Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀንና ጋዜጠኝነት በኢትዮጵያ

የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀንና ጋዜጠኝነት በኢትዮጵያ

ቀን:

ባለፈው ሳምንት የፕሬስ ነፃነት ቀን ተከብሯል፡፡ በሪፖርተር ጋዜጣም በቀጥታም እንኳን ባይሆን በተዘዋዋሪ መንገድ ዕለቱን የሚያስታውስ ጽሑፍ ‹‹ዴሞክራሲና ዴሞክራሲያዊነት›› በሚል ርዕስ በአጋጣሚ አስተያየት ተጽፎ ለንባብ በቅቷል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ደግሞ በጥቅሉም ቢሆን ጋዜጠኝነት ምን እንደሆነና የኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ታሪክ እስከ 1983 ዓ.ም. ያለውን ለመዳሰስ ይሞከራል፡፡ ከ1983 ዓ.ም. እስካሁን ያለውን በእጅጉ አጠር አድርጎ ካቀረበ በኋላ ቀሪውን ለመግለጽ ጸሐፊው ቀነ ቀጠሮ ይጠይቃል፡፡ ጋዜጠኝነት ምንድነው? ጋዜጠኛ ሕይወት የጣመቻቸውንና የመረረቻቸውን፣ የተነሱትንና የወደቁትን፣ የተሳካላቸውንና በውጥን የቀሩትን፣ የመጠቁትንና እጅግ ኋላ የቀሩትን፣ ያሸነፉትንና የተሸነፉትን ራሱን እንዳለ ገልብጦ እንኳን ባይሆን እንደ መስታወት፣ ወይም ሌላ አንፀባራቂ አካል ምሥሉን በተለያዩ ዘዴዎች ቀርቦ ለስሜት ሕዋሶቻችን እንዲታዩ የሚያደርግ ነው፡፡

ያለ ጋዜጠኛው ዕረፍት የለሽ እንቅስቃሴ እንደምን የልዩ ልዩ ሙያዎችንና የልዩ ልዩ ሥራዎችን፣ የልዩ ልዩ ውጤቶችን፣ የልዩ ልዩ ዕቅዶችንና የልዩ ልዩ ግምቶችን ሁኔታ ማወቅ ይቻል ነበር? እስቲ ራስዎን ይህንን ፍርድ በአሉታዊ ወይም በአዎንታዊ ለመስጠት ዓይንዎን ጨፈን አድርገው ያስቡ፡፡ የሚያስቡት ምናልባት አንድ ሁለት ደቂቃ ሊሆን ይችላል፡፡ እናም በዚያ ጊዜ ዓለምን ያለ ጋዜጣ፣ ያለ መጽሔት፣ ያለ ሬድዮ፣ ያለ ቴሌቪዥን ያስቧት፡፡ አዎን የጋዜጠኛ ሙያ የክቡሮች ሁሉ ክቡርና የአስደናቂዎች አስደናቂ ሁሉ እንኳን ባይባል ‹‹እጅግ በጣም አስገራሚ ሙያ›› መሆኑ ግን ጥርጥር የለውም፡፡ ይህንን ለማረጋገጥ ከፈለጉ ማንኛውንም ሙያ ያንሱና ወሬውን ይዞልዎት ከተፍ የሚለው ማን እንደሆነ ያስቡት፡፡ መቼም ስለጋዜጠኛነት ሙያ ሲነሳ በሙያው ስለመካን ጉዳይ መነሳቱ አይቀርም፡፡ ጋዜጠኛ መሆን የሚገባው ሰው ማን ነው? በኮሌጆችና በሌሎች የጋዜጠኞች ማሠልጠኛ ያለፉ ሁሉ ጋዜጠኛ ሊሆኑ ይችላሉ? መልሱ እንዲህ በዋዛ የሚወረወር አይደለም፡፡ ዓለማችን ሠልጥና (እንኳንስ ሰውን ያህል ፍጡር ሰው የሠራው ሮቦት አንዳንድ ጠቃሚ መልዕክቶችን ተንትኖ በማስተላለፍ ላይ ባለበት ጊዜ) ‹‹አይሆንም፣ አይደረግም፣ እንዴት ብሎ?›› ማለት ይከብዳል፡፡ ከበደም አልከበደም ስለጋዜጠኛነት ሙያ ያጠና ሁሉ የተዋጣለት ጋዜጠኛ እንደማይሆን ግን ጥርጥር የለውም፡፡ ከሥልጠናው ጋር ተፈጥሮ ስጦታ ሲኖረው እንደሚልቅ ብዙ ማስረጃዎች መጥቀስ ይቻላል፡፡ የመሠልጠንና የተፈጥሮ ስጦታ ጉዳይ በሚነሳበት ጊዜ እንደ ሥዕል፣ ሙዚቃ፣ ውዝዋዜ፣ ተውኔት፣ የፈጠራ ሥራዎችና የመሳሰሉት በርካታ የኪነ ጥበብ ዘርፎች ባለቤቶች የዩኒቨርሲቲን በር ረግጠው የማያውቁ ናቸው፡፡

ስለጋዜጠኞችና የጋዜጣ ሥራ በተለይ ስለ አዲስ ጋዜጠኛነት ሙያ ከተነሳ ደግሞ የሚጠቀሱት በርካታ ሰዎች አሉ፡፡ ‹‹ጋዜጠኞች አዲስ ነገሮችን የተለመዱ፣ የተለመዱትን ደግሞ አዲስ ነገሮችን አዲስ የሚያደርጉ ናቸው፤›› የሚሉት የቺካጎው ቴሌቪዥን በተለይም የቻናል ጋዜጠኛ የነበሩት ዮል ዳሊት ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ናቸው፡፡ የኤንቢሲ ጋዜጠኛ ሮስ ተርናቤን ደግሞ ‹‹የመገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኛ ለመሆን ወደ ኮሌጅ ብትገባ ምን ማጥናት አለብህ? ለመሆኑ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ጋዜጠኞች ከሁሉም በላይ ምን ማወቅ አለባቸው? የገጠር ወይም የከተማ ወይም በውጭ አገር ያሉ ሰዎች ማወቅ የሚፈልጉት ምንድነው? በመጽሐፉ ውስጥ ያለው ምንድነው? በፕሮፌሰሩ ጭንቅላትስ? የሕዝብ ፍርኃት ወይም ተስፋ ምንድነው? የልቡ ትርታስ? እነዚህንና እነዚህን የመሳሰሉ ጥያቄዎች በአዕምሮው የሚያመላልስና መልስ ለመስጠት ጥረት የሚያደርግ ነው፡፡ በጥቁር አሜሪካዊ በርናንድ ሾ አገላለጥ ደግሞ ጋዜጠኝነት አንዳንድ ሰዎች እንደሚገምቱት መኳሻ አይደለም፡፡ እንዲያውም ለመኳሽ ቦታ የለውም፡፡ ምናልባት በጋዜጠኛነት ሙያ ላይ ዝነኛ መሆን ይቻላል፡፡ ክብርና ሞገስን የማግኛ ቦታ ግን አይደለም፡፡ ጋዜጠኛ በመሆናቸው ከሁሉም የበለጠ አድርገው ራሳቸውን የሚገምቱ ሰዎች ካሉም በጣም ተሳስተዋል፡፡ አንድ ሰው በሕይወቱ ጋዜጠኛ ለመሆን ይፈልግ ይሆናል፡፡ በመሠረቱ መፈለግ ጥሩ ነው፡፡ እንደ ጋዜጠኝነት ያለ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ወዳለበትና ነውጥ የሚፈጥር ሙያን መምረጥም እንደ ቀላል አይታይም፤›› ብሏል፡፡

