ ለማሳወቅ ብዙ የአስተምህሮ ሥራ ይጠብቀናል፡፡ ነገር ግን ሌላኛውን አስተሳሰብም ቢሆን አስገድደህ አታስቆመውም፡፡ በአዋጅ አታስቆመውም፡፡ ሰዎች እንዲገነዘቡ፣ ፈትሸው እንዲያውቁ የማደፋፈር ሥራ ነው ሊሠራ የሚችለው፡፡ አሁን ግን የሰላ የሐሳብ ፍጭት የለም፡፡ የትኛውን አተያይ እንቀበል የሚለውን ጉዳይ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ የሐሳብ ፍጭት አካሂደን ልናጎላውና ሕዝቡም ተረድቶ ወደ አንዱ እንዲያዘነብል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ዞሮ ዞሮ የጋራ ጥቅም እስከሆነ ድረስ ወደ አንድ ጫፍ እንደርሳለን፡፡ የማይመቸው ካለም ሌለኛውን ጎራ ሊቀላቀል ይችላል፡፡ ይህንን ደግሞ አስገድደህ የምታመጣው አይደለም፡፡ ማነፃፀሪያ ይሆንሀል መቀጠሉ፡፡
ሪፖርተር፡- የሐሳብ ፍጭት ለማስተናገድ የሚያስችል ምኅዳር አለ ወይ? የተለየ ሐሳብ የሚያነሱ መጨረሻቸው ማረሚያ ቤት ነው፡፡ በመጻፋቸው ብቻ ለእስር የተዳረጉ አሉ፡፡ መንግሥት በእርግጥ ለሐሳብ ፍጭት ቦታ ይሰጣል ወይ?
አቶ ሬድዋን፡- ለምን ሪፖርተር ራሱን እንደ አብነት አወይስድም? ሪፖርተር በርዕሰ አንቀጹ ጭምር መንግሥት ሊቀበል የማይችላቸውን ሐሳቦች ያራምዳል፡፡ ይህ የሐሳብ ፍጭት ነው፡፡ ‹‹እዚህ ጋ ትኩረት ሊሰጥ ይገባ ነበር፡፡ እዚህ ትክክል አይደለም…›› ይላል ሪፖርተር፡፡ ችግር መናገር የሐሳብ ልዩነት ነው ተብሎ ሐሳቡ ተቀባይነት የለውም ተብሎ ሪፖርተር በጥላቻ ሊፈረጅ ይገባ ነበር ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ሪፖርተር አንዱ ተዓማኒ ሚዲያ ነው፡፡ የሚያነሳቸው ጉዳዮች አንዳንዴ ሊጋነኑ ይችላሉ፡፡ አንዳንዴ መረጃ ሊያጥራቸው ይችላል፡፡ ግን የተቋሙ ሐሳብ ናቸው፡፡ ሐሳቦቹ ሥርዓት በማፍረስ የተቃኙ ግን አይደሉም፡፡ ሥርዓቱን ለማቃናት በመሰለው መንገድ የሚያቀርባቸው ሐሳቦች ናቸው፡፡ ሥርዓቱን በማደፍረስ ሒሳብ ሳይሆን ሥርዓቱን እንዲስተካከል በሚያስችል መልኩ የተቃኙ ናቸው፡፡ ጎደሉ የሚባሉ ጉዳዮችን በመጠቆም የተመሠረቱ ሐሳቦች ናቸው፡፡ ነገር ግን ሪፖርተር የሚጽፋቸው ሐሳቦች ከመንግሥት አቋም ጋር የተጣጣሙ ናቸው ማለት አይደለም፡፡ አንዳንዴ ከመንግሥት አቋም ጋር ይጣረሳሉ፡፡ የጽሑፎቹ መነሻ ሥርዓት ማናጋት አይደለም፡፡ አንድን ማኅበረሰብን በሌላ ማኅበረሰብ ላይ ማነሳሳት አይደለም፡፡ ሕገ መንግሥትን ማዛባት አይደለም፡፡ ሕዝብ እንዲተራመስ የሚያደርግ አይደለም፡፡ ግን