Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገትከሕዝብ ፍላጎት የተነጠለ አፈንጋጭነት ማንንም የትም አያደርስም

ከሕዝብ ፍላጎት የተነጠለ አፈንጋጭነት ማንንም የትም አያደርስም

ቀን:

በያሲን ባህሩ

ሽብርተኝነትን አስመልክቶ ውይይት ሊያጭር የሚችል ጽሑፍ ያቀረብኩት ባለፈው ሳምንት ነበር፡፡ መነሻዬ አይኤስ በወገኖቻችን ላይ በፈጸመው ግፍና ጭካኔ የተሞላበት ግድያ ነበር፡፡ በእርግጥም እነዚያ ሰማዕታት በሃይማታኖቸውና በማንነታቸው ተለይተው ለመቀላትና ለመረሸን የተዳረጉት በዓለም አቀፍ ሽብርተኞችና በፀረ ሰብዓዊነት ኃይሎች ቢሆንም፣ አደጋው ለኢትዮጵያውያን የቀይ መብራት ምልክት ማሳያ ነው፡፡

የዜጎቻችን ዕልቂት የፖለቲካ ሽሚያውንና አለመግባባታችንን አይተንበታል፡፡ በመንግሥት በኩል መዘናጋትና ፈጥኖ ያለመወሰን ማንገራገርም ተንፀባርቆበታል፡፡ ሕዝቡም ከዳር እስከ ዳር የተቆጣበትና ያዘነበት እውነታም ሳይደበቅ ጎልቶ ወጥቷል፡፡ አገራችን ከውጭ ጠላትና ከአሸባሪ ኃይል በንቃት እየተጠበቀች ቢሆንም፣ ‹‹እንደ ጨው ዘር›› በየአገሩ ለአደጋ ተጋልጠው የተበተኑ ወገኖች ግን በጥቃት ሠይፍ ላይ የተመቀጡ ናቸው፡፡ እንግዲህ መፍትሔው ላይ ማተኮርና ችግሮችን መለየት መቅደም አለበትና ባለፈው ሳምንት በጀመርኩት መንገድ ልቀጥል፡፡

- Advertisement -

የሽብርተኞች የመርዝ ስንኮፍ የትም አገር አለ

ሽብርተኝነት ዓለም አቀፍ አደጋ ቢሆንም ጉዳያችን የአገራችን ሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ለዘመናት ተጭኖ የኖረው የብሔርና የማንነት ጭቆና ተወግዶ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ከሞላ ጎደል በእኩልነትና በነፃነት እየኖሩ ነው፡፡ ሁሉም ሃይማኖቶችም ቢሆኑ ሕገ መንግሥታዊ ነፃነታቸው ተጠብቆላቸው እየተራመዱ መሆናቸውን ማንም ሊክድ አይችልም፡፡ የመንግሥትና የእምነት ተቋማት መለያየት ጉዳይም ላይመለስ ተቀብሯል ለማለት ይቻላል፡፡

በዚህ መንፈስ ተነሳስተው እምነታቸውን የሚያራምዱትና ሃይማኖታዊ አስተምህሮታቸውን የሚያከናውኑት ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ከ38 ሚሊዮን በላይ እንደሚደርሱ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ነገር ግን የዓለም ሰላማዊ ሃይማኖቱ እስልምና የተደቀነበት የአስተሳሰብ መዳቀል ኢትዮጵያ ውስጥ የለም ለማለት ያስቸግራል፡፡ መረጃዎች እንደሚያስረዱት የአገራችን ሙስሊሞች በሃይማኖታዊ መሠረታቸው ሱኒዎች ናቸው፡፡ ወሐቢያና ሰለፊያ የሚባሉት አክራሪና ጽንፈኛ ባህሪ ያላቸውም ያሉት ሱኒ ውስጥ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ሰለፊ ያልሆነ ሙስሊም የሚያስጠጋውን አይኤስን ጨምሮ፣ በሰለፊያ ውስጥ ተደብቀው ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ የእዚህ አክራሪ አስተምህሮ አድናቂዎችና ተቀባዮች በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች አገሮች የሉም አልነበሩም ማለት አይቻልም፡፡