‹‹ማንኛውም የጋዜጠኛነትን ሙያ የሚመርጥ ሁሉ ለምን እንደሚፈልግ ከሁሉ አስቀድሞ ራሱን መጠየቅ ወይም ለምን ይህን ሙያ እንደመረጠ ምክንያቱን ጠንቅቆ ማወቅ አለበት፤›› የሚሉት ጄ ደብዲዩ ሮበርትስ፣ ‹‹አንድ ጋዜጠኛ ለመሆን የሚሻ ሰው አርኪ ያልሆኑ፣ የአካልም የመንፈስም ኹከት የሚያስከትሉ ነገሮች ሲገጥመው፣ በትዕግሥት የማይቀበል ከሆነ ግን ሙያውን ባይመርጥ ይበጀዋል፤›› በማለት ያስጠነቅቃሉ፡፡ እውነተኛውን ነገር ለማግኘት መራብ እንዳለባቸው ያስገነዝባሉ፡፡ ‹‹ወደ ኮሌጅ የጋዜጠኛነትን ሙያ ለማጥናት ስገባ እውነት የሚገኝበት ትክክለኛው መንገድ ነው ብዬ ስለአመንኩበት ነው፤›› ያሉት ጀሪ ኤድዊንም በእርግጥ ጋዜጠኛ በመሆናቸው ወደ ሕዋው ስለሄዱ ሰዎች፣ ስለሕዝብ መብትና መብቱን ለማስከበር ስለሚያደርገው ትግል ለመናገር እንዳስቻለ ለወጣት ጋዜጠኞች ምክር እንዲሰጡ ሲጠየቁ፣ ጋዜጠኛው እውነትን መቅረብ እንዳለበት ከጠቆሙ በኋላ ስለእውነት ከላረንስ ዳሮን በመጥቀስ፣ ‹‹አንዳንድ ጊዜ እውነት የፈነጠቀችልኝ ይመስለኛል … ይህም እውነት ለወሬ ሳይሆን ምንጊዜም እውነት ሆኖ የሚዘልቅ ይመስለኛል፡፡ አንዳንድ ጊዜም ያገኘኋት በሌላ ጊዜም ያጣኋት ይመስለኛል፡፡ በዚህም ምክንያት በእጄ ጨብጫት የነበርኳት እውነት ባዶ ህልም ብቻ ትሆንብኛለች፡፡ እንደገናም ደግሜ ደጋግሜ እፈልጋታለሁ፣ እዚህ አገኛታለሁ፣ እዚያ ደግሞ አጣታለሁ፡፡ በዚህ ዓይነትም እስከ መጨረሻ የምቀጥል ይመስለኛል፤›› እያሉ ያስረዳሉ ጀሪ አድዊን፡፡ ለአንድ ጋዜጠኛ እስከ ሕይወቱ ፍፃሜ እውነትን መፈለግ እንጂ ሌላ ሥራ አይጠብቀውም፡፡

ጋዜጠኝነት ከዕለት ተዕለት የሕይወት ገጠመኝ፣ ከጠመንጃ አፈሙዝ ከሚንቦገቦግ የእሳት ላንቃ፣ ከተወሳሰበ የመንግሥትም ሆነ የድርጅት ሚስጥር አንዳች ጠቃሚ የፕሬስ ውጤትን ፈልቅቆ ለማውጣት ጥረት የሚደረግበት የሕይወት መስክ ወይም ሙያ ነው፡፡ ለጋዜጠኛነት ሥራ፣ የሙያ ብቃት ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑን ለመግለጽ ምናልባት፣ «ጋዜጠኛው በአንሸራታች ቀለም ወይም ጭቃ በተሞላ ጎዳና በፍፁም ጥንቃቄ እንደሚጓዝ ወይም በበረዶ በተሸፈነ መሬት ላይ ባለተሽከርካሪ ጫማ እንደሚከንፈው ሰው የሚቆጠር ነው፤» በሚል ቢገለጥ ምናልባት ይቀል ይሆናል፡፡ ጋዜጠኛነት፣ ዕውቀት፣ ጥበብ፣ ክህሎት በትምህርት ቤት ውስጥ ማግኘት ይቻላል፡፡ ነገር ግን የማንበብ፣ የማንበብ፣ የማንበብ፣ የማንበብ፣ የማንበብ፣ የማንበብ፣ ሌት ተቀን የማንበብ፣… የመጻፍ፣ የመጻፍ፣ የመጻፍ፣ የመጻፍ፣ የመጻፍ፣ ሌት ተቀን የመጻፍ፣… የማረም፣ የማረም፣ የማረም፣ የማረም፣ የማረም፣ ሌት ተቀን የማረም ውስጣዊ ፍላጎት ነው፡፡ የጋዜጠኝነት ሙያ ምግብ ሳይበላ የሚሠራበት፣ ወይም በሆነ አጋጣሚ ረዥም መንገድ በእግር የሚኬድበት፣ የጋዜጠኝነት መሣሪያዎችን ተሸክሞ የሚጓዝበት፣ ያለረዳትና አይዞህ ባይ የሚዋትቱበት በመሆኑ ጋዜጠኛ ሆኖ ለመቀጠል ፍላጐት ብቻ ሳይሆን አካላዊ ብቃት፣ አዕምሯዊ ብቃትና የባህርይ ብቃት እንዲኖረው ያስፈልገዋል፡፡

ጋዜጠኛው ለማወቅ፣ አውቆም ለማሳወቅ የተዘጋጀ ዜጋ እንደመሆኑ መጠን ሊቀ ሊቃውንቱን እንኳን ባይሆን መካከለኛዎቹን ከመካከለኞቹም የተሻሉትን መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ይህንንም ደረጃ ለመያዝ ፍላጐት ወይም ምኞች ወይም ዝንባሌ ብቻ አይበቃም፡፡ ራስን በንባብ ማነፅንና ከሌሎች በመማር ለማደራጀት ጥረት ማድረግን ይጠይቃል፡፡ በጥቅሉ ጋዜጠኝነት የተራራቀን ዓለም በሴኮንዶች ጊዜ ውስጥ የማገናኘት ሙያ ነው ልንለው እንችላለን፡፡ ጋዜጠኝነት በየብስ ላይ ሳይወሰን ዕድገቱን ከሳይንስ ጋር አጣምሮ በመጓዝ ስለህዋውና ስለባህር ውስጥ ጥበባት መረጃዎችን፣ ትምህርቶችን እየሰጠ በዚያው ልክም እያዝናና እንደሚገኝም ከዕድገት ታሪኩ እንገነዘባለን፡፡