ደግሞ ሪፖርተር የተለየ አቋም አለው፡፡ ሌሎቹ ሚዲያዎችና ሪፖርተር የሚያራምዷቸው ሐሳቦች ምን ላይ ነው የሚቆሙት የሚለው ጉዳይ ሊታይ ይገባል፡፡ ከሪፖርተር ወጣ ብለው የዘለቁ ስድስት ያህል ሚዲያዎችም እንዲሁ ናቸው፡፡ ከዚያ ውጪ ያሉ ሚዲያዎች በየሳምንቱ ያትሙ በየወሩ ያትሙ ይዘታቸውን ስትመለከት ምን ያህሉ መሬት ላይ ያለ ዕውነታን የሚያንፀባርቁ ናቸው? ምን ያህሉ ሕጋዊ መንገድን የተከተሉ ናቸው? የሚለውን ጉዳይ ማየት ይችላል፡፡ በዚህ ምክንያት ባጠፉ ቁጥር የሐሳብ ፍጥጫን አንታገስም ብለን እናስገባቸው ብንል፣ ምን ያህሉ ከሁለትና ከሦስት ዕትም በላይ ይዘልቁ ነበር? አሁን በምሳሌ እናስደግፈው ካልን፣ ‹የኢትዮጵያ መንግሥት ኢንተርኔት ይሰልላል፡፡ የሰዎችን ሜሴጅ ያያል፣ ብሎገሮች ያስራል፣ ወዘተ› ይባላል፡፡ ነገር ግን ሰሞኑን የፈረንሣይ መንግሥት ምንድነው ያደረገው? በኢንተርኔት ብቻ ሳይሆን በመኖሪያ ቤት ጭምር ካሜራ ማስቀመጥ የሚያስችል ሕግ አፅድቋል፡፡ እኛ ግን ሥጋት ውስጥ ስንገባና እሱን የሚከላከል ሥራ ስንሠራ፣ እከሌ የሚባል ሰው ተነካ በማለት የሚጨፍር አካል አለ፡፡ እሱ ጋ ትንሽ ክብሪት ሲጫር ነገር ዓለሙን በሙሉ ጠቅልሎ በአይቻልም መንፈስ የሚያስገባው ከሆነ፣ ጥያቄ የሚያስነሳው የእኛ ሥጋትም ሊሰመርበት ይገባል ወይስ አይገባም የሚለው ነው፡፡
እንግሊዝ ይህንኑ ሕግ በቅርቡ ያወጣል ተብሎ ይጠበቃል፣ ካናዳም ሕጉን አውጥቷል፡፡ ሌላው ዓለም በዚህ በኩል ሥጋት አድሮበታል፡፡ እኛ ስንሠጋና ራሳችንን ለመከላከል ስንሞክር ለምን ኃጢያት ይሆናል? ይህ ጥያቄ ሊታይ ይገባዋል፡፡ እነዚህ የሚከስሱት ሰዎች መንግሥት ሲከሳቸው ምን ብሎ ከሰሳቸው? የጻፉት አንድ ሺሕ ቆሻሻ ነገር ነው፡፡ እሱ ለፍርድ ቤት አይቀርብም፡፡ ከጽሑፍ ጀርባ ያለው ጉዳይ ነው ቁምነገሩ፡፡ ራሳቸው በጀት መድበው የሚያሰማሩት አካላት ናቸው ጩኸት የሚያሰሙት፡፡ ለእኛ ደግሞ ዋናው ቁምነገር የተረጋጋ አገር እንዲኖረን ማድረግ ነው፡፡ ይህን ሥርዓት ካልያስያዘ አንድ መንግሥት መንግሥት ሊባል አይችልም፡፡ የተጻፈ ነገር ብቻ ይዘን እንክሰስ ካልን ብዙዎቹ ሁለተኛ ዕትም አይደግሙም ነበር፡፡ ፀረ ሽብር ሕጉንና እነሱ የሚጽፉትን ተመልከቱ፡፡ ሕገ መንግሥቱንና እነሱ የሚጽፉትን ተመልከቱ፡፡ የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉንና እነሱ የሚጽፉትን ተመልከቱ፡፡ የትኛውም ሰው አንዴ ከጻፈ በኋላ ሁለተኛ አይደግምም ነበር፡፡ የመንግሥት ትዕግሥት ባይኖር