የአገራችን ሙስሊም እምነት ተከታዮች ከነባሩ የነቢዩ መሐመድ (ሰዓወ) ተከታዮች አንስቶ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ መሠረቱን ጠብቀው የኖሩ ናቸው፡፡ በአገራችን ካሉ የሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር በመቻቻል የየራሳቸውን እምነት በአንድ የጋራ አገር ውስጥ፣ በሰላምና በመረዳዳት የማስቀጠላቸው ሚስጥርም ይኼው ነው፡፡ መላው የአገሪቱ ዜጎች የጋራ ጠላት ሲመጣባቸው በጽናት በመታገል እናት አገራቸውን ሳያስደፍሩ በርካታ የችግርና የደስታ ዘመናት ማሳለፋቸውም ለዚህ ነው፡፡

በየትኛውም ዓለም የሚገኙ ወጣት የእስልምና ተከታዮችና አዲሱን ትውልድ እየመረዘው ያለው የአክራሪነትና የጽንፈኝነት አስተሳሰብ ግን ገፍቶ ‹‹እስላማዊ መንግሥት›› ዓለምን ይመራል የሚል ቅዥት ላይ የሚጥል ነው፡፡ እስልምና መንፈሳዊና ሰማያዊ እሴት ከመሆኑም ያለፈና የምድር አገዛዝ ላይ እንዲያተኩር የሚገፋም ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ለዚህ አስተሳሰብ መፋፋት ደግሞ ራቢጣ አል ዓለም ኢስላሚያ (Muslim World League) በሚል ስያሜ እ.ኤ.አ. በ1962 በመካ ሳዑዲ ዓረቢያ የተመሠረተው ተቋም ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡ ይህ የዓለም አቀፍ እስላማዊ ድርጅት ዋነኛ ዓላማው ሃይማኖትን በማስፋፋትና በማስረፅ ሙስሊም በሆኑና ባልሆኑ ሕዝቦች ላይ መጫን ነው፡፡ የእምነቱን አተገባበሮች በወሐቢያ አስተምህሮ መሠረት ማድረግንም ይሻል፡፡ በዚሁ ላይ የሚነሱ ተቃውሞዎችንም በፍጥነትና በስፋት ለመታገል ይታትራል፡፡ ለዚህም ከፍተኛ በጀትና ግብዓት መድቦ ይንቀሳቀሳል፡፡

በአገራችንም ከነባሩ እስልምናም ሆነ ሐበሻዊ አስተምህሮ ባፈነገጠ መንገድ ከሌሎች እምነቶችና አብሮነት በሚቃረን አኳኋን ለመንቀሳቀስ ተሞክሯል፡፡ ከሁሉም በላይ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ወደ ጎን ለማለት በመሻት ኃይል የተቀላቀለበት የአመፅና የሁከት ሙከራም ሰዎችን (የሃይማኖት መሪዎችን) እስከ መግደል ታይቷል፡፡ በአወሊያና በአካባቢው ተቀስቅሶ በስልጤ፣ በጅማ፣ በአርሲ፣ በምሥራቅ ሐረርጌ፣ በከሚሴና በደቡብ ወሎ ዞኖች ጐልቶ የታየው አክራሪያዊ መንፈስ ሕዝብና መንግሥት በእንጭጩ ባይነቁበት፣ ከላይ በተጠቀሰው ዓለም አቀፍ ፕሮጀክቶች አገሪቷ አለመታቀፏን ማረጋገጥ ያስቸግራል፡፡

አንዳንድ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ሳይቀሩ የወሐቢያ ሰለፊያ አስተምህሮን ደፍረው አክራሪና ጽንፈኛ ነው ብሎ ለመፈረጅ አፋቸው ተሸብሽቦ ነበር፡፡ ዛሬም ድረስ አክራሪነት ሲባሉ ወደ ሌላ ሃይማኖትም በመውሰድ ነባራዊ መሠረት የሌለውን ማደናገሪያ በማምጣት፣ ለሽብርም ሆነ ለጥፋትና መገዳደል መሠረት የሚሆነው ሃይማኖታዊ አክራሪነት በሌሎች ሃይማኖቶች የለም ባይባልም፣ ዓይነቱንና ሰንኮፉን እየለዩ መታገል ግን ለነገ የሚባል ሥራ ሊሆን አይገባም፡፡ ለምሳሌ ከላይ የተጠቀሰው ጽንፈኛ እስላማዊ አስተምህሮ ከዜጎች መብት (ከሴቶችና ከወጣቶች ነፃነት) አንፃር የሚጥለውን ገደብ እንመልከተው፡፡ ከዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የመቻቻል ባህልም ሆነ ከዘመናዊነት ጋር የሚያጣላውን እውነታም እንበርብር፡፡