የሩቅ አገር መልካም ወሬ በሚል ርዕስ የጻፉት ቤን ጀንስን፣ «ጋዜጠኛው በከፊልም ቢሆን የተቀደሰ ነው፣ ካለበለዚያም ጠቢቡ ሰለሞን ‘ከሩቅ አገር የሚመጣ ወሬ (ዜና) ጥማትን እንደሚያረካ ቀዝቃዛ ውኃ ነው’ እንዳለው መሆን ይኖርበታል፤» በማለት፣ የጋዜጠኛው የሙያ ብቃት ብዙ ሰዎች ከሚገምቱት በላይ ከፍተኛ ተልዕኮ ያለው መሆኑን ሲጠቅሱ፣ ሒንሪ ማርቲን የተባለው እንግሊዛዊ «የማወቅ ፍላጐቱ አነሳስቶት ያኔ ምንም ዓይነት መገናኛ ወዳልነበረውና ጫካ ወደበዛበት ምሥራቅ አፍሪካ በመጓዝ የዶክተር ዴቪድ ሊቪንግስተንን መገኘት ሥፍራው ሄዶ በማየት ባያበስር ኖሮ፣ ሚስጥሩ የጥቂት ሰዎች ብቻ ሆኖ ይቀር ነበር፤» በማለት በምሳሌ ይገልጡልናል፡፡ እንደ ቤን ጆንሰን አገላለጥ አንድ ጋዜጠኛ ማንም ሰው በቀላሉ የማያገኘውንና ተቀብሮ ይቀር የነበረውን በእግሩ በመጓዝ ጭምር ፈልፍሎ የማውጣት ከፍተኛ ችሎታ ያለው ነው፡፡ በዚህም ሒደት ሕይወትን ያህል ትልቅ ቁምነገር ለደን አራዊትና አደገኛ ሕመም አሳልፎ መስጠትን የሚጠይቅ ሙያም ነው፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ገጽታ እስከ 1983

የጋዜጣና የመጽሔት ሥራ በአውሮፓ ከኅትመት መሣሪያዎች መፈጠር ጋር የተያያዘ ታሪክ ቢኖረውም በአገራችን ግን የተጀመረው ዘግይቶ ነው፡፡ ይህም ከሆነበት መሠረታዊ ምክንያቶች አንዱ ከአሥራ አምስተኛው ክፍለ ዘመን እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን ማለትም ዘመነ መሳፍንት ተብሎ በሚጠራበት ጊዜ ያልተቋረጠ የእርስ በርስ ጦርነት ስለነበረ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህም ማለት የመረጃዎች ልውውጥ አልነበረም ማለት አይደለም፡፡ በአውሮፓውያኑ አገሮች መሳፍንትና መኳንንት ስለአካባቢያቸው በተለይም ስለጠላቶቻቸው እንቅስቃሴ በደብዳቤና በሰው መልዕክተኛነት መረጃ ያገኙ እንደነበረ ሁሉ፣ ኢትዮጵያውያን መኳንንትና መሳፍንትም እንደዚሁ የደብዳቤ መልዕክት ልውውጥ ያደርጉ እንደነበር ላያጠያይቅ ይችላል፡፡

ኢትዮጵያ ከዘመነ መሳፍንት እየተላቀቀች ወደ አንድነት አቅጣጫ ስትጓዝ ግን፣ የውጭ ጐብኚዎችም በሰላም መጥተው በሰላም ወደ አገራቸው የሚመለሱበት ሁኔታ ስለተፈጠረ አንዳንድ የኅትመት ሥራዎች መጀመራቸው አልቀረም፡፡ የማስታወቂያ ሚኒስቴር የሥነ ጽሑፍ ማዘጋጃ ክፍል በ1959 «የዜና ማሠራጫ ዘዴ በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ ባሳተመው ባለ 44 ገጽ በራሪ ጽሐፍ (ብሮሸር) በተለይም፣ «የማተሚያ ቤት የጋዜጦችን የመጽሔቶች ታሪክ» በሚል ንዑስ ርዕስ በጻፈው መሠረት፣ የመጀመሪያው መጽሐፍ በ1857 ዓ.ም. ታትሟል፡፡ ይህም መጽሐፍ ስለአማርኛ ሲሆን፣ ያሳተሙትም ሎሬንዞ ቢያንኬር የተባሉ ሰው ነበሩ፡፡ በ1872 ዓ.ም. በከረን የላዛሪስት ሚሲዮን አባላት የአማርኛና የግዕዝ ሰዋሰው መጽሐፍ አሳትመው ነበር፡፡ የመጻሕፍት ኅትመት ቀደም ብሎ ይሁን እንጂ የጋዜጦች ኅትመት ግን የተጀመረው በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ነበር፡፡ በዚህም መሠረት አባ ማረ በርናርድ የተባሉ የፍራንሲስካን ሚሲዮናዊ በ1893 ዓ.ም. «ላ ስሜ ኢትዮጵያ» የተባለ ሳምንቲዊ ጋዜጣ በፈረንሳይኛና በእንግሊዝኛ እያተሙ ማውጣት ጀመሩ፡፡ አንድሪያስ ኢካቫዲያ የተባሉት ግሪካዊም ከ1895 ዓ.ም. ጀምሮ «አዕምሮ» የተባለውን ሳምንታዊ ጋዜጣ እያተሙ ማሠራጨት ጀመሩ፡፡ ከ1905 ዓ.ም. እስከ 1908 ዓ.ም. ባለው ጊዜም የስዊድን ሚሲዮናውያን «መልዕክተ ሰላም» የተባለ ጋዜጣ እያተሙ ያድሉ ነበር፡፡ በመጀመሪያው የዓለም ጦርነትም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጦር ቃል ኪዳን አገሮች «የጦር ወሬ» የተባለ ጋዜጣ በአማርኛ እያሳተሙ አሠራጭተዋል፡፡ ማስታወቂያ ሚኒስቴር በ1959 ዓ.ም. ያሳተመው ይኼው መጽሔት እንደሚያስረዳን በ1890 ዓ.ም. ከሴሜር ኢትዮጵያ፣ በ1891 ዓ.ም. ከጀምሮ፣ በ1915 መልዕክተ ሰላም፣ በ1918 ዓ.ም. የጦር ወሬ፣ በ1920 ዓ.ም. ጐሃ ፅበሃ፣ በ1921 ዓ.ም. ካሮስፓንዳስ ደኢትዮጲ፣ ከ1935 እስከ 1940 ዓ.ም. የቄሳር መልዕክተኛና የሮማ ብርሃን፣ በ1940 ዓ.ም. ብርሃንና ሰላም እንዲሁም ባንዲራችን፣ በ1941 ዓ.ም. ሰንደቅ ዓላማችን፣ በ1942 ዓ.ም. አዲስ ዘመን፣ በ1944 ዓ.ም. የሐማሴን ድምፅና ዘ ኢትዮጵያ ሔራልድ፣ በ1945 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ድምፅ፣ በ1952 ዓ.ም. የዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ በ1958 ዓ.ም. አዲስ ስዋር፣ በ1975 ዓ.ም. ለፕሬግረስ ሶሻሊስት የተባሉ ጋዜጦች መታተም ጀመሩ፡፡ ከእነዚህም ሌላ ወታደርና ዓላማው፣ ፖሊስና ዕርምጃው፣ ታጠቅ፣ የሚባሉ ጋዜጦች ከእነዚህ ጋዜጦች በኋላ ወጥተዋል፡፡ ከ1983 ዓ.ም. በኋላ የቅድመ ምርመራ ሲነሳ ደግሞ በርካታ ጋዜጦች ለንባብ በቅተዋል፡፡