ኖሮ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ነው ካለው አካል ጋር ከሠራ፣ ነፃ ፍርድ ቤት ወንጀለኛ ነው ያለውን ሰው ጀግና ነው ካለ፣ ሁኔታው ከባድ መሆኑን ያሳያል፡፡ በሌላው ዓለም ይህ የሚያስቀስፍ ከሆነ እኛ ጋ የሚያፀድቅ እንዲሆን ለምን ይጠበቃል? አንድ ሰው የሆነ አካል አይዞህ ስላለው ብቻ፣ ስፖንሰር ስለሆነው ብቻ፣ ስኮላርሺፕ ቃል ስለገባለት ብቻ፣ እየዘለለ የአገሩን ወጪት መስበር አለበት? የአገሩን ሕግስ መጣስ አለበት? ሁላችንም ይህንን አስተዋጽኦ አድርገን መልክ ካላስያዝን፣ ለእኛ የሚሆን አገር ይተርፈናል ወይ የሚለውን ጉዳይ ማየት ያስፈልጋል፡፡
ሪፖርተር፡- ብዙ ጊዜ ለዚህ የሚቀርበው መከራከሪያ ሌሎች አገሮች የዴሞክራሲ ተቋሞቻቸው ጠንካራ በመሆናቸው የሚወጡትን ሕግጋት በትክክል ተግባራዊ ያደርጋሉ፡፡ በአንፃሩ ኢትዮጵያ ውስጥ የዴሞክራሲ ተቋማት ደካማ ከመሆናቸው በተጨማሪ፣ የተቋቋሙባቸው ሕግጋት ላይም መግባባት ላይ ባለመደረሱ መንግሥት በሚወስደው ዕርምጃ አለመተማመን አለ፡፡
አቶ ሬድዋን፡- የተዓማኒነት ጉዳይ አይደለም፡፡ ምዕራባውያኑ እነሱ የሚሠሩትን ሥራ ስንሠራ ስህተት ነው ይላሉ፡፡ ፀረ ሽብር ሕግ ያወጣሉ፡፡ እኛም እናወጣለን፡፡ የእናንተ ችግር አለበት ይላሉ፡፡ እኛ ደግሞ ኧረ ሕጉ የእናንተ ሕግ ኮፒ ነው እንላለን፡፡ እነሱ ደግሞ ኮፒውማ ልክ ነው፡፡ ስትሠሩ ግን ተሳስታችሁ ይሉናል፡፡ ስንሠራማ ልንሳሳት እንችላለን፡፡ እነሱ ይሳሳቱ የለ እንዴ? እነሱ ጋ አንድ የተፈረደበት ሰው በስህተት ነው እየተባለ ከስንት ዓመት በኋላ ነፃ ነው ይባል የለ እንዴ? ስህተት ከሆነ እዚያም ስህተት ይሠራል፡፡ ስህተት ከሆነ እዚህም ስህተት ሊሠራ ይችላል፡፡ ሲስተምና ስህተት መለያየት ይኖርበታል፡፡ እኛ ጋ ተቋማቱ አዲስ ናቸው፡፡ ከዚህ ሁሉ ዓመት በኋላም እነሱ ሕግ እያወጡ ነው፡፡ እኛ ሁለት አሥርት ላይ ሆነን ሕግ አውጥተን ገና ምኑን ጨረስነው? የማሻሻል ብቻ ሳይሆን ገና ፍሬ ሕጎች እናወጣለን፡፡ እነሱም አውጥተው አልጨረሱም፡፡ እነሱ የ20 ዓመታት የዴሞክራሲ ዕድሜ ላይ በነበሩበት ጊዜ ገና ተገዳድለው አልጨረሱም ነበር፡፡ እኛ እየተቋቋምን እየሄድን ነው፡፡ ስህተት ቢያጋጥመን ያን ያህል የሚያስደንቅ አይደለም፡፡ ስህተት የማይፈጠርበት መንግሥት የለም፡፡ ጥያቄው መንግሥት ስህተት ይሸፍናል ወይ ነው፡፡ የእኛ መንግሥት ስህተትን የሚናዘዝ ነው፡፡ እንኳን ሕዝብ የደረሰበትን ራሱ ገምግሞ የደረሰበትን ይቅርና ሜዳ ላይ የሚዘረግፍ መንግሥት ነው፡፡