መረጃዎች እንደሚያሳዩት የወሐቢያ/ሰለፊያ አስተምህሮ ሴት ልጅ ካለባሏ ፈቃድ መፆም አትችልም ይላል (ባሏ ካልፈለጋት ይቻላል)፡፡ የሴት ልጅን ከእጮኛዋ ጋር በስልክ መነጋገር አይፈቅድም፡፡ ተሽከርካሪ መንዳት፣ ባሏን ወሲብ መከልከል (ካላመማት በስተቀር) አይቻልም፡፡ በአንፃሩ ባል ወሲብ ሊከለክል ይችላል፡፡ ማስቲካ ማኘክ፣ መጨፈር፣ ፀጉር ማሳጠር፣ ወደ ቀብር ሥፍራ መሄድ፣ በፊት ለፊት እየታዩ የአደባባይ ንግግር ማድረግ ለሴቶች የተከለከሉ ናቸው፡፡ እንግዲህ ከሴቶች መብት አንፃር ያለውን ፈተና ማስተዋል ይቻላል፡፡

ለማንኛውም የእምነቱ ተከታይ ሙዚቃ፣ ዘፈንም ሆነ ዳንስ ክልል ነው፡፡ ሃይማኖታዊ ፕሮግራሞች ካልሆኑ በስተቀር ቴሌቪዥን መመልከት እንኳን ነውር ነው፡፡ አድናቆትን በጭብጨባ መግለጽ፣ የአበባና የፖስት ካርድ ስጦታ ማበርከት፣ የሰውም ሆነ የእንስሳት ሥዕል መሣል፣ በድራማም ሆነ በፊልም ታዋቂ ተዋናይ መሆን (የውሸት ነውና) የአስተምህሮው ፀያፍ ድርጊቶች ናቸው፡፡ ልብ ወለድ መጻፍ፣ ሥዕል ያለበት ልብስ መልበስ፣ ሪዝን ማሳጠር፣ በግራ እጅ መጻፍም ሆነ መብላት፣ የነብዩ መሐመድንም ቢሆን ልደትን ማክበር እንደ ነውር ይቆጠራል፡፡ …

ለእነዚህና ለሌሎች በርካታ ጉዳዮች ሃይማኖታዊ አመንክዮ ለማስቀመጥ ቢሞክሩም፣ ከሰብዓዊና ከዴሞክራሲያዊ መብት አኳያ ወይም ከሌሎች ጋር ተቻችሎና ተባብሮ ለመኖር ካላቸው እንቅፋት አኳያ አልፈተሿቸውም፡፡ እንደ ታዛቢ በሃይማኖታዊ ጉዳይ ውስጥ ጠለቅ በማለት ለመግባት እየተሞከረ ያለው፣ በአገራችን የምንገኝ ሁላችንም ቅን አሳቢዎች በአገራችን የጋራ እሴቶችና በመንግሥት ሴኩላር (ዓለማዊ) ባህሪ ላይ የተጋረጡ መሰናክሎችን ለይተን ለመታገል እንድንችል ነው፡፡ አክራሪነትና ጽንፈኝነት እንዳይኖር መንቃትና በጋራ መሥራት የሚያስፈልገውም ሽብርተኝነት የሚወለድበት ሰንኮፍ በውስጡ ስላለ ነው፡፡

‹‹እኔ ከሞትኩ . . .›› ፖለቲካ አያሻንም!

በሰሞኑ የአይኤስ ጥቃት ወቅት የተማርነው ሌላው ጉዳይ የአገራችን ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች በብሔራዊ ጥቅምና የፀረ ሽብር ትግልን በመሰሉ የጋራ ግንባሮች ላይ እኩል የሚተኩሱ አለመሆናቸውን ነው፡፡ በእርግጥ ካለፉት ጊዜያት በተሻለ መንገድ ብዙዎቹ የአገራችን የፖለቲካ ኃይሎች ድርጊቱን በማውገዝ፣ ለዜጎች ደኅንነት መንግሥት ከሚወስደው ዕርምጃ ጎን ለመሠለፍ ቁርጠኛ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

አንዳንዶች ደግሞ ጉዳዩን የፖለቲካ ትርፍ መሸመቻ ማድረጋቸው እጅግ መወገዝ ያለበት ድርጊት ነው፡፡ በመሠረቱ ኢሕአዴግም ቢሆን መተቸት ያለበት ዴሞክራሲንና መልካም አስተዳደርን በተገቢው መጠን አለማስፈኑ ካልሆነ በስተቀር፣ ልማትን በማቀላጠፍ የሥራ ዕድል አልፈጠረም ሊባል አይችልም፡፡ አልሸባብን የታገለበት መንገድም ሆነ ፀረ ሽብር ሕግ ቀርጾ አክራሪነትና ጽንፈኝነትን የመከተበት (በጅምላ መሸማቀቅ ከፈጠረ መፈተሽ አለበት) ሥልትም ቢሆን ሊያስተቸው ይችላል ብዬ አላምንም፡፡