የሬዲዮ ጋዜጠኛነት ታሪክ

የሬዲዮ ጋዜጠኝነት ዕድገት የሚጀምረው እ.ኤ.አ. ከ1906 ማለትም መረጃዎችና ሙዚቃ በድምፅ ከተላለፈበት ጊዜ አንስቶ ሲሆን፣ ይህም ሥርጭት ከ25 ማይልስ የሚበልጥ አልነበረም፡፡ በ1910 ግን 500 ማይልስ ያህሉን ሸፍኗል፡፡ በ1915 ላይም 3,500 ማይልስ አቋርጦ ከአሜሪካ ፈረንሳይ ደርሷል፡፡ በ1921 ደግሞ በሾርት ዌቭ ለመጠቀም ተችሏል፡፡ በ1923 ደግሞ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አሜሪካውያን እንኳን የሬዲዮ ሥርጭት የማዳመጥ ዕድል እንደነበራቸው እንረዳለን፡፡ ይሁንና የሬዲዮ ጋዜጠኛነት በይፋ መተላለፍ የጀመረው እ.ኤ.አ ከኖቬምበር 14 ቀን 1922 ጀምሮ ከለንደን የምርጫ ውጤት ይፋ በሆነበት ጊዜ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ሁሉ የአሜሪካም ሆነ የኢንግላንድ ጓሮዎች ትልልቅ የአንቴና መትከያ አጠናዎች አጥለቅልቀዋት እንደነበረ ሳይጠቀስ አይታለፍም፡፡ የሬዲዮ ጋዜጠኝነት ታሪክ በልዩ ልዩ አገሮች ልዩ ልዩ መልክ ያለው ቢሆንም ሕዝብ ፈጥኖ ዜናዎችን፣ ትምህርታዊ ፕሮግራሞችንና የመዝናኛ ፕሮግራሞችን እንዲያዳምጥ በማድረግ ተመሳሳይ ሚና እንደተጫወተ ግን የሚታወቅ ነው፡፡ በተለይም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ያሳየው ዕድገት እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ከ1946 እስከ 1948 ባሉት ሁለት ዓመታት ብቻ በአሜሪካ ውስጥ 50 ሚሊዮን የሚያህሉ ሬዲኖች ተመርተው ለገበያ ቀርበዋል፡፡

የሬዲዮ ጋዜጠኛነት ታሪክ በጥቅሉ ሲቀርብ ይህን ይምሰል እንጂ፣ አገሮች በኢኮኖሚ እያደጉ ሲሄዱ በአመለካከትም እያደጉ በመሄዳቸው የሥራ አድማሱም ከጊዜ ወደጊዜ እየሰፋ መሄዱ አልቀረም፡፡ በዚህም መሠረት የዜና ሥርጭት፣ የወታደራዊ ጉዳይ ዝግጅት፣ የፖሊስ ዝግጅት፣ የሳይንስ ዝግጅት፣ ወዘተ እየተባለ መሰናዳቱ ቀጠለ፡፡ አንዳንዱ የሬዲዮ ጣቢያም አብዛኛውን የአየር ጊዜ የሚሸፍነው በሃይማኖት ነክ ጉዳዮች ሆነ፡፡ እንደዚሁም ማስታወቂያ ከፍተኛውን ጊዜ የሚሸፍንባቸው ነበሩ፡፡ በኋላም ትምህርት በሬዲዮ የሚሰጥባቸው ጣቢያዎች እንዲኖሩ ተደረገ፡፡

በኢትዮጵያ የሬዲዮ ጋዜጠኛነት የተጀመረው መስከረም ከ1928 ዓ.ም. ጀምሮ ሲሆን፣ ይህም ሥርጭት የተጀመረው ንጉሠ ነገሥቱ የኢጣሊያ ፋሽሽት ኢትዮጵያን በመውረሩ ላይ መሆኑን አስመልክተው ባደረጉት ንግግር ነበር፡፡ ይሁንና በዚሁ ዓመት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በመውረሩ የተቋቋመውን ሬዲዮ ጣቢያ አጥፍተውት ሄዱ፡፡ ከዚያም በኋላ የኢጣሊያ ፋሽስት መንግሥት ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም. ባደረገው ቆይታ ለራሱ ፕሮፓጋንዳ አገልግሎት የሚውል የሬዲዮ ጣቢያ አቋቋመ፡፡ በዚህም ሬዲዮ ጣቢያ በአማርኛ፣ በኢጣሊያንኛ፣ በእንግሊዝኛ፣ በኦሮሚኛ፣ በሱማሊኛ፣ በዓረብኛ ልዩ ልዩ ዝግጅቶች ይካሄዱ ስለነበር ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞችም አብረዋቸው እንደሠሩ ይታወቃል፡፡ ከነፃነት በኋላም ኢጣሊያ አፈራርሶ የተወውን መሣሪያ በመጠጋገን የፕሮግራም ሥርጭቱ ቀጠለ፡፡ በ1933 ዓ.ም. ባለ 2.5 ኪሎ ዋት የነበረው ጣቢያ በ1940 ዓ.ም. ወደ 7.5 ኪሎ ዋት ከፍ አለ፡፡ በ1941 ዓ.ም. የቴክኒክ ሥራውን የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሲያከናውን፣ ከቤተ መንግሥት ጽሕፈት ቤት ተዘጋጅቶ የሚቀርበው ዜናና በሞርስ እየተተረጐመ የሚገኘው ዜናም በወቅቱ በነበሩ ጋዜጠኞች እየተቀናበረ ይቀርብ ነበር፡፡

በወቅቱም በአማርኛ፣ በእንግሊዝኛ፣ በዓረብኛ፣ በሶማሊኛና በፈረንሳይኛ ይተላለፍ ነበር፡፡ በ1950ዎቹ ላይም አዳዲስ የመቅረጫና የማሠራጫ ጣቢያዎች በመምጣታቸው የተሻለ ሥራ ማከናወን ተጀመረ፡፡ ሐረር ሐኪም ጋራ ላይ፣ አስመራ አዲ ኡግሪ ላይ፣ ጌጃ ሠፈር ላይ የቅብብል ጣቢያዎች በመቋቋማቸውም የምሥራቅና የደቡብ ምሥራቅ፣ የሰሜንና የመሀል አገር ግዛቶች የተሻለ ሥርጭት ማግኘት ጀመሩ፡፡ በዚህም ጊዜ የአዲስ አበባ ሬዲዮ የነበረው ብሔራዊ ባህርይ ኖረው፡፡ በ1953 ዓ.ም. ቀድሞ ብሥራተ ወንጌል ይባል የነበረው ሬዲዮ ጣቢያ 70 በመቶ ያህል ሥርጭቱን ትምህርታዊና አዝናኝ ፕሮግራሞች 30 በመቶ ያህሉን ደግሞ መንፈሳዊ ሰበካውን እንዲያራምድበት ከኢቫንጀሊካን ቤተ ክርስቲያን ጋር ስምምነት ተደረገ፡፡ በስምምነቱ መሠረትም ሬዲዮ ጣቢያው ተሠርቶ በ1957 ዓ.ም. በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ማሠራጨት ጀመረ፡፡ ይኸው ሬዲዮ ጣቢያ ለአሥር ዓመታት ያህል የሃይማኖት፣ የትምህርትና የመዝናኛ ፕሮግራሞችን ሲያስተላልፍ ከቆየ በኋላ በ1967 ዓ.ም. ደግሞ በደርባ መንግሥት ተወረሰና የዓለም አቀፍ ሬዲዮ አገልግሎት እንዲሆን ተደረገ፡፡ ከ1983 ዓ.ም. በፊት ከነበሩት የቅብብሎሽ ጣቢያዎች ሌላ የመቱና የባህር ዳር ሬዲዮ ጣቢያዎች ተቋቁመዋል፡፡ በአርባ ምንጭና በባሌ ጐባ ላይም በቅርቡ ይቋቋማል፡፡ በእነዚህ የሬዲዮ ማሠራጫዎችም በመላው ኢትዮጵያ ያለምንም ችግር ሥርጭቱ በጥራት ይካሄዳል ተብሎ ይታመናል፡፡ ከዓለም አቀፍና ከብሔራዊ አገልግሎት ሌላ የትምህርት ሬዲዮ ሥርጭት ጣቢያዎች፣ የሬዲዮ ፋናና የሕወሓት ሬዲዮ ጣቢያ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ስለ ሬዲዮ ጋዜጠኝነት ሲወሳ በእነዚህ ጣቢያዎች የሚሠሩ ጋዜጠኞች ታሪክ እንደሚጨመር አጠያያቂ አይደለም፡፡ ይሁንና ይህ ራሱ ከፍተኛ ጥናት የሚጠይቅ በመሆኑ ለጊዜው አናተኩርበትም፡፡

በጥቅሉ ግን የሬዲዮ ጋዜጠኝነት እንደ ሥርዓቱ ተከፋፍሎ የሚታይ መሆኑን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በዚህም መሠረት በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የዘውዳዊውን አገዛዝ፣ በኢጣሊያ መንግሥት የፋሽስትን የዕድሜ ዘመን ለማራመድ፣ በደርግም የወታደራዊና የአንድ ፓርቲ ፈላጭ ቆራጭነትን የማያራምድ ፖሊሲ ይተላለፍበት ነበር፡፡ ይልቁንም እንደ ኢሕአዴግ ያሉ የሬዲዮ ጣቢያዎች የደርግን መንግሥት መታገል የጀመሩት በአሸናፊነታቸው ዋዜማ ላይ ስለነበር፣ በተለይም የተማረው ሕዝብ በአብዛኛው ያዳምጥ የነበረው የውጭ አገር ሬዲዮ ጣቢያዎችን ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሳንሱር ሰንሰለት እጅግ ጠንካራ ስለነበረ፣ በዓለም የሚሠራጩ ዜናዎች በአገሩ ሬዲዮ ጣቢያዎች ተሠራጭተው ለመስማት ዕድል አልነበረውም፡፡ የሬዲዮ ጋዜጠኝነት በአሁኑ ጊዜ የመንግሥና የግል ብሎ በሁለት ከፍሎ ማየት ሲቻል፣ የሳንሱር ማነቆ በመነሳቱም ከአምስት ዓመታት በፊት ጆሮውን ለውጭ ሬዲዮ ጣቢያዎች ሰጥቶ የነበረው ሕዝብ ወደ አገሩ ሬዲዮ ጣቢያ እየመለሰ ነው፡፡

የቴሌቪዥን ጋዜጠኛነት

የቴሌቪዥን ጋዜጠኝነት ከሬዲዮም ዘግይቶ የተፈጠረ ሲሆን፣ ይህም የጋዜጠኝነት መስክ በተሟላ ሁኔታ ይቀጥል ዘንድ እ.ኤ.አ. ከ1928 እስከ 1947 ያለውን ጊዜ ጠይቋል፡፡ በዚህም መሠረት የመጀመሪያው የቴሌቪዥን ሥርጭት በ1939 በኒውዮርክ የሁለት ሰዓት ፕሮግራም መተላለፍ ጀመረ፡፡ በዚህም ጊዜ ፕሬዚዳንት ፍራንክሊን ዲላኖ ሩዝቬልት ቴሌቪዥኑ ሲከፈት ንግግር ሲያደርጉ በመታየታቸው፣ ከፍተኛ አድናቆትን አትርፎ እንደነበረ ሲታወስ ይኖራል፡፡ ከዚያም ከ1940 አንስቶ የንግድ ቴሌቪዥን መስፋፋት ጀመረ፡፡ በ1941 ደግሞ አሥር ያህል የንግድ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ተቋቁመው ከ5,000 እስከ 10,000 ለሚያህሉ ቴሌቪዥኖች ያሠራጩ ነበር፡፡ ይሁንና የሁለተኛው ዓለም ጦርነት መጀመር ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን የቴሌቪዥንን ዕድገት ገትቶት ነበር፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፍፃሜ በኋላ ግን ዕድገቱ በከፍተኛ ፍጥነት ቀጠለ፡፡ በ1947 አሥራ አንድ ያህል የነበረው የቴሌቪዥን ጣቢያ ወደ 17 ከፍ አለ፡፡ በ1949 ዓ.ም. አሥራ ዘጠኝ ያህል፣ ከ1948 እስከ 1952 ባለው ጊዜም የቴሌቪዥን ጋዜጠኝነት ሥርዓት ባለው ሁኔታ እንዲመራ ተደረገ፡፡ የቴሌቪዥን ወርቃማ ዘመን በተሰኘው ከ1952 እስከ 1960 ባለው ጊዜም ዕድገቱ ቀጥሎ በ1954 357 የነበራት በ1960 ጣቢያዎች ወደ 501 ከፍ ብለው ነበር፡፡ በ1952 ላይ 33 በመቶ የሚያህለው ሕዝብ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ሲከታተል የነበረ ሲሆን፣ በ1960 ደግሞ 90 በመቶ ሆነ፡፡ ይልቁንም ከ1954 ጀምሮ ባለቀለም ቴሌቪዥን በሥራ ላይ በመዋሉ ተፈላጊነቱ እጅግ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደረሰ፡፡ በ1960 የኒክሰንና የኬኒዲ ክርክር ከተካሄደበት በኋላም ተቀባይነቱ እየጐላ ከመሄዱም በላይ፣ ከ1968 ጀምሮ የምርጫ ውድድር ውጤት ሲገለጥበት አገልግሎቱ ከፍተኛ መሆኑ ይበልጥ ታወቀ፡፡ የፕሬዚዳንት ኬኒዲ፣ የማርቲን ሉተር ኪንግና የሮበርት ኬኔዲ ግድያ ለመታየት መቻሉም አድናቆትን አገኘ፡፡ ከ1970 እስከ 1971 ባለው ጊዜም ካርቱን ፊልም ታየበት፡፡ ከዚያም ጊዜ ወዲህ የተለያዩ አስደናቂ ፊልሞች፣ ዜናዎች፣ ጥናታዊ ፊልሞችና የመዝናኛ ፕሮግራሞች እየተቀረፁ በመተላለፍ ላይ ናቸው፡፡ የፊልሙ ቀረፃም ከዱዳነት ወደ ባለድምፅነት፣ ከዚያም ወደ ቪዲዮ ተለውጧል፡፡ ካሜራዎቹና አሠራራቸውም እንደየወቅቱ ተሻሽለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም በቀደማዊ ኃይለ ሥላሴ 37ኛ የዘውድ በዓል ማለትም ጥቅምት 23 ቀን 1957 ዓ.ም. በማዘጋጃ ቤት ፎቅ ላይ ተቋቋመ፡፡ ያኔም በአብዛኛው በኢትዮጵያ ሬዲዮ ይሠሩ የነበሩ ጋዜጠኞች ወደ ጣቢያው ተዛውረው መሥራት ጀመሩ፡፡ በወቅቱ የነበሩ ሠራተኞች እንደሚናገሩት አብዛኛው የቴሌቪዥን ፕሮግራም ይሸፈን የነበረው በውጭ አገር ፊልሞች ነበር፡፡ የሚያስተላልፈውም በነጭና በጥቁር እንደነበር ይታወቃል፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የተሻሻለው ከ1967 ዓ.ም. ወዲህ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ መላው ክልሎችን ለመሸፈን ጥረት እያደረገ ነው፡፡ በጥቂት ሰዎች ሥራውን የጀመረው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በአሁኑ ጊዜ ከ500 በላይ የሆኑ ሠራተኞች አሉት፡፡ ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ ደግሞ ከማዘጋጃ ቤት ጥገኝነት ወጥቶ ራሱን እንዲችል አዲስ ሕንፃ ተሠርቶለታል፡፡ የሥርጭቱ ጊዜም ጨምሯል፡፡ የኦሮሚኛና የትግርኛ ዝግጅቶችንም እያስተላለፈ ነው፡፡

ይሁንና ቶምሰን ፋውንዴሽን ኢንተርናሽናል ፕሬስ ሴንተር የተባለው እ.ኤ.አ. በ1977 ባደረገው ጥናት እንዳመለከተው እስከዚያ ዘመን ድረስ የነበረው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሁኔታ እጅግ ኋላቀር ከመሆኑ የተነሳ፣ ከዓለም ጋር ያለው ግንኙነት ጋር አብሮ ሊሄድ እንደማይችል አመልክቶ እንደነበረ መታወስ ይኖርበታል፡፡ ይኼው ድርጅት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አቅሙ ደካማ እንኳን ቢሆን ዋጋቸው ቀለል ባለ ፕሮፌሽናል የቪዲዮ ካሜራዎች ሊሠራ እንደሚችል ሲያስታውስ ምን ያህል ችግር እንደነበረበት እንረዳለን፡፡ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ እንደሚያስታውሰውም ማዘጋጃ ቤት የነበረው የስቱዲዮ ጣራ ለቀረፃ እንዲሆን ባለመዘጋጀቱ ቴራስ ላይ የነበሩ የወንበሮች መንኳኳት ሳይቀር ይሰማ ነበር፡፡ የአዲሱ ቴሌቪዥን ስቱዲዮ የተሠራው በመጨረሻ ላይ መሆኑን ስንመለከትም አስቀድሞ እንዳልታሰበበት እንገነዘባለን፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በጥቅሉ ሲታይ ከጊዜ ወደጊዜ እየተሻሻለ የመጣ ቢሆንም፣ አሁንም ችግር ያለበት መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ይልቁንም የቴሌቪዥን ጣቢያው አንድ በመሆኑ ምክንያት የተመልካችን ፍላጐት ያረካል ብሎ ማሰብ ያስቸግራል፡፡ ስለዚህም የቴሌቪዥን ጋዜጠኝነት የበለጠ ተወዳጅና የሰመረ እንዲሆን የግል ድርጅቶች እንዲያቋቁሙ ሁኔታዎች መመቻቸት ይኖርባቸዋል፡፡ ይህንንም እውነታ ከሬዲዮ ፋና መቋቋም ልንረዳው እንችላለን፡፡

የዜና አገልግሎት

የዜና አገልግሎት ጋዜጠኛነት መቼ እንደተጀመረ በውል ባይታወቅም፣ ከኢንሳይክሎፒዲያ አሜሪካና እንደምንረዳው ከመካከለኛው ዘመን ይሆናል ተብሎ ይገመታል፡፡ በዚህም ጊዜ የነበሩ ወሬ መሰብሰብ የሚወዱ አውሮፓውያን ለመሳፍንቱና ለመኳንንቱ እንዲሁም ለነጋዴዎች የሚሆኑ ወሬዎችን በደብዳቤ ይልኩ እንደነበረ አንዳንድ ማስረጃዎች ይጠቅሳሉ፡፡ በኋላም ቡና ቤቶች ዋነኛ የዜና ማሠራጫ ማዕከሎች ሆነው ነበር፡፡ ዘመናዊ የዜና አገልግሎት ተብሎ የሚታወቀው ወይም «የዜና አገልግሎት አባት» ተብሎ የሚጠራው በኒውዮርክ ከተማ እ.ኤ.አ በ1849 የተማረው «ጄኔራል ኒውስ አሶሴሽን» ነው፡፡

ኦክስፎርድ ጁኔር ኢንሳይክሎፒዲያ በቅጽ አራት (ኮሙኒኬሽን) ላይ እንደገለጸው ደግሞ፣ የዜና አገልግሎት ወይም የዜና ወኪል ማለት ዜና የሚሸጥ ድርጅት ነው፡፡ ብዙዎቹ የዜና ወኪሎች በአንድ ሰው የሚካሄዱ ሥራዎች ሲሆኑ፣ እነዚህም በወኪልነት የሚያገለግሉ ጠንካራ ጋዜጠኞች በአንድ በተወሰነ አካባቢ አንድን የተወሰነ ድርጊት አነፍንፈው በመድረስ ዜና ይሠሩና ለደንበኞቻቸው በአነስተኛ ዋጋ ይሸጡላቸዋል፡፡ ደንበኞቹም ብዙ ሰዎችን በወር ደመወዝ ከመቅጠር ይልቅ በሠሩት መጠን አነስተኛ ዋጋ ከፍለው የሚያገኙትን መረጃ ይመርጡ ነበር፡፡ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ለተወሰነ ጊዜ ከቆየ በኋላ እያደር የዜና አገልግሎት ድርጅቶች ኅብረት መፍጠር ወይም በከፍተኛ ደረጃ መደራጀት ጀመሩ፡፡ ቆይቶ ጋዜጦችም ዜና የሚያገኙት በአብዛኛው ከሮይተርስ፣ ከአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ፣ ከታስ ሲሆን፣ ታንጁንግ፣ ሴቴካ፣ ግራንማ፣ ያሉትም ትልልቆች ነበሩ፡፡ ከእነዚህም ሌላ በየአገሩ የዜና አገልግሎት ድርጅቶች አሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በጣም በርካታ ድርጅቶች አሉ፡፡ «ኒው ሰርቬይ ኦቭ ጆርናሊዝም» በሚል ርዕስ ጆርጅ ፎክስ ሞት ባዘጋጁት መጽሐፋቸው፣ በዓለም ላይ ዜና የሚያሠራጩ ሁለት ግዙፍ የፕሬስ ማኅበራት እንዳሉ ጠቅሰው እነሱም አሶሼትድ ፕሬስና ዩናይትድ ፕሬስ ኢንተርናሽናል እንደሆኑ ያስረዳሉ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1965 በአሜሪካ ከሚገኙ የታወቁ ጋዜጦች ውስጥ 1755 ያህሉ ከእነዚህ የዜና ምንጮች ይጠቀሙ ነበር፡፡ ሁለቱም የፕሬስ ማኅበራት በመቶና በሺሕ በሚቆጠሩ የከተማና የገጠር የዜና ወኪሎቻቸው ያሰባሰቡትን ዜና ለጋዜጣ፣ ለሬዲዮና ለቴሌቪዥን ያሠራጫሉ፡፡ በውጭ አገርም ቢሆን የራሳቸው ወኪሎች ስላሉዋቸው ችግር የለባቸውም፡፡ ዜና አገልግሎቶች ቀደም ሲል ዜናዎቻቸውን ሲቀበሉና ሲያሠራጩ የነበሩት በደብዳቤ፣ በኋላም በሞርስ፣ ዛሬ ደግሞ በስልክ፣ በቴሌ ፕሪንተር፣ በፋክስ በኢንተርኔት፣ በኢሜይል፣ ወዘተ ነው፡፡ የዜና አገልግሎት ለማግኘት አቅሙ የሌላቸው ጋዜጦችና መጽሔቶች ግን ሬዲዮና በየአካባቢው በፍሪላንሰርነት የሚሠሩላቸው ግለሰቦችን እንደ ዜና ምንጭ እንደሚጠቀሙ ማስተዋል ይገባል፡፡

የአገራችን የዜና ምንጭ ጋዜጠኝነት ከነአዕምሮ ጋዜጣ መታተም ጋር ሊጀምር እንደሚችል ጥርጥር ባይኖረውም በሞርስ ኮድ፣ ቀጥሎም እንደሮይተርስና አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ባሉ የዜና ወኪሎች መጠቀም ከጀመረ ግን ከ60 ዓመታት አይበልጥም፡፡ ድርጅቱ በትክክል የተቋቋመበትን ዘመን ሲገልጽም 57 እንደሆነ ሐምሌ 21 ቀን 1988 ባወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ አስታውቋል፡፡ ያኔ ሲቋቋም ሞርስ ኮድን በመጠቀም የጀመረው ኢዜአ የሲግናል ሠራዊት አባላትን በመቅጠር እንደሆነ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በዜና አገልግሎት ውስጥ ይሠሩ የነበሩ ሠራተኞች ይናገራሉ፡፡ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በከተሞችና በክፍለ አገር በመቶዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ሲኖሩት፣ በአሁኑ ጊዜም በዘመናዊ ዘዴ ዜናዎችን እየተቀበለ በማሠራጨት ላይ ነው፡፡ በቅርቡም በ15 ዓበይት ቅርንጫፎች ጽሕፈት ቤቶች ከዋናው መሥሪያ ቤት ጋር በኮምፒዩተር ለማገናኘት ዕቅድ አለው፡፡ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በተጨማሪም ዘመናዊ የቡለቲን ማምረቻ፣ የፎቶግራፍ ካሜራዎች፣ የቴሌፎን ዜና መቀበያዎችን ማሠራጫዎች እንዲሁም ሌሎች ዘመናዊ መሣሪያዎች እንዲኖሩት ተደርጓል፡፡ ከሮይተርስ፣ ከአጃንስ ፍራንስ ፕሬስና ከመላው አፍሪካ የዜና አገልግሎት እንዲሁም ታዋቂ ከሆኑ የዓለም ሬዲዮ ጣቢያዎች የሚከታተላቸውን ዜናዎች በአማርኛና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች እያዘጋጀ ለመገናኛ ብዙኃንና ለሌሎቹም ደንበኞቹ የሚያሠራጭ ድርጅት ነው፡፡ ወደፊት ግን ሌሎች የግል የዜና ወኪሎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜም ዋልታ የኢንፎርሜሽን ድርጅት ጥሩ ተፎካካሪ እየሆነ በመምጣት ላይ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የፕሬስ ገጽታ ከ1983 በኋላ

የኢትዮጵያ ፕሬስ ከ1983 ጀምሮ እስከ 1993 ዓ.ም. በነበሩት አሥር ዓመታት ከሞላ ጎደል መልካም የነበረበት ጊዜ ሲሆን፣ ይህም የሆነበት መሠረታዊ ምክንያት የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት ጥቅምት 11 ቀን 1985 ዓ.ም. ያወጀው የፕሬስ ነፃነት (አዋጅ ቁጥር 34/1985) ‹‹ሐሳብን በነፃ የመግለጽ መብት በኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት ቻርተር የተረጋገጠ ስለሆነ ሐሳብን በነፃ የመግለጽ መብት በተሟላ መልኩ ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው ነፃ የሆነና የተጠናከረ ፕሬስ ሲኖር፣ ሊጎለብትና ሊፋፋ በመሆኑ፣ ነፃ ፕሬስ ዜጎች ሐሳባቸውን በነፃ የሚገልጹበት መድረክ ከመሆኑም በላይ የባለሰብዕና ሕዝቦች መብት እንዲከበር ዴሞክራሲያዊ ባህል እንዲዳብር ለማድረግ፣ እንዲሁም ዜጎች በተለያዩ አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ሚዛናዊ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና በመንግሥት አመራርና አሠራር ላይ ሐሳብ እንዲያቀርቡ በማስቻል ጉልህ የሆነ ሚና የሚጫወቱ ስለሆነ፣ ፕሬስ ይህንን ተግባሩን ሊያከናውን የሚችለው የቅድሚያ ምርመራ (ሴንሰርሺፕ) እና ሌላም ተመሳሳይ ገደብ ሳይደረግበት በነፃና በኃላፊነት ስሜት ሊንቀሳቀስ የሚችልበት ምቹ ሁኔታ ሲፈጠርለት እንደሆነ በማመኑ›› ነበር፡፡

ምንም እንኳን ፕሬስ ከመንግሥት ቁጥጥር ነፃ እንዲሆን የረዥም ጊዜ ትግል የተደረገ ቢሆንም፣ ሕጉ ሲረቀቅ እጅግ አከራካሪ ነጥቦች ተነስተው እንደነበሩም ማስታወስ ጠቀሜታ አለው፡፡ በተለይም ነፃ ፕሬስ መንግሥትን፣ አገርንና ሕዝብን የሚያናጉ ጽሑፎች እንዳይወጡ ሕጉ መጥበቅ እንደሚኖርበት አበክረው ያሳሰቡ ወግ አጥባቂዎች እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ እጅግ ተራማጅ የሆኑት ደግሞ በቻርተሩ ላይ ነፃ መሆኑን አውጀን እስከነጭራሹ ሕግ የሚባል ነገር አያስፈልግም የሚል አቋም ነበራቸው፡፡ ይህም ሆኖ ሽግግር ዘመን ላይ የሚገኝ መንግሥት መሆኑንና ከአምባገነናዊ አመራር ገና በመላቀቅ ላይ የሚገኝ አስተሳሰብ መኖሩን በመገንዘብ በሚቻል መንገድ ሁሉ ዴሞክራሲያዊ፣ አስተማሪና መሪ ሐሳብ ያለበት የፕሬስ ነፃነት እውን ሆኖ ነበር፡፡ በዚህም ሕግ መሠረት በርካታ መጽሔቶችና ጋዜጦች እየታተሙ ነበር፡፡ የሚመስላቸውንም አስተያየት ከካርቱንና ከፎቶግራፎች ጋር አውጥተዋል፡፡ የኤሌክትሮኒክስ አታሚዎችም ሆኑ ሌሎች ማተሚያ ቤቶች የምርመራ ፈቃድ ሳያሳዩ የቀረቡላቸውን ሁሉ አትመዋል፡፡

የፕሬስ ነፃነቱ በነፃ ፕሬሶች አመለካከት

ያኔ ሁሉም በሥራቸው ስኬታማ ውጤት አያስመዝግቡ እንጂ፣ ከተመዘገቡት መጽሔቶችና ጋዜጦች አብዛኛዎቹ ‹‹የነፃ ፕሬስ አሠራርን መንገድ ተከትለናል›› በሚል ስሜት የመንግሥትን አሠራርና አመራርን ያለተፅዕኖ ነቅፈዋል፡፡ ከመጽሔቶቻቸው ሽፋን (አብዛኛውን ጊዜ ካርቱን) ጀምሮ በውስጥ እስከሚያወጧቸው ጽሑፎች መንግሥት የሚከተለው አመራር ትክክል አለመሆኑን ጠቅሰው፣ የራሳቸውን አስተያየት ያለአንዳች ለዘብተኝነት በመግለጻቸውም እስከ 1992 ዓ.ም. ድረስ ከተወሰኑት በስተቀር የተቀጡ በርካታ የፕሬስ ውጤቶች አልነበሩም፡፡

በነፃ ፕሬስ ከሚቀርቡት አስተያየቶች ጥቂቶቹ ለአብነት ያህል ብንመለከት ‹‹ወታደራዊ ድል ኢትዮጵያን የመምራት ችሎታን አያሳይም›› (ኅብረት ጥር 1985)፣ ‹‹በዩኒቨርሲቲው ኅብረተሰብ ላይ የደረሰው አሰቃቂ ጭፍጨፋ ከሰብዓዊና ከሕጋዊነት የወጣ ነው…›› (ኢትዮጵያ ሪቪው ፌብሩዋሪ 1993)፣ ‹‹… ሕዝቡን እንደብቅ፣ እንሸሽግ፣ አለበለዚያ ቀሪው ጊዜ ደርግ አሥር ጊዜ አስቸኳይ ስብሰባ ከጠራን በኋላ በመፈራረስ የምንደመድመው እንዳይሆን እንሰጋለን፡፡ መካሪ ያጣ ንጉሥ ያለ አንድ ዓመት… እንዳይባልም ብንጠነቀቅ መልካም ነው፡፡›› (ሩሕ ሐምሌ 1984)፣ ‹‹አብዛኛው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉት ተቃዋሚ ኃይሎች የሚመሳሰሉበት ዓቢይ ነጥብ ቢኖር የኤርትራን ሪፈረንደም መቃወማቸው ነው፡፡›› (አቢሲኒያ ጥር 1985)፣ ‹‹የሽግግር መንግሥት በሒሳቡ ቀመር መደመሩን ትቶ መቀነስ ጀመረ…››፣ ድሮም መደመሩ አላሳድግ ካለ፣ ዛሬስ መቀነሱ ቢሞከር ምን አለ፡፡›› (ኢሌፍ ታኅሣሥ 1985 ካርቱን)፣ ‹‹ቻርተሩም ሆነ የሽግግሩ መንግሥት የኢትዮጵያ ሕዝብ አይደሉም›› (ሉሲ ቁጥር 2/1985)፣ ወዘተ. በምሳሌነት ይጠቀሳሉ፡፡

እነዚህንና እነዚህ የመሳሰሉ ምናልባትም ከዚህ እጅግ የጠነከሩ አስተያየቶች በሽግግር መንግሥቱ ጊዜ ተሰንዝረዋል፡፡ ይህም ሆኖ ስለፕሬስ ነፃነትና ባርነት አሳምረው ያውቃሉ የሚባሉ ምሁራን ሳይቀሩ እስከ 1993 ዓ.ም. በነበረው ጊዜ ስለፕሬስ ነፃነቱ ነፃ አለመሆን የተለያዩ መጽሔቶችና ጋዜጦች የጻፉ ቢሆንም፣ ‹‹የፕሬስ ሕግ ግን ግልጽ ነፃነትን አውጆ ግልጽ ደስታን አላጎናጸፈም…›› (ሩሕ ጥቅምት 1985)፣ የፕሬስ ነፃነት የማያሠራ መሆኑን በመጀመሪያ ዕትሟ ይዛ የወጣችው መድረክ (ሚያዝያ 1985)፣ ‹‹ገንጣይ ሲባል የነበረው ኢሕአዴግ አዲስ አበባ ከገባ በኋላ ነገሮች ተከረባብተው ንጉሡም ወታደሩም ለአገር አንድነት አይበጁም ተባለ፡፡ ጋዜጠኞች ይህንኑ አስተጋቡ፡፡ አዲስ መፈክር መጣ፡፡ ጋዜጠኛውም ይህንን ማስተጋባት ጀመረ…›› ለመሆኑ ለኢትዮጵያ የሚበጀው የቱ ነው? የንጉሡ? የደርጉ? ወይስ የአሁኑ? … ሁኔታ በተቀየረ ቁጥር ጋዜጦች እጥፍ ሲሉ ሕዝቡ ቢንገፈገፍ ይነሰው? (ማኅሌት ታኅሣሥ 1985) የሚሉት ጥቂቶቹን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡

ታዲያ፣ ከ1994 ዓ.ም. ወዲህ የግል ጋዜጦችና መጽሔቶች ቁጥር እየተመናመነ መጣ፡፡ የት ይደርሳሉ ተብለው በጉጉት ሲጠበቁ የነበሩት እንደ ጦቢያ፣ አፍሪካ ቀንድ፣ ሙዳይ፣ ጦማር፣ መስተዋት፣ ሚዛን፣ አቢሲኒያ፣ አሌፍ፣ ሳሌም፣ ኢትዮጵያ፣ እፎይታ፣ እፍታ፣ ማህሌት ቀርተው፣ በእንጭጩ ይቀራሉ የተባሉት ቀጠሉ፡፡ ጋዜጦችም እንዲሁ፡፡ (ስለአገራችን መጻሕፍትና ሌሎች የፕሬስ ውጤቶች እባክዎ የሚያዝያ 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ዕትም ይመልከቱ፡፡)

ከ1997 ዓ.ም. በኋላ በነፃው ፕሬስ አካባቢ የታየው ጉራማይሌ ነገር የፈጠረው ችግር ተጉዞ ተጉዞ፣ ዛሬ በአሥር ቤት የሚቆጠሩ ጋዜጦችና መጽሔቶች አሉ፡፡ በሪፖርተር፣ በአዲስ አድማስ፣ በካፒታል፣ በፎርቹን፣ በሞኒተር፣ እንዲሁም በአዲስ ዘመን፣ በኢትዮጵያን ሔራልድና በዘመን መጽሔት ማዝገምም መጥፎ አይደለም ካልተባለ በስተቀር ያሉት መጽሔቶችና ጋዜጦች የዲሞክራሲን ችቦ ብቻቸውን የሚያንቦገቡጉ አይደሉም፡፡ አንዳንዶቹ ጋዜጦችና መጽሔቶችም ‹‹ሰው የለም ወይ በአገር?›› የሚያሰኙ ናቸው፡፡ እርግጥ ነው በአገራችን የተጀመሩ ልማቶች አሉ፡፡ መንገዶቹ፣ ስልኩ፣ ትምህርት ቤቱ፣ የተለያዩ መሠረተ ልማቶች፣ ወዘተ. ሁሉ መልካም ናቸው፡፡ ነገር ግን ፕሬስ የልማት ዋነኛው አጋዥ መሣሪያ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል፡፡ ያለ ነፃ ፕሬስ ዴሞክራሲም እንበለው ነፃ ገበያ የሚታሰብ አይደለም፡፡ የልማት ጋዜጠኛነት ማለትም ጥቂት ፍሬዎችን አግዝፎ፣ ጠባብ መሬትን አተልቆ፣ ጥቂት ዛፎችን ደን አስመስሎ ማቅረብ ማለት አይደለም፡፡ ይህ መንግሥትንም፣ ሕዝብንም ማታለል ይሆናል፡፡ ሕዝብ በውኃ መጠማቱ፣ በመንገድ እጦት ወይም መበላሸት ተቸግሮ፣ በመብራትና በስልክ እጦት እክል እየደረሰበት፣ ወዘተ. ሳይታይ እንደተሠራለት ‹‹የአካባቢው ሕዝብ በዚህና በዚያ ተሠራለት›› ብሎ ማቅረብም አይደለም፡፡ የልማት ጋዜጠኛ ማለት ያልተሠራው እንዲሠራ፣ የተበላሸው እንዲጠገን፣ የሌለው እንዲኖር የሚታገል ስለሆነ አሁን በመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ከሚቀርበው በተቃራኒው ነው፡፡ አንዳንዶቹ የግል የፕሬስ ውጤቶችም ቢሆኑ በየስብሰባው እየገቡ ሰዎች ያላሉትን፣ ያላሰቡትን፣ አቋማቸውና አመለካከታቸው ያልሆነውን፣ የእነሱ የፕሬስ ውጤት ደንበኛ ደስ እንዲለው በማለት ተጠቃሹ ያላለውን ‹‹ብሏል›› ማለት ነውርና የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር አጥብቆ የሚኮንነው መሆኑን መረዳት አለባቸው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...