ከዚያም አልፎ በሺዎች ኪሎ ሜትር በሚቆጠር ርቀት ላይ በዜጎቻችን ላይ በሚደርስ የትኛውም ዓይነት አደጋ ረገድ መንግሥትን ማብጠልጠሉ ፋይዳው አይታየኝም፡፡ ‹‹መንግሥት በንፋስ ፍጥነት ሄዶ ሽብርተኞችን ካልፈረጀ፣ በውቅያኖስ ውስጥ የሰጠሙ ዜጎችን ሕይወት ካልታደገ…›› ብሎ ለንግግር ብቻ መዛለፍ አንድም የመንግሥትና የአገርን አቅም አለመረዳት፣ በሌላ በኩል የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት በድንክ አዕምሮ መደነጋገር ከመሆን አይዘልም፡፡ በርካታ ችግሮች እንዳሉ ሆነው ማለቴ ነው፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ከሰሞኑ አደጋ አኳያ የሚወቀስባቸው ግልጽ እውነታዎች አሉ፡፡ አንደኛው በማንኛውም መንገድ ቢሆን በአገርና ሕዝብ ላይ አንዳች ስሜት ሊፈጥር የሚችል ደስታና ሐዘን በፍጥነት ተገንዝቦ ምላሽ መስጠት ላይ ያለው  አዝጋሚነቱን አለማስወገዱ ነው፡፡ በማኅበራዊ ድረ ገጽ በስፋት እንደተተቸው እንዲህ ዓይነት ጉዳት የሕዝብን ስሜት ረብሾ ወዳጅን ጠላት፣ ማኅበራዊ መሠረትን ተቀናቃኝ ለማድረግ አንድ ጀንበር ይበቃዋል፡፡ ስለዚህ ብሔራዊ ስሜት ያለው፣ ቁጭት የተላበሰና የሚያረጋጋ መግለጫ አለመስጠት ያስከተለውን መዘዝ የሚያጠና ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ካቢኔም ሆነ የፕሮፓጋንዳ ሰው ሊኖር አይገባም? በማለት እጠይቃለሁ፡፡

ሁለተኛው መንግሥት መፈተሽ ያለበት ዜጎች በሕጋዊም ይባል በሕገወጥ መንገድ የሚሰደዱበትና ሕይወታቸውን ለአደጋ የሚያጋልጡበት ምክንያት ምንድነው? ብሎ መሥራቱ ላይ ነው፡፡ ‹‹የተሻለ የሥራ ዕድል ፍለጋና ገቢን ለማሳደግ ዜጎች ይሰደዳሉ›› መባሉን ባልቃወምም፣ የዴሞክራሲ መብት መከበርና የፖለቲካ ምኅዳሩ መጥበብ የሚያስገድዳቸው የሉንም!? ብሎ አጥብቆ መጠየቅ ይገባል፡፡ ኢፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል፣ የመልካም አስተዳደር እጦትና በክልሎች እየጠፋ የመጣው እንደፈለጉ ተንቀሳቅሶ የመሥራት መብት የሚገፋቸውስ? መባል አለበት፡፡ ይህን የመሰለ አስከፊ የመልካም አስተዳደር ጉድለትን ለማየት አለመፈለግ ችግር አለው፡፡

ከሰሞኑ በተለያዩ መገናኛ በዙኃን የሰማናቸው ስደተኞች ሊቢያና የመን እሳት ላይ ሆነው እንኳን ለምን ‹‹መመለስ አንፈልግም!›› አሉ? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ እዚህ በሥራ አጥነት ተተብትበው ወይም በጠባቂነትና በሥራ ማማረጥ ልክፍት ተሸብበው፣ ወጣቶችም ተሥለውና ተበድረው ከአገር ለመውጣት እየቋመጡ መሆናቸው ሊታይ ይገባል፡፡ ይህን አደጋ ለማስቀረትም ከለብለብ የወጣ ጠንካራ ብሔራዊ ዘመቻና አብዮት ሊቀሰቀስም ይገባዋል፡፡ ከእነዚህ በዓይን የሚታዩ እውነታዎች ውጪ መንግሥትና ገዥው ፓርቲን ለመተቸት ሲባል ከአሸባሪው አይኤስ ያልተለየ ተግባር መፈጸም በፍፁም ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም፡፡ ‹‹ሰሞኑን ግንቦት 7 እና ሰማያዊ ፓርቲ ደጋፊዎቻቸውን በማስተባበር ሽብርተኝነትን ለመቃወም የወጣውን ሕዝብ ወደ ሁከት ለመውሰድ ሞክረዋል፤›› የሚለው የመንግሥት ክስ መታየት ያለበት ከዚህ አንፃር ነው፡፡ ለመሆኑ በዜጎቻችን ዕልቂት አንድ መሆን ካልተቻለ መቼ ሊኮን ነው? ለፖለቲካ ትርፍ ሲባል የሃይማኖት አክራሪነትና ጽንፈኝነትን እየደገፉ መንጎዱስ መጨረሻው ምን ሊሆን ይችላል? ብለን መመርመር አለብን፡፡

መንግሥትም ሆነ ኢሕአዴግ መተቸትና መወቀስ ያለባቸው በጉድለታቸው እንጂ፣ ‹‹ግርግር ለሌባ ይመቻል›› እንዲሉ በትርምስ ሊሆን አይገባም፡፡ አገራችን ደሃና ታዳጊ መሆኗን ዘንግቶ በተለኮሰ አነስተኛ ጉዳይ ሁሉ ቤንዚን እያርከፈከፉ እሳት ማቀጣጠልም ቢሆን ከምንም በላይ አገር የሚያጠፋ ድርጊት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን እስላም፣ ክርስቲያን ሳይሉ በዘርና በብሔር ሳይከፋፈሉ በአንድነት የሚቆሙለትን ብሔራዊ ጥቅምና ክብር የማይጠብቅ ፖለቲከኛ መንገዱ ገደል ነው፡፡ ከሕዝብ ፍላጎት የተነጠለ የአፈንጋጭነት አካሄድም በሕዝብ ለመተፋት ቀናት አይፈጅበትም፡፡ ማንንም የትም አያደርስም፡፡ ስለዚህ የትኛውም ወገን ቢሆን ይህን እውነታ በማጤን መጓዝ ግድ ይለዋል፡፡

ለማጠቃለል ሲሞከር

ዓለማችን የሽብር ቋያ እየለበለባት እንደ መሆኑ መጠን የአገራችን ጉዳትም ከዚያው ተነጥሎ ሊታይ የሚችል አይደለም፡፡ በሃይማኖታዊ አክራሪነትና በጽንፈኝነት ታጅቦ የሚቀጣጠል ግብረ ሽብር ደግሞ መቆሚያ የሌለው እንዲሆን፣ በሁሉም አገሮች እንዲቀጣጠል የሚያደርገው አመለካከቱን የሚሸከሙ ኃይሎች የትም ሆነ መቼ ስለሚከሰቱ ነው፡፡

በአገራችን ያሉ የሃይማኖት ተቋማት፣ የፖለቲካ ኃይሎችና ሕዝቡ ጭምር በአንድ ሊቆሙ የሚገባቸው ይህን የተለያዩ የዓለም አገሮችን እየበታተነ ያለውን አክራሪነትና ጽንፈኝነት በመታገል ረገድ ሊሆን ይገባል፡፡ መንግሥትም አገርና ሕዝብ የመጠበቅ ኃላፊነቱ ላይ እንዳይዘናጋ የመትጋትና የመተባበር ግዴታ አለባቸው፡፡ ከእንዲህ ያለ በአገር ላይ ከተቃጣ ፍላፃ ፊት ለፊት ቆሞ ራሱን ሰለባ ለማድረግ የሚሻ እንደሌለ ሁሉ፣ በእጅ አዙርም ሆነ በጊዜያዊ ጥቅም ተታሎ የሚነጉድ ይኖራል ተብሎም አይታሰብም፡፡ ለሁሉም በሁሉም መስክ መጠናከርና መደማመጥ አለብን፡፡ ይህን ካላደረግን ሽብርተኝነቱም ሆነ ሌላው ሊበረታብን መቻሉ አይቀርም፡፡ አሁንም ደግመንና ደጋግመን ማሰብ ያለብን ማንም ሆነ ማን ከሕዝብ ፍላጎት የተነጠለ አፈንጋጭነት የትም እንደማያደርሰው